በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት መማር እንችላለን

ከመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት መማር እንችላለን

ከመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት መማር እንችላለን

አምላክ ፕላኔቷ ምድርን በጥሞና ተመለከተ። ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያነት እያዘጋጀ ነበር። ሥራው ሁሉ መልካም መሆኑን አየ። እንዲያውም ሥራው ሲጠናቀቅ “እጅግ መልካም” መሆኑን ገልጿል። (ዘፍጥረት 1:​12, 18, 21, 25, 31) ሆኖም አምላክ እዚህ ፍጹም ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት ‘መልካም ስላልሆነ’ አንድ ነገር ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ አምላክ እንከን ያለው ነገር አልሠራም። ጉዳዩ የፍጥረት ሥራው ገና ያልተጠናቀቀ መሆኑ ብቻ ነው። ይሖዋ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” ብሏል።​—⁠ዘፍጥረት 2:​18

የይሖዋ ዓላማ የሰው ልጅ ኅብረተሰብ በምድራዊ ገነት ላይ ጥሩ ጤናና ደስታ አግኝቶ እንዲሁም የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተሟልቶለት ለዘላለም እንዲኖር ነበር። የሰው ልጆች ሁሉ አባት አዳም ነው። ሚስቱ ሔዋን “የሕያዋን ሁሉ እናት” ሆናለች። (ዘፍጥረት 3:​20) በአሁኑ ጊዜ ምድር በቢልዮን በሚቆጠሩ ዝርያዎ​ቻቸው ብትሞላም እንኳ ሰዎች ፍጹማን አይደሉም።

የአዳምና የሔዋን ታሪክ በሰፊው ይታወቃል። ይሁን እንጂ ለእኛ የሚሆን ምን ተግባራዊ ጥቅም ይዟል? የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ካጋጠማቸው ነገር ምን መማር እንችላለን?

“ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው”

አዳም ለእንስሳቱ ስም ሲያወጣ እንደ እነሱ ተጓዳኝ እንደሌለው ተገነዘበ። በመሆኑም ይሖዋ ከጎኑ በወሰደው አጥንት የሠራለትን ውብ ፍጡር ሲመለከት በጣም ተደሰተ። አዳም ለየት ባለ መልኩ የተሠራች የእሱ አካል እንደሆነች በመገንዘብ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ሲል በደስታ ተናገረ።​—⁠ዘፍጥረት 2:​18-23

ሰው “ረዳት” ያስፈልገው ነበር። አሁን ምቹ የሆነች ረዳት አገኘ። ሔዋን ገነት የሆነውን ቤታቸውንና እንስሳቱን በመንከባከብ፣ ልጆች በመውለድ እንዲሁም ከእውነተኛ ወዳጅ የሚገኘውን ሐሳብና ድጋፍ በመስጠት ረገድ ለአዳም ፍጹም ተስማሚ ማሟያ ነበረች።​—⁠ዘፍጥረት 1:​26-30

ይሖዋ ባልና ሚስቱ ሊመኙ የሚችሉትን አግባብነት ያለው ነገር ሁሉ አሟልቶላቸዋል። አምላክ ሔዋንን ወደ ባልዋ በማምጣትና ጥምረታቸውን በማጽደቅ ለኅብረተሰብ መሠረት የሆኑትን ጋብቻንና ቤተሰብን አቋቋመ። የዘፍጥረት ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” እንዲሁም ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ሲባርካቸውና እንዲባዙ ሲነግራቸው እያንዳንዱ ልጅ የአባቱንና የእናቱን እንክብካቤ በሚያገኝበት አሳቢ ቤተሰብ ውስጥ እንዲወለድ አቅዶ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 1:​28፤ 2:​24

‘በእግዚአብሔር መልክ’

አዳም በአምላክ ‘መልክና ምሳሌ’ የተሠራ ፍጽምና የተላበሰ የአምላክ ልጅ ነበር። ሆኖም ‘እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ’ በአካል ሊመሳሰሉ አይችሉም። (ዘፍጥረት 1:​26፤ ዮሐንስ 4:​24) ተመሳሳይነታቸው ሰውን ከእንስሳት የላቀ እንዲሆን ባስቻሉት ባሕርያት ላይ የተመሠረተ ነበር። አዎን፣ ከመጀመሪያው አንስቶ የፍቅር፣ የጥበብ፣ የኃይልና የፍትሕ ባሕርያት በሰው ልቦና ውስጥ ተተክለዋል። ሰው የመምረጥ ነፃነትና መንፈሳዊ ባሕርያት የመላበስ ችሎታ ተሰጥቶታል። በተፈጥሮ ያገኘው የሥነ ምግባር ስሜት ወይም ሕሊና ክፉና ደጉን እንዲለይ ያስችለዋል። የሰው ልጆች በተፈጠሩበት ዓላማ ላይ ለማሰላሰል፣ ስለ ፈጣሪው እውቀት ለመሰብሰብና ከፈጣሪው ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል የማሰብ ችሎታ ነበረው። አዳም ይህን ችሎታ ይዞ በመፈጠሩ በምድራዊው የአምላክ የእጅ ሥራ ላይ አስተዳዳሪ በመሆን የሚያከናውነውን ሥራ ለመወጣት የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ነበረው።

