የተቀበልነው ውድ ውርሻ—ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
የተቀበልነው ውድ ውርሻ—ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
“እናንተ የአባቴ ብሩካን፣ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።”—ማቴዎስ 25:34
1.ሰዎች ምን የተለያዩ ነገሮችን በውርሻ አግኝተዋል?
ሁሉም ሰው በውርሻ ያገኘው ነገር አለ። አንዳንድ ሰዎች ያገኙት ውርሻ በቁሳዊ ሁኔታ የተደላደለ ኑሮ መምራትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ድህነትን ወርሰው ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ወቅቶች ቀደም ያሉት ትውልዶች በደረሰባቸው ወይም በሰሙት ነገር ምክንያት በአንድ ጎሳ ላይ ያደረባቸውን የመረረ ጥላቻ ለቀጣዩ ትውልድ አስተላልፈዋል። ይሁን እንጂ ሁላችንም አንድ ውርሻ በጋራ ተቀብለናል። ሁላችንም ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ኃጢአትን ወርሰናል። ይህም ውርሻ ውሎ አድሮ ሞት ያስከትላል።—መክብብ 9:2, 10፤ ሮሜ 5:12
2, 3. ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ለአዳምና ለሔዋን ልጆች ምን ውርሻ አዘጋጅቶላቸው ነበር? ውርሻውን ሳያገኙ የቀሩትስ ለምንድን ነው?
2 ይሖዋ አፍቃሪ ሰማያዊ አባት እንደመሆኑ መጠን መጀመሪያ ላይ ለሰው ዘሮች የሰጠው ውርሻ ከዚህ ፍጹም የተለየ ሲሆን ይህም ፍጹም ሕይወት አግኝቶ በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ነበር። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን የነበሩበት ሁኔታ ከጅምሩ ፍጹምና ኃጢአት የሌለበት ነበር። ይሖዋ አምላክ ፕላኔቷን ምድር ለሰው ዘሮች ስጦታ አድርጎ አበረከተ። (መዝሙር 115:16) መላዋ ምድር ወደፊት ምን ልትመስል እንደምትችል ለማሳየት ኤደን ገነትን እንደ ናሙና አድርጎ በመስጠት አስደሳች የሆነ ትልቅ ሥራ ከፊታቸው ዘረጋላቸው። ልጆችን መውለድ፣ ምድርንና በላይዋ የሚገኙትን የተለያዩ ዓይነት እጽዋትንና እንስሳትን መንከባከብ እንዲሁም መላዋን ፕላኔት እስክትሸፍን ድረስ ገነትን ማስፋት ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9, 15) ልጆቻቸውም በዚህ ሥራ ይካፈላሉ። ለልጆቻቸው ሊያስተላልፉ የሚችሉት እንዴት ያለ አስደናቂ ውርሻ ነበር!
3 ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ልጆቻቸው በዚህ ሁሉ መደሰት የሚችሉት ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እስከኖራቸው ድረስ ብቻ ነበር። ይሖዋን መውደድና መታዘዝ ይጠበቅባቸው ነበር፤ አዳምና ሔዋን ግን አምላክ ለሰጣቸው ስጦታ አድናቆት ሳያሳዩ ቀሩና ትእዛዙን ጣሱ። መኖሪያቸው ከነበረችው ገነት ከመባረራቸውም በላይ አምላክ ከፊታቸው የዘረጋላቸውን ታላላቅ ተስፋዎች አጡ። በዚህም ምክንያት እነዚህን ነገሮች ለልጆቻቸው ማስተላለፍ ሳይችሉ ቀሩ።—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1-24
4. አዳም ያጣውን ውርሻ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
4 የአዳምና የሔዋን ልጆች አዳም ያጣውን ውርሻ ለማግኘት የሚያስችል አጋጣሚ ይኖራቸው ዘንድ ይሖዋ በምሕረቱ ተገፋፍቶ ዝግጅት አደረገ። እንዴት? አምላክ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም ዘሮች ሲል ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ሰጠ። በዚህ መንገድ ክርስቶስ ሁሉንም ገዛ። ሆኖም ውርሻውን ወዲያው ያገኛሉ ማለት አይደለም። ኃጢአት በሚያስተሰርየው የኢየሱስ መሥዋዕት ዋጋ በማመንና ይህንንም በታዛዥነት በማሳየት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 3:16, 36፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6፤ ዕብራውያን 2:9፤ 5:9) አኗኗርህ ለዚህ ዝግጅት አድናቆት እንዳለህ የሚያሳይ ነውን?
