በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሥነ ምግባር ንጽሕና ሊኖረን የሚገባው አምላካዊ አመለካከት

ለሥነ ምግባር ንጽሕና ሊኖረን የሚገባው አምላካዊ አመለካከት

ለሥነ ምግባር ንጽሕና ሊኖረን የሚገባው አምላካዊ አመለካከት

“እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”​—⁠ኢሳይያስ 48:​17

1, 2. (ሀ) ሰዎች በአጠቃላይ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖችስ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?

 ሬ በብዙ የምድር ክፍሎች የሥነ ምግባር አቋም የእያንዳንዱ ግለሰብ ምርጫ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። ሰዎች የፆታ ግንኙነትን በባለ ትዳሮች መካከል ብቻ መወሰን ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ሳይሆን ደስ ባላቸው ጊዜ ሁሉ ሊፈጽሙት እንደሚችሉ የተለመደ የፍቅር መግለጫ አድርገው ይመለከቱታል። በአድራጎቱ የሚጎዳ ሰው እስከሌለ ድረስ የፈለጉትን ቢያደርጉ ስህተት መስሎ አይታያቸውም። በእነርሱ አመለካከት ሰዎች ሥነ ምግባርን በተለይ ደግሞ ወሲብን በተመለከተ እንዲህ መሆን አለበት ተብሎ ሊነገረን አይገባም ብለው ያስባሉ።

2 ይሖዋን የሚያውቁ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ይሖዋን ስለሚወዱና እርሱን ማስደሰት ስለሚፈልጉ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ደስ ብሏቸው ይታዘዛሉ። ይሖዋ እንደሚወድዳቸውና ለጥቅማቸው ሲል መመሪያ እንደሚሰጣቸው ይገነዘባሉ። በእርግጥም የሚሰጣቸው መመሪያ ጠቃሚና ለደስታቸው ምክንያት የሚሆን ነው። (ኢሳይያስ 48:​17) አምላክ የሕይወት ምንጭ በመሆኑ በአካላቸው አጠቃቀም ረገድ በተለይም ደግሞ ዘር ከማፍራት ጋር የቅርብ ትስስር ባለው በዚህ ጉዳይ ረገድ የእርሱን መመሪያ ለማግኘት መጣራቸው ምክንያታዊ ይሆናል።

አፍቃሪ ከሆነ ፈጣሪ የተገኘ ስጦታ

3. በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ የተማሩት ነገር ምንድን ነው? ይህስ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር ስናወዳድረው ምን ይመስላል?

3 ዛሬ ካለው የዓለም አስተሳሰብ በተቃራኒው በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ አንዳንዶች የፆታ ግንኙነት አሳፋሪ ድርጊትና ኃጢአት እንደሆነ እንዲሁም በኤድን ገነት የተፈጸመው “የመጀመሪያው ኃጢአት” ሔዋን አዳምን በፆታ ማባበሏ እንደሆነ ያስተምራሉ። እንዲህ ያለው ሐሳብ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚናገሩት ፍጹም ተቃራኒ ነው። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት የሚጠራቸው “አዳምና ሚስቱ” በማለት ነው። (ዘፍጥረት 2:​25) አምላክ “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት” በማለት ልጆችን እንዲወልዱ ነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 1:​28) አምላክ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ ትእዛዝ ከሰጠ በኋላ ይህንን ትእዛዝ በመፈጸማቸው ምክንያት ከቀጣቸው ትርጉም የለሽ ይሆናል።​—⁠መዝሙር 19:​8

4. አምላክ ለሰዎች የተራክቦ ኃይል የሰጣቸው ለምንድን ነው?

4 ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ከተሰጠውና በኋላም ለኖኅና ለልጆቹ ከተደገመላቸው ከዚህ ትእዛዝ እንደምንረዳው የፆታ ግንኙነት ዋነኛው ዓላማ ልጆችን መውለድ ነው። (ዘፍጥረት 9:​1) ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል እንደሚያሳየው የተጋቡ አገልጋዮቹ የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙት የግድ ልጆች ለመውለድ ብቻ ነው ማለት አይደለም። እንዲህ ያለው ግንኙነት የተጋቡ ሰዎችን ስሜታዊና አካላዊ ፍላጎት የሚያሟላ ከመሆኑም ሌላ የደስታ ምንጭ ይሆንላቸዋል። አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ጥልቅ የመውደድ ስሜት የሚገልጹበት መንገድ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 26:​8, 9፤ ምሳሌ 5:​18, 19፤ 1 ቆሮንቶስ 7:​3-5

መለኮታዊ ገደቦች

5. አምላክ በሰዎች ፆታዊ ተግባር ላይ ምን ገደብ አበጅቷል?

