ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ምንጊዜም ይባርካል
የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ምንጊዜም ይባርካል
ቨርነን ዳንከም እንደተናገረው
መክሰሴን በልቼ ስጨርስ እንደተለመደው ሲጋራ ለኮስኩ። ከዚያም ባለቤቴን አይሊንን “የዛሬው ምሽት ስብሰባ እንዴት ነበር?” ስል ጠየቅኋት።
ትንሽ አሰብ አደረገችና እንዲህ አለች:- “አዲስ የተሾሙ ወንድሞችን ስም የያዘ ደብዳቤ ተነበበልን። አንዱ አንተ ነህ። የድምፅ ክፍል አገልጋይ ልትሆን ነው። የደብዳቤው የመጨረሻ ዓረፍተ ነገር ‘ከእነዚህ አዲስ የተሾሙ ወንድሞች መካከል ሲጋራ የሚያጨስ ካለ ኃላፊነቱን መቀበል እንደማይችል የሚገልጽ ደብዳቤ ለማኅበሩ የመላክ ግዴታ አለበት’ ይላል።” a “እንደዚያማ ከሆነ በቃ!” ብዬ ቁርጥ ያለ ውሳኔ አደረግሁ።
ጥርሴን ነክሼ የለኮስኩትን ሲጋራ አጠገቤ ባለው መተርኮሻ ላይ ደፈጠጥኩት። “ለዚህ ኃላፊነት ለምን እንደተመረጥኩ አልገባኝም። ከዚህ በፊት ኃላፊነት አልቀበልም ብዬ አላውቅም፤ ይህንንም ቢሆን እምቢ አልልም።” ሁለተኛ ላለማጨስ ወሰንኩ። ይህ ውሳኔ በክርስቲያናዊና በሙዚቃ ሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። እስቲ እዚህ ውሳኔ ላይ እንድደርስ ያደረጉኝን አንዳንድ ሁኔታዎች ልንገራችሁ።
የልጅነት ሕይወቴ
መስከረም 21, 1914 በቶሮንቶ ካናዳ ተወለድኩ። አፍቃሪና ትጉህ ከሆኑት ወላጆቻችን ከቨርነን እና ሊላ አራት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች መካከል የበኩር ልጅ እኔ ነኝ። የእኔ ታናሽ ዮርክ ሲሆን ከዚያም ኦርላንዶ፣ ዳግላስ አይሊን እና ኮረል አሉ። እናቴ ልክ በዘጠኝ ዓመቴ ቫዮሊን ገዛችልኝና ሃሪስ የሙዚቃ ትምህርት ቤት አስገባችኝ። ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው ቀላል ባይሆንም እናቴና አባቴ የመጓጓዣና የትምህርት ቤት ይከፍሉልኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ቶሮንቶ በሚገኘው ሮያል የሙዚቃ ትምህርት ቤት የሙዚቃን ቲዮሪና ስልት ያጠናሁ ሲሆን በ12 ዓመቴ መሃል ከተማ ባለውና ስመ ጥር በሆነው ማሲ የሙዚቃ አዳራሽ በተደረገው ከተማ አቀፍ የሙዚቃ ውድድር ተካፈልኩ።
በውድድሩ አንደኛ በመውጣቴ ከአዞ ቆዳ የተሠራ ማኅደር ያለው ግሩም ቫዮሊን ተሸለምኩ።እንዲሁም ከጊዜ በኋላ ፒያኖና ደብል ባስ ቫዮሊን መጫወት ተማርኩ። ብዙውን ጊዜ በቡድን ሆነን ዓርብና ቅዳሜ ምሽት ላይ በትናንሽ ግብዣዎችና ተማሪዎች በሚያዘጋጁት ፕሮግራም ላይ እንጫወት ነበር። ከአይሊን ጋር የተዋወቅኩት በእንደዚህ ዓይነቱ የተማሪዎች ዝግጅት ላይ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ባጠናቀቅሁበት ዓመት በከተማው ከሚገኙ ብዙ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ተጫውቻለሁ። ትምህርቴን ካጠናቀኩ በኋላ ፈርዲ ማውሪ በሚባል የሙዚቃ ቡድን ውስጥ እንድታቀፍ የተጋበዝኩ ሲሆን እስከ 1943 ድረስ ጥሩ ክፍያ ያለው ቋሚ ሥራ ሆኖልኝ ነበር።
