በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥላቻን ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ

ጥላቻን ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ

ጥላቻን ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ

“ፍርሃት ከሌለ ጥላቻም አይኖርም። . . . የምንፈራውን ነገር እንጠላለን፤ ጥላቻ ባለበት ቦታ ሁሉ ፍርሃት ያደባል።”​—⁠ሐያሲና ደራሲ የሆኑት ሰር ኮኖሊ

ብዙዎቹ የማኅበራዊ ኑሮ ጠበብት ጥላቻ በሰዎች ደመ ነፍስ ውስጥ የተቀበረ ነገር ነው ብለው ያምናሉ። አንድ የፖለቲካ ሳይንቲስት ጥላቻ “በአብዛኛው በሰው ልጅ ውስጥ የተቀረጸ” የሰብዓዊ ተፈጥሮው አካል ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ሰብዓዊ ተፈጥሮን የሚያጠኑ ሰዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ መድረሳቸው አያስገርምም። ጥናታቸውን የሚያካሄዱት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚለው ‘በዓመፃ ተጸንሰው በኃጢአት በተወለዱ’ ወንዶችና ሴቶች ላይ ነው። (መዝሙር 51:​5) ሌላው ቀርቶ ፈጣሪ እንኳን ሳይቀር ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆችን ሲመዝን “የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ” ተመልክቷል።​—⁠ዘፍጥረት 6:​5

ጭፍን ጥላቻ፣ ዘረኝነትና የእነዚህ ውጤት የሆነው ጥላቻ የሰው ልጅ ከወረሰው አለፍጽምናና የራስ ወዳድነት ስሜት የሚመነጩ ናቸው። (ዘዳግም 32:​5) የሚያሳዝነው የትኛውም ሰብዓዊ ድርጅት ወይም መስተዳድር ምንም ዓይነት ፖሊሲ ቢያረቅቅ የሰው ልብ እንዲለወጥ የሚያደርግ ሕግ ሊያወጣ አልቻለም። የውጭ አገር ዘጋቢ የሆኑት ጆሃን ማክጌሪ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ይሁን እንጂ በጣም ኃያል የሆነና ዓለም አቀፍ መረጋጋት ለማስፈን የሚጥር ወገን በቦስኒያ፣ በሶማሊያ፣ በላይቤሪያ፣ በካሽሚር እና በካውካሰስ ያን ያህል ደም መፋሰስ እንዲከሰት ያደረገውን ጥላቻ ለማስወገድ ምንም ማድረግ የሚችለው ነገር የለም።”

ይሁን እንጂ ጥላቻ ሊወገድ ወደሚችልበት መፍትሔ ከመሄዳችን በፊት ለጥላቻ መንስኤ ከሆኑት ነገሮች በስተጀርባ ስላለው ነገር መሠረታዊ እውቀት ማግኘት ይኖርብናል።

ፍራቻ የሚፈጥረው ጥላቻ

የተለያየ ዓይነት ጥላቻ አለ። አንድሪው ሱሊቫን ጉዳዩን እንዲህ በማለት ጥሩ አድርገው ገልጸውታል:- “ከፍርሃት የሚመጣ ጥላቻ አለ፣ ከንቀት የሚመጣ ጥላቻ አለ፤ በኃይል የሚገለጥ ጥላቻ አለ እንዲሁም ኃይል ከማጣት የሚመጣ ጥላቻ አለ፤ ከቅንዓት የሚመጣ በቀልና ጥላቻ አለ . . . የጨቋኝ ጥላቻ አለ፣ የተጨቋኝ ጥላቻ አለ። ውስጥ ውስጡን የሚነድና ቀስ በቀስ እየከሰመ የሚሄድ ጥላቻ አለ። በድንገት የሚፈነዳ ጥላቻ አለ እንዲሁም የተዳፈነ ጥላቻ አለ።”

በዘመናችን ጥላቻ የሞላባቸው ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ ከሚያደርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንደሆኑ ጥርጥር የለውም። ብዙውን ጊዜ ጠንካራ የሆነ ጭፍን ጥላቻና የጥላቻ መገንፈል የሚከሰተው አናሳው ቡድን የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ በሚገኝበት አካባቢ ነው። በተጨማሪም የባዕድ አገር ሰዎች መጉረፍ የሚፈጥረው ስጋት መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ጥላቻን እንዲኮተኩት ያደርጋል።

