በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል

ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል

ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል

“ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።”​—⁠ምሳሌ 11:​2

1, 2. ትዕቢት ምንድን ነው? ለውድቀት ሊዳርግ የሚችለውስ እንዴት ነው?

 አንድ ምቀኛ ሌዋዊ ይሖዋ በሾማቸው ላይ ለማመፅ የተነሱ ሰዎች አስተባባሪ ሆነ። የሥልጣን ጥም ያሰከረው አንድ ልዑል የአባቱን ዙፋን ለመቀማት በተንኮል አሴረ። ትዕግሥት የሌለው አንድ ንጉሥ የአምላክ ነቢይ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ናቀ። እነዚህን ሦስት እስራኤላውያን የሚያመሳስላቸው አንድ ባሕርይ አለ። ይኸውም ትዕቢት ነው።

2 ትዕቢት እገሌ ከገሌ ሳይል ሁሉንም ሰው ለችግር ሊዳርግ የሚችል የልብ ዝንባሌ ነው። (መዝሙር 19:​13) ትዕቢተኛ የሆነ ሰው አንድን ነገር የማድረግ ሥልጣን ሳይኖረው በማን አለብኝነት ይሠራል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው አካሄድ ለውድቀት ይዳርጋል። እንዲያውም፣ ትዕቢት ነገሥታትን ጥሏል፣ ግዛቶችን አፍርሷል። (ኤርምያስ 50:​29, 31, 32፤ ዳንኤል 5:​20) አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮችንም እንኳ ሳይቀር አጥምዶ ለጥፋት ዳርጓቸዋል።

3.ትዕቢት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል እንዴት ማወቅ እንችላለን?

3 መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” ብሎ የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም። (ምሳሌ 11:​2) መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ምሳሌ እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ምሳሌዎች ይዞልናል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን መመርመራችን ገደብን አልፎ መሄድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ስለዚህ ምቀኝነት፣ የሥልጣን ጥመኝነትና ትዕግሥት ማጣት በመግቢያው ላይ የተጠቀሱትን ሰዎች በትዕቢት እርምጃ እንዲወስዱ እንዴት እንዳነሳሳቸውና ለጥፋት እንዴት እንደዳረጋቸው እንመርምር።

ቆሬ​—⁠ቅናት ያደረበት ዓመፀኛ

4. (ሀ) ቆሬ ማን ነው? በየትኛው ታሪካዊ ክንውን ውስጥ ተካፋይ ሳይሆን አይቀርም? (ለ) ቆሬ ወደኋላ ላይ ምን መጥፎ ድርጊት ፈጸመ?

4 ቆሬ ከቀዓት ወገን የሆነ ሌዋዊ ሲሆን የሙሴና የአሮን የአጎት ልጅ ነው። ለአሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግል እንደነበረ ግልጽ ነው። ቆሬ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ቀይ ባሕርን በሕይወት የመሻገር መብት ካገኙት ሰዎች መካከል አንዱ ከመሆኑም በላይ በሲና ተራራ በጥጃ አምልኮ በተካፈሉ እስራኤላውያን ላይ የይሖዋን ፍርድ ካስፈጸሙት ሰዎች መካከል አንዱ ሳይሆን አይቀርም። (ዘጸአት 32:​26) ዳሩ ምን ያደርጋል በመጨረሻ የሮቤልን ልጆች ዳታንን፣ አቤሮንን እና አንን ጨምሮ 250 የእስራኤል አለቆች በሙሴና በአሮን ላይ እንዲያምፁ በማድረግ ረገድ ቀንደኛ የዓመፁ መሪ ሆነ። a “ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፣ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ ተናገሩ።​—⁠ዘኁልቁ 16:​1-3

5, 6. (ሀ) ቆሬ በሙሴና በአሮን ላይ ያመፀው ለምንድን ነው? (ለ) ቆሬ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የተሰጠውን ቦታ አቅልሎ ተመልክቶታል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

5 ቆሬ ለዓመታት ታማኝ ሆኖ ከቆየ በኋላ ዓመፀኛ የሆነው ለምንድን ነው? ሙሴ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” ስለነበር እስራኤልን በጭቆና እንዳልመራ የተረጋገጠ ነው። (ዘኁልቁ 12:​3) ቆሬ በሙሴና በአሮን ላይ ባደረበት ቅናት ሥልጣናቸውን ለመቀበል ሳይፈልግ የቀረ ይመስላል፤ ይህም በማን አለብኝነትና በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ ራሳቸውን ከጉባኤው በላይ ከፍ አድርገዋል ብሎ በተሳሳተ መንገድ እንዲናገር አደረገው።​—⁠መዝሙር 106:​16

