በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስኬትን የምትለካው በምንድን ነው?

ስኬትን የምትለካው በምንድን ነው?

ስኬትን የምትለካው በምንድን ነው?

አንድ መዝገበ ቃላት ስኬት ለሚለው ቃል ፍቺ ሲሰጥ “ሃብት ማግኘት፣ ሞገስ ማግኘት ወይም ልቆ መገኘት” ብሏል። ይህ የቃሉ የተሟላ ፍቺ ነውን? የስኬት መለኪያ ሃብት፣ ሞገስ ወይም ልቆ መገኘት ብቻ ነውን? ይህን ከመመለስህ በፊት የሚከተለውን ልብ በል:- ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት ዘመኑ ምንም ቁሳዊ ሃብት አልነበረውም። በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም፣ በዘመኑ ተሰሚነት በነበራቸው ሰዎች ዘንድም ከፍተኛ ግምት አልተሰጠውም። ሆኖም ኢየሱስ የተሳካለት ሰው ነበር። እንዴት?

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “በእግዚአብሔር ዘንድ ባለ ጠጋ” ነበር። (ሉቃስ 12:​21) ከትንሣኤው በኋላ አምላክ “የክብርና የምስጋና” ዘውድ በመጫን ወሮታ ከፍሎታል። ይሖዋ ልጁን ‘ያለ ልክ ከፍ ከፍ በማድረግና ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም በመስጠት’ አከበረው። (ዕብራውያን 2:​9፤ ፊልጵስዩስ 2:​9) ኢየሱስ የተከተለው የሕይወት መንገድ የይሖዋን ልብ አስደስቷል። (ምሳሌ 27:​11) ምድራዊ ሕይወቱ ስኬታማ ነበረ፤ ምክንያቱም ዓላማውን ከግብ አድርሷል። የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ለስሙ ክብር አምጥቷል። በአጸፋው አምላክ ማንም የተማረ፣ የፖለቲካ ሰው ወይም የስፖርት ጀግና አግኝቶት የማያውቀውን ሃብት፣ ሞገስና የላቀ ቦታ በመስጠት አክብሮታል። ኢየሱስ በእርግጥም በምድር ላይ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ የተሳካለት ሰው ነበር።

ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው እንደ ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ ባለጠጋ በመሆን የክርስቶስን ፈለግ የሚከተሉ ከሆነ በአሁን ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያጭዱና በመጪው የነገሮች ሥርዓት ደግሞ የላቀ ሽልማት እንደሚያገኙ ይገነዘባሉ። አንድ ወጣት ከቻለ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈለ ኢየሱስ ያከናወነውን ሥራ በመሥራት የክርስቶስን ፈለግ ከመከተል የተሻለ ሊያደርገው የሚችለው ነገር የለም።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ ባሕሎች ያለው ልማድ ወጣቶች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰማሩ የሚያበረታታ አይደለም። አንድ ልጅ ትምህርቱን ሲጨርስ ሥራ ይዞና ትዳር መሥርቶ የተደላደለ ሕይወት እንዲመራ ይጠበቅበታል። አንዳንድ ጊዜ በእንዲህ ዓይነት ባሕል ውስጥ ያደጉ ወጣቶች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሠማራት አይነሳሱም። (ምሳሌ 3:​27) ለምን? አካባቢው የሚያስከትለው ተጽዕኖ ስለሚያሸንፋቸው ነው። ሮበርትንም ያጋጠመው ይኸው ነው። a

ባህልና ሕሊና በሚጋጭበት ጊዜ

ሮበርት ከልጅነቱ ጀምሮ የይሖዋ ምሥክር ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜው ጠባዩና የጓደኛ ምርጫው ጥሩ አልነበረም። እናቱ ስለእሱ ትጨነቅ ጀመር። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ አንድ አቅኚ ልጅዋን እንዲያበረታታላት ጠየቀችው። ቀጥሎ የሆነውን ሮበርት እንዲህ ሲል ተናግሯል።

“አቅኚው ወንድም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ስላበረታታኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። መልካም ምሳሌነቱ ትምህርቴን እንደጨረስኩ አቅኚነትን ሥራዬ ብዬ እንድይዝ ፍላጎት አሳደረብኝ። ይህ ደግሞ እማዬን እንደገና አስጨነቃት፤ ምክንያቱ ግን በፊት ካስጨነቃት የተለየ ነበር። ምን መሰላችሁ፣ በባህላችን አንዲት ልጅ ትምህርቷን እንደጨረሰች አቅኚ ብትሆን ምንም ችግር የለውም፤ ወንድ ግን በመጀመሪያ የገንዘብ አቅሙን ማጠናከር ይኖርበታል፤ ከዚያ በኋላ ስለ አቅኚነት ማሰብ ይችላል።

