በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተትረፈረፈ ልግስና ደስታ ያስገኛል

የተትረፈረፈ ልግስና ደስታ ያስገኛል

የተትረፈረፈ ልግስና ደስታ ያስገኛል

ሐዋርያው ጳውሎስ አፍቃሪ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች እንደመሆኑ መጠን ለእምነት ጓደኞቹ ከልቡ ያስብ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:​28) ከዚህ የተነሳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በ50ዎቹ አጋማሽ ላይ በይሁዳ ለሚገኙ ችግረኛ ክርስቲያኖች ገንዘብ ማዋጣት የሚቻልበት ዝግጅት ባደረገበት ወቅት አጋጣሚውን ተጠቅሞ ልግስናን የሚመለከት ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቷል። ጳውሎስ በደስተኝነት መንፈስ መስጠትን ይሖዋ በጣም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ጠበቅ አድርጎ ገልጿል:- “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 9:​7

በከፍተኛ ድህነት ሥር ቢኖሩም ልግስና አሳይተዋል

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው አልነበሩም። ጳውሎስ በመካከላቸው “ኀያላን የሆኑ ብዙ​ዎች” አለመኖራቸውን ጠቅሷል። ክርስቲያኖች ‘የዓለም ደካማ ነገር፣’ ‘የዓለም ምናምንቴ ነገር’ ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 1:​26-28) ለምሳሌ ያህል በመቄዶንያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ‘በጥልቅ ድህነት’ እና ‘በመከራ’ ሥር ነበሩ። ሆኖም እነዚህ በመቄዶንያ የሚኖሩ ትሑት አማኞች “ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት” የገንዘብ መዋጮ የማድረግ መብት ለማግኘት ልመና አቅርበዋል። ደግሞም ‘ከአቅማቸው የሚያልፍ’ እንደሰጡ ጳውሎስ መስክሯል!​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:​1-4

ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ልግስና በስጦታው መጠን ላይ የተመካ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ውስጣዊ ግፊት፣ ለማካፈል ፈቃደኛ መሆንና የልብ ዝንባሌ አስፈላጊ ነገሮች ነበሩ። ጳውሎስ መዋጮ በመስጠት ረገድ አእምሮም ሆነ ልብ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገልጿል። “በጎ ፈቃዳችሁን [“አእምሯችሁ ዝግጁ መሆኑን፣” NW ] አውቄአለሁና . . . ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፣ ቅንዓታችሁም የሚበዙትን አነሣሥቶአል” ብሏል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልግስና ለመስጠት ‘በልባቸው አስበው’ ነበር።​—⁠2 ቆሮንቶስ 9:​2, 7

‘መንፈሳቸው እሺ አሰኛቸው’

ሐዋርያው ጳውሎስ በልግስና በመስጠት ረገድ እሱ ከኖረበት ከ15 መቶ ዓመታት በፊት በምድረ በዳ የተከናወነውን አንድ የቆየ ምሳሌ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ከግብፅ ባርነት ነፃ ወጥተዋል። አሁን ሲና ተራራ ሥር የሰፈሩ ሲሆን ይሖዋ አምልኮ የሚከናወንበት የማደሪያ ድንኳን እንዲሠሩና በዚያ ለሚካሄደው አምልኮ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እንዲያሟሉ አዘዛቸው። ይህ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ብሔሩም መዋጮ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበለት።

እስራኤላውያን የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? “ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ . . . ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ።” (ዘጸአት 35:​21) ብሔሩ ያመጣው ስጦታ ልግስና የታከለበት ነበርን? ከፍተኛ ልግስና ተንጸባርቆበታል! ሙሴ ቀጥሎ ያለው ሪፖርት ደርሶት ነበር:- “እግዚአብሔር ለማገልገያ ሥራ ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ከሚበቃ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ።”​—⁠ዘጸአት 36:​5

