በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ የተደሰተባቸው መሥዋዕቶች

አምላክ የተደሰተባቸው መሥዋዕቶች

አምላክ የተደሰተባቸው መሥዋዕቶች

“ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና።”​—⁠ዕብራውያን 8:​3

1. ሰዎች ወደ አምላክ ዞር ማለት አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

 አልፍሬድ ኤደርሻይም የተባሉ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፊ “መሥዋዕት ማቅረብ ልክ እንደ መጸለይ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ይመስላል፤ መሥዋዕት ግለሰቡ ስለ ራሱ የሚሰማውን ስሜት የሚያመለክት ሲሆን ጸሎት ደግሞ ስለ አምላክ የሚሰማውን ስሜት ያመለክታል” በማለት ጽፈዋል። ኃጢአት ወደ ዓለም ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የጥፋተኝነትን፣ ከአምላክ የመራቅንና የከንቱነትን ስሜት አምጥቷል። ከእነዚህ ስሜቶች መገላገል አስፈላጊ ነው። ሰዎች ተስፋ በሚያስቆርጡ እንዲህ በመሰሉ ስሜቶች በሚዋጡበት ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ወደ አምላክ ዞር ማለት እንዳለባቸው የሚሰማቸው ለምን እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።​—⁠ሮሜ 5:​12

2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጥንት ጊዜ ስለቀረቡ መሥዋዕቶች የሚገልጹ ምን ዘገባዎች እናገኛለን?

2 ለአምላክ መሥዋዕት እንደቀረበ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው ቃየን እና አቤል መሥዋዕት እንዳቀረቡ በሚናገረው ዘገባ ውስጥ ነው። እንዲህ እናነባለን:- “ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትን ከስቡ አቀረበ።” (ዘፍጥረት 4:​3, 4) ከዚያም ኖኅ በዘመኑ የነበረውን ክፉ ትውልድ ጠራርጎ ካጠፋው የጎርፍ መጥለቅለቅ ላዳነው አምላክ ለይሖዋ ‘በመሠውያው ላይ መሥዋዕት አቅርቧል።’ (ዘፍጥረት 8:​20) የአምላክ ታማኝ አገልጋይና ወዳጅ የነበረው አብርሃም አምላክ ቃል በገባቸው ተስፋዎችና በረከቶች በመገፋፋት በተደጋጋሚ ‘መሠውያ ሠርቶ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቷል።’ (ዘፍጥረት 12:​8፤ 13:​3, 4, 18) ከዚያም አብርሃም ልጁን ይስሐቅን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ይሖዋ በነገረው ጊዜ እምነቱ በከፍተኛ ደረጃ ተፈትኖ ነበር። (ዘፍጥረት 22:​1-14) እነዚህ ታሪኮች አጠር ባለ መልክ የቀረቡ ቢሆኑም ቀጥለን እንደምንመለከተው መሥዋዕትን በሚመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ደማቅ ብርሃን ይፈነጥቃሉ።

3. መሥዋዕቶች በአምልኮ ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?

3 ይሖዋ መሥዋዕት ማቅረብን በሚመለከት ግልጽ የሆነ ሕግ ከመስጠቱ ከረዥም ጊዜ በፊት መሥዋዕት ማቅረብ የአምልኮ አንዱ መሠረታዊ ክፍል እንደነበር ከእነዚህና ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በግልጽ ለመረዳት እንችላለን። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ከእዚህ ሐሳብ ጋር በመስማማት “መሥዋዕት” የሚለውን ቃል “ሰው እንደ ቅዱስ አድርጎ ከሚመለከተው አካል ጋር ለመዛመድ፣ ዝምድናውን ጠብቆ ለማቆየት ወይም ለማደስ ሲል ለመለኮታዊ ኃይል አንድ ነገር በማቅረብ የሚከናወን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት” በማለት ይፈታዋል። ይሁን እንጂ ይህ በጥንቃቄ ልንመረምራቸው የሚገቡትን እንደሚከተሉት ያሉ አስፈላጊ ጥያቄዎች ያስነሳል:- በአምልኮ ውስጥ መሥዋዕት ማቅረብ ያስፈለገው ለምንድን ነው? በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሥዋዕቶች የትኞቹ ናቸው? እንዲሁም በጥንት ጊዜ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች በዛሬ ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም አላቸው?

