በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለማንበብና ለማጥናት ጊዜ መዋጀት

ለማንበብና ለማጥናት ጊዜ መዋጀት

ለማንበብና ለማጥናት ጊዜ መዋጀት

“ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።”​—⁠ኤፌሶን 5:​16

1. ጊዜያችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት መመደቡ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው? ጊዜያችንን የምንጠቀምበት መንገድ ስለ እኛ ምን ሊጠቁም ይችላል?

 ጊዜን መምረጥ ጊዜን መቆጠብ ነው” የሚል አንድ አባባል አለ። ጊዜ መድቦ ሥራዎቹን የሚያከናውን ሰው ጊዜውን በተሻለ መንገድ ሊጠቀምበት ይችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው” በማለት ጽፏል። (መክብብ 3:​1) ሁላችንም ያለን ጊዜ እኩል ነው። ልዩነት የሚያመጣው አጠቃቀማችን ላይ ነው። ቅድሚያ የምንሰጣቸው ነገሮችና ጊዜያችንን የምንከፋፍልበት መንገድ የትኞቹን ነገሮች አብልጠን እንደምንወድ በተወሰነ መጠን ይገልጣሉ።​—⁠ማቴዎስ 6:​21

2. (ሀ) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን በሚመለከት ምን ተናግሯል? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን ብንመረምር ጥሩ ይሆናል?

2 ለመብላትና ለመተኛት ጊዜ ማጥፋታችን የማይቀር ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ፍላጎቶች አካላችን ሊያገኛቸው የሚገቡ ነገሮች ናቸው። ሆኖም ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንስ? መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንም መሟላት እንዳለባቸው እናውቃለን። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:​3 NW ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ መመደብ አስፈላጊ መሆኑን ዘወትር የሚያሳስበን በዚህ የተነሳ ነው። (ማቴዎስ 24:​45) ይህን ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ትገነዘብ ይሆናል። ሆኖም መጽ​ሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወይም ለማንበብ ጊዜ እንደሌለህ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። እንደዚያ የሚሰማህ ከሆነ የአምላክን ቃል ለማንበብ፣ የግል ጥናት ለማድረግና ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል አንዳንድ መንገዶችንና ዘዴዎችን እንመርምር።

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት ጊዜ ማግኘት

3, 4. (ሀ) የጊዜ አጠቃቀማችንን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ምክር ሰጥቷል? ይህስ ምንን ይጨምራል? (ለ) ጳውሎስ ‘ዘመኑን ዋጁ’ ብሎ ሲመክረን ምን ማለቱ ነው?

3 ከምንኖርበት ጊዜ አንጻር ሁላችንም የሚከተሉትን የሐዋርያው ጳውሎስን ቃላት በጥንቃቄ መከተል ይኖርብናል:- “እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።” (ኤፌሶን 5:​15-17) እርግጥ ነው፣ ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይህ ምክር ለጸሎት፣ ለጥናት፣ ለስብሰባዎችና ‘በመንግሥቱ ምሥራች’ ስብከት ሥራ የተቻለውን ያህል ሙሉ ተሳትፎ ማድረግን ጨምሮ መላውን የሕይወታችንን ዘርፍ ይዳስሳል።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20

4 ዛሬ ያሉ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብንና ጥልቀት ያለው ጥናትን የሕይወታቸው ክፍል ማድረግ የተሳናቸው ይመስላል። በቀናችን ላይ ሰዓት መጨመር እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ስለዚህ ጳውሎስ የሰጠው ምክር የተለየ ትርጉም የሚያስተላልፍ መሆን አለበት። “ዘመኑን ዋጁ” የሚለው ግሪክኛው ሐረግ አንድን ነገር ለማግኘት የሆነ ነገር መክፈል የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ደብልዩ ኢ ቫይን ኤክዝፖዚታሪ ዲክሽነሪ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ “አንዴ ካመለጠን መልሰን ማግኘት ስለማንችል እያንዳንዱን አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም፣ እያንዳንዱን አጋጣሚ ጠቃሚ ለሆነ ነገር ማዋል” የሚል ትርጉም ሰጥተውታል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት ጊዜ የምንዋጀው ከምን ወይም ከየት ነው?

ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ማስቀደም አለብን

5. ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር መለየት’ ያለብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

5 ከሰብዓዊ ግዴታዎቻችን በተጨማሪ ልንፈጽማቸው የሚገቡ በርካታ መንፈሳዊ ግዴታዎች አሉብን። ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ‘የጌታ ሥራ ሁልጊዜ የበዛልን ነን።’ (1 ቆሮንቶስ 15:​58) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የነበሩት ክርስቲያኖች ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር እንዲለዩ’ መክሯቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:​10 NW ) ይህም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስቀደም ማለት ነው። መንፈሳዊ ነገሮች ምንጊዜም ከቁሳዊ ነገሮች መቅደም አለባቸው። (ማቴዎስ 6:​31-33) ሆኖም፣ መንፈሳዊ ግዴታዎቻችንን በምንወጣበት ጊዜም ሚዛናችንን መጠበቅ ይኖርብናል። ለተለያዩ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ጊዜያችንን ማብቃቃት የምንችለው እንዴት ነው? ክርስቲያኖች ሊያከናውኗቸው ከሚገቧቸው ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች’ መካከል የግል ጥናትና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ቸል እንደሚባሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሪፖርት ያደርጋሉ።

6. ሰብዓዊ ሥራን ወይም የቤት ውስጥ ሥራዎችን በተመለከተ ጊዜ መዋጀት ምን ነገር ማድረግን ሊጨምር ይችላል?

6 ጊዜን መዋጀት ማለት “እያንዳንዱን አጋጣሚ በሚገባ መጠቀምን” እና “እያንዳንዱን አጋጣሚ ጠቃሚ ለሆነ ነገር ማዋልን” እንደሚያጠቃልል ቀደም ሲል ተመልክተናል። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና የጥናት ልማዳችን ደካማ ከሆነ ጊዜያችንን የምናሳልፈው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ራሳችንን ብንመረምር ጥሩ ይሆናል። ሰብዓዊ ሥራችን አብዛኛውን ጊዜያችንንና ጉልበታችንን የሚወስድብን ከሆነ ጉዳዩን አንስተን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል። (መዝሙር 55:​22) ጥናትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን ጨምሮ ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ለማከናወን የሚያስችል ጊዜ ለማግኘት አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንችል ይሆናል። የሴት ሥራ አያልቅም የሚባል ትክክለኛ አባባል አለ። ስለዚህ ክርስቲያን እህቶችም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ቅድሚያ መስጠትና መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና በቁም ነገር ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ መመደብ አለባቸው።

7, 8. (ሀ) ለንባብና ለጥናት የሚሆን ጊዜ በአብዛኛው ከየትኞቹ እንቅስቃሴዎች ላይ መዋጀት ይቻላል? (ለ) የመዝናናት ዓላማ ምንድን ነው? ይህን ማስታወሳችንስ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

7 በጥቅሉ ብዙዎቻችን እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ለጥናት የሚሆን ጊዜ መዋጀት እንችላለን። ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ዓለማዊ መጽሔቶችን ወይም ጋዜጦችን በማንበብ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመመልከት፣ ሙዚቃ በመስማት ወይም የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት ምን ያህል ጊዜ አጠፋለሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ከማሳልፈው ጊዜ ይልቅ ኮምፒዩተር ላይ የማሳልፈው ጊዜ ይበልጣልን?’ ጳውሎስ “የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች [“ምክንያታዊነት የጎደላችሁ፣” NW ] አትሁኑ” ብሏል። (ኤፌሶን 5:​17) በርካታ ምሥክሮች የግል ጥናት ለማድረግና መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ የሚያስችል በቂ ጊዜ እንዳይኖራቸው የሚያደርጋቸው ዋነኛ ምክንያት ቴሌቪዥን በመመልከት በሚያጠፉት ጊዜ ረገድ ምክንያታዊ አለመሆናቸው ይመስላል።​—⁠መዝሙር 101:​3፤ 119:​37, 47, 48

8 አንዳንዶች መቼም ሁልጊዜ ማጥናት እንደማይችሉና አልፎ አልፎ መዝናናት እንደሚያስፈልጋቸው ይናገሩ ይሆናል። ይህ እውነት መሆኑ ባይካድም ለመዝናናት የምናሳልፈውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ወይም በማንበብ ከምናሳልፈው ጊዜ ጋር ብናወዳድር ጥሩ ይሆናል። ውጤቱ የሚያስገርም ሊሆን ይችላል። መዝናናትና ማረፍ አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም ከልክ ማለፍ የለባቸውም። የመዝናናት ዓላማ ለተጨማሪ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ እኛን ማደስ ነው። አብዛኞቹ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና የቪዲዮ ጨዋታዎች አንድ ሰው ድክም እንዲለው የሚያደርጉ ሲሆኑ የአምላክን ቃል ማንበብና ማጥናት ግን መንፈስን የሚያድስና የሚያበረታ ነው።​—⁠መዝሙር 19:​7, 8

አንዳንዶች ለጥናት የሚሆን ጊዜ የሚያገኙት እንዴት ነው?

9. ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር​ —⁠1999 ቡክሌት ላይ ያለውን ምክር መከተሉ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

9 ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር የተባለው ቡክሌት በ1999 እትሙ መቅድም ላይ እንዲህ ይላል:- “በዚህ ቡክሌት ውስጥ ያለውን ጥቅሱንና ሐሳቡን ጠዋት ላይ ማንበቡ ጥቅም አለው። ታላቁ አስተማሪ ይሖዋ በትምህርቶቹ አማካኝነት ያነቃህ ያክል ሆኖ እንዲሰማህ ያደርጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በየዕለቱ ጠዋት ከይሖዋ ትምህርቶች ጥቅም እንደሚያገኝ በትንቢታዊ ሁኔታ ተገልጿል:- ‘[ይሖዋ] ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፣ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል።’ ይህ ዓይነቱ ትምህርት ኢየሱስ ‘የደከመውን በቃል እንዴት እንደሚደግፍ ያውቅ ዘንድ’ ‘የተማሩትን ምላስ’ እንዲያገኝ አስችሎታል። (ኢሳ. 30:​20፤ 50:​4፤ ማቴ. 11:​28-30) ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ከአምላክ ቃል የሚገኝ ወቅታዊ ምክር ለማግኘት መንቃትህ የግል ችግሮችህን እንድትቋቋም መርዳት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መርዳት ትችል ዘንድ ‘የተማሩትን ምላስ’ በመስጠት ያስታጥቅሃል።” a

10. አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ ያገኙት እንዴት ነው? ምን ጥቅሞችስ አስገኝቶላቸዋል?

10 በርካታ ክርስቲያኖች የዕለቱን ጥቅስና ሐሳቡን በማንበብና ማለዳ ተነስተው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ወይም በማጥናት ይህን ምክር ይሠሩበታል። በፈረንሳይ የምትኖር አንዲት ታማኝ አቅኚ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት እየተነሳች መጽሐፍ ቅዱስን ለ30 ደቂቃ ታነብባለች። ለብዙ ዓመታት እንዲህ እንድታደርግ ያስቻላት ነገር ምንድን ነው? “መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልባዊ ፍላጎት አለኝ፣ እንዲሁም ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመኝ ለንባብ ያወጣሁትን ፕሮግራም ፈጽሞ አልሰርዝም!” ብላለች። በቀኑ ውስጥ የትኛውንም ሰዓት ለንባብ እንምረጥ ዋናው ነገር ያወጣነውን ፕሮግራም በጥብቅ መከተላችን ነው። በአውሮፓና በሰሜን አፍሪካ ከ40 ዓመት በላይ በአቅኚነት ያገለገለው ሬና ሚካ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከ1950 ጀምሮ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በየዓመቱ አንብቤ የመጨረስ ግብ ነበረኝ። እስከ አሁን ድረስ 49 ጊዜ ወጥቼዋለሁ። ከፈጣሪዬ ጋር ያዳበርኩትን የቀረበ ዝምድና ጠብቄ እንዳቆይ የረዳኝ ይህ እንደሆነ ይሰማኛል። የአምላክን ቃል ማሰላሰል የይሖዋን ፍትሕና ሌሎች ባሕርያቱን በተሻለ መንገድ እንድገነዘብ ረድቶኛል። እንዲሁም ከፍተኛ ጥንካሬ የማገኝበት ምንጭ ሆኖልኛል።” b

‘በጊዜው የሚቀርብ ምግብ’

11, 12. (ሀ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” ምን ‘መንፈሳዊ ምግብ’ ሲያቀርብ ቆይቷል? (ለ) ‘ምግቡ’ በተገቢው ጊዜ የቀረበው እንዴት ነው?

