በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሥራ ወደ ፓስፊክ ደሴቶች መጓዝ!

ለሥራ ወደ ፓስፊክ ደሴቶች መጓዝ!

ለሥራ ወደ ፓስፊክ ደሴቶች መጓዝ!

በአውስትራሊያ የብሪስቤንና የሲድኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች የመንገደኞች ማቆያ ክፍሎች ከወትሮው የተለየ ድምቀት ይታይባቸዋል። አርባ ስድስት ሰዎችን የያዘ አንድ ቡድን ወደ ሐሩራማው ሳሞአ በመብረር ከኒውዚላንድ፣ ከሃዋይና ከዩናይትድ ስቴትስ ከሚመጡ 39 ሰዎች ጋር ለመገናኘት መሰናዶውን አጠናቋል። በሻንጣዎቻቸው የያዟቸው ዕቃዎች የሚያስገርሙ ዓይነት ነበሩ። በአብዛኛው መዶሻዎችን፣ መጋዞችንና መሰርሰሪያዎችን የያዙ ሲሆን እነዚህ መሣሪያዎች ውብ ወደ ሆነችው የፓስፊክ ደሴት ለእረፍት የሚሄድ ተጓዥ የሚይዛቸው ነገሮች አይደሉም። በእርግጥም እነዚህ ሰዎች ወደዚያ የሚጓዙት ለእረፍት አልነበረም።

በራሳቸው ወጪ የሚጓዙት እነዚህ ሰዎች አውስትራሊያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ያለው የአካባቢ የሕንፃ ምህንድስና ቢሮ በሚቆጣጠረው የግንባታ ፕሮግራም ያለ ክፍያ በፈቃደኛ ሠራተኝነት ለሁለት ሳምንታት ያገለግላሉ። በፈቃደኝነት በሚለገሱ መዋጮዎች የሚካሄደው ይህ ፕሮግራም በፓስፊክ ደሴቶች ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ ላለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚሆኑ የመንግሥት አዳራሾችን፣ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን፣ የሚስዮናውያን ቤቶችንና የቅርንጫፍ ወይም የትርጉም ሥራ የሚከናወንባቸው ቢሮዎች መሥራትን ያካትታል። በየአገራቸው የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድን አባላት ከነበሩት ከአንዳንዶቹ ሠራተኞች ጋር እስቲ እንተዋወቅ።

ማክስ ይባላል፣ አናጺ ሲሆን የመጣው በአውስትራሊያ ኒው ሳውዝ ዌልስ ከምትገኝ ካውራ ከምትባል ከተማ ነው። ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነው። አርኖልድ ይባላል፣ የመጣው ከሃዋይ ነው። ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ከመሆኑም በተጨማሪ የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው። አርኖልድ ልክ እንደ ማክስ በጉባኤው ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው እነዚህም ሆኑ በፕሮግራሙ ውስጥ የተሳተፉት ሌሎች አባላት በፈቃደኛ ሠራተኛነት የተካፈሉት ጊዜ ስለተረፋቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ እነርሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው መሠራት ያለበት አስፈላጊ ሥራ እንዳለ በመገንዘብ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል መርዳት ስለፈለጉ ነው።

በጣም ጠቃሚ ሥራ የሚያበረክቱ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሠራተኞች

በሙያቸውና በጉልበታቸው እርዳታ እንዲያበረክቱ ከተፈለጉባቸው ቦታዎች አንዱ ቱቫሉ ነበር። ቱቫሉ በምድር ወገብ አቅራቢያ በሳሞአ ሰሜን ምዕራብ ከዘጠኝ ደሴቶች መካከል ራቅ ብላ የምትገኝ ወደ 10, 500 ሕዝብ የሚኖርባት የፓስፊክ አገር ናት። እነዚህ ደሴቶች እያንዳንዳቸው በአማካኝ 2.5 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አላቸው። በዚያ የሚገኙት 61 የይሖዋ ምሥክሮች በ1994 አዲስ የመንግሥት አዳራሽና ሰፋ ያለ የትርጉም ቢሮ በአስቸኳይ ማግኘት አስፈልጓቸው ነበር።