“አንድ ዓይነት ሙያ ተማርኩና የራሴን ሥራ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ በሥራው በጣም ስለተጠመድኩ ስብሰባ ላይ የምገኘውና አገልግሎት የምወጣው እንዲያው ለደንቡ ያክል ነበር። ይሖዋን ከዚህ የበለጠ ማገልገል እንደሚገባኝ ስለማውቅ ሕሊናዬ እረፍት ነሳኝ። የሆነ ሆኖ ሌሎች ከእኔ የሚጠብቁብኝን ነገር አላሟላሁም ከሚለው ሐሳብ መላቀቅ ከባድ ትግል ጠይቆብኝ ነበር፤ ሆኖም ስለተሳካልኝ ደስ ብሎኛል። አሁን ባለትዳር ስሆን እኔና ባለቤቴ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአቅኚነት አገልግለናል። በቅርቡ ደግሞ የጉባኤ አገልጋይ የመሆን መብት አግኝቻለሁ። ይሖዋን በሙሉ ልቤና በሙሉ ኃይሌ ለማገልገል በመቻሌ አሁን እውነተኛ እርካታ አግኝቻለሁ ብዬ መናገር እችላለሁ።”

ይህ መጽሔት ወጣቶች የሚቻል ከሆነ ገና በትምህርት ቤት እያሉ አንድ ዓይነት የእጅ ሙያ እንዲማሩ ወይም አንዳንድ ጠቃሚ ችሎታዎችን እንዲያዳብሩ ሲያበረታታ ቆይቷል። ዓላማው ምንድን ነው? ሃብታም እንዲሆኑ? በፍጹም። ዋነኛው ምክንያት ሲያድጉ ራሳቸውን እንዲችሉና አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል በተለይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይሖዋን እንዲያገለግሉ ነው። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በሰብዓዊ ሥራ ስለሚጠመዱ ለአገልግሎት የሚሰጡት ግምት ይቀንሳል። አንዳንዶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ጨርሶ ወደ አእምሮአቸው እንኳ አያመጡትም። ለምን?

ሮበርት የሰጠው ሐሳብ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ፍንጭ ይሰጠናል። ሮበርት ሙያ ከተማረ በኋላ ሥራ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ሕይወት እንዲሁ ማብቂያ የሌለው ሽክርክ​ሪት ሆነበት። ግቡ አስተማማኝ የገንዘብ አቅም መገንባት ነበር። ሆኖም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ሆነ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ያለ ሰው ሙሉ በሙሉ እዚህ ግብ ላይ መድረስ ይችላልን? ክርስቲያኖች በገንዘብ ረገድ ያለባቸውን ግዴታ ለመወጣት ተግተው በመሥራት በገንዘብ ራሳቸውን ለመቻል መጣር ይኖርባቸዋል። ሆኖም በዚህ ዋስትና በሌለው ዘመን አስተማማኝ የገንዘብ አቅም በመገንባት ረገድ የተሳካላቸው ቢኖሩ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ሊገነዘቡት ይገባል። በማቴዎስ 6:​33 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የሰጠው ተስፋ ለክርስቲያኖች አጽናኝ የሆነው ለዚህ ነው።

ሮበርት ባህሉ የሚጠብቅበትን ከመከተል ይልቅ ልቡ የሚመኘውን ለመከተል በመወሰኑ ደስተኛ ነው። በአሁኑ ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሥራዬ ብሎ ይዞታል። አዎን፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ክቡር ሥራ ነው። ሮበርት እንደተናገረው ‘በሙሉ ኃይሉ’ ይሖዋን በማገልገሉ ውስጣዊ ሰላም አግኝቷል።

በተፈጥሮ ችሎታዎችህ ተጠቀም

በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ተሰጥኦ ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። አንዳንዶች የሚደነቅ የአእምሮ እውቀት ያላቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የተዋጣላቸው የእጅ ሞያተኞች ናቸው። እነዚህ ሁሉ ስጦታዎች የተገኙት “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ” ከሚሰጠው ከይሖዋ ነው። (ሥራ 17:​25) ያለ ሕይወት እነዚህ ስጦታዎች ምንም እርባና የላቸውም።

