በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ አምላክ መቅረብ የምትችልበት መንገድ

ወደ አምላክ መቅረብ የምትችልበት መንገድ

ወደ አምላክ መቅረብ የምትችልበት መንገድ

ያዕቆብ 4:​8 “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” ይላል። ይሖዋ አምላክ ለእኛ ሲል ልጁን መስጠቱ ሰዎች ምን ያህል ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ እንደሚፈልግ ያሳያል።

አምላክ ቀዳሚ በመሆን ላደረገልን ፍቅራዊ ዝግጅት ሐዋርያው ዮሐንስ ምላሽ ሲሰጥ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ [አምላክን] እንወደዋለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:​19) ሆኖም እኛ በግላችን ወደ አምላክ ለመቅረብ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ አለብን። ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው እነዚህ እርምጃዎች ከሰዎች ጋር ለመቀራረብ ከሚረዱን አራት መንገዶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እስቲ መንገዶቹን እንመርምር።

የአምላክን ግሩም ባሕርያት ተመልከት

አምላክ በርካታ ግሩም ባሕርያት አሉት። ጎላ ብለው ከሚታዩት ባሕርያቱ መካከል ፍቅር፣ ጥበብ፣ ፍትሕ እና ኃይል ይገኙበታል። ጥበቡና ኃይሉ በጣም ግዙፍ ከሆኑት የከዋክብት ረጨቶች አንስቶ ጥቃቅን እስከሆኑት አተሞች ድረስ ርቆ በሚገኘው አጽናፈ ዓለምም ሆነ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በሚገባ ተንጸባርቋል። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።”​—⁠መዝሙር 19:​1፤ ሮሜ 1:​20

የፍጥረት ሥራ የአምላክን ፍቅርም ያንጸባርቃል። ለምሳሌ ያህል የተፈጠርንበት መንገድ አምላክ በሕይወት እንድንደሰት እንደሚፈልግ ያሳያል። ቀለም የመለየት፣ የመቅመስና የማሽተት፣ ሙዚቃ የማጣጣም፣ የመሳቅ፣ ውበት የማድነቅ ችሎታ በተጨማሪም ለመኖር የግድ አስፈላጊ ያልሆኑ ሌሎች በርካታ ተሰጥኦዎችና ባሕርያት ሰጥቶናል። አዎን፣ አምላክ በእርግጥ ለጋስ፣ ደግና አፍቃሪ ነው። እነዚህ ባሕርያት “ደስተኛ አምላክ” እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ምንም ጥርጥር የለውም።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​11 NW፤ ሥራ 20:​35

ይሖዋ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበትና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን ለሉዓላዊነቱ የሚሰጡት ድጋፍ በዋነኛነት በፍቅር ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው ያስደስተዋል። (1 ዮሐንስ 4:​8) ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ቢሆንም ሰዎችን በተለይ ደግሞ ታማኝ አገልጋዮቹን አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹን በሚይዝበት መንገድ ይይዛቸዋል። (ማቴዎስ 5:​45) ከሚጠቅማቸው ነገር ውስጥ ምንም አያስቀርባቸውም። (ሮሜ 8:​38, 39) ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ለእኛ ሲል የአንድያ ልጁን ሕይወት እንኳ ሰጥቷል። አዎን፣ የአምላክ ፍቅር ሕልውና እንድናገኝና የዘላለማዊ ሕይወት ተስፋ እንዲኖረን አስችሎናል።​—⁠ዮሐንስ 3:​16

ኢየሱስ ፍጹም በሆነ መንገድ የአባቱን ባሕርያት ስላንጸባረቀ የአምላክን ባሕርያት በጥልቅ እንድናስተውል አስችሎናል። (ዮሐንስ 14:​9-11) ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ፈጽሞ የራቀ፣ ለሰው ስሜት የሚጠነቀቅና አሳቢ ነበር። በአንድ ወቅት ሰዎች መስማት የተሳነውና አጥርቶ መናገር የማይችል ሰው ወደ ኢየሱስ ይዘው መጡ። ሰውዬው በሕዝቡ መሃል በነበረበት ጊዜ ተሸማቅቆ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ትችላለህ። ኢየሱስ ሰውዬውን ከሕዝቡ ገለል አድርጎ በመውሰድ መፈወሱ ትኩረት የሚስብ ነው። (ማርቆስ 7:​32-35) ለስሜትህ የሚጠነቀቁና ክብርህን የሚጠብቁ ሰዎችን ታደንቃለህን? የምታደንቅ ከሆነ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ የበለጠ ባወቅህ መጠን ወደ እነሱ ይበልጥ እንደምትቀርብ የተረጋገጠ ነው።

