በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆች ያልወለዱት ለምንድን ነው?

ልጆች ያልወለዱት ለምንድን ነው?

ልጆች ያልወለዱት ለምንድን ነው?

ዴሌ እና ፎላ a የተባሉ ባልና ሚስት የሚኖሩትና የሚሠሩት ናይጄሪያ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነው። እዚያ ማገልገል ከጀመሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የፎላ እናት ልትጠይቃቸው መጣች። እዚህ ድረስ ረጅም ርቀት ተጉዛ የመጣችው ያስጨነቃትንና እንቅልፍ የነሳትን በጣም አሳሳቢ ነገር ልታዋያቸው ነበር።

“ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ” አለቻቸው። “ስጦታዎች ትልኩልኛላችሁ። መጥታችሁ ትጠይቁኛላችሁ። እንዲህ ያሉትን የፍቅር መግለጫዎች ከልብ የማደንቅ ቢሆንም በሌላው በኩል ግን ያስጨንቁኛል። ምክንያቱም እኔ ዕድሜ ላይ ስትደርሱ ማን እንደዚህ ያደርግላችኋል ብዬ አስባለሁ። ከተጋባችሁ ሁለት ዓመት ሆኗችኋል፤ ግን ልጆች የሏችሁም። አሁን ቤቴልን ለቅቃችሁ የራሳችሁን ቤተሰብ መመሥረት ያለባችሁ አይመስላችሁም?”

እናትየዋ እንደሚከተለው በማለት አስባ ነበር:- ዴሌ እና ፎላ በቤቴል በቂ ጊዜ አሳልፈዋል። አሁን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ይኖርባቸዋል። ሌሎች ሰዎች እነርሱን ተክተው ሊሠሩ ይችላሉ። ዴሌ እና ፎላ የግድ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ማቋረጥ ባይኖርባቸውም ልጆች መውለድና ወላጅ መሆን የሚያስገኘውን ደስታ ለመቅመስ በሚያስችላቸው አንድ ዓይነት የአገልግሎት ዘርፍ መሠማራት ይችላሉ።

እናትየዋን ያሳሰባት ነገር

እናትየዋ እንዲህ መጨነቋ አያስገርምም። ልጅ ለመውለድ ያለው ፍላጎት በጣም ሥር የሰደደ ከመሆኑም በላይ በሁሉም ባሕሎችና ጊዜያት የነበረና ያለ ነው። ልጅ መውለድ ከፍተኛ የደስታና የተስፋ ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው” በማለት ይናገራል። አዎን፣ ልጅ የመውለድ ችሎታ ከአፍቃሪው ፈጣሪያችን የተገኘ ውድ ስጦታ ነው።​—⁠መዝሙር 127:​3

በብዙ አገሮች ውስጥ የተጋቡ ወንድና ሴት ልጆች እንዲወልዱ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ግፊት ያደርግባቸዋል። ለምሳሌ አንዲት ሴት በአማካኝ ስድስት ልጆች በምትወልድበት በናይጄሪያ በሠርግ ሥነ ሥርዓት ወቅት ለአዲሶቹ ተጋቢዎች መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹ ሰዎች “ከዘጠኝ ወር በኋላ በቤታችሁ የሚያለቅስ ሕፃን ድምፅ እንደምንሰማ ተስፋ እናደርጋለን” ብለው ሲናገሩ መስማት የተለመደ ከመሆኑም በላይ ሙሽሮቹ የሕፃን አልጋ በስጦታ መልክ ሊሰጣቸው ይችላል። አማቶች ደግሞ የቀን መቁጠሪያውን በጥንቃቄ ስለሚከታተሉ ሙሽራዋ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ካላረገዘች ችግር ሊኖር ይችላል ብለው ስለሚያስቡ ችግሩን ለመቅረፍ እርዳታ ማበርከት ይችሉ እንደሆነ ይጠይቃሉ።

