በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

ተስፋ ያደረግነው ነገር ሲፈጸምና ምኞታችን ሲሞላ እርካታ እናገኛለን። ይሁን እንጂ ያለምናቸውና የጠበቅናቸው ነገሮች ሁሉ እኛ በተመኘነው መንገድ እውን ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ እሙን ነው። ይሆናል ብለን የጠበቅነው ነገር ሳይሳካልን ሲቀር በራሳችን ሌላው ቀርቶ በሌሎች ላይ በጣም ልንበሳጭ እንችላለን። ጠቢቡ “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ሲል መናገሩ ትክክል ነው።​—⁠ምሳሌ 13:​12

እንድንበሳጭ ሊያደርጉን ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድስ ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህም በላይ ይህን ማድረጋችንስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ተስፋ እና ብስጭት

በዛሬው ጊዜ ካለው የሕይወት ሩጫ እኩል ለመጓዝ ምንም ያህል ብንጥር ወደኋላ እንደቀረን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ጊዜያችንንና ጉልበታችንን የሚሹ ብዙ ጉዳዮች የሚያጋጥሙን ሲሆን ለመሥራት ያቀድነውን ነገር ማከናወን ሳንችል በመቅረታችን ራሳችንን ልንኮንን እንችላለን። ሌላው ቀርቶ ሌሎች ቅር እንደተሰኙብን ሊሰማን ይችላል። ሚስትም እናትም እንደመሆኗ መጠን ልጆች ማሳደግ ተፈታታኝ መሆኑን አሳምራ የምታውቀው ሲንቲያ “ለልጆቼ የምሰጠው እርማት ወጥ አለመሆኑ በቂ ሥልጠና ልሰጣቸው እንዳልቻልኩ ስለሚሰማኝ እበሳጫለሁ” በማለት ተናግራለች። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ስቴፋኒ ትምህርቷን አስመልክታ እንዲህ ብላለች:- “ማድረግ የምፈልገውን ሁሉ ለማከናወን በቂ ጊዜ የለኝም። ይህ ደግሞ ዕረፍት ይነሳኛል።”

የምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ያልሆነና የተጋነነ ከሆነ በቀላሉ ፍጽምናን ወደ መጠበቅ ሊያደርሰንና የበለጠ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። ቤን የተባለ ወጣት ባለትዳር እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “ስለማደርጋቸው፣ ስለማስባቸው ወይም ስለሚሰሙኝ ነገሮች ቁጭ ብዬ ሳስብ ምን ባደርግ የተሻለ ይሆን እንደነበር በግልጽ ይታየኛል። ምንጊዜም ፍጹም መሆን እንዳለብኝ ይሰማኛል። ይህ ደግሞ ትዕግሥት እንዳጣ፣ ተስፋ እንድቆርጥና ብስጩ እንድሆን አድርጎኛል።” ክርስቲያን ሚስት የሆነችው ጌል እንዲህ ትላለች:- “ከራሱ ፍጽምናን የሚጠብቅ ሰው ምንም ስህተት መሥራት የለብኝም ብሎ ያስባል። ፍጽምናን የምንጠብቅ ሴቶች የማትሳሳት እናትና የማትሳሳት ሚስት መሆን እንፈልጋለን። ደስተኛ ለመሆን ውጤታማ መሆን አለብን፤ ጥረታችን መና ሲቀር የምንበሳጨው ለዚህ ነው።”

አንድ ሰው እንዲበሳጭ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ጤና ማጣትና እርጅና ነው። እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻልና ጉልበት ማጣት የአቅም ገደብ እንዳለብን ስለሚጠቁመን እንድንበሳጭ ያደርገናል። ኤሊዛቤት “ከመታመሜ በፊት በቀላሉ አከናውናቸው የነበሩትን ሥራዎች አሁን መሥራት ሲያቅተኝ እበሳጫለሁ።” ስትል ገልጻለች።

እንድንበሳጭ ሊያደርጉን ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን አይተናል። ይህ ስሜት እንዲሁ ከቀጠለ ሌሎች ስለ እኔ ምንም ደንታ የላቸውም ብሎ እስከማመን ሊያደርሰን ይችላል። ስለዚህ ብስጭትን ለማሸነፍና ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ለመሆን ምን አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን?