በአብርሃም በኩል የተላለፈ ውርሻ
5. አብርሃም ከይሖዋ ጋር ለነበረው ዝምድና አድናቆት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ በሚያከናውንበት ጊዜ ከአብርሃም ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት መሥርቷል። ይህን ታማኝ ሰው አገሩን ለቅቆ እንዲወጣና አምላክ ራሱ ወደሚያሳየው ምድር እንዲሄድ አዘዘው። አብርሃም በፈቃደኝነት ታዘዘ። አብርሃም እዚያ ከደረሰ በኋላ ምድሪቱን እንደ ውርሻ አድርጎ የሚቀበለው አብርሃም ራሱ ሳይሆን ዘሮቹ እንደሚሆኑ ይሖዋ ተናገረ። (ዘፍጥረት 12:1, 2, 7) አብርሃም ምን ተሰማው? አብርሃም ዘሮቹ ውርሻቸውን መቀበል ይችሉ ዘንድ አምላክ ወዳዘዘው ወደየትኛውም ቦታ ለመሄድና የሚሰጠውን ማንኛውንም ትእዛዝ ተቀብሎ ይሖዋን ለማገልገል ፈቃደኛ ነበር። አብርሃም እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የእርሱ ባልሆነች አገር ላይ ይሖዋን ለ100 ዓመት አገልግሏል። (ዘፍጥረት 12:4፤ 25:8-10) አንተ ብትሆን ኖሮ እንዲህ ታደርግ ነበር? አብርሃም ‘ወዳጁ’ እንደሆነ ይሖዋ ተናግሯል።—ኢሳይያስ 41:8
6. (ሀ) አብርሃም ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ያሳየው ፈቃደኝነት ለምን ነገር ምሳሌ ይሆናል? (ለ) አብርሃም ለዘሮቹ ማስተላለፍ የቻለው ውድ ውርሻ ምንድን ነው?
6 አብርሃም በጣም የሚወደውን ወንድ ልጁን ይስሐቅን ለማግኘት በርካታ ዓመታት ጠብቋል። ልጁ ለአካለ መጠን በደረሰ ጊዜ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ይሖዋ አዘዘው። አብርሃም አምላክ ራሱ ልጁን ቤዛ አድርጎ በማቅረብ የሚያከናውነውን ነገር ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሊያሳይ መሆኑን አላወቀም። ሆኖም አብርሃም በመታዘዝ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ ሲል የይሖዋ መልአክ አስቆመው። (ዘፍጥረት 22:9-14) ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል ፍጻሜውን የሚያገኘው በይስሐቅ በኩል እንደሚሆን ቀደም ሲል ተናግሯል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ከሞት የተነሳ ሰው ባይኖርም እንኳ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አምላክ ይስሐቅን ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል አብርሃም እምነት እንደነበረው ግልጽ ነው። (ዘፍጥረት 17:15-18፤ ዕብራውያን 11:17-19) አብርሃም ልጁን እንኳ ሳይቀር ለመስጠት ወደኋላ ባለማለቱ ምክንያት ይሖዋ “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ” በማለት ተናገረ። (ዘፍጥረት 22:15-18) ይህም በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ዘር ማለትም ነፃ የሚያወጣው መሲሕ በአብርሃም የትውልድ መሥመር በኩል እንደሚመጣ አመለከተ። ይህ እንዴት ያለ ውድ ውርሻ ነው!
7. አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ያገኙትን ውርሻ እንዳደነቁ ያሳዩት እንዴት ነው?
7 አብርሃምም ሆነ ‘የተስፋውን ቃል አብረውት የሚወርሱት’ ይስሐቅና የልጁ ልጅ የሆነው ያዕቆብ ይሖዋ በዚያን ወቅት እያደረገ ያለውን ነገር ትርጉም አልተረዱም ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም በይሖዋ ላይ እምነት ነበራቸው። የተሻለ ነገር ማለትም “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ” ይጠብቁ ስለነበር በምድሪቱ ላይ ከሚኖር ከየትኛውም የከተማ መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት አልፈጠሩም። (ዕብራውያን 11:8-10, 13-16) ሆኖም በአብርሃም በኩል የተላለፈው ውርሻ ያለውን ውድ ዋጋ ከፍ አድርገው የተመለከቱት ሁሉም የአብርሃም ዘሮች አልነበሩም።
ውርሻውን ያቃለሉ ሰዎች
8. ኤሳው ለውርሻው ዋጋማነት አድናቆት እንደሌለው ያሳየው እንዴት ነው?
