ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችሁን ጠብቃችሁ መኖር ትችላላችሁ
ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችሁን ጠብቃችሁ መኖር ትችላላችሁ
“ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና።”—1 ዮሐንስ 5:3
1. ዛሬ ባሉት ሰዎች መካከል ምን የሥነ ምግባር ልዩነት ይታያል?
ከረጅም ጊዜ በፊት ነቢዩ ሚልክያስ የአምላክ ሕዝቦች አካሄድ አምላክን ከማያገለግሉት ሰዎች ተለይቶ የሚታይበት ጊዜ እንደሚመጣ በመንፈስ አነሳሽነት ትንቢት ተናግሮ ነበር። ነቢዩ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።” (ሚልክያስ 3:18) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና መጠበቅን ጨምሮ ሌሎቹን የአምላክ ሕግጋት ማክበር ጥበብ ያለበትና ትክክለኛ የሕይወት ጎዳና ነው። ይሁን እንጂ እንደዚያ ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቲያኖች መዳን ለማግኘት መጋደል አለባቸው ሲል የተናገረው ያለ ምክንያት አልነበረም።—ሉቃስ 13:23, 24
2. አንዳንዶች ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው እንዳይኖሩ ችግር የሚፈጥርባቸው ውጫዊ ተጽእኖ ምንድን ነው?
2 ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ጠብቆ መኖር አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ውጫዊ ተጽዕኖዎች በመኖራቸው ነው። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ሕገ ወጥ የፆታ ግንኙነት የሚያስከትለውን መዘዝ ችላ በማለት እንዲህ ያለው ድርጊት ፍቅር የነገሠበት፣ አስደሳችና የአዋቂነት መለኪያ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል። (ኤፌሶን 4:17-19) አብዛኞቹ ግንኙነቶች ባልተጋቡ ወንድና ሴት መካከል የሚፈጸሙ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በድንገተኛ መቼት የፆታ ግንኙነት ሲፈጸም ያሳያሉ። ብዙውን ጊዜ በመካከላቸው ሞቅ ያለ ስሜትና የጋራ መከባበር አይታይም። ከልጅነታቸው ጀምሮ ለዚህ መልእክት የተጋለጡት ሰዎች ቁጥር ብዙ ነው። ከዚህም በላይ እጅግ ልል ከሆነው የዛሬው ሥነ ምግባራዊ አቋም ጋር እንድንስማማ እኩዮች የሚያሳድሩት ከፍተኛ ተጽእኖ አለ። ለተጽዕኖው እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኞች የማይሆኑ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ይፌዝባቸዋል አልፎ ተርፎም የስድብ ናዳ ይወርድባቸዋል።—1 ጴጥሮስ 4:4
3. በዓለም ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች በሥነ ምግባር ብልግና የሚወድቁባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
3 ውስጣዊ ግፊትም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ጠብቆ መኖርን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው የፆታ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። ይህ ፍላጎት ደግሞ ኃይለኛ ሊሆን ይችላል። ውስጣዊ ፍላጎታችን ከምናስበው ነገር ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። የሥነ ምግባር ብልግና ደግሞ ከይሖዋ ሐሳብ ጋር በማይጣጣሙ ጉዳዮች ላይ ከማውጠንጠን ጋር የተያያዘ ነው። (ያዕቆብ 1:14, 15) ለምሳሌ ያህል በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ላይ የወጣ አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደገለጸው ለመጀመሪያ ጊዜ የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ ብዙ ሰዎች ይህን ድርጊት የፈጸሙት ነገሩ ምን ይመስላል በሚል የማወቅ ጉጉት ተነሳስተው እንደሆነ ጠቁሟል። ሌሎች ደግሞ በእነርሱ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሌሎች የፆታ ግንኙነት እንደሚፈጽሙ በማመን እነርሱም በድንግልና የሚኖሩበት ምክንያት አልታያቸውም። ሌሎቹ ደግሞ ድርጊቱን የፈጸሙት ስሜታቸው አሸንፏቸው ወይም “በወቅቱ በመጠጥ ኃይል ተገፋፍተው” እንደሆነ ተናግረዋል። አምላክን ማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ ከዚህ በተለየ መንገድ ማሰብ ይኖርብናል። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመቆየት ምን ዓይነት አስተሳሰብ ሊረዳን ይችላል?