5 የፆታ ስሜት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ቢሆንም የሚገለጽበት መንገድ ገደብ የለውም ማለት አይደለም። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በትዳር ውስጥም ሳይቀር ይሠራል። (ኤፌሶን 5:​28-30፤ 1 ጴጥሮስ 3:​1, 7) ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ የፆታ ግንኙነት ፍጹም የተከለከለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚናገረው ነገር ምንም አያሻማም። አምላክ ለእስራኤል ብሔር በሰጠው ሕግ ውስጥ “አታመንዝር” የሚል ቃል ሰፍሮ ይገኛል። (ዘጸአት 20:​14) ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ ‘ክፉ ሐሳብን’ ጨምሮ “ዝሙት” እና “ምንዝር” ከልብ እንደሚመነጩና እነዚህም አንድን ሰው እንደሚያረክሱ ገልጿል። (ማርቆስ 7:​21, 22) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ በቆሮንቶስ ለነበሩት ክርስቲያኖች “ከዝሙት ሽሹ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 6:​18) በተጨማሪም ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በላከው መልእክቱ ውስጥ ደግሞ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና [“ዝሙት የሚፈጽሙትንና፣” NW ] አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” ሲል ጽፏል።​—⁠ዕብራውያን 13:​4

6. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዝሙት” የሚለው ቃል ምን ነገሮችን ያካትታል?

6 “ዝሙት” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ፖርኒያ ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተገኘ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነት ለማመልከት ያገለግላል። (1 ቆሮንቶስ 6:​9) እንደ ማቴዎስ 5:​32 እና ማቴዎስ 19:​9 ባሉት ሌሎች ቦታዎች ላይ ቃሉ ይበልጥ ሰፋ ባለ መንገድ የተሠራበት ሲሆን ምንዝርን፣ በቅርብ ዘመዳሞች መካከልና ከእንስሳት ጋር የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነትም ጭምር ያመለክታል። ባልተጋቡ ሰዎች መካከል በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነት እንዲሁም የፆታ ስሜትን ለማርካት ሲባል የሌላውን ሰው የፆታ ብልት በማሻሸት የሚፈጸመው ወሲባዊ ተግባርም ፖርኒያ ሊባል ይችላል። እንዲህ ያሉት ድርጊቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በአምላክ ቃል ውስጥ ተወግዘዋል።​—⁠ዘሌዋውያን 20:​10, 13, 15, 16፤ ሮሜ 1:​24, 26, 27, 32 a

ከአምላክ የሥነ ምግባር ሕግጋት መጠቀም

7. ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን በመጠበቃችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ስለ ፆታ ምግባር የሰጠውን መመሪያ መከተል ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። በ12ኛው መቶ ዘመን የነበረው ታዋቂው የአይሁዳውያን ፈላስፋ ማይሞኒደስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በቶራህ [በሙሴ ሕግ] ውስጥ ከተከለከሉት ነገሮች ሁሉ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸምን ወሲብና የተከለከሉ የፆታ ግንኙነቶችን በተመለከተ የተሰጠውን ሕግ ያህል የሚያስቸግር ትእዛዝ የለም።” ይሁንና የአምላክን መመሪያ ብንታዘዝ በእጅጉ እንጠቀማለን። (ኢሳይያስ 48:​18) ለምሳሌ ያህል በዚህ ረገድ ታዛዦች መሆናችን በፆታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች እንድንጠበቅ ይረዳናል። ከእነዚህ በሽታዎች መካከል አንዳንዶቹ መድኃኒት የሌላቸውና ሕይወታችንን ሊቀጥፉ የሚችሉ ናቸው። b ከጋብቻ ውጭ ከሚከሰተው እርግዝናም እንጠበቃለን። በአምላካዊው ጥበብ መመራት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረንም አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንዲህ ማድረግ ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረን ከማድረጉም በላይ ዘመዶቻችንን፣ የትዳር ጓደኛችንን፣ ልጆቻችንና ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ጨምሮ በሌሎች ሰዎች ዘንድ አክብሮት ያተርፍልናል። እንዲሁም ስለ ፆታ ጤናማና አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ስለሚረዳን በትዳር ሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የአምላክ ቃል እውነት ከሁሉ የተሻለ ጥበቃ ነው። እስካሁን አላገባሁም። ያኔ ግን ለማገባው ክርስቲያን በልበ ሙሉነት ንጽሕናዬን ጠብቄ እንደኖርኩ እነግረዋለሁ።”

8. ንጹሕ አኗኗራችን ንጹሑን አምልኮ በመደገፍ ረገድ አስተዋጽኦ የሚያደርገው በምን መንገድ ነው?

