በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጦር መሣሪያ ግንባታ ወደ ሕይወት አድን ተግባር

ከጦር መሣሪያ ግንባታ ወደ ሕይወት አድን ተግባር

የሕይወት ታሪክ

ከጦር መሣሪያ ግንባታ ወደ ሕይወት አድን ተግባር

ኢሲዶረስ ኢስማይሊዲስ እንደተናገረው

በጉልበቴ እንደተንበረከክሁ እንባዬ በጉንጮቼ ላይ ኮለል እያለ ይወርድ ነበር። “አቤቱ አምላኬ፣ በጦር መሣሪያ ግንባታ ተቋም ውስጥ መሥራቴን ማቆም እንዳለብኝ ሕሊናዬ ይነግረኛል። ሌላ ሥራ ለማግኘት ተጣጥሬያለሁ፤ ሆኖም አልቻልኩም። ነገ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገባለሁ። እባክህ ይሖዋ፣ አራቱ ልጆቻችን የሚበሉት አጥተው እንዲራቡ አትፍቀድ” የሚል ጸሎት አቀረብኩ። ለመሆኑ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት እንዴት ነው?

በ1932 በተወለድኩባት በሰሜን ግሪክ በምትገኘው በድራማ ውስጥ ሕይወት የተረጋጋና ቀላል ነበር። አባቴ ወደፊት ምን ባደርግ ደስ እንደሚለው በየጊዜው ይነግረኝ ነበር። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄጄ እንድማር አበረታቶኛል። ግሪክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከተበዘበዘች በኋላ የአብዛኞቹ ግሪካውያን መፈክር “ንብረታችንን መዝረፍ ትችላላችሁ፤ በአእምሯችን ውስጥ ያለውን ግን ፈጽሞ መስረቅ አትችሉም” የሚል ነበር። ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል ማንም ሊሰርቀው የማይችለውን ነገር ለማግኘት ቆርጬ ተነሳሁ።

ከልጅነቴ ጀምሮ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ በምትሰጣቸው የተለያዩ የወጣት ቡድኖች ውስጥ አባል ሆኛለሁ። እዚያም ከአደገኛ ኑፋቄዎች እንድንርቅ ይነገረን ነበር። በተለይ ጸረ ክርስቶስ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ስለነበረውና የይሖዋ ምሥክሮች ተብሎ ስለሚጠራው አንድ ቡድን ሲጠቀስልን አስታውሳለሁ።

በ1953 አቴንስ ከሚገኝ አንድ የሞያ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ በኋላ ሥራ ለመፈለግና በዚያው ትምህርቴን ለመከታተል በማሰብ ወደ ጀርመን ሄድኩ። ሆኖም አልተሳካልኝም፤ ስለዚህ ወደ ሌሎች አገሮች አቀናሁ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በቤልጅየም ወደብ ላይ ሳለሁ ገንዘቤ በሙሉ ማለቁን ተረዳሁ። ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ፣ ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩት አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። አምላክ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንድሄድ ከረዳኝ ቁሳዊ ሃብት እንደማላሳድድ፣ ነገር ግን ትምህርቴን ከተከታተልኩ በኋላ ጥሩ ክርስቲያንና ጥሩ ዜጋ ለመሆን እንደምጣጣር በመግለጽ ጸሎት አቀረብኩ። በመጨረሻ በ1957 ዩናይትድ ስቴትስ ገባሁ።

አዲስ ሕይወት በዩናይትድ ስቴትስ

ቋንቋውን ለማይችልና ቤሳ ቤስቲን ለሌለው አንድ ስደተኛ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መኖር እጅግ ፈታኝ ነበር። ሌሊት ሌሊት ሁለት ሥራዎችን እየሠራሁ ቀን ቀን ትምህርቴን ለመከታተል እጣጣር ነበር። በተለያዩ ኮሌጆች ትምህርቴን ከተከታተልኩ በኋላ ዲፕሎማዬን አገኘሁ። ከዚያም ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በፊዚክስ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዬን አገኘሁ። አባቴ ትምህርት እንድከታተል የሰጠኝ ምክር በእነዚህ አስቸጋሪ ዓመታት ውስጥ ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድቶኛል።