8 የይስሐቅ የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ኤሳው የብኩርና መብቱን ከፍ አድርጎ ሳይመለከት ቀርቷል። ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አድናቆት አላሳየም። በዚህም የተነሳ አንድ ቀን ኤሳው ተርቦ ሳለ የብኩርና መብቱን ለወንድሙ ለያዕቆብ ሸጠለት። የሸጠለት በምንድን ነው? በአንድ መብል እንጀራና ምስር ወጥ ነው! (ዘፍጥረት 25:29-34፤ ዕብራውያን 12:14-17) አምላክ ለአብርሃም የገባለት የተስፋ ቃል ፍጻሜውን የሚያገኝበት ብሔር የመጣው አምላክ ስሙን እስራኤል ብሎ ከቀየረው ከያዕቆብ ነው። ይህ ውርሻ ምን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል?
9. የያዕቆብ ወይም የእስራኤል ዘሮች በመንፈሳዊ ውርሻቸው ምክንያት ያገኙት መዳን ምንድን ነው?
9 ረሃብ በሆነ ጊዜ ያዕቆብና ቤተሰቡ ወደ ግብፅ ሄዱ። እዚያም ተባዝተው ቁጥራቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም በባርነት ቀንበር ሥር ለመውደቅ ተገደዱ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አልረሳም። አምላክ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ የእስራኤልን ልጆች ከባርነት ነፃ አወጣቸውና “ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር” ማለትም ለአብርሃም ቃል ወደ ገባለት ምድር እንደሚያስገባቸው አስታወቃቸው።—ዘጸአት 3:7, 8፤ ዘፍጥረት 15:18-21
10. ከእስራኤል ልጆች ውርሻ ጋር በተያያዘ በሲና ተራራ ምን ተጨማሪ ያልተለመደ ሁኔታ ተፈጽሟል?
10 የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ ምድር እየተጓዙ እያለ ይሖዋ በሲና ተራራ ሰበሰባቸው። እዚያም እንዲህ አላቸው:- “ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ።” (ዘጸአት 19:5, 6) ሕዝቡ በፈቃዳቸው በአንድ ድምፅ ከተስማሙ በኋላ ይሖዋ ሕጉን በመስጠት ለሌላ ለማንም ሕዝብ ያላደረገውን ነገር አደረገላቸው።—መዝሙር 147:19, 20
11. በእስራኤል ልጆች መንፈሳዊ ውርሻ ውስጥ የተካተቱት አንዳንድ ውድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
11 ይህ አዲስ ብሔር ያገኘው መንፈሳዊ ውርሻ ምንኛ ውድ ነው! እውነተኛውን አንድ አምላክ የማምለክ መብት አግኝተው ነበር። ከግብፅ ነፃ ያወጣቸው እርሱ ነው፤ በሲና ተራራ ሕጉን በተቀበሉ ጊዜ የደረሰውን አክብሮታዊ ፍርሃት የሚያሳድር ክስተት በዓይናቸው ተመልክተዋል። በነቢያት አማካኝነት ተጨማሪ ‘የእግዚአብሔር ቃል’ ሲቀበሉ ደግሞ ውርሻቸው ይበልጥ በልጽጓል። (ሮሜ 3:1, 2) ይሖዋ ምሥክሮቹ እንዲሆኑ መርጧቸዋል። (ኢሳይያስ 43:10-12) መሲሐዊው ዘር የሚገለጠው ከእነርሱ ብሔር መካከል ነበር። ሕጉ መሲሑን እንዲጠባበቁ ከማድረጉም ሌላ እርሱን ለይቶ የሚያሳውቅና መሲሑ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ የሚረዳቸው ነበር። (ገላትያ 3:19, 24) ከዚህም በላይ የመንግሥት ካህናትና ቅዱስ ሕዝብ ሆነው ከመሲሐዊው ዘር ጋር ተባብረው ማገልገል የሚችሉበት አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል።—ሮሜ 9:4, 5
12. እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር የገቡ ቢሆንም ምን ነገር ሳያገኙ ቀርተዋል? ለምንስ?
