“በየአቅጣጫው ብንገፋም እምነታችን አይላላም”!
የሕይወት ታሪክ
“በየአቅጣጫው ብንገፋም እምነታችን አይላላም”!
ኸርበርት ሙለርእንደተናገረው
የሂትለር ጦር ኔዘርላንድን ከወረረ ከጥቂት ወራት በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ እገዳ ተጣለ። ብዙም ሳይቆይ ናዚ በጥብቅ በሚፈልጋቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ላይ የእኔም ስም በመውጣቱ እንደ አውሬ እታደን ጀመር።
አንድ ወቅት ሁልጊዜ እየተሽሎከለክሁ መኖሩ በጣም ስለታከተኝ ባለቤቴን አሁንስ ይዘውኝ ብገላገል ይሻለኛል አልኳት። ከዚያም “በየአቅጣጫው ብንገፋም እምነታችን አይላላም” የሚለው የአንድ መዝሙር ስንኝ ትዝ አለኝ። a በዚህ መዝሙር ላይ ማሰላሰሌ ኃይሌ እንዲታደስ ከማድረጉም በላይ ጀርመን የነበሩትን ወላጆቼንና ጓደኞቼ ለእኔ ሽኝት ይህን መዝሙር የዘመሩበትን ቀን አስታወሰኝ። ከእነዚህ ትዝታዎቼ መካከል አንዳንዶቹን ላካፍላችሁ?
የወላጆቼ ምሳሌነት
በጀርመን በኮፒትስ ከተማ በ1913 ስወለድ ወላጆቼ የኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን አባላት ነበሩ። b ከሰባት ዓመታት በኋላ በ1920 አባቴ ከቤተ ክርስቲያኑ ለቀቀ። ሚያዝያ 6 ኪርክናውስትሪትስቤሻይነገን (ከቤተ ክርስቲያኑ የመልቀቂያ ወረቀት) እንዲሰጠው ጠየቀ። የከተማይቱ የመዘጋጃ ቤት ሹም ሞልቶ ሰጠው። ይሁን እንጂ በተሰጠው መልቀቂያ ወረቀት ላይ የሴት ልጁ ስም እንደሌለ ለመግለጽ ከሳምንት በኋላ ወደዚያ ቢሮ ተመለሰ። ሹሙ መልቀቂያው ማርታ ማርጋሬታ ሙለርንም የሚጨምር መሆኑን የሚገልጽ ሌላ መልቀቂያ ወረቀት ሞልቶ ሰጠው። በዚያን ጊዜ እህቴ ማርጋሬታ ገና የዓመት ከስድስት ወር ሕፃን ነበረች። አባቴ ይሖዋን ለማገልገል ከወሰኑ አይቀር ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል የሚል አቋም ነበረው!
በዚያው ዓመት ወላጆቼ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው በሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች ተጠመቁ። አባታችን ጥብቅ ሆኖ ነበር ያሳደገን፤ ሆኖም
ለይሖዋ ያለው ታማኝነት የሚሰጠንን አመራር ለመቀበል ቀላል አድርጎልናል። ታማኝነት ቤተሰቦቼ አንዳንድ ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉም አነሳስቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት እሑድ እሑድ ሜዳ ላይ ወጥተን እንድንጫወት አይፈቀድልንም ነበር። ይሁን እንጂ በ1925 አንድ እሑድ ዕለት ወላጆቻችን ሽርሽር እንደምንሄድ ነገሩን። ቀላል ምግብ ይዘን ሄደን የነበረ ሲሆን አስደሳች ጊዜ አሳለፍን። ሙሉ ቀን ቤት ውስጥ ታጉረን ከመዋል የሚሻል እንዴት ያለ ለውጥ ነበር! አባቴ በቅርቡ ካደረግነው የአውራጃ ስብሰባ የተማራቸው አንዳንድ ነጥቦች እሑድ ዕለት በሚኖረው እንቅስቃሴ ረገድ አመለካከቱን እንዲያስተካክል እንዳደረገው ተናግሯል። በሌሎች ጊዜያትም ተጨማሪ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ተመሳሳይ ፈቃደኝነት አሳይቷል።ምንም እንኳ ወላጆቼ ጥሩ ጤንነት ባይኖራቸውም በስብከቱ ሥራ ከመካፈል ወደኋላ አላሉም። ለምሳሌ ያህል ካህናት ተወነጀሉ የሚለውን ትራክት ለማሰራጨት አንድ ምሽት ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር በባቡር ተሳፍረን ከድሬስደን 300 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ወደሚገኘው ሬጀንስበርግ ከተማ ተጓዝን። በሚቀጥለው ቀን ትራክቱን ከተማው ውስጥ አሰራጭተን ስንጨርስ በባቡር ተመለስን። ቤታችን ለመድረስ ባጠቃላይ የፈጀብን ጊዜ ወደ 24 ሰዓት ገደማ ነበር።
