በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አለመግባባቶችን የምትፈቱት እንዴት ነው?

አለመግባባቶችን የምትፈቱት እንዴት ነው?

አለመግባባቶችን የምትፈቱት እንዴት ነው?

በየቀኑ የተለያየ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር እንገናኛለን። እንዲህ ያለው ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ደስታ የሚያመጣልንና አዳዲስ ከሆኑ አስተሳሰቦች ጋር የሚያስተዋውቀን ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አለመግባባቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን አለመግባባቶች መካከል ጥቂቶቹ ከባድ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በቀላሉ የሚፈቱ ናቸው። በመካከላችን የሚፈጠሩት አለመግባባቶች ምንም ዓይነት ቢሆኑ እነርሱን የምንፈታበት መንገድ በአእምሮአችን፣ በስሜታችንና በመንፈሳዊነታችን ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።

አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት የቻልነውን ያህል መጣራችን ጤናማ የሆነ ሕይወት እንድንመራና ከሌሎች ጋር ይበልጥ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንድ የጥንት ምሳሌ “ትሑት ልብ [“ሰላም ያለው አእምሮ፣” የ1980 ትርጉም ] የሥጋ ሕይወት ነው” ይላል።​—⁠ምሳሌ 14:​30

ከዚህ ፍጹም በተለየ መልኩ “ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፣ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።” (ምሳሌ 25:​28) በሌሎችም ሆነ በራሳችን ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን እንድናደርግ ለሚገፋፉን የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ወረራ መጋለጥ የሚፈልግ ማን አለ? ቁጥጥር ያልተደረገባቸው የቁጣ ቃላት መሰንዘር በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ያስከትላል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለውን ማንኛውንም አለመግባባት በምንፈታበት መንገድ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድርብን የሚችለውን የራሳችንን ዝንባሌ መመርመር እንዳለብን አሳስቧል። (ማቴዎስ 7:​3-5) ሌሎችን ከመንቀፍ ይልቅ የተለያየ አመለካከትና አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኝነት ለመመሥረትና ይህንንም ጠብቀን ለማቆየት ስለምንችልበት መንገድ ልናስብ ይገባል።

አስተሳሰባችን

በግላችሁ አለመግባባት እንደሆነ አድርጋችሁ ያሰባችሁትን ሁኔታም ሆነ የተፈጠረውን እውነተኛ አለመግባባት ለመፍታት የሚያስፈልገው የመጀመሪያው እርምጃ ሁላችንም ለተሳሳቱ አስተሳሰቦችና ዝንባሌዎች የተጋለጥን መሆናችንን አምነን መቀበል ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች ሁላችንም ኃጢአት እንደምንሠራና ‘የእግዚአብሔርም ክብር እንደጎደለን’ ያሳስቡናል። (ሮሜ 3:​23) በተጨማሪም የማስተዋል ችሎታችንን ተጠቅመን ቆም ብለን ስናስብ ለተፈጠረው ችግር መንስኤው ሌላኛው ሰው እንዳልሆነ የምንገነዘብበት ሁኔታም ሊኖር ይችላል። እስቲ ከዚህ ጋር በተያያዘ የዮናስን ተሞክሮ እንመርምር።