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ምክንያታዊ እንደሆነና ችግራችንን እንደሚረዳልን አስታውስ። መዝሙር 103:​14 ‘ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ እኛ አፈር እንደሆንን ያስባል’ ሲል ይነግረናል። ይሖዋ አቅምና ችሎታችንን ስለሚያውቅ ከእኛ የሚጠብቀው ማድረግ የምንችለውን ብቻ ነው። ከእኛ የሚፈልገው አንደኛው ነገር ‘ከአምላካችን ጋር ልካችንን አውቀን እንድንሄድ’ ነው።​—⁠ሚክያስ 6:​8

ይሖዋ በጸሎት አማካኝነት ወደ እርሱ እንድንቀርብም ያበረታታናል። (ሮሜ 12:​12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​17) ሆኖም ጸሎት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ጸሎት አስተሳሰባችንና ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። ልባዊ ጸሎት እርዳታ እንደሚያስፈልገን የምናሳይበት መንገድ ሲሆን ልክን የማወቅና የትሕትናም ምልክት ነው። ይሖዋ ፍቅርን፣ ቸርነትን፣ ጥሩነትን እንዲሁም ራስ መግዛትን እንድናፈራ የሚያስችለንን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጸሎታችንን ለመመለስ ዝግጁ ነው። (ሉቃስ 11:​13፤ ገላትያ 5:​22, 23) ጸሎት ከጭንቀትና ከብስጭት እፎይ እንድንልም ያደርጋል። ኤሊዛቤት በጸሎት አማካኝነት “ከሌላ ከየትም የማታገኙትን መጽናኛ ታገኛላችሁ” ብላለች። ኬቨን “አንድን ችግር መወጣት እችል ዘንድ የተረጋጋ ልብና ብሩህ አእምሮ እንዲሰጠኝ እጸልያለሁ። ይሖዋ ፈጽሞ አይጥለኝም” ሲል ተናግሯል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጸሎት ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ያውቃል። “በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” የሚል ምክር የሰጠው በዚህ ምክንያት ነው። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) አዎን፣ ከይሖዋ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊነትን እንድናዳብር ይረዳናል።

ይሁን እንጂ በዚያው በተበሳጨንበት ወቅት ማጽናኛ ማግኘት የሚያስፈልገን ጊዜ ሊኖር ይችላል። በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል ጥቅም አለው። ለምናምነው የጎለመሰ ጓደኛችን የሚሰማንን ብናጫውተው ስላበሳጨን ወይም ስላስጨነቀን ጉዳይ ተገቢ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል። (ምሳሌ 15:​23፤ 17:​17፤ 27:​9) ከተስፋ መቁረጥ ጋር ትግል የገጠሙ ወጣቶች የወላጅ ምክር ለመጠየቅ መጣራቸው ሚዛናቸውን ለመጠበቅ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። ካንዲ “ከወላጆቼ ያገኘሁት ፍቅራዊ መመሪያ ይበልጥ ምክንያታዊና ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረኝ እንዲሁም በሌሎች እንድቀረብ አድርጎኛል” ስትል አድናቆቷን ገልጻለች። አዎን፣ “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና” የሚለው የ⁠ምሳሌ 1:​8, 9 ማሳሰቢያ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ወቅታዊ ነው።

ፍጽምናን የመጠበቅ ባሕርይ የሚያስከትለው መዘዝ “ሕይወት ከእኔ ፍላጎት ጋር ካልተጣጣመ ብሎ ድርቅ ማለት ትርፉ ብስጭት ነው” በሚለው ምሳሌያዊ አባባል ጠቅለል ተደርጎ ተገልጿል። ከዚህ ለመራቅ የአመለካከት ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ትሕትና እና ልክን ማወቅ በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊና ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ያስችለናል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በ⁠ሮሜ 12:​3 ላይ ‘ማሰብ ከሚገባን በላይ አልፈን በትዕቢት አናስብ’ የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ፊልጵስዩስ 2:​3 ትሕትና እንዲኖረንና ሌሎች ከእኛ ይሻላሉ ብለን እንድናስብ ያበረታታናል።

ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ኤሊዛቤት በሕመሟ ምክንያት ነጭናጫ ሆና ነበር። ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት ለመገንዘብና የምናቀርብለትን አገልግሎት እንደማይረሳ በማወቅ ለመጽናናት ጊዜ ወስዶባታል። ኮለን በያዘው የሚያልፈሰፍስ በሽታ ምክንያት እንደልብ መንቀሳቀስ አይችልም። በመጀመሪያ፣ አሁን የሚያቀርበው አገልግሎት ጥሩ ጤንነት በነበረው ጊዜ ከሚያቀርበው አገልግሎት ጋር ሲነጻጸር ምንም ዋጋ እንደሌለው ይሰማው ነበር። ሁለተኛ 2 ቆሮንቶስ 8:​12ን በመሳሰሉ ጥቅሶች ላይ በማሰላሰል ይህን ስሜት ማስወገድ ቻለ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በጎ ፈቃድ ቢኖር፣ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም።” ኮለን እንዲህ ይላል:- “መስጠት የምችለው እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም እንኳ አሁንም መስጠት እችላለሁ። ይህ ደግሞ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” በ⁠ዕብራውያን 6:​10 ላይ “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።

ታዲያ ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን አለመሆናችንን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ:- ‘እኔ ከራሴ የምጠብቀው ነገር አምላክ ከሚጠብቅብኝ ነገር ጋር ይስማማልን?’ ገላትያ 6:​4 እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል።” ኢየሱስም “ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” እንዳለ አትዘንጋ። አዎን፣ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የተሸከምነው ቀንበር አለ። ይሁን እንጂ ቀንበሩ “ልዝብ” እና “ቀሊል” ነው። ደግሞም ኢየሱስ ይህን ቀንበር በተገቢው መንገድ ከተሸከምነው እረፍት እንደሚያመጣልን ቃል ገብቶልናል።​—⁠ማቴዎስ 11:​28-30

በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ይክሳል

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ለመሆን ስንጣጣር የአምላክ ቃል የሚለውን የምንሰማና ምክሩን ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ አሁን ከምናገኘው በረከት በተጨማሪ ዘላቂ ጥቅም ያስገኝልናል። ለምሳሌ ያህል ለአካላዊ ጤንነታችን ጥቅም አለው። ይሖዋ ከሚሰጠው ማሳሰቢያ ጥቅም ያገኘችው ጄኒፈር “ለሕይወት ያለኝ አድናቆትና ጉጉት ከፍተኛ ሆኗል” በማለት ገልጻለች። ይሖዋ የሚሰጠው ማሳሰቢያ ‘ለሚያገኙት ሕይወት፣ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ’ ስለሆነ ምሳሌ 4:​21, 22 ከዓይናችንና ከልባችን እንዳናርቀው ማበረታታቱ ተገቢ ነው።

ሌላው ሽልማት አእምሯዊና ስሜታዊ ደህንነት ማግኘት ነው። ቴሬሳ “አእምሮዬና ልቤ በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩር ሳደርግ በጣም ደስተኛ እሆናለሁ” ብላለች። እርግጥ ነው፣ አሁንም ቢሆን በሕይወታችን ውስጥ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ያጋጥሙናል። ሆኖም በቀላሉ ልንወጣቸው እንችላለን። ያዕቆብ 4:​8 “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” ሲል ያሳስባል። ይሖዋ የሕይወትን ውጣ ውረድ እንድናሸንፍ በማጠንከርና ሰላም በመስጠት እንደሚባርከን ቃል ገብቶልናል።​—⁠መዝሙር 29:​11

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ከሆንን መንፈሳዊ መረጋጋትም እናገኛለን። ይህም ቢሆን በረከት ነው። በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ብሩህ አመለካከት መያዝ እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 1:​10) የምናወጣቸው ግቦች ያልተጋነኑና የሚደረስባቸው ከሆኑ ታላቅ ደስታና እርካታ እናገኛለን። ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውነው ለጥቅማችን እንደሆነ ካወቅን ራሳችንን ለእርሱ በአደራ ለመስጠት ፈቃደኞች እንሆናለን። ጴጥሮስ “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” ሲል ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 5:​6) የይሖዋን አክብሮት ከማግኘት የበለጠ ምን ሽልማት ሊኖር ይችላል?

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ብስጭትንና ተስፋ መቁረጥን እንድናሸንፍ ሊረዳን ይችላል