በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጸለይ የሚፈይደው ነገር አለን?

መጸለይ የሚፈይደው ነገር አለን?

መጸለይ የሚፈይደው ነገር አለን?

ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ቢያንስ በሆነ ወቅት ላይ መጸለይ እንዳለበት እንዲሰማው የሚያደርግ ሁኔታ ሊገጥመው ይችላል። እርግጥ፣ በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ማለት ይቻላል ከልባቸው አጥብቀው ይጸልያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የቡድሃ እምነት ተከታይ የሆነ ሰው “እምነቴን በአሚዳ ቡድሃ ላይ እጥላለሁ” የሚለውን ጸሎት በቀኑ ውስጥ በሺህ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ይደጋግም ይሆናል።

በምድር ዙሪያ እየተባባሱ ካሉት ችግሮች አንጻር ሰዎች በጸሎት ማግኘት የሚፈልጉት ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ሁሉ ጸሎቶችስ የፈየዱት ነገር አለን? ብሎ መጠየቁ ምክንያታዊ ነው።

ሰዎች የሚጸልዩት ለምንድን ነው?

ብዙ ምሥራቃውያን ወደ ቀድሞ አባቶቻቸውና ሺንቶ ወይም ታኦ ወደተባሉት አምላኮች ይጸልያሉ። ይህንንም የሚያደርጉት የትምህርት ቤት ፈተናዎችን ለማለፍ፣ ጥሩ ምርት ለመሰብሰብ ወይም በሽታ እንዳይዛቸው ለመከላከል ስለሚፈልጉ ነው። የቡድሃ እምነት ተከታዮች በገዛ ጥረታቸው የእውቀት ብርሃን ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። ሂንዱዎች ደግሞ እውቀት፣ ሃብትና ጥበቃ ለማግኘት ሲሉ አብልጠው ወደሚወዷቸው ወንድና ሴት አማልክት ከልባቸው ይጸልያሉ።

አንዳንድ ካቶሊኮች የሰውን ዘር ለመጥቀም በማሰብ መላ ሕይወታቸውን በገዳማት ውስጥ በመነኩሴነት እየጸለዩ ያሳልፋሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ካቶሊኮች ደግሞ ምናልባትም ባለ ዶቃ መቁጠሪያዎችን ተጠቅመው በቃል የተጠኑ ጸሎቶችን ለማርያም በማቅረብ ሞገሷን ለማግኘት ይለምናሉ። በሩቅ ምሥራቅ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ጸሎት ተጽፎ የተቀመጠባቸውን እንደ ሙዳይ ያሉ ነገሮች ይጠቀማሉ። ፕሮቴስታንቶች በራሳቸው ቃላት ስሜታቸውን ለአምላክ የሚገልጹ ቢሆንም በጌታ ጸሎት ውስጥ የሚገኙትን ቃላት ይደጋግሟቸዋል። ብዙ አይሁዳውያን ደግሞ የመቅደሱን እንደገና መገንባት እንዲሁም ብልጽግናና ሰላም የሚሰፍንበትን አዲስ ዘመን መምጣት ተስፋ በማድረግ በኢየሩሳሌም ምዕራባዊ ቅጥር ተገኝተው ጸሎት ለማድረስ ረዥም ጉዞ ያደርጋሉ።

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጸሎት ቢተጉም የሰው ዘር እየተባባሰ በመጣ ድህነት፣ በአደገኛ ሱሶች፣ በቤተሰብ መፈራረስ፣ በወንጀልና በጦርነት እየታመሰ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ምናልባት ሁሉም ሰዎች በትክክለኛው መንገድ ስላልጸለዩ ይሆን? ደግሞስ በእርግጥ ጸሎቶችን የሚሰማ አካል ይኖር ይሆን?

ጸሎቶችን የሚሰማ አካል አለን?

ጸሎቶች ተሰሚነት ካላገኙ ምንም የሚፈይዱት ነገር አይኖርም። አንድ ሰው ሲጸልይ በማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ያለ አንድ አካል ይሰማኛል ብሎ እንደሚያምን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ጸሎቶች የሚተላለፉት በድምፅ ሞገዶች አማካኝነት አይደለም። ብዙ ሰዎች የሚጸልየውን ሰው ሐሳብ እንኳ ማወቅ የሚችል አንድ አካል እንዳለ ያምናሉ። ያ አካል ማን ሊሆን ይችላል?

