በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስ ቅዱስን የግል ረዳቴ አድርጌዋለሁን?

መንፈስ ቅዱስን የግል ረዳቴ አድርጌዋለሁን?

መንፈስ ቅዱስን የግል ረዳቴ አድርጌዋለሁን?

ሌላውን ሕዝብ እንኳ ብንተወው ሃይማኖታዊ ምሁራን የሚባሉት ራሳቸው የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ምንነት በተመለከተ ያላቸው ሐሳብ የተለያየ ነው። ሆኖም እንዲህ ያለው ግራ መጋባት አላስፈላጊ ነው። መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይነግረናል። አንዳንዶች እንደሚሉት ራሱን የቻለ አንድ አካል ሳይሆን አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምበት ብርቱ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው።​—⁠መዝሙር 104:​30፤ ሥራ 2:​33፤ 4:​31፤ 2 ጴጥሮስ 1:​21

መንፈስ ቅዱስ የአምላክን ዓላማዎች ከማስፈጸም ጋር በቅርብ የተሳሰረ በመሆኑ ሕይወታችን ከዚህ መንፈስ ጋር እንዲስማማ መጣር ይኖርብናል። የግል ረዳታችን እንዲሆን መፈለግ ይኖርብናል።

ረዳት​—⁠ለምን አስፈለገ?

ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚሄድበት ጊዜ ሲቃረብ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ሲል አጽናናቸው:- “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ [“ረዳት፣” NW ] ይሰጣችኋል።” አክሎም “እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” በማለት ተናገረ።​—⁠ዮሐንስ 14:​15, 16, 17፤ 16:​7

ኢየሱስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ከበድ ያለ ተልዕኮ ሰጣቸው። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ይህ ሥራ ተቃውሞ እያለም መሠራት ስላለበት ቀላል አይሆንም።​—⁠ማቴዎስ 10:​22, 23

ከውጭ ከሚያጋጥማቸው ተቃውሞ በተጨማሪ በጉባኤው ውስጥም መጠነኛ ግጭት ነበር። በ56 እዘአ አካባቢ ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፎላቸው ነበር:- “ወንድሞች ሆይ፣ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፣ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፣ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ።” (ሮሜ 16:​17, 18) ይህ ሁኔታ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ በጣም ይባባስ ስለነበር ጳውሎስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው:- “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኵላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።”​—⁠ሥራ 20:​29, 30

እነዚህን እንቅፋቶች ለመቋቋም የአምላክ እርዳታ ያስፈልግ ነበር። አምላክም በኢየሱስ በኩል አስፈላጊውን እርዳታ ሰጥቷል። ከትንሣኤው በኋላ ማለትም በ33 እዘአ በዋለው የጰንጤቆስጤ ዕለት በ120 ተከታዮቹ ላይ “መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።”​—⁠ሥራ 1:​15፤ 2:​4

በዚህ ጊዜ የፈሰሰው መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ እልከዋለሁ ብሎ ቃል የገባው ረዳት እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱ ተገንዝበው ነበር። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ የሰጠውን ማብራሪያ ደቀ መዛሙርቱ አሁን በተሻለ መንገድ እንደሚረዱት ምንም ጥርጥር የለውም። “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ [“ረዳት፣” NW ] እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐንስ 14:​26) በተጨማሪም ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን “ረዳት” እና “የእውነት መንፈስ” በማለት ጠርቶታል።​—⁠ዮሐንስ 15:​26 NW 

መንፈስ ረዳት የሚሆነው እንዴት ነው?

መንፈስ እንደ ረዳት ሆኖ የሚያገለግለው በብዙ መንገዶች ነው። በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን ነገሮች መንፈስ እንደሚያስታውሳቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። ሆኖም እንዲህ ሲል መንፈስ እንዲያስታውሱ የሚረዳቸው ቃላትን ብቻ ነው ማለት አይደለም። የኢየሱስን ትምህርቶች ጥልቅ ትርጉምና የሚያስተላልፉትን ቁም ነገር እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል። (ዮሐንስ 16:​12-14) በአጭሩ፣ መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እውነትን በተሻለ መንገድ እንዲረዱ ያደርጋቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው።” (1 ቆሮንቶስ 2:​10) ቅቡዓን የኢየሱስ ተከታዮች ትክክለኛውን እውቀት ለሌሎች ማስተላለፍ እንዲችሉ እነርሱም ጠለቅ ያለ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል።

ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲጸልዩና ይህንንም አዘውትረው እንዲያደርጉ አስተምሯቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት መጸለይ እንደሚገባቸው እርግጠኞች በማይሆኑበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሊማልድላቸው ወይም ሊረዳቸው ይችላል። “እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል።”​—⁠ሮሜ 8:​26

ሦስተኛ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለእውነት ጠበቃ ሆነው በሕዝብ ፊት በሚቆሙበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ይረዳቸዋል። ኢየሱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር:- “ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ በምኵራቦቻቸውም ይገርፉአችኋል . . . ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ። አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፣ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፣ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።”​—⁠ማቴዎስ 10:​17-20

መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያን ጉባኤን ለይቶ ለማወቅ ከማስቻሉም በላይ አባላቱም በግላቸው ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል። እነዚህን ሁለት ዘርፎች ይበልጥ ሰፋ ባለ መልኩ በማየት በዛሬው ጊዜ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳዘሉ እንመርምር።

መለያ ምልክት ሆኖ ያገለግላል

ለብዙ መቶ ዘመናት አይሁዳውያን በሙሴ ሕግ የሚመሩ የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ሆነው አገልግለዋል። ሆኖም የኢየሱስን መሲሕነት ባለመቀበላቸው ብዙም ሳይቆይ አምላክ እንደሚተዋቸው ኢየሱስ አስቀድሞ ተናግሯል። “ግንበኞች የናቁ[ት] ድንጋይ፣ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፣ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።” (ማቴዎስ 21:​42, 43) የክርስቲያን ጉባኤ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ከተቋቋመ በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች ‘የአምላክን መንግሥት ፍሬ የሚያደርግ ሕዝብ’ ሆነዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ጉባኤ አምላክ የሚጠቀምበት የመገናኛ መሥመር ሆኖ አገልግሏል። አምላክ መለኮታዊውን ሞገስ የሰጣቸውን ሰዎች ለይቶ ለማወቅ እንዲቻል ሲል የማያሳስት መለያ ምልክት ሰጠ።

በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ከዚህ በፊት ፈጽሞ ተምረውት በማያውቁት ቋንቋ እንዲናገሩ ሲያደርጋቸው ይህንን የተመለከቱ ሰዎች በአድናቆት ተውጠው “እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?” ብለው ጠይቀዋል። (ሥራ 2:​7, 8) ሐዋርያት በማያውቁት ቋንቋ መናገራቸውና “ብዙ ድንቅና ምልክት” ማድረጋቸው ሦስት ሺህ የሚያክሉ ሰዎች በእርግጥ የአምላክ መንፈስ በመሥራት ላይ መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።​—⁠ሥራ 2:​41, 43

በተጨማሪም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃትና ራስን መግዛት ያሉትን ‘የመንፈስ ፍሬዎች’ በማፍራት የአምላክ አገልጋዮች መሆናቸው በግልጽ ተለይቶ ሊታወቅ ችሏል። (ገላትያ 5:​22, 23) እንዲያውም ፍቅር ከምንም በላይ እውነተኛውን የክርስቲያን ጉባኤ ለይቶ አሳውቋል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 13:​34, 35

የመጀመሪያው ክርስቲያን ጉባኤ አባላት የመንፈስ ቅዱስን አመራር ከመቀበላቸውም በላይ መንፈሱ ከሚሰጣቸው እርዳታ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ክርስቲያኖች አምላክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዳደረገው የሞቱትን የማያስነሳና ተዓምራትን የማያደርግ መሆኑን ቢገነዘቡም የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች እውነተኞቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እነርሱ መሆናቸውን ለይተው እንዲያሳውቋቸው ይፈቅዳሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​8

የግል ውሳኔዎች ለማድረግ የሚያግዝ ረዳት

መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስ ውጤት ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲመራን ስንፈቅድ ልክ መንፈስ ቅዱስ ያስተማረን ያህል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ይሁን እንጂ እንደዚያ እንዲያደርግ እንፈቅድለታለን?