12 ይሖዋ በገባው ቃል መሠረት እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቷቸዋል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ እንደገለጸው እምነት በማጣታቸው ምክንያት የወረሱት ምድር “የእረፍት ቦታ” ሳይሆንላቸው ቀርቷል። አዳምና ሔዋን ከተፈጠሩ በኋላ የጀመረው የአምላክ የዕረፍት ቀን ዓላማ ስላልገባቸውና ከዓላማውም ጋር ተስማምተው ባለመሥራታቸው ምክንያት በብሔር ደረጃ ‘ወደ አምላክ እረፍት’ ሳይገቡ ቀርተዋል።—ዕብራውያን 4:3-10
13. እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ ውርሻቸው አድናቆት ሳያሳዩ በመቅረታቸው በብሔር ደረጃ ምን መብት አጡ?
13 ሥጋዊ እስራኤላውያን የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ሆነው መሲሑ በሚያስተዳድረው ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ ተካፋይ የሚሆኑትን ሰዎች የተሟላ ቁጥር ማስገኘት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ውድ ለሆነው ውርሻቸው አድናቆት ሳያሳዩ ቀሩ። መሲሑ በመጣ ጊዜ ሥጋዊ እስራኤላውያን በጣም የተወሰኑ ናቸው። በዚህም የተነሳ ትንቢት በተነገረለት የካህናት መንግሥት ውስጥ የተካተቱት ጥቂቶች ናቸው። መንግሥቱ ከሥጋዊ እስራኤላውያን ተወሰደና “ፍሬ[ው]ንም ለሚያደርግ ሕዝብ” ተሰጠ። (ማቴዎስ 21:43) ይህ ሕዝብ የትኛው ነው?
በሰማይ የሚገኝ ውርሻ
14, 15. (ሀ) ከኢየሱስ ሞት በኋላ አሕዛብ በአብርሃም ‘ዘር’ አማካኝነት ራሳቸውን መባረክ የጀመሩት እንዴት ነው? (ለ) ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት እንደ ውርሻ የሚቀበሉት ነገር ምንድን ነው?
14 መንግሥቱ የተሰጠው ይህ ሕዝብ በመንፈስ የተወለዱትን 144, 000 የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ያቀፈው ‘የአምላክ እስራኤል’ ማለትም መንፈሳዊ እስራኤል ነው። (ገላትያ 6:16፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-3) ከእነዚህ 144, 000 ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሥጋዊ አይሁዳውያን ሲሆኑ ብዙዎቹ ከአሕዛብ የተመረጡ ናቸው። ‘በዘሩ’ አማካኝነት አሕዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ ይሖዋ ለአብርሃም የገባው ቃል በዚህ መንገድ ፍጻሜውን ማግኘት ጀመረ። (ሥራ 3:25, 26፤ ገላትያ 3:8, 9) በዚህ የመጀመሪያ ፍጻሜ ላይ ከአሕዛብ የተውጣጡ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ሲሆን ይሖዋም መንፈሳዊ ልጆቹ ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች አድርጎ ተቀብሏቸዋል። በዚህም መንገድ እነርሱም ‘የዘሩ’ ሁለተኛ ክፍል ሆነዋል።—ገላትያ 3:28, 29
15 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ወደፊት የዚህ አዲስ ብሔር አባላት ለሚሆኑት አይሁዳውያን በደሙ አማካኝነት የሚጸድቅ አዲስ ቃል ኪዳን አስተዋውቋል። በእርሱ መሥዋዕት ላይ በሚኖራቸው እምነት መሠረት በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚታቀፉት ‘ለዘላለም ፍጹማን’ ይሆናሉ። (ዕብራውያን 10:14-18) ‘ጻድቃን’ ሊባሉና ኃጢአታቸው ይቅር ሊባልላቸው ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 6:11) በዚህ መንገድ አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት እንደነበረው ይሆናሉ። ይሁን እንጂ የሚኖሩት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ አይደለም። ኢየሱስ በሰማይ ቦታ ሊያዘጋጅላቸው እንደሚሄድ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:2, 3) ‘በሰማይ የተጠበቀላቸውን ርስት’ ለመውረስ ምድራዊ ተስፋቸውን ይተዋሉ። (1 ጴጥሮስ 1:4) እዚያ ምን ያደርጋሉ? ኢየሱስ “ለመንግሥት እሾማችኋለሁ” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 22:29
16. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከፊታቸው ምን ዓይነት አስደሳች የአገልግሎት ሥራ ተዘርግቶላቸዋል?