ዮናስ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት አምላክ በአጭር ጊዜ ውስጥ በነነዌ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ስለሚያስፈጽመው ፍርድ ለመስበክ ወደ ከተማዋ ተጓዘ። ደስ የሚለው ግን መላው የነነዌ ከተማ ሰዎች ንስሐ በመግባት በእውነተኛው አምላክ አመኑ። (ዮናስ 3:​5-10) ይሖዋ ሰዎቹ ካሳዩት የንስሐ ዝንባሌ አንጻር ምሕረት እንደሚገባቸው ስለተሰማው ከጥፋቱ አተረፋቸው። “ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፣ እርሱም ተቆጣ።” (ዮናስ 4:​1) ዮናስ ለይሖዋ ምሕረት የሰጠው ምላሽ የሚያስገርም ነበር። ዮናስ በይሖዋ ላይ የተቆጣው ለምንድን ነው? ክብሩ እንደተነካ ስለተሰማው ሙሉ በሙሉ በራሱ ስሜቶች የተዋጠ ይመስላል። የይሖዋን ምሕረት አላደነቀም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በሚታይ ነገር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት ዮናስ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክልና የበለጠውን የአምላክ ምሕረት ዋጋ እንዲያስተውል በደግነት ረድቶታል። (ዮናስ 4:​7-11) መስተካከል ያስፈለገው የይሖዋ ሳይሆን የዮናስ አስተሳሰብ እንደነበረ ግልጽ ነው።

እኛስ አንዳንድ ጊዜ ስለ አንድ ጉዳይ ያለንን አስተሳሰብ እንደዚሁ መለወጥ ያስፈልገን ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” በማለት አጥብቆ መክሮናል። (ሮሜ 12:​10) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? በአንድ በኩል ምክንያታዊ በመሆን ለሌሎች ክርስቲያኖች ጥልቅ አክብሮት እንድናሳይና ክብራቸውን እንድንጠብቅላቸው እያበረታታን ሲሆን ይህም እያንዳንዱ ሰው ነጻ ምርጫ የማድረግ መብት እንዳለው አምኖ መቀበልን ይጨምራል። በተጨማሪም ጳውሎስ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና” በማለት አሳስቦናል። (ገላትያ 6:​5) ከዚህ የተነሣ አለመግባባቶች ተፈጥረው ክፍተት ከማበጀታቸው በፊት የራሳችን አስተሳሰብ መስተካከል ያስፈልገው እንደሆነና እንዳልሆነ መመርመራችን እንዴት ጥበብ ነው! የይሖዋን አስተሳሰብ ለማንጸባረቅና ለአምላክ ልባዊ ፍቅር ካላቸው ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል።​—⁠ኢሳይያስ 55:​8, 9

አቀራረባችን

አንድን አሻንጉሊት ለመውሰድ በኃይል እየተጓተቱ ያሉ ሁለት ትንንሽ ልጆች በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ። አንደኛው የያዘውን እስኪለቅ ወይም ደግሞ አንድ ሰው መጥቶ እስኪገላግላቸው ድረስ ልጆቹ በመሃል የቁጣ ቃላት ሊለዋወጡ ይችላሉ።

የዘፍጥረት ታሪክ አብርሃም በእርሱ እረኞችና በወንድሙ ልጅ በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ መፈጠሩን እንደሰማ ይነግረናል። አብርሃም ቅድሚያውን በመውሰድ ሎጥን እንዲህ አለው:- “እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ።” አብርሃም ከሎጥ ጋር የነበረውን ግንኙነት ምንም ነገር እንዲያበላሸው ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። ይህስ ምን ጠይቆበታል? አብርሃም ታላቅ እንደመሆኑ መጠን የነበረውን የመምረጥ መብት መሥዋዕት ለማድረግና ለእርሱ ይገባ የነበረውንም ነገር በፈቃደኝነት ለመተው ዝግጁ ነበር። ሎጥ ለቤተሰቡና ለመንጋው መውሰድ የሚፈልገውን ቦታ ራሱ እንዲመርጥ አድርጓል። የኋላ ኋላ ሎጥ ለምለም የሆነውን የሰዶምና የገሞራ ቦታ በመውሰዱ አብርሃምና ሎጥ በሰላም መለያየት ቻሉ።​—⁠ዘፍጥረት 13:​5-12