መሥዋዕት ማቅረብ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

4. አዳምና ሔዋን ኃጢአት መሥራታቸው ምን አስከተለባቸው?

4 አዳም ኃጢአት የሠራው ሆን ብሎ ነው። መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ ፍሬ ወስዶ መብላቱ ታስቦበት የተደረገ የዓመፅ ድርጊት ነው። አምላክ “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” በማለት በግልጽ እንዳስቀመጠው ለዚህ ዓይነቱ የዓመፀኝነት ድርጊት የሚከፈለው ቅጣት ሞት ነው። (ዘፍጥረት 2:​17) ውሎ አድሮ አዳምና ሔዋን የኃጢአት ደሞዝ የሆነውን ሞትን አጭደዋል​—⁠ዘፍጥረት 3:​19፤ 5:​3-5

5. ይሖዋ ለአዳም ዝርያዎች ሲል ቀዳሚውን እርምጃ የወሰደው ለምንድን ነው? ምንስ አደረገላቸው?

5 ስለ አዳም ዘሮችስ ምን ሊባል ይቻላል? ኃጢአትንና አለፍጽምናን ከአዳም በመውረሳቸው ምክንያት በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ላይ እንደደረሰው እነርሱም ከአምላክ የራቁ እንዲሁም ለከንቱነትና ለሞት የተዳረጉ ሆኑ። (ሮሜ 5:​14) ይሁን እንጂ ይሖዋ የፍትሕና የኃይል አምላክ ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም በዋነኝነት የሚታወቀው የፍቅር አምላክ እንደሆነ ነው። (1 ዮሐንስ 4:​8, 16) ስለዚህም የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን ራሱ ቅድሚያውን ወስዷል። መጽሐፍ ቅዱስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ካለ በኋላ ቀጥሎ “የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ይናገራል።​—⁠ሮሜ 6:​23

6. በአዳም ኃጢአት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የአምላክ ፈቃድ ምንድን ነው?

6 ከጊዜ በኋላ ይሖዋ አምላክ ለዚህ ስጦታ ዋስትና ለመስጠት ሲል አዳም ሕጉን በመተላለፉ ምክንያት የደረሰውን ጥፋት የሚሸፍን አንድ ነገር አዘጋጀ። ካፋር የሚለው የዕብራይስጥ ቃል መጀመሪያ ላይ “መሸፈን” ምናልባትም “መጥረግ” የሚል ትርጉም የነበረው ይመስላል። “ስርየት” ተብሎም ይተረጎማል። a በሌላ አነጋገር ይሖዋ ለዚህ ስጦታ ብቁ የሆኑ ሰዎች ከኃጢአትና ከሞት ኩነኔ ነፃ መውጣት ይችሉ ዘንድ ከአዳም የተወረሰውን ኃጢአት ለመሸፈንና ያስከተለውንም ጉዳት ለማስወገድ አንድ ጥሩ ዝግጅት አደረገ።​—⁠ሮሜ 8:​21

7. (ሀ) አምላክ በሰይጣን ላይ ባስተላለፈው ፍርድ ውስጥ ምን ተስፋ ይገኛል? (ለ) የሰው ዘር ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንዲወጣ ምን ዓይነት ዋጋ መከፈል አለበት?

7 የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ የመውጣቱ ተስፋ በተዘዋዋሪ መንገድ ተገልጿል። ይሖዋ በእባብ በተመሰለው በሰይጣን ላይ ፍርድ ሲያስተላልፍ እንዲህ ብሏል:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:​15) ይህ ትንቢታዊ ቃል በዚህ የተስፋ ቃል ላይ ለሚያምኑ ሁሉ አንድ የተስፋ ጭላንጭል ፈንጥቋል። ይሁን እንጂ ይህ ነፃነት እንዲገኝ አንድ ዋጋ መከፈል ነበረበት። ተስፋ የተሰጠበት ዘር እንዲሁ መጥቶ ሰይጣንን አያጠፋም፤ ለዘለቄታው ባይሆንም እንኳ ተረከዙ መቀጥቀጥ ማለትም መሞት ነበረበት።

8. (ሀ) ቃየል እንደተጠበቀው ሆኖ ያልተገኘው እንዴት ነው? (ለ) አቤል ያቀረበው መሥዋዕት በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረገው ምንድን ነው?