በዚያን ወቅት የነበሩት እስራኤላውያን የገንዘብ አቅማቸው እንዴት ነበር? ከጥቂት ጊዜ በፊት ‘በብርቱ ሥራ ተጨንቀው’ ‘መራራ’ ‘የመከራ’ ሕይወት የሚመሩ አሳዛኝ ባሪያዎች ነበሩ። (ዘጸአት 1:​11, 14፤ 3:​7፤ 5:​10-18) ከዚህ የተነሳ በቁሳዊ ሀብት ባለጸጋ ነበሩ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። እርግጥ እስራኤላውያን በባርነት የኖሩበትን አገር ለቅቀው የወጡት ከመንጎችና ከከብቶች ጋር ነበር። (ዘጸአት 12:​32) ይሁን እንጂ ከግብፅ ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የምንበላው ሥጋም ሆነ እንጀራ አጣን ብለው ስላማረሩ ይዘውት የወጡት መንጋና ከብት ብዙም የሚጋነን እንዳልነበረ መረዳት ይቻላል።​—⁠ዘጸአት 16:​3

ታዲያ እስራኤላውያን ለማደሪያው ድንኳን ግንባታ ያዋጧቸውን ውድ ዕቃዎች ያገኙት ከየት ነበር? ቀድሞ ጌቶቻቸው ከነበሩት ከግብፃውያን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- ‘የእስራኤልም ልጆች ከግብፃውያን የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ። ግብፃውያንም የፈለጉትን ሰጡአቸው።’ ግብፃውያን ያሳዩት ይህ ልግስና ከፈርዖን ሳይሆን ከይሖዋ የተገኘ በረከት ነበር። መለኮታዊው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ።”​—⁠ዘጸአት 12:​35, 36

በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ምን እንደተሰማቸው ገምት። በርካታ ትውልዶች በአስከፊ ባርነትና ድህነት ማቅቀዋል። አሁን ነፃ ወጥተው በርካታ ቁሳዊ ንብረቶች አካብተዋል። ከእነዚህ ንብረቶች ውስጥ የተወሰነውን ስለ መስጠት ያላቸው ስሜት ምን ይሆን? ለፍተው ያገኙት እንደሆነና ለራሳቸው የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ንጹሕ አምልኮን ለመደገፍ የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ መዋጮ ያደረጉት እያቅማሙ ወይም እየሰሰቱ አልነበረም! በእጃቸው ያሉትን ቁሳዊ ነገሮች እንዲያገኙ ያስቻላቸው ይሖዋ መሆኑን አልዘነጉም። በመሆኑም የነበራቸውን ብር፣ ወርቅና ከብት በልግስና ሰጥተዋል። ‘ልባቸው ፈቅዶ ነበር።’ ‘ልባቸው አነሣስቷቸዋል፣ መንፈሳቸውም እሺ አሰኝቷቸዋል።’ በእርግጥም “ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው” አምጥተው ነበር።​—⁠ዘጸአት 25:​1-9፤ 35:​4-9, 20-29፤ 36:​3-7

በበጎ ፈቃድ መስጠት

የሰጪውን ልግስና ሁልጊዜ በስጦታው መጠን መመዘን አይቻልም። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች በቤተ መቅደሱ መዝገብ ውስጥ መዋጮ ሲያደርጉ ይመለከት ነበር። ባለጸጋ የሆኑ ሰዎች ብዙ ገንዘብ ያዋጡ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ አንዲት ድሀ መበለት አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ሳንቲሞች ስታዋጣ በማየቱ ተደነቀ። “ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች . . . ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች” ሲል ተናገረ።​—⁠ሉቃስ 21:​1-4፤ ማርቆስ 12:​41-44

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሐሳብ ከኢየሱስ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ ነበር። በችግር ላይ ላሉ የእምነት ጓደኞቻቸው መዋጮ ማድረግን በተመለከተ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “በጎ ፈቃድ ቢኖር፣ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 8:​12) አዎን፣ መዋጮዎች ለፉክክር ወይም አንዱን ከሌላው ለማበላለጥ የሚደረጉ ነገሮች አይደሉም። አንድ ሰው መስጠት የሚችለው እንደ አቅሙ ሲሆን ይሖዋም የለጋስነት መንፈስ ያስደስተዋል።

