በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጸለይ ያለብህ ለምንድን ነው?

መጸለይ ያለብህ ለምንድን ነው?

መጸለይ ያለብህ ለምንድን ነው?

“ትለምናላችሁ . . . በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም . . . ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል።” (ያዕቆብ 4:​3, 8) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው ያዕቆብ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት የምንጸልይባቸውን ምክንያቶች እንድንመረምር ይገፋፉን ይሆናል።

ጸሎት ምን ነገር እንደሚያስፈልገን ለአምላክ የምንነግርበት መንገድ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና።” ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል” ሲልም ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:​8፤ 7:​7) ስለዚህ ይሖዋ እንደሚያስፈልገን ሆኖ የተሰማንን ነገር እንድንነግረው ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ጸሎት ሌላም ነገር ይጨምራል።

እውነተኛ ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩት አንድ ነገር ሲፈልጉ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንዳቸው ለሌላው የሚያስቡ ሲሆን ስሜታቸውን ሲገላለጹ ወዳጅነታቸው እየተጠናከረ ይሄዳል። በተመሳሳይም ጸሎት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከመጠየቅ የበለጠም ዓላማ አለው። ለይሖዋ ያለንን ከልብ የመነጨ አምልኮታዊ ፍቅር በመግለጽ ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና የማጠናከር አጋጣሚ ይሰጠናል።

አዎን፣ አምላክ ወደ እርሱ መቅረብ እንድንችል የጸሎት መብት ሰጥቶናል። ወደ አምላክ መቅረብ የምንችለው በቃል የተጠኑ ጸሎቶችን በመድገም ሳይሆን ውስጣዊ ስሜታችንን በመግለጽ ብቻ ነው። ከይሖዋ ጋር በጸሎት መነጋገር እንዴት ያስደስታል! በተጨማሪም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው” ይላል።​—⁠ምሳሌ 15:​8

መዝሙራዊው አሳፍ “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 73:​28) ይሁን እንጂ ወደ አምላክ ለመቅረብ ከመጸለይ የበለጠ ነገር ማድረግ አለብን። ቀጥሎ የቀረበው ታሪክ ይህንን የሚያረጋግጠው እንዴት እንደሆነ ተመልከት:-

“ከ[ኢየሱስ] ደቀ መዛሙር[ት] አንዱ:- ጌታ ሆይ . . . እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው።” ኢየሱስም “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ” ሲል መለሰ:- “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ።” (ሉቃስ 11:​1, 2) በመጀመሪያ የአምላክ ስም ማን እንደሆነና እንዴት እንደሚቀደስ ሳናውቅ እንደዚያ ብለን ትርጉም ባለው መንገድ መጸለይ እንችላለንን? የአምላክን መንግሥት ምንነት ሳንረዳ ከኢየሱስ ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ መጸለይ እንችላለንን? መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ከመረመርን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንችላለን። በዚህ መንገድ ያገኘነው እውቀትም አምላክን እንድናውቅና መንገዶቹን እንድናስተውል ይረዳናል። ከዚህም በላይ ከይሖዋ አምላክ ጋር መተዋወቃችን ይበልጥ ወደ እርሱ እንደቀረብንና ለእርሱ እንዳደርን ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል። ይህ ደግሞ በጸሎት አማካኝነት ከእርሱ ጋር ይበልጥ በነፃነት እንድንነጋገር የሚያደርግ ነው።

ጸሎት ለችግሮች መፍትሄ ሊያስገኝ ይችላል

ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረታችን ችግሮችን ለመፍታት ያስችለናል። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ከዚህ በታች ከቀረበው ከእያንዳንዱ ታሪክ ተመልከት። ይጸልዩ የነበሩት ሰዎች ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ዝምድና ማጠንከር እንደቻሉ የሚያሳዩ ናቸው።