6 ቆሬ ከነበሩበት ችግሮች መካከል አንደኛው በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የነበረውን ቦታ ከፍ አድርጎ ለመመልከት ሳይችል መቅረቱ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሌዋዊ የነበሩት ቀዓታውያን ካህናት ሆነው አያገልግሉ እንጂ የአምላክ ሕግ አስተማሪዎች ነበሩ። እንዲሁም የመገናኛ ድንኳኑ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚጓጓዝበት ጊዜ ዕቃዎቹንና ቁሳቁሶቹን ተሸክመው ይወስዱ ነበር። ዕቃዎቹን ተሸክመው ከሚያጓጉዙት ሰዎች ሃይማኖታዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ይጠበቅ ስለነበር ይህ ዓይነቱ ሥራ እንደ ተራ የሚታይ አልነበረም። (ኢሳይያስ 52:​11) ስለዚህም ሙሴ ቆሬን የተሰጠህን የአገልግሎት ሥራ ንቀህ ነው የክህነት አገልግሎት ለመያዝ የፈለግኸው? ብሎ የጠየቀው ያህል ነበር። (ዘኁልቁ 16:​9, 10) ቆሬ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ በተመደቡበት ቦታ በታማኝነት ማገልገል ልዩ ሥልጣን ወይም ደረጃ ከማግኘት የበለጠ ነገር መሆኑን ሳይገነዘብ ቀርቷል።​—⁠መዝሙር 84:​10

7. (ሀ) ሙሴ የቆሬንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ጉዳይ በተመለከተ ምን አደረገ? (ለ) የቆሬ ዓመፅ መጨረሻው ጥፋት የሆነው እንዴት ነው?

7 ሙሴ በቀጣዩ ቀን ጠዋት የእሳት ጥና እና ዕጣን ይዘው በመገናኛው ድንኳን አጠገብ እንዲሰበሰቡ ቆሬንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ጋበዛቸው። ቆሬና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ካህናት ስላልሆኑ ዕጣን የማቅረብ ሥልጣን አልነበራቸውም። ጉዳዩን በጥሞና እንዲያስቡበት የሚያስችል አንድ ሙሉ ሌሊት ካገኙ በኋላም እንኳ የእሳት ጥና እና ዕጣን ይዘው ከመጡ እነዚህ ሰዎች በክህነት የማገልገል መብት እንዳላቸው ሆኖ የሚሰማቸው መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ይሆናል። በቀጣዩ ቀን ራሳቸውን ሲያቀርቡ ይሖዋ በቀጥታ ቁጣውን ገለጸ። “መሬት ተሰነጠቀ፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ” የሮቤልን ልጆች ዋጠች። ቆሬን ጨምሮ የቀሩት ከአምላክ እሳት መጥቶ በላቸው። (ዘዳግም 11:​6፤ ዘኁልቁ 16:​16-35፤ 26:​10) ቆሬ ትዕቢተኛ መሆኑ ለከፋ ውርደት ዳርጎታል ማለትም የአምላክን ሞገስ አሳጥቶታል!

‘የቅንዓትን ዝንባሌ’ መዋጋት

8. ‘የቅንዓት ዝንባሌ’ በክርስቲያኖች መካከልም ሊንጸባረቅ የሚችለው እንዴት ነው?

8 ስለ ቆሬ የሚናገረው ዘገባ ለእኛ ማስጠንቀቂያ ነው። ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች ውስጥ ‘የቅንዓት ዝንባሌ’ የሚገኝ በመሆኑ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንኳ ሳይቀር ይህ ባሕርይ ሊንጸባረቅ ይችላል። (ያዕቆብ 4:​5) ለምሳሌ ያህል ሥልጣን ፈላጊዎች ልንሆን እንችላለን። እኛ የተመኘነውን መብት ሌሎች ሲያገኙት ስናይ እንደ ቆሬ የቅናት ስሜት ሊያድርብን ይችላል። ወይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው እንደ ዲዮጥራጢስ ልንሆን እንችላለን። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደምንችለው የሐዋርያነትን ሥልጣን ይመኝ ስለነበር ይህን ቦታ አብዝቶ ይነቅፍ ነበር። እንዲያውም ዮሐንስ “ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ” በማለት ጽፏል።​—⁠3 ዮሐንስ 9

9. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ኃላፊነቶችን በተመለከተ የትኛውን አመለካከት ማስወገድ ይኖርብናል? (ለ) በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ስላለን ቦታ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው?