በዚህ ጊዜ ገደማ ኢካተሪኒ ከምትባል አንዲት ቆንጆ ግሪካዊት ጋር ተዋወቅኩና በ1964 ተጋባን። የመጀመሪያው ልጃችን ከሦስት ዓመት በኋላ የተወለደ ሲሆን አራት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሌሎች ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ወለድን። በእውነቱ ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ ቤተሰብ ማስተዳደር እጅግ ፈታኝ ነበር።

ካሊፎርኒያ ሱኒቫሌ በሚገኘው የሚሳኤልና የጠፈር ምርምር ተቋም ውስጥ ለዩ ኤስ አየር ኃይል እሠራ ነበር። አጄና እና አፖሎ የሚባሉ ፕሮግራሞችን ጨምሮ በተለያዩ የአየርና የጠፈር ፕሮጀክቶች ውስጥ ተካፍያለሁ። እንዲያውም ለአፖሎ 8 እና አፖሎ 11 ተልዕኮ መሳካት ላበረከትኩት አስተዋጽዖ ኒሻኖች ተሸልሜያለሁ። ከዚያ በኋላ ትምህርቴን ቀጠልኩና በተለያዩ ወታደራዊ የጠፈር ፕሮጀክቶች ውስጥ ያለኝን ተሳትፎ ከፍ አደረግሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ምን እፈልጋለሁ፤ ተወዳጅ ሚስት፣ አራት ጥሩ ልጆች፣ ጥሩ ሥራ እንዲሁም ጥሩ ቤት አለኝ ብዬ አሰብኩ።

መንፈሰ ጠንካራ ሰው

በ1967 መጀመሪያ ላይ በመሥሪያ ቤቴ ከሚሠራ ጂም የተባለ በጣም ትሁትና ደግ ሰው ጋር ተዋወቅኩ። ጂም ፈገግታ ከፊቱ የማይለየው ሲሆን ለሻይ እረፍት አብረን እንድንሆን የማቀርብለትን ግብዣ እምቢ ብሎ አያውቅም። አጋጣሚውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘውን እውቀት ለእኔም ለማካፈል ይጠቀምበታል። ጂም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማጥናት ላይ እንደሚገኝ ነገረኝ።

ከዚህ ሃይማኖታዊ ቡድን ጋር እንደሚተባበር ስሰማ በጣም ደነገጥኩ። ይህን የመሰለ ጥሩ ሰው ጸረ ክርስቶስ በሆነ ኑፋቄ እንዴት ሊታለል ይችላል? ይሁን እንጂ ጂም ለእኔ ያለውን ጥሩ ግምትና ደግነቱን ማጣት አልፈለግሁም። በየዕለቱ አዲስ ጽሑፍ እንዳነብ ይሰጠኛል። ለምሳሌ ያህል አንድ ቀን ቢሮዬ መጣና “ኢሲዶረስ፣ በዚህ መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘው ይህ ርዕስ የቤተሰብን ኑሮ እንዴት ማጠንከር እንደሚቻል ይናገራል። ወስደህ ከቤተሰብህ ጋር አንብበው” አለኝ። መጽሔቱን እንደማነብ ከነገርኩት በኋላ ትንሽ ቆይቼ ወደ መጸዳጃ ቤት ሄድኩና ብጭቅጭቅ አድርጌ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ጣልኩት።

ጂም የሚሰጠኝን መጽሐፍና መጽሔት ሁሉ ለሦስት ዓመታት ያህል እየቀ​ዳደድኩ እጥል ነበር። ለይሖዋ ምሥክሮች መሠረተ ቢስ ጥላቻ ቢኖረኝም የጂምን ጓደኝነት ማጣት አልፈልግም ነበር። ስለዚህ እሱ የሚለኝን እየሰማሁ ሐሳቡን ቶሎ ከአእምሮዬ ባወጣው እንደሚሻል ተሰማኝ።

