የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባር ከሁሉ የተሻለ ነውን?
የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባር ከሁሉ የተሻለ ነውን?
“አንድ ኅብረተሰብ በሥሩ ላሉት ሰዎች ዋስትናና መመሪያ የሚሆን መሠረታዊ የሥነ ምግባር መዋቅር ያስፈልገዋል።” ይህንን አስተያየት የሰጡት አንድ ልምድ ያላቸው ጀርመናዊ ጸሐፊና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ናቸው። በእርግጥም ይህ እውነትነት ያለው አባባል ነው። የሰው ዘር ኀብረተሰብ የተረጋጋና የበለጸገ እንዲሆን ሰዎች ትክክልና ስህተቱን እንዲሁም ጥሩና መጥፎውን በመለየት ረገድ ጽኑ መሠረት ያላቸውና የጋራ ተቀባይነት ያገኙ መሥፈርቶች ሊኖሯቸው ይገባል። አሁን ግን ጥያቄው ለኀብረተሰቡም ሆነ ለአባላቱ ከሁሉ የተሻሉ መሥፈርቶች የሚሆኑት የትኞቹ ናቸው? የሚል ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ናቸው ከተባለ እነዚህ መሥፈርቶች ግለሰቦች የተረጋጋና ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩ ሊረዷቸው ይገባል። ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ እነዚህኑ መሥፈርቶች የሚጠብቅ ደስተኛና የተረጋጋ ኀብረተሰብ ይፈጥራል። በእርግጥ ጉዳዩ እንደዚያ ነውን? እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለት አስፈላጊ ጉዳዮች ማለትም በትዳር ውስጥ ታማኝነት ስለማሳየትና በዕለት ተዕለት ሕይወት ሐቀኛ ስለመሆን ምን እንደሚል እንመርምር።
ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተጣበቁ
ፈጣሪያችን አዳምን ከፈጠረ በኋላ ሔዋንን የትዳር ጓደኛው እንድትሆን አድርጎ ሠራት። ይህ ቁርኝት በታሪክ ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:24፤ ማቴዎስ 5:27-30፤ 19:5
ውስጥ የመጀመሪያው ጋብቻ ሲሆን እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ ጥምረትም እንዲሆን ታስቦ ነበር። አምላክ እንዲህ አለ:- “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል።” ከ4,000 ዓመታት ገደማ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንኑ የጋብቻ መሥፈርት ለተከታዮቹ ደግሞላቸዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ ከትዳር ውጭ የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት አውግዟል።—ትዳር ደስታ ያለበት እንዲሆን ተጋቢዎቹ ሊያሳዩአቸው የሚገቡ ሁለቱ ቁልፍ ባሕርያት ፍቅርና አክብሮት መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። የቤተሰቡ ራስ የሆነው ባል የሚስቱን ፍላጎት በማስቀደም ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር ማሳየት አለበት። ባል ከሚስቱ ጋር “በማስተዋል [“በእውቀት፣” NW ]” አብሮ መኖር ይኖርበታል። በተጨማሪም በሚስቱ ላይ “መራራ” መሆን አይኖርበትም። ሚስትም ባሏን “በጥልቅ ማክበር” ይኖርባታል። ባለ ትዳሮች እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከተከተሉ አብዛኞቹን የጋብቻ ችግሮች ማስቀረት ወይም ማስወገድ ይቻላል። ባልየው ከሚስቱ እንዲሁም ሚስትየው ከባሏ ጋር መጣበቅ ይኖርባቸዋል።—1 ጴጥሮስ 3:1-7፤ ቆላስይስ 3:18, 19፤ ኤፌሶን 5:22-33 NW
ከትዳር ጓደኛ ጋር በታማኝነት መጣበቅ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ደስታ ያለበት ትዳር ለመመሥረት አስተዋጽኦ ያደርጋልን? በጀርመን የተካሄደውን የአንድ ጥናት ውጤት ተመልከት። ሰዎች ለጥሩ ትዳር የሚያስፈልጉት ነገሮች ምንድን ናቸው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። በውጤቱም የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ የተገኘው እርስ በርስ ታማኝ መሆን የሚለው ምላሽ ነበር። ባለትዳሮች አንደኛው ለሌላው ታማኝ መሆኑን ማወቃቸው ይበልጥ ደስተኞች ያደርጋቸዋል ቢባል አትስማማም?