8 ንጹሕ የሥነ ምግባር አካሄድ መከተላችን ሰዎች ስለ እውነተኛው አምልኮ ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ውድቅ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም ሌላ ወደ አምላካችን እንዲሳቡ ያደርጋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 2:​12) አምላክን የማያገለግሉት ሰዎች ንጹሕ አኗኗራችንን ማስተዋል ወይም ማድነቅ ቢሳናቸው እንኳ ሰማያዊው አባታችን የእርሱን መመሪያ ለመከተል የምናደርገውን ጥረት እንደሚያይ፣ እንደሚያደንቅና ደስ እንደሚሰኝበት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 27:​11፤ ዕብራውያን 4:​13

9. ምክንያቱ ሙሉ በሙሉ ባይገባን እንኳ በአምላክ መመሪያ ላይ ትምክህት ማሳደር የሚገባን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

9 አምላክ እርሱ በሚፈልገው መንገድ እንድንሄድ መመሪያ የሰጠን ለምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ባይገባን እንኳ በአምላክ ላይ ያለን እምነት ለእኛ የሚበጀውን ያውቃል የሚል ትምክህት እንዲያድርብን ይረዳናል። ከሙሴ ሕግ አንድ ምሳሌ እንጥቀስ። ወታደራዊ ሠፈራን በተመለከተ የተሰጠ አንድ መመሪያ እዳሪያቸውን ከሠፈሩ ውጭ እንዲቀብሩ ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 23:​13, 14) ምናልባት እስራኤላውያኑ እንዲህ ያለ መመሪያ የተሰጠበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል ብለው ግራ ተጋብተው ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶቹ መመሪያውን ማክበሩ አስፈላጊ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከዚያ ወዲህ የሕክምናው ሳይንስ ይህ ሕግ የውኃ ምንጮች እንዳይበከሉ ከማድረጉም ሌላ በሦስት አጽቄዎች የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል እንደረዳ ተገንዝቧል። በተመሳሳይም አምላክ የፆታ ግንኙነት በጋብቻ ውስጥ ብቻ እንዲወሰን ያደረገባቸው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ስሜታዊ፣ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ምክንያቶች አሉት። እስቲ ከዚህ ቀጥሎ የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን የጠበቁ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ዮሴፍ​—⁠በሥነ ምግባር አቋሙ ተባርኳል

10. ዮሴፍን በፆታ ልታባብለው የሞከረችው ማን ናት? እርሱስ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?

10 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘውን የያዕቆብ ልጅ የዮሴፍን ምሳሌ ሳታውቀው አትቀርም። በ17 ዓመቱ የግብጹ ፈርዖን የዘበኞች አለቃ ለነበረው ለጲጥፋራ ባሪያ ሆኖ ተሸጠ። ይሖዋ ዮሴፍን ስለባረከው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጲጥፋራ በቤቱ ባለው ሁሉ ላይ ሾመው። ዮሴፍ ወደ 20ዎቹ ዕድሜ ሲቃረብ “ፊቱ መልከ መልካምና ውብ ነበረ።” በዚህ ጊዜ የጲጥፋራ ሚስት ዓይኗን ጣለችበትና ታባብለው ጀመር። ዮሴፍ የእርሷን ጥያቄ መቀበል በጌታው ላይ ክህደት መፈጸም ብቻ ሳይሆን ‘በአምላክም ላይ ኃጢአት መሥራት’ እንደሆነ በመንገር አቋሙን ግልጽ አደረገ። ዮሴፍ እንዲህ ብሎ ያሰበው ለምን ነበር?​—⁠ዘፍጥረት 39:​1-9

11, 12. ዝሙትና ምንዝር መፈጸምን የሚከለክል በጽሑፍ የሠፈረ መለኮታዊ ሕግ በጊዜው ባይኖርም እንኳ ዮሴፍ እንደዚያ ብሎ ያሰበው ለምን መሆን ይኖርበታል?