በዚህ ሐሩራማ የፓስፊክ ክፍል የሚገነቡት ሕንፃዎች በየጊዜው የሚነሱ ከባድ ማዕበሎችንና አውሎ ነፋሶችን የሚቋቋሙ መሆን ይገባቸዋል። ሆኖም በደሴቶቹ ላይ ጥራት ያላቸው የግንባታ ቁሳቁስ እንደልብ አይገኙም። ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? የቤት ክዳን ቆርቆሮና የጣሪያ ማዋቀሪያ ብረት፣ እንደ ወንበርና ጠረጴዛ የመሳሰሉ ዕቃዎች፣ መጋረጃዎች፣ የመጸዳጃ ቋቶች እንዲሁም የሻወር አናት ሌላው ቀርቶ ቡሎንና ምስማር ሳይቀር አስፈላጊ የሆነው ዕቃ ሁሉ በመርከብ ከአውስትራሊያ እንዲመጣ ተደርጓል።

ቀደም ብሎ ወደ ስፍራው የተጓዘው አንድ አነስተኛ ቡድን ዕቃው ከመድረሱ በፊት ግንባታው የሚካሄድበትን ቦታ አሰናድቶና መሠረት ጥሎ ይጠብቅ ነበር። ከዚያም ዓለም አቀፍ ሠራተኞች ሕንፃውን ለመገንባት፣ ቀለም ለመቀባትና ዕቃዎቹን አስገብተው ለመገጣጠም መጡ።

በነገራችን ላይ በቱቫሉ የተደረገው ይህ የግንባታ እንቅስቃሴ ያናደደው አንድ የአካባቢው ቄስ የይሖዋ ምሥክሮች “የባቤልን ግንብ” እየገነቡ እንዳሉ በራዲዮ ተናግሯል! ሆኖም ሐቁ ምን ነበር? “በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች ባቤልን ሲገነቡ አምላክ ቋንቋቸውን ስለደባለቀባቸው እርስ በርስ መግባባት ስላልቻሉ የጀመሩትን ግንባታ አቋርጠው መበተን ግድ ሆኖባቸው ነበር። የይሖዋ ሥራ ሲሠራ ግን ሁኔታው ከዚህ ፈጽሞ ተቃራኒ ነው። የቋንቋና የባህል ልዩነቶች ቢኖሩም የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ ይጠናቀቃሉ” ሲል ግሬሚ የሚባል ፈቃደኛ ሠራተኛ አስተያየት ሰጥቷል። (ዘፍጥረት 11:​1-9) በቱቫሉ የተጀመረው ፕሮጀክትም ልክ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጠናቋል። እንዲያውም ሕንፃው ለአምላክ አገልግሎት በሚወሰንበት ሥነ ሥርዓት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ባለቤት ጨምሮ 163 ሰዎች ተገኝተዋል።

ዳግ የሚባለው የፕሮጀክቱ ሱፐርቫይዘር ያሳለፉትን ጊዜ መለስ ብሎ በማስታወስ እንዲህ ብሏል:- “ከተለያየ አገር ከመጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጋር መሥራት በጣም አስደሳች ነበር። ሥራዎችን የምናከናውንበት መንገድ፣ የምንጠቀምባቸው የስያሜ ቃላት ሌላው ቀርቶ የመለኪያ ዘዴዎቻችን የተለያዩ ናቸው። ሆኖም ከእነዚህ የትኛውም ቢሆን ችግር አልፈጠረብንም።” ከዚያ በፊት በሌሎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ ተካፍሎ ስለነበር አክሎ እንዲህ አለ:- “አንድ ቦታ ምንም ያህል ገለልተኛና አስቸጋሪ ቢሆን በይሖዋ እርዳታ ሕዝቦቹ በዚህች ምድር ላይ የትም ይሁን የት ያቀዱትን መሥራት ይችላሉ የሚል ትምክህት አሳድሮብኛል። በጣም ጥሩ ችሎታ ያላቸው ብዙ ወንድሞች እንዳሉን አይካድም፤ ሆኖም ለስኬቱ በዋነኝነት አስተዋጽዖ የሚያደርገው የይሖዋ መንፈስ ነው።”