የሙያ ወይም የሥራ ምርጫችንን በተመለከተ ምን ማለት ይቻላል? መንፈስ ቅዱስ አንድ ሥራ ለመጀመር ስናስብ ሥራውን በይሖዋ ዓይን እንድንመለከተው ይረዳናል። ተቀጥረን የምንሠራው ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። በተጨማሪም ቲኦክራሲያዊ ግቦችን እንድንከታተል የሚረዳን መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። ደሞዙ ወይም ከሥራው ጋር ተያይዞ የሚመጣው ክብርና ዝና ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር አይደለም። ዋናው ነገር ሥራው ለመኖር የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች እንድናሟላ የሚያስችለንና ክርስቲያናዊ ግዴታዎቻችንን ለመፈጸም በቂ ጊዜና አጋጣሚ የሚሰጠን መሆኑ ነው።

በሕይወት ለመደሰት መፈለግ ተፈጥሯዊም ተገቢም ነው። (መክብብ 2:​24፤ 11:​9) ስለዚህ ሚዛናዊ የሆነ ክርስቲያን አእምሮውን ለማደስና ለመደሰት በመዝናኛ ይጠቀም ይሆናል። ሆኖም ይህን ሲያደርግ የመንፈስ ፍሬ የሚንጸባረቅበትን የመዝናኛ ዓይነት እንጂ “የሥጋ ሥራ” የሚንጸባረቅበትን የመዝናኛ ዓይነት አይመርጥም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቊጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል ነው።” በተጨማሪም ‘እርስ በርስ መነሣሣት፣ መቀናናትና በከንቱ መመካት’ ሊወገድ የሚገባው ነገር ነው።​—⁠ገላትያ 5:​16-26

የጓደኛ ምርጫን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጓደኞች በምንመርጥበት ጊዜ እንደ መመዘኛ አድርገን የምንወስደው ውጫዊ መልካቸውን ወይም ያሏቸውን ነገሮች ሳይሆን መንፈሳዊነታቸውን መሆኑ ጥበብ ነው። ዳዊት የተባለው ሰው በእርግጥ የአምላክ ወዳጅ ስለነበር “እንደ ልቤ የሆነ ሰው” በማለት አምላክ ተናግሮለታል። (ሥራ 13:​22) አምላክ “ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” በሚለው መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት የዳዊትን ውጫዊ መልክ ሳያይ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን መርጦታል።​—⁠1 ሳሙኤል 16:​7

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጓደኝነቶች በውጫዊ መልክ ወይም በንብረት ላይ በመመሥረታቸው ፈርሰዋል። በሚያልፍ ባለጠግነት ላይ የተመሠረቱ ጓደኝነቶች ድንገት ሊያከትሙ ይችላሉ። (ምሳሌ 14:​20) በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ለጓደኝነት የምንመርጣቸው ሰዎች ይሖዋን ለማገልገል ሊረዱን የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ይመክረናል። ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ስለሚያስገኝ በመስጠት ላይ እንድናተኩር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ሥራ 20:​35) ለጓደኞቻችን መስጠት ከምንችላቸው በጣም ውድ ስጦታዎች መካከል ጊዜያችንና ፍቅራችን ይገኙበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ጓደኛ ለሚፈልግ አንድ ክርስቲያን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ:- ‘ፊትና ቁመናን ብቻ ሳይሆን እግርንም ተመልከት’ የሚለን ያህል ነው። እግር? አዎን፣ እግሮቹን ይሖዋ የሰጠንን የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ሥራ ለማካሄድ እየተጠቀመባቸው ነውን? በይሖዋ ፊትስ ያማሩ ሆነው ይታያሉ ለማለት ይቻላልን? የእውነትን መልእክትና የሰላሙን ምሥራች ተጫምተዋልን? እንዲህ የሚል እናነባለን:- “የምስራች የሚናገር፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም:- አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።”​—⁠ኢሳይያስ 52:​7፤ ኤፌሶን 6:​15

የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ እርዳታ ያስፈልገናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ረዳት የሆነው መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የግል ረዳት ከመሆኑም በላይ ይሠሩት ለነበረው ሥራ ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥቷቸዋል። እኛም የመንፈስ ቅዱስ ውጤት የሆነውን የአምላክ ቃል በትጋት ማጥናታችን መንፈስ ቅዱስ የግል ረዳታችን እንዲሆን ማድረግ የምንችልበት ዋነኛ መንገድ ነው። እኛስ እንዲህ አድርገናል?