ጽኑ እምነት ይኑራችሁ
4. ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ማድረግ ይገባናል?
4 ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመኖር እንዲህ ያለውን ጎዳና መከተል ፈጽሞ የማያስቆጭ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል። ይህ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ከተናገረው ቃል ጋር የሚስማማ ነው:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ [እወቁ]።” (ሮሜ 12:2) ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅ የማያስቆጭ ነገር መሆኑን መገንዘብ ማለት የሥነ ምግባር ብልግና በአምላክ ቃል ውስጥ የተወገዘ መሆኑን ማወቅ ማለት ብቻ አይደለም። የሥነ ምግባር ብልግና የተወገዘበትን ምክንያትና ከዚያ ድርጊት በመራቃችን የምንጠቀመው እንዴት እንደሆነ መረዳትንም ይጨምራል። ከእነዚህ ምክንያቶች አንዳንዶቹ በፊተኛው ርዕስ ውስጥ ተጠቅሰዋል።
5. ክርስቲያኖች ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ የሚፈልጉበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
5 ሆኖም ክርስቲያኖች ከፆታ ብልግና የምንርቅበት ዋነኛው ምክንያት ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና ነው። እርሱ ለእኛ የሚበጀውን ነገር እንደሚያውቅ ተምረናል። ለእርሱ ያለን ፍቅር ክፉ የሆነውን ነገር እንድንጠላ ይረዳናል። (መዝሙር 97:10) አምላክ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ የፍጹምም በረከት’ ምንጭ ነው። (ያዕቆብ 1:17) እርሱ ይወድደናል። እርሱን በመታዘዝ እንደምንወድደውና ያደረገልንን ነገር ሁሉ እንደምናደንቅ እናሳያለን። (1 ዮሐንስ 5:3) የጽድቅ ሕግጋቱን በማፍረስ ይሖዋን ቅር ማሰኘትም ሆነ እርሱን ማሳዘን አንፈልግም። (መዝሙር 78:41) ቅድስናና ጽድቅ የተላበሰውን የአምልኮ መንገዱን የሚያሰድብ ነገር ማድረግ አንፈልግም። (ቲቶ 2:4, 5፤ 2 ጴጥሮስ 2:2) ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን በመጠበቅ ከሁሉ የበላይ የሆነውን አምላክ ደስ እናሰኛለን።—ምሳሌ 27:11
6. ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን ለሌሎች ማሳወቁ የሚረዳን እንዴት ነው?
6 ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን በኋላ ይህን ጽኑ አቋማችንን ለሌሎች ማሳወቅ ተጨማሪ ጥበቃ ይሆንልናል። ሌሎች ሰዎች የይሖዋ አምላክ አገልጋይ መሆንህንና ከፍ ያሉ የአቋም ደረጃዎቹን ጠብቀህ ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረግህ ይወቁ። የአንተ ሕይወት ነው፣ የአንተ አካል ነው፣ ምርጫውም የአንተ ነው። አደጋ ላይ የሚወድቀው ከሰማያዊው አባትህ ጋር ያለህ ውድ ዝምድና ነው። ስለዚህ ሥነ ምግባራዊ አቋምህ ለድርድር የሚቀርብ ነገር እንዳልሆነ በግልጽ አስረዳ። የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች በማክበር እርሱን መወከል በመቻልህ ልትኮራ ይገባል። (መዝሙር 64:10 NW ) ለሥነ ምግባር ያለህን አቋም በተመለከተ ከሌሎች ጋር ለመወያየት ፈጽሞ ልታፍር አይገባም። ሐሳብህን አውጥተህ መናገርህ ይበልጥ ያጠነክርሃል፣ ጥበቃ ይሆንልሃል እንዲሁም ሌሎች የአንተን ምሳሌ እንዲከተሉ ያበረታታል።—1 ጢሞቴዎስ 4:12
7. ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመኖር ባደረግነው ውሳኔ መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?