ይሖዋን ማወቅ
ወላጆቼ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሰሙት አንደኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ ጥቂት ቀደም ብሎ አባቴ መሃል ቶሮንቶ በሚገኝ አንድ የገበያ አዳራሽ ውስጥ በሚሠራበት ጊዜ ነበር። ምሳ በሚበሉበት ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት ስም ነው) የሆኑ ሁለት ሠራተኞች እርስ በርስ ያደረጉትን ጭውውት አዳምጦ ማታ ወደ ቤት ሲመለስ የሰማውን ለእናቴ ይነግራታል። ከዓመታት በኋላ በ1927 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቶሮንቶ ካናዳ ብሔራዊ የኤግዝቢሽን ማዕከል ውስጥ በሚገኘው ግዙፍ ስታዲየም ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ አደረጉ። ከኤግዝቢሽኑ የምዕራብ በር ሁለት መደዳ ርቆ በሚገኘው ቤታችን ውስጥ ከኦሃዩ፣ ዩ ኤስ ኤ የመጡ 25 እንግዶች አርፈው ነበር።
ከዚያ በኋላ ኤዳ ብሌስቶ የምትባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አዲስ የወጡ ጽሑፎችን እየያዘች ዘወትር እናቴን ትጠይቃት ጀመር። አንድ ቀን “ወይዘሮ ዳንከም፣ ጽሑፎችን ማምጣት ከጀመርኩ የተወሰነ ጊዜ ሆኖኛል። ለመሆኑ አንብበሻቸው ታውቂያለሽ?” ስትል ጠየቀቻት። እናቴ ስድስት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት ቢኖርባትም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መጽሔቶቹን ለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ አደረገች። ከዚያም በኋላ ንባቧን አቋርጣ አታውቅም። እኔ ግን ለእነዚህ ጽሑፎች ብዙም ትኩረት አልሰጠኋቸውም ነበር። ጥረቴ ትምህርቴን መጨረስ ሲሆን የሙዚቃ ሥራው ጭልጥ አድርጎ ወስዶኝ ነበር።
እኔና አይሊን ሰኔ 1935 በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጋባን። በ13 ዓመቴ ከዩናይትድ ቸርች ከቀረሁበት ጊዜ አንስቶ የየትኛውም ሃይማኖት አባል አልነበርኩም። የይሖዋ ምሥክር ባልሆንም በጋብቻዬ መዝገብ ላይ የይሖዋ ምሥክር ብዬ አስሞላሁ።
ወደፊት ልጆች ወልደን እናሳድጋለን የሚል ሐሳብ ስለነበረን ጥሩ ወላጆች ለመሆን እንፈልግ ነበር። ስለዚህ አዲስ ኪዳንን አንድ ላይ ማንበብ ጀመርን። የማንበብ ፍላጎቱ ቢኖረንም ሌሎች ነገሮች እንቅፋት ሆነውብን ነበር። ትንሽ ቆይተን እንደገና ለመጀመር ሞከርን፤ ግን አሁንም አልተሳካም። ከዚያም በ1935 ለሚከበረው የገና በዓል የአምላክ በገና (እንግሊዝኛ) የሚለው መጽሐፍ በስጦታ መጣልን። ባለቤቴ “ይገርማል፣ እናትህ የላኩልን የገና ስጦታ ደግሞ ለየት ያለ ነው” አለች። የሆነው ሆኖ እኔ ወደ ሥራ ከሄድኩ በኋላ መጽሐፉን ስታነበው በጣም ደስ አላት። ለተወሰነ ጊዜ እኔ ስለ ሁኔታው የማውቀው ነገር አልነበረም። ልጆች ለማሳደግ የነበረን ፍላጎት አልተሳካም። የካቲት 1, 1937 የተወለደችው ልጃችን ሞተች። የተሰማን ሐዘን በጣም ጥልቅ ነበር!