ይሁን እንጂ ካደረግናቸው ውይይቶች እኔ የማምንባቸውና የማደ​ርጋቸው አብዛኞቹ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳልተመሠረቱ አስተዋልኩ። ስለ ሥላሴ፣ ስለ ሲኦል እሳታማነትና ስለ ነፍስ አለመሞት የሚገልጹት ትምህርቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ እንደሌላቸው ተገነዘብኩ። (መክብብ 9:​10፤ ሕዝቅኤል 18:​4፤ ዮሐንስ 20:​17) ኩሩ የግሪክ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ስለሆንኩ ጂም ትክክል መሆኑን በግልጽ መቀበል አልፈለግሁም። ሆኖም ሁሌ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚጠቅስና ፈጽሞ ከራሱ ስለማይናገር የኋላ ኋላ ይህ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ መልዕክት እያካፈለኝ እንዳለ ተገነዘብኩ።

ባለቤቴ አንድ ነገር እንዳለ ስለጠረጠረች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ቅርርብ ካለው ጓደኛዬ ጋር ተወያይቼ እንደሆነ ጠየቀችኝ። እንደተወያየሁ ስነግራት “ሌላ የፈለገው ቤተ ክርስቲያን እንሂድ እንጂ መቼም የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አንሄድም” አለችኝ። ሆኖም ብዙም ሳንቆይ እኔና ባለቤቴ ልጆቻችንን ይዘን የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘት ጀመርን።

ከባድ ውሳኔ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ስቀጥል “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም” የሚሉት ነቢዩ ኢሳይያስ የጻፋቸውን ቃላት አነበብኩ። (ኢሳይያስ 2:​4) እንዲህ ስል ራሴን ጠየቅኩ ‘ሰላም ወዳድ የሆነውን አምላክ የሚያገለግል ሰው አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች ንድፍ በማውጣትና በመገንባት ሥራ እንዴት ይሰማራል?” (መዝሙር 46:​9) ሥራ መለወጥ እንዳለብኝ ለመወሰን ጊዜ አልፈጀብኝም።

ይህ ከባድ ፈተና እንደሆነ መረዳት አያስቸግርም። ይህ የማይገኝ ሥራ ነበር። እዚህ ደረጃ ላይ ልደርስ የቻልኩት ለዓመታት ጠንክሬ በመሥራት፣ ተግቼ በመማርና ብዙ መሥዋዕትነት በመክፈል ነው። ለዚህ ትልቅ ቦታ ከበቃሁ በኋላ አሁን ይህን ሥራዬን የመልቀቅ ፈታኝ ሁኔታ ከፊቴ ተደቀነ። ይሁን እንጂ ለይሖዋ ያለኝ ጥልቅ ፍቅርና ፈቃዱን ለማድረግ ያለኝ ከፍተኛ ምኞት አሸነፈ።​—⁠ማቴዎስ 7:​21

ዋሽንግተን ሲያተል በሚገኝ አንድ ኩባንያ ውስጥ ለመቀጠር ወሰንኩ። የሚገርመው ነገር ሥራው ከ⁠ኢሳይያስ 2:​4 ጋር ይበልጥ የሚቃረን እንደሆነ ወዲያው ተገነዘብኩ። ከዚህ ጥቅስ ጋር በማይቃረኑ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ለመሥራት ያደረግሁት ጥረት ስላልተሳካልኝ ሕሊናዬ አሁንም ያስጨንቀኝ ነበር። ይህን ሥራ እየሠራሁ ንጹሕ ሕሊና ማግኘት ዘበት እንደሆነ ግልጽ ሆነልኝ።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​21