8 አዳምና ሔዋን ተስፋ የተሰጠበትን ዘር ማንነት ለማወቅ ብዙ ሳያስቡ አልቀረም። ሔዋን የመጀመሪያ ልጅዋን ቃየንን ስትወልድ “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ” በማለት ተናግራለች። (ዘፍጥረት 4:​1) ምናልባት ልጅዋ ተስፋ የተሰጠበት ዘር እንደሚሆን አድርጋ አስባ ይሆን? እሷ እንደዚያ ብላ አሰበችም አላሰበች ቃየንም ሆነ ያቀረበው መሥዋዕት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በሌላ በኩል ግን ወንድሙ አቤል አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንዳለው ከማሳየቱም በላይ ከመንጋው በኩራቱን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። እንዲህ እናነባለን:- “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፣ በዚህም፣ . . . እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት።”​—⁠ዕብራውያን 11:​4

9. (ሀ) አቤል ምን እምነት ነበረው? ይህንን እምነቱን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) አቤል ያቀረበው መሥዋዕት ምን ነገር አከናውኗል?

9 የአቤል እምነት የአምላክን ሕልውና በማመን ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ቃየንም ቢሆን እምነት የነበረው መሆን አለበት። አቤል ታማኝ ለሆኑ የሰው ልጆች መዳን በሚያስገኘው አምላክ ተስፋ በሰጠበት ዘር ላይ እምነት ነበረው። አቤል ይህ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ ባይገለጥለትም እንኳ አንድ ሰው ተረከዙ መቀጥቀጡ እንደማይቀር አምላክ ከገባው ተስፋ ተገንዝቧል። አዎን፣ ደም መፍሰስ እንዳለበት የተገነዘበ ይመስላል። ይህ ደግሞ የመሥዋዕትን ትርጉም በጥቅሉ የሚገልጽ ሐሳብ ነው። አቤል ይሖዋ የገባው ተስፋ ሲፈጸም ለማየት ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት በመነሳት ሳይሆን አይቀርም የሕይወት ምንጭ ለሆነው አካል ሕይወትና ደም መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። ይሖዋ በአቤል መሥዋዕት እንዲደሰት ያደረገው አቤል እምነቱን በዚህ መንገድ መግለጡ ሲሆን ይህም ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ዘሮች በመሥዋዕት አማካኝነት ወደ አምላክ መቅረብና የእርሱን ሞገስ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን በትንሹ አሳይቷል።​—⁠ዘፍጥረት 4:​4፤ ዕብራውያን 11:​1, 6

10. አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ይሖዋ ባቀረበው ጥያቄ የመሥዋዕት ትርጉም ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ ልጁን ይስሐቅን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ አብርሃምን ባዘዘው ጊዜ የመሥዋዕት ጥልቅ ትርጉም አስደናቂ በሆነ መንገድ ግልጽ ሆነ። ምንም እንኳ ያ መሥዋዕት ቃል በቃል ባይቀርብም ይሖዋ ለሰው ዘሮች ያለውን ፈቃድ ለማስፈጸም አንድ ልጁን ከሁሉ የላቀ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ወደፊት ለሚያከናውነው ነገር እንደ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል። (ዮሐንስ 3:​16) ይሖዋ ምርጥ ሕዝቦቹ ለኃጢአታቸው ይቅርታ ለማግኘትና የመዳን ተስፋቸውን የበለጠ ለማጠናከር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለማስተማር በሙሴ ሕግ የሚቀርቡትን መሥዋዕቶችና መባዎች ትንቢታዊ ጥላ አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል። ከእነዚህ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሥዋዕቶች

11. የእስራኤል ሊቀ ካህናት ያቀርባቸው የነበሩት በሁለት የተከፈሉት መባዎች ምንድን ናቸው? ዓላማቸውስ ምን ነበር?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና” በማለት ተናግሯል። (ዕብራውያን 8:​3) ጳውሎስ የጥንቱ እስራኤል ሊቀ ካህናት የሚሠዋቸውን ነገሮች “መባ” እና “መሥዋዕት” ወይም ‘ስለ ኃጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት’ በማለት ለሁለት ከፍሎ እንደተናገረ ልብ በል። (ዕብራውያን 5:​1) በጥቅሉ ሰዎች ፍቅራቸውንና አድናቆታቸውን ለመግለጽም ሆነ ወዳጅነታቸውን ለማዳበር እንዲሁም በሌሎች ዘንድ ሞገስ ወይም ተቀባይነት ለማግኘት ስጦታ ይሰጣሉ። (ዘፍጥረት 32:​20፤ ምሳሌ 18:​16) በተመሳሳይም ሕጉ በሚያዘው መሠረት የሚቀርቡት ብዙዎቹ መሥዋዕቶች በአምላክ ዘንድ ሞገስ ወይም ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል የሚሰጡ ‘መባዎች’ እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። b አንድ ሰው ሕጉን ቢተላለፍ ካሳ እንዲከፈል ይጠበቅበት ነበር፤ ካሳውም “ስለ ኃጢአት” በሚቀርብ “መሥዋዕት” ይከፈል ነበር። ፔንታቱች (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) በተለይ ደግሞ የዘጸአት፣ የዘሌዋውያንና የዘኁልቁ መጻሕፍት መሥዋዕቶችንና መባዎችን በተመለከተ ብዙ ሐሳብ ይሰጣሉ። እነዚህን ሁሉ ዝርዝር ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ መረዳትና ማስታወሱ አስቸጋሪ ሊሆንብን ቢችልም ስለተለያዩ ዓይነት መሥዋዕቶች በሚናገሩ አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦች ላይ ትኩረት ብናደርግ ተገቢ ነው።

12. መሥዋዕቶችን ወይም መባዎችን በተመለከተ ጠቅለል ያለ ግንዛቤ ልናገኝ የምንችለው በየትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ነው?

12 በ⁠ዘሌዋውያን ምዕራፍ 1 እስከ 7 ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቁርባን፣ የኅብረት መሥዋዕት፣ የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት የሚባሉ አምስት ዋና ዋና የመባ ዓይነቶች ለየብቻ መጠቀሳቸውን አስተውለን ሊሆን ይችላል። እርግጥ አንዳንዶቹ መባዎች አንድ ላይ የሚቀርቡ ናቸው። በተጨማሪም እነዚህ መባዎች በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ለተለያየ ዓላማ ሁለት ጊዜ መገለጻቸውን እናስተውላለን። የመጀመሪያው ከዘሌዋውያን 1:​2 እስከ 6:​7 ላይ ያለው ሲሆን በመሠዊያው ላይ ምን ነገር መቅረብ እንዳለበት ዝርዝር መግለጫ ይሰጣል። ሁለተኛው ደግሞ ከ⁠ዘሌዋውያን 6:​8 እስከ 7:​36 ላይ የሚገኝ ሲሆን ለካህናቱ ስለሚሰጠውና መሥዋዕቱን ለሚያቀርበው ሰው ስለሚቀረው ድርሻ ይናገራል። ከዚያም በ⁠ዘኁልቁ ምዕራፍ 28 እና 29 ላይ በየዕለቱ፣ በየሳምንቱ፣ በየወሩና በዓመታዊ በዓላት ላይ ምን መቅረብ እንዳለባቸው የሚዘረዝረውን እንደ ፕሮግራም ተደርጎ ሊታይ የሚችል መግለጫ እናገኛለን።