16 ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ሆነው የሚገዙት ሰዎች ከሚሳተፉባቸው ተግባሮች አንዱ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳውን የዓመፅ ርዝራዥ በሙሉ ጠራርጎ በማስወገዱ ሥራ መካፈል ይሆናል። (ራእይ 2:26, 27) የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር ሁለተኛ ደረጃ አባላት እንደመሆናቸው መጠን ለአሕዛብ ሁሉ ፍጹም የሆነ የሕይወት በረከት በማምጣቱ ሥራ ይካፈላሉ። (ሮሜ 8:17-21) ውርሻቸው ምንኛ ውድ ነው!—ኤፌሶን 1:16-18
17. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምድር እያሉም ምን ውርሻ አግኝተዋል?
17 ይሁን እንጂ የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ሁሉንም ውርሻቸውን የሚያገኙት ወደፊት ነው ማለት አይደለም። ሌላ ማንም ሰው ሊያደርግ በማይችለው መንገድ ኢየሱስ እውነተኛውን አንድ አምላክ ይሖዋን እንዲያውቁ ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ 11:27፤ ዮሐንስ 17:3, 26) ‘በይሖዋ መታመን’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ለይሖዋ መታዘዝ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በቃልና በተግባር አስተምሯቸዋል። (ዕብራውያን 2:13፤ 5:7-9) ኢየሱስ የአምላክን ዓላማ በሚመለከት የእውነትን እውቀት በአደራ ሰጥቷቸዋል እንዲሁም ይህን እውቀት ሙሉ በሙሉ መረዳት ይችሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንደሚረዳቸው አረጋግጦላቸዋል። (ዮሐንስ 14:24-26) በአእምሯቸውና በልባቸው ውስጥ የአምላክን መንግሥት አስፈላጊነት ቀርጿል። (ማቴዎስ 6:10, 33) በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲመሠክሩና በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና በምድር ዳርቻዎች ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ አደራ ጥሎባቸዋል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8
እጅግ ብዙ ሰዎች የሚያገኙት ውድ ውርሻ
18. በአብርሃም “ዘር” በኩል አሕዛብ ሁሉ ራሳቸውን እንደሚባርኩ ይሖዋ የገባው ቃል በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
18 የመንፈሳዊ እስራኤል ማለትም የመንግሥቱ ወራሾች “ታናሽ መንጋ” አባላት ቁጥር ሙሉ በሙሉ የተሟላ ይመስላል። (ሉቃስ 12:32) ባለፉት አሥርተ ዓመታት ይሖዋ ትኩረቱን ያደረገው ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎችን በመሰብሰቡ ሥራ ላይ ነው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ‘በዘሩ’ አማካኝነት አሕዛብ ራሳቸውን እንደሚባርኩ ለአብርሃም የገባው ቃል በከፍተኛ ደረጃ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። እነዚህ ብሩካንም ለይሖዋ በደስታ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ እንዲሁም መዳናቸው የተመካው የአምላክ በግ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት ላይ እንደሆነም ያውቃሉ። (ራእይ 7:9, 10) የዚህ ደስተኛ ቡድን አባል እንድትሆን ይሖዋ በደግነት ያቀረበውን ግብዣ ተቀብለሃል?
19. በአሁኑ ጊዜ እየተባረኩ ያሉት አሕዛብ ወደፊት የሚጠባበቁት ውርሻ ምንድን ነው?
19 ይሖዋ የታናሹ መንጋ ክፍል ላልሆኑት ያቀረበው ውድ ውርሻ ምንድን ነው? ይህ ውርሻ የሚገኘው በሰማይ አይደለም። ውርሻው አዳም ለዘሮቹ ማስተላለፍ ይችል የነበረው ምድርን ቀስ በቀስ በሚሸፍነው ገነት ውስጥ ፍጹም ሕይወት አግኝቶ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነው። ‘ሞት፣ ኀዘን፣ ጩኸት ወይም ሥቃይ የማይኖርበት’ ዓለም ይሆናል። (ራእይ 21:4) እንግዲያው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የሚከተለው የአምላክ ቃል የተነገረው ለአንተ ነው:- “በእግዚአብሔር ታመን፣ መልካምንም አድርግ፣ በምድርም ተቀመጥ፣ ታምነህም ተሰማራ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:3, 4, 10, 11, 29
20. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያገኙትን አብዛኛውን መንፈሳዊ ውርሻ ‘ሌሎች በጎችም’ ያገኙት እንዴት ነው?