11 መደበኛ የሆነ አመጋገብ ልማድ ለጥሩ አካላዊ ጤንነት አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ሁሉ ለጥናትና መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የሚያስችል መደበኛ ፕሮግራም ማውጣት ለመንፈሳዊ ጤንነት ጠቃሚ ነው። በሉቃስ ወንጌል ላይ የሚከተሉትን የኢየሱስን ቃላት እናነባለን:- “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው?” (ሉቃስ 12:​42) ላለፉት 120 ዓመታት መንፈሳዊ ‘ምግብ’ በመጠበቂያ ግንብ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ በሌሎች መጻሕፍትና ጽሑፎች አማካኝነት ‘በጊዜው’ ሲያቀርብ ቆይቷል።

12 “በጊዜው” የሚለውን አገላለጽ ልብ በል። ‘ታላቁ አስተማሪያችን’ ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ በልጁና በባሪያው አማካኝነት መሠረተ ትምህርትንና ጠባይን በሚመለከት ሕዝቡን ሲመራ ቆይቷል። ይህም በቡድን ደረጃ “ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ” የሚለውን ቃል የሰማን ያህል ነው። (ኢሳይያስ 30:​20, 21) ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ግለሰብ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በሙሉ በትጋት በሚያነብበት ጊዜ በውስጡ የተመዘገቡት ሐሳቦች በቀጥታ ለእርሱ እንደተጻፉ ሆኖ ይሰማዋል። አዎን፣ አምላካዊ ምክሮችና መመሪያዎች በጊዜው የሚደርሱን ሲሆን ይህም ፈተናዎችን እንድንቋቋምና ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል።

ጥሩ የአመጋገብ ልማድ አዳብሩ

13. ደካማ የሆኑ አንዳንድ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማዶች የትኞቹ ናቸው?

13 በተገቢው ጊዜ ከሚቀርበው ከዚህ ‘ምግብ’ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ሊኖረን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና የግል ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ቋሚ ፕሮግራም ማውጣትና ያወጣነውን ፕሮግራም በጥብቅ መከተል ወሳኝ ነው። በመንፈሳዊ ለመመገብ የሚያስችል ጥሩ የአመጋገብ ልማድ አለህ? ጥልቀት ያለው የግል ጥናት የምታደርግበት ቋሚ ጊዜ አለህ? ወይስ በጥንቃቄ ተዘጋጅቶ የቀረበልንን ትምህርት በችኮላ ቀመስ ቀመስ አድርጎ የመሄድን ወይም ጭራሽ ሳይበሉ የመዋልን ያህል ገረፍ ገረፍ አድርገን እንተወዋለን? ደካማ የሆነ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማድ አንዳንዶች በእምነታቸው እንዲዳከሙ፣ ከዚያም አልፎ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​19፤ 4:​15, 16

14. የምናውቀው የሚመስለንን ጽሑፍ በጥንቃቄ ማጥናቱ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

14 አንዳንዶች መሠረታዊ የሆኑትን ትምህርቶች እንደሚያውቁና የሚወጡት ርዕሰ ትምህርቶች በሙሉ አዲስ ነገር የሚገኝባቸው እንዳልሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። በዚህም የተነሳ በደንብ አስበውበት ማጥናትም ሆነ በስብሰባዎች ላይ መገኘት አስፈላጊ ሆኖ አይታያቸውም። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም የተማርናቸውን ትምህርቶች ዳግመኛ ማስታወሱ ተገቢ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (መዝሙር 119:​95, 99፤ 2 ጴጥሮስ 3:​1፤ ይሁዳ 5) አንዲት ባለሞያ ሴት ምግብ ለመሥራት የምትጠቀምባቸው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ሆነው የተለያዩ የምግብ አሠራር ዘዴዎችን በመጠቀም ልዩ ልዩ ጣዕም ያላቸው ምግቦች ማዘጋጀት እንደምትችል ሁሉ የባሪያው ክፍልም ገንቢ የሆኑ መንፈሳዊ ምግቦችን በተለያዩ መንገዶች ያቀርባል። ሌላው ቀርቶ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተብራሩ ትምህርቶችን የሚሸፍን አንድ ርዕሰ ትምህርት እንኳ በጣም ጠቃሚ የሆኑና ይበልጥ ጥልቀት ያላቸውን ነጥቦች ይዞ ይወጣል። ከምናነበው ጽሑፍ ውስጥ የምናገኘው ጥቅም በአብዛኛው የተመካው ጽሑፉን ለማጥናት በምናጠፋው ጊዜና በምናደርገው ጥረት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።