ብዙ እናቶች አንድ ወንድና ሴት የሚጋቡት ልጆች ለመውለድና የቤተሰቡ የትውልድ መሥመር እንዲቀጥል ለማድረግ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። የፎላ እናት እንዲህ ብላት ነበር:- “ልጆች የማትወልዱ ከሆነማ ለምን ተጋባችሁ? ወላጆቻችሁ እናንተን እንደወለዱ ሁሉ እናንተም የራሳችሁን ልጆች መውለድ አለባችሁ።”

ከዚህም በላይ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ። በብዙ የአፍሪካ አገሮች በዕድሜ ለገፉ ሰዎች የሚሰጥ ድጎማም ሆነ ለአረጋውያን እንክብካቤ የሚያደርግ መንግሥታዊ ተቋም እምብዛም የለም። ትልልቅ የሆኑት ልጆች ሕፃናት ሳሉ ወላጆቻቸው እንደተንከባከቧቸው ሁሉ ልጆች ደግሞ በተራቸው ወላጆቻቸውን መንከባከባቸው የተለመደ ነው። ስለዚህ የፎላ እናት ልጆቿ የራሳቸው የሆኑ ልጆች ካልወለዱ በስተቀር በኋለኞቹ ዓመታት ማንም ዞር ብሎ የማያያቸው ብቸኞች ሊሆኑና ሊደኸዩ ብሎም በሚሞቱበት ወቅት ቀባሪ የማጣት አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል የሚል ስጋት አድሮባት ነበር።

በብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ልጆች አለመውለድ እንደ እርግማን ተደርጎ ይቆጠራል። እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች ሴቶች ገና ሳያገቡ ልጅ የመውለድ ችሎታቸውን እንዲያረጋግጡ ይጠበቅባቸዋል። ለመፀነስ ያልቻሉ ብዙ ሴቶች ሕክምና በማድረግና መድሃኒት በመውሰድ መካንነታቸውን ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

እንዲህ ካሉት አመለካከቶች የተነሣ ሆነ ብለው ልጅ ላለመውለድ የወሰኑ ባልና ሚስት ራሳቸውን ጥሩ ነገር እየነፈጉ እንዳሉ ተደርጎ ይታሰባል። እንዲህ ያሉትን ባልና ሚስቶች ብዙውን ጊዜ ከሌላው ሰው የተለዩ፣ አርቀው የማያስቡና በጣም የሚያሳዝኑ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል።

ደስታና ኃላፊነት

የይሖዋ ሕዝቦች ልጆች ማሳደግ ደስታ እንደሚያስገኝ ቢያውቁም ኃላፊነት እንደሚያስከትልም ይገነዘባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​8 ላይ “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” በማለት ይናገራል።

ወላጆች ለልጆቻቸው ሥጋዊና መንፈሳዊ ነገሮችን ማቅረብ አለባቸው። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ልጆች የሚሰጠን አምላክ እስከሆነ ድረስ እሱ ያውቃል ብሎ ኃላፊነቱን ለእሱ የመተው ዝንባሌ የላቸውም። ልጆችን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ኮትኩቶ ማሳደግ ለሌሎች የሚተው ሳይሆን አምላክ ሙሉ በሙሉ ለወላጆች የሰጠው ኃላፊነት መሆኑን ይገነዘባሉ።​—⁠ዘዳግም 6:​6, 7

በተለይ በዚህ ‘አስጨናቂ የመጨረሻ ቀን’ ልጆችን ማሳደግ በጣም ከባድ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) እየከፋ ከሚሄደው የኢኮኖሚ ሁኔታ በተጨማሪ በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ያለው የኅብረተሰቡ አምላክ የለሽነት በዛሬው ጊዜ ልጆችን ማሳደግ ይበልጥ ተፈታታኝ እንዲሆን አድርጎታል። ያም ሆኖ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ይህንን ፈታኝ ሁኔታ ተቋቁመው ‘በጌታ ምክርና ተግሣጽ’ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ልጆች ለማሳደግ ችለዋል። (ኤፌሶን 6:​4) እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጠንክረው ስለሚሠሩ ይሖዋ ይወዳቸዋል እንዲሁም ይባርካቸዋል።