7 ከፍተኛ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎችን ጠብቀን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ካደረግንና ይህን አቋማችንን ሌሎችም እንዲያውቁ ካደረግን በኋላ ከዚህ ውሳኔያችን ጋር ተስማምተን ለመቀጠል እርምጃዎች መውሰድ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ በባልንጀራ ምርጫ ረገድ ጠንቃቃ መሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” በማለት ይናገራል። የሥነ ምግባር አቋምህን ከሚያከብሩልህ ሰዎች ጋር ተወዳጅ። ያበረቱሃል። ይህ ጥቅስ በመቀጠል “የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) በተቻለህ መጠን ያደረግኸውን ቁርጥ ውሳኔ ከሚያዳክሙብህ ሰዎች ራቅ።—1 ቆሮንቶስ 15:33
8. (ሀ) አእምሯችንን ጤናማ ነገር መመገብ የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) ከምንስ መራቅ ይገባናል?
8 ከዚህም በላይ አእምሯችንን መመገብ ያለብን እውነት የሆነውን፣ ጭምትነት ያለበትን፣ ንጹሕ የሆነውን፣ ፍቅር ያለበትን፣ መልካም የሆነውን፣ በጎነት ያለበትንና ምስጋና የሚገባውን ነገር ነው። (ፊልጵስዩስ 4:8) በምናየውና በምናነበው ነገር እንዲሁም በምናዳምጠው ሙዚቃ ረገድ መራጮች በመሆን ይህንን እናደርጋለን። የብልግና ጽሑፎች መጥፎ ተጽእኖ አያሳድሩብኝም ማለት ሥነ ምግባራዊ ጽሑፎች ምንም አዎንታዊ ተጽዕኖ የላቸውም ከማለት ተለይቶ አይታይም። ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በሥነ ምግባር ብልግና በቀላሉ ሊጠመዱ እንደሚችሉ አስታውስ። በመሆኑም የፆታ ስሜትን የሚያነሳሱ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ፊልሞች እና ሙዚቃዎች የተሳሳተ ምኞት ወደ ማሳደርና በመጨረሻም ወደ ኃጢአት ሊመሩ ይችላሉ። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ አእምሮአችንን በአምላካዊ ጥበብ መሙላት ይኖርብናል።—ያዕቆብ 3:17
ወደ ፆታ ብልግና የሚያመሩ እርምጃዎች
9-11. ሰሎሞን በዝርዝር እንደገለጸው አንድን ብላቴና ቀስ በቀስ ወደ ሥነ ምግባር ብልግና የመሩት እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?
9 ብዙውን ጊዜ ወደ ፆታ ብልግና የሚመሩ ተለይተው የሚታወቁ እርምጃዎች አሉ። እያንዳንዱ እርምጃ ወደኋላ መመለስን ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርግ ነው። ይህ ጉዳይ በምሳሌ 7:6-23 ላይ እንዴት እንደተገለጸ ልብ በል። ሰሎሞን ‘ልብ የጎደለው’ ማለትም ጥሩ ውስጣዊ ስሜት የሌለው አንድ “ብላቴና” ተመልክቷል። “በአደባባይ ሲሄድ በቤትዋም [በጋለሞታዋ ቤት] አቅራቢያ ሲያልፍ፤ የቤትዋን መንገድ ይዞ ወደ እርስዋ አቀና፣ ማታ ሲመሽ፣ ውድቅትም ሲሆን።” የመጀመሪያው ስህተቱ ይህ ነው። ደንገዝገዝ ሲል ‘ልቡ’ የመራው እንዲሁ ወደ ማንኛውም መንገድ ሳይሆን አንዲት ጋለሞታ ሴት እንደምትገኝ በሚታወቅበት መንገድ ነበር።
10 ቀጥሎ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እነሆ፣ ሴት ተገናኘችው የጋለሞታ ልብስ የለበሰች፣ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች።” አያት! ፊቱን አዙሮ ወደ ቤቱ መመለስ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ በሥነ ምግባር ደካማ ስለሆነ ይህን ማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ አስቸጋሪ ሆነበት። ከዚያ ያዝ አድርጋ ሳመችው። መሳሙን በፀጋ ተቀብሎ የሚያባብል ንግግሯን ማዳመጥ ይጀምራል:- “መሥዋዕትንና የደኅንነት ቍርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ” ትለዋለች። የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ፣ ዱቄት፣ ዘይትና ወይንን የሚያካትት ነበር። (ዘሌዋውያን 19:5, 6፤ 22:21፤ ዘኁልቁ 15:8-10) መንፈሳዊነት እንደማይጎድላት በተዘዋዋሪ መንገድ ልትጠቁመው ፈልጋ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም በቤቷ ብዙ የሚበሉና የሚጠጡ ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንዳሉ መናገሯ ሊሆን ይችላል። “ና፣ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፣ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን” በማለት ትለምነዋለች።
11 መጨረሻው ምን እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም። “በከንፈርዋ ልዝብነት ትጎትተዋለች።” “በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፣ . . . ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል” ተከትሏት ወደ ቤቷ ይሄዳል። ሰሎሞን በሚከተሉት ትኩረት የሚሹ ቃላት ይደመድማል:- “ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን [አላወቀም]።” ‘ሴሰኞችንና አመንዝሮችን አምላክ ስለሚፈርድባቸው’ ይህ ነፍሱን ወይም ሕይወቱን የሚመለከት ጉዳይ ነው። (ዕብራውያን 13:4) ይህ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች እንዴት ያለ ትልቅ ትምህርት ነው! የአምላክን ሞገስ ሊያሳጣን በሚችለው ጎዳና ለመሄድ የመጀመሪያውን እርምጃ እንኳ መውሰድ አይኖርብንም።
12. (ሀ) “ልብ የጎደለው” የሚለው መግለጫ ምን ማለት ነው? (ለ) ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን መገንባት የምንችለው እንዴት ነው?
12 በዚህ ዘገባ ውስጥ የተገለጸው ብላቴና “ልብ የጎደለው” [NW ] እንደሆነ ልብ በል። ይህ መግለጫ ሐሳቡ፣ ምኞቱ፣ ፍቅሩ፣ ስሜቱ እንዲሁም የሕይወት ግቡ አምላክ ከሚፈቅደው ነገር ጋር የሚስማማ እንዳልሆነ የሚገልጽ ነው። የሥነ ምግባር ድክመቱ ለአሳዛኝ ውጤት ዳርጎታል። በእነዚህ አስጨናቂ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬን መገንባት ጥረት ይጠይቃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አምላክ እኛን ለመርዳት ዝግጅት አድርጓል። በትክክለኛው መንገድ እንድንጓዝ እኛን ለማበረታታትና እንደኛው ዓይነት ግብ ካላቸው ሰዎች ጋር እንድንገናኝ የክርስቲያን ስብሰባዎችን ዝግጅት አድርጎልናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) እዚያም እረኝነት የሚያደርጉልንና የጽድቅን መንገድ የሚያስተምሩን የጉባኤ ሽማግሌዎችም አሉን። (ኤፌሶን 4:11, 12) የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ይሰጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በተጨማሪም በማንኛውም ጊዜ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን።—ማቴዎስ 26:41
ዳዊት ከፈጸመው ኃጢአት መማር
13, 14. ንጉሥ ዳዊት ከባድ ኃጢአት ውስጥ የተዘፈቀው እንዴት ነው?
13 የሚያሳዝነው ግን ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው የአምላክ አገልጋዮች ሳይቀሩ በፆታ ብልግና ወድቀዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለው ንጉሥ ዳዊት ነው። ለአምላክ የጠለቀ ፍቅር እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ በኃጢአት ድርጊት ውስጥ ተዘፈቀ። ሰሎሞን እንደገለጸው ብላቴና ዳዊትንም ወደ ኃጢአት የመሩትና ኃጢአቱን ያወሳሰቡበት እርምጃዎች ነበሩ።
14 በዚህ ወቅት ዳዊት በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ምናልባትም በ50ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ሳይሆን አይቀርም። ከቤቱ ሰገነት ላይ ሆኖ ውብ የነበረችው ቤርሳቤህ ስትታጠብ ተመለከተ። ስለ ማንነቷ ሲያጠያይቅ አንዳንድ መረጃዎችን አገኘ። ባሏ ኦርዮ የአሞናውያኑን ከተማ ረባትን ለመያዝ በሚደረገው ውጊያ ላይ እንደተሰለፈ አወቀ። ዳዊት ወደ ቤተ መንግሥቱ አስመጣትና ከእርሷ ጋር ተኛ። ከዚያ በኋላ ነገሮች ሁሉ ተወሳሰቡ። ከዳዊት እንደፀነሰች አወቀች። ኦሪዮ ከሚስቱ ጋር ያድር እንደሆን ብሎ በማሰብ ዳዊት ከጦር ሜዳ አስጠራው። ይህን ያደረገው ቤርሳቤህ ከኦሪዮ እንደፀነሰች ለማስመሰል ነበር። ይሁን እንጂ ኦሪዮ ወደ ቤቱ ሳይሄድ ቀረ። ዳዊት ኃጢአቱን ለመሸፈን ቆርጦ ስለነበር ኦሪዮን ሊገደል በሚችልበት ግንባር እንዲያሰልፈው የሚገልጽ ደብዳቤ ለጦር አዛዡ ጽፎ ኦሪዮን ወደ ረባት ላከው። ኦሪዮ በዚህ መንገድ ሲገደል ዳዊት መበለት የሆነችው ቤርሳቤህ ማርገዟ ይፋ ከመሆኑ በፊት ቶሎ ብሎ አገባት።—2 ሳሙኤል 11:1-27
15. (ሀ) የዳዊት ኃጢአት የተጋለጠው እንዴት ነው? (ለ) ናታን ላቀረበው ጥበብ የተሞላበት ወቀሳ የዳዊት ምላሽ ምን ነበር?
