በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች”

“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች”

“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች”

“እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? . . . ከአምላክህም ጋር በትሕትና [“ልክህን አውቀህ፣” NW ] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”​—⁠ሚክያስ 6:​8

1, 2. ልክን ማወቅ ምንድን ነው? ከትዕቢት የሚለየውስ እንዴት ነው?

 አንድ የታወቀ ሐዋርያ የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሱ መሳብ አልፈለገም። አንድ ደፋር እስራኤላዊ መስፍን በአባቱ ቤት የሁሉ ታናሽ እንደሆነ ተናገረ። እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን እንደሌለው ገለጸ። ሦስቱም ልክን የማወቅ ባሕርይ አሳይተዋል።

2 ልክን የማወቅ ባሕርይ የትዕቢት ተቃራኒ ነው። ልኩን የሚያውቅ ሰው ለችሎታዎቹና ለማንነቱ ያለው አመለካከት ሚዛኑን የጠበቀ ነው። እንዲሁም ከዕብሪትና ከግብዝነት የራቀ ነው። ልኩን የሚያውቅ ሰው ኩራተኛ፣ ጉረኛ ወይም የሥልጣን ጥመኛ ከመሆን ይልቅ አቅሙ ውስን መሆኑን በሚገባ ያውቃል። ከዚህም የተነሳ ለሌሎች ሰዎች ስሜትና አመለካከት ተገቢውን አክብሮትና አሳቢነት ያሳያል።

3. ጥበብ ‘ልካቸውን በሚያውቁ ሰዎች’ ዘንድ የሚገኘው እንዴት ነው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ “በትሑታን [“ልካቸውን በሚያውቁ፣” NW ] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” ብሎ መናገሩ አለምክንያት አይደለም። (ምሳሌ 11:​2) ልኩን የሚያውቅ ሰው አምላክ የሚቀበለውን ጎዳና ስለሚከተል ጥበበኛ ነው፤ እንዲሁም ውርደት ከሚያስከትለው ከትዕቢት መንፈስ ይርቃል። (ምሳሌ 8:​13፤ 1 ጴጥሮስ 5:​5) ልክን የማወቅ ባሕርይ ጥበብ መሆኑ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች በተከተሉት የሕይወት ጎዳና ተረጋግጧል። እስቲ ለአብነት ያክል በመግቢያው አንቀጽ ላይ የተጠቀሱትን ሦስት ሰዎች ምሳሌ እንመርምር።

‘ሎሌና’ ‘መጋቢ’ የነበረው ጳውሎስ

4. ጳውሎስ ምን ልዩ መብቶች ነበሩት?

4 ጳውሎስ በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ጉልህ ቦታ ነበረው፤ ደግሞም እንደዚያ መሆኑ አያስገርምም። በአገልግሎት በተካፈለባቸው ጊዜያት በባሕር፣ በየብስ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል፤ በርካታ ጉባኤዎችንም አቋቁሟል። በተጨማሪም ራእይ እንዲያይና በልሳን እንዲናገር በማድረግ ይሖዋ ባርኮታል። (1 ቆሮንቶስ 14:​18፤ 2 ቆሮንቶስ 12:​1-5) እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑትን 14 ደብዳቤዎች እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ጳውሎስ ከሌሎቹ ሐዋርያት ይበልጥ ደክሟል ተብሎ ሊነገርለት ይችላል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​10

5. ጳውሎስ ስለ ራሱ የነበረው አመለካከት ልክን የማወቅ ባሕርይ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

5 ጳውሎስ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ስለነበር አንዳንዶች የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት እንዲያውም ሥልጣኑን ለማሳወቅ የሚፈልግ ሰው እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱት ይችሉ ይሆናል። ሆኖም ጳውሎስ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ አልነበረውም። “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” በማለት ራሱን ከመጥራቱም በላይ “የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ” ነኝ በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:​9) ጳውሎስ ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረ እንደመሆኑ ልዩ የአገልግሎት መብት ማግኘት ይቅርና ወደ አምላክ መቅረብ የቻለው ይገባኛል በማይለው ደግነቱ እንደሆነ ፈጽሞ አልረሳም። (ዮሐንስ 6:​44፤ ኤፌሶን 2:​8) በመሆኑም ጳውሎስ በአገልግሎቱ ብዙ ማከናወን መቻሉ ከሌሎች የላቀ ሆኖ እንዲሰማው አላደረገውም።​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:​16

6. ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር በነበረው ግንኙነት ልክን የማወቅ ባሕርይ ያሳየው እንዴት ነው?