ምንም እንኳ ማንኛውም ሰው የሁሉ ነገር ባለቤት የሆነውን ይሖዋን ማበልጸግ ባይችልም አምላኪዎቹ መዋጮ የማድረግ መብት ማግኘታቸው ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲገልጹ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። (1 ዜና መዋዕል 29:​14-17) ለታይታ ወይም ራስ ወዳድነት ለታከለባቸው ሌሎች ዓላማዎች ሳይሆን በትክክለኛ ዝንባሌ ተገፋፍቶ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የሚሰጥ መዋጮ ደስታ አልፎ ተርፎም የአምላክን በረከት ያስገኛል። (ማቴዎስ 6:​1-4) ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሏል። (ሥራ 20:​35) ጉልበታችንን በይሖዋ አገልግሎት ላይ በማዋል እንዲሁም እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍና ችግር ላይ የወደቁትን ለመርዳት ከቁሳዊ ንብረታችን ውስጥ የተወሰነውን መዋጮ በማድረግ መስጠት ከሚያስገኘው ደስታ ተካፋዮች መሆን እንችላለን።​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:​1, 2

በዛሬው ጊዜ በበጎ ፈቃድ መስጠት

በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ‘በመንግሥቱ ወንጌል’ ስብከት በታየው እድገት ተደስተዋል። (ማቴዎስ 24:​14) በ20ኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ አሥርተ ዓመት ከ3, 000, 000 በላይ ሰዎች ለይሖዋ አምላክ የገቡትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት ያሳዩ ሲሆን ወደ 30, 000 የሚጠጉ አዳዲስ ጉባኤዎችም ተቋቁመዋል። አዎን፣ በዛሬው ጊዜ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የተመሠረቱት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ነው! በአብዛኛው ይህ ጭማሪ ሊገኝ የቻለው ወደ ጎረቤቶቻቸው በመሄድ ስለ ይሖዋ ዓላማ ለመንገር ሲሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሰዉ ቅን ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ባሳዩት ትጋት የተሞላበት ጥረት አማካኝነት ነው። ከዚህ ጭማሪ ውስጥ የተወሰነው ሊገኝ የቻለው ሚስዮናውያን በመንግሥቱ ስብከት ሥራ እርዳታ ለማበርከት ሲሉ ቤታቸውን ትተው ርቀው ወደሚገኙ አገሮች ሄደው በማገልገላቸው ነው። በዚህ ጭማሪ ሳቢያ አዳዲስ ወረዳዎች የተቋቋሙ ሲሆን ይህ ደግሞ አዳዲስ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እንዲሾሙ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ለስብከትና ለግል ጥናት የሚያገለግሉ ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሶች አስፈልገዋል። ተጨማሪ ጽሑፎች መታተማቸው አስፈላጊ ሆኗል። እንዲሁም በበርካታ አገሮች ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ማስፋፋት ወይም በሌሎች ትልልቅ ሕንፃዎች መቀየር ግድ ሆኗል። እነዚህ ሁሉ አስፈላጊ ነገሮች ሊሟሉ የቻሉት የይሖዋ ሕዝቦች በፈቃደኝነት በሚያደርጓቸው መዋጮዎች አማካኝነት ነው።