9 እርግጥ ነው፣ አንድ ክርስቲያን ለጉባኤ ኃላፊነቶች ለመብቃት ቢጣጣር ምንም ስህተት የለበትም። እንዲያውም ጳውሎስ እንዲህ ማድረግን አበረታቷል። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1) ይሁን እንጂ የአገልግሎት መብቶችን ማግኘት ከሌሎች በላይ የሚያደርግ ልዩ ሥልጣን እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይገባንም። ኢየሱስ “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፣ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” በማለት የተናገረውን አስታውስ። (ማቴዎስ 20:​26, 27) በአምላክ ፊት ያለን ዋጋ የሚለካው በድርጅቱ ውስጥ ባለን “ቦታ” እንደሆነ አድርገን በማሰብ ከፍተኛ ኃላፊነት ባላቸው ሰዎች ላይ መቅናት ተገቢ አይደለም። ኢየሱስ “እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:​8) አዎን፣ አስፋፊም ሆኑ አቅኚዎች፣ በቅርቡ የተጠመቁም ሆኑ ለረዥም ጊዜያት ጽኑ አቋማቸውን የጠበቁ፣ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ የሚያገለግሉ ሁሉ በእርሱ ዝግጅት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ አላቸው። (ሉቃስ 10:​27፤ 12:​6, 7፤ ገላትያ 3:​28፤ ዕብራውያን 6:​10) “እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ከሚጣጣሩ በሚልዮን ከሚቆጠሩ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት በእርግጥም በረከት ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​5

አቤሴሎም​—⁠የሥልጣን ጥም የተጠናወተው አድርባይ ሰው

10. አቤሴሎም ማን ነበር? ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጡ ሰዎችን ልብ ለመማረክ የሞከረውስ እንዴት ነበር?

10 የንጉሥ ዳዊት ሦስተኛ ልጅ የነበረው አቤሴሎም ከተከተለው የሕይወት ጎዳና ለሥልጣን መቋመጥን በተመለከተ ተግባራዊ የሆነ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ይህ መሠሪና አድርባይ የሆነ ሰው ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጡት ሰዎችን ልብ ለመማረክ ሙከራ አድርጓል። በመጀመሪያ ዳዊት ለእነርሱ ችግር ምንም ደንታ እንደሌለው በረቀቀ መንገድ ተናገረ። ከዚያም ዙሪያ ጥምጥም መናገሩን አቆመና በቀጥታ ድብቅ ምኞቱን ይፋ አወጣ። አቤሴሎም “ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?” በማለት ተናገረ። የአቤሴሎም ተንኮል በዚህ ብቻ አላበቃም። “ሰውም እጅ ሊነሣው ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ ይይዝና ይስመው ነበር። እንዲሁም አቤሴሎም ከንጉሥ ፍርድ ሊሰማ ከእስራኤል ዘንድ በሚመጣ ሁሉ ያደርግ ነበር።” ውጤቱስ ምን ሆነ “አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።”​—⁠2 ሳሙኤል 15:​1-6

11. አቤሴሎም የዳዊትን ዙፋን ለመቀማት ሙከራ ያደረገው እንዴት ነው?

11 አቤሴሎም የአባቱን ዙፋን ለመቀማት ቆርጦ ተነስቶ ነበር። ከአምስት ዓመት በፊት የአቤሴሎምን እህት ትዕማርን በመድፈሩ ምክንያት የተበቀለው በማስመሰል አምኖን የተባለውን የዳዊትን የመጀመሪያ ልጅ ገደለ። (2 ሳሙኤል 13:​28, 29) ይሁን እንጂ የአምኖን መገደል የሚቀናቀነው እንዳይኖር እንደሚያደርግለት ስለሚያውቅ በዚያን ጊዜም ቢሆን ቀልቡ ያረፈው በዙፋኑ ላይ ሊሆን ይችላል። b ያም ሆነ ይህ አቤሴሎም ምቹ ነው ብሎ ያሰበው ጊዜ ሲደርስ ሌላ እርምጃ ወሰደ። ንግሥናው በአገሩ ሁሉ እንዲታወጅ አደረገ።​—⁠2 ሳሙኤል 15:​10