በብራዚል የምትኖረው ማሪያ አምላክ እንዲረዳት ጸለየች። ከዚህ ቀደም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን የሥነ ምግባር መስፈርቶች በመቃወም ማመፅ ፈልጋ የነበረ ሲሆን ለዚህ በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገው በኅብረተሰቡ ውስጥ ያየችው ግብዝነት ነበር። ባሏን፣ ልጆቿንና ቤቷን ሳይቀር ጥላ ሄደች። አደገኛ ዕፆችን መውሰድ ጀመረች። ይሁን እንጂ ደስታ ባለማግኘቷ ልቧን በማፍሰስ አምላክ እንዲረዳት ጸለየች።

ብዙም ሳይቆይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ማሪያን አነጋገሯትና መለኮታዊ መመሪያ መቀበል ያለውን ጥቅም የሚያብራራ አንድ የመጠበቂያ ግንብ እትም ሰጧት። ያነበበችው ነገር ልቧን ስለነካው በዚያው እለት ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። ይህም ውሎ አድሮ ወደ ቤተሰቧ እንድትመለስ ረዳት። ስለ ይሖዋ መማሯን ስትቀጥል ለእርሱ ያላትን ፍቅር በተግባር ማሳየት ፈለገች። ማሪያ “ባሕሪዬን ለማሻሻል ስል ለውጦች አደረግሁ” በማለት ትናገራለች። “መጀመሪያ ላይ ባለቤቴና ቤተሰቦቼ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ቢቃወሙም የማደርገውን ለውጥ ሲመለከቱ ግን ያበረታቱኝ ጀመር።” ከጊዜ በኋላ ማሪያ ጸሎት ሰሚ የሆነውን አምላክ ለማገልገል ራሷን ለእርሱ ወሰነች።

ሆሴ ቆንጆ ሚስትና ቦሊቪያ ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያለው ንግድ ቢኖረውም ደስተኛ አልነበረም። ምንዝር በመፈጸሙ ሚስቱ ጥላው ሄደች። ከመጠን በላይ መጠጣት ሲጀምር ዋጋ ቢስ እንደሆነ ተሰማው። ሆሴ “አምላክን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንዳለብኝ በመጠየቅ ከልቤ መጸለይ ጀመርኩ” በማለት ይናገራል። “ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ቦታዬ መጥተው ነጻ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድጀምር ግብዣ አቀረቡልኝ፤ እኔ ግን አባረርኳቸው። ሦስት ጊዜ እንደዚያ አድርጌያለሁ። ለእርዳታ በጸለይኩ ቁጥር ግን ምሥክሮቹ ይመጣሉ። በመጨረሻም በሚቀጥለው ጊዜ ሲመጡ ለማዳመጥ ወሰንኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ስላነበብኩ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ። ሆኖም ምሥክሮቹ ሁልጊዜ የሚያረካ መልስ ይሰጡኝ ነበር። ስለ ይሖዋ መማሬ ለሕይወቴ አዲስ ትርጉም ሰጠው። ከምሥክሮቹ መካከል ያገኘኋቸው ጓደኞቼ በጣም የሚያበረታቱ ምሳሌዎች ነበሩ! የሴት ጓደኛዬንና የመጠጥ ጓደኞቼን ተውኳቸው። ብዙም ሳይቆይ ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር አብሬ መኖር ጀመርኩ። ከዚያም በ1999 መጀመሪያ ላይ ተጠመቅሁ።”

በኢጣሊያ የምትኖረው ታማራ በትዳሯ ውስጥ ችግር ተከስቶ ስለነበር ጥበብ ለማግኘት ጸለየች። ታማራ ተደብድባ ከቤት የወጣችው ገና በ14 ዓመቷ ስለነበር የጠበኝነት ዝንባሌ አዳበረች። እንዲህ ብላለች:- “መጽሐፍ ቅዱስ አገኘሁና ማንበብ ጀመርኩ። ሆኖም አንድ ምሽት ላይ ‘ጥበብን ማግኘት የተቀበረ እንቁ እንደማግኘት’ ያህል እንደሆነ አነበብኩ። በመሆኑም እንዲህ ያለውን ጥበብ ለማግኘት ጸለይኩ። (ምሳሌ 2:​1-6) በሚቀጥለው ቀን ጠዋት የይሖዋ ምሥክሮች አነጋገሩኝ። ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ብጀምርም የተማርኩትን በተግባር ለማዋል የተወሰነ ጊዜ ወሰደብኝ። በመጨረሻም ክርስቲያናዊውን የሕይወት መንገድ ለመከተል ወስኜ ተጠመቅኩ። አሁን ከባሌ ጋር ሆኜ ሌሎች ሰዎች ከአምላክ ጥበብ እንዲጠቀሙ በመርዳት ላይ ነኝ።”