ችግሮች ቢፈጠሩስ?
በባልና በሚስት መካከል ከባድ አለመግባባቶች ቢፈጠሩስ? ፍቅራቸው ቢያልቅስ? እንዲህ የመሳሰሉ ሁኔታዎች ካጋጠሙ መፋታቱ የተሻለ አይደለምን? ወይስ በዚህም ጊዜ ቢሆን ከትዳር ጓደኛ ጋር በታማኝነት መጣበቅ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ማክበር ምክንያታዊ ይሆናል?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሁሉም ባለ ትዳሮች በአለፍጽምና ምክንያት ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ተገንዝበው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መስፈርቶች የሚከተሉ ባልና ሚስት ይቅር ለመባባልና በጋራ ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለማግኘት ይጥራሉ። እርግጥ፣ አንድ ክርስቲያን ለመለያየት ወይም ለመፋታት መወሰኑን ተገቢ የሚያደርጉት እንደ ዝሙት ወይም አካላዊ ሥቃይ የመሳሰሉ ሁኔታዎች አሉ። (ማቴዎስ 5:32፤ 19:9) ይሁን እንጂ አለምንም በቂ ምክንያት ወይም ሌላ ሰው ለማግባት ሲባል ብቻ ትዳሩን በችኮላ ማፍረስ ራስ ወዳድነትንና ለትዳር ጓደኛው ደንታ ቢስ መሆንን ያሳያል። በእርግጥም ይህ ለአንድ ሰው መረጋጋትም ሆነ ደስታ አያመጣለትም። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
ፒተር ትዳሩ በአንድ ወቅት የነበረውን ድምቀት እንዳጣ ስለተሰማው ሚስቱን ትቶ ባሏን ጥላ ከመጣች ሞኒካ የተባለች ሴት ጋር መኖር ጀመረ። a ሁኔታዎች ምን መልክ ይዘው ይሆን? ከጥቂት ወራት በኋላ ፒተር ከሞኒካ ጋር መኖር “እንዳሰብኩት ቀላል አልነበረም” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ለምን? ሰብዓዊ ድክመቶች በመጀመሪያው ትዳሩ ውስጥ እንደነበሩ ሁሉ በአዲሱ ዝምድናው ውስጥም ነበሩ። በችኮላና በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስቶ ያደረገው ውሳኔ ከባድ የገንዘብ ችግር ውስጥ ስለከተተው ሁኔታው በጣም ተባባሰ። ከዚህም በላይ የሞኒካ ልጆች በቤተሰባቸው ውስጥ በተፈጠረው ድንገተኛ ለውጥ ምክንያት ስሜታቸው ተደቆሰ።
ከዚህ ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው በትዳር ውስጥ ከባድ ችግር ሲነሳ ጥሎ መሸሹ መፍትሄ አይሆንም። በሌላ በኩል ግን እንደ ማዕበል ያለ ችግር ሲያጋጥም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት ብዙውን ጊዜ ትዳሩ ማዕበሉን አልፎ የሰከነ ጉዞ እንዲጀምር ያደርገዋል። የቶማስና የዶሪስ ሁኔታ ይህንን ይመስላል።
ቶማስና ዶሪስ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት ተጋብተው ከቆዩ በኋላ ቶማስ ከባድ ጠጪ ሆነ። ሁኔታው ዶሪስን ጭንቀት ላይ ስለጣላት ሁለቱም ስለ ፍቺ አንስተው ተወያዩ። ዶሪስ ምስጢሯን ለአንዲት የይሖዋ ምሥክር ስታካፍላት ምሥክሯ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻ ምን እንደሚል በማስረዳት ለመፋታት ከመቸኮል ይልቅ በመጀመሪያ ሁለቱም ተነጋግረው ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት እንዲጥሩ አበረታታቻት። ዶሪስም እንደተባለችው አደረገች። በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ ስለ ፍቺ መነሳቱ ቀረና ሁለቱም ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተላቸው ትዳራቸውን ከማጠናከሩም በላይ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚያስችል በቂ ጊዜ ሰጥቷቸዋል።
በሁሉም ነገር ሐቀኝነት ማሳየት
ከትዳር ጓደኛ ጋር በታማኝነት መጣበቅ ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬንና ለመሠረታዊ ሥርዓቶች ፍቅር ማዳበርን ይጠይቃል። ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ሐቀኛ ሆኖ ለመገኘትም ተመሳሳይ የሆኑ ባሕርያት ያስፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኝነትን አስመልክቶ ብዙ የሚለው አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳ ለሚገኙት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በመልካም [“በሐቀኝነት፣” NW ] እንድንኖር [ወደናል]።” (ዕብራውያን 13:18) ይህ ምን ማለት ነው?