አንዳንዶች ልጆች የማይወልዱበት ምክንያት

በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ልጆች የሏቸውም። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ልጅ የመውለድ ችሎታ ባይኖራቸውም እንኳ የሌሎች ሰዎችን ልጆች በጉዲፈቻ ለማሳደግ አልመረጡም። ልጅ የመውለድ ችሎታ ያላቸው ሌሎች ደግሞ ላለመውለድ ወስነዋል። እንዲህ ያሉት ባልና ሚስቶች ይህንን ውሳኔ ያደረጉት ከኃላፊነት ለመሸሽ ወይም ወላጅ መሆን የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መጋፈጥ ስላስፈራቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ልጆች ቢወልዱ ሊሳተፉ በማይችሉባቸው የተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች በሙሉ ልባቸው ለመካፈል ቁርጥ ውሳኔ ስላደረጉ ነው። አንዳንዶቹ ሚስዮናዊ ሆነው ሲያገለግሉ ሌሎች ደግሞ ይሖዋን ተጓዥ የበላይ ተመልካች ወይም ቤቴላዊ በመሆን ያገለግላሉ።

እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እነርሱም ሊሠራ የሚገባው አጣዳፊ ሥራ እንዳለ ይገነዘባሉ። ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል ተናግሯል። ይህ ሥራ ዛሬ በመሠራት ላይ ይገኛል። “መጨረሻው” ምሥራቹን ሰምተው እርምጃ ላልወሰዱ ሰዎች ጥፋት ማለት ስለሆነ ሥራው በጣም ወሳኝ ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ 2 ተሰሎንቄ 1:​7, 8

አሁን እኛ ያለንበት ጊዜ ኖህና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ ያዳናቸውን ግዙፍ መርከብ ሲገነቡ ከነበሩበት ጊዜ ጋር ይመሳሰላል። (ዘፍጥረት 6:​13-16፤ ማቴዎስ 24:​37) ሦስቱ የኖህ ልጆች አግብተው የነበረ ቢሆንም ከጥፋት ውኃው በፊት ማንኛቸውም ልጆች አልወለዱም። ለዚህ አንደኛው ምክንያት እነዚህ ባልና ሚስቶች ሙሉ ትኩረታቸውንና ኃይላቸውን አጣዳፊ በነበረው ሥራ ላይ ማድረግ ስለፈለጉ ሊሆን ይችላል። ሌላው ምክንያት ደግሞ ‘የሰው ክፋት . . . በበዛበት፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ’ በሆነበት የረከሰና ዓመፀኛ ዓለም ውስጥ ልጆች መውለድ ስላልፈለጉ ሊሆን ይችላል።​—⁠ዘፍጥረት 6:​5

እንዲህ ሲባል በአሁኑ ጊዜ ልጆች መውለድ ስህተት ነው ማለት ባይሆንም ብዙ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ይሖዋ ሕዝቦቹ እንዲሠሩት በሰጣቸው አጣዳፊ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለመካፈል ሲሉ በፈቃዳቸው ልጆች ላለመውለድ ወስነዋል። አንዳንድ ባልና ሚስቶች ልጆች ሳይወልዱ በይሖዋ አገልግሎት የተወሰነ ጊዜ ሲያሳልፉ ሌሎች ደግሞ ጽድቅ የሚሰፍንበት የይሖዋ አዲስ ዓለም እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ልጅ ሳይወልዱ በይሖዋ አገልግሎት ተጠምደው መቀጠል መርጠዋል። ይህ አርቆ አለማሰብ ነውን? በሕይወታቸው ውስጥ አንድ ጥሩ አጋጣሚ እያመለጣቸው ነውን? በጣም የሚያሳዝኑ ሊያሰኛቸውስ ይገባልን?