ስለ አምላክ ባሕርያት አስብ

አንድ ሰው የሚደነቁ ባሕርያት ሊኖሩት ይችላሉ። ሆኖም ወደ ሰውዬው መቅረብ እንድንችል ስለ ባሕርያቱ ማሰብ ይኖርብናል። ወደ ይሖዋ ለመቅረብም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በይሖዋ ባሕርያት ላይ ማሰላሰል ወደ እሱ ለመቅረብ የሚያስችል ሁለተኛው ወሳኝ እርምጃ ነው። ይሖዋን ከልቡ ይወድ የነበረውና ‘እንደ [ይሖዋ] ልብ’ ሆኖ የተገኘው ንጉሥ ዳዊት “የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፣ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ” ሲል ተናግሯል።​—⁠ሥራ 13:​22፤ መዝሙር 143:​5

አስደናቂ የሆኑትን የፍጥረት ሥራዎች ስትመለከት ወይም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ እንደ ዳዊት አንተም በምታየውና በምታነበው ነገር ላይ ታሰላስላለህን? አባቱን በጣም የሚወድ ልጅ ከአባቱ የተላከለት ደብዳቤ ሲደርሰው ምን እንደሚያደርግ አስብ። ደብዳቤውን እንዴት ይመለከተዋል? እንዲሁ ላይ ላዩን ተመልክቶ እንደጨረሰ መሳቢያ ውስጥ እንደማያስቀምጠው የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ ለመረዳት በጥንቃቄ ያነብበዋል። በተመሳሳይ የአምላክ ቃል “አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” ሲል ለዘመረው ለመዝሙራዊው ውድ እንደነበረ ሁሉ ለእኛም ውድ መሆን አለበት።​—⁠መዝሙር 119:​97

ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማዳበር

ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማንኛውም ዓይነት ወዳጅነት ወሳኝ ነው። ይህ ደግሞ ልብ ለልብ መነጋገርን እና መደማመጥን ይጠይቃል። በጸሎት አማካኝነት ፈጣሪን የምናነጋግረው ሲሆን ይህም አምልኮታዊ በሆነ መንገድ ከአምላክ ጋር ሐሳብ መለዋወጥ ማለት ነው። ይሖዋ የሚወዱትና የሚያገለግሉት እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ የእሱ ዋና ወኪል መሆኑን አምነው የሚቀበሉ ሰዎች በሚያቀርቡት ጸሎት ይደሰታል።​—⁠መዝሙር 65:​2፤ ዮሐንስ 14:​6, 14

ባለፉት ዘመናት አምላክ በራእይ፣ በሕልም፣ በመላእክትና በሌሎችም መንገዶች በመጠቀም ለሰው ልጆች ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜ ግን የሚናገረው በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ብዙ ጥቅሞች አሉት። በማንኛውም ጊዜ ምክር ልናገኝበት እንችላለን። ልክ እንደ ደብዳቤ ደግመን ደጋግመን ልናነበው እንችላለን። እንዲሁም በቃል እንደሚተላለፍ መልእክት በቀላሉ የሚዛባበት ሁኔታ አይፈጠርም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ አፍቃሪ ከሆነው ሰማያዊ አባትህ የተላከ ትልቅ የደብዳቤዎች ጥርቅም እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው፤ እንዲሁም በእነዚህ ደብዳቤዎች አማካኝነት በየዕለቱ እንዲያነጋግርህ ፍቀድለት።​—⁠ማቴዎስ 4:​4

ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ያለውን አመለካከት ይገልጻል። አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ያለውን ዓላማ ይናገራል። እንዲሁም ታማኝ ከሆኑ አምላኪዎች አንስቶ ክፉ እስከሆኑት ጠላቶች ድረስ ከተለያዩ ሰዎችና መንግሥታት ጋር የነበረውን ግንኙነት ይገልጻል። ይሖዋ ከሰዎች ጋር ያደረገው ግንኙነት በዚህ መንገድ እንዲሰፍር በማድረግ ባሕርይውን በተመለከተ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዝርዝር መግለጫ ሰጥቶናል። ፍቅሩን፣ ደስታውን፣ ሐዘኑን፣ ቅሬታውን፣ ቁጣውን፣ ምህረቱንና አሳቢነቱን ጨምሮ አስተሳሰቡንና ስሜቱን በአጠቃላይ እንዲሁም ከበስተኋላ ያሉትን ምክንያቶች ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉበት መንገድ ገልጿል።​—⁠መዝሙር 78:​3-7