12. አቤሴሎም ትዕቢተኛ መሆኑ ለውርደት የዳረገው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

12 አቤሴሎም ጊዜያዊ ስኬት በማግኘቱ “ሴራውም ጽኑ ሆነ ከአቤሴሎምም ጋር ያለው ሕዝብ እየበዛ ሄደ።” በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ሲል ለመሸሽ ተገደደ። (2 ሳሙኤል 15:​12-17) ብዙም ሳይቆይ ኢዮአብ አቤሴሎምን ገድሎና ጉድጓድ ውስጥ ጥሎ ድንጋይ በከመረበት ጊዜ የሕይወት ታሪኩ በዚያው አከተመ። እስቲ አስበው ንጉሥ ለመሆን ይቋምጥ የነበረው ይህ ሰው በሞተ ጊዜ በሥርዓት እንኳ አልተቀበረም! c በእርግጥም ትዕቢት በአቤሴሎም ላይ ውርደት አስከትሎበታል።​—⁠2 ሳሙኤል 18:​9-17

በራስ ወዳድነት ላይ ከተመሠረተ የሥልጣን ምኞት ራቅ

13. የሥልጣን ምኞት በአንድ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ሥር ሊሰድ የሚችለው እንዴት ነው?

13 አቤሴሎም ለሥልጣን ከነበረው ምኞትና በኋላም ከደረሰበት ውድቀት እኛም ትምህርት እናገኛለን። ስለ ሌላው ምንም ደንታ በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ ሰዎች አንድ ዓይነት ስሜት ለማሳደር ምናልባትም አንድ ዓይነት ጥቅም ወይም ሹመት ለማግኘትና ተወዳጅነት ለማትረፍ ሲሉ አለቆቻቸውን መሸንገላቸው የተለመደ ነገር ነው። በተመሳሳይም የበታቾቻቸውን ትኩረትና ድጋፍ ለማግኘት ሲሉም በጉራ ሊናገሩ ይችላሉ። እኛም ካልተጠነቀቅን እንዲህ ያለው የሥልጣን ምኞት በልባችን ውስጥ ሥር ሊሰድ ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ የመሰለ ነገር በአንዳንዶች ላይ ተከስቶ ስለነበር ሐዋርያት ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ስለመራቅ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈልጓቸው ነበር።​—⁠ገላትያ 4:​17፤ 3 ዮሐንስ 9, 10

14. በሥልጣን ጥም ራስን ከፍ ከፍ ከማድረግ መንፈስ መራቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ ‘የራሳቸውን ክብር በመፈለግ’ ከሌሎች ልቀው ለመታየት የሚሞክሩ ሰዎች በድርጅቱ ውስጥ እንዲኖሩ አይፈቅድም። (ምሳሌ 25:​27) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፣ ታላቅ ነገርን የምትናገረውንም ምላስ” በማለት ያስጠነቅቃል። (መዝሙር 12:​3) አቤሴሎም ልዝብ ከንፈሮች ነበሩት። የቋመጠለትን ሥልጣን ለማግኘት ሲል ትኩረት እንዲሰጡት የሚፈልጋቸውን ሰዎች ይሸነግላቸው ነበር። ከዚህ በተቃራኒ “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር” የሚለውን የጳውሎስ ምክር በሚከተል የወንድማማች ማኅበር መካከል መገኘታችን ምንኛ በረከት ነው!​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​3

ሳኦል​—⁠ትዕግሥት የለሹ ንጉሥ

15. በአንድ ወቅት ሳኦል ልኩን ያውቅ እንደነበረ ያሳየው እንዴት ነው?

15 ከጊዜ በኋላ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ሳኦል በአንድ ወቅት ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል ወጣት በነበረበት ጊዜ የሆነውን ተመልከት። የአምላክ ነቢይ የነበረው ሳሙኤል ስለ እርሱ መልካም ወሬ በተናገረ ጊዜ ሳኦል “እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ?” በማለት በትሕትና መልሷል።​—⁠1 ሳሙኤል 9:​21

16. ሳኦል ትዕግሥት እንደሌለው ያሳየው እንዴት ነው?