13. ለአምላክ እንደ ስጦታ በፈቃደኝነት ይቀርቡ የነበሩትን መባዎች ጥቀስ።

13 በስጦታ መልክ ወይም ወደ አምላክ ለመቅረብና የእርሱን ሞገስ ለማግኘት ሲባል በፈቃደኝነት ከሚቀርቡት መባዎች መካከል የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቁርባንና የደኅንነት መሥዋዕት ይገኙበታል። አንዳንድ ምሁራን “የሚቃጠል መሥዋዕት”ን የሚያመለክተው የዕብራይስጡ መግለጫ “የማረግ መሥዋዕት” ወይም “የሚያርግ መሥዋዕት” የሚል ትርጉም እንዳለው ያምናሉ። የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ የታረደው እንስሳ በመሠዊያው ላይ ስለሚቃጠልና ጣፋጭ ሽታ ወይም መልካም መዓዛ ወደ ሰማይ ወደ አምላክ ዘንድ ስለሚያርግ ይህ መግለጫ ተስማሚ ነው። የሚቃጠልን መሥዋዕት ከሌሎች መሥዋዕቶች ልዩ የሚያደርገው ገፅታ ደሙ በመሥዋዕቱ ዙሪያ ከተረጨ በኋላ እንስሳው ሙሉ በሙሉ ለአምላክ የሚቀርብ መሆኑ ነው። ካህናቱ ‘ሁሉን የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቁርባን አድርገው በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥሉት’ ነበር።​—⁠ዘሌዋውያን 1:​3, 4, 9፤ ዘፍጥረት 8:​21

14. የእህል ቁርባን ይቀርብ የነበረው እንዴት ነው?

14 የእህል ቁርባን በ⁠ዘሌዋውያን ምዕራፍ 2 ላይ ተገልጿል። ይህ ብዙውን ጊዜ ዘይት የሚፈስስበትና ዕጣን የሚጨመርበት ከጥሩ ዱቄት የሚዘጋጅ መሥዋዕት ሲሆን በፈቃደኝነት የሚቀርብ ነበር። “ከመልካም ዱቄቱና ከዘይቱም አንድ እፍኝ ሙሉና ዕጣኑን ሁሉ ወስዶ ካህኑ የእሳት ቁርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።” (ዘሌዋውያን 2:​2) እዚህ ላይ የተገለጸው የዕጣን ዓይነት በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚገኘው የዕጣን መሠዊያ ላይ የሚቃጠለው ቅዱስ ዕጣን አንዱ ክፍል ነው። (ዘጸአት 30:​34-36) ንጉሥ ዳዊት “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፣ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን” ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን በአእምሮው ይዞ እንደነበረ ግልጽ ነው።​—⁠መዝሙር 141:​2

15. የኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብበት ዓላማ ምንድን ነው?

15 ሌላው በፈቃደኝነት ይቀርብ የነበረው የኅብረት መሥዋዕት ሲሆን ይህም በ⁠ዘሌዋውያን ምዕራፍ 3 ላይ ተብራርቷል። ስሙ “የሰላም መባ መሥዋዕት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በዕብራይስጥ “ሰላም” የሚለው ቃል ከጦርነት ወይም ከሁከት ነፃ ከመሆን የበለጠ ነገርን ያመለክታል። “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህንንና በተጨማሪም ከአምላክ ጋር የሚመሠረተውን ሰላማዊ ሁኔታ ወይም ዝምድና፣ ብልጽግናን፣ ደስታንና ፍስሃን ያመለክታል” በማለት ስተዲስ ኢን ዘ ሞዛይክ ኢንስቲትዩሽን የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። ስለሆነም የኅብረት መሥዋዕት አምላክን በመለማመን ከአምላክ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሚቀርብ ሳይሆን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሰዎች ከአምላክ ጋር ላገኙት ሰላም ምስጋናቸውን ወይም ደስታቸውን ለመግለጽ የሚያቀርቡት ነው። ደሙና ስቡ ለይሖዋ ከቀረበ በኋላ ካህናቱና መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው ከመሥዋዕቱ ይካፈላሉ። (ዘሌዋውያን 3:​17፤ 7:​16-21፤ 19:​5-8 የ1980 ትርጉም ) መሥዋዕቱን ያቀረበው ሰው፣ ካህናቱና ይሖዋ አምላክ ውብና ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ከአንድ ማዕድ የሚካፈሉ ሲሆን ይህም በመካከላቸው ሰላማዊ ዝምድና መኖሩን የሚያመለክት ነው።

16. (ሀ) የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት የሚቀርቡበት ዓላማ ምን ነበር? (ለ) ከሚቃጠል መሥዋዕት የሚለዩትስ እንዴት ነው?