ለይሖዋ የወሰንነውን ሕይወታችንን ለእሱ አገልግሎት ማዋላችን ተገቢ የሚሆነው ለዚህ ነው። ጥሩ ተሰጥዎ የነበረው አንድ ወጣት ለማድረግ የወሰነው ይኽንኑ ነው። ይህ ወጣት የኖረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ነበር። ስመ ጥር ከሆነ ቤተሰብ የወጣ ሲሆን ያደገው በጣም ታዋቂ በሆነችው በኪልቅያ በምትገኘው ጠርሴስ ነበር። በትውልድ አይሁዳዊ ቢሆንም ከአባቱ የሮማ ዜግነት አግኝቷል። ይህ ደግሞ ብዙ መብቶችንና አጋጣሚዎችን አስገኝቶለታል። ትልቅ ሲሆን በወቅቱ የላቀ ስፍራ ከነበራቸው “ፕሮፌሰሮች” መካከል አንዱ ከነበረው ከገማልያል ሕግ ተማረ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ‘ሃብት፣ ሞገስና ታዋቂነት’ የሚያገኝ ይመስል ነበር።​—⁠ሥራ 21:​39፤ 22:​3, 27, 28

ለመሆኑ ይህ ወጣት ማን ነው? ሳውል ይባላል። ሆኖም ሳውል ክርስቲያን ሆነና ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ እየተባለ ይጠራ ጀመር። የቀድሞ ምኞቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ ክርስቲያን በመሆን መላ ሕይወቱን ለይሖዋ አገልግሎት አዋለ። ጳውሎስ በሕግ ዐዋቂነቱ ሳይሆን ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ በመሆኑ በሰፊው ይታወቅ ጀመር። ጳውሎስ ወደ 30 የሚጠጉ ዓመታት በሚስዮናዊነት ካሳለፈ በኋላ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ወዳጆቹ አንድ ደብዳቤ ጻፈላቸው። በደብዳቤው ላይ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ስላከናወናቸው አንዳንድ ነገሮች ከጠቀሰ በኋላ “ስለ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ሁሉን ተጐዳሁ፣ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ . . . ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:​8) ጳውሎስ ሕይወቱን በዚህ መንገድ ስለተጠቀመበት ፈጽሞ አልተቆጨም!

ጳውሎስ ከገማልያል ስላገኘው ስልጠናስ ምን ለማለት ይቻላል? ጠቃሚ ሆኖ አግኝቶት ይሆን? እንዴታ! በተለያዩ አጋጣሚዎች “ምሥራቹን በሕግ ለመከላከል” ተጠቅሞበታል። ሆኖም ጳውሎስ በዋነኛነት የተሰማራው ምሥራቹን በመስበክ ሥራ ነበር። ይህ ደግሞ ቀድሞ ከቀሰመው ትምህርት ያላገኘው ነገር ነው።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:​7፤ ሥራ 26:​24, 25

ዛሬም በተመሳሳይ አንዳንዶች ተሰጥዎቻቸውንና ችሎታዎቻቸውን ሌላው ቀርቶ የቀሰሙትን ትምህርት የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማስቀደም ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል ኤሚ በንግድ ሥራ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ በሕግ ደግሞ ሌላ ዲግሪ ይዛለች። በአንድ ወቅት በአንድ የሕግ ተቋም ጥሩ ክፍያ ያለው ሥራ አግኝታ ነበር፤ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በአንድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ያለ ክፍያ በፈቃደኝነት በማገልገል ላይ ትገኛለች። አሁን ስለምትመራው ሕይወት እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “በሕይወቴ የተሻለውን ምርጫ አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ። . . . አሁን ያለሁበትን ቦታ በዩኒቨርሲቲ አብሮኝ ከተማረ ከማንም ሰው ጋር መለዋወጥ አልፈልግም። በምርጫዬ በጣም ኮርቻለሁ። የምፈልገውንና የሚያስፈልገኝን ሁሉ ይኸውም አርኪና ደስተኛ ሕይወት እንዲሁም ውጤታማና አስደሳች ሥራ አግኝቻለሁ።”

ኤሚ የአእምሮ ሰላም፣ እርካታና የይሖዋን በረከት የሚያስገኝ መንገድ ለመከተል መርጣለች። ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው ከዚህ የተለየ ነገር እንደማይመርጡ የተረጋገጠ ነው!

በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስኬት ማግኘት

እርግጥ ነው፣ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስኬት ስለማግኘትም ተገቢውን አመለካከት መያዝ እጅግ አስፈላጊ ነው። በመስክ አገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስናበረክት ወይም ከቤቱ ባለቤቶች ጋር አስደሳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ስናደርግ ተሳክቶልናል ብለን ማሰባችን አይቀርም። ሆኖም አልፎ አልፎ አድማጭ ጆሮ ስናጣ ጊዜያችን እንዲያው በከንቱ እንዳለፈ ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ስኬት የሚለው ቃል አንዱ ፍቺ ‘ሞገስ ማግኘት’ እንደሆነ አስታውስ። የምንፈልገው የማንን ሞገስ ለማግኘት ነው? የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ይህንን ደግሞ ሰዎች ለመልእክታችን ጆሮአቸውን ሰጡም አልሰጡ ማግኘት እንችላለን። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ግሩም ትምህርት አስተምሯል።

