በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር የፈተና ቦታ ብቻ ናትን?

ምድር የፈተና ቦታ ብቻ ናትን?

ምድር የፈተና ቦታ ብቻ ናትን?

በቃ ተገላገለች! ፈተናውን አልፋለች። ተማሪዋ ለሁለት ሳምንት በጣም አድ​ካሚ ፈተና ከተፈተነች በኋላ አስደሳች ውጤት አገኘች። አሁን፣ ለረጅም ጊዜ ትመኘው የነበረውን ሥራ ማግኘት ትችላለች።

ብዙ ሰዎች በምድር ላይ የምናሳልፈውን ሕይወት የሚያዩት ከዚህ ባልተለየ መልኩ ነው። ምድራዊ ሕይወት ሁሉም ሰው ሊያልፍበት የሚገባ የመጀመሪያ ደረጃ ፈተና እንደሆነ ያስባሉ። ፈተናውን “ያለፉ” ሰዎች በአንድ ዓይነት መልኩ ከሞት በኋላ ወደሚገኝ ሕይወት በመሻገር የተሻለ ነገር ያገኛሉ። በእርግጥም ሰዎች ተስፋ ሊያደርጉ የሚችሉት ከሁሉ የተሻለ ሕይወት የአሁኑ ሕይወት ብቻ ቢሆን ኖሮ ሁኔታው አሳዛኝ ይሆን ነበር። የአሁኑ ሕይወት ለአብዛኛዎቹ ሰዎች በሕልውና የመቆየት ጉዳይ ብቻ ነው። አብዛኛውን የሕይወቱን ዘመን በብልጽግናና በጤንነት ያሳለፈው የመጽሐፍ ቅዱሱ ባለ ታሪክ ኢዮብ እንኳ “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፣ መከራም ይሞላዋል” ብሏል።​—⁠ኢዮብ 14:​1

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ የብዙዎችን አስተሳሰብ በማንጸባረቅ እንዲህ ብሏል:- “ሰማያዊ ክብር አምላክ ለሰዎች ያዘጋጀው ዕጣ ፈንታ ነው። . . . የሰው ደስታ ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ደስታ በማግኘቱ ላይ የተመካ እንደሆነ ሊታይ ይችላል።” በቅርቡ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ያካሄደው ጥናት እንዳሳየው ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 87 በመቶ የሚሆኑት ከሞት በኋላ ወደ ሰማይ እንሄዳለን የሚል እምነት አላቸው።

ከክርስትና እምነት ውጪ ያሉ በርካታ ሰዎችም ከሞት በኋላ ምድርን ትተው ወደ ተሻለ ቦታ ለመሄድ ተስፋ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል ሙስሊሞች በሰማይ ወደሚገኝ ገነት ለመሄድ ተስፋ ያደርጋሉ። በጃፓንና በቻይና የሚገኙት ከቡዲዝም የተገነጠለው ንጹሕ ምድር የተባለው ቡድን ተከታዮች ገደብ የሌለው የብርሃን ምንጭ የሆነው የቡድሃ መጠሪያ የሆነውን “አሜዳ” የሚል ስም ደጋግመው በመጥራት የላቀ ደስታ አግኝተው በሚኖሩባት ንጹሕ ምድር ወይም ምዕራባዊ ገነት ውስጥ ዳግም እንወለዳለን ብለው ያምናሉ።

በዓለም ላይ በከፍተኛ ቁጥር የተተረጎመውና የተሰራጨው ቅዱስ መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን የሚገልጻት ትተዋት ሊሄዱ እንደሚገባ መሸጋገሪያ ቦታ አድርጎ አለመሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። (መዝሙር 37:​29) እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” የሚለው ኢየሱስ የተናገረው የታወቀ ጥቅስ ይገኛል።​—⁠ማቴዎስ 5:​5

ምድር ጊዜያዊ መኖሪያችን ናት የሚለው ሰፊ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ከሞት በኋላ ፍጹም ደስታ ወደሰፈነበት ሕይወት የሚያሸጋግረው በር ሞት ነው የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህ እውነት ከሆነ ሞት በእርግጥ በረከት ነው። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሰዎች ለሞት ያላቸው አመለካከት ይህ ነውን? ወይስ የአሁኑ ሕይወታቸውን ለማራዘም ይጥራሉ? ሰዎች በቂ ጤንነትና ዋስትና ያለው ሕይወት እንዳላቸው ሲሰማቸው መሞት እንደማይፈልጉ በግልጽ የሚታይ ነው።

የሆነ ሆኖ ምድራዊ ሕይወት በክፋትና በመከራ የተሞላ በመሆኑ ብዙዎች አሁንም ቢሆን የሚያስቡት እውነተኛ ሰላምና ደስታ የሚገኝበት ብቸኛው ቦታ ሰማይ እንደሆነ ነው። ሰማይ እንዲሁ ከክፋትና ከቅራኔ የጸዳ ፍጹም ሰላም የሰፈነበት መኖሪያ ቦታ ብቻ ነውን? እንዲሁም ከሞት በኋላ ሕይወት ሊኖር የሚችለው በሰማያዊ ዓለም ብቻ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው መልስ ትደነቅ ይሆናል። እባክህ ማንበብህን ቀጥል።