በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎች ሃይማኖቶችን መመርመር ይኖርብሃልን?

ሌሎች ሃይማኖቶችን መመርመር ይኖርብሃልን?

ሌሎች ሃይማኖቶችን መመርመር ይኖርብሃልን?

“ለአንድ ዓመት ያህል በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የተገኘሁ ሲሆን ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች መናገር ያስደስተኛል” ሲል በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር የሆነውና በደቡብ አሜሪካ የሚኖረው ሜጌል ተናግሯል። “ከዚያም በሬዲዮ የሚተላለፉ ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞችን መከታተልና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ሃይማኖታዊ ሰባኪዎችን መመልከት ጀመርኩ። እንዲህ ያሉት ፕሮግራሞች የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ስለሆኑ ሰዎች በተሻለ መንገድ እንድረዳ ያስችለኛል ብዬ አስብ ነበር። ትምህርቶቻቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጩ ብገነዘብም የማወቅ ጉጉት አድሮብኝ ነበር።”

በዚሁ አገር የሚኖረው ሆርሄ ስለ እውነተኛው አምልኮ ሌሎች ሰዎችን በቅንዓት ያስተምር ነበር። ሆኖም እርሱም በሆነ አጋጣሚ በራዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡትን ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች መከታተል ጀመረ። ብዙውን ጊዜ “ሌሎች ምን ብለው እንደሚያስቡ ማወቅ አለብህ” ይል ነበር። ለሐሰት ትምህርቶች መጋለጥ የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተ ሲጠየቅ “አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ካወቀ እምነቱን ምንም ነገር ሊሸረሽረው አይችልም” የሚል መልስ ይሰጣል። እነዚህ ሁኔታዎች አንድ አንገብጋቢ ጥያቄ ያስነሳሉ። ሌሎች ምን ብለው እንደሚያምኑ ማዳመጥ ጥበብ ነውን?

እውነተኛውን ክርስትና ለይቶ ማወቅ

ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ እውነተኛው አምልኮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በመጣው በክርስትና ስም የሚደረግ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ተበከለ። ኢየሱስ አስቀድሞ ይህንን በመገንዘብ እንዲህ ያሉትን አስመሳይ ክርስትናዎች ከእውነተኛው ክርስትና መለየት የሚቻልበትን አንድ መንገድ ገልጿል። በመጀመሪያ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠ:- “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።” ከዚያም “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ሲል አከለ። (ማቴዎስ 7:​15-23) እውነተኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች እርሱ ያስተማራቸውን ነገሮች ተግባራዊ የሚያደርጉ ሲሆን በመልካም ፍሬያቸው በቀላሉ ተለይተው ይታወቃሉ። ኢየሱስ ራሱ እንዳደረገው እነርሱም የአምላክን መንግሥት ከቅዱሳን ጽሑፎች ለማብራራት ወደ ሰዎች ይሄዳሉ። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከዓለም ፖለቲካም ሆነ ከማህበራዊ ውዝግቦች ይርቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስን የአምላክ ቃል አድርገው የሚቀበሉ ሲሆን መጽሐፉ እውነት መሆኑን ከማመን የመነጨ አክብሮት አላቸው። የአምላክን ስም ለሌሎች ያሳውቃሉ። ከአምላክ የተማሩትን ፍቅር በተግባር ለማዋል ከፍተኛ ጥረት ስለሚያደርጉ በጦርነቶች አይካፈሉም። ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳቸው እንደ ወንድማማች ይተያያሉ።​—⁠ሉቃስ 4:​43፤ 10:​1-9፤ ዮሐንስ 13:​34, 35፤ 17:​16, 17, 26

ቅዱሳን ጽሑፎችን “በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል” ያለውን ልዩነት ማስተዋል እንደሚቻል ይናገራሉ። (ሚልክያስ 3:​18) በዛሬው ጊዜ የሚገኙት እውነተኛ አምላኪዎች እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በሐሳብና በሥራ አንድ ናቸው። (ኤፌሶን 4:​4-6) እንዲህ ያለውን የእውነተኛ ክርስቲያኖች ቡድን አንዴ ካገኘህ በኋላ ስለ ሌሎች እምነቶች ለማወቅ የምታጠያይቅበትና የምትጓጓበት ምን ምክንያት ይኖራል?

ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ተጠንቀቁ

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከተማሩም በኋላ በሐሰት ትምህርቶች አማካኝነት በመንፈሳዊ የመበከል አደጋ ሊያጋጥም አንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል:- “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ [“እንዳያጠምዳችሁ፣” የ1980 ትርጉም] ተጠበቁ።” (ቆላስይስ 2:​8) እንዴት ሕያው የሆነ መግለጫ ነው! ሊያጠምዱህና ሊውጡህ እንደሚፈልጉ አውሬዎች ሁሉ የሐሰተኛ አስተማሪዎችም በጣም አደገኞች ሊሆኑ ይችላሉ።

እርግጥ ነው፣ ጳውሎስም ሌሎች ምን ብለው እንደሚያምኑ ያውቅ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ንግግሩን የከፈተው እንዲህ በማለት ነበር:- “የአቴና ሰዎች ሆይ፣ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ:- ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና።” (ሥራ 17:​22, 23) ሆኖም ጳውሎስ ዘወትር በግሪካውያን ፍልስፍና አእምሮውን ይሞላ ነበር ማለት አይደለም።

የሐሰት ሃይማኖቶችን መሠረትና እምነት ማወቁ አንድ ነገር ሲሆን አእምሮን በትምህርቶቻቸው መሙላት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። a ይሖዋ በቃሉ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ምግብ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾሟል። (ማቴዎስ 4:​4፤ 24:​45) ጳውሎስ ራሱ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። ወይስ ጌታን እናስቀናውን?”​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​20-22

አንዳንድ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ቀድሞ እውነተኛ ክርስቲያኖች የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም በአንድ ወቅት ከእውነት ፊታቸውን በማዞር ወደ ስህተት ተመልሰዋል። (ይሁዳ 4, 11) ይህ ሊያስደንቀን አይገባም። ኢየሱስ የቅቡዕ ክርስቲያኖችን ቡድን ስለሚያመለክተው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከተናገረ በኋላ “ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል” በማለት ባልንጀሮቹን መምታት ስለሚጀምር “ክፉ ባሪያ” አክሎ ተናግሮአል። (ማቴዎስ 24:​48, 49) እንዲህ ያሉት ግለሰቦችና ተከታዮቻቸው አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸው የሆነ ግልጽ ትምህርት የላቸውም። እነርሱ የሚፈልጉት የሌሎችን እምነት መገልበጥ ብቻ ነው። እንዲህ ያሉትን ሰዎች አስመልክቶ ሐዋርያው ዮሐንስ የሚከተለውን ጽፏል:- “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት።”​—⁠2 ዮሐንስ 10፤ 2 ቆሮንቶስ 11:​3, 4, 13-15

እውነትን የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከተለያዩ ሃይማኖቶች የሚሰሟቸውን ነገሮች በጥንቃቄ መመርመር ይኖርባቸዋል። አምላክ እውነትን የሚፈልጉ ቅን ሰዎችን ይባርካል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ጥበብን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ . . . የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።” (ምሳሌ 2:​4, 5) እውነተኛ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት እንዲህ ያለውን የአምላክ እውቀት በማግኘታቸውና እንዲህ በመሰለው እውቀት የሚመሩትን ሰዎች ይሖዋ ሲባርካቸው በመመልከታቸው የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን ማዳመጣቸውን አይቀጥሉም።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​14

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ (እንግሊዝኛ) በሚል ርዕስ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማህበር የተዘጋጀው መጽሐፍ የአብዛኞቹን የዓለም ሃይማኖቶች አመጣጥና ትምህርት በተመለከተ መሠረታዊ የሆነ እውቀት ይሰጣል።