በዚህ ጊዜ ቤተሰቦቼ በስብከቱ ሥራ በንቃት ይሳተፉ የነበረ ሲሆን ከቤተሰባችን መካከል ኮንሶሌሽን (አሁን ንቁ!) የሚባለውን መጽሔት ኮንትራት ያላስገባው አስፋፊ አባቴ ብቻ እንደሆነ ሰማሁ። የዚያ ወር የመስክ አገልግሎት ግብ ኮንትራት ማስገባት ነበር። ምንም እንኳ የማኅበሩን ጽሑፎች አንብቤ ባላውቅም አባቴ ስላሳዘነኝ “እሺ አባባ፣ እኔን ኮንትራት አስገባኝ። ከዚያ ከሌሎቹ እኩል ትሆናለህ” አልኩት። በጋ ስለገባ የሙዚቃ ቡድናችን በመዝናኛ ቦታዎች ለመጫወት ከከተማው ወጣ። ኮንሶሌሽን መጽሔት በፖስታ ቤት በኩል ይመጣ ጀመር። በመከር ወቅት የሙዚቃ ቡድናችን ወደ ቶሮንቶ ተመለሰ። መጽሔቱ በአዲሱ አድራሻችን መምጣቱን ቀጥሎ ነበር። እኔ ግን ማንበብ ይቅርና አንዱንም ከፖስታው አውጥቼው አላውቅም።
በአንድ የገና እረፍት ወቅት የተከማቹትን መጽሔቶች ተመለከትኩና ገንዘብ እስካወጣሁበት ድረስ ምን እንደሚል ለማወቅ ቢያንስ አንዳንዶቹን ማንበብ ይገባኛል ስል ወሰንኩ። በመጀመሪያ የከፈትኩት መጽሔት ትንሽ አስደነገጠኝ። በፖለቲካ ዓለም የሚፈጸመውን ሴራና በጊዜው የነበረውን ሙስና የሚያጋልጥ ነበር። ስላነበብኳቸው ነገሮች አብረውኝ ለሚሠሩ ሙዚቀኞች መናገር ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ይህ እውነት አይደለም በማለት ስለተከራከሩኝ ላለመረታት ስል ብዙ ማንበብ ነበረብኝ። ሳይታወቀኝ ስለ ይሖዋ መመስከር ጀመርኩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ግሩም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ማንበቤን አላቋረጥኩም።—ማቴዎስ 24:45
በአዘቦት ቀናት ሥራው ፋታ ባይሰጠኝም እሁድ ዕለት በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ከአይሊን ጋር መገኘት ጀመርን። በ1938 አንድ እሁድ ቀን ጉባኤ እንደደረስን ሁለት አረጋውያን እህቶች ሰላም አሉንና አንደኛዋ “ወንድም፣ ከይሖዋ ጎን ለመቆም እርምጃ ወስደሃል? አርማጌዶን እያንዣበበ ነው!” አለችኝ። ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አውቃለሁ፤ በዚህ ድርጅት እየተጠቀመ እንዳለም አምናለሁ። የዚህ ድርጅት አባል ለመሆን ፍላጎት ስላደረብኝ ጥቅምት 15, 1938 ተጠመቅኩ። አይሊን ከስድስት ወራት በኋላ ተጠመቀች። ሁሉም የቤተሰባችን አባላት የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸው በጣም ያስደስተኛል።
ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በመተባበሬ ታላቅ ደስታ አግኝቼአለሁ! ከእነርሱ ጋር ለመቀላቀል ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ጉባኤ መሄድ ካልቻልኩ ሁልጊዜ ስብሰባው እንዴት እንደነበረ ለማወቅ እጓጓለሁ። በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ያ ልዩ ምሽት ለይሖዋ በማቀርበው አገልግሎት ረገድ ትልቅ ለውጥ ያደረግኩበት ቀን ነው።
ትልቅ ለውጥ ያደረግንበት ጊዜ
ግንቦት 1, 1943 ትርጉም ያለው ሌላ ለውጥ አደረግን። መስከረም 1942 በክሌቭላንድ ኦሃዩ በተደረገው የአዲሱ ዓለም ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ በተባለ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኘን። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ኖር ማቆሚያ የሌለው የሚመስለው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጧጡፎ እያለ “ሰላም—ዘላቂ ሊሆን ይችላልን?” በሚል ርዕስ በድፍረት ያቀረበውን የሚመስጥ ንግግር አዳመጥን። ከጦርነቱ በኋላ ታላቅ የስብከት ሥራ የሚከናወንበት የሰላም ጊዜ እንደሚኖር ከራእይ ምዕራፍ 17 ላይ እየጠቀሰ ሲያብራራ በደንብ ትዝ ይለናል።