11 ዮሴፍ ይህን ውሳኔ ያደረገው ሌሎች ሰዎች ያውቁብኛል የሚል ፍርሃት ስላደረበት እንዳልሆነ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። ቤተሰቦቹ የሚኖሩት በጣም ርቀው ሲሆን አባቱም ቢሆን ዮሴፍ ሞቷል ብሎ ነበር የሚያስበው። ዮሴፍ የፆታ ብልግና ቢፈጽም ቤተሰቡ ድርጊቱን የሚያውቅበት መንገድ አልነበረም። ጲጥፋራና ወንዶች ባሪያዎቹ ቤት ውስጥ የማይኖሩባቸው ጊዜያት ስለሚኖሩ እንዲህ ያለው ኃጢአት ከእነርሱም እንኳ ሳይቀር ሊደበቅ ይችል ነበር። (ዘፍጥረት 39:​11) ይሁንና ዮሴፍ እንዲህ ያለው አድራጎት ከአምላክ ሊሰወር እንደማይችል አውቋል።

12 ዮሴፍ ስለ ይሖዋ የሚያውቀውን ነገር ወደ አእምሮው አምጥቶ መሆን አለበት። ይሖዋ በኤድን ገነት ውስጥ “ስለዚህ ሰው እናትና አባቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” በማለት የተናገረውን ነገር እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። (ዘፍጥረት 2:​24) ከዚህም በተጨማሪ ዮሴፍ ቅድመ አያቱን ሣራን ለማባበል ቆርጦ ለነበረው ለፍልስጥኤማዊው ንጉሥ ይሖዋ ምን እንዳለው ሳያውቅ አይቀርም። ይሖዋ ንጉሡን እንዲህ ብሎታል:- “እነሆ፣ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ምውት ነህ፤ እርስዋ ባለ ባል ናትና። . . . እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፤ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውሁም።” (ዘፍጥረት 20:​3, 6፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ይሖዋ በዚህ ጊዜ ለሰዎች የሰጠው በጽሑፍ የሠፈረ ሕግ ባይኖርም ለጋብቻ ያለው አመለካከት ግልጽ ነበር። ዮሴፍ የነበረው ሥነ ምግባራዊ ስሜት ይሖዋን ላለማሳዘን ከነበረው ስሜት ጋር ተዳምሮ ከፆታ ብልግና እንዲርቅ ረድቶታል።

13. ዮሴፍ ከጲጥፋራ ሚስት መራቅ ያልቻለው ለምን ሊሆን ይችላል?

13 ይሁን እንጂ የጲጥፋራ ሚስት ከእርሷ ጋር ይተኛ ዘንድ “በየዕለቱ” መወትወቷን አልተወችም። ዮሴፍ ለምን ከእርሷ አይርቅም ነበር? ባሪያ እንደመሆኑ መጠን ሥራውን የግዴታ ማከናወን ነበረበት። ሁኔታውን መለወጥ የሚችልበት መንገድም አልነበረም። አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት የግብጻውያን ቤቶች አሠራር ወደ ዕቃ ማከማቻው ክፍል ለመግባት የግድ በዋናው ቤት ማለፍ የሚጠይቅ ነበር። በመሆኑም ዮሴፍ ከጲጥፋራ ሚስት መራቅ የማይቻል ነገር ሆኖበት መሆን አለበት።​—⁠ዘፍጥረት 39:​10

14. (ሀ) ዮሴፍ ከጲጥፋራ ሚስት ከሸሸ በኋላ ምን ነገር ተከሰተ? (ለ) ይሖዋ ዮሴፍን ላሳየው ታማኝነት የባረከው እንዴት ነው?

14 አንድ ቀን ሁለቱ ብቻ ቤት በነበሩበት ጊዜ የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን “ከእኔ ጋር ተኛ” ስትል ተጠምጥማ ያዘችው። እርሱም ጥሏት ሸሸ። እምቢ ማለቱ ውስጧን አሳርሯት ስለነበር አስገድዶ ሊደፍረኝ ነበር ብላ ከሰሰችው። ውጤቱስ ምን ነበር? ዮሴፍ ላሳየው የአቋም ጽናት ይሖዋ ወሮታውን የከፈለው ወዲያው ነበርን? የለም፣ ዮሴፍ በወኅኒ ተጥሎ በእግረ ሙቅ ታሠረ። (ዘፍጥረት 39:​12-20፤ መዝሙር 105:​18) የኋላ ኋላ ግን ይሖዋ የተፈጸመውን የፍትሕ መጓደል ተመልክቶ ዮሴፍን ከወኅኒ በማውጣት ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲገባ አደረገው። በመላዋ ግብጽ ሁለተኛው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ሆኖ የተሾመ ሲሆን ሚስትና ልጆች በማግኘትም ተባርኳል። (ዘፍጥረት 41:​14, 15, 39-45, 50-52) ከዚህም በላይ የዮሴፍ የጸና አቋም ከዚያ በኋላ ለሚመጡት የአምላክ አገልጋዮች ጥቅም ሲባል ከዛሬ 3, 500 ዓመት በፊት በጽሑፍ ተመዝግቧል። ለአምላክ የጽድቅ ሕግጋት ታማኝ በመሆኑ ያገኛቸው እንዴት ያሉ ግሩም በረከቶች ናቸው! እኛም ዛሬ ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን መጠበቁ የሚያስገኘው ጥቅም ሁልጊዜ ቶሎ አይታየን ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደሚያይና በጊዜው እንደሚባርከን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።​—⁠2 ዜና መዋዕል 16:​9