6 ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር የነበረው ግንኙነት ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን ይበልጥ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። አንዳንዶች አጵሎስን፣ ኬፋንና ራሱን ጳውሎስን ጨምሮ ዋነኛ ብለው ላሰቧቸው አንዳንድ የበላይ ተመልካቾች ከፍተኛ ግምት ሰጥተው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:​11-15) ሆኖም ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን በማግባባት የእነርሱን ውዳሴም ሆነ አድናቆት ለማግኘት አልሞከረም። በሚጎበኛቸው ጊዜ “በቃልና በጥበብ ብልጫ” ራሱን አላቀረበም። ከዚያ ይልቅ ጳውሎስ ስለ ራሱም ሆነ ስለ ባልንጀሮቹ ሲናገር “እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን” በማለት ተናግሯል። a​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​1-5፤ 4:​1

7. ጳውሎስ ምክር በሚሰጥበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር ልክን የማወቅ ባሕርይ ያንጸባረቀው እንዴት ነው?

7 ጳውሎስ ሌላው ቀርቶ ጠንካራ ምክርና መመሪያ እንዲሰጥ በተገደደበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ልክን የማወቅ ባሕርይ አሳይቷል። ክርስቲያን ባልንጀሮቹን በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ሳይሆን “በእግዚአብሔር ርኅራኄ” እና “ስለ ፍቅር” ለምኗቸዋል። (ሮሜ 12:​1, 2፤ ፊልሞና 8, 9) ጳውሎስ እንደዚህ ያደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘በእምነታቸው ላይ እንደሚገዛ’ ሳይሆን የእነርሱ ‘የሥራ ባልደረባ’ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ይቆጥር ስለነበር ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:​24) ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤዎች ዘንድ እንዲወደድ ያደረገው ይኸው ልክን የማወቅ ባሕርይ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።​—⁠ሥራ 20:​36-38

ላገኘናቸው መብቶች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

8, 9. (ሀ) ስለ ራሳችን ባለን አመለካከት ረገድ ልክን የማወቅ ባሕርይ ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው? (ለ) በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ልክን የማወቅ ባሕርይ ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ጳውሎስ ዛሬ ለምንኖረው ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ምንም ዓይነት መብት ይኑረን ከሌሎች እንደምንበልጥ ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ጳውሎስ “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 6:​3) ለምን? ምክንያቱም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:​23፤ 5:​12) አዎን፣ ሁላችንም ከአዳም ኃጢአትንና ሞትን እንደወረስን ፈጽሞ መርሳት የለብንም። ልዩ መብቶችን ማግኘት ከወደቅንበት የኃጢአተኝነት ሁኔታ ቅንጣት ታክል እንኳ ከፍ አያደርገንም። (መክብብ 9:​2) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም አንዳንድ መብቶችን ማግኘት ይቅርና ወደ አምላክ መቅረብ የቻልነው ይገባናል በማንለው ደግነቱ ነው።​—⁠ሮሜ 3:​12, 24

9 ልኩን የሚያውቅ ሰው ይህንን ከተገነዘበ ባገኘው መብት አይመጻደቅም እንዲሁም ባከናወነው ነገር አይኩራራም። (1 ቆሮንቶስ 4:​7) ምክር ወይም መመሪያ በሚሰጥበት ጊዜ እንደ ጌታ ሳይሆን እንደ ሥራ ባልደረባ ሆኖ ይሰጣል። በአንድ ዓይነት ሥራ ከሌሎች የተሻለ ብቃት ያለው አንድ ሰው የእምነት ባልደረቦቹን በማግባባት የእነርሱን ውዳሴም ሆነ አድናቆት ለማግኘት ቢጥር በእርግጥም ስህተት ይሆንበታል። (ምሳሌ 25:​27፤ ማቴዎስ 6:​2-4) ውዳሴ ዋጋ የሚኖረው ከሌላ ወገን ሲመጣ ነው። ያም ደግሞ እኛ ጎትጉተን መሆን የለበትም። ሌሎች ቢያወድሱን እንኳ ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን እንድናስብ ሊያደርገን አይገባም።​—⁠ምሳሌ 27:​2፤ ሮሜ 12:​3

10. ብዙም ጉልህ ቦታ የሌላቸው መስለው የሚታዩ ሰዎች “በእምነት ባለ ጠጎች” ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አብራራ።