ሥር ነቀል ለውጦች የማድረጉ አስፈላጊነት በግልጽ ታየን። ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአኗኗራችን ላይ ለውጥ አደረግን፤ እንዲሁም የቤት ወጪያችንን በግማሽ ቀነስን። ከዚያም የተንደላቀቀ ቤታችንን ሸጠን ኮሎራዶ ዴንቨር ውስጥ አነስተኛ ቤት ገዛን። አሁን የመጨረሻውን እርምጃ ለመውሰድ ይኸውም ሥራዬን ለማቆም ዝግጁ ሆንኩ። ሕሊናዬ የሚለኝን በመግለጽ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ጻፍኩ። በዚያን ዕለት ሌሊት ልጆች ከተኙ በኋላ ከባለቤቴ ጋር ተንበርክከን በመግቢያው ላይ የጠቀስኩትን ጸሎት ወደ ይሖዋ አቀረብን።

ከወር በሚያንስ ጊዜ ውስጥ ወደ ዴንቨር የተዛወርን ሲሆን ከሁለት ሳምንት በኋላ ሐምሌ 1975 እኔና ባለቤቴ ተጠመቅን። ለስድስት ወር ሥራ ማግኘት ስላልቻልኩ ያጠራቀምነው ገንዘብ ቀስ በቀስ ተሟጠጠ። በሰባተኛው ወር ላይ የቀረን ገንዘብ ለቤታችን ዕዳ በወር ከምንከፍለው ገንዘብ ያነሰ ነበር። ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት ማፈላለግ ጀመርኩ፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የምህንድስና ሥራ አገኘሁ። ደሞዙ በፊት ከማገኘው በግማሽ የሚያንስ ቢሆንም ይሖዋን ከጠየኩት ጋር ሲወዳደር ግን እጅግ በጣም ብዙ ነበር። ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠቴ ምንኛ ደስተኛ ነኝ!​—⁠ማቴዎስ 6:​33

ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱ አድርጎ ማሳደግ

በመሃሉ እኔና ኢካተሪኒ አራት ልጆቻችንን በአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ኮትኩቶ በማሳደጉ ፈታኝ ሥራ ተጠምደን ነበር። ደስ የሚለው ሁሉም በይሖዋ እርዳታ በጣም አስፈላጊ ለሆነው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ወስነው ጎልማሳ ክርስቲያኖች ሲሆኑ ለማየት በቅተናል። ክሬስቶስ፣ ላኪስ እና ግሪጎሪ የሚባሉት ወንዶች ልጆቻችን ከአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከተመረቁ በኋላ ጉባኤዎችን ለመጎብኘትና ለማጠንከር የተለያየ ምድብ ተቀብለው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ሴት ልጃችን ቱላ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆና እያገለገለች ነው። ሁሉም ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ለጥሩ ደረጃ የሚያበቃቸውን ሞያና ደህና ደሞዝ የሚያስገኝላቸውን ሥራ መሥዋዕት ሲያደርጉ በማየታችን ልባችን በጥልቅ ተነክቷል።

ብዙ ሰዎች እንዲህ ላለው ስኬታማ የልጅ አስተዳደግ ቁልፉ ምን እንደሆነ ይጠይቃሉ። እርግጥ ነው፣ ልጆችን ስለማሳደግ አንድ ቋሚ ደንብ የለም። ይሁን እንጂ እኛ በበኩላችን በልጆቻችን ልብ ውስጥ ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር ለመቅረጽ ያለመታከት ጥረናል። (ዘዳግም 6:​6, 7፤ ማቴዎስ 22:​37-39) ፍቅራቸውን በተግባር ሳያሳዩ ይሖዋን እንወዳለን ብሎ መናገር ብቻውን ዋጋ እንደሌለው ተምረዋል።

በሳምንት አንድ ቀን በተለይ ቅዳሜ ቅዳሜ በቤተሰብ ደረጃ በመስክ አገልግሎት እንካፈላለን። ዘወትር ሰኞ ማታ ከእራት በኋላ የቤተሰብ ጥናት የምናደርግ ሲሆን እያንዳንዱን ልጅ በነፍስ ወከፍ መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናለን። ልጆቹ ገና ትንንሾች እያሉ በሳምንቱ ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት አጠር አጠር ያሉ ጥናቶችን እንመራ የነበረ ሲሆን በዕድሜ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ግን በሳምንት አንድ ጊዜ ረዥም ጥናት እናደርጋለን። ልጆቻችንን በምናስጠናበት ወቅት የሚሰማቸውን ሁሉ ያለምንም ፍርሃት ያማክሩናል።