ሔዋን ሕግ ተላለፈች

መልካምና ክፉን ከምታስታውቀው ዛፍ በስተቀር ገነት በሆነችው መኖሪያቸው ከሚገኙት ዛፎች ሁሉ ፍሬ መብላት እንደሚችሉ በመግለጽ ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ አዳም ወዲያውኑ ለሔዋን ነግሯት እንደሚሆን አያጠራጥርም። መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ መብላት የለባቸውም። ፍሬውን ከበሉ፣ በዚያው በበሉበት ቀን ይሞታሉ።​—⁠ዘፍጥረት 2:​16, 17

ብዙም ሳይቆይ የተከለከለውን ፍሬ በተመለከተ አንድ ጥያቄ ተነሳ። አንድ በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ አካል ቃል አቀባይ አድርጎ የተጠቀመበት እባብ ሔዋንን አነጋገራት። ቅን መስሎ በመቅረብ እባቡ እንዲህ ሲል ጠየቃት:- “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” ሔዋን ከአንዱ ዛፍ በስተቀር ከተቀረው ሁሉ መብላት የተፈቀደላቸው መሆኑን ነገረችው። ሆኖም እባቡ አምላክን በመቃወም ሴቲቱን እንዲህ አላት:- “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።” ሴቲቱ እንዳይበሉ የተከለከሉትን ዛፍ ለየት ባለ ስሜት መመልከት ጀመረች። ‘ዛፉ ለመብላት ያማረ ለዓይንም የሚያስጎመጅ ነበር።’ ሔዋን ሙሉ በሙሉ በመታለሏ የአምላክን ሕግ ጣሰች።​—⁠ዘፍጥረት 3:​1-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​14

ሔዋን ኃጢአት ከመሥራት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበራትም ማለት ነውን? በፍጹም! ራስህን በእሷ ቦታ አስቀምጠህ ሁኔታውን ለማየት ሞክር። እባቡ የነገራት ነገር አምላክና አዳም ከነገሯት ፍጹም ተቃራኒ ነበር። አንድ የማታውቀው ግለሰብ፣ የምትወድደውንና የምታምነውን ሰው በእምነት ማጉደል ቢወነጅለው ምን ይሰማሃል? ሔዋን የሰማችውን ነገር በመጸየፍና ቁጣዋን በመግለጽ አልፎ ተርፎም ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆን የተለየ ምላሽ መስጠት ነበረባት። ደግሞስ እባቡ ማንሆነና ነው የአምላክን ጽድቅና ባልዋ የነገራትን ነገር አጠያያቂ የሚያደርገው? ሔዋን ለራስነት መሠረታዊ ሥርዓት አክብሮት በማሳየት ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ከማድረጓ በፊት ምክር መጠየቅ ነበረባት። እኛም አምላክ ካወጣው መመሪያ ጋር የሚቃረን መረጃ ከደረሰን እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አለብን። ሆኖም ሔዋን መልካሙንና ክፉውን ራስዋ ለመወሰን በመፈለጓ ፈታኙ የነገራትን ቃል አመነች። በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ባውጠነጠነች መጠን የዚያኑ ያህል ማራኪ ሆኖ ታያት። መጥፎውን ምኞት ከአእምሮዋ ከማውጣት አሊያም ከቤተሰቧ ራስ ጋር በጉዳዩ ላይ ከመወያየት ይልቅ ጉዳዩን በአእምሮዋ በማጉላላቷ ትልቅ ስህተት ላይ ወደቀች!​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:​3፤ ያዕቆብ 1:​14, 15

አዳም የሚስቱን ቃል ሰማ

ሔዋን ብዙም ሳይቆይ አዳም በኃጢአቷ እንዲተባበራት አግባባችው። አዳም በቀላሉ እጅ መስጠቱን በተመለከተ ምን ማለት እንችላለን? (ዘፍጥረት 3:​6, 17) አዳም ለማን ታማኝ እንደሚሆን ግራ ተጋብቶ ነበር። ተወዳጅ የትዳር ጓደኛው የሆነችውን ሔዋንን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለሰጠው ለፈጣሪው ይታዘዝ ይሆን? አዳም በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት ለማወቅ ከአምላክ መመሪያ ይጠይቅ ይሆን? ወይስ ከሚስቱ ጋር በኃጢአቷ ለመተባበር ይወስናል? አዳም ሚስቱ የተከለከለውን ፍሬ በመብላት ለማግኘት የተመኘችው ነገር ሊሆን የማይችል ነገር መሆኑን በሚገባ ያውቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የተታለለም አዳም አይደለም፣ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች።” (1 ጢሞቴዎስ 2:​14) በመሆኑም አዳም ሆነ ብሎ ይሖዋን ለመቃወም መረጠ። ከሚስቱ የሚለያይ መሆኑ ያሳደረበት ስጋት አምላክ ሁኔታውን ለማስተካከል ባለው ችሎታ ላይ ካለው እምነት የላቀ እንደነበር ግልጽ ነው።