16 የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ወይም ሕጉን በመተላለፍ ምክንያት ለተፈጸመ ኃጢአት ስርየት ለማግኘት ከሚቀርቡት መሥዋዕቶች መካከል የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት ይገኙበታል። እነዚህ መሥዋዕቶች በመሠዊያ ላይ ማቃጠልን የሚጠይቁ ቢሆኑም እንኳ በእሳት የሚቃጠለው የእንስሳው ስብና አንዳንድ ክፍሎቹ ብቻ በመሆኑ ሙሉውን እንስሳ በእሳት በማቃጠል ለአምላክ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ይለያሉ። የተቀረው የእንስሳው ክፍል ከሰፈሩ ውጭ ይጣላል ወይም በአንዳንድ ወቅቶች ለካህናቱ ይከፋፈላል። እንዲህ ያለ ልዩነት እንዲኖር የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም። የሚቃጠል መሥዋዕት ወደ አምላክ ለመቅረብ እንደ ስጦታ ሆኖ የሚቀርብ በመሆኑ ከመሥዋዕቱ ምንም ሳይጓደል ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ብቻ ይቀርባል። ብዙውን ጊዜ የሚቃጠል መሥዋዕት ከመቅረቡ በፊት የኃጢአት መሥዋዕት ወይም የበደል መሥዋዕት የሚቀርብ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ሲሆን ይህም ኃጢአተኛው የሚያቀርበው ስጦታ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ኃጢአቱ ይቅር መባል እንዳለበት ያሳያል።​—⁠ዘሌዋውያን 8:​14, 18፤ 9:​2, 3፤ 16:​3, 5

17, 18. የኃጢአት መሥዋዕት የሚቀርበው ለምን ነበር? የበደል መሥዋዕት ይቀርብ የነበረው ለምን ዓላማ ነው?

17 የኃጢአት መሥዋዕት ተቀባይነት የሚኖረው ባለማወቅ በሕጉ ላይ ለሚፈጸም ኃጢአት ማለትም በሥጋ ድካም ምክንያት ለሚፈጸም ኃጢአት ብቻ ነው። “ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔርም:- አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ” ኃጢአት የፈጸመው ሰው በማኅበሩ ውስጥ ካለው ቦታ ወይም ደረጃ ጋር የሚመጣጠን የኃጢአት መሥዋዕት ያቀርባል። (ዘሌዋውያን 4:​2, 3, 22, 27) በሌላው በኩል ደግሞ ንስሐ ለመግባት አሻፈረን የሚሉ ኃጢአተኞች ይገደሉ ነበር፤ ለእነርሱ መሥዋዕት አይቀርብም።​—⁠ዘጸዓት 21:​12-15፤ ዘሌዋውያን 17:​10፤ 20:​2, 6, 10፤ ዘኁልቁ 15:​30፤ ዕብራውያን 2:​2

18 የበደል መሥዋዕት ትርጉሙና ዓላማው በ⁠ዘሌዋውያን ምዕራፍ 5 እና 6 ላይ ተገልጿል። አንድ ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል። ሕግ በመተላለፍ የሠራው ስህተት በባልንጀራው ወይም በይሖዋ አምላክ ላይ ኃጢአት እንዲፈጽም አድርጎት ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ለፈጸመው ስህተት ካሳ መክፈል ወይም ማስተካከያ ማድረግ ይኖርበታል። የተለያዩ የኃጢአት ዓይነቶች ተጠቅሰዋል። አንዳንዶቹ አንድ ሰው በግሉ የሚፈጽማቸው ኃጢአቶች ናቸው (5:​2-6)፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ‘ለእግዚአብሔር በተቀደሱ ነገሮች’ ላይ የሚፈጸሙ ኃጢአቶች ናቸው (5:​14-16)፣ ሌሎቹ ደግሞ አንድ ሰው ሙሉ በሙሉ ሳያውቅ የሚፈጽማቸው ናቸው ሊባሉ የሚችሉ ዓይነት ባይሆኑም እንኳ ከመጥፎ ምኞት ወይም ከሥጋ ድክመት የተነሳ የሚፈጸሙ ኃጢአቶች ናቸው። (6:​1-3) እነዚህን ኃጢአቶች የፈጸመ ግለሰብ መናዘዝ ያለበት ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ካሳ እንዲከፍልና ከዚያም ለይሖዋ የበደል መሥዋዕት እንዲያቀርብ ይጠበቅበት ነበር።​—⁠ዘሌዋውያን 6:​4-7

ወደፊት የሚመጣ የተሻለ ነገር

19. እስራኤላውያን ሕጉና በሕጉ ውስጥ የታቀፉት መሥዋዕቶች እያሉም የአምላክን ሞገስ ያጡት ለምንድን ነው?