ይበልጥ የነካን ግን ወንድም ኖር ከዚያ ቀደም ብሎ “ዮፍታሔ እና ስዕለቱ” በሚል ርዕስ ያቀረበው ንግግር ነበር። ከዚያም ተጨማሪ አቅኚዎች እንደሚያስፈልጉ የሚገልጽ ጥሪ ቀረበ! እኔና አይሊን ተያየንና በአንድነት “ይህ ለእኛ ነው!” አልን። በዚያ የተገኙ ሌሎችም እንዲሁ ተሰምቷቸዋል። በጣም አስፈላጊ የሆነውን ሥራ ለመጀመር ወዲያውኑ እቅድ አወጣን።
ከሐምሌ 4, 1940 ጀምሮ ካናዳ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር። ግንቦት 1, 1943 አቅኚነት ስንጀምር ስለ ይሖዋ መመስከርም ሆነ በመስክ አገልግሎት የማኅበሩን ጽሑፎች ማበርከት ሕገ ወጥ ተግባር እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ለማከናወን ስንወጣ የምንይዘው የኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብቻ ነበር። በመጀመሪያው የአቅኚነት ምድባችን በፓሪ ሳውንድ፣ ኦንታሪዮ ከደረስን ከጥቂት ቀናት በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው አብሮን የሚያገለግል ስቲዋርት ማን የሚባል ተሞክሮ ያለው አቅኚ ላከልን። እንዴት ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት ነበር! ወንድም ማን ሥርዓታማና ፈገግታ የማይለየው ሰው ነበር። ከእርሱ ብዙ ተምረናል፤ አብረንም አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል። ማኅበሩ ወደ ሂሚልተን ከተማ ሲቀይረን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንመራ ነበር። ምንም እንኳን ዕድሜዬ ከወጣው ገደብ ቢያልፍም ለውትድርና መለመሉኝ። የሠራዊቱ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ስላልነበርኩ ታኅሣሥ 31, 1943 ተይዤ ታሰርኩ። ጉዳዩ በፍርድ ቤት ከታየ በኋላ በውትድርና አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ሌላ አገልግሎት እንዲሰጡ ወደሚደረግበት ካምፕ እንድገባ ተፈርዶብኝ እስከ ነሐሴ 1945 በዚያ ቆየሁ።
ከዚያ ከወጣሁ በኋላ እኔና አይሊን ወዲያውኑ በኮርንዎል ኦንታሪዮ አዲስ የአቅኚነት ምድብ ተሰጠን። ብዙም ሳይቆይ በኪዩቤክ ልዩ የፖሊስ ችሎት የተያዙ ጉዳዮች ስለነበሩ የማኅበሩ የሕግ ክፍል ወደዚያ ላከን። ይህ የሆነው ኪዩቤክ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጀመረው ስደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ዱፕለሲስ በሚባለው ዘመን ነው። ወንድሞቻችንን ለመርዳት በየሳምንቱ ለብዙ ቀናት በአራት የተለያዩ ፍርድ ቤቶች እገኝ ነበር። እነዚህ በእርግጥም ለየት ያለ ስሜት የሚፈጥሩና እምነት የሚያጠነክሩ ጊዜያት ነበሩ።
በ1946 በክሌቭላንድ ከተደረገው የአውራጃ ስብሰባ