ከቤት መውጣት
በተጨማሪም በጉባኤያችን ከሚገኘው ዩገንትግሩፕ (የወጣቶች ቡድን) ጋር ያደረኩት ቅርርብ በመንፈሳዊ እንዳድግ ረድቶኛል። ዕድሜያቸው ከ14 በላይ የሚሆናቸው ወጣቶች በጉባኤው ውስጥ ካሉ በዕድሜ ከፍ ካሉ ወንድሞች ጋር በየሳምንቱ አንድ ላይ ይገናኙ ነበር። የሙዚቃ መሣሪያዎችንና አንዳንድ ጨዋታዎችን እንጫወት የነበረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ እናጠናለን እንዲሁም ስለ ፍጥረትና ስለ ሳይንስ እናወራለን። ይሁን እንጂ በ1932 የ19 ዓመት ልጅ ሳለሁ ከዚያ ቡድን ጋር የነበረኝ ግንኙነት ተቋረጠ።
በዚያው ዓመት በሚያዝያ ወር አባቴ ማግደቡርግ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ አንድ ደብዳቤ ደረሰው። ማኅበሩ መኪና መንዳት የሚችልና አቅኚ ለመሆን ፍላጎት ያለው ሰው ይፈልግ ነበር። ወላጆቼ እኔ አቅኚ ብሆን ደስ እንደሚላቸው አውቃለሁ፤ ሆኖም መሆን እንደማልችል ተሰማኝ። ወላጆቼ ድሃ ስለነበሩ ብስክሌቶችን፣ የስፌት መኪናዎችን፣ የጽሕፈት መኪናዎችን እንዲሁም ሌሎች የቢሮ ዕቃዎችን መጠገን የጀመርኩት በ14 ዓመቴ ነበር። ታዲያ ቤተሰቤን እንዴት ትቼ እሄዳለሁ? የእኔ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም በላይ ገና አልተጠመኩም። አባቴ ጥምቀት ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል የተረዳሁ መሆኑን ማረጋገጥ ስለፈለገ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠየቀኝ። ከሰጠሁት መልስ ለመጠመቅ የሚያበቃ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እንዳደረግሁ ሲገነዘብ “ለዚህ ኃላፊነት ራስህን ማቅረብ ይገባሃል” አለኝ። እኔም እንዳለኝ አደረግሁ።
ከሳምንት በኋላ ወደ ማግደቡርግ እንድሄድ ግብዣ ቀረበልኝ። ሁኔታውን በወጣት ቡድኑ ለሚገኙ ጓደኞቼ ስነግራቸው አንድ ደስ የሚል መዝሙር ዘምረውልኝ ሊሸኙኝ ፈለጉ። ኃይለኛ መልእክት የያዘ መዝሙር ይመርጣል ብለው አልጠበቁም ነበር። ቢሆንም ቫዮሊናቸውን፣ ማንዶሊናቸውንና ጊታራቸውን ይዘው “በየአቅጣጫው ብንገፋም እምነታችን አይላላም፤ ምንም ዓይነት ምድራዊ መከራ ቢደርስብን አንናወጥም” በማለት
ዘመሩ። ያን ዕለት እነዚህ ቃላት በመጪዎቹ ዓመታት ምን ያህል ብርታት እንደሚጨምሩልኝ አልተገነዘብኩም ነበር።ፈታኝ ጅምር
በማግደቡርግ የሚገኙት ወንድሞች መኪና የመንዳት ችሎታዬን ከፈተኑ በኋላ እኔና ሌሎች አራት አቅኚዎች አንድ መኪና ተሰጥቶን በቤልጅየም ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው ሽኒፈ ወደሚባል አካባቢ አቀናን። ብዙም ሳይቆይ የመኪናው መኖር የግድ አስፈላጊ እንደነበር ተረዳን። የእኛ በዚያ መገኘት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን አላስደሰተም። የመንደሩ ነዋሪዎች በቀሳውስቱ ተገፋፍተው እኛን ከዚያ ለማባረር አመቺ ጊዜ ይጠብቁ ነበር። መኪናው የመንደሩ ሰዎች በመኮትኮቻና በመንሽ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት እንድናመልጥ በተደጋጋሚ ረድቶናል።