ከአምላክ ቃል የተወሰነ ክፍል አንብበህ ስትጨርስ ካነበብከው ነገር ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? በተለይ ደግሞ ይበልጥ ወደ አምላክ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ነጥቡ ልብህን እንዲነካ በመፍቀድ ስለ አምላክ ባነበብከውና በተማርከው ነገር ላይ አስብ። ከዚያም ስላገኘኸው ትምህርት የሚሰማህን ውስጣዊ ስሜትና ሐሳብ እንዲሁም ከትምህርቱ ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት ለይሖዋ በጸሎት ንገረው። የሐሳብ ግንኙነት የምታደርገው በዚህ መንገድ ነው። በአእምሮህ የያዝካቸው ሌሎች ነገሮችም ካሉ እነዚህም በጸሎትህ ሊካተቱ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።

ከአምላክ ጋር ሥሩ

መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ታማኝ ሰዎች ከአምላክ ጋር ወይም በእውነተኛው አምላክ ፊት እንደሄዱ ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:​9፤ 1 ነገሥት 8:​25) ይህ ምን ማለት ነው? በሕይወት ባሳለፉት በእያንዳንዱ ቀን አምላክ ልክ አጠገባቸው እንዳለ አድርገው ያስቡ ነበር ማለት ነው። እርግጥ ኃጢአተኞች ናቸው። ሆኖም የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ይወድዱ ነበር፤ ደግሞም ከአምላክ ዓላማ ጋር ተስማምተው ኖረዋል። መዝሙር 32:​8 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ እንደነዚህ ወዳሉት ሰዎች ይቀርባል እንዲሁም ያስብላቸዋል:- “አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ።”

ለአንተም ይሖዋ አብሮህ የሚሄድ፣ የሚያስብልህና አባታዊ ምክር የሚሰጥህ የቅርብ ወዳጅ ሊሆንልህ ይችላል። ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ‘የሚረባህን ነገር የሚያስተምርህ በምትሄድበትም መንገድ የሚመራህ’ እንደሆነ ገልጿል። (ኢሳይያስ 48:​17) እነዚህን ጥቅሞች ስናገኝ ልክ እንደ ዳዊት እኛም ይሖዋ ‘በቀኛችን’ እንዳለ ሆኖ ይሰማናል።​—⁠መዝሙር 16:​8

የአምላክ ስም ባሕርያቱን ይወክላል

ብዙ ሃይማኖቶችና ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን የግል ስም ከመጠቀምና ከማሳወቅ ታቅበዋል። (መዝሙር 83:​18 NW ) ሆኖም በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም ወደ 7, 000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል! (ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም ቢያወጡትም እንኳ በአንጻሩ እንደ በኣል፣ ቤል፣ ሜሮዳክና አልፎ ተርፎም ሰይጣን የመሳሰሉትን በበኩረ ጽሑፉ ላይ የተጠቀሱ በርካታ የሐሰት አማልክት ስሞች ተጠቅመዋል!)

አንዳንድ ሰዎች የአምላክን ስም ማውጣቱ ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም እስቲ አስበው:- ስም የሌለውን ሰው በሚገባ ማወቅና ከእንዲህ ዓይነቱ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ከባድ ነው ወይስ ቀላል? እንደ አምላክ እና ጌታ የመሳሰሉት የማዕረግ ስሞች (ለሐሰት አማልክትም ይሠራባቸዋል) ይሖዋ ባለው ኃይል፣ ሥልጣን ወይም ቦታ ላይ እንድናተኩር ሊያደርጉ ቢችሉም ምንም በማያሻማ መልኩ እሱን ለይቶ የሚያሳውቀው የግል ስሙ ብቻ ነው። (ዘጸአት 3:​15፤ 1 ቆሮ​ንቶስ 8:​5, 6) የእውነተ​ኛው አምላክ የግል ስም ባሕርያቱንና ዓይነተኛ ጠባዮቹን ይወክላል። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ዎልተር ሎውሬ እንዲህ ሲሉ በትክክል ተናግረዋል:- “አምላክን በስሙ የማያውቅ ሰው ስብዕና ያለው አካል አድርጎ ሊመለከተው አይችልም።”

በአውስትራሊያ የምትኖረውንና ቅን ካቶሊክ የነበረችውን ማሪያን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ማሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስትገናኝ ምሥክሮቹ የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩአት። ምን ምላሽ ሰጠች? “ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የአምላክን ስም ስመለከት አለቀስኩ። የአምላክን የግል ስም በትክክል ማወቅና መጠ⁠ቀም እንደምችል ስገነዘብ በጥልቅ ተነካሁ።” ማሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን ቀጠለችና በሕይወቷ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሖዋ ስብዕና ያለው አካል እንደሆነ በመገንዘብ ከእሱ ጋር ዘላቂ ወዳጅነት መመሥረት ቻለች።