በኋላ እኔና ባለቤቴ መላውን ካናዳ የሚያዳርስ የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ላይ ተመደብን። ሁኔታዎች በፍጥነት ይለዋወጡ ነበር። በ1948 በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 11ኛ ክፍል እንድንሳተፍ ተጋበዝን። አስተማሪዎቻችን ወንድም አልበርት ሽሮደርና ወንድም ማክስዌል ፍሬንድ ሲሆኑ ከ108 ተማሪዎች ውስጥ 40ዎቹ ቅቡዓን ወንድሞችና እህቶች ናቸው። ለረጅም ዓመታት ይሖዋን ካገለገሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶች መካከል መገኘት በእርግጥም ልዩና የሚክስ ተሞክሮ ነበር!አንድ ቀን ወንድም ኖር ከብሩክሊን መጥቶ ጎበኘን። ባቀረበው ንግግር ላይ የጃፓንን ቋንቋ ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ 25 ተማሪዎች እንደሚያስፈልጉ ተናገረ። በዚህ ጊዜ 108ቱም ተማሪዎች ፈቃደኛነታቸውን ገለጹ! ማን መማር እንዳለበት የመምረጡ ሥራ የፕሬዚዳንቱ ሆነ። የተመረጡት ተማሪዎች ያገኙትን ስኬት ስመለከት ምርጫው የይሖዋ እጅ ነበረበት ብዬ አስባለሁ። በዚያ ወቅት ከተመረጡትና ሥራውን በጃፓን ለመጀመር መብት ካገኙት 25 ወንድሞችና እህቶች መካከል አብዛኞቹ አሁንም እዚያው በማገልገል ላይ ናቸው። እርግጥ ነው፣ በዕድሜ ገፍተዋል፤ ሆኖም እስከአሁን እዚያው ናቸው። ሎይድ እና ሜልባ ባሪን የመሳሰሉ አንዳንድ ሚስዮናውያን ግን ወደ ሌላ አገር ተቀይረዋል። ሎይድ ባለፈው ዓመት እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የአስተዳደር አካል አባል በመሆን አገልግሏል። ከእነዚህ ሁሉ ጋር ይሖዋ በሚሰጠው በረከት አብረን ተደስተናል።
የምንመረቅበት ቀን ደረሰና ጃማይካ ተመደብን። ይሁን እንጂ በኪዩቤክ መፍትሔ ያላገኙ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ስለነበሩ ወደ ካናዳ እንድንመለስ ተነገረን።
የሙዚቃ ተሳትፎዬን ማሳደግ!
በአቅኚነት አገልግሎት ምክንያት ሙዚቃ የተውኩ ቢሆንም ሙዚቃ ግን የተወኝ አይመስልም ነበር። በሚቀጥለው ዓመት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የነበረው ናታን ኖርና ጸሐፊው ሚልተን ሄንሽል ቶሮንቶ ወደሚገኘው ማፕል ሊፍ ጋርደን መጡ። ወንድም ኖር “ጊዜው እናንተ ከምታስቡት ይበልጥ ገፍቷል!” በሚል ርዕስ ያቀረበው የሕዝብ ንግግር ሁላችንንም አነቃቅቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ የአውራጃ ስብሰባውን የሙዚቃ ቡድን እንድመራ ተጋበዝኩ። የመንግሥት አገልግሎት የመዝሙር መጽሐፍ (1944) (እንግሊዝኛ) ላይ የሚገኙትን አንዳንድ ተወዳጅ መዝሙሮች በብዙ የሙዚቃ መሣሪያ አቀነባበርናቸው። ወንድሞች የወደዱት ይመስላል። የቅዳሜው ፕሮግራም ከሰዓት በኋላ ሲደመደም ለእሑድ የምናቀርበውን ዝግጅት ተለማመድን። ወንድም ሄንሽል አዳራሹን አቋርጦ ወደ እኛ አቅጣጫ ሲመጣ አየሁትና ሙዚቃውን አስቁሜ ወደ እሱ ሄድኩ። ወንድም ሄንሽል “በቡድኑ ውስጥ ስንት ሙዚቀኞች አሉህ?” ሲል ጠየቀኝ። “ሁላችንም ስንገኝ ወደ 35 እንሆናለን” ብዬ መለስኩለት። “ደህና፣ በመጪው በጋ በኒው ዮርክ ከዚህ እጥፍ ይኖርሃል” አለኝ።
ሆኖም በጋው ከመድረሱ በፊት ወደ ብሩክሊን ተጠራሁ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት አይሊን በመጀመሪያ አብራኝ መምጣት አልቻለችም። አዲሱ 124 ኮሎምቢያ ሃይትስ ሕንፃ ገና ስላላለቀ በቀድሞው ሕንፃ ላይ በአንዲት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ከሁለት ቅቡዕ ወንድሞች ጋር ተመደብኩ። አንደኛው ፔን የሚባል አረጋዊ ወንድም ሲሆን ሌላው ደግሞ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅኩት ካርል ክላይን ነበር። ክፍሉ ጠቦን ነበር? አዎ። የሆነ ሆኖ ተስማምተን እንኖር ነበር። በዕድሜ የገፉት ወንድሞች ታጋሽና ቻይ ነበሩ። እኔም ችግር ላለመፍጠር እጠነቀቅ ነበር! የአምላክ መንፈስ ምን ሊያከናውን እንደሚችል ጥሩ ትምህርት አግኝቼአለሁ። ከወንድም ክላይን ጋር መተዋወቄና አብሬው መሥራቴ ብዙ በረከቶች አስገኝቶልኛል! ሁልጊዜ ደግና ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ ነበር። አብረን በጥሩ ሁኔታ የሠራን ሲሆን ላለፉት 50 ዓመታት የቅርብ ጓደኞች ሆነን ቆይተናል።