በ1933 የመታሰቢያውን በዓል ካከበርን በኋላ የአካባቢ የበላይ ተመልካች የነበረው ፖል ግሮስማን በጀርመን በማኅበሩ ሥራ ላይ እገዳ እንደተጣለ ነገረን። ብዙም ሳይቆይ ቅርንጫፍ ቢሮው መኪናውን ይዤ ወደ ማግደቡርግ እንድመለስና ጽሑፍ ጭኜ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ዛክሶኒ እንዳደርስ ጠየቀኝ። ሆኖም ማግደቡርግ ስደርስ ጌስታፖ (የናዚ ምስጢራዊ ፖሊስ) የማኅበሩን ቢሮ አሽጎታል። መኪናውን ሊፕዚግ በሚገኝ አንድ ወንድም ቤት ትቼ ወደ ቤት ተመለስኩ፤ ሆኖም እዚያ ብዙ አልቆየሁም።
በስዊዘርላንድ የሚገኘው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ኔዘርላንድ ውስጥ በአቅኚነት እንድሠራ ጥሪ አቀረበልኝ። በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እሄዳለሁ ብዬ አስቤ ነበር። ይሁን እንጂ አባቴ ወዲያውኑ እንድሄድ መከረኝ። ምክሩን ተቀበልኩና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከቤት ወጣሁ። በማግሥቱ ፖሊስ አገር ከድቷል በሚል ክስ ሊያስረኝ አባቴ ቤት መጣ። ደግነቱ እዚያ አልነበርኩም።
በኔዘርላንድ ሥራ መጀመር
ነሐሴ 15, 1933 ከአምስተርዳም 25 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሆምስቲድ ከተማ ወዳለው የአቅኚዎች ቤት ደረስኩ። አንዲት የደች ቃል የማላውቅ ቢሆንም በማግሥቱ አገልግሎት ወጣሁ። የስብከት መልእክት የሰፈረባቸው የመመሥከሪያ ካርዶች ይዤ አገልግሎት ጀመርኩ። አንዲት የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሪኮንሲሌሽን! የተባለውን መጽሐፍ መውሰዷ ምንኛ አበረታች ነበር! የዚያኑ ዕለት ተጨማሪ 27 ቡክሌቶች አበርክቻለሁ። ለመስበክ እንደገና ነፃነት በማግኘቴ ያን ዕለት ምሽት እጅግ ተደስቼ ነበር።
በዚያን ጊዜ አቅኚዎች ጽሑፍ አበርክተው ከሚያገኙት ገንዘብ ውጪ ምንም ገቢ አልነበራቸውም። ገንዘቡ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት ይውላል። በወሩ መጨረሻ በእጃችን ላይ ጥቂት ገንዘብ ከቀረ አቅኚዎች የግል ወጪያቸውን ለመሸፈን ይከፋፈሉታል። በቁሳዊ ነገር ረገድ ምንም የሌለን ብንሆንም ይሖዋ አስፈላጊውን ሁሉ ስለሚያሟላልን በ1934 ስዊዘርላንድ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ መገኘት ችያለሁ።
ታማኝ ጓደኛ
በአውራጃ ስብሰባው ላይ ኤሪካ ፊንኪ የምትባል የ18 ዓመት ወጣት አየሁ። አገር ቤት እያለሁ ጀምሮ አውቃት ነበር። የእኅቴ የማርጋሬታ ጓደኛ የነበረች ሲሆን ኤሪካ ለእውነት ባላት ጽኑ አቋም ሁልጊዜ እደነቅ ነበር። በ1932 ከተጠመቀች በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ ሰው “ሃይል ሂትለር!” ለማለት እምቢ ብላለች ብሎ ለጌስታፖ ጠቆመባት። ጌስታፖዎች ፈልገው ካገኟት በኋላ ለምን እንደማትል ጠየቋት። ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ላነጋገራት መኮንን ሥራ 17:3ን አነበበችና አምላክ አዳኝ አድርጎ የሾመው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ እንደሆነ ገለጸች። መኮንኑ “እንደዚህ ብለው የሚያምኑ ሌሎች ሰዎች አሉ?” ሲል ጠየቃት። ኤሪካ የማንንም ስም ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረችም። ፖሊሱ እዚያው እንደሚያቆያት ሲዝትባት ስማቸውን ከምትሰጥ ብትሞት እንደምትመርጥ ነገረችው። ዓይኑን ካፈጠጠባት በኋላ “በይ ሂጂ ከዚህ። ድራሽሽ ይጥፋ። ሃይል ሂትለር!” ሲል አንባረቀባት።
