በፔሩ አልቲፕላኖ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ
ከሚያምኑት ወገን ነን
በፔሩ አልቲፕላኖ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ
አልቲፕላኖ ቦሊቪያንና ፔሩን በሚያገናኛቸው ምሥራቃዊና ምዕራባዊ የኤንዲስ የተራራ ሰንሰለቶች መካከል ይገኛል። የስሙ ትርጉም “ከፍ ያለ ሜዳ” ወይም “አምባ” ማለት ሲሆን አብዛኛው የቦታው ክፍል የሚገኘው ቦሊቪያ ውስጥ ነው።
አልቲፕላኖ 100 ኪሎ ሜትር ስፋትና 1,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን አማካይ ከፍታው ደግሞ 3,700 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ ነው። በባሕር ዳርቻ ላይ ከሚገኘው ከፔሩ ዋና ከተማ ከሊማ በሚነሳ አውሮፕላን ተሳፍረህ ስትበርር ወደዚህ አካባቢ የምትደርሰው በበረዶ የተሸፈነውን የኤል ሚስቲን እሳተ ገሞራ አልፈህ ነው። ይህ እሳተ ገሞራ እስከ 5, 822 ሜትር ከፍታ ያለውና ጫፉ በደመና የተሸፈነ ነው። ራቅ ብሎ ደግሞ ከ6, 000 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸውና አናታቸው በበረዶ የተሸፈነ የኔባዶ፣ የኤምፔቶና የኔባዶ ኮሮፑኔ ተራሮች ይታያሉ። ወዲያው እይታችንን የሚሰርቀው የተንጣለለ አምባ የደቡባዊው ፔሩ አልቲፕላኖ ነው።
የፔሩ አልቲፕላኖ ዋና ከተማ በዓለማችን ከፍተኛ የውኃ ላይ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው ሐይቆች አንዱ ከሆነው ከቲቲካካ ሐይቅ ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ ላይ የሚገኘው ፑኖ ነው። ክልሉ ከሦስት ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ከፍታ ያለው በመሆኑ ጎብኚዎች ከስሱ አየር ጋር ራሳቸውን ለማላመድ ጥቂት ጊዜ ይወስድባቸዋል። ከቲቲካካ ሐይቅ አጠገብ የኬቹዋና የአይማራ ሕንዳውያን የሚገኙ ሲሆን የሚያማምሩ ቀያይ፣ አረንጓዴ ወይም ሰማያዊ ልብሶቻቸውን ለብሰው በቼክሬስ ወይም በትንንሽ እርሻዎቻቸው ላይ ሲሠሩ ይታያሉ። የፔሩ ዋነኛ የመነጋገሪያ ቋንቋ ስፓኒሽ ቢሆንም ኬቹዋና አይማራ ቋንቋዎችም በአልቲፕላኖ ይነገራሉ።
የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት መምራት
ትሑትና ጠንካራ ሠራተኞች የሆኑት የኬቹዋና አይማራ ቋንቋ ተናጋሪዎች በቅርቡ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አግኝተዋል። ይህ ውጤት በአብዛኛው ሊገኝ የቻለው ልዩ አቅኚዎች ሆነው የሚያገለግሉ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ያደረጉትን ቅንዓት የተሞላበት ጥረት ይሖዋ አትረፍርፎ በመባረኩ ነው።
ለምሳሌ ያህል ሆሴ እና ሲልቪያ የተባሉ ሁለት ልዩ አቅኚዎች ከቲቲካካ ሐይቅ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ፑቲና የተባለ ከተማ ተመድበው ነበር። በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሲልቪያ 16 ጥናቶች ስትመራ ሆሴ ደግሞ 14 ጥናቶች ይመራ ነበር። በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ የጉባኤው አስፋፊዎች ቁጥር ከ23 ወደ 41 ከፍ አለ። በመሃሉ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከ48 ወደ 132 አደገ።
ሆሴ እንዲህ ይላል:- “በእነዚህ ርቀው በሚኖሩ ማኀበረሰቦች መካከል የጉባኤ ስብሰባዎች ማድረግ ስንጀምር በሕዝባዊ ስብሰባና በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት መጀመራችን ተግባራዊ ሆኖ አግኝተነዋል። ይህም ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲጀምሩ ቀላል ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።”