በ1950, 1953, 1955 እና 1958 በያንኪ ስታዲዮም በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሙዚቃ ቡድኑን የማገዝ እንዲሁም በ1963 ፓሳዴና ካሊፎርኒያ በሮዝ ቦውል ስታዲዮም በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከአል ካቨሊን ጋር በሙዚቃ ቡድኑ ውስጥ በኃላፊነት የመሥራት መብት አግኝቻለሁ። በ1953 በያንኪ ስታዲየም በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እሁድ ዕለት ከቀረበው የሕዝብ ንግግር በፊት የሙዚቃ ፕሮግራም ቀርቦ ነበር። ኤሪክ ፍሮስት “እናንተ ምሥክሮች ወደፊት ግፉ!” በሚል ርዕስ ራሱ ያቀነባበረውን መዝሙር እኛ በሙዚቃ መሣሪያ እያጀብናት እንድትዘምር ጥሩ ድምፅ ያላት ኤዲት ሺምዮኒክን (ከጊዜ በኋላ ቫይጋንት ተብላለች) ጋበዛት። ቀጥሎ የአፍሪካ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መረዋ ድምፅ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሰማ በጣም ተደሰትን። ሃሪ አርነት የተባለ ሚስዮናዊ ከሰሜን ሮዴዥያ (ከዛሬዋ ዛምቢያ) የቴፕ ቅጂ አምጥቶ ስለነበር ይበልጥ ደስ አለን። ድምፁ በስታዲዮሙ ከዳር እስከ ዳር ይሰማ ነበር።
በ1966 የተዘጋጀውን የመዝሙር መጽሐፍ ሙዚቃ መቅዳት
“በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” (እንግሊዝኛ) የሚለው ባለ ሐምራዊ ሽፋን የመዝሙር መጽሐፍ ትዝ ይላችኋል? ወንድም ኖር በዚህ መጽሐፍ ዝግጅት ማገባደጃ ላይ “አንዳንድ የሙዚቃ ቅጂዎችን እንሠራለን። ጥቂት ቫዮሊኖችንና ዋሽንቶችን ያካተተ አነስተኛ የሙዚቃ ቡድን እንድታደራጅ እፈልጋለሁ። ‘ጡሩንባውን የሚነፋ ሰው አልፈልግም’!” ሲል ተናገረ። ቤቴል የሚገኘውን የመንግሥት አዳራሽ እንደ ስቱዲዮ ልንጠቀምበት አሰብን። ነገር ግን ያሳሰቡን አንዳንድ ሁኔታዎች ነበሩ። ድምፅ እንዳያስተጋባ ሙሉ በሙሉ ድፍን ያልሆነውን ግድግዳ፣ የጡብ ወለሉንና ታጣፊ የብረት ወንበሮቹን ምን ልናደርጋቸው እንችላለን? የሚገጥሙንን የድምፅ ችግሮች ለማስወገድ ማን ሊረዳን ይችላል? አንድ ሰው “ቶሚ ሚሼል በኤቢሲ ኔትወርክ ስቱዲዮ ስለሚሠራ” እሱ ሊረዳን እንደሚችል ጠቆመን። ወንድም ሚሼልን ስናማክረው ሊረዳን ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸልን።
ሙዚቃውን መቅዳት የምንጀምርበት የመጀመሪያው ቅዳሜ ጠዋት ደረሰ። ሙዚቀኞቹን ማስተዋወቅ ሲጀመር አንድ ወንድም ጡሩምባ ይዞ አየሁት። “ጡሩንባውን የሚነፋ ሰው አልፈልግም” የሚለው የወንድም ኖር ማስጠንቀቂያ ትዝ አለኝ። ታዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ? ወንድም ጡሩምባውን አውጥቶ ሲገጥምና ሲሞክር አየሁት። ይህ ወንድም ቶም ሚሼል ሲሆን ለሙከራ ያሰማቸው ድምፆች በጣም አስደሳች ነበሩ። ከጡሩምባው የሚወጣው ድምጽ ቫዮሊን ይመስል ነበር! ‘ይህ ወንድም ያስፈልገናል’ ብዬ አሰብኩ። ወንድም ኖርም አልተቃወመም።