ኢዮብ ‘ከዓይኑ ጋር የገባው ቃል ኪዳን’

15. ኢዮብ ከዓይኑ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ምንድን ነው?

15 ሌላው የአቋም ጽናቱን የጠበቀ ሰው ኢዮብ ነው። ኢዮብ በዲያብሎስ በተፈተነበት ወቅት ሕይወቱን መለስ ብሎ በመመልከት ሌሎች ነገሮችን ጨምሮ ይሖዋ ስለ ጾታ ሥነ ምግባር ያወጣውን መሠረታዊ ሥርዓት ጥሶ ከተገኘ የሚመጣበትን ከባድ ቅጣት ለመቀበል ፈቃደኛ እንደሆነ ተናግሯል። ኢዮብ “ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቆንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?” ብሏል። (ኢዮብ 31:​1) ኢዮብ ይህንን ሲል ለአምላክ ያለውን የጸና አቋም ለመጠበቅ ባለው ቁርጠኝነት አንዲትን ሴት በምኞት ዓይን እንኳ ላለመመልከት ቆርጦ ነበር። በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ሴቶችን አያይም ማለት አይደለም። እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሆኖ ከተገኘም ይረዳቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ በፆታ ስሜት በአትኩሮት መከታተል ግን የማይታሰብ ነገር ነበር። ፈተናው ሳይደርስበት በፊት በሀብቱ “በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ።” (ኢዮብ 1:​3) ይሁን እንጂ ብዙ ሴቶችን ለመማረክ ሀብቱን መሣሪያ አድርጎ አልተጠቀመም። ከወጣት ቆነጃጅት ጋር ሕገ ወጥ የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ሕልም ኖሮት እንደማያውቅ ግልጽ ነው።

16. (ሀ) ኢዮብ ላገቡ ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ወንዶች አድራጎት ከኢዮብ ፈጽሞ የተለየ የነበረው እንዴት ነው? ዛሬ ስላለውስ ሁኔታ ምን ማለት ይቻላል?

16 በመሆኑም ኢዮብ በደህናውም ሆነ በችግሩ ጊዜ የአቋም ጽናቱን ጠብቋል። ይሖዋም ይህንን በመገንዘብ አትረፍርፎ ባርኮታል። (ኢዮብ 1:​10፤ 42:​12) ኢዮብ ባለ ትዳር ለሆኑ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ይሖዋ ቢወድደው ምንም አያስገርምም! ዛሬ ያሉት የአብዛኛዎቹ ሰዎች ባሕርይ ግን በተቃራኒው በሚልክያስ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ብዙ ባሎች ወጣት ሴቶችን ለማግባት ሲሉ የትዳር ጓደኞቻቸውን መተዋቸውን ነቢዩ ኮንኗል። የይሖዋ መሠዊያ ባሎቻቸው በተዉአቸው ሚስቶች እንባ ተሞልቶ ነበር። አምላክም የትዳር ጓደኞቻቸውን ‘ያታለሉትን’ ወንዶች አውግዟቸዋል።​—⁠ሚልክያስ 2:​13-16

ንጽሕናዋን የጠበቀች ወጣት

17. ሱነማዊቷ ልጃገረድ “የተቆለፈ ገነት” የነበረችው በምን መንገድ ነው?