አዎን፣ በሥጋዊ ዓይናችን ልናየው ባንችልም እንኳ ‘ወደ አምላክ መቅረብ’ እንችላለን። በአእምሯችንና በልባችን እጅግ ማራኪ የሆነውን ስብዕናውን “ማየት” የምንችል ሲሆን በዚህ መንገድ እኛ ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ ነው።”​—⁠ቆላስይስ 3:​14 NW

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይሖዋ ለምታሳዩት ፍቅር ምላሽ ይሰጣል

ዝምድና በሁለት ወገን ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ነው። ወደ አምላክ ስንቀርብ እሱም ይበልጥ ወደ እኛ በመቅረብ ምላሽ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለየት ባለ ሁኔታ ለተጠቀሱት አረጋውያን ለስምዖን እና ለሐና የነበረውን ስሜት ተመልከት። ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ፣ ስምዖን መሲሑን የሚጠባበቅ “ጻድቅና ትጉህ” ሰው እንደነበረ ይነግረናል። ይሖዋ የስምዖንን ግሩም ባሕርያት ተመልክቶ “የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንደማያይ” በማሳወቅ ለዚህ ተወዳጅ አረጋዊ ፍቅር አሳይቷል። ይሖዋ ቃሉን በማክበር ወላጆቹ ሕፃኑ ኢየሱስን በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ይዘውት ሲመጡ ስምዖን እንዲያገኘው አድርጓል። ስምዖን ከተሰማው ደስታና ጥልቅ አድናቆት የተነሳ ሕፃኑን እቅፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “ጌታ ሆይ፣ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ . . . ማዳንህን አይተዋልና።”​—⁠ሉቃስ 2:​25-35

“በዚያችም ሰዓት” ይሖዋ የ84 ዓመት አረጋዊት የሆነችውን ሐናንም ወደ ኢየሱስ በመምራት ለእሷ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህች የተወደደች መበለት ይሖዋን “እያገለገለች” ምንጊዜም ከቤተ መቅደስ አትለይም ነበር ሲል ይነግረናል። እሷም እንደ ስምዖን በአድናቆት ተሞልታ ይሖዋ ላሳያት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ደግነት ካመሰገነችው በኋላ “የኢየሩሳሌምን ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ” ስለ ልጁ ነገረቻቸው።​—⁠ሉቃስ 2:​36-38

አዎን፣ ይሖዋ ስምዖንና ሐና ምን ያህል እንደሚወዱትና እንደሚፈሩት እንዲሁም የዓላማው መፈጸም ምን ያህል እንደሚያሳስባቸው ተመልክቷል። እንደዚህ ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወደ ይሖዋ እንድትቀርብ አያደርጉህም?

ኢየሱስም እንደ አባቱ የሰውን ውስጣዊ ማንነት ተመልክቷል። በቤተ መቅደሱ እያስተማረ በነበረበት ጊዜ አንዲት “ድሀ መበለት” “ሁለት ሳንቲም” መዋጮ ስታደርግ ተመለከተ። በሌሎች ዓይን ስጦታዋ ከቁብ የማይቆጠር ቢሆንም በኢየሱስ ዓይን ግን እንደዚያ አልነበረም። ይህች ሴት የነበራትን ሁሉ ስለሰጠች ኢየሱስ አመስግኗታል። (ሉቃስ 21:​1-4) ስለዚህ ይሖዋና ኢየሱስ ስጦታችን ትልቅም ይሁን ትንሽ ምርጣችንን እስከሰጠናቸው ድረስ እንደሚያደንቁ እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

አምላክ ለእሱ ፍቅር ባላቸው ሰዎች የሚደሰት ቢሆንም ሰዎች ከእሱ ርቀው የተሳሳተ ጎዳና ሲከተሉ ያዝናል። ዘፍጥረት 6:​6 ከኖኅ የጥፋት ውኃ በፊት ይሖዋ ከሰው ልጆች ክፋት የተነሳ ‘በልቡ ማዘኑን’ ይነግረናል። ከጊዜ በኋላ ታዛዥ ያልሆኑ እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ‘እግዚአብሔርን እንደፈተኑትና የእስራኤልን ቅዱስ እንዳሳዘኑት’ መዝሙር 78:​41 ይናገራል። አዎን፣ አምላክ ማንም ሊቀርበው የማይችል ስሜት አልባ ‘ፈጣሪ’ አይደለም። በእርግጥም አምላክ ስብዕና ያለው አካል ነው። እንደ እኛ በአለፍጽምና የተዛባ ወይም የደነዘዘ ስሜት ያለው አምላክ አይደለም።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ማሰላሰል ወደ እሱ የምንቀርብበት አንዱ መንገድ ነው