በሙዚቃ ቡድኑ ውስጥ ያሉን አባላት ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሙዚቀኞችና አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች ነበሩ። በመካከላችን የሚያውክ ሰው አልነበረም! ሙዚቃውን መቅዳት ትዕግሥት አስጨራሽ ሥራ ነበር። ሆኖም የሚያማርር አልነበረም። ሥራው ሲጠናቀቅ ሁላችንም ተላቀስን። በሥራው የተካፈሉትን ሁሉ በጣም አቀራርቦአቸዋል። ሁላችንም ይህን መብት በማግኘታችን ተደስተናል። ይሖዋ የተመሰገነ ይሁንና ሥራውን አጠናቅቀናል።
በተጨማሪ መብቶች መባረክ
ዛሬ ከብዙ ዓመታት በኋላም የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን ቀጥያለሁ። የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ለ28 ዓመታት የሠራሁ ሲሆን ሁሉም አስደሳች ነበሩ። ከዚያም በኦንታሪዮ በኖርቫል የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ለአምስት ዓመት ያህል የአስተዳደር ሥራ ሠርቻለሁ። እኔና አይሊን ዘወትር ቅዳሜና እሁድ የወረዳ ስብሰባዎች እንዲሁም በውጪ አገር ቋንቋ የአውራጃ ስብሰባዎች ይደረጉ ስለነበር ብዙ የሚሠራ ነገር ነበረን። በ1979/80 ንድፍ አውጪዎችና መሐንዲሶች በሃልተን ሂልስ ሊገነባ ለታቀደው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ የንድፍ ሥራዎችን ያከናወኑት በዚህ የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ነበር። በአዳራሹ ውስጥ የነበረንን ሥራ ካጠናቀቅን በኋላ ከ1982 እስከ 1984 በብሩክሊን በሙዚቃው መስክ ተጨማሪ ተሳትፎ የማደርግበት ምድብ አገኘሁ።
ውዷ ባለቤቴ ሰኔ 17, 1994 ጋብቻችን 59ኛውን ዓመት ከሞላ ከሰባት ቀን በኋላ አረፈች። በአቅኚነት 51 ዓመታት አብረን አሳልፈናል።
በሕይወቴ ያሳለፍኩትን ተሞክሮ መለስ ብዬ ስመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የላቀ ውድ መመሪያ እንደሆነልኝ አስታውሳለሁ። አንዳንድ ጊዜ የአይሊንን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበብኩ በጥቅሱ፣ በተወሰኑት ሐረጎች እንዲሁም በአንዳንድ ቃላት ላይ ያደረገችውን ምልክት እየተመለከትኩ ምን ነገር ልቧን እንደነካው ማሰላሰል ያስደስተኛል። እኔም እንደ አይሊን ለእኔ የተለየ ትርጉም ያዘሉ ናቸው የምላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉኝ። አንደኛው ለይሖዋ የቀረበውን አስደሳች ጸሎት የያዘው መዝሙር 137 ነው። “ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺን ብረሳሽ፣ በገና የምጫወትበት ቀኝ እጄ ይክዳኝ፤ አንቺን ባላስታውስሽና ታላቅ ደስታዬ አድርጌ ባልቆጥርሽ የመዘመር ችሎታዬ ይክዳኝ” ይላል። (መዝሙር 137:5, 6 የ1980 ትርጉም ) ሙዚቃን የምወድ ቢሆንም ታላቅ ደስታ የማገኘው የተሟላና አርኪ ሕይወት እንድመራ የባረከኝን ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሰኔ 1, 1973 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከዚያ ጊዜ አንስቶ አንድ ሰው ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ከመሆኑ በፊት ሲጋራ ማቆም ያለበት ለምን እንደሆነ አብራርቷል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1947 ከአይሊን ጋር
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀደም ባሉት ዓመታት የሙዚቃ ቅጂ ሲከናወን