በተጨማሪም የአምላክ መንፈስ የደሴቶቹ ነዋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች ለሠራተኞቹ ምግብ በማቅረብና ማረፊያ በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ አነሳስቷቸዋል። እርግጥ ነው፣ ለአንዳንዶች እንዲህ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ይህ መስተንግዶ የተደረገላቸው ወንድሞች ከልብ አድንቀዋል። ከሜልቦርን አውስትራሊያ የመጣው ኬን በፍሬንች ፖሊኔዥያ በተደረገ ተመሳሳይ ፕሮጀክት ተካፍሎ ነበር። “እንደ ባሪያ ለማገልገል የመጣን ቢሆንም የተስተናገድነው ግን እንደ መኳንንት ነበር” በማለት ገልጿል። የአካባቢው ምሥክሮችም ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ሁሉ በግንባታ ሥራው ረድተዋል። በሰሎሞን ደሴቶች እህቶች አርማታ በማቡካት አግዘዋል። አንድ መቶ ወንዶችና ሴቶች ከባድ ዝናብ ወደ ጣለባቸው ተራራዎች በመውጣት ከ40 ቶን በላይ የሚመዝን እንጨት በሸክም አጓጉዘዋል። ልጆችም ጭምር በግንባታ ሥራው በቅንዓት ተሳትፈዋል። ከኒውዚላንድ የመጣ አንድ ሠራተኛ “አንድ ወጣት ወንድም በአንድ ጊዜ ሁለትና ሦስት ከረጢት ሲሚንቶ ሲሸከም ትዝ ይለኛል። ዝናብና ፀሐይ ሳይል ሙሉ ቀን ኮረት ሲዝቅ ይውላል” ሲል ተናግሯል።

የአካባቢው ወንድሞች በሥራው መሳተፋቸው ሌላም ጥቅም አስገኝቷል። በሳሞአ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል:- “የደሴቲቱ ወንድሞች የመንግሥት አዳራሾችን ለመሥራት፣ ከባድ አውሎ ነፋስ ከደረሰ በኋላ የፈራረሰውን ለመጠገንና እንደገና ለመገንባት የሚያስችል ሥልጠና አግኝተዋል። ይህ ሥልጠና ሥራ ማግኘት ፈታኝ በሆነበት ኅብረተሰብ ውስጥ ኑሯቸውን ለመምራት ሳይረዳቸውም አይቀርም።”

የግንባታ ፕሮግራም ግሩም ምሥክርነት ይሰጣል

በሆኒያራ የነበረው ኮለን በሰሎሞን ደሴቶች የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ሲሠራ ተመልክቷል። ባየው ነገር በጣም ስለተደነቀ በዚያ ለሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በፒድጂን እንግሊዝኛ የሚከተለውን መልእክት ጽፏል:- “አንድነት አላቸው፤ ግልፍተኞች አይደሉም፤ እንደ አንድ ቤተሰብ ናቸው።” ብዙም ሳይቆይ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አሩሊጎ ወደሚገኘው መንደሩ ሲመለስ ከቤተሰቡ ጋር የራሳቸውን የመንግሥት አዳራሽ ሠሩ። ከዚያም ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው “የመንግሥት አዳራሻችን አትራኖሱ እንኳ ሳይቀር ተሟልቶለታል፤ ስለዚህ አሁን እዚህ አንዳንድ ስብሰባዎችን ማድረግ እንችላለን?” የሚል ሌላ ደብዳቤ ላኩ። ስብሰባዎችን እንዲያካሂዱ ወዲያው አስፈላጊው ዝግጅት የተደረገላቸው ሲሆን ከ60 የሚበልጡ ሰዎች በዚያ አዘውትረው ይሰበሰባሉ።

አንድ የአውሮፓ ኅብረት አማካሪ በቱቫሉ የሚገኘውን ፕሮጀክት ተመልክቶ ነበር። በዚያ ለሚገኝ አንድ ሠራተኛ አስተያየቱን ሲሰጥ እንዲህ አለ:- “ሁሉም ሰው እንዲህ እንደሚላችሁ እገምታለሁ፤ በእርግጥም ይህ ለእኔ ተአምር ሆኖብኛል!” አንዲት የቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኛ ከሌላ አገር ለመጣች ፈቃደኛ ሠራተኛ “እንዴት ደስተኞች ልትሆኑ ቻላችሁ? እዚህ እኮ ሙቀቱ የሚቻል አይደለም!” የሚል ጥያቄ አቅርባለች። እነዚህ ሰዎች ክርስትና እንዲህ ተግባራዊ በሆነና የራስን ጥቅም መሥዋዕት በሚያደርግ መንገድ ሲገለጽ ተመልክተው አያውቁም።