የአእምሮአችን አንጎለ አእምረት ልሕፅ [cerebral cortex] በተገነባባቸው በቢልዮን የሚቆጠሩ ሕዋሰ ነርቮች ውስጥ ሐሳብ የሚፈልቀው እንዴት እንደሆነ ለተመራማሪዎችም እንቆቅልሽ የሆነ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አእምሮን የነደፈው አካል እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች ማንበብ ይችላል ቢባል ምክንያታዊ ነው። ይህ አካል ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (መዝሙር 83:​18፤ ራእይ 4:​11) ጸሎቶች መቅረብ ያለባቸው ለእርሱ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ጸሎቶች በሙሉ ይሰማልን?

ሁሉም ጸሎቶች ተሰሚነት አላቸውን?

የጥንቷ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት የጸሎት ሰው ነበር። መዝሙራዊው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት “ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 65:​2) ይሖዋ በሺህ በሚቆጠሩ የሰው ዘር ቋንቋዎች የሚቀርቡትን ጸሎቶች የመስማት ችሎታ አለው። የትኛውም የሰው አእምሮ ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ ማስተናገድ አለመቻሉ አምላክ ተቀባይነት ባለው መንገድ ወደ እርሱ የሚጸልዩትን ሰዎች በሙሉ መስማት አይችልም ማለት አይደለም።

ይሁን እንጂ ሌላው የጸሎት ሰው የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ጸሎቶች አምላክን እንደማያስደስቱ ገልጿል። ኢየሱስ በወቅቱ በብዙዎች ዘንድ ይደረግ የነበረውን በቃል የተጠኑ ጸሎቶች የመድገም ልማድ አስመልክቶ የተናገረውን ልብ በል። በካቶሊኮች የተዘጋጀው ጀሩሳሌም ባይብል ጥቅሱን እንደሚከተለው ሲል ተርጉሞታል:- “አረማውያን በቃላት ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትለፍልፉ።” (ማቴዎስ 6:​7) ይሖዋ ውስጣዊ ስሜታችንን የማይገልጹ ጸሎቶችን ያዳምጣል ብለን መጠበቅ አንችልም።

አንዳንድ ጸሎቶች አምላክን የማያስደስቱት ለምን እንደሆነ ሲገልጽ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዲህ ይላል:- “ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት።” (ምሳሌ 28:​9) ሌላው ምሳሌ ደግሞ “እግዚአብሔር ከኀጥኣን ይርቃል፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 15:​29) የጥንቷ ይሁዳ መሪዎች ከባድ ኃጢአት በተሸከሙ ጊዜ ይሖዋ “እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፣ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል” ብሏቸው ነበር።​—⁠ኢሳይያስ 1:​1, 15

ሐዋርያው ጴጥሮስ ጸሎቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኙ የሚያደርጋቸውን ተጨማሪ ነገር ጠቅሷል። “እናንተ ባሎች ሆይ፣ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል፣ አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።” (1 ጴጥሮስ 3:​7) እንዲህ ያለውን ምክር ችላ የሚል ሰው የሚያቀርበው ጸሎት ከጣሪያው አያልፍም!

በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ጸሎቶች ተሰሚነት እንዲኖራቸው ከተፈለገ መሟላት የሚገባቸው ብቃቶች አሉ። ይሁን እንጂ ወደ አምላክ ከሚጸልዩት ሰዎች መካከል ብዙዎች አምላክ ከእኛ የሚፈልገውን ነገር ስለማድረግ ምንም ግድ የላቸውም። በጸሎት መትጋቱ ብቻ የተሻለ ዓለም ያላስገኘበትም ምክንያት ይኸው ነው።

ታዲያ አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ልናሟላቸው የሚገቡን ብቃቶች ምንድን ናቸው? የዚህ ጥያቄ መልስ ጸሎት ከምናቀርብበት ዓላማ ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው። በእርግጥም ደግሞ ጸሎቶች ፋይዳ ይኑራቸው አይኑራቸው ለማወቅ ከፈለግን ዓላማቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። ይሖዋ ከእርሱ ጋር የመነጋገር አጋጣሚ የሰጠን ለምንድን ነው?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

G.P.O., Jerusalem