ሐቀኛ የሆነ ሰው እውነተኛና ከማጭበርበር ድርጊት የነጻ ነው። ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ አድሎ የማያሳይ፣ ቅን፣ ጨዋ እንዲሁም የማያጭበረብር ወይም የማያምታታ ሰው ነው። ከዚህም በላይ ሐቀኛ ሰው ባልንጀራውን የማያታልል የጸና አቋሙን የሚጠብቅ ሰው ነው። ሐቀኛ የሆኑ ሰዎች የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይህም ጤናማ አመለካከትና ጠንካራ ሰብዓዊ ግንኙነቶች ለመመስረት ያስችላል።
ሐቀኛ የሆኑ ሰዎች ደስተኞች ናቸው? ደግሞም ደስተኞች የሚሆኑበት ምክንያት አላቸው። ሙስናና ማጭበርበር በእጅጉ የተስፋፉ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ሐቀኛ ሰዎች በሌሎች ዘንድ አድናቆት ያተርፋሉ። በሌላው በኩል ደግሞ የእነዚህ ነገሮች መስፋፋትም ሐቀኛ የሆኑ ሰዎች እንዲደነቁ ምክንያት ይሆናል። በወጣቶች ላይ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ለሐቀኝነት ከፍተኛ ግምት ሰጥተዋል። ከዚህም በላይ ዕድሜያችን ምንም ያህል ይሁን ምን ሐቀኝነት ከጓደኞቻችን በጣም የምንፈልገው ነገር ነው።
ክርስቲን ከ12 ዓመቷ ጀምሮ ስርቆት በመማሯ ከዓመታት በኋላ ደንበኛ ኪስ አውላቂ ሆነች። እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ወደ 2,200 የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ቤት የማመጣባቸው ጊዜያት ነበሩ።” ይሁን እንጂ ክርስቲን ብዙ ጊዜ የታሰረች ሲሆን የምትኖረው ዘወትር ወደ ወህኒ እወርዳለሁ በሚል ስጋት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐቀኝነት ምን እንደሚል ሲያብራሩላት በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተማረከች። “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ” የሚለውን ምክር መታዘዝን ተማረች።—ኤፌሶን 4:28
ክርስቲን ከይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዷ ሆና ስትጠመቅ መስረቋን አቁማ ነበር። ምሥክሮቹ ለሐቀኝነትና ለሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርያት የላቀ ግምት ስለሚሰጡ ክርስቲን በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን ጥረት እያደረገች ነበር። ላውዚትስ ሩንትሻው የተባለው ጋዜጣ “እንደ ሐቀኝነት፣ ልከኝነትና የጎረቤት ፍቅር የመሳሰሉት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በምሥክሮቹ ሃይማኖት ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ነገሮች ናቸው” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ክርስቲን በሕይወቷ ውስጥ ባደረገችው ለውጥ ምን ተሰማት? “መስረቅ በማቆሜ አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ። የተከበርኩ የሕብረተሰቡ አባል እንደሆንኩ ይሰማኛል።”
መላው ኀብረተሰብ ይጠቀማል
በትዳራቸው ውስጥ ታማኞች የሆኑና በሐቀኝነት የሚመላለሱ ሰዎች ራሳቸው ደስተኞች ከመሆናቸውም በላይ ለኅብረተሰቡ በአጠቃላይ ጠቃሚ ናቸው። አሠሪዎች የማያጭበረብሩ ሠራተኞችን ይመርጣሉ። ሁላችንም ብንሆን እምነት የሚጣልባቸው ጎረቤቶች እንዲኖሩን እንፈልጋለን። በተጨማሪም በሐቀኛ ሰዎች በሚተዳደሩ መደብሮች ውስጥ መገብየት እንፈልጋለን። በሙስና ተግባር የማይካፈሉትን ፖለቲከኞች፣ ፖሊሶችና ዳኞች አናከብርምን? የአንድ ማሕበረሰብ አባላት ጠቃሚ መስሎ ሲታያቸው ብቻ ሐቀኝነትን ከማሳየት ይልቅ ይህንን ባህርይ የሕይወታቸው የዕለት ተዕለት መርህ ማድረጋቸው ለማኅበረሰቡ የላቀ ጥቅም አለው።