ዋስትና ያለው አስደሳች ሕይወት

አስቀድመው የተጠቀሱት ዴሌ እና ፎላ ከተጋቡ ከአሥር ዓመት በላይ ቢሆናቸውም አሁንም ልጅ ሳይወልዱ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። “አሁንም እንኳ ዘመዶቻችን ልጆች እንድንወልድ ግፊት ያደርጉብናል” በማለት ዴሌ ይናገራል። “በዋነኛነት የሚያሳስባቸው ነገር የወደፊቱ ደኀንነታችን ነው። ለአሳቢነታቸው ያለንን አድናቆት ዘወትር የምንገልጽላቸው ቢሆንም እየሠራነው ባለነው ሥራ በጣም ደስተኞች እንደሆንን በዘዴ እንነግራቸዋለን። በታማኝነት ከእርሱ ጎን ለሚጓዙት ሰዎች ደህንነት በሚያስበው በይሖዋ ስለምንታመን ደህንነታችን ሊያሳስባቸው እንደማይገባ እንነግራቸዋለን። በተጨማሪም ልጆች መውለድ ወላጆች በሚያረጁበት ጊዜ የልጆቻቸውን እንክብካቤ እንደሚያገኙ ዋስትና ሊሆን እንደማይችል እንገልጽላቸዋለን። አንዳንድ ልጆች ለወላጆቻቸው የሚያደርጉት እንክብካቤ በጣም ውስን ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የመርዳት አቅሙ የላቸውም። እንዲሁም ሌሎች ከወላጆቻቸው በፊት ይሞታሉ። በሌላው በኩል ግን እኛ በይሖዋ ዘንድ የተረጋገጠ የወደፊት ተስፋ አለን።”

ዴሌ እና እንደ እርሱ ያሉት ሌሎች ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” ሲል በገባው ቃል ላይ ሙሉ ትምክህት አላቸው። (ዕብራውያን 13:​5) በተጨማሪም ‘የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን እንደማያጥር፣ ጆሮውም ከመስማት እንደማይደነቁር’ ያምናሉ።​—⁠ኢሳይያስ 59:​1

በይሖዋ እንዲታመኑ ያደረጋቸው ሌላው ምክንያት ደግሞ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት እንደሚደግፋቸው መመልከታቸው ነው። ንጉሥ ዳዊት “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል . . . አላየሁም” ሲል ጽፏል። እስቲ አስበው፣ ‘ፈጽሞ የተጣለ’ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ አይተህ ታውቃለህ?​—⁠መዝሙር 37:​25

ሕይወታቸውን ሙሉ ይሖዋንና ክርስቲያን ባልደረቦቻቸውን በማገልገል ያሳለፉ ክርስቲያኖች ያለፈውን ጊዜ ሲያስቡ እርካታ እንጂ ጸጸት አይሰማቸውም። ወንድም ኢሮ ኡማ ለ45 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈለ ሲሆን አሁን በናይጄሪያ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግላል። “እኔና ሚስቴ ልጆች የሌሉን ቢሆንም ይሖዋ ዘወትር በመንፈሳዊና በሥጋዊ እንደተንከባከበን ይሰማናል። ምንም ነገር አላጣንም። ስናረጅም ቢሆን አይተወንም። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍናቸው እነዚያ ዓመታት በሕይወታችን ውስጥ በጣም አስደሳች የሆኑ ጊዜያት ናቸው። ወንድሞቻችንን ማገልገል በመቻላችንና እነርሱም አገልግሎታችንን በማድነቅ ስለረዱን አመስጋኞች ነን።”

ብዙ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ሥጋዊ ልጆች ባይወልዱም ሌሎች ልጆች ማለትም ይሖዋን የሚያመልኩ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት አፍርተዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” ብሎ ሲጽፍ 100 ዓመት ገደማ ሆኖት ነበር። (3 ዮሐንስ 4) ‘እውነትን’ ያሳወቃቸው ‘ልጆቹ’ ያሳዩት ታማኝነት ታላቅ ደስታ አምጥቶለታል።

