በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠቃሚና አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ

ጠቃሚና አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ

ጠቃሚና አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ

“በቀንም በሌሊትም አስበው [“አንብበው፣” NW ]።”​—⁠ኢያሱ 1:​8

1. በጥቅሉ ማንበብ በተለይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ምን ጥቅም አለው?

 ዋጋማ የሆኑ ጽሑፎችን ማንበብ ጥቅም አለው። ፈረንሳዊው የፖለቲካ ፈላስፋ ሞንቴስኪየ (ሻርል ሉዊ ደ ሰኮንዳ) እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ጥናት ኑሮ ለሚያስከትለው ድካም ፈውስ የሚሆን ፍቱን መድኃኒት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የአንድ ሰዓት ንባብ የማያስወግደው ዓይነት ችግር ገጥሞኝ አያውቅም።” መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ረገድ ይህ አባባል በእጅጉ ይሠራል። መዝሙራዊው በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቶ “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፣ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፣ ዓይንንም ያበራል” በማለት ተናግሯል።​—⁠መዝሙር 19:​7, 8

2. ይሖዋ ባለፉት ዘመናት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን ጠብቆ ያቆየው ለምንድን ነው? ሕዝቦቹስ ምን እንዲያደርጉት ይጠብቅባቸዋል?

2 ይሖዋ አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ እንደመሆኑ መጠን መጽሐፉን ባለፉት ብዙ መቶ ዘመናት ከሃይማኖታዊም ሆነ ከሌሎች ጠላቶቹ ከተሰነዘረበት ጠንካራ ተቃውሞ ጠብቆታል። ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ፈቃዱ ስለሆነ ቃሉ ለመላው የሰው ዘር እንዲዳረስ አድርጓል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​4) አንድ መቶ ቋንቋዎችን በመጠቀም 80 ከመቶ የሚሆነው የምድር ነዋሪ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብ ማድረግ ይቻላል ተብሎ ይገመታል። ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በ370 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በ1, 860 ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ይገኛል። ይሖዋ ሕዝቡ ቃሉን እንዲያነቡ ይፈልጋል። ለቃሉ ትኩረት የሚሰጡትን አዎን፣ በየቀኑ የሚያነቡትን አገልጋዮቹን ይባርካቸዋል።​—⁠መዝሙር 1:​1, 2

የበላይ ተመልካቾች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ይጠበቅባቸዋል

3, 4. ይሖዋ የእስራኤል ነገሥታት ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር? ዛሬ ያሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ይህንኑ ብቃት እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸውስ ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ የእስራኤል ብሔር ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲሾምላቸው እንደሚጠይቁ በተናገረው ትንቢት ላይ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር:- “በመ​ንግሥቱም ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ። አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፣ ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኮራ ከትእዛዙም ቀኝና ግራ እንዳይል፣ እርሱም ልጆቹም በእስራኤል ልጆች መካከል ረጅም ዘመን ይነግሡ ዘንድ መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፣ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።”​—⁠ዘዳግም 17:​18-20

4 ይሖዋ ወደፊት በእስራኤል ላይ የሚነግሡት ነገሥታት መለኮታዊ ሕግ የሰፈረበትን መጽሐፍ በየቀኑ እንዲያነቡ ይጠብቅባቸው የነበረው ለምን እንደሆነ ልብ በል:- (1) “አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ”፤ (2) “ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኮራ”፤ (3) “ከትእዛዙም ቀኝና ግራ እንዳይል።” ዛሬ ያሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችስ ይሖዋን መፍራት፣ ትእዛዙን መጠበቅ፣ ልባቸው በወንድሞቻቸው ላይ እንዳይኮራ ማድረግና ከይሖዋ ሕግጋት እንዳይርቁ መጠንቀቅ አይኖርባቸውም? የእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንዲያነቡ ይጠበቅባቸው ከነበረ ከእነርሱም ይኸው ነገር ይጠበቃል።

5. የአስተዳደር አካሉ በቅርቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን በማስመልከት ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ምን ጽፎ ነበር? ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሙሉ ይህን ምክር መከተላቸውስ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