15 ዳዊት ኃጢአቱን ለመሸፈን የወጠነው ሴራ የሰመረ ይመስል ነበር። በዚህ ሁኔታ ወራት አለፉ። ወንድ ልጅ ተወለደ። ዳዊት መዝሙር 32ን ያቀናበረው ይህን ክስተት በአእምሮው ይዞ ከነበረ ሕሊናው አሰቃይቶት እንደነበር ግልጽ ነው። (መዝሙር 32:3-5) ይሁን እንጂ ኃጢአቱ ከአምላክ የተሠወረ አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ “ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ” ይላል። (2 ሳሙኤል 11:27) ይሖዋ የላከው ነቢዩ ናታን ዳዊት የሠራውን ነገር በጥበብ አጋልጧል። ዳዊት ወዲያውኑ ኃጢአቱን በመናዘዝ የይሖዋን ይቅርታ ለማግኘት ለምኗል። ልባዊ ንስሐ በመግባቱ ከአምላክ ጋር ሊታረቅ ችሏል። (2 ሳሙኤል 12:1-13) ዳዊት የተሰጠውን ተግሳጽ አልተቃወመም። ይልቁንም በመዝሙር 141:5 ላይ የተገለጸው ዓይነት ዝንባሌ አንጸባርቋል:- “ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፣ ይዝለፈኝም፣ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና።”
16. ሰሎሞን ኃጢአትን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያና ምክር ሰጥቷል?
16 ዳዊት ከቤርሳቤህ የወለደው ሁለተኛ ልጅ ማለትም ሰሎሞን በአባቱ ሕይወት ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈውን ይህን ነገር መለስ ብሎ አስቦት ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።” (ምሳሌ 28:13) ከባድ ኃጢአት ብንሠራ ማስጠንቀቂያም ምክርም ያዘለውን ይህን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ቃል ልንከተል ይገባል። ለይሖዋ ልንናዘዝና ለእርዳታ ወደ ጉባኤ ሽማግሌዎች ልንሄድ ይገባል። የሽማግሌዎች ትልቁ ኃላፊነት ኃጢአት ውስጥ የወደቁ ሰዎች እንዲስተካከሉ መርዳት ነው።—ያዕቆብ 5:14, 15
ኃጢአት የሚያስከትለውን መዘዝ መቋቋም
17. ይሖዋ ኃጢአትን ይቅር የሚል ቢሆንም ከምን ነገር አያስጥለንም?
17 ይሖዋ ዳዊትን ይቅር ብሎታል። ለምን? ምክንያቱም ዳዊት የአቋም ጽናቱን ያስመሰከረና ሌሎችን ይቅር የሚል ሰው ስለነበር እንዲሁም እውነተኛ ንስሐ ስለገባ ነው። ያም ሆኖ ግን ዳዊት ከዚያ በኋላ ከተከተለው አስከፊ መዘዝ አላመለጠም። (2 ሳሙኤል 12:9-14) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ ንስሐ በገቡ ሰዎች ላይ ክፉ ነገር ባያመጣም የፈጸሙት ስህተት ከሚያስከትለው የተለመደ መዘዝ አያስጥላቸውም። (ገላትያ 6:7) የፆታ ብልግና ከሚያስከትላቸው ውጤቶች መካከል ፍቺ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች እንዲሁም አመኔታና አክብሮት ማጣት ይገኙበታል።
18. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በወቅቱ ተፈጽሞ የነበረውን የፆታ ብልግና በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለቆሮንቶስ ጉባኤ የነገራቸው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለኃጢአተኞች ፍቅርና ምሕረት የሚያሳየው እንዴት ነው?