በተጨማሪም እርስ በርሳቸው ታማኝ የሆኑ ባልና ሚስት የተረጋጋ ቤተሰብ መሠረት ናቸው። ብዙ ሰዎች “የሰው ልጅ ያለ ስጋት እንዲያርፍና ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖር በማድረግ ረገድ [ባሕላዊው] ቤተሰብ እስከ ዛሬ በጣም ጠቃሚ ድርሻ ሲያበረክት ቆይቷል” ብለው ከተናገሩት አውሮፓዊ የፖለቲካ ሰው ጋር ይስማማሉ። ሰላም የሰፈነበት ቤተሰብ አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች ስሜታዊ ደህንነት የሚያገኙበት ከሁሉ የተሻለው ቦታ ነው። በመሆኑም ታማኝ የሆኑ ባለትዳሮች የተረጋጋ ኅብረተሰብ በመመሥረት ረገድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።
የትዳር ጓደኞቻቸው ጥለዋቸው የሄዱ ሰዎች፣ ለፍቺ ወይም ልጆች የማሳደግ መብት ለማግኘት የሚደረጉ የፍርድ ቤት ሙግቶች ባይኖሩ ኖሮ እያንዳንዱ ሰው ምን ያህል ይጠቀም እንደነበር አስብ። በተጨማሪም ኪስ አውላቂዎች፣ የሱቅ ሌቦች፣ የሌላውን ንብረት ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ሰዎች፣ ሙስና የሚፈጽሙ ባለ ሥልጣናት ወይም አጭበርባሪ የሳይንስ ሊቃውንት ባይኖሩ ኖሮስ? ይህ እንዲያው ሕልም ብቻ ይመስላል? መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ተስፋችን የሚናገረውን ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ሕልም አይደለም። በቅርቡ መዝሙር 37:29
የይሖዋ መሢሐዊ መንግሥት ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ የማስተዳደሩን ሥልጣን እንደሚረከብ የአምላክ ቃል ይናገራል። በዚያ መንግሥት ሥር ሁሉም ተገዥዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ትምህርት ይሰጣቸዋል። በዚያን ጊዜ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባር ከሁሉም የላቀ ነው
ቅዱሳን ጽሑፎችን የመረመሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ከሰብዓዊ አስተሳሰብ በሚልቀው አምላካዊ ጥበብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተገንዝበዋል። እንዲህ ያሉት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝና ለዘመናዊው ዓለም የሚሠራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ሰምቶ እርምጃ መውሰዱ ለገዛ ራሳቸው ጥቅም እንደሆነ ያውቃሉ።
ስለሆነም እንደዚህ ያሉት ግለሰቦች “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ። በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ። (ምሳሌ 3:5, 6) እንዲህ በማድረግ የራሳቸውን ሕይወት ከማሻሻላቸውም በላይ በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ይጠቅማሉ። በተጨማሪም ሁሉም የሰው ዘር የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚከተልበትን ‘የሚመጣውን ሕይወት’ በተመለከተ ጽኑ እምነት ያዳብራሉ።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ ያሉት ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በትዳር ውስጥ እንደ ማዕበል ያለ ችግር ሲያጋጥም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት ብዙውን ጊዜ ትዳር ማዕበሉን አልፎ የሰከነ ጉዞ እንዲጀምር ያስችላል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሙስናና ማጭበርበር በእጅጉ የተስፋፉ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ሐቀኛ ሰዎች በሌሎች ዘንድ አድናቆት ያተርፋሉ። በሌላው በኩል ደግሞ የእነዚህ ነገሮች መስፋፋትም ሐቀኛ የሆኑ ሰዎች እንዲደነቁ ምክንያት ይሆናል