10 ልክን የማወቅ ባሕርይ አንድ ዓይነት ኃላፊነት በሚሰጠን ጊዜ የእኛ ጥረትና ችሎታ ባይኖር ኖሮ ጉባኤው በሁለት እግሩ ሊቆም እንደማይችል ሌሎች እንዲሰማቸው በማድረግ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ወደ ራሳችን ከመሳብ እንድንቆጠብ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል ጥሩ የማስተማር ችሎታ ይኖረን ይሆናል። (ኤፌሶን 4:​11, 12) ይሁን እንጂ ልክን የማወቅ ባሕርይ ካለን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከምንማራቸው ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ያወቅነው ከመድረክ በሚቀርብ ትምህርት እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ለምሳሌ ያህል ልጆቻቸውን ይዘው አዘውትረው ወደ መንግሥት አዳራሽ የሚመጡ ነጠላ ወላጆች ወይም ምንም ዋጋ እንደሌለው ቢሰማውም እንኳ በታማኝነት ስብሰባ የሚመጣ የተጨነቀ ነፍስ ወይም በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ቦታ የሚደርሱበትን መጥፎ ተጽዕኖዎች ተቋቁሞ በመንፈሳዊ እድገት እያደረገ የሚሄድ ወጣት ስትመለከት አትበረታታም? (መዝሙር 84:​10) እነዚህ ሰዎች ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ምን ዓይነት የአቋም ጽናትን የሚጠይቁ ፈተናዎችን እየተቋቋሙ እንዳሉ በአብዛኛው ሌሎች አያውቁላቸውም። ሆኖም በኃላፊነት ቦታ ላይ ካሉት ያላነሰ “በእምነት ባለ ጠጎች” ሊሆኑ ይችላሉ። (ያዕቆብ 2:​5) ደግሞም መጨረሻ ላይ የይሖዋን ሞገስ የሚያስገኘው ታማኝነት ነው።​—⁠ማቴዎስ 10:​22፤ 1 ቆሮንቶስ 4:​2

በአባቱ ቤት “ታናሽ” የነበረው ጌዴዎን

11. ጌዴዎን ከአምላክ መልአክ ጋር ባደረገው ውይይት ልክን የማወቅ ባሕርይ ያሳየው እንዴት ነው?

11 ከምናሴ ነገድ የተነሳውና ኃያል ሰው የነበረው ወጣቱ ጌዴዎን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ሁከት በነገሠበት ዘመን ይኖር ነበር። የአምላክ ሕዝቦች ለሰባት ዓመታት በምድያማውያን ጭቆና ሥር ሲማቅቁ ኖረዋል። ይሁን እንጂ አሁን ይሖዋ ሕዝቡን የሚያድንበት ጊዜ ደረሰ። ስለሆነም አንድ መልአክ ለጌዴዎን ተገለጠና “አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፣ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።” ጌዴዎን ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለነበር ይህን ያልጠበቀውን ሙገሳ ሲሰማ ኩራት አልተሰማውም። ከዚያ ይልቅ በአክብሮት መልአኩን “ጌታዬ ሆይ፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን?” አለው። መልአኩ ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ካደረገለት በኋላ ‘እስራኤልን በእርግጥ ከምድያም እጅ ታድናለህ’ በማለት ነገረው። ታዲያ ጌዴዎን ምን ተሰማው? ይህንን አጋጣሚ ራሱን ስመ ጥር ጀግና አድርጎ ለማስጠራት የሚያስችለው አጋጣሚ እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር የተሰጠውን የሥራ ኃላፊነት ተቻኩሎ ከመቀበል ይልቅ “ጌታ ሆይ፣ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ” በማለት መለሰ። እንዴት ያለ ልክን የማወቅ ባሕርይ ነው!​—⁠መሳፍንት 6:​11-15

12. ጌዴዎን የተሰጠውን ተልእኮ በሚወጣበት ጊዜ ብልህነትን ያሳየው እንዴት ነው?

