በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓይን ወደማይታይ አምላክ መቅረብ ትችላለህን?

በዓይን ወደማይታይ አምላክ መቅረብ ትችላለህን?

በዓይን ወደማይታይ አምላክ መቅረብ ትችላለህን?

‘በዓይን ከማላየው አካል ጋር እንዴት የቅርብ ዝምድና መመሥረት እችላለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይህ ተገቢ ጥያቄ ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ እስቲ ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር:-

ፍቅራዊና ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት የማየት አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? ሊታዩ የማይችሉ ነገሮች በዓይን ከሚታዩት በማይተናነስ መልኩ ምናልባትም በበለጠ ሁኔታ አስፈላጊ አይደሉምን? በእርግጥ ናቸው! ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች በቋሚነት በሚደረግ የደብዳቤ ልውውጥ አማካኝነት ከሌሎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ችለዋል። ደብዳቤዎቻቸው የሚወዷቸውንና የሚጠሏቸውን ነገሮች፣ ግቦቻቸውን፣ የሚመሩባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ተጫዋችነታቸውንና ሌሎች የግል ባሕሪዎቻቸውን ወይም ፍላጎቶቻቸውን በግልጽ ያንጸባርቃሉ።

ማየት የተሳናቸው ሰዎችም ከሌላ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ማየት የግድ አስፈላጊ አለመሆኑን ሊያረጋግጡ ይችላሉ። ማየት የተሳናቸውን የትዳር ጓደኛሞች ኤድዋርድንና ግዌንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። a ኤድዋርድና ግዌን የተገናኙት ማየት የተሳናቸው ሰዎች በሚማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ጎልማሳ ተማሪዎች በነበሩበት ጊዜ ነበር። ኤድዋርድ በግዌን ባሕርያት በተለይ ደግሞ በንግግሯና በጠባይዋ በሚንጸባረቀው ሐቀኝነት እንዲሁም ለሥራ ባላት ግሩም አመለካከት ተማርኮ ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ግዌን በኤድዋርድ ልትማረክ የቻለችበትን ምክንያት ስትገልጽ “ከልጅነቴ ጀምሮ የተማርኳቸው አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያት በሙሉ ስለነበሩት ነው” ብላለች። መጠናናት ጀመሩና ከሦስት ዓመት በኋላ ተጋቡ።

ኤድዋርድ እንዲህ ይላል:- “ከሌላ ሰው ጋር አብራችሁ በምትሆኑበት ጊዜ ወዳጅነት በመመሥረት ረገድ ማየት አለመቻል የሚያመጣው ለውጥ የለም። እርስ በርሳችሁ መተያየት ባትችሉም እንኳ አንዱ የሌላውን ስሜት መረዳት ይችላል።” አሁን 57 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም በመካከላቸው ያለው የጠበቀ ፍቅር አልቀዘቀዘም። ግሩም የሆነ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ያስቻሏቸው ቢያንስ አራት ነገሮች እንዳሉ ይናገራሉ:- (1) የሌላውን ሰው ጥሩ ባሕርያት ማስተዋል፣ (2) በእነዚህ ባሕርያት ላይ ማሰላሰልና በባሕርያቱ መሳብ፣ (3) ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማዳበር እና (4) አንዳንድ ነገሮችን አብሮ መሥራት።

እነዚህ አራት ነጥቦች ለማንኛውም ዓይነት ዝምድና ማለትም በወዳጆችም ሆነ በትዳር ጓደኛሞች መካከል ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰዎችና በአምላክ መካከል ጥሩ ወዳጅነት ለመመሥረት ወሳኝ ናቸው። ምንም እንኳ አምላክን ማየት ባንችልም እነዚህን ነጥቦች በሥራ ላይ ማዋላችን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት እንዴት ሊረዳን እንደሚችል ቀጥሎ ባለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን። b

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

b ከሰዎች ጋር ከሚኖረን ዝምድና በተለየ መልኩ ከአምላክ ጋር የሚኖረን ዝምድና ሕልውናውን አምኖ በመቀበል ላይ የተመሠረተ ነው። (ዕብራውያን 11:​6) በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት መገንባትን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመውን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ልታነብ ትችላለህ።