የመንግሥት አዳራሾች እጥረት

ከይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የመንግሥት አዳራሾች እጥረት ተከስቷል። በ2000 መጀመሪያ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደጠቆሙት የገንዘብ እጥረት ባለባቸው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ከ11, 000 በላይ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። በአንጎላ ያለውን ሁኔታ እንመልከት። በዚህች አገር ለበርካታ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ቢካሄድም በመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ረገድ በአማካይ በዓመት 10 በመቶ ገደማ ጭማሪ ይታያል። ሆኖም በዚህች ሰፊ አፍሪካዊት አገር ከሚገኙት 675 ጉባኤዎች መካከል አብዛኞቹ የሚሰበሰቡት ሜዳ ላይ ነው። በዚህች አገር ውስጥ 22 የመንግሥት አዳራሾች ብቻ ያሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ጣራ ያላቸው 12 ብቻ ናቸው።

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል። በዋና ከተማው በኪንሻሳ ወደ 300 የሚሆኑ ጉባኤዎች ቢኖሩም እንኳ በከተማዋ ያሉት የመንግሥት አዳራሾች አሥር ብቻ ናቸው። በመላ አገሪቱ ከ1, 500 በላይ የመንግሥት አዳራሾች በአስቸኳይ ያስፈልጋሉ። የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ፈጣን እድገት በማድረጋቸው ሩስያና ዩክሬይን በድምሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች እንደሚያስፈልጓቸው ሪፖርት አድርገዋል። በላቲን አሜሪካ ያለው ፈጣን እድገት በብራዚል ጎልቶ ይታያል። በዚህች አገር ከግማሽ ሚልዮን በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ሲሆን ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች በእጅጉ ያስፈልጋሉ።

በእነዚህ አገሮች ያለውን ችግር ለመቅረፍ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾችን በፍጥነት ለመገንባት የሚያስችል ፕሮግራም በሥራ አውለዋል። ፕሮግራሙ የሚካሄደው ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በሚያደርገው ልግስና የተሞላበት መዋጮ ነው። ይህም በጣም ድሀ የሆኑት ጉባኤዎች እንኳ ሳይቀር ተስማሚ የአምልኮ ቦታ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።

በጥንቱ የእስራኤል ዘመን እንደታየው ሁሉ ቅን ክርስቲያኖች ‘ይሖዋን ከሀብታቸው ስለሚያከብሩ’ ብዙ ነገር ማከናወን ይቻላል። (ምሳሌ 3:​9, 10) በዚህ አጋጣሚ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል በፈቃደኝነት በሚደረገው ልግስና ለመካፈል ልባቸው ላነሳሳቸው ሁሉ የሚሰማውን ጥልቅ ምስጋና ለመግለጽ ይወድዳል። እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄደውን የመንግሥቱን ሥራ ፍላጎቶች እንዲደግፉ የይሖዋ መንፈስ የሕዝቡን ልብ ማነሳሳቱን እንደሚቀጥል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው እድገት እየቀጠለ ሲሄድ ጉልበታችንን፣ ጊዜያችንንና ሀብታችንን በመስጠት ረገድ ደስተኞችና ፈቃደኞች መሆናችንን ለማሳየት ምንጊዜም ያሉትን አጋጣሚዎች ሁሉ እንጠቀም። በዚህ መንገድ እንዲህ ዓይነቱ የለጋስነት መንፈስ የሚያስገኘውን እውነተኛ ደስታ እንቅመስ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“በአግባቡ ተጠቀሙበት!”

“የአሥር ዓመት ልጅ ነኝ። ይህን ገንዘብ የላኩላችሁ መጽሐፍ ለማተም የሚሆን ወረቀትም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ነገር መግዛት እንድትችሉ ነው።”​—⁠ሲንዲ

“ተጨማሪ መጻሕፍት እንድታዘጋጁልን ይህን ገንዘብ ልልክላችሁ እወዳለሁ። አባቴን በመርዳት ያጠራቀምኩት ገንዘብ ነው። ስለዚህ በአግባቡ ተጠቀሙበት!”​—⁠የሰባት ዓመቷ ፓም

“በተከሰተው ዓውሎ ነፋስ በጣም አዝኛለሁ። ከባድ ጉዳት እንዳልደረሰባችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ያጠራቀምኩትን ገንዘብ [2 የአሜሪካ ዶላር] በሙሉ ልኬላችኋለሁ።”​—⁠የአራት ዓመቷ አሊሰን