5 በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጊዜያቸው በጣም የተጣበበ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቡ ፈታኝ ይሆንባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላትና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በሙሉ ሥራ ይበዛባቸዋል። ሆኖም የአስተዳደር አካሉ በቅርቡ ለመላው የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በላከው ደብዳቤ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ጥሩ የጥናት ልማድ የማዳበርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህም ለይሖዋና ለቃሉ ያለንን ፍቅር ከፍ የሚያደርግልን ከመሆኑም በላይ “እስከ መጨረሻው ድረስ እምነታችንን፣ ደስታችንንና ጽናታችንን ይዘን እንድንዘልቅ ይረዳናል” በማለት ደብዳቤው ጠቁሟል። በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ ማንበባቸው ‘በጥበብ እንዲመላለሱ’ ይረዳቸዋል። (ኢያሱ 1:​7, 8 NW ) ሽማግሌዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸው በተለይ “ለትምህርት፣ ለተግሣጽ፣ ለእርማትና በጽድቅ መንገድ ሥልጠና ለማግኘት” ይጠቅማቸዋል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16 ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርሽን

ለወጣቶችም ለአዋቂዎችም አስፈላጊ ነው

6. ኢያሱ በፊቱ ተሰብስበው ለነበሩት ለእስራኤል ነገድና ለመጻተኞች መላውን የይሖዋን ሕግ ቃላት ድምፁን ጮክ አድርጎ ያነበበው ለምንድን ነው?

6 በጥንት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የግሉ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ ስላልነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ይደረግ የነበረው ብዙ ሕዝብ አንድ ላይ ተሰብስቦ ነበር። ይሖዋ በጋይ ከተማ ላይ ድል ካቀዳጀው በኋላ ኢያሱ መላውን የእስራኤል ነገድ በጌባል እና በገሪዛን ተራራ አጠገብ ሰበሰባቸው። ከዚያም ዘገባው እንዲህ ይለናል:- “በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ሁሉ፣ የሕጉን ቃሎች ሁሉ በረከቱንና እርግማኑን አነበበ። ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶቹም በሕፃናቱም በመካከላቸውም በሚኖሩት መጻተኞች ፊት ሁሉን አነበበ እንጂ ሙሴ ካዘዘው አንዲት ቃል አላስቀረም።” (ኢያሱ 8:​34, 35) ወጣቶችና አዋቂዎች፣ የአገሬው ተወላጅና መጻተኛው የይሖዋን በረከት የሚያስገኘውና የእርሱን ሞገስ የሚያሳጣው አኗኗር የትኛው እንደሆነ በምሳሌያዊ አባባል በልባቸውና በአእምሯቸው ጽላት ላይ መጻፍ ነበረባቸው። ዘወትር የሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በዚህ ረገድ እርዳታ እንደሚያበረክት የተረጋገጠ ነው።

7, 8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ‘በመጻተኞች’ የተመሰሉት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ የሚኖርባቸውስ ለምንድን ነው? (ለ) በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የሚገኙት ‘ሕፃናት’ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

7 በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በሚል​ዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘መጻተኞችን’ ይመስላሉ። በአንድ ወቅት የዓለምን የአኗኗር መንገድ ይከተሉ የነበረ ሲሆን አሁን ግን አኗኗራቸውን ለውጠዋል። (ኤፌሶን 4:​22-24፤ ቆላስይስ 3:​7, 8) ይሖዋ መልካምና ክፉ ለሆኑ ነገሮች ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች ለአንድ አፍታ እንኳ መዘንጋት አይኖርባቸውም። (አሞፅ 5:​14, 15) በየዕለቱ የሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ይህን እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።​—⁠ዕብራውያን 4:​12፤ ያዕቆብ 1:​25