ኢየሱስ 70 የመንግሥቱን ሰባኪዎች “እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ” እንደላካቸው ታስታውሳለህ። (ሉቃስ 10:​1) የተላኩት ኢየሱስ በሌለበት በየከተማውና በየመንደሩ እንዲሰብኩ ነበር። እንደዚህ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር። በዚህ ምክንያት እነሱን ከመላኩ በፊት ዝርዝር መመሪያዎችን ሰጣቸው። “የሰላም ልጅ” ሲያገኙ መንግሥቱን በተመለከተ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት የሚቀበላቸው ሲያጡ ደግሞ ቅር ሳይሰኙ መንገዳቸውን መቀጠል ነበረባቸው። ኢየሱስ እነርሱን ለማዳመጥ እምቢተኛ የሆኑ ሰዎች የማይቀበሉት ይሖዋን እንደሆነ ተናግሯል።​—⁠ሉቃስ 10:​4–7, 16

ሰባዎቹ ደቀ መዛሙርት የስብከት ተልዕኳቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ኢየሱስ “በደስታ ተመልሰው:- ጌታ ሆይ፣ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል” የሚል ሪፖርት አቀረቡ። (ሉቃስ 10:​17) ፍጹም ያልነበሩት እነዚያ ሰዎች ኃያል መንፈሳዊ ፍጥረታትን ማስወጣት በመቻላቸው ተደንቀው መሆን አለበት! ይሁን እንጂ ኢየሱስ በስሜት ተውጠው የነበሩትን ደቀ መዛሙርቱን ሲያስጠነቅቅ “መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፣ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ” አላቸው። (ሉቃስ 10:​20፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚህ 70 ደቀ መዛሙርት ሁልጊዜ አጋንንት የማስወጣት ኃይል ይኖራቸዋል ወይም በአገልግሎቱ ሁልጊዜ ጥሩ ውጤት ያገኛሉ ማለት አይደለም። ሆኖም በታማኝነት ከጸኑ ሁልጊዜ የይሖዋን ሞገስ ያገኛሉ።

የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ታደንቃለህ?

አንድ ወጣት ለአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ሥራ ለማግኘት እሞክራለሁ። ሥራ ማግኘት ካልቻልኩ ግን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እጀምራለሁ” ብሎት ነበር። ይሁን እንጂ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ አቅኚዎች ይህ ዓይነቱ አመለካከት የላቸውም። አንዳንዶች አቅኚ ለመሆን ሲሉ ጥሩ ክፍያ ያለው ሥራ ለመያዝ የነበራቸውን አጋጣሚ ትተዋል። ሌሎች ደግሞ አስደሳች የትምህርት አጋጣሚዎችን ወደ ጎን ብለዋል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ መሥዋዕትነቶችን ከፍለዋል፤ ሆኖም ጳውሎስ፣ ሮበርትና ኤሚ በምርጫቸው እንዳልተቆጩ ሁሉ እነርሱም አይቆጩም። ተሰጥዎቻቸውን ከሁሉም በላይ ክብር የሚገባውን ይሖዋን ለማክበር የመጠቀም መብት በማግኘታቸው በጣም ደስተኞች ናቸው።

ብዙዎቹ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አቅኚ መሆን አልቻሉም። ምናልባትም ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች ይኖሯቸው ይሆናል። ያም ሆኖ አምላክን ‘በሙሉ ልባቸው፣ ነፍሳቸው እና ሐሳባቸው’ እስካገለገሉ ድረስ ይሖዋ ይደሰትባቸዋል። (ማቴዎስ 22:​37) ራሳቸው አቅኚዎች መሆን ባይችሉም አቅኚ መሆን የቻሉ ጥሩ ምርጫ እንዳደረጉ ይገነዘባሉ።

ሐዋርያው ጳውሎስ “ይህን ዓለም አትምሰሉ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 12:​2) ጳውሎስ ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ስንል ባህል ወይም የአካባቢው የኑሮ ደረጃ አስተሳሰባችንን እንዲቀርጽብን መፍቀድ አይገባንም። አቅኚ ሆንክም አልሆንክ በሕይወትህ ዋነኛውን ትኩረት የምትሰጠው ለይሖዋ አገልግሎት ይሁን። የይሖዋን ሞገስ እስካገኘህ ድረስ ስኬታማ ትሆናለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማብቂያ በሌለው ሽክርክሪት ውስጥ ገብተህ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