አዳም የወሰደው እርምጃ የራስን ሕይወት ከማጥፋት ተለይቶ የሚታይ አልነበረም። በተጨማሪም ይሖዋ ባሳየው ምሕረት የወለዳቸው ልጆች ሁሉ በኃጢአት እርግማን ሥር ለሞት የተወለዱ በመሆናቸው ድርጊቱ እንደ ነፍስ ግድያ ሊቆጠር የሚችል ነው። (ሮሜ 5:​12) በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ አሻፈረኝ ብሎ ማመፅ ምንኛ ከባድ ኪሳራ ያስከትላል!

የኃጢአት መዘዝ

የሠሩት ኃጢአት ወዲያውኑ የኀፍረት ስሜት አስከተለባቸው። ባልና ሚስቱ ይሖዋን ለማነጋገር በደስታ ከመሄድ ይልቅ ተሸሸጉ። (ዘፍጥረት 3:​8) ከአምላክ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ተቋረጠ። ሁለቱም የአምላክን ሕግ መጣሳቸውን ቢያውቁም እንኳ ምን እንደሠሩ ሲጠየቁ ምንም የጸጸት ስሜት አላሳዩም። የተከለከለውን ፍሬ በመብላት አምላክ ላሳያቸው መለኮታዊ ደግነት ጀርባቸውን ሰጡ።

በዚህ ምክንያት አምላክ ልጅ መውለድ ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚያስከትል ተናገረ። ሔዋን ፈቃድዋ ወደ ባልዋ ይሆናል፤ ባልዋም ገዥዋ ይሆናል። በመሆኑም በራስዋ ለመመራት ያደረገችው ሙከራ ውጤቱ ተገላቢጦሽ ሆነ። ከዚህ በኋላ አዳም የምድርን ፍሬ የሚበላው በብዙ ድካም ይሆናል። በኤደን ውስጥ ያለ ምንም ልፋት የምግብ ፍላጎቱን ማርካቱ ቀርቶ ወደወጣበት መሬት እስኪመለስ ድረስ ለሕይወት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማግኘት መፍጨርጨር ሊኖርበት ነው።​—⁠ዘፍጥረት 3:​16-19

በመጨረሻ አዳምና ሔዋን ከኤደን ገነት ተባረሩ። ይሖዋ እንዲህ አለ:- “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፣ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር . . .” የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ጎርዶን ዊናም “ዓረፍተ ነገሩ አልተቋጨም” ሲሉ ተናግረዋል። የቀረውን የአምላክ ሐሳብ ምናልባትም “ከገነት ላስወጣው” ብለን ማሟላት ሊኖርብን ነው። በአብዛኛው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሙሉውን የአምላክ ሐሳብ ያሰፍራል። በዚህኛው ሁኔታ ግን “ዓረፍተ ነገሩ ሳይቋጭ መቅረቱ አምላክ እርምጃ የወሰደበትን ፍጥነት ያሳያል። ገና ተናግሮ ሳይጨርስ ከገነት ተባርረው ወጥተዋል” ሲሉ ዊናም አክለው ተናግረዋል። (ዘፍጥረት 3:​22, 23) ከዚህ በኋላ በይሖዋና በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት መካከል የነበረው ማንኛውም ዓይነት የሐሳብ ግንኙነት የተቋረጠ ይመስላል።

አዳምና ሔዋን በዚያ የ24 ሰዓት ቀን ውስጥ በአካላዊ ሁኔታ አልሞቱም። ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሞተዋል። የሕይወት ምንጭ ከሆነው አካል ጋር ለዘለቄታው በመቆራረጣቸው ወደ ሞት ማዝገም ጀመሩ። የመጀመሪያ ልጃቸው ቃየን ሁለተኛ ልጃቸውን አቤልን በመግደሉ ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደርስባቸው ምንኛ መራራ እንደሚሆንባቸው አስብ!​—⁠ዘፍጥረት 4:​1-16

ከዚህ በኋላ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ስለ መጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። ሦስተኛው ወንድ ልጃቸው ሴት የተወለደው አዳም 130 ዓመት ሲሞላው ነበር። አዳም ከ800 ዓመት በኋላ በ930 ዓመቱ የሞተ ሲሆን በዚህ