16 ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ሳኦል የነበረው ልክን የማወቅ ባሕርይ እልም ብሎ ጠፋ። ከፍልስጤማውያን ጋር ውጊያ ገጥሞ በነበረበት ጊዜ ሳሙኤል እስኪመጣና መሥዋዕት አቅርቦ አምላክን እስኪለምን ድረስ መጠበቅ ስለነበረበት ወደ ጌልገላ ሄደ። ሳሙኤል በተባለው ሰዓት ሳይመጣ በዘገየ ጊዜ ሳኦል በትዕቢት ተነሳስቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ራሱ አቀረበ። መሥዋዕቱን አቅርቦ እንደጨረሰ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም “ያደረግኸው ምንድር ነው?” በማለት ጠየቀው። ሳኦልም “ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፣ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ . . . አየሁ፤ . . . ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ።”​—⁠1 ሳሙኤል 13:​8-12

17. (ሀ) እንዲሁ ከላይ ሲታይ ሳኦል የፈጸመው ድርጊት ትክክል ሊመስል የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ትዕግሥት የማጣት እርምጃ የወሰደውን ሳኦልን ያወገዘው ለምንድን ነው?

17 እንዲሁ ከላይ ሲታይ ሳኦል ያደረገው ነገር ትክክል ሊመስል ይችላል። ደግሞም የአምላክ ሕዝቦች በነበሩበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የተነሳ “ተጨንቀው” ይንቀጠቀጡ ነበር። (1 ሳሙኤል 13:​6, 7) እርግጥ ነው፣ ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ በራስ ተነሳሽነት አንድ ነገር ማድረጉ ምንም ስህተት የለበትም። d ሆኖም ይሖዋ ልብን ማንበብና የተነሳሳንበትን ውስጣዊ ግፊት ማወቅ እንደሚችል አትዘንጋ። (1 ሳሙኤል 16:​7) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ባይጠቀስም ሳኦልን በሚመለከት አንድ ያየው ነገር መኖር አለበት። ለምሳሌ ያህል ሳኦል ትዕግሥት ያጣው በውስጡ ባደረበት ትዕቢት እንደሆነ ይሖዋ ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ምናልባት የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ሳኦል ዕድሜው ከመግፋቱ የተነሳ እያዘገመ እንደሚመጣ አድርጎ የተመለከተውን ነቢይ መጠበቁ አበሳጭቶት ሊሆን ይችላል! ያም ሆነ ይህ የሳሙኤል መዘግየት ነገሮችን በራሱ መንገድ ማከናወንና የተሰጠውን ጥብቅ መመሪያም ችላ ብሎ ማለፍ እንደሚያስችለው ሆኖ ተሰምቶት ይሆናል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሳሙኤል ጎሽ አበጀህ አላለውም። ከዚያ ይልቅ “መንግሥትህ አይጸናም . . . እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና” በማለት በቁጣ ተናግሮታል። (1 ሳሙኤል 13:​13, 14) አሁንም ቢሆን ትዕቢት ውርደትን አስከትሏል።

ትዕግሥት ከማጣት ተጠበቁ

18, 19. (ሀ) ትዕግሥት ማጣት በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችን ወደ ትዕቢት ሊመራቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ። (ለ) የክርስቲያን ጉባኤን እንቅስቃሴ በተመለከተ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?

18 ሳኦል በትዕቢት ተነሳስቶ ስለፈጸመው ነገር የሚናገረው ታሪክ ለእኛ ጥቅም ሲባል በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቧል። (1 ቆሮንቶስ 10:​11) በወንድሞቻችን አለፍጽምና በቀላሉ ልንበሳጭ እንችላለን። ማንኛውንም ነገር እኔው ራሴ ካልሠራሁት በስተቀር በትክክል አይሠራም ብለን የምናስብ ከሆነ እንደ ሳኦል ትዕግሥት የለሽ ልንሆን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድም አንዳንድ ነገሮችን በማደራጀት ረገድ የላቀ ችሎታ አለው እንበል። ሰዓት አክባሪ፣ ከጉባኤ የአሠራር ሥርዓቶች ጋር እኩል የሚራመድና የመናገርና የማስተማር ተሰጥዖ ያለው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ወንድም ሌሎች የእርሱን ጥብቅ የአቋም ደረጃዎች እንደማያሟሉና እርሱ የሚፈልገውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆኑ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። ታዲያ ይህ ትዕግሥት የለሽ እንዲሆን ሰበብ ሊሆነው ይችላልን? ምናልባትም እርሱ ባይኖር ኖሮ ምንም ነገር ሊሠራ እንደማይችልና ጭራሹኑ ጉባኤው ሊዳከም እንደሚችል በተዘዋዋሪ መንገድ በመናገር ወንድሞቹን መንቀፍ ይኖርበታልን? እንዲህ ቢያደርግ ትዕቢት ይሆንበታል!