በተጨማሪም በቤተሰብ ሆነን ገንቢ በሆነ መዝናኛ እንካፈላለን። የሙዚቃ መሣሪያዎችን በአንድነት የምንጫወት ሲሆን እያንዳንዳቸው የሚወዱትን መዝሙር መጫወት ያስደስታቸዋል። በአንዳንድ ቅዳሜና እሑዶች ላይ የሚያንጽ ጊዜ አብረን ለማሳለፍ ሌሎች ቤተሰቦችን ቤታችን እንጋብዛለን። እንዲሁም በቤተሰብ ሆነን ለዕረፍት ወጣ እንላለን። ለዕረፍት ከተጓዝንባቸው ጊዜያት በአንዱ ላይ የኮሎራዶ ተራራዎችን በመጎብኘትና በአካባቢው ከሚገኝ ጉባኤ ጋር በመስክ አገልግሎት በመካፈል ሁለት ሳምንት አሳልፈናል። ልጆቻችን በአውራጃ ስብሰባዎች የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በመሥራትና በመንግሥት አዳራሽ ግንባታዎች ላይ በመካፈል ያሳለፏቸው ጥሩ ትዝታዎች አሏቸው። እንዲሁም ዘመዶቻችንን ለመጠየቅ ወደ ግሪክ በሄድን ጊዜ በእምነታቸው ምክንያት እስራት ከደረሰባቸው ብዙ ታማኝ ምሥክሮች ጋር ተዋውቀዋል። ይህም በእውነት ለመጽናትና ድፍረት ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።

እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹ ልጆች አልፎ አልፎ መጥፎ ጠባይ ያሳዩበትና የተሳሳተ የጓደኛ ምርጫ ያደረጉበት ጊዜ ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ እኛ ራሳችን ከልክ በላይ ጥብቅ በመሆን በልጆቻችን ላይ ችግር ሳንፈጥር አልቀረንም። ይሁን እንጂ ሁላችንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ‘የይሖዋን ምክርና ተግሣጽ’ የሙጥኝ በማለት መንገዳችንን ለማቅናት ጥረናል።​—⁠ኤፌሶን 6:​4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩበት ጊዜ

ልጆቻችን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከገቡ በኋላ እኔና ኢካተሪኒ ሕይወት አድን በሆነው በዚህ ሥራ ያለንን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ምን ማድረግ እንደምንችል በቁም ነገር አሰብንበት። በዚህ ምክንያት በ1994 ቀደም ብዬ ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ሁለታችንም በዘወትር አቅኚነት ማገልገል ጀመርን። በአካባቢው ባሉ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የምናገለግል ሲሆን እዚያም ለተማሪዎች እየመሠከርን ለአንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንመራላቸዋለን። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እኔም አሁን እነሱ ባሉባቸው ሁኔታዎች ውስጥ በማለፌ ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ያደረኩት ጥረት ስኬት አስገኝቶልኛል። ከቦሊቭያ፣ ከብራዚል፣ ከቺሊ፣ ከቻይና፣ ከግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከሜክሲኮ፣ ከታይላንድና ከቱርክ የመጡ ተማሪዎች ማስጠናት እንዴት ደስ ያሰኛል! በስልክ በሚደረገው ምሥክርነት በተለይ የአፍ መፍቻ ቋንቋዬን ለሚናገሩ ሰዎች በመስበክ ተካፍያለሁ።

ምንም እንኳን በዕድሜ መግፋትና ወደ ግሪክኛ በሚወስደው አነጋገሬ የተነሳ እንደምፈልገው መሆን ባልችልም “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት ኢሳይያስ ያሳየውን መንፈስ በመያዝ ምንጊዜም ራሴን ለማቅረብ ጥረት አደርጋለሁ። (ኢሳይያስ 6:​8) ከስድስት የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ በመርዳታችን ደስተኞች ነን። ይህ በእርግጥም ታላቅ የደስታ ጊዜ ነበር።