ከአውራጃ ስብሰባው በኋላ ኤሪካ ስዊዘርላንድ ስትቆይ እኔ ወደ ኔዘርላንድ ተመለስኩ። ሁለታችንም ጓደኝነታችን እንደጠነከረ ተሰምቶን ነበር። ኤሪካ ስዊዘርላንድ እያለች አገር ቤት ጌስታፖዎች እንደሚፈልጓት ሰማች። እዚያው ቆይታ አቅኚ ለመሆን ወሰነች። ከጥቂት ወራት በኋላ ማኅበሩ ወደ ስፔን እንድትሄድ ጠየቃት። በማድሪድ ከዚያም በቢልባኦ በኋላም ቀሳውስት ስደት ቀስቅሰው እሷና የአገልግሎት ጓደኛዋ በታሰሩበት በሳን ሴባስቲያን በአቅኚነት አገልግላለች። በ1935 ከስፔን እንዲወጡ ታዘዙ። ኤሪካ ወደ ኔዘርላንድ መጣችና በዚያው ዓመት ተጋባን።
ከአድማስ የሚታይ የጦርነት ዳመና
ከተጋባን በኋላ በሂምስቴድ በአቅኚነት የሠራን ሲሆን ከዚያ ወደ ሮተርዳም ከተማ ተቀየርን። ልጃችን ቮልፍገን በ1937 እዚያ ተወለደ። ከዓመት በኋላ በሰሜን ኔዘርላንድ ወደምትገኘው ግሮኒንገን ከተማ ተዛወርን። እዚያም ጀርመናዊ አቅኚዎች ከነበሩት ከፈርዲናንድ እና ከሄልጋ ሆልቶርፍ እንዲሁም ከሴት ልጃቸው ጋር አብረን ኖረናል። ማኅበሩ የዳች መንግሥት በኔዘርላንድ የሚኖሩ የጀርመን ዜግነት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ እንዲሰብኩ እንደማይፈቀድላቸው ማስጠንቀቂያ ማስተላለፉን ሐምሌ 1938 አስታወቀን። በዚያው ወቅት የዞን አገልጋይ (የወረዳ የበላይ ተመልካች) ሆኜ ተሹሜ የነበረ ሲሆን ቤተሰባችን በሰሜን ኔዘርላንድ ለሚሰብኩ አቅኚዎች በማረፊያነት ወደምታገለግለው ሊክትድራከር (ብርሃን አብሪ) ወደምትባለው የማኅበሩ ጀልባ ተዛወረ። ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቤ ተለይቼ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው በብስክሌት እየተጓዝኩ ወንድሞች ስብከታቸውን እንዲቀጥሉ አበረታታ ነበር። ወንድሞች እንደተባሉት አድርገዋል። እንዲያውም አንዳንዶች የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ አድርገዋል። ቪም ኬትላሬ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው።
ከቪም ጋር በተዋወቅን ጊዜ እውነትን የተቀበለ ጎልማሳ ነበር፤ ሆኖም ተቀጥሮ በሚሠራበት የግብርና ሥራ ተጠምዶ ነበር። “ይሖዋን ለማገልገል ጊዜ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ሥራ መቀየር ይኖርብሃል” የሚል ምክር ሰጠሁት። እንዳልኩት አደረገ። ከጊዜ በኋላ እንደገና ስንገናኝ አቅኚ እንዲሆን አበረታታሁት። “ጉሮሮዬን ለመድፈን መሥራት ይኖርብኛል” ሲል መለሰልኝ። “በምንም ተዓምር ጦምህን አታድርም። ይሖዋ የሚያስፈልግህን ያሟላልሃል” በማለት በእርግጠኝነት አበረታታሁት። ቪም አቅኚነት ጀመረ። ከጊዜ በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንኳን በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግሏል። ዛሬ በ80ዎቹ ዕድሜው የሚገኝ ሲሆን አሁንም ቀናተኛ ምሥክር ነው። በእርግጥም ይሖዋ ተንከባክቦታል።
እገዳና መታደን
በግንቦት 1940 ሁለተኛ ልጃችን ሪና በተወለደች በዓመቱ የደች ሠራዊት በጦርነቱ ድል ተመታና ናዚ ኔዘርላንድን ተቆጣጠረ። በሐምሌ ወር ጌስታፖ የማኅበሩን ቢሮና ማተሚያ ወረሰ። በሚቀጥለው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮችን ለማሰር የተጠናከረ ዘመቻ የተካሄደ ሲሆን እኔም ተያዝኩ። የይሖዋ ምሥክር ከመሆኔ ባሻገር ዕድሜዬ ለውትድርና በሚፈለገው ገደብ ውስጥ የሚገኝ ጀርመናዊ ስለነበርኩ ጌስታፖዎች ምን እንደሚያደርጉኝ መገመት አያስቸግርም። ከእንግዲህ ከቤተሰቦቼ ጋር እገናኛለሁ የሚለውን ሐሳብ ከአእምሮዬ ለማውጣት ሞከርኩ።