19 ለመሆኑ የክርስቲያን ጉባኤን አንድ አድርጎ የሚያቆመው ምንድን ነው? የአስተዳደር ብቃት? ቅልጥፍና? የጠለቀ እውቀት? እርግጥ ነው፣ ጉባኤው ያለ ችግር መንቀሳቀስ ይችል ዘንድ እነዚህ ነገሮች የሚያበረክቱት የራሳቸው የሆነ ድርሻ እንዳላቸው እሙን ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:​40፤ ፊልጵስዩስ 3:​16፤ 2 ጴጥሮስ 3:​18) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተከታዮቹ በዋነኝነት ተለይተው የሚታወቁት በመካከላቸው ባለው ፍቅር እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:​35) ከዚህም የተነሳ አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ሥርዓታማ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ቢያውቁም ጉባኤው ምንም የማያፈናፍን አመራር የሚያስፈልገው የንግድ ተቋም እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ከዚያ ይልቅ ጉባኤው በርኅራኄ መያዝ የሚፈልግ መንጋ ያለበት እንደሆነ ያውቃሉ። (ኢሳይያስ 32:​1, 2፤ 40:​11) በትዕቢት እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ማለት ብዙውን ጊዜ ወደ ብጥብጥ ይመራል። በተቃራኒው ደግሞ አምላካዊ ሥርዓትን መከተል ሰላምን ያሰፍናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 14:​33፤ ገላትያ 6:​16

20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን ነገሮች ይብራራሉ?

20 ስለ ቆሬ፣ አቤሴሎም እና ሳኦል የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በምሳሌ 11:​2 ላይ እንደሰፈረው ትዕቢት ለውርደት እንደሚዳርግ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ ያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ “በትሑታን [“ልካቸውን በሚያውቁ፣” NW ] ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” በማለት ጨምሮ ይናገራል። ልክን ማወቅ ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለዚህ ባሕርይ ተጨማሪ ብርሃን የሚፈነጥቁ ምን ምሳሌዎች ይገኛሉ? እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ልክን የማወቅ ባሕርይ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ጥናት ላይ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ሮቤል የያዕቆብ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ የእርሱ ዘሮች ከቆሬ ጋር አብረው ያመፁት ሌዋዊው ሙሴ በእነርሱ ላይ ያለውን የማስተዳደር ሥልጣን ለመቀበል ፈቃደኞች ስላልነበሩ ሊሆን ይችላል።

b የዳዊት ሁለተኛ ልጅ የነበረው ዶሎሕያ ከተወለደ በኋላ ዳግመኛ በስም አልተጠቀሰም። ምናልባት አቤሴሎም ከማመፁ በፊት ሞቶ ሊሆን ይችላል።

c በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው አስከሬኑ የቀብር ሥርዓት ማግኘቱ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነበር። በዚህም የተነሳ አንድ ሰው የቀብር ሥርዓት ሳይደረግለት መቅረቱ እንደ ትልቅ ውርደት የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ የአምላክን ሞገስ ማጣቱን ያመለክት ነበር።​—⁠ኤርምያስ 25:​32, 33

d ለምሳሌ ያህል ፊንሐስ በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው መቅሰፍት እንዲገታ ለማድረግ ፈጣን እርምጃ ወስዷል። እንዲሁም ዳዊት ከእርሱ ጋር ያሉ እርቧቸው የነበሩ ሰዎች ‘በእግዚአብሔር ቤት’ የሚገኘውን የተቀደሰ እንጀራ አብረውት እንዲበሉ ጋብዟቸዋል። አምላክ የሁለቱንም ድርጊት እንደ ትዕቢት ቆጥሮ አላወገዘውም።​—⁠ማቴዎስ 12:​2-4፤ ዘኁልቁ 25:​7-9፤ 1 ሳሙኤል 21:​1-6

ታስታውሳለህን?

• ትዕቢት ምንድን ነው?

• ቅናት ቆሬ የትዕቢት እርምጃ እንዲወስድ ያደረገው እንዴት ነው?

• የሥልጣን ጥም ከነበረው ከአቤሴሎም ታሪክ ምን እንማራለን?

• ሳኦል ካንጸባረቀው ትዕግሥት የማጣት መንፈስ ልንርቅ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳኦል ትዕግሥት በማጣት የትዕቢት እርምጃ ወስዷል