በአንድ ወቅት ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎችን በመገንባት ሥራ ላይ ተሰማርቼ ነበር። ይሖዋ እኔና ቤተሰቤ ራሳችንን የወሰንን አገልጋዮቹ እንድንሆንና ሕይወታችንን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት የሚናገረውን ምሥራች ለሰዎች እንድንሰብክ ይገባናል በማንለው ደግነቱ መንገድ ከፍቶልናል። ከባድ ውሳኔዎች ለማድረግ ሳስብ “የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” የሚሉት የ⁠ሚልክያስ 3:​10 ቃላት ትዝ ይሉኛል። በእርግጥም አትረፍርፎ ባርኮናል!

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ላኪስ:- አባቴ ግብዝነትን ይጠላል። በተለይ ለቤተሰቡ ትክክለኛ አርዓያ ለመተው ሲል ግብዝ ላለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ብዙ ጊዜ እንዲህ ይለን ነበር:- “ሕይወታችሁን ለይሖዋ መወሰናችሁ አንድ ነገር ነው። ለይሖዋ መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች መሆን አለባችሁ። ክርስቲያን የመባል ትርጉሙ ይኸው ነው።” የማልረሳቸው እነዚህ ቃላት ለይሖዋ መሥዋዕት በመክፈል ረገድ የእርሱን ምሳሌ እንድኮርጅ አስችለውኛል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ክሬስቶስ:- ወላጆቼ በሙሉ ነፍሳቸው ለይሖዋ ታማኝ ስለሆኑ የወላጅነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት ስላደረጉ ከልብ አደንቃቸዋለሁ። አገልግሎትም ሆነ፣ እረፍት ማንኛውንም ነገር የምናደርገው በአንድነት ነበር። ምንም እንኳን ወላጆቼ ሌሎች ብዙ ሥራዎችን ያከናወኑ ቢሆንም ሕይወታቸው ቀላልና በአገልግሎቱ ላይ ያተኮረ እንዲሆን አድርገዋል። ዛሬ በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከተጠመድኩ ደስተኛ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ግሪጎሪ:- ወላጆቼ አገልግሎቴን እንዳሰፋ በቃል ከሰጡኝ ማበረታቻ ይበልጥ ምሳሌነታቸውና የይሖዋ አገልግሎት ያስገኘላቸው ደስታ እኔም ሁኔታዬን እንድመረምር፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዳልጀምር እንቅፋት የሚሆኑ ሐሳብና ጭንቀቶችን ወደ ጎን እንድተው እንዲሁም ራሴን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ሥራ እንዳስጠምድ አነሳስቶኛል። ራሴን በማቅረብ ደስታ እንዳገኝ ስለረዱኝ ወላጆቼን አመሰግናቸዋለሁ።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ቱላ:- ወላጆቼ ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ከማንኛውም ሃብት ይልቅ በጣም ውድ እንደሆነና እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠታችን እንደሆነ አዘውትረው ያሳስቡኝ ነበር። ይሖዋ እውን እንዲሆንልን አድርገዋል። አባቴ፣ ይሖዋን ለማስደሰት አቅማችን የሚፈቅድልንን ሁሉ እንዳደረግን ተሰምቶንና ንጹሕ ህሊና ይዘን ወደ መኝታችን ከመሄድ ጋር የሚተካከል አንዳች ደስታ እንደሌለ ሁልጊዜ ይነግረን ነበር።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1951 ግሪክ ውስጥ ወታደር በነበርኩበት ወቅት

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1966 ከኢካተሪኒ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1996 ከቤተሰቤ ጋር:- (ከኋላ፣ ከግራ ወደ ቀኝ) ግሪጎሪ፣ ክሬስቶስ፣ ቱላ፤ (ከፊት ለፊት) ላኪስ፣ ኢካተሪኒ እና እኔ