በማንበብና በማጥናት የሚገኙ መንፈሳዊ ጥቅሞች

15. መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት የተሻልን የአምላክ ቃል አገልጋዮች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት የምናገኛቸው ጥቅሞች በርካታ ናቸው። መሠረታዊ ከሆኑ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች መካከል አንዱን ማለትም በግለሰብ ደረጃ ‘የእውነትን ቃል በትክክል የምንጠቀም የማያሳፍር ሠራተኛ ሁን’ የሚለውን ብቃት እንድናሟላ ይረዳናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​15) መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ባነበብንና ባጠናን መጠን አእምሯችንም የዚያኑ ያህል በአምላክ ሐሳቦች ይሞላል። ከዚያም እንደ ጳውሎስ እኛም ድንቅ የሆኑትን የይሖዋን ዓላማዎች ‘ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀስን ማስረዳት’ እንችላለን። (ሥራ 17:​2, 3) የማስተማር ችሎታችን ይዳብራል፣ እንዲሁም ጭውውታችን፣ ንግግራችንና ምክራችን በመንፈሳዊ ይበልጥ የሚገነባ ይሆናል።​—⁠ምሳሌ 1:​5

16. የአምላክን ቃል በማንበብና በማጥናት በግለሰብ ደረጃ ምን ጥቅሞችን እናገኛለን?

16 ከዚህም በተጨማሪ ጊዜ ወስደን የአምላክን ቃል መመርመራችን አኗኗራችንን ከይሖዋ መንገዶች ጋር ሙሉ በሙሉ እንድናስማማ ያስችለናል። (መዝሙር 25:​4፤ 119:​9, 10፤ ምሳሌ 6:​20-23) እንደ ትሕትና፣ ታማኝነትና ደስታ የመሰሉ መንፈሳዊ ባሕርያትን ያጠነክርልናል። (ዘዳግም 17:​19, 20፤ ራእይ 1:​3) መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት ያገኘነውን እውቀት በሥራ ላይ ስናውል የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ ይፈስሳል፤ ይህም በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የመንፈስ ፍሬዎችን በብዛት እንድናፈራ ያደርገናል።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

17. በግለሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን የምናነብበትና የምናጠናበት ብዛትና ጥራት ከይሖዋ ጋር በሚኖረን ዝምድና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

17 ከሁሉም ይበልጥ ግን የአምላክን ቃል ለማንበብና ለማጥናት ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ጊዜ መዋጀታችን ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድና ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልናል። ጳውሎስ ክርስቲያን ባልደረቦቹ ‘[የአምላክ] የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ [ሞልቶባቸው]፣ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈሩ በነገር ሁሉ ደስ ሊያሰኙ ለጌታ እንደሚገባ እንዲመላለሱ’ ጸልዮአል። (ቆላስይስ 1:​9, 10) በተመሳሳይም እኛ ‘ለይሖዋ እንደሚገባ እንድንመላለስ በፈቃዱ እውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና አእምሮ ሁሉ መሞላት’ አለብን። የይሖዋን በረከትና ሞገስ ማግኘታችን በአብዛኛው የተመካው በግለሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበትና በምናነብበት ብዛትና ጥራት ላይ ነው።

18. በ⁠ዮሐንስ 17:​3 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የኢየሱስን ቃላት ብንከተል ምን በረከቶች እናገኛለን?

18 “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:​3) የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ቃል ማጥናት ያለውን ጥቅም ለሌሎች ለማስገንዘብ በአብዛኛው ከሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች መካከል አንዱ ይህ ጥቅስ ነው። ይህን የማድረጉ አስፈላጊነት ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም እንደሚሠራ የታወቀ ነው። ለዘላለም የመኖር ተስፋችን በይሖዋና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት በማደጋችን ላይ የተመካ ነው። ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ። ስለ ይሖዋ የምንማረው ትምህርት ማብቂያ የለውም። ስለ እርሱም ለመማር የሚያስችል ዘላለማዊነት ከፊታችን ተዘርግቶልናል!​—⁠መክብብ 3:​11፤ ሮሜ 11:​33

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

b የግንቦት 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 20-1 ላይ የሚገኘውን “መቼ እንደሚያነቡና እንዴት እንደተጠቀሙ የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

የክለሳ ጥያቄዎች

• የጊዜ አጠቃቀማችን ምን ነገር ይጠቁማል?

• መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ ከየትኞቹ እንቅስቃሴዎች ላይ መዋጀት ይቻላል?

• መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማዳችንን መከታተል የሚኖርብን ለምንድን ነው?

• ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብና ማጥናት ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበባችንና ማጥናታችን ‘የእውነትን ቃል በትክክል እንድንጠቀም ’ ያስችለናል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሕይወታችን የምናከናውናቸውን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችን ጋር ሚዛናዊ ማድረጉ በእጅጉ ይክሳል