ከዚያም ግንቦት 1941 ጌስታፖ ከእስር ቤት ከለቀቀኝ በኋላ ለውትድርና አገልግሎት እንዳመለክት አዘዘኝ። ያልጠበቅሁት በመሆኑ ማመን አልቻልኩም። በዚያው ዕለት ከዓይናቸው የተሰወርኩ ሲሆን በዚያው ወር የወረዳ ሥራዬን ቀጠልኩ። ከዚያም ጌስታፖዎች
ስሜን በጣም ከሚታደኑ ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ አስገቡት።ቤተሰቤ ችግሮችን የተቋቋመበት መንገድ
ባለቤቴና ልጆቼ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ወደሚገኘው ቮርደን የሚባል መንደር ተዛወሩ። ይሁን እንጂ ሊያስከትልባቸው የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ስል ወደ ቤት የምሄድበትን ጊዜ ወዲያው ውስን ማድረግ ነበረብኝ። (ማቴዎስ 10:16) ወንድሞች ለደህንነት ሲባል በስሜ አይጠሩኝም ነበር። የሚጠሩኝ ዳይተስ ያን (ጀርመን ጆን) በሚባለው የምስጢር ስም ነበር። የአራት ዓመቱ ልጄ ቮልፍገን እንኳ ስለ “ኦመ ያን” (አንክል ጆን) ካልሆነ በስተቀር ስለ “አባቱ” እንዲያነሳ አይፈቀድለትም ነበር። ሁኔታው በስሜት ረገድ ችግር ፈጥሮበት ነበር።
ከአንዱ ወደ አንዱ እየተሽሎኮሎክሁ በኖርኩባቸው ጊዜያት ኤሪካ ልጆቹን ትንከባከብ የነበረ ሲሆን መስበኳንም አላቋረጠችም ነበር። ሪና የሁለት ዓመት ልጅ ሳለች በብስክሌቱ የዕቃ መጫኛ ላይ ታስቀምጣትና ለአገልግሎት ወደ ገጠር ይዛት ትሄድ ነበር። ምግብ ማግኘት ፈታኝ ቢሆንም ኤሪካ ለቤተሰቡ የምታቀምሰውን አጥታ ተቸግራ አታውቅም። (ማቴዎስ 6:33) የስፌት መኪናውን የጠገንኩለት የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነ አንድ ገበሬ ድንች ይሰጣት ነበር። እንዲሁም ለኤሪካ መልእክት ያደርስልኝ ነበር። አንድ ቀን ከመድኃኒት ቤት መድኃኒት ገዝታ አንድ ጉልደን ከፈለች። የመድኃኒት ቤቱ ባለቤት በድብቅ እንደምትኖርና የራሽን ካርድ ማግኘት እንደማትችል ስላወቀ ዕቃውን በነጻ የሰጣት ሲሆን ሁለት ጉልደንም ጨመረላት። ይህን የመሰሉት የርህራሄ መግለጫዎች ችግሮቹን እንድትቋቋም ረድተዋታል።—ዕብራውያን 13:5
ደፋር ከሆኑ ወንድሞች ጋር ጎን ለጎን ሆኖ መሥራት
ምንም እንኳ የምገናኘው በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር ብቻ ቢሆንም ጉባኤዎችን መጎብኘት ቀጥዬ ነበር። ጌስታፖዎች እግር በእግር ስለሚከታተሉኝ አንድ ቦታ ከጥቂት ሰዓታት በላይ መቆየት አልችልም ነበር። ብዙዎቹ ወንድሞችና እህቶች ከእኔ ጋር እንዲገናኙ አይፈቀድላቸውም። ትውውቃቸው እነርሱ ባሉበት አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ውስጥ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ብቻ ነበር። በዚህ ምክንያት በአንድ ከተማ ውስጥ በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ሁለት እኅትማማቾች አንዷ ሌላዋ የይሖዋ ምሥክር መሆኗን ያወቀችው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነበር።
ሌላው ኃላፊነቴ የማኅበሩ ጽሑፎች የሚደበቁበትን ቦታ መፈለግ ነበር። መጠበቂያ ግንብ ለማባዛት የሚረዳ ወረቀት፣ ስቴንስልና የጽሕፈት መኪና ወደፊት ያስፈልገን ይሆናል በሚል እንደብቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የደበቅናቸውን የማኅበሩን መጽሐፎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው እናዘዋውር ነበር። አንድ ቀን 30 ካርቶን ጽሑፍ ሳይነቃብን ለማጓጓዝ ያደረግነው ሙከራ አይረሳኝም። እጅግ አስፈሪ ሥራ ነበር!