ከሌሎች ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ጠብቀን ለማቆየት የሚያስችለንን የአብርሃም ዓይነት መንፈስ ለማሳየት ዝግጁ ነንን? ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አለመግባባቶችን ለመፍታት ስንሞክር ልንኮርጀው የሚገባንን እጅግ በጣም ጥሩ ምሳሌ ይዞልናል። አብርሃም “ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ” በማለት ጠይቋል። የአብርሃም ቅን ፍላጎት ሁለቱም ሰላማዊ መፍትሄ ላይ እንዲደርሱ ነበር። በእርግጥም ሰላማዊ ግንኙነትን ጠብቆ ለማቆየት የቀረበው እንዲህ ያለው ግብዣ ማንኛውንም አለመግባባት ለማስቀረት ይረዳል። አብርሃም “እኛ ወንድማማች ነንና” የሚለውን መግለጫ ተጠቅሞአል። እንዲህ ያለውን ውድ ዝምድና ለምን ብሎ ለግል ምርጫው ወይም ለክብሩ ሲል መሥዋዕት ያደርጋል? አብርሃም በጣም አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረት አድርጎ ነበር። ይህንን ያደረገው ለራሱ አክብሮት እንዳለው በሚያሳይ መንገድ ሲሆን ወዲያውም የወንድሙን ልጅ አክብሮታል።

ለተፈጠሩት አለመግባባቶች መፍትሄ ለማስገኘት የውጭ ሰው ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልግባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ለተነሳው ችግር ሁለት ሰዎች ብቻቸውን ሆነው መፍትሄ ቢያገኙለት እንዴት የተሻለ ነው! ኢየሱስ ካስፈለገም ይቅርታ በመጠየቅ ከወንድማችን ጋር ሰላም ለመፍጠር ቀዳሚዎች እንድንሆን አበረታቶናል። a (ማቴዎስ 5:​23, 24) እንዲህ ማድረጉ ትህትናን ወይም ራስን ዝቅ ማድረግ ቢጠይቅም ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።” (1⁠ጴጥሮስ 5:​5) የአምልኮ አጋሮቻችንን የምንይዝበት መንገድ ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያሳድራል።​—⁠1⁠ዮሐንስ 4:​20

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሰላምን ለመጠበቅ ሲባል መብታችን የሆነውን ነገር እንድንተው ልንጠየቅ እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር ከሆኑት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ወደ አምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ቤተሰብ የመጡት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ነው። ይህ እጅግ አስደስቶናል! የምናሳየው ባሕርይ በእነዚህና በሌሎች የጉባኤው አባላት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር የታወቀ ነው። ይህም ሌሎች ለእኛ ሊኖራቸው የሚችለውን አመለካከት ግምት ውስጥ በማስገባት ስለ መዝናኛ ምርጫችን፣ ስለ ትርፍ ጊዜ ማሳለፊያችን፣ ስለ ማህበራዊ እንቅስቃሴያችን ወይም ተቀጥረን ስለምንሠራው ሥራ በጥንቃቄ እንድናስብ የሚያደርገን በቂ ምክንያት ነው። የምናደርጋቸውን ነገሮች ወይም የምንናገራቸውን ቃላት ሌሎች በደንብ ሳይረዷቸው ቀርተው መሰናከያ ሊሆንባቸው ይችል ይሆን?

ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ” በማለት አሳስቦናል። (1⁠ቆሮንቶስ 10:​23, 24) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችንን ፍቅርና አንድነት ለማጠንከር ከልባችን መጣር አለብን።​—⁠መዝሙር 133:​1፤ ዮሐንስ 13:​34, 35

ፈዋሽ ቃላት

መልካም ቃላት ኃይለኛ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል። “ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው።” (ምሳሌ 16:​24) ጌዴዎን ከኤፍሬም ነገድ ጋር ሊፈጠር ይችል የነበረውን ጦርነት ወደ ሰላም እንደለወጠው የሚናገረው ታሪክ የዚህን ምሳሌ እውነተኛነት ያረጋግጣል።