ቤትሪስ ቬኔዝዌላ ካራካስ ውስጥ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው ማኅበረሰብ ክፍል ነበረች። ይሁን እንጂ ባሏ ስለፈታት በጭንቀት ተውጣ ነበር። በጣም ተስፋ ቆርጣ ስለነበር ለብዙ ሰዓታት ያለማቋረጥ ጸለየች። በሚቀጥለው ቀን ጧት የበሯ ደወል ጮኸ። ተበሳጭታ በበሩ ማሾለቂያ ስትመለከት ሁለት ቦርሳ የያዙ ሰዎች ቆመዋል። ቤት እንደሌለች ለማስመሰል ሞከረች። ሆኖም ባልና ሚስቱ ከመሄዳቸው በፊት የስብሰባ ጥሪ ወረቀት በበሩ ሥር ላኩ። ወረቀቱ “መጽሐፍ ቅዱስህን እወቅ” የሚል ነበር። አመጣጣቸው ምናልባት ባለፈው ምሽት ካቀረበችው ጸሎት ጋር የተያያዘ ይሆን? ተመልሰው እንዲመጡ ጠራቻቸው። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረችና በኋላም ተጠመቀች። በመጨረሻም ቤትሪስ ደስተኛ ሆነች። አሁን ሌሎች ሰዎች ደስታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ በማስተማር ላይ ነች።

ካርሜን ከድህነት ጋር በምታደርገው ትንቅንቅ አምላክ እንዲረዳት ጸለየች። ራፋኤል የሚባል ጠጪ ባልና አሥር ልጆች አሏት። ካርሜን “ልብስ በማጠብ ገንዘብ ለማግኘት ሞከርኩ” በማለት ትናገራለች። ይሁን እንጂ የራፋኤል የጠጪነት ልማድ ተባባሰ። “ባሌ መለወጥ የጀመረው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስንጀምር ነበር። ይሖዋ በቅርቡ ድህነትንና ጭቆናን ከምድር ገጽ እንደሚያጠፋ የሚናገረውን የመንግሥት ተስፋ ተማርን። ለአምላክ ያቀረብኳቸው ጸሎቶች በመጨረሻ መልስ አገኙ!” ራፋኤል ስለ ይሖዋ መንገዶች መማሩ መጠጣቱን እንዲያቆምና “አዲሱን ሰው” እንዲለብስ ረድቶታል። (ኤፌሶን 4:​24) እርሱና ቤተሰቡ ኑሮአቸውን ማሻሻል ችለዋል። “ሃብታሞች ባንሆንም እንዲሁም የራሳችን የሆነ ቤት ባይኖረንም ለሕይወት የሚያስፈልጉን ነገሮች ስላሉን ደስተኞች ነን።”

ሁሉም ጸሎቶች መልስ የሚያገኙበት ጊዜ

እነዚህ ሰዎች መጸለያቸው የፈየደው ነገር አለን? እንዴታ! በአብዛኞቹ ሁኔታዎች ጸሎታቸው የተመለሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲቀርቡ ሲረዳቸው መሆኑን አስተውለሃል?​—⁠ሥራ 9:​11

እንግዲያው እንድንጸልይ የሚያደርጉን በቂ ምክንያቶች አሉ። የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፈቃዱ በምድር እንዲሆን የሚቀርበው ጸሎት በቅርቡ መልስ ያገኛል። (ማቴዎስ 6:​10) አምላክ ምድርን እርሱን ከሚቃወሙት ሰዎች ካጸዳ በኋላ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:​9) ከዚያ በኋላ ይሖዋን የሚወዱ ሁሉ “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ይደርሳሉ። በእርግጥም ጸሎታቸው መልስ ያገኛል።​—⁠ሮሜ 8:​18-21

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጸለይ ያለብን ለምን እንደሆነ ታውቃለህ ?