ዛሬም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ደስታ በብዛት ይገኛል። በርኒስ የተባለች ናይጄሪያዊት ሴት ካገባች 19 ዓመት ሲሆናት በፈቃዷ ልጅ ሳትወልድ ቆይታለች። ላለፉት 14 ዓመታት የዘወትር አቅኚ በመሆን አገልግላለች። በርኒስ ልጅ መውለድ የማትችልበት ዕድሜ እየተቃረበ ሲመጣ እንኳ ሕይወቷን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ በማዋሏ ምንም የጸጸት ስሜት አልተሰማትም። እንዲህ ብላለች:- “መንፈሳዊ ልጆቼ ሲያድጉ መመልከት ያስደስተኛል። ልጆች ወልጄ ቢሆን እንኳ እውነትን እንዲማሩ ከረዳኋቸው ሰዎች የበለጠ ከእኔ ጋር መቀራረባቸውን እጠራጠራለሁ። ደስታቸውን በማካፈልና ችግር ሲደርስባቸው ምክር በመጠየቅ ልክ እንደ እናታቸው አድርገው ይመለከቱኛል። ደብዳቤ ይጽፉልኛል። እርስ በእርስም እንጠያየቃለን።

“አንዳንዶች ልጅ አለመውለድ እርግማን እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ልጆች ከሌሏችሁ በእርጅና ዘመናችሁ ትሰቃያላችሁ በማለት ይናገራሉ። እኔ ግን እንደዚያ አድርጌ አልመለከተውም። ይሖዋን በሙሉ ነፍሴ እስካገለገልኩ ድረስ እንደሚክሰኝና እንደሚንከባከበኝ አውቃለሁ። ሳረጅ ፈጽሞ አይጥለኝም።”

በአምላክ የተወደዱና ከፍ ያለ ግምት የሚሰጣቸው

ልጅ የወለዱና ‘በእውነት መንገድ እንዲሄዱ’ አድርገው ያሳደጉ ወላጆች አመስጋኝ የሚሆኑባቸው ብዙ ምክንያቶች አሏቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፣ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል። አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፣ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት” ማለቱ ምንም አያስገርምም!​—⁠ምሳሌ 23:​24, 25

ልጆች ወደዚህ ዓለም ማምጣት የሚያስገኘውን ደስታ ያላጣጣሙ ክርስቲያኖች በሌሎች መንገዶች ተባርከዋል። ከእነዚህ ባልና ሚስት መካከል ብዙዎቹ የመንግሥቱን ፍላጎቶች በማስፋፋት ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፏቸው ዓመታት ውስጥ ለመንግሥቱ ሥራ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ልምድ፣ ጥበብና ችሎታ በማግኘታቸው በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ በዚህ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው ያገለግላሉ።

ለመንግሥቱ ፍላጎቶች ሲሉ ልጆች ላለመውለድ ቢወስኑም ይሖዋ የከፈሉትን መሥዋዕት በጥልቅ የሚያደንቅ አፍቃሪ መንፈሳዊ ቤተሰብ በመስጠት ባርኳቸዋል። ይህም ኢየሱስ “ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ አሁን በዚህ ዘመን . . . ቤቶችን ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም” ብሎ እንደተናገረው ነው።​—⁠ማርቆስ 10:​29, 30

ታማኞች የሆኑ ሁሉ በይሖዋ ፊት እንዴት ውድ ናቸው! ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” በማለት ልጆች ላሏቸውም ሆኑ ለሌሏቸው ታማኞች በጠቅላላ ዋስትና ሰጥቷል።​—⁠ዕብራውያን 6:​10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች የሌሏቸው ባልና ሚስቶች አፍቃሪ መንፈሳዊ ቤተሰብ በማግኘት ተባርከዋል