19 እስራኤላውያን ብዙ መሥዋዕቶችንና መባዎችን አካትቶ የያዘው የሙሴ ሕግ የተሰጣቸው ተስፋ የተሰጠበት ዘር እስኪመጣ ድረስ ወደ አምላክ በመቅረብ ሞገሱንና በረከቱን ማግኘትና በዚያው መቀጠል እንዲችሉ ለማድረግ ነው። የአይሁድ ተወላጅ የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል” በማለት ሁኔታውን ገልጾታል። (ገላትያ 3:​24) የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ለዚህ ሞግዚት ጥሩ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ይባስ ብለው ያንን መብት አለአግባብ ተጠቀሙበት። በመሆኑም ያቀርቧቸው የነበሩት እጅግ ብዙ መሥዋዕቶች በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ሆነዋል። “የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም” ብሏቸዋል።​—⁠ኢሳይያስ 1:​11

20. ሕጉንና በሕጉ ውስጥ የተካተቱትን መሥዋዕቶች በሚመለከት በ70 እዘአ ምን ደረሰ?

20 የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ከቤተ መቅደሱና ከክህነት አገልግሎቱ ጋር በ70 እዘአ ጠፋ። ከዚያ በኋላ ሕጉ በሚያዘው መሠረት መሥዋዕቶችን የማቅረብ ሥርዓት አከተመ። ታዲያ ይህ ማለት የሕጉ ዓይነተኛ ክፍል የነበሩት መሥዋዕቶች በዛሬው ጊዜ አምላክን ለሚያመልኩ ሰዎች ምንም ትርጉም የላቸውም ማለት ነው? ይህን ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመው ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ማብራሪያ ይሰጣል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም መሠረት ‘ስርየት’ የሚለው ቃል ‘መሸፈን’ ወይም ‘መለወጥ’ የሚሉ መሠረታዊ ሐሳቦች ያዘለ ሲሆን ከሚለወጠው ወይም ‘ከሚሸፈነው’ ነገር ጋር አንድ ዓይነት መሆን አለበት። . . . አዳም ያጣውን ነገር የሚተካከል ስርየት ለማቅረብ ፍጹም ከሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ጋር የሚመጣጠን ዋጋ ያለው የኃጢአት መባ መቅረብ ነበረበት።”

b “መባ” ተብሎ በተደጋጋሚ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ቆርባን የሚለው ነው። ኢየሱስ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይከተሉት የነበረውን ሥነ ምግባር የጎደለው ልማድ ማውገዙን ማርቆስ በመዘገበ ጊዜ “ቁርባን” የሚለው ቃል ትርጉሙ “መባ” [“ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ፣” NW ] ማለት እንደሆነ ገልጿል።​—⁠ማርቆስ 7:​11

ልታብራራ ትችላለህ?

• በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ የገፋፋቸው ምንድን ነው?

• መሥዋዕት ማቅረብ ያስፈለገው ለምን ነበር?

• በሕጉ ሥር ይቀርቡ የነበሩት ዋና ዋና መሥዋዕቶች ምንድን ናቸው? ዓላማቸውስ ምን ነበር?

• ጳውሎስ በተናገረው መሠረት ሕጉና በሕጉ ውስጥ የተካተቱት መሥዋዕቶች ለምን ቁልፍ ዓላማ ያገለግሉ ነበር?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቤል ያቀረበው መሥዋዕት ይሖዋ በገባው ተስፋ ላይ እምነት እንዳለው የሚያሳይ በመሆኑ የሚያስደስት ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዚህን ትዕይንት ትርጉም ታውቃለህ ?