ከምድያማውያን ጋር በከባድ ሁኔታ በመዋጋት ላይ የነበረው ጌዴዎን የኤፍሬም ነገድ እንዲረዳው ጠየቀ። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ኤፍሬማውያን ወደ ጌዴዎን በመምጣት በፍልሚያው መጀመሪያ ላይ ለምን አልጠራኸንም በማለት አምርረው ተናገሩ። ታሪኩ “ጽኑ ጥልም ተጣሉት” ይላል። ጌዴዎንም እንዲህ ሲል መለሰ:- “እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዝር ወይን መከር አይሻልምን? እግዚአብሔር የምድያምን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል?” (መሳፍንት 8:​1-3) ጌዴዎን በጥሩ ሁኔታ መርጦ በተናገራቸው የሚያረጋጉ ቃላት አማካኝነት ሊቀሰቀስ የነበረውን አሰቃቂ የጎሳ ግጭት አስቀርቷል። ምናልባትም እነዚያ የኤፍሬም ነገድ አባላት ራሳቸውን በጣም ተፈላጊ አድርገው የመመልከት ወይም የኩራት ችግር የነበረባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ጌዴዎንን ሰላማዊ መፍትሄ ለማግኘት ከመጣር ወደ ኋላ እንዲል አላደረገውም። እኛስ እንዲህ ማድረግ እንችላለን?

ሰዎች በውስጣቸው ቁጣ ሊቀሰቀስባቸውና ይህም እኛን በጥላቻ ስሜት እንዲመለከቱን ሊያደርጋቸው ይችላል። እንዲህ በሚሆንበት ወቅት ስሜታቸውን ተገንዘቡላቸው እንዲሁም አመለካከታቸውን ለመረዳት ጣሩ። ምናልባት ሳይታወቀን እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲቀሰቀስባቸው አስተዋጽኦ አድርገን ይሆን? ከሆነ ለምን ስህተታችንን በማመን ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ በማድረጋችን ማዘናችንን አንገልጽላቸውም? በጥንቃቄ የታሰበባቸው ጥቂት ቃላት የተበላሸውን ዝምድና ወደ ቀድሞ ሁኔታው ሊመልሱት ይችላሉ። (ያዕቆብ 3:​4) አንዳንድ የተበሳጩ ሰዎች የሚፈልጉት የእኛን ደግነት የተሞላባቸው የማጽናኛ ቃላት ብቻ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል” ሲል ይገልጻል። (ምሳሌ 26:​20) አዎን፣ በጥንቃቄ ተመርጠው በትክክለኛው መንፈስ የተነገሩ ቃላት ‘ቁጣን ሊመልሱ’ እንዲሁም ፈውስ ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠ምሳሌ 15:​1

ሐዋርያው ጳውሎስ “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ሲል አሳስቧል። (ሮሜ 12:​18) የሌሎችን ስሜት መቆጣጠር እንደማንችል የታወቀ ቢሆንም ሰላምን በመፍጠር ረገድ ግን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። እኛ ራሳችን ለምናሳየውም ሆነ ሌሎች ለሚያሳዩት ፍጹም ያልሆነ ምላሽ ተገዥዎች ከምንሆን ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ላይ ለማዋል አሁኑኑ እርምጃ እንውሰድ። አለመግባባቶችን ይሖዋ ባስተማረን መንገድ ለመፍታት መጣር ዘላለማዊ ሰላምና ደስታ ያስገኛል።​—⁠ኢሳይያስ 48:​17

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በጥቅምት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ከልባችሁ ይቅር በሉ” እንዲሁም “ወንድምህን ገንዘብ ልታደርገው ትችላለህ” በሚል ርዕስ የወጡትን ትምህርቶች ተመልከቱ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነገሮች እኛ በምንፈልገው መንገድ ብቻ ይከናወኑ ብለን ድርቅ እንላለን?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም አለመግባባትን ለማስወገድ ሲባል የራስን ጥቅም በመሠዋት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል