‘የሚናገሩት ስለ ጥሩነትና ስለ ፍቅር ነው’
‘የሚናገሩት ስለ ጥሩነትና ስለ ፍቅር ነው’
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፈረንሳይ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ስም የማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል። ተቃዋሚዎቻቸው ስለ እነርሱ በሕዝብ ፊት አዛብተው ለማቅረብ ሲሉ ሐቀኝነት የጎደላቸውንና የተሳሳቱ መረጃዎችን ተጠቅመዋል። በ1999 መጀመሪያ ላይ በመላው ፈረንሳይ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች የፈረንሳይ ሕዝብ ሆይ፣ ተታልለሃል! የሚል ርዕስ ያለውን ትራክት 12 ሚልዮን ቅጂዎች አሰራጭተዋል። በዚህ ትራክት ውስጥ እነርሱን በመቃወም የተሰጡትን ስም የሚያጠፉ መግለጫዎች አውግዘዋል።
ዘመቻው ከተካሄደ ከጥቂት ቀን በኋላ የሕክምና ዶክተርና የቀድሞ የፓርላማ አባል የሆኑት ሚስተር ዣን ቦኖም በአገሩ ጋዜጣ ታትሞ የወጣ አንድ የተቃውሞ ደብዳቤ ጽፈው ነበር። “አልፎ አልፎ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ ይመጣሉ። የሚመጡት ስለ ጥሩነትና ስለ ዓለም አቀፋዊ ፍቅር ለመወያየት ነው። . . . ሳያስፈቅዱ ወደ ቤት አይገቡም። ሐሳባቸውን የሚገልጹት ረጋ ባለ መንገድ ሲሆን ጥርጣሬዬን ስገልጽላቸው በደግነት ያዳምጡኛል።”
ሚስተር ቦኖም የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን መንፈሳዊ አመለካከት አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “የእነርሱ ገራገርነት ምንም ጉዳት አያስከትልም። በሌላው በኩል ግን የአንዳንድ ፖለቲከኞች ገራገርነት ለዜጎች ሰላምና ለማኅበረሰቡ አንድነት ይበልጥ አስጊ ነው።”