አንዳንዶች እነዚህ አዲስ መጤዎች በዝቅተኛ ደሞዝ እየተቀጠሩ በሥራው መስክ እንደሚቀናቀኗቸው ወይም የዕቃ ዋጋ እንዲቀንስ እንደሚያደርጉ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ትክክል ነው ወይስ ትክክል አይደለም የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው። ኢኮኖሚ ሊወድቅ ይችላል የሚለው ፍርሃት እና የማኅበረሰቡ የአኗኗር ደረጃ ወይም የአኗኗር ዘይቤ ዝቅ እያለ ይሄዳል የሚለው ፍርሃት ጭፍንና ሥር የሰደደ ጥላቻ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

ጥላቻን ለማስወገድ መወሰድ ያለበት የመጀመሪያው እርምጃ ምን መሆን አለበት? የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ነው።

የአመለካከት ለውጥ

ማክጌሪ “እውነተኛ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች ፈቃደኞች ሲሆኑ ብቻ ነው” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ ሰዎች ፈቃደኛ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? ጥላቻን በማስቆም ረገድ ከሁሉም የበለጠ ኃይል፣ ከሁሉም የበለጠ ግፊትና ከሁሉም የበለጠ ዘላቂ ተጽዕኖ ያለው የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑ ከተሞክሮ ታይቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት ‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያው፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ የሚወጋ፣ የልብንም ስሜትና አሳብ የሚመረምር’ በመሆኑ ነው።​—⁠ዕብራውያን 4:​12

ጭፍንና ሥር የሰደደ ጥላቻን ወዲያው ወይም በአንድ ጀንበር ከሥሩ ነቅሎ ማስወገድ እንደማይቻል የታወቀ ነው። ሊወገድ ግን ይችላል። የሰዎችን ልብ በማነሳሳትና ሕሊናቸው ስል እንዲሆን በማድረግ ረገድ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ኢየሱስ ሰዎች ለውጥ እንዲያደርጉ ማንቀሳቀስ ችሏል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ . . . ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ጥበብ የሞላበት ምክር መከተል ችለዋል።​—⁠ማቴዎስ 5:​44

ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ጋር በመስማማት ከአይሁድ ኅብረተሰብ በደረሰበት ጥላቻ ተገልሎ ይኖር የነበረውን የቀድሞውን ቀረጥ ሰብሳቢ ማቴዎስን በጣም ያምናቸው ከነበሩት ወዳጆቹ ጋር እንዲቀላቀል አድርጓል። (ማቴዎስ 9:​9፤ 11:​19) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ቀደም ሲል ተገልለውና ተጠልተው የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ አሕዛብ ከጊዜ በኋላ አባል የሚሆኑበት ንጹሕ አምልኮ የሚቋቋምበትን መንገድ ጠርጎ ነበር። (ገላትያ 3:​28) በዚያን ወቅት ይታወቁ ከነበረው ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ሆነዋል። (ሥራ 10:​34, 35) እነዚህ ሰዎች እርስ በርስ በነበራቸው የላቀ ፍቅር ተለይተው ይታወቁ ነበር። (ዮሐንስ 13:​35) ጥላቻ የተሞሉ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረውን እስጢፋኖስን በድንጋይ በሚወግሩት ጊዜ ሊሞት ሲል የተናገረው የመጨረሻ ቃል “ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው” የሚል ነበር። እስጢፋኖስ ለእርሱ ጥላቻ ለነበራቸው ሰዎች ክፉ ነገር አልተመኘም።​—⁠ሥራ 6:​8-14፤ 7:​54-60

በዘመናችን የሚገኙ ክርስቲያኖችም ለክርስቲያን ወንድሞቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሚጠሏቸው ሰዎች እንኳን ሳይቀር መልካም በማድረግ ኢየሱስ ለሰጠው ምክር ተመሳሳይ የሆነ ምላሽ ሰጥተዋል። (ገላትያ 6:​10) ተንኮል አዘል ጥላቻን ከውስጣቸው ነቅለው ለማጥፋት በመጣር ላይ ናቸው። በውስጣቸው ጥላቻ እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርጉት ኃይለኛ ግፊቶች ምን እንደሆኑ ስለሚገነዘቡ አዎንታዊ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ጥላቻን በፍቅር ይተካሉ። አዎን፣ በጥንት ጊዜ የነበረ አንድ ጠቢብ ሰው እንደተናገረው “ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች።”​—⁠ምሳሌ 10:​12

ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።” (1 ዮሐንስ 3:​15) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ያምናሉ። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ከተለያየ ዘር፣ ባሕል፣ ሃይማኖትና ፖለቲካዊ መደብ የመጡ ሰዎች አንድ በመሆን ከጥላቻ ነፃ የሆነ አንድ ኅብረተሰብ ማለትም እውነተኛ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ማቋቋም ችለዋል።​—⁠ሣጥኖቹን ተመልከት።

ጥላቻ ይወገዳል!

ምናልባት ‘ይህ በግለሰቦች መካከል ሊኖር የሚችለውን ችግር ያስወግድ ይሆናል። ከምድራችን ላይ ጥላቻን ሙሉ በሙሉ ሊያስወግድ ግን አይችልም’ ትል ይሆናል። አንተ በልብህ ውስጥ ጥላቻ ባይኖርም እንኳን የጥላቻ ተጠቂ ልትሆን እንደምትችል እሙን ነው። ስለዚህ ለዚህ ዓለም አቀፋዊ ችግር እውነተኛ መፍትሔ ለማግኘት ወደ አምላክ ዞር ማለት አለብን።

አምላክ በቅርቡ ምንም ርዝራዥ ሳያስቀር ጥላቻን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ዓላማ አለው። ይህም የሚፈጸመው ኢየሱስ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይ ባስተማረን ሰማያዊው መስተዳድር አማካኝነት ነው።​—⁠ማቴዎስ 6:​9, 10

ይህ ጸሎት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ሲያገኝ ጥላቻ እንዲስፋፋ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በሙሉ አይኖሩም። ጥላቻ እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሁሉ ይወገዳሉ። ፕሮፓጋንዳ፣ ድንቁርናና ጭፍን ጥላቻ በእውቀት፣ በእውነትና በጽድቅ ይተካሉ። ከዚያም አምላክ ‘እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ አይሆንም።’​—⁠ራእይ 21:​1-4

በአሁኑ ጊዜም ቢሆን አንድ ትልቅ ምሥራች አለ! “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር የሚያረጋግጥ የማያሻማ ማስረጃ አለ። ይህም ጥላቻ ከምድር ላይ የሚጠፋበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እርግጠኞች ያደርገናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ማቴዎስ 24:​3-14) አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ ወደ ፍጽምና ስለሚደርስ የእውነተኛ ወንድማማችነት መንፈስ ይሰፍናል።​—⁠ሉቃስ 23:​43፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

ሆኖም በዚህ እውነተኛ በሆነ ወንድማማችነት ለመደሰት የግድ እስከዚያ ድረስ መጠበቅ አይኖርብህም። እንዲያውም ሣጥኖቹ እንደሚያሳዩት በጥላቻ ሊሞሉ ይችሉ የነበሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልቦች በክርስቲያናዊ ፍቅር ተሞልተዋል። አንተም እርስ በርስ መፈቃቀር የሚታይበት የዚህ የወንድማማች ማኅበር አባል እንድትሆን ተጋብዘሃል!

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን

“ኢየሱስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር?”

ሰኔ 1998 በዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ገጠራማ ክልል የሚኖሩ ሦስት ነጮች ጀምስ ብያርድ ጄ አር በሚባል አንድ ጥቁር ላይ ጥቃት ያደርሳሉ። ሰው ወደማይደርስበት በጣም ሩቅ ወደሆነ አካባቢ ወስደው ከደበደቡት በኋላ እግሮቹን በሰንሰለት አሰሩት። ከዚያም ከአንድ የጭነት መኪና ጋር አስረው 5 ኪሎ ሜትር ያህል እየጎተቱ ሲወስዱት ከአንድ የውኃ መውረጃ ቱቦ ጋር ተጋጨ። ይህ ድርጊት በ1990ዎቹ ዓመታት ከተፈጸሙት አሰቃቂ ወንጀሎች ሁሉ እጅግ የከፋው ተብሎለታል።