8 ይሖዋ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች ከወላጆቻቸው የተማሩ ሆኖም የእሱ ፈቃድ ጽድቅ መሆኑን ራሳቸውን ማሳመን የሚኖርባቸው ‘ሕፃናት’ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ይገኛሉ። (ሮሜ 12:​1, 2) ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በእስራኤል መካከል የነበሩት ካህናትና ሽማግሌዎች የሚከተለውን እንዲያደርጉ ታዝዘው ነበር:- “እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ስፍራ ሲከማች፣ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው። ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፣ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፣ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውን መጻተኛ ሰብስብ። የሕግን ቃላት የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ።” (ዘዳግም 31:​11-13) በሕጉ ሥር የነበረው ኢየሱስ 12 ዓመት በሆነው ጊዜ የአባቱን ሕግጋት ለመረዳት ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው አሳይቷል። (ሉቃስ 2:​41-49) ከዚያም በኋላ በነበሩት ጊዜያት ወደ ምኩራብ ሄዶ ቅዱሳን ጽሑፎች ሲነበቡ የማዳመጥና ተሳትፎ የማድረግ ልማድ ነበረው። (ሉቃስ 4:​16፤ ሥራ 15:​21) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብና መጽሐፍ ቅዱስ በሚነበብባቸውና በሚጠናባቸው ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው በመገኘት የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ ተበረታተዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል

9. (ሀ) የምናነብበውን ነገር መምረጥ የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ አዘጋጅ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያግዙ ጽሑፎችን በተመለከተ ምን ብሎ ነበር?

9 ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ተግሣጽን ስማ፤ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፣ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 12:​12) በዛሬው ጊዜ የሚታተሙ በርካታ መጻሕፍት ሥጋን የሚያደክሙ ብቻ ሳይሆኑ ግልጹን ለመናገር ለአእምሮም አደገኛ ናቸው። ስለዚህ መራጭ መሆን ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያግዙ ጽሑፎችን ከማንበብም በተጨማሪ ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይኖርብናል። የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ አዘጋጅ “መጽሐፍ ቅዱስ ዋናው መጽሐፋችን እንደሆነና አምላክ የሰጠን ለማጥኛ የሚያግዙ ጽሑፎች ግን ‘እርዳታ የሚያበረክቱ’ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የሚተኩ እንዳልሆኑ በጭራሽ አትርሱ” በማለት ለአንባቢዎቹ ጽፏል። a ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያግዙ ጽሑፎችን ችላ ሳንል ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይኖርብናል።

10. “ታማኝና ልባም ባሪያ” መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

10 የዚህን አስፈላጊነት በመረዳት “ታማኝና ልባም ባሪያ” በእያንዳንዱ ጉባኤ በሚካሄደው በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም እንዲካተት አድርጓል። (ማቴዎስ 24:​45) አሁን ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ አንብቦ ለመጨረስ ያስችላል። ይህ ፕሮግራም ለሁሉም የሚጠቅም ሲሆን በተለይ ደግሞ ከዚህ ቀደም መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብበው ለማያውቁ አዲሶች በይበልጥ ይጠቅማል። በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብተው የሚሠለጥኑ ሚስዮናውያንና በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሚካፈሉ እንዲሁም አዳዲስ የቤቴል ቤተሰብ አባላት መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አንብበው እንዲጨርሱ ይጠበቅባቸዋል። በግልም ይሁን በቤተሰብ ደረጃ የምትከተለው የንባብ ፕሮግራም ምንም ዓይነት ይሁን ፕሮግራምህን ለመጠበቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብሃል።

ከንባብ ልማድህ ምን ትገነዘባለህ?

11. ከይሖዋ አፍ የሚወጣውን ቃል በየዕለቱ መመገብ ያለብን ለምንድን ነው? የምንመገበውስ እንዴት ነው?

11 መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ያወጣኸውን ፕሮግራም በመጠበቅ ረገድ ችግር ካለብህ ‘የማንበብ ወይም ቴሌቪዥን የመመልከት ልማዶቼ የይሖዋን ቃል ለማንበብ ባለኝ ችሎታ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ሙሴ የጻፈውንና ከዚያም ኢየሱስ ደግሞ የተናገረውን “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” የሚለውን አስታውስ። (ማቴዎስ 4:​4፤ ዘዳግም 8:​3) ሰብዓዊ አካላችንን ጠብቀን ለማቆየት በየዕለቱ እንጀራ ወይም ሌላ ዓይነት ምግብ መመገብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን ለማቆየትም የይሖዋን ሐሳቦች በየዕለቱ መቅሰም ይኖርብናል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በማንበብ የአምላክን ሐሳቦች በየዕለቱ ማግኘት እንችላለን።

12, 13. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአምላክ ቃል ሊኖረን ስለሚገባ ጉጉት በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንኑ ምሳሌ ከጴጥሮስ በተለየ መንገድ የተጠቀመበት እንዴት ነው?