12 ይሖዋ ጌዴዎንን ወደ ጦርነት ከመላኩ በፊት ፈተና አቀረበለት። እንዴት? ጌዴዎን አባቱ ያሠራውን የበኣል መሠዊያ እንዲያፈርስና ከመሠዊያው አጠገብ ተተክሎ የነበረውን የማምለኪያ ዐፀድ እንዲቆርጥ ተነገረው። ይህን ማድረግ ድፍረት የሚጠይቅ ነበር። ሆኖም ጌዴዎን የተሰጠውን ተልእኮ በሚያከናውንበት ጊዜ ልክን የማወቅንና የብልህነትን ባሕርይ አሳይቷል። ጌዴዎን ተልእኮውን በገሃድ ከመፈጸም ይልቅ የማንንም ትኩረት ሳይስብ ጨለማን ተገን በማድረግ የተባለውን አከናወነ። በተጨማሪም ጌዴዎን የተሰጠውን ተልእኮ በሚፈጽምበት ጊዜ ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጓል። መሠዊያውንና የማምለኪያ ዐፀዱን በሚያፈርስበት ጊዜ ግማሾቹ እንዲረዱት ሌሎቹ ደግሞ ፈንጠር ብለው አካባቢውን መቃኘት እንዲችሉ ሳይሆን አይቀርም ከእርሱ ጋር አሥር አገልጋዮችን ወሰደ። b ያም ሆነ ይህ ጌዴዎን በይሖዋ ድጋፍ የተሰጠውን ተልዕኮ ያከናወነ ሲሆን በኋላም አምላክ እስራኤልን ከምድያማውያን ነፃ እንዲያወጣ ተጠቅሞበታል።​—⁠መሳፍንት 6:​25-27

ልክን የማወቅን ባሕርይና ብልህነትን ማሳየት

13, 14. (ሀ) አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ሲሰጠን ልካችንን የምናውቅ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ልክን የማወቅ ባሕርይ በማንጸባረቅ ረገድ ወንድም ኤ ኤች ማክሚላን ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

13 ጌዴዎን ካሳየው ልክን የማወቅ ባሕርይ ብዙ የምንማረው ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት በሚሰጠን ጊዜ የምንሰጠው ምላሽ ምን ዓይነት ነው? በመጀመሪያ ወደ አእምሯችን የሚመጣው መብቱ ስለሚያስገኝልን እውቅና ወይም ክብር ነው? ወይስ ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ መወጣት እችል ይሆን ብለን ልክን የማወቅ ባሕርይ በማንጸባረቅ በጸሎት እናስብበታለን? በ1966 ምድራዊ ሕይወቱን የጨረሰው ወንድም ኤ ኤች ማክሚላን በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ሲ ቲ ራስል በአንድ ወቅት እርሱ በማይኖርበት ጊዜ ሥራውን ማን ተክቶ ሊሠራ እንደሚችል ወንድም ማክሚላንን ጠይቆት ነበር። ከዚያም በኋላ ስለ ጉዳዩ ባደረጉት ውይይት አጋጣሚው የነበረው ቢሆንም አንድም ጊዜ እርሱ ሊተካው እንደሚችል አልተናገረም። መጨረሻ ላይ ወንድም ራስል ሥራውን ስለመቀበል እንዲያስብበት ለወንድም ማክሚላን ነገረው። “በድንጋጤ ፈዝዤ ቀረሁ” በማለት ወንድም ማክሚላን ከብዙ ዓመት በኋላ ጽፏል። “በቁም ነገር ካሰብኩበትና ጊዜ ወስጄ ጉዳዩን በጸሎት ከመረመርኩ በኋላ እርሱን ለመርዳት የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኔን ነገርኩት።”

14 ወንድም ራስል የሞተው ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር። በዚህ ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንትነቱ ቦታ ክፍት ሆነ። ወንድም ራስል የመጨረሻውን የስብከት ጉዞ ባደረገበት ወቅት ቦታውን ተክቶ ይሠራ የነበረው ወንድም ማክሚላን ስለነበር አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ነገረው:- “ማክ፣ ፕሬዚዳንት የመሆን አጋጣሚው ተከፍቶልሃል። ወንድም ራስል በማይኖርበት ጊዜ እርሱን ተክተህ ትሠራ የነበረው አንተ ነህ፤ ሁላችንም አንተ ያልከንን ሁሉ እንድንሠራ ነግሮን ነበር። አሁን ደግሞ እርሱ አንዴ ላይመለስ ሄዷል። በእርሱ እግር መተካት የሚኖርብህ አንተ ትመስለኛለህ።” ወንድም ማክሚላን እንዲህ በማለት መለሰ:- “ወንድም፣ ይህን ጉዳይ መመልከት የሚኖርብን በዚህ መንገድ አይደለም። ይህ የጌታ ሥራ ነው። በጌታ ድርጅት ውስጥ የሚኖርህ ማንኛውም ቦታ ጌታ ለአንተ የሚሰጥህ ተስማሚ ሆኖ ያገኘውን ነው። እኔ ደግሞ ለዚህ ሥራ የምበቃ አይደለሁም።” ከዚያም ወንድም ማክሚላን በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሌላ ሰው እንዲቀመጥ ሐሳብ አቀረበ። ልክ እንደ ጌዴዎን ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን አሳይቷል። እኛም እንዲህ የመሰለው አመለካከት ሊኖረን ይገባል።

15. ለሌሎች በምንሰብክበት ጊዜ ማስተዋል ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ የሆኑ መንገዶች ምንድን ናቸው?