20 የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” በሰማያዊው መንግሥት የሚተዳደረውን ምድር ይወርሳሉ። (ዮሐንስ 10:16ሀ) ወደ ሰማይ ባይሄዱም እንኳ ቅቡዓኑ ያገኙት አብዛኛው መንፈሳዊ ውርሻ ለእነርሱ ተላልፏል። ሌሎች በጎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ውድ ተስፋዎች ሊገነዘቡ የቻሉት የቅቡዓን አባላት ስብስብ በሆነው ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 24:45-47፤ 25:34) ቅቡዓንና ሌሎች በጎች በአንድነት እውነተኛውን አንድ አምላክ ይሖዋን ያውቃሉ እንዲሁም ያመልካሉ። (ዮሐንስ 17:20, 21) የኢየሱስ መሥዋዕት ላለው ኃጢአትን የማስተሰረይ ዋጋ አምላክን በአንድነት ያመሰግናሉ። በአንድ እረኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር አንድ መንጋ ሆነው ያገለግላሉ። (ዮሐንስ 10:16ለ) ሁሉም ፍቅር የሰፈነበት የአንድ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አባላት ናቸው። የይሖዋና የመንግሥቱ ምሥክሮች የመሆን የጋራ መብት አላቸው። አዎን፣ ራስህን ለአምላክ የወሰንክና የተጠመቅክ የይሖዋ አገልጋይ ከሆንክ ይህ ሁሉ በመንፈሳዊ ውርሻህ ውስጥ የሚካተት ይሆናል።
21, 22. ሁላችንም መንፈሳዊ ውርሻችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከት እንዴት ማሳየት እንችላለን?
21 ይህ መንፈሳዊ ውርሻ ለአንተ ምን ያህል ውድ ነው? ለውርሻው ያለህ አድናቆት የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በሕይወትህ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ የሚገፋፋ ነውን? በክርስቲያናዊ ጉባኤ በሚደረጉ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ እንድትገኝ በቃሉና በድርጅቱ በኩል የሚሰጥህን ምክር በመከተል ይህን በተግባር ታሳያለህን? (ዕብራውያን 10:24, 25) መከራ ቢደርስብህም እንኳን ለውርሻው ያለህ አድናቆት አምላክን ማገልገልህን እንድትቀጥል ይገፋፋሃልን? ለውርሻው ያለህ አድናቆት ውርሻውን እንድታጣ የሚያደርግ ጎዳና እንድትከተል የሚገጥምህን ፈተና መቋቋም የሚያስችልህ ነውን?
22 ሁላችንም ይሖዋ የሰጠንን መንፈሳዊ ውርሻ ከፍ አድርገን እንመልከት። ዓይናችን ወደፊት በሚመጣው ገነት ላይ እንዲያተኩር በማድረግ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በሰጠን መንፈሳዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንካፈል። መላ ሕይወታችን ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ዝምድና ላይ እንዲያተኩር በማድረግ አምላክ የሰጠን ውርሻ ለእኛ ምን ያህል ውድ እንደሆነ አሳማኝ በሆነ መንገድ እናሳያለን። “አምላኬ ንጉሤ ሆይ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ” ብለው ከሚያውጁት ሰዎች መካከል ያድርገን።—መዝሙር 145:1
ምን ብለህ ታብራራለህ?
• አዳም ለአምላክ ታማኝ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ውርሻ ሊያወርሰን ይችል ነበር?
• የአብርሃም ዘሮች ያገኙትን ውርሻ የተመለከቱት እንዴት ነው?
• የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ባገኙት ውርሻ ውስጥ ምን ነገር ተካትቷል?
• እጅግ ብዙ ሰዎች የሚያገኙት ውርሻ ምንድን ነው? ውርሻቸውን እንደሚያደንቁ ሊያሳዩ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአብርሃም ዘሮች ቃል የተገባውን ውድ ውርሻ ተቀብለዋል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያገኘኸውን መንፈሳዊ ውርሻ ታደንቃለህ?