12 መጽሐፍ ቅዱስን ‘እንደ ሰው ሳይሆን በእውነት እንዳለ እንደ እግዚአብሔር ቃል’ አድርገን የምንመለከተው ከሆነ የእናቱን ጡት ለመጥባት እንደሚጓጓ ሕፃን እኛም የአምላክን ቃል ለማንበብ እንጓጓለን። (1 ተሰሎንቄ 2:​13) ሐዋርያው ጴጥሮስ ተመሳሳይ ንጽጽር በመጠቀም “ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፣ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:​2, 3) “ጌታ ቸር መሆኑን” በግላችን ቀምሰን ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ከፍተኛ ጉጉት ያድርብናል።

13 ጴጥሮስ እዚህ ላይ ወተትን ያነጻጸረው ሐዋርያው ጳውሎስ ካነጻጸረበት በተለየ መንገድ እንደሆነ ማስተዋል ይገባል። ወተት ገና ለተወለደ ሕፃን የተሟላ ምግብ ነው። የአምላክ ቃል “ለመዳን” የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ አሟልቶ እንደያዘ የጴጥሮስ ምሳሌ ያሳያል። በሌላው በኩል ደግሞ ጳውሎስ በመንፈሳዊ ጎልማሳ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ ሆኖም ደካማ የአመጋገብ ልማድ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ወተት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሷል። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከጊዜው የተነሣ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፣ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።” (ዕብራውያን 5:​12-14) ትጋት የተሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የማስተዋል ችሎታችንን ለማዳበርና ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን ፍላጎት ለመቀስቀስ ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚኖርብን እንዴት ነው?

14, 15. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ምን መብት ሰጥቶናል? (ለ) ከመለኮታዊ ጥበብ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌዎችን ጥቀስ።)

14 ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በቀጥታ ወደ ንባቡ ከመግባት ይልቅ መጸለይ ጥሩ ነው። ጸሎት አስደናቂ መብት ነው። ጥልቀት ያለው ትምህርት ያለበትን አንድ መጽሐፍ በደንብ መረዳት ትችል ዘንድ ከማንበብህ በፊት ደራሲው እንዲረዳህ የመጠየቅ ያህል ነው። እንዲህ ማድረጉ ምን ያህል ጥቅም እንደሚያስገኝ ገምት! የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የሆነው ይሖዋ እንዲህ ያለ መብት ሰጥቶሃል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል አባል ለወንድሞቹ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።” (ያዕቆብ 1:​5, 6) በጊዜያችንም ያለው የአስተዳደር አካል መጽሐፍ ቅዱስን በጸሎት እንድናነብ በተደጋጋሚ አጥብቆ ይመክረናል።

15 ጥበብ እውቀትን ተግባራዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ማለት ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስህን ከመክፈትህ በፊት በግል ሕይወትህ ውስጥ በሥራ ልታውላቸው የሚገቡህን ነጥቦች ከንባብህ ማግኘት ትችል ዘንድ እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቅ። ያነበብካቸውን አዳዲስ ነጥቦች ቀደም ሲል ከምታውቃቸው ነገሮች ጋር አገናዝብ። ከምታውቃቸው ‘ከጤናማ ቃል ምሳሌ’ ጋር አስማማቸው። (2 ጢሞቴዎስ 1:​13) በጥንት ጊዜ የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮችን የሕይወት ታሪክ በምታነብበት ጊዜ ትንሽ ቆም በልና እንዲህ ያለው ሁኔታ እኔን ቢገጥመኝ ኖሮ ምን አደርግ ነበር ብለህ ራስህን ጠይቅ።​—⁠ዘፍጥረት 39:​7-9፤ ዳንኤል 3:​3-6, 16-18፤ ሥራ 4:​18-20

16. ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንድንችል ምን ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦች ተሰጥተዋል?

