በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቺሊ የሚገኙትን የእውነት ዘሮች ውኃ ማጠጣት

በቺሊ የሚገኙትን የእውነት ዘሮች ውኃ ማጠጣት

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

በቺሊ የሚገኙትን የእውነት ዘሮች ውኃ ማጠጣት

በረሃማ በሆነው የሰሜናዊ ቺሊ ግዛት ዝናብ ሳይጥል ለብዙ ዓመታት ሊቆይ ቢችልም በሚዘንብበት ጊዜ ግን ተሰነጣጥቆና በየቦታው አለቶች አፍጥጠው ይታዩበት የነበረው መሬት በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አበቦች ይሸፈናል። ይህ በጣም አስደናቂ የሆነ ትዕይንት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ጎብኚዎችን ይስባል።

ይሁን እንጂ ቺሊ ውስጥ ከዚህ ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነገር በመከሰት ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ የእውነት ውኃ በእያንዳንዱ የቺሊ ግዛት ውስጥ በመፍሰስ ላይ ሲሆን ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመሆን “እያበቡ” ነው። ይህንን የእውነት ውኃ ለማሰራጨት እንደ አንድ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለው ስልክ ነው። የሚከተሉት ተሞክሮዎች በዚህ የምሥክርነት መስጫ ዘዴ በመጠቀም እየተገኙ ያሉትን ጥሩ ውጤቶች ያሳያሉ።

• ካሪና የተባለች አንዲት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊት በአንድ የወረዳ ስብሰባ ኘሮግራም ላይ በስልክ መመሥከር የሚቻልበትን መንገድ በሠርቶ ማሳያ እንድታቀርብ ተጠየቀች። ይሁን እንጂ ካሪና አንድም ቀን በስልክ መሥክራ አታውቅም ነበር። ካሪና በወረዳ ስብሰባው ኘሮግራም ላይ እንድትሳተፍ ለማበረታታት ሲሉ አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ሚስቱ በስልክ መመስከር ስለሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች አወያዩአት። በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ የይሖዋን አመራር ለማግኘት እንድትጸልይ አበረታቷት። እሷም እንዳሏት ካደረገች በኋላ ስልክ ለመደወል ወሰነች።

ካሪና በአቅራቢያዋ በሚገኘው መንደር ውስጥ ካሉት ስልኮች አንዱን መርጣ ስትደውል አንዲት የስልክ ኦኘሬተር ስልኩን አነሳች። ካሪናም የደወለችበትን ምክንያት አብራራችላት። ሴትዮዋ ጥሩ ምላሽ በመስጠቷ ከሦስት ቀን በኋላ እንደገና በስልክ ለመገናኘት ዝግጅት አደረጉ። በስልክ በተደረገላት ተመላልሶ መጠየቅ አማካኝነት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹር ከሴትዮዋ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ አስደሳችና ስሜት የሚቀሰቅሱ ጥናቶች ከማካሄዳቸውም በላይ ካሪና ሴትዮዋ ያሏትን ጥያቄዎች የሚመልስ ጽሑፍ ልካላታለች።

• ቤርናርዳ በስህተት ስልክ ቤቷ ለደወለላት አንድ ሰው በራሷ ተነሳስታ ለመመስከር አሰበች። በሰውየው ከመበሳጨት ይልቅ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች በመግለጽ ራሷን ካስተዋወቀች በኋላ ልትረዳው ትችል እንደሆነ ሐሳብ አቀረበች። በዚህም ውይይት ተጀመረና በቅርቡ የአምላክ መንግሥት የፍትሕ መጓደልን እንዴት እንደሚያስወግድ ስታብራራለት አዳመጣት። ሰውየው ለቤርናርዳ የስልክ ቁጥሩን ሰጥቶአት ስለነበር ለተወሰነ ጊዜ ያህል እየደወለች ተመላልሶ መጠየቅ አደረገችለት። በአንደኛው የስልክ ውይይታቸው ወቅት ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ላይ የተወሰነ ክፍል አነበበችለት። ሰውየው አንድ ቅጂ ማግኘት ይችል እንደሆነ በመጠየቁ መጽሐፉንና አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ላከችለት። በኋላም በአቅራቢያው የሚገኝ አንድ ወንድም ሄዶ እንዲያነጋግረው ዝግጅት ተደረገ። አሁን ይህ ወንድም በመብቀል ላይ ያለውን ይህንን “ተክል” “ውኃ ማጠጣቱን” ቀጥሏል።

አዎን፣ በዚህ ዓለም ደረቅ መንፈሳዊ አፈር ውስጥ የተደበቁ ዘሮች ሕይወት ሰጪ የሆነው የእውነት ውኃ ሲደርሳቸው ለማበብ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ይህንን ውኃ የተጠሙ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ አምላክ ታማኝ አገልጋዮች ለመሆን “መብቀላቸውን” እንዲሁም “ማበባቸውን” ይቀጥላሉ።​—⁠ኢሳይያስ 44:​3, 4