በተጨማሪም ምግብ ማጓጓዝ የተከለከለ ቢሆንም በምሥራቅ ኔዘርላንድ ከሚገኙ የእርሻ ቦታዎች በምዕራብ ወደሚገኙ ከተማዎች ምግብ የምናጓጉዝበትን ሁኔታ አደራጅተን ነበር። ምግቡን በፈረስ በሚጎተት ሰረገላ እንጭንና ወደ ምዕራብ እናቀናለን። ወንዝ ለመሻገር የትኛውንም ድልድይ መጠቀም አንችልም፤ ምክንያቱም በወታደሮች ይጠበቅ ነበር። ከዚህ ይልቅ ጭነቱን በአነስተኛ ጀልባዎች አራግፈን ካሻገርን በኋላ በሌላ ሰረገላ እንደገና እንጭናለን። የምንፈልገው ከተማ ስንደርስ እስኪጨልም እንጠብቅና በፈረሱ ኮቴ የእግር ሹራብ እናጠልቅና ምንም ድምፅ ሳናሰማ ቀስ ብለን ወደ ጉባኤው ድብቅ የምግብ ማከማቻ እንሄዳለን። ከዚያ ምግቡ ለተቸገሩ ወንድሞች ይከፋፈላል።
የጀርመን ጦር እንደዚህ ያለውን የምግብ ማከማቻ ቢደርስበት ቤቱን ለዚህ የፈቀደውን ሰው ጨምሮ እዚያ የተገኘውን ሁሉ ሕይወት ሊያሳጣ ይችላል። ያም ሆኖ በርካታ ወንድሞች እኛን ከማገዝ ወደኋላ አላሉም። ለምሳሌ ያህል በአመርስፉርት ከተማ የሚኖረው የብሉሚንክ ቤተሰብ ምንም እንኳ ቤታቸው ከጀርመን ጦር ሠራዊት ካምፕ የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ የሚገኝ ቢሆንም ሳሎናቸው የምግብ ማከማቻ እንዲሆን ፈቅደዋል! እነዚህን የመሰሉ ደፋር ምሥክሮች ለወንድሞቻቸው ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል።
ይሖዋ እገዳው በቆየባቸው ዓመታት በሙሉ እኔና ባለቤቴ ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ ረድቶናል። በመጨረሻም ግንቦት 1945 የጀርመን ጦር በመሸነፉ ከድብብቆሽ ሕይወት ተገላገልኩ። ሌሎች ወንድሞች እስኪገኙ ድረስ ተጓዥ የበላይ ተመልካችነቱን ሥራ እንድቀጥል ማኅበሩ ጠየቀኝ። በ1947 በርቱስ ፋን ደር ቤል ሥራውን ተረከበኝ። c በዚያን ጊዜ ሦስተኛ ልጅ የወልድን ሲሆን በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ተደላድለን መኖር ጀመርን።
ሐዘን እና ደስታ
እኔ ወደ ኔዘርላንድ ከሄድኩ ከአንድ ዓመት በኋላ አባቴ ታስሮ እንደነበረ ከጦርነቱ በኋላ ሰማሁ። ጤንነቱ በመቃወሱ ሁለት ጊዜ ከእስር ተፈትቶ የነበረ ቢሆንም ሁለቱንም ጊዜ እንደገና ይዘው አስረውታል። የካቲት 1938 ወደ ቡከንቫልድ ማጎሪያ ካምፕ ከዚያም ወደ ዳካው አዛውረውት ነበር። እዚያ እያለ ግንቦት 14, 1942 ሞተ። እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ጽኑ እና ታማኝ ሆኖ ቆይቷል።
እናቴም በዳካው ካምፕ ታስራ ነበር። በ1945 እስከተፈታችበት ጊዜ ድረስ እዚያው ቆይታለች። የወላጆቼ ጽኑ ምሳሌነት ላገኘሁት መንፈሳዊ በረከት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ስላደረገልኝ እናቴ በ1954 ከእኛ ጋር ለመኖር መምጣቷ ትልቅ መብት ነበር። ኮሚኒስት አገር በነበረችው በምሥራቅ ጀርመን ከ1945 ጀምሮ በአቅኚነት ስትሠራ የቆየችው እህቴ ማርጋሬታም አብራት መጥታለች። እናቴ ሁልጊዜ የምትታመምና ደች ቋንቋ መናገር የማትችል ቢሆንም ጥቅምት 1957 ምድራዊ ሕይወቷን በታማኝነት እስካጠናቀቀችበት ጊዜ ድረስ በመስክ አገልግሎት ትካፈል ነበር።
