በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የጠፋው ለምንድን ነው?

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የጠፋው ለምንድን ነው?

ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የጠፋው ለምንድን ነው?

“በተገቢው ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ፣ ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሥልጣን ላይ የማመፅ ዓለም አቀፋዊ ባሕርይ ያለፈው አሥርተ ዓመት መለያ መሆኑ በትውስታ የሚነገርበት ቀን ይመጣ ይሆናል።”

የታሪክና የፍልስፍና ምሁር የሆኑት ሃና አረንት ከላይ ከጠቀሱት አሥርተ ዓመት ማለትም ከ1960ዎቹ አንስቶ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። ዛሬ ለሥልጣን አክብሮት ያለማሳየት ማዕበል ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው።

ለምሳሌ ያህል ለንደን በሚታተመው ዘ ታይምስ ላይ በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ወላጆች አስተማሪ በልጃቸው ላይ ያለውን ሥልጣን ለመቀበል አሻፈረኝ ይላሉ። እንዲሁም ልጃቸውን የመቅጣት ሙከራ ከተደረገ ለምን ተነካ ብለው አቤቱታቸውን ያሰማሉ።” አብዛኛውን ጊዜ፣ ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ቅጣት ከተሰጣቸው ወላጆች አስተማሪዎቹን አስጠንቅቀው ለመመለስ ብቻ ሳይሆን ለመደባደብ ጭምር ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ።

በብሪታንያ፣ የርዕሰ መምህራን ብሔራዊ ማኅበር ቃል አቀባይ እንዲህ ብለው መናገራቸው ተጠቅሷል:- “ብዙሃኑ ‘ኃላፊነት አለብኝ’ ከማለት ይልቅ ‘መብቴ ነው’ ማለት ይቀናዋል።” አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ለሥልጣን ጤናማ አክብሮት እንዲኖራቸው አለማስተማር ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸውን አይቀጡም፤ ሌሎች እንዲቀጧቸውም አይፈቅዱም። “ለመብታቸው” የሚቆሙ ልጆች ለወላጆቻቸውም ሆነ ለአስተማሪዎቻቸው ሥልጣን ንቀት እንዲያሳዩ መተዋቸው የሚያስከትለውን ውጤት መገመት አይከብድም። የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ማርጋሬት ድሪስኮል “ለሥልጣን ምንም አክብሮት የሌለው እንዲሁም ክፉና በጎውን መለየት የተሳነው አዲስ ትውልድ” በማለት ገልጸውታል።

ታይም መጽሔት “ብልሹ ትውልድ” በሚል ባወጣው ርዕስ ላይ “ዘለቄታ ያለው ነገር በሌለበትና ፍትሕ በጠፋበት ዓለም ውስጥ የተወለደ ማንኛውም ሰው በኅብረተሰቡ ላይ እንዴት እምነት ሊጥል ይችላል?” ሲል አንድ እውቅ የራፕ አቀንቃኝ የተናገረውን በመጥቀስ በርካታ ሩሲያውያን ወጣቶች የሚሰማቸውን ግራ መጋባት ጠቁሟል። የማኅበራዊ ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ሚካኤል ቶፓሎቭ ይህን አስተሳሰብ እንደሚደግፉ ገልጸዋል:- “እነዚህ ወጣቶች ሞኝ አይደሉም። መንግሥት ወላጆቻቸውን ሲያታልል፣ ያጠራቀሙትን ገንዘብ ሲነጥቅና ከሥራ ሲያፈናቅል ተመልክተዋል። ታዲያ እነዚህ ልጆች ለሥልጣን አክብሮት እንዲኖራቸው መጠበቅ እንችላለን?”

ይሁን እንጂ በሥልጣን ላይ እምነት ማጣት በወጣቱ ትውልድ ላይ ብቻ የሚታይ ባሕርይ እንደሆነ መደምደም ስህተት ነው። ዛሬ በየትኛውም እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት ሥልጣን በጥርጣሬ አልፎ ተርፎም በንቀት ይመለከታሉ። ይህ ማለት እምነት ሊጣልበት የሚችል የሥልጣን ዓይነት የለም ማለት ነውን? ሥልጣን የሚለው ቃል “የሌሎችን ድርጊት ለመቆጣጠር፣ ለመዳኘት ወይም ለማገድ የሚያስችል ኃይል ወይም መብት” የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን በተገቢ መንገድ ከተሠራበት ለበጎ ዓላማ የሚያገለግል ኃይል ሊሆን ይችላል። ሥልጣን ግለሰቦችንም ሆነ ኅብረተሰቡን ሊጠቅም ይችላል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።