16 የተወሰኑ ገጾችን ለመሸፈን ብለህ ብቻ አታንብብ። አትጣደፍ። በምታነበው ነገር ተመሰጥ። ትኩረትህን የሳበው ነጥብ ካለና የምታነበው መጽሐፍ ቅዱስ ማጣቀሻ ካለው ማጣቀሻውን ተመልከት። ነጥቡ አሁንም ካልገባህ ንባብህን ከጨረስክ በኋላ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ እንድትችል በወረቀት ላይ ጻፈው። በምታነብበት ጊዜ በተለይ ዳግመኛ ማስታወስ ወይም መገልበጥ የምትፈልጋቸውን ነጥቦች ምልክት አድርግባቸው። በተጨማሪም በኅዳጉ ላይ አንዳንድ ማስታወሻዎችን ወይም ማጣቀሻዎችን ማስፈር ትችላለህ። በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ይጠቅሙኛል ብለህ የምታስባቸውን ጥቅሶች ቁልፍ በሆነው ቃል ላይ ምልክት አድርግና በመጽሐፍ ቅዱስህ የመጨረሻ ገጽ ላይ ተዘርዝረው የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ የቃላት መፍቻዎች ተመልከት። b

የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ

17. መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ መደሰት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

17 መዝሙራዊው ‘በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ስለሚለውና ሕጉንም በቀንና በሌሊት ስለሚያስብ’ ደስተኛ ሰው ተናግሯል። (መዝሙር 1:​2) በየዕለቱ የምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አሰልቺ ሥራ ሳይሆን እውነተኛ ደስታ የምናገኝበት መሆን ይኖርበታል። አስደሳች ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ የምንማራቸው ነገሮች ያላቸውን ዋጋማነት መገንዘብ ነው። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፣ . . . መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፣ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፣ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 3:​13, 17, 18) የጥበብ መንገድ ፍስሐ፣ ሰላም፣ ደስታና በመጨረሻም ሕይወት የሚገኝበት መንገድ እንደመሆኑ ጥበብ ለማግኘት ስንል የምናደርገው ጥረት ፈጽሞ የሚያስቆጨን አይሆንም።

18. መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ በተጨማሪ ምን ማድረግ አስፈላጊ ነው? በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የምንመረምረው ምንድን ነው?

18 አዎን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጥቅምም ሆነ ደስታ የሚገኝበት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ብቻ በቂ ነው? የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባላት መጽሐፍ ቅዱስን ለብዙ መቶ ዘመናት ሲያነቡ ቢኖሩም “ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ” አይችሉም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​6, 7) የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ፍሬያማ እንዲሆንልን ከፈለግን ስናነብ ያገኘነውን እውቀት በግል ሕይወታችን ላይ ተግባራዊ ለማድረግና በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ለመጠቀም የሚያስችል ግብ ይዘን ማንበብ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20) ይህም ጥረት ማድረግና ጥሩ የጥናት ዘዴ መጠቀምን የሚጠይቅ ሲሆን በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ እንደምንመለከተውም እንዲህ ማድረጉ አስደሳችና የሚክስ ሊሆን ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመው የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 241 ተመልከት።

b በግንቦት 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-17 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሐሳቦች” የሚለውን ተመልከት።

የክለሳ ጥያቄዎች

• በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ የበላይ ተመልካቾችም የሚሠራ ለእስራኤል ነገሥታት የተሰጠ ምክር የትኛው ነው? ምክሩ ዛሬ ላሉ የበላይ ተመልካቾች የሚሠራ የሆነውስ ለምንድን ነው?

• በዛሬው ጊዜ “በመጻተኞች” እና “በሕፃናት” የተመሰሉት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ የሚኖርባቸውስ ለምንድን ነው?

• “ታማኝና ልባም ባሪያ” መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን እንድናነብ በምን ተግባራዊ መንገዶች ይረዳናል?

• የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን ጠቃሚና አስደሳች ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተለይ ሽማግሌዎች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ይኖርባቸዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በምኩራቦች ቅዱሳን ጽሑፎችን የማንበብ ልማድ ነበረው