ሦስቱ የጀምስ ብያርድ እህቶች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ይህን ዘግናኝ ወንጀል በፈጸሙት ሰዎች ላይ ምን ዓይነት ስሜት ይኖራቸው ይሆን? ቤተሰቡ በጻፈው ጽሑፍ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “የምትወዱት ሰው አሰቃቂ ድብደባ ተፈጽሞበት በጭካኔ መገደሉ የሚፈጥረውን የሐዘንና የባዶነት ስሜት መግለጽ ያስቸግራል። አንድ ሰው እንዲህ ላለው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው? በቀል፣ የጥላቻ ንግግር ወይም ጥላቻን የሚያስፋፋ ፕሮፓጋንዳ ፈጽሞ ወደ አእምሯችን አልመጣም። ‘ኢየሱስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር? ምን ምላሽ ይሰጥ ነበር?’ ብለን አሰብን። የሚናገረው ስለ ሰላምና ተስፋ ብቻ እንደሚሆን ግልጽ ነው።”

በልባቸው ውስጥ ጥላቻ እንዳይበቅል ከረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል ሮሜ 12:17-19 ይገኝበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ . . . ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።”

እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ:- “ፍትሕ የጎደላቸው አንዳንድ ድርጊቶች ወይም ወንጀሎች በጣም አሰቃቂ ከመሆናቸው የተነሳ በቀላሉ ‘ይቅር ማለትና’ መርሳት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል በጽሑፎቻችን ላይ እንዳነበብን ትዝ ይለናል። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ይቅር ብሏል የሚባለው ያደረበትን ምሬት ትቶ ሕይወቱን ሲመራና ይህን ስሜት እንደያዘ መቆየቱ ሊያስከትልበት ከሚችለው የአካልም ሆነ የአእምሮ ጉዳት ራሱን ሲጠብቅ ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ ጥላቻ በልብ ውስጥ ሥር እንዳይሰድድ ለመከላከል የሚያስችል ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ይህ እንዴት ያለ ልብ የሚነካ ምሥክርነት ነው!

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከጠላትነት ወደ ወዳጅነት

በቅርብ ዓመታት ሥራ ለማግኘት ሲሉ በሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ግሪክ ፈልሰዋል። ይሁን እንጂ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ባለው የኢኮኖሚ ሁኔታ የተነሳ ያለው የሥራ ዕድል አነስተኛ መሆኑ ሥራ ለማግኘት የሚደረገውን ትግል ይበልጥ አስቸጋሪ አድርጎታል። ይህም ከተለያየ አገር በመጡ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ጥላቻ እንዲፈጠር አድርጓል። ከአልባንያ እና ከቡልጋርያ በመጡ ስደተኞች መካከል ያለው ፉክክር ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆናል። ግሪክ ውስጥ በብዙዎቹ አካባቢዎች በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ፉክክር አለ።

በሰሜን ምሥራቅ ፔሎፖኒሶሰ በምትገኘው በኪያቶ ከተማ አንድ የቡልጋርያ ቤተሰብና አንድ አልባንያዊ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይጀምሩና እርስ በርስ ይተዋወቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋቸው ከእነዚህ ሁለት አገሮች በመጡ በርካታ ሰዎች መካከል ያለውን ጥላቻ አጥፍቶላቸዋል። በተጨማሪም በእነዚህ ግለሰቦች መካከል እውነተኛ ወዳጅነት እንዲመሠረት አስተዋጽኦ አበርክቷል። ሌላው ቀርቶ ቡልጋርያዊው ኢቫን አልባናዊ የሆነው ሉሊስ ከቤቱ አጠገብ መኖሪያ እንዲያገኝ ረድቶታል። ሁለቱ ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ ያላቸውን አብረው ይቃመሳሉ እንዲሁም ያሏቸውን ጥቂት ዕቃዎች እየተዋዋሱ ይጠቀማሉ። አሁን ሁለቱም ወንዶች የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ አንድ ላይ ሆነው ምሥራቹን ይሰብካሉ። እንዲህ ያለው ክርስቲያናዊ ወዳጅነት በጎረቤቶቻቸው ዘንድ ሳይስተዋል አላለፈም።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ማንኛውም የጥላቻ ርዝራዥ ከምድር ገጽ ይወገዳል