በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥላቻ በእጅጉ ተስፋፍቷል

ጥላቻ በእጅጉ ተስፋፍቷል

ጥላቻ በእጅጉ ተስፋፍቷል

“ሰዎች የሚጠሏቸውን ሰዎች ባሕርይ በትክክል አይረዱም።”—⁠የብዕር ሰውና ዲፕሎማት የሆኑት ጀምስ ራስል ሎዌል

በዛሬው ጊዜ ጥላቻ በሁሉም ቦታ ተስፋፍቶ ይገኛል። ምሥራቅ ቲሞር፣ ኮሶቮ፣ ላይቤሪያ፣ ሊትልቶን እና ሳራዬቮ የሚሉትን ስሞች እንዲሁም አፍቃሪ ናዚዎች፣ የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች የሚሉትን የመሳሰሉ መጠሪያዎች ስንሰማ የተቃጠሉ የፍርስራሽ ክምሮች፣ በቅርብ ጊዜ የተማሱ የጅምላ መቃብሮችና የተረፈረፉ አስከሬኖች ወዲያው ወደ አእምሯችን ይመጣሉ።

ጥላቻ፣ ግጭትና ዓመፅ የሌለበት ጊዜ ይመጣል የሚለው ተስፋ ሕልም ሆኖ ቀርቷል። የሟቹ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ባለቤት ዳንዬል ሚቴራን ወጣት የነበሩበትን ጊዜ በማስታወስ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ሰዎች ምንም ስጋት በማይፈጥርባቸው ወንድማማች በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ በነፃነት መኖር የሚችሉበትን ጊዜ ያልሙ ነበር፤ ከራሳቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር ሰላም እንዲኖራቸው ይመኙ ነበር፤ እንክብካቤ በሚያደርግላቸው ለጋስ በሆነ ዓለም ውስጥ ጤናማ፣ ሰላማዊና ክብራማ የሆነ ሕይወት ሲመሩ ይታያቸው ነበር።” እነዚህ ሁሉ ሕልሞች እምን ደረሱ? “ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ሕልማችን ሁሉ መና ሆኖ ቀርቷል” በማለት በምሬት ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ እያንሰራራ ያለው ጥላቻ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም። ጥላቻ በስፋት ከመዛመቱም በላይ መልኩን እየቀያየረ ብቅ በማለት ላይ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ቀላል ያዩት የነበረው በግለሰብ ደረጃ ያለምንም ስጋት ተረጋግቶ የመኖር ሁኔታ እንደ ማዕበል እያጥለቀለቀ በመጣው በጥላቻ ምክንያት በሚፈጸሙ ትርጉም የለሽ ድርጊቶች እየጠፋ መጥቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጸመው የጥላቻ ድርጊት ይበልጥ ዘግናኝ እየሆነ የሚሄድ ይመስላል። ጥላቻ ቤታችን ወይም አገራችን ውስጥ ባይገጥመን እንኳ ሌላ ቦታ አድፍጦ ይጠብቀናል። ይህንንም በየዕለቱ በሚተላለፉ የዕለቱ ጉዳይ በሚዘገብባቸው የቴሌቪዥን ዜናዎች ላይ ተመልክተን ይሆናል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በኢንተርኔት እንኳ ሳይቀር ተሰራጭተዋል። ለአብነት ያህል አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ያለፈው አሥርተ ዓመት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የብሔረተኝነት ስሜት የታየበት ነው። በሃርቫርድ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ማዕከል ምክትል ዲሬክተር የሆኑት ጆሴፍ ኤስ ናይ ጁኒየር እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “በአብዛኛው የዓለም ክፍል ብሔረተኝነት እየተቀጣጠለ እንጂ እየከሰመ ሲሄድ አይታይም። ዓለማችን እንደ አንድ መንደር ከመሆን ይልቅ እርስ በርሳቸው በዓይነ ቁራኛ በሚተያዩ በተለያዩ መንደሮች ተከፋፍላለች። ይህ ደግሞ ግጭት የሚፈጠርበትን አጋጣሚ በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል።”

በሌላ በኩል ደግሞ ከአገሬው አልፎ ተርፎም ከአካባቢው ነዋሪዎች በስተቀር በሌሎች ዘንድ እምብዛም የማይታወቅ ስውር የሆነ ጥላቻም ሊኖር ይችላል። በካናዳ የባዕድ አገር ሰዎችን የሚጠሉ ፀጉራቸውን የተላጩ አምስት ሰዎች አንድን በዕድሜ የገፉ የሲክ ሃይማኖት ተከታይ መግደላቸው “ብዙውን ጊዜ የተለያዩ ዘሮች ተቻችለው የሚኖሩባት አገር እንደሆነች ተደርጋ በምትወደሰው በዚህች አገር በጥላቻ የሚፈጸም ወንጀል እያንሰራራ እንዳለ አንዳንዶች የሚሰነዝሩትን ሐሳብ የሚያጠናክር ሆኗል።” በጀርመን ባለፉት ዓመታት ጽንፈኞች የሚፈጽሙት የዘረኝነት ጥቃት በእጅጉ ካሽቆለቆለ በኋላ በ1997 በድንገት 27 በመቶ አሻቅቧል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ማንፍሬድ ካንተር “ይህ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነው” በማለት ተናግረዋል።

በሰሜናዊ አልባንያ ከ6, 000 የሚበልጡ ልጆች በቤተሰባቸው ጠላቶች እንዳይገደሉ በመፍራት በራሳቸው ቤት ውስጥ እስረኞች መሆናቸውን አንድ ዘገባ ይፋ አድርጓል። እነዚህ ልጆች “በሺህ የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ሕይወት እያናወጠ” ባለው ደምን የመበቀል ባህል የጥቃት ዒላማ ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራሉ የምርመራ ቢሮ (FBI) እንዳለው ከሆነ “በ1998 ለኤፍ ቢ አይ ሪፖርት ከተደረጉት በጥላቻ ምክንያት ከተፈጸሙት 7, 755 ወንጀሎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዘር ጥላቻ የተቆሰቆሱ ናቸው።” የተቀሩት በጥላቻ ምክንያት የተፈጸሙ ወንጀሎች በሃይማኖት፣ በጎሳ ወይም በትውልድና በአካል ጉዳተኞች ጭፍን ጥላቻ የተቆሰቆሱ ናቸው።

ከዚህም በላይ በየዕለቱ በጋዜጦች ላይ እየታተሙ የሚወጡ ርዕሰ ዜናዎች በአሁኑ ጊዜ በዋነኛነት ከ21 ሚልዮን በላይ በሆኑት ስደተኞች ላይ ያነጣጠረውንና እንደ ወረርሽኝ የተዛመተውን የባዕድ አገር ሰዎችን የመጥላት ዝንባሌ በጉልህ የሚያሳዩ ናቸው። የሚያሳዝነው ደግሞ ለባዕድ አገር ሰዎች የከረረ ጥላቻ ካላቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው። ከበስተጀርባ ሆነው በወጣቶች ልብ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ጥላቻ የሚዘሩት ኃላፊነት የጎደላቸው የፖለቲካ ሰዎችና ይህን ጥላቻቸውን በሌሎች ለማላከክ የሚጥሩ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ጥርጣሬ፣ አለመቻቻልና ለተለዩ ሰዎች ጥሩ ያልሆነ አመለካከት መያዝ ብዙም በገሃድ የማይታዩ የዚሁ ምልክት ገጽታዎች ናቸው።

ጥላቻ እንደ ወረርሽኝ እንዲዛመት ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ጥላቻን ለማስወገድ ምን ሊደረግ ይችላል? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Cover, top: UN PHOTO 186705/​J. Isaac

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Daud/Sipa Press