18 በግላችን አንድ ከባድ ስህተት ብንሠራ የሠራነው ስህተት የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ በኃዘን እንድንደቆስ ሊያደርገን ይችላል። የሆነ ሆኖ ንስሐ ገብተን ከአምላክ ጋር እንደገና ከመታረቅ ምንም ነገር እንዲያግደን ልንፈቅድ አይገባም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ ከቅርብ ዘመዱ ጋር ዝሙት የፈጸመውን ሰው ከመካከላቸው ማስወገድ እንደሚገባቸው ለቆሮንቶስ ሰዎች ጽፎላቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 5:1, 13) ሰውዬው ከልቡ ንስሐ ከገባ በኋላ ጳውሎስ “ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 2:5-8) በመንፈስ አነሳሽነት በሰፈረው በዚህ ምክር ውስጥ ይሖዋ ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች የሚያሳየው ፍቅርና ምሕረት ተንጸባርቆ እናገኘዋለን። በሰማይ ያሉ መላእክት አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ ደስ ይላቸዋል።—ሉቃስ 15:10
19. ስለ አንድ የኃጢአት ድርጊት በአግባቡ ማዘን ምን ጥቅሞች ሊኖሩት ይችላሉ?
19 በስህተት ድርጊታችን ብናዝንም የሚሰማን የቁጭት ስሜት ‘እንደገና ወደ ኃጢአት ከመመልከት እንድንጠነቀቅ’ ይረዳናል። (ኢዮብ 36:21) በእርግጥ ኃጢአት የሚያስከትለው መራራ ውጤት አንድን ኃጢአት ከመድገም ሊያግደን ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ዳዊት በኃጢአተኛ አካሄዱ ምክንያት የገጠመውን አሳዛኝ ሁኔታ ሌሎችን ለመምከር ተጠቅሞበታል። “ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፣ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ” ብሏል።—መዝሙር 51:13
ይሖዋን ማገልገል ደስታ ያስገኛል
20. የአምላክን የጽድቅ ብቃቶች መታዘዝ ምን ጥቅሞች አሉት?
20 “ብፁዓንስ [“ደስተኞች፣” NW ] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:28) የአምላክን የጽድቅ ብቃቶች ማሟላት አሁንም ሆነ ወደፊት በምናገኘው ዘላለማዊ ሕይወት ደስታ ያስገኝልናል። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ከኖርን ይሖዋ እኛን ለማገዝ ያደረገልንን ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም በዚሁ አካሄዳችን እንቀጥል። በሥነ ምግባር ብልግና ወድቀንም ከሆነ ይሖዋ ከልባቸው ንስሐ የሚገቡትን ሰዎች ይቅር ለማለት ዝግጁ እንደሆነ ባገኘነው እውቀት ተበረታትተን ይህንን ኃጢአት ደግመን ላለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ኢሳይያስ 55:7
21. ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመቀጠል የሚያስችለን የትኛውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር መከተላችን ነው?
21 በቅርቡ ይህ ኃጢአተኛ ዓለም ከብልግና ዝንባሌዎቹና ልማዶቹ ጋር ያልፋል። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን በመጠበቅ አሁንም ሆነ ለዘላለም እንጠቀማለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፣ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፣ . . . ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፣ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ።”—2 ጴጥሮስ 3:14, 17
ልታብራራ ትችላለህን?
• ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ጠብቆ መኖር አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
• ከፍተኛ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎችን ጠብቀን ለመመላለስ ያለንን ቁርጥ አቋም የሚደግፉልን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
• ሰሎሞን የጠቀሰው ብላቴና ከፈጸመው ኃጢአት ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
• ንስሐ መግባትን በተመለከተ ከዳዊት ምሳሌ ምን እንማራለን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሥነ ምግባር ጉዳይ ያለህን አቋም ለሌሎች ማሳወቅ ጥበቃ ነው
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ከልቡ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ ይቅር ብሎታል