15 እኛም የተሰጠንን ሥራ በምንፈጽምበት ጊዜ ልካችንን የምናውቅ መሆን አለብን። ጌዴዎን ጠንቃቃ በመሆን ሳያስፈልግ ተቃዋሚዎቹን ላለማስቆጣት ጥረት አድርጓል። እኛም በተመሳሳይ መንገድ በስብከቱ ሥራችን ላይ ተሠማርተን ሌሎችን ስናነጋግር ልካችንን የምናውቅና ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ ‘ምሽግን’ እና ‘አሳብን’ ለማፍረስ በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ እንገኛለን። (2 ቆሮንቶስ 10:​4, 5) ይሁን እንጂ ሌሎችን ማንኳሰስ ወይም በመልእክታችን ቅር እንዲሰኙ ማድረግ አይኖርብንም። ከዚያ ይልቅ በጋራ በምንስማማበት ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ የእነርሱን አመለካከት ማክበርና መልእክታችን ግሩም በሆኑት ተስፋዎች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል።​—⁠ሥራ 22:​1-3፤ 1 ቆሮንቶስ 9:​22፤ ራእይ 21:​4

ኢየሱስ​—⁠ልክን የማወቅን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ

16. ኢየሱስ ስለ ራሱ ልከኛ አመለካከት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?

16 ልክን በማወቅ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። c ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ያለው ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጉዳዮች ከእርሱ ሥልጣን በላይ እንደሆኑ ከመናገር ወደኋላ አላለም። (ዮሐንስ 1:​14) ለምሳሌ ያህል የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ሁለቱ ልጆቿ በመንግሥቱ ከእርሱ አጠገብ እንዲቀመጡ በጠየቀችው ጊዜ ኢየሱስ “በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን . . . እኔ የምሰጥ አይደለሁም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:​20-23) በሌላ ወቅትም ኢየሱስ “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም . . . የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻም” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 5:​30፤ 14:​28፤ ፊልጵስዩስ 2:​5, 6

17. ኢየሱስ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት ልክን የማወቅ ባሕርይ ያንጸባረቀው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ፍጽምና ከጎደላቸው ሰዎች በሁሉም አቅጣጫ የሚበልጥ ሲሆን አባቱ ይሖዋም ከማንም የበለጠ ሥልጣን ሰጥቶታል። ሆኖም ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር በነበረው ግንኙነት ሁሉ ልክን የማወቅ ባሕርይ አንጸባርቋል። የሚያውቃቸውን ነገሮች ሁሉ በመናገር እንዲጨነቁ አላደረጋቸውም። ሰብዓዊ ፍላጎቶቻቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሐዘኔታንና ርኅራኄን አሳይቷቸዋል። (ማቴዎስ 15:​32፤ 26:​40, 41፤ ማርቆስ 6:​31) ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም እንኳ ከሌሎች ፍጽምናን የሚጠብቅ አልነበረም። ደቀ መዛሙርቱ ከአቅማቸው በላይ እንዲያደርጉ አልጠበቀባቸውም፤ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይም አልጫነባቸውም። (ዮሐንስ 16:​12) ብዙዎች ኢየሱስን ዕረፍት የሚሰጥ ሆኖ ማግኘታቸው ምንም አያስደንቅም።​—⁠ማቴዎስ 11:​29

ኢየሱስ ያሳየውን ልክን የማወቅ ባሕርይ ኮርጁ

18, 19. (ሀ) ራሳችንን በምንመለከትበት መንገድ (ለ) ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ኢየሱስ ያሳየውን ልክን የማወቅ ባሕርይ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

18 እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ልክን የማወቅ ባሕርይ ካሳየ እኛ ደግሞ ይህን ባሕርይ ይበልጥ ማሳየት እንዳለብን የታወቀ ነው። ብዙውን ጊዜ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ሥልጣናቸው ገደብ ያለው መሆኑን አምኖ መቀበል ይከብዳቸዋል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ምሳሌ በመኮረጅ የልከኝነትን ባሕርይ ለማሳየት ይጥራሉ። ብቃቱ ላላቸው ሰዎች ኃላፊነት ለመስጠት እስኪያዳግታቸው ድረስ ኩራተኞች አይደሉም፤ ወይም ደግሞ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች የሚሰጡትን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረን በማለት ትዕቢተኛና እንቢተኛም አይደሉም። የትብብር መንፈስ በማሳየት በጉባኤ ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ “በአገባብና በሥርዓት” እንዲከናወኑ ይፈቅዳሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 14:​40

19 ልክን የማወቅ ባሕርይ ከሌሎች በምንጠብቀው ረገድ ምክንያታዊ እንድንሆንና ለሚያስፈልጋቸው ነገር ደግሞ አሳቢነት እንድናሳይ ይገፋፋናል። (ፊልጵስዩስ 4:​5) ሌሎች ሰዎች የሌሏቸው አንዳንድ ችሎታዎችና ጠንካራ ጎኖች ሊኖሩን ይችላሉ። ሆኖም ልካችንን የምናውቅ ከሆንን ሌሎች ሁልጊዜ እኛ እንደምንፈልገው እንዲያደርጉ አንጠብቅባቸውም። እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የሆነ የአቅም ገደብ እንዳለበት ማወቃችን የሌሎችን ስህተት በትህትና እንድናልፍ ይረዳናል። ጴጥሮስ “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​8

20. ያለብንን ማንኛውንም ዓይነት ልክን ያለማወቅ ዝንባሌ ለማሸነፍ ምን ልናደርግ እንችላለን?

20 እስካሁን እንደተማርነው በእርግጥም ጥበብ ልካቸውን በሚያውቁ ሰዎች ዘንድ ይገኛል። ይሁን እንጂ ልክን ያለማወቅ ወይም የትዕቢተኝነት ዝንባሌ እንዳለብህ ብትገነዘብስ? ተስፋ አትቁረጥ። ከዚያ ይልቅ “የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ [“በትዕቢት ኃጢአት እንዳልሠራ፣” NW ] ባሪያህን ጠብቅ” ብሎ የጸለየውን የዳዊትን ምሳሌ ተከተል። (መዝሙር 19:​13) ጳውሎስ፣ ጌዴዎንና ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰሉ ሰዎችን እምነት በመኮረጅ “በትሑታን [“ልካቸውን በሚያውቁ፣” NW ] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” የሚሉት ቃላት ምን ያህል እውነት መሆናቸውን በራሳችን ሕይወት ልናጣጥም እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 11:​2

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a “ሎሌ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በአንድ ትልቅ መርከብ ላይ ለመቅዘፍ የተመደበን ባሪያ ሊያመለክት ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ አንድ “መጋቢ” ርስትን እስከ ማስተዳደር ድረስ ብዙ ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል። የሆነ ሆኖ፣ መጋቢም ሆነ መርከብ የሚቀዝፍ ባሪያ በአብዛኞቹ ጌቶች ዓይን ልዩነት የላቸውም።

b ጌዴዎን ያሳየው ጥንቃቄና ብልህነት የፈሪነት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ በስህተት ሊወሰድ አይገባውም። ከዚህ ይልቅ ደፋር መሆኑን በ⁠ዕብራውያን 11:​32-38 ላይ የተረጋገጠ ሲሆን እዚያም ላይ “ከድካማቸው በረቱ” እንዲሁም “በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ” ከተባለላቸው ሰዎች መካከል ጌዴዎንም አብሮ ተጠቅሷል።

c ልክን ማወቅ አንድ ሰው አቅሙ ውስን መሆኑን እንዲገነዘብ የሚጠይቅ ባሕርይ በመሆኑ ይሖዋ ልኩን የሚያውቅ እንደሆነ ተደርጎ ሊነገር አይችልም። ይሁን እንጂ ትሑት ነው።​—⁠መዝሙር 18:​35 NW

ታስታውሳለህ?

• ልክን ማወቅ ምንድን ነው?

• ጳውሎስ ያሳየውን ልክን የማወቅ ባሕርይ እንዴት ልንኮርጅ እንችላለን?

• ጌዴዎን ከተወው ምሳሌ ልክን ስለማወቅ ምን ትምህርቶች እናገኛለን?

• ኢየሱስ ልክን በማወቅ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ልከኛ መሆኑ በክርስቲያን ባልንጀሮቹ ዘንድ እንዲወደድ አድርጎታል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጌዴዎን የአምላክን ፈቃድ በሚፈጽምበት ጊዜ የብልህነትን ባሕርይ አሳይቷል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ልኩን የሚያውቅ መሆኑን አሳይቷል