“ስሜ ሩዲ ይባላል፤ የ11 ዓመት ልጅ ነኝ። ታናሽ ወንድሜ ራልፍ ስድስት ዓመቱ ነው። እህቴ ጁዲት ደግሞ ሁለት ዓመት ተኩል ሆኗታል። [በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች] የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ለመርዳት ብለን ከሚሰጠን የኪስ ገንዘብ ውስጥ ለሦስት ወር ያህል ስናጠራቅም ቆይተናል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ያጠራቀምነውን 20 ዶላር ልከንላችኋል።”

“ወንድሞች [በዓውሎ ነፋስ በመመታታቸው] አዝኛለሁ። ከአባቴ ጋር እየሠራሁ ያገኘሁት 17 ዶላር አለኝ። ይህን ገንዘብ ለዚህ ዓላማ አውሉት የምለው ነገር የለኝም። እናንተ እንዳስፈላጊነቱ ተጠቀሙበት።”​—⁠የስምንት ዓመቱ ማክሌን

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥንል]

አንዳንዶች ለዓለም አቀፉ ሥራ

መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች

ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:​14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአካባቢው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።

በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎች በቀጥታ Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገርህ ወደሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም በእርዳታ መስጠት ይቻላል። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።

ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት

አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ መልሶ ሊያገኝ የሚችልበትን ልዩ ዝግጅት በማድረግ ለማኅበሩ ሊሰጥ ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።

በእቅድ የሚደረግ ስጦታ

ለማኅበሩ በቀጥታ የገንዘብ ስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም መስ​ጠት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ:-

ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።

የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።

አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችና ቦንዶች እንዳለ በስጦታ መልክ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ መስጠት ይቻላል።

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች:- ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዳለ በስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ መስጠት ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ በፊት ከማኅበሩ ጋር መገናኘት ይኖርበታል።

ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት።

“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል በትንሹም ቢሆን እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። ማኅበሩን በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደጎም ለሚፈልጉ ግለ​ሰቦች ማኅበሩ የዓለም አቀፉን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ አዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ማኅበሩ ለቀረቡለት ብዛት ያላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ነው። በተጨማሪም ብሮሹሩ ከንብረት፣ ከገንዘብና ከታክስ ጋር በተያያዘ እቅድ ማውጣትን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዘ ነው። ከዚህም ሌላ ብሮሹሩ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩና በአሁኑ ጊዜ ለማኅበሩ ልዩ ስጦታ ለመስጠት እቅድ ያላቸው ወይም በሚሞቱበት ጊዜ ውርስ ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች የቤተሰባቸውና የግል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ጠቃሚና ውጤታማ ዘዴ ለመምረጥ እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የዚህን ብሮሹር አንድ ቅጂ ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ ለሚከታተለው ቢሮ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል።

ይህን ብሮሹር በማንበብና በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ በሚከታተለው ቢሮ ውስጥ ከሚሠሩት ወንድሞች ምክር በመጠየቅ ብዙዎች ማኅበሩን ለመርዳት ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ ቅናሽ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ችለዋል። በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለው ቢሮ ከእነዚህ ዝግጅቶች ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሰነዶች ሊነገረውና የሰነዶቹ ቅጂ ሊላክለት ይገባል። ከእነዚህ በእቅድ የሚደረጉ ስጦታዎች በአንዱ ለመካፈል የሚፈልጉ ከታች ያለውን አድራሻ ተጠቅመው ወይም በአገራቸው ወዳለው የማኅበሩ ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል ማሳወቅ አለባቸው።

CHARITABLE PLANNING OFFICE

Watch Tower Bible and Tract Society of

Pennsylvania

100 Watchtower Drive,

Patterson, New York 12563-9204

Telephone: (845) 306-0707