በ1955 በጀርመን ኑረምበርግ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ በዓይነቱ ልዩ ነበር። እዚያ ከደረስን በኋላ ከድሬስደን የመጡ ወንድሞች እናቷ ለስብሰባው እንደመጡ ለኤሪካ ነገሯት። በወቅቱ ድሬስደን በምሥራቅ ጀርመን አገዛዝ ሥር ስለነበረች ኤሪካ እናቷን ለ21 ዓመታት አላየቻቸውም ነበር። የሚገናኙበት ሁኔታ ተመቻቸላቸውና እናትና ልጅ ዳግም ለመተቃቀፍ በቁ። ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ መገናኘት እንዴት ያስደስታል!
ከጊዜ በኋላ ልጆቻችን ስምንት ደርሰው ነበር። አንዱን ልጃችንን በመኪና አደጋ ማጣታችን አሳዝኖናል። ይሁን እንጂ የቀሩት ልጆቻችን በሙሉ ይሖዋን ሲያገለግሉ ማየት የደስታ ምንጭ ሆኖልናል። ልጃችን ቮልፍገን እና ባለቤቱ በወረዳ ሥራ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ደስተኞች ስንሆን የእነርሱ ልጅም በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እያገለገለ ነው።
የይሖዋ ሥራ በኔዘርላንድ እያደገ ሲሄድ ለመመልከት በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ። በ1933 በኔዘርላንድ አቅኚነትን ስጀምር መቶ የሚያክሉ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ከ30, 000 በላይ ሆነዋል። ምንም እንኳ አቅማችን እየተዳከመ ቢመጣም እኔና ኤሪካ “በየአቅጣጫው ብንገፋም እምነታችን አይላላም” ከሚለው መዝሙር ስንኝ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር አሁንም ቁርጥ ውሳኔያችን ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a መዝሙር 194።—ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ (1928)።
b አሁን ፒርና እየተባለች የምትጠራው ኮፒትስ ከተማ የምትገኘው ከድሬስደን ከተማ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኢልቤ ወንዝ ዳርቻ ነው።
c በጥር 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ከእውነት የተሻለ ምንም ነገር የለም” በሚል ርዕስ የወጣውን የወንድም ፋን ደር ቤልን ተሞክሮ ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ዩገንትግሩፕ” ከመስክ አገልግሎት በኋላ እረፍት ላይ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኔና አቅኚ ጓደኞቼ የስቼንፊልን የአገልግሎት ክልል ሸፍነናል። በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ 20 ነበር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1940 ከኤሪካ እና ከቮልፍገን ጋር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከግራ ወደ ቀኝ:- የልጅ ልጄ ዮናታን እና ባለቤቱ ሚርያም፣ ኤሪካ፣ እኔ፣ ልጄ ቮልፍገን እና ባለቤቱ ዩልያ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአባቴ ጋር ታስሮ የነበረ አንድ ወንድም በ1941 የሣለው የአባቴ ፎቶ