በሥጋ እህትማማች የሆኑ ሁለት እህቶች ምሥራቹን ከፑቲና 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው የሙንዬኒ ማኅበረሰብ ለማድረስ የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። አንደኛዋ እህት አቅኚ ነች። እዚያም ሉስዮ የተባለ አንድ ዓይነ ስውር ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመሩ። a ሉስዮ በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ የካቶሊክ ሚስዮናዊና የመንደሩ አለቃ የሆነውን ሚጌል የተባለ ወንድሙን በጥናቱ ላይ እንዲገኝ ጋበዘው። አንድ ጓደኛው ሚጌልን በየሳምንቱ ወደ ሙንዬኒ የምትሄደው ለምንድን ነው ብሎ ሲጠይቀው ሚጌል ስለ ይሖዋና ስለ ቃሉ ለመማር ብሎ መለሰለት። በዚህ ጊዜ “ለምን መጽሐፍ ቅዱስን እዚሁ አናጠናም?” የሚል ጥያቄ ተነሳ። በሚጌል መንደር ውስጥ ያሉት ሰዎች ፍላጎት በማሳየታቸው ምሥክሮቹ ወዲያውኑ የጉባኤ ስብሰባዎች ለማድረግ ዝግጅት አደረጉ።
ሚጌል የተማረውን ለሌሎች ማካፈል ጀመረ። ሆኖም የካቶሊክ ሚስዮናዊ እና የመንደሩ ምክትል አለቃ በመሆን የነበረውስ ኃላፊነት? በመንደሩ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተከናወነው ስብሰባ ላይ የካቶሊክ ሚስዮናዊ ሆኖ ማገልገሉን በፈቃዱ እንዳቆመ ተናገረ። ሌላ ሰው ይሾም ይሆን? ከአድማጮች መካከል አንዱ “እውነትን እየተማርን ነው። ሌላ ሚስዮናዊ ለምን ያስፈልገናል?” ሲል ተናገረ። ከይሖዋ ምሥክሮች የሚማሯቸውን ነገሮች በተመለከተ መናገሩ ነበር። ሌላው ሰው ደግሞ እንዲህ
በማለት አከለ:- “ብቻህን ለመልቀቅ ባቀረብከው ሐሳብ አንስማማም። ለምን ሁላችንም ለቅቀን አንወጣም?” ከዚያም በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ በአንድ ድምፅ “ሁላችንም ለቅቀናል!” በማለት ጮኹ።ከዚያ በኋላ በመንደሩ በተደረገው አንድ ስብሰባ ላይ ጣዖታትንና ሥነ ስቅለትን አስመልክቶ ውይይት ተደረገ። አንድ ሰው “የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፣ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ። በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ” የሚለውን የዘዳግም 7:25 ጥቅስ በስብሰባው ላይ የተገኙት በሙሉ እንዲያነብቡ ጠየቀ።
ከዚያም ሰውዬው በዚህ መሠረት ጣዖቶቻቸውን ለማቃጠል የተስማሙ በሙሉ እጃቸውን እንዲያነሱ ጠየቀ። ወዲያው ሁሉም እጃቸውን አወጡ። (ሥራ 19:19, 20) በአሁኑ ጊዜ በመንደሩ ውስጥ ከሚገኙት 25 ቤተሰቦች መካከል 23ቱ የአምላክን ቃል በማጥናት ላይ ናቸው። ሁለት ሰዎች ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ አምስት ባልና ሚስት ደግሞ በይሖዋ ፊት ንጹህ ሕሊና ለማግኘት ሲሉ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ለማድረግ አቅደዋል።—ቲቶ 3:1፤ ዕብራውያን 13:4
በክሮች አማካኝነት ማስተማር
አብዛኞቹ የአልቲፕላኖ ነዋሪዎች ማንበብና መጻፍ ስለማይችሉ በአካባቢው ቋንቋ የተዘጋጁ የመጠበቂያ ግንብ የቪዲዮና የቴፕ ክሮች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራትም እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ እርዳታ አበርክተዋል። ዶራ የተባለች አንዲት ልዩ አቅኚ በቴፕ ክር የተዘጋጀውን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለውን ብሮሹር ተጠቅማ ጥናቶች ትመራለች። ቴፑን ተጠቅማ አንድ አንቀጽ እንዲያዳምጡ ታደርግና አንቀጹን ተመርኩዛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን ጥያቄ ትጠይቃቸዋለች።
አንድ የአካባቢው ራዲዮ ጣቢያ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር የተወሰኑትን ክፍሎች በኩቹዋ ቋንቋ ዘወትር ያስተላልፋል። በተመሳሳይም ይኸው ጣቢያ ከንቁ! መጽሔት የተወሰኑ ክፍሎች በስፓንኛ ያቀርባል። ከዚህ የተነሣ ብዙዎች የመንግሥቱን መልእክት የሰሙ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ቤታቸው ሲመጡ ደግሞ ይበልጥ ለማወቅ ይፈልጋሉ።
አልቲፕላኖ ከመላው ዓለም እይታ ርቆ የሚገኝ ቢሆንም ከአምላክ እይታ ግን አልራቀም። ይሖዋ ለሰው ልጆች ላለው ፍቅር ምስጋና ይግባውና ከፍ ባለው የኤንዲስ አልቲፕላኖ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ግርማ ሞገስ ያለውን የእውነተኛ አምልኮ ቤት ከሚያስጌጡት ብዙ ሰዎች ጋር እየተቀላቀሉ ነው።—ሐጌ 2:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።