ምንም የማያስቆጭ መሥዋዕትነት

መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠2 ቆሮንቶስ 9:​6 ላይ “በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል” ይላል። ሠራተኞቹ፣ ቤተሰቦቻቸውና ጉባኤዎቻቸው በፓስፊክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን በመርዳት ረገድ በበረከት መዝራታቸውን ቀጥለዋል። በሲድኒ አቅራቢያ ከሚገኘው ከኪንከምበር የመጣ ሮስ የተባለ ሽማግሌ ወንድም “አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ የሰጠኝ ጉባኤያችን ነው። አብሮኝ የመጣው የባለቤቴ ወንድም ደግሞ 500 የአሜሪካ ዶላር ጨመረልኝ” ሲል ተናግሯል። ሌላው ፈቃደኛ ሠራተኛ የመጓጓዣ ወጪውን የቻለው መኪናውን በመሸጥ ነው። አሁንም ሌላኛው ደግሞ መሬቱን ቆርጦ ሸጧል። ኬቨን 900 የአሜሪካን ዶላር ጎድሎት ስለነበር ሁለት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን 16 እርግቦች ለመሸጥ ወሰነ። አንድ የሚያውቀው ሰው እነዚህን እርግቦች ልክ በ900 የአሜሪካን ዶላር ሊገዛ የሚፈልግ ሰው እንዳለ ጠቆመው!

ዳኒ እና ሼረል “የቀረባችሁ የወር ደሞዛችሁን ጨምሮ የመጓጓዣ ወጪያችሁ ወደ 6, 000 የአሜሪካ ዶላር አይጠጋም?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። “ልክ ነው ይጠጋል! የዚያን እጥፍ ቢሆን እንኳ ምንም አይቆጨንም” የሚል መልስ ሰጥተዋል። ከኔልሰን ኒውዚላንድ የመጣው አለን እንዲህ በማለት አክሎ ተናግሯል:- “ቱቫሉ ለመሄድ ያወጣሁት ወጪ አውሮፓ ሄጄበት ይተርፈኝ ነበር። ሆኖም ወደ አውሮፓ ሄጄ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ያለ በረከት፣ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን ብዙ ጓደኞች ማፍራት ወይም ከራሴ ይልቅ ለሌላ ሰው አንድ ነገር ማድረግ እንዴት እችል ነበር? በፍጹም አልችልም! በደሴቲቱ ላይ ለሚኖሩት ወንድሞች ያደረግሁት ምንም ይሁን ምን እነርሱ በአጸፋው የበለጠ አድርገውልኛል።”

ፕሮግራሙ እንዲሳካ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ የቤተሰብ ድጋፍ ነው። አንዳንድ ሚስቶች ከባሎቻቸው ጋር ሄደው እርዳታ ያበረከቱ ሲሆን ሌሎቹ ግን ተማሪ ልጆች ስላሏቸው ወይም የሚከታተሉት የቤተሰብ ጉዳይ ስለነበረባቸው አብረው መጓዝ አልቻሉም። ክሌይ “ባለቤቴ እኔ በሌለሁበት ልጆቹንና የቤቱን ጉዳይ ለመከታተል ፈቃደኛ በመሆን ከእኔ የሚበልጥ መሥዋዕትነት ከፍላለች” ብሏል። እርግጥ ነው፣ ሚስቶቻቸውን ይዘው መምጣት ያልቻሉ ባሎች ሁሉ ይህን አባባል ይጋራሉ!

በቱቫሉ የሚገኘው ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ ፈቃደኛ ሠራተኞች በፊጂ፣ በቶንጋ፣ በፓፕዋ ኒው ጊኒ፣ በኒው ካሊዶንያ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የመንግሥት አዳራሾች፣ የትልቅ ስብሰባ አዳራሾችን፣ የሚስዮናውያን ቤቶችን እንዲሁም የትርጉም ሥራ የሚከናወንባቸው ቢሮዎችን ሠርተዋል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ፕሮጀክቶችም በእቅድ ተይዘዋል። ታዲያ በቂ ሠራተኞች ይገኙ ይሆን?

የሠራተኞች እጥረት ይኖራል የሚል ስጋት የለም። በሃዋይ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ “በዓለም አቀፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሠራተኞች በሙሉ ሌላ ፕሮጀክት በሚጀመርበት ጊዜ እንድንጠራቸው ጠይቀዋል። ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ገንዘብ ማጠራቀም ጀምረዋል” ሲል ጽፏል። እንደዚህ ባለው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ላይ የይሖዋ በረከት ሲታከልበት የታቀደው ሳይሳካ እንዴት ይቀራል?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለፕሮጀክቱ የሚሆን ቁሳቁስ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሠራተኞች በግንባታው ቦታ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግንባታው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የአምላክ መንፈስ ባከናወነው ሥራ ተደሰትን