17 የአቋም ጽናቷን የጠበቀችው ሦስተኛዋ ምሳሌ ሱነማዊቷ ልጃገረድ ነች። በለጋ ወጣትነቷና ውበቷ የተማረከው እረኛው ልጅ ብቻ ሳይሆን ባለጠጋ የነበረው ንጉሥ ሰሎሞንም ጭምር ነበር። በመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ውስጥ በተገለጸው ውብ ታሪክ ውስጥ ሱነማዊቷ ንጽሕናዋን ጠብቃ በመመላለሷ በዙሪያዋ ከነበሩት ሁሉ አድናቆትን አትርፋለች። ሰሎሞንን ፊት ብትነሳውም በመንፈስ አነሳሽነት ታሪኳን ጽፏል። እርሷ ያፈቀረችው እረኛም ንጹሕ አቋሟን አድንቆላታል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ቆም ብሎ ካሰላሰለ በኋላ ሱነማዊቷን ‘ከተቆለፈ ገነት’ ጋር አመሳስሏታል። (መኃልየ መኃልይ 4:​12) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የነበሩት ውብ የአትክልት ስፍራዎች ግሩም መዓዛ ያላቸውን አበቦችና ግርማ ያላቸውን ዛፎች ጨምሮ የተለያየ ዓይነት ያላቸው ውብ ዕጽዋትን የያዙ ነበሩ። እንዲህ ያሉት የአትክልት ቦታዎች በአጥር ወይም በግድግዳ ዙሪያቸውን የታጠሩ ሲሆን መግባት የሚቻለው በሚቆለፈው በር በኩል ብቻ ነው። (ኢሳይያስ 5:​5) ሱነማዊቷ የነበራት የሥነ ምግባር ንጽሕናና ተወዳጅ ባሕርይ ለእረኛው የተለየ ውበት እንዳለው የአትክልት ስፍራ ነበር። ንጽሕናዋን የጠበቀች ነበረች። ፍቅሯን የምትለግሰው ወደፊት ባሏ ለሚሆነው ሰው ብቻ ይሆናል።

18. የዮሴፍ፣ የኢዮብና የሱነማዊቷ ታሪክ ስለ ምን ነገር ማሳሰቢያ ይሰጠናል?

18 ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን በመጠበቅ ረገድ ሱነማዊቷ ዛሬ ላሉት ክርስቲያን ሴቶች ግሩም ምሳሌ ትሆናለች። ይሖዋ የሱነማዊቷን ልጃገረድ ምግባረ መልካምነት በማየት ዮሴፍንና ኢዮብን እንደባረካቸው እርሷንም ባርኳታል። የእነርሱ የንጽሕና አካሄድ ለእኛ ጥቅም ሲባል በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቦልናል። ዛሬ እኛ ጽኑ አቋሟችንን ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይመዘገብም ይሖዋ ፈቃዱን ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎችን የሚመዘግብበት “የመታሰቢያ መጽሐፍ” አለው። ይሖዋ ‘በትኩረት እንደሚከታተልና’ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ በታማኝነት ስንጥር ደስ እንደሚለው ፈጽሞ አንዘንጋ።​—⁠ሚልክያስ 3:​16 NW

19. (ሀ) ለሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ስለ ምን ነገር እንወያያለን?

19 እምነት የሌላቸው ሰዎች ሊያፌዙ ቢችሉም እኛ ግን ለአፍቃሪው አባታችን በመታዘዛችን ደስ ይለናል። እኛ ያለን የሥነ ምግባር አቋም ከፍ ያለና አምላካዊ ነው። ልንኮራበትና ከፍ አድርገን ልናየው የሚገባ ነገር ነው። ንጹሕ የሆነ የሥነ ምግባር አቋም በመጠበቃችን በአምላክ በረከት ደስ ሊለን እንዲሁም ዘላለማዊ በረከቶች የማግኘት ብሩሕ ተስፋ ሊኖረን ይችላል። ይሁን እንጂ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመቆየት ምን ተግባራዊ እርምጃዎችን ልንወስድ እንችላለን? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን በጣም አስፈላጊ ጥያቄ የሚዳስስ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የመጋቢት 15, 1983 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 29-31ን ተመልከት።

b የሚያሳዝነው አንዳንድ ንጹሕ ክርስቲያኖች የማያምን የትዳር ጓደኛቸው የአምላክን መመሪያ ስለማይከተል ብቻ በፆታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች የሚያዙባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

[ልታብራራ ትችላለህን?

• መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ያስተምራል?

• መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው “ዝሙት” የሚለው ቃል ምን ነገሮችን ያካትታል?

• ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን በመጠበቃችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?

• ዮሴፍ፣ ኢዮብና ሱነማዊቷ ልጃገረድ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮሴፍ ከሥነ ምግባር ብልግና ሸሽቷል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሱነማዊቷ ልጃገረድ ‘እንደ ተቆለፈ ገነት’ ነበረች

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ ‘ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር’