በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥናት—አስደሳችና የሚክስ ሥራ ነው

ጥናት—አስደሳችና የሚክስ ሥራ ነው

ጥናት​—⁠አስደሳችና የሚክስ ሥራ ነው

“ብትፈላልጋት፣ . . . የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”​—⁠ምሳሌ 2:​4, 5

1. በትርፍ ጊዜ የሚደረግ ንባብ በጣም አስደሳች ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

 ብዙ ሰዎች እንዲሁ ደስታ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ያነብባሉ። የሚነበበው ነገር ጤናማ ከሆነ ንባብ መንፈስን የሚያድስ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በቋሚነት ከሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራማቸው በተጨማሪ መዝሙርን፣ ምሳሌን፣ የወንጌል ዘገባዎችን ወይም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አለፍ አለፍ እያሉ በማንበብ እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ። የእነዚህ መጻሕፍት ውብ የአጻጻፍ ስልትና ያዘሉት መልእክት ጥልቅ ደስታ ይፈጥርላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ትርፍ ጊዜያቸውን የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ የተባለውን መጽሐፍ ወይም በንቁ! መጽሔት ላይ የሚወጡትን የሕይወት ታሪኮች ወይም ታሪክን፣ ጂኦግራፊንና በተፈጥሮ ጥናት ላይ የሚወጡ ዘገባዎችን በማንበብ ያሳልፋሉ።

2, 3. (ሀ) ጥልቀት ያለው መንፈሳዊ ትምህርት ከጠንካራ ምግብ ጋር ሊወዳደር የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ጥናት ምን ማድረግን ያጠቃልላል?

2 እንዲሁ ደስታ ለማግኘት ተብሎ የሚደረግ ንባብ ሊያዝናና ቢችልም ጥናት ግን አእምሮ ማሠራትን ይጠይቃል። እንግሊዛዊው ፈላስፋ ፍራንሲስ ቤከን “አንዳንድ መጻሕፍት የሚቀመሱ፣ ሌሎች ደግሞ የሚዋጡ ሲሆኑ ጥቂቶቹ ግን ማላመጥና ማዋሃድ የሚጠይቁ ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል። መጽሐፍ ቅዱስ መጨረሻ ላይ ከተጠቀሱት ዓይነት የሚመደብ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጽፏል:- “ስለ እርሱም [ንጉሥና ካህን የነበረው መልከጼዴቅ ምሳሌ ስለሆነለት ስለ ክር​ስቶስ] የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፣ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልተረጒመው ጭንቅ ነው። ጠንካራ ምግብ . . . መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።” (ዕብራውያን 5:​11, 14) ጠንካራ ምግብ ከመዋጡና ከመዋሃዱ በፊት በሚገባ መታኘክ አለበት። ጥልቀት ያላቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች ወደ ውስጥ ገብተው እንዲዋሃዱ ለማድረግ በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል።

3 አንድ መዝገበ ቃላት “ጥናት” የሚለውን ቃል “በንባብ፣ በምርምር፣ ወዘተ አማካኝነት እውቀት ወይም ማስተዋል ለማግኘት አእምሮን ማሠራት” ብሎ ተርጉሞታል። ስለዚህ እንዲሁ ገረፍ ገረፍ አድርጎ ምናልባትም የተወሰኑ ቃላትን እያሰመሩ ከማንበብ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ጥናት ማለት ሥራ፣ የአእምሮ ጥረትና የማሰብ ችሎታን መጠቀም ማለት ነው። ጥናት ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም አስደሳች ሊሆን አይችልም ማለት ግን አይደለም።

ጥናትን አስደሳች ማድረግ

4. መዝሙራዊው እንደተናገረው የአምላክን ቃል ማጥናት መንፈስን የሚያድስና የሚክስ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

4 የአምላክን ቃል ማንበብና ማጥናት መንፈስን የሚያድስና የሚያበረታታ ሊሆን ይችላል። መዝሙራዊው የሚከተለውን ብሏል:- “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፣ ዓይንንም ያበራል።” (መዝሙር 19:​7, 8) የይሖዋ ሕግጋትና ማሳሰቢያዎች ነፍሳችንን ያድሳሉ፣ መንፈሳዊነታችን እንዲሻሻል ያደርጋሉ፣ ውስጣዊ ደስታ ይሰጡናል እንዲሁም የይሖዋ አስደናቂ ዓላማዎች ጥርት ብለው እንዲታዩን ዓይናችንን ያበሩልናል። ምንኛ የሚያስደስት ነው!

5. ጥናት ከፍተኛ ደስታ ሊያስገኝልን የሚችለው እንዴት ነው?

5 ሥራችን መልካም ውጤት እያስገኘ እንዳለ ስናይ ሥራውን ይበልጥ እንወደዋለን። ስለዚህ ጥናት የሚ​ያስደስት እንዲሆንልን ከፈለግን በቅርቡ የቀሰምነውን እውቀት ቶሎ ብለን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፣ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፣ በሥራው የተባረከ ይሆናል።” (ያዕቆብ 1:​25) የተማርነውን ነገር ወዲያው ተግባራዊ ማድ​ረግ ከፍተኛ እርካታ ያስገኛል። በምንሰብክበት ወይም በምናስተምርበት ጊዜ ለቀረበልን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ስንል ምርምር ማድረጉም ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል።

ለአምላክ ቃል ፍቅር ማዳበር

6. የ⁠መዝሙር 119 ጸሐፊ ለይሖዋ ቃል ፍቅር እንዳለው የገለጸው እንዴት ነው?

6 የ⁠መዝሙር 119 አቀናባሪ ሕዝቅያስ ሳይሆን አይቀርም ገና ወጣት መስፍን በነበረበት ጊዜ ለይሖዋ ቃል ፍቅር እንዳለው ገልጿል። በግጥም የአጻጻፍ ስልት እንዲህ ብሏል:- “በትእዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። ምስክርህም ተድላዬ ነው፣ . . . እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል። ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፣ በሕይወትም ልኑር። አቤቱ፣ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ተድላዬ ነው።”​—⁠መዝሙር 119:​16, 24, 47, 77, 174

7, 8. (ሀ) በአንድ መዝገበ ቃላት መሠረት የአምላክን ቃል “መውደድ” ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ለይሖዋ ቃል ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) ዕዝራ የይሖዋን ሕግ ከማንበቡ በፊት ልቡን ያዘጋጀው እንዴት ነው?

7 በ⁠መዝሙር 119 [NW ] ላይ የሚገኘውን “መውደድ” ተብሎ የተተረጎመውን ቃል ሲያብራራ አንድ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መዝገበ ቃላት እንዲህ ብሏል:- “በመዝ 119 ቁጥር 16 ላይ ያለው አገባብ መደሰት . . . እና ማሰላሰል ከሚሉት [ግሦች] ጋር የሚመሳሰል ነው። . . . ቅደም ተከተሉ መደሰት፣ ማሰላሰል፣ ፍስሐ የሚሉት ናቸው። . . . እነዚህ ሁሉ በአንድ ላይ ተጣምረው መቀመጣቸው አንድ ሰው በያህዌህ ቃላት መደሰት እንዲችል በዓላማ ማጤን እንዳለበት ለማሳየት ሊሆን ይችላል። . . . ትርጉሙ ስሜት መቀስቀስን የሚያጠቃልል ነው።” a

8 አዎን፣ ለይሖዋ ቃል ያለን ፍቅር የስሜት መቀመጫ ከሆነው ከልባችን የሚወጣ መሆን ይኖርበታል። አንድ ክፍል ካነበብን በኋላ ባነበብነው ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ጥልቀት ባላቸው መንፈሳዊ ሐሳቦች መመሰጥ፣ ሙሉ በሙሉ መዋጥና ማሰላሰል ይኖርብናል። ይህ ደግሞ በጸጥታ ማብላላትንና ጸሎትን ይጠይቃል። እንደ ዕዝራ የአምላክን ቃል ለማንበብና ለማጥናት ልባችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ስለ እርሱ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:​10) ዕዝራ ለሦስት ነገሮች ማለትም ለማጥናት፣ በሕይወቱ ላይ በተግባር ለማዋልና ለማስተማር ልቡን እንዳዘጋጀ ልብ በል። እኛም የእርሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል።

ጥናት የአምልኮ ክፍል ነው

9, 10. (ሀ) መዝሙራዊው የይሖዋን ቃል እንደሚያሰላስል ያሳየው በምን መንገዶች ነው? (ለ) “ማሰላሰል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ግስ ምን ትርጉም አለው? (ሐ) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት “የአምልኮ” ክፍል እንደሆነ አድርጎ መመልከቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 መዝሙራዊው የይሖዋን ሕግጋት፣ ትእዛዛትና ማሳሰቢያዎች እንደሚያሰላስል ተናግሯል። እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፣ መንገድህንም እፈልጋለሁ። እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ ሥርዓትህንም አሰላስላለሁ። አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ።” (መዝሙር 119:​15, 48, 97, 99) የይሖዋን ቃል ‘ማሰላሰል’ ምን ማድረግን ያመለክታል?

10 “ማሰላሰል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ግስ “ማብሰልሰል፣ መመሰጥ፣” “አንድን ጉዳይ በአእምሮ ውስጥ ማውጣት ማውረድ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። “የአምላክን ሥራዎች . . . እና የአምላክን ቃል ጸጥ ብሎ ማሰብን ለማመልከትም ተሠርቶበታል።” (ቲኦሎጂካል ዎርልድቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት ) “ማሰላሰል” የሚለው ቃል በስም መልክ ሲቀመጥ “መዝሙራዊው” የአምላክን ሕግ “የአምልኮው” ክፍል እንደሆነ አድርጎ በመመልከት “በፍቅር ተነሳስቶ ማጥናቱን” ያመለክታል። የአምላክን ቃል ማጥናት አንዱ የአምልኮታችን ክፍል እንደሆነ አድርገን መመልከታችን ጥናትን በቁም ነገር እንድንይዝ ይረዳናል። እንደዚያ ከሆነ በጥንቃቄና በጸሎት መደረግ ይኖርበታል። ጥናት የአምልኮታችን አንዱ ክፍል ሲሆን አምልኳችንን ለማሻሻል የሚደረግ ነው።

የአምላክን ቃል አጥልቆ መቆፈር

11. ይሖዋ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ሐሳቦችን ለሕዝቡ የሚገልጠው እንዴት ነው?

11 መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፣ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው” በማለት ከፍ ያለ አድናቆቱን ገልጿል። (መዝሙር 92:​5) ሐዋርያው ጳውሎስም ይሖዋ ታማኝና ልባም ባሪያምን በሚያንቀሳቅሰው “በመንፈሱ በኩል” ለሕዝቡ የገለጣቸውን ‘የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች’ ማለትም ጥልቅ ሐሳቦች ጠቅሷል። (1 ቆሮንቶስ 2:​10፤ ማቴዎስ 24:​45) የባሪያው ክፍል ለሁሉም ማለትም ለአዲሶች “ወተት፣” “ለጎለመሱ” ደግሞ “ጠንካራ ምግብ” ማለትም መንፈሳዊ ምግብ በትጋት ሲያቀርብ ቆይቷል።​—⁠ዕብራውያን 5:​11-14

12. የባሪያው ክፍል ማብራሪያ ከሰጠባቸው ‘የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገሮች’ መካከል አንዱን ጥቀስ።

12 እነዚህን “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች” ለመረዳት በጸሎት ማጥናትና በቃሉ ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ፍትሕንና ምሕረትን እንዴት ጎን ለጎን ማሳየት እንደሚችል የሚገልጽ ግሩም ትምህርት ወጥቶ ነበር። ምሕረትን ያሳያል ማለት ፍትሑን ያዛባል ማለት አይደለም፤ ከዚያ ይልቅ መለኮታዊ ምሕረት የአምላክ ፍትሕና ፍቅር መግለጫ ነው። ይሖዋ በአንድ ኃጢአተኛ ላይ በሚፈርድበት ጊዜ በመጀመሪያ በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ በመመርኮዝ ምሕረት ማሳየት ይችል እንደሆነ ይወስናል። ኃጢአተኛው ንሥሐ የማይገባ ወይም ዓመፀኛ ከሆነ አምላክ ምሕረት ማሳየት ሳያስፈልገው ፍትሑን በቀጥታ ተግባራዊ ያደርጋል። በዚያም ሆነ በዚህ ከፍ ያለ ደረጃ ላላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ታማኝ ነው። b (ሮሜ 3:​21-26) ‘ጥበቡ እንዴት ጥልቅ ነው!’​—⁠ሮሜ 11:​33

13. እስከ አሁን ድረስ ለተገለጡልን ‘ብዙ’ መንፈሳዊ እውነቶች አድናቆታችንን ማሳየት ያለብን እንዴት ነው?

13 ይሖዋ በርካታ ሐሳቦቹን ስለሚያካፍለን እኛም እንደ መዝሙራዊው ደስተኞች ነን። ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አቤቱ፣ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደ ምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቁጥራቸው እንደ ምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፤ ተነሣሁም፣ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ።” (መዝሙር 139:​17, 18) አሁን ያለን እውቀት ይሖዋ ወደፊት ለዘላለም ከሚገልጥልን ቁጥር ስፍር ከሌለው ሐሳቡ ጋር ሲነጻጸር በጣም ኢምንት ቢሆንም እንኳ እስከ አሁን ድረስ ለተገለጡልን ‘እጅግ ብዙ’ ውድ መንፈሳዊ እውነቶች ከፍተኛ አድናቆት ያለን ከመሆኑም በላይ የአምላክን ቃል አጥልቀን መቆፈራችንን እንቀጥላለን።​—⁠መዝሙር 119:​160 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ

ጥረትና ውጤታማ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ

14. ምሳሌ 2:​1-6 የአምላክን ቃል ለማጥናት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናት ጥረት ይጠይቃል። ምሳሌ 2:​1-6ን በጥንቃቄ በማንበብ የዚህን አባባል እውነተኝነት በግልጽ ለማየት ይቻላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን መለኮታዊ እውቀትን፣ ጥበብንና ማስተዋልን ለማግኘት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠንከር አድርጎ ለመግለጽ የተጠቀመባቸውን ገላጭ ግሦች ልብ በል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ ከጥናት ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን አንድን የተደበቀ ሃብት ለማግኘት እንደምናደርገው ዓይነት ፍለጋ ምርምር ማድረግና መቆፈር አለብን።

15. ጥሩ የጥናት ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጎላ አድርጎ ይገልጻል?

15 በተጨማሪም መንፈሳዊነትን ለማሻሻል ጥሩ የጥናት ዘዴ መጠቀምን ይጠይቃል። ሰሎሞን “የደነዘ መጥረቢያውን የማይስል ሰው ኃይሉን በከንቱ ይጨርሳል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 10:​10 የ1980 ትርጉም ) አንድ ሠራተኛ ስል ባልሆነ መሣሪያ ለመቁረጥ ቢሞክር ወይም በጥሩ ዘዴ ካልተጠቀመበት ጉልበቱን ሁሉ በከንቱ ያባክናል እንዲሁም ሥራው ጥራት የጎደለው ይሆናል። በተመሳሳይም በጥናት ከምናሳልፈው ጊዜ የምናገኘው ጥቅም በአጠናን ዘዴያችን ላይ የተመካ ነው። ጥናታችንን ለማሻሻል የሚረዱ ግሩም የሆኑ ተግባራዊ ሐሳቦችን ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ጥናት 7 ላይ ማግኘት ይቻላል። c

16. በጥልቀት ለማጥናት የሚረዱ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምን ሐሳቦች ተሰጥተዋል?

16 አንድ ባለሙያ ሥራ በሚጀምርበት ጊዜ ለሥራው የሚያስፈልጉትን መሣሪያዎች በሙሉ በቅርብ ያስቀምጣል። በተመሳሳይም ማጥናት ልንጀምር ስንል ለጥናት የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎች በሙሉ ከግል ቤተ መጻሕፍታችን መርጠን ማውጣት ይኖርብናል። ጥናት ሥራና አእምሮን ማሠራት የሚጠይቅ በመሆኑ ተመቻችቶ መቀመጥም አስፈላጊ ነው። አእምሯችን ንቁ ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለግን አልጋ ላይ ተኝቶ ወይም የሚደላ ወንበር ላይ ተቀምጦ ከማጥናት ይልቅ ወንበራችንን ጠረጴዛ ወይም ዴስክ አጠገብ አድርገን መቀመጡ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል። ሐሳብህን ሁሉ አሰባስበህ ለተወሰነ ጊዜ ስታጠና ከቆየህ በኋላ ከወንበርህ ላይ ተነስተህ መንጠራራት ወይም ወጣ ብሎ መናፈስ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል።

17, 18. የተዘጋጁልህን የማጥኛ መሣሪያዎች እንዴት እንደምትጠቀምባቸው ምሳሌ ስጥ።

17 በተጨማሪም ወደር የማይገኝላቸው የማጥኛ መሣሪያዎች አሉልን። ከእነዚህ መካከል ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በ37 ቋንቋዎች የተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መደበኛ እትም ማጣቀሻ እንዲሁም የጸሐፊውን ስም፣ የተጻፈበትን ቦታና የሚሸፍነውን ጊዜ የያዘ “የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሰንጠረዥ” አሉት። ከዚህም በተጨማሪ በፊደል ተራ የተቀመጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫ፣ ተጨማሪ መግለጫዎችና ካርታዎች አሉት። በአንዳንድ ቋንቋዎች ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ባለ ማጣቀሻ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ በሚታወቅ ተለቅ ባለ መጠን ታትሞ ይገኛል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በቅደም ተከተል የተዘጋጀ ሰፊ የግርጌ ማስታወሻዎችን ጨምሮ ከላይ የተገለጹትና ሌሎች ገጽታዎችም አሉት። የአምላክን ቃል አጥልቀህ ለመቆፈር እንድትችል በቋንቋህ በሚገኙ በሁሉም መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ ትጠቀማለህ?

18 ሌላው ግሩም የማጥኛ መሣሪያ ደግሞ በሁለት ጥራዝ የተዘጋጀው ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔዲያ ነው። ይህን መጽሐፍ ልትረዳው በምትችለው ቋንቋ ካገኘህ በምታጠናበት ጊዜ ከአጠገብህ መለየት አይኖርበትም። አብዛኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ከሥረ መሠረታቸው አንስቶ ያብራራል። ተመሳሳይ እርዳታ የሚያበረክተው ሌላው መሣሪያ “ ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ የተጻፈና ጠቃሚ ነው” (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ነው። አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ማንበብ በምትጀምርበት ጊዜ የመጽሐፉን ይዘትና የሚሰጠውን ጥቅም ጨምሮ መልክአ ምድራዊና ታሪካዊ መቼቶቹን ለማወቅ “ ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ” በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ይህንኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚያብራራውን ጥናት መመርመሩ ጥሩ ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ በዘጠኝ ቋንቋዎች የሚገኘው በኮምፒዩተር የተዘጋጀው የመጠበቂያ ግንብ ቤተ መጻሕፍት በጽሑፍ ከተዘጋጁት በርካታ የማጥኛ መሣሪያዎች ጋር ሊደመር ይችላል።

19. (ሀ) ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ግሩም መሣሪያዎችን የሰጠን ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ተገቢ በሆነ መንገድ ለማጥናትና ለማንበብ ምን ነገር ያስፈልጋል?

19 ይሖዋ በምድር ላይ የሚገኙ አገልጋዮቹ ‘የአምላክን እውቀት ይፈልጉና ያገኙ’ ዘንድ እነዚህን ሁሉ መሣሪያዎች “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት አዘጋጅቷል። (ምሳሌ 2:​4, 5) ጥሩ የጥናት ልማድ ይሖዋ የሚሰጠውን እውቀት በተሻለ መንገድ እንድናገኝና ከእርሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዲኖረን ያስችለናል። (መዝሙር 63:​1-8) አዎን፣ ጥናት ሥራ ነው፤ ሆኖም አስደሳችና የሚክስ ሥራ ነው። ጊዜም ይፈልጋል። ‘መጽሐፍ ቅዱስን በትኩረት ለማንበብና በግል ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ ከየት ላገኝ እችላለሁ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይህንን ዘርፍ የዚህ ተከታታይ ርዕስ መደምደሚያ በሆነው በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሺነሪ ኦቭ ኦልድ ቴስታመንት ቲኦሎጂ ኤንድ ኤክዘጄሲስ፣ ጥራዝ 4 ገጽ 205-207

b ነሐሴ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13 አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ በዚህ እትም ላይ የወጡትን ሁለቱን የጥናት ርዕሶች ልትከልስ በተጨማሪም በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔዲያ ላይ የሚገኙትን “ፍትሕ፣” [Justice] “ምሕረት” [Mercy] እና “ጽድቅ” [Righteousness] የሚሉትን ርዕሶች መመልከት ትችላለህ።

c ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመ። ይህ መሣሪያ በቋንቋህ ማግኘት የማትችል ከሆነ ከነሐሴ 15, 1993 ገጽ 13-17፤ ከግንቦት 15, 1986 (እንግሊዝኛ) ገጽ 19-20 መጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ ግሩም የሆኑ የአጠናን ዘዴዎችን ማግኘት ትችላለህ።

የክለሳ ጥያቄዎች

• የግል ጥናታችንን መንፈስን የሚያድስና የሚክስ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

• እንደ መዝሙራዊው የይሖዋን ቃል ‘መውደድ’ እና ‘ማሰላሰል’ የምንችለው እንዴት ነው?

• የአምላክን ቃል ለማጥናት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ምሳሌ 2:​1-6 የሚያሳየው እንዴት ነው?

• ይሖዋ ምን ግሩም የማጥኛ መሣሪያዎች ሰጥቶናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጸጥታ ማብላላትና ጸሎት የአምላክን ቃል እንድንወድድ ይረዱናል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል በጥልቀት ለመቆፈር የተዘጋጁልህን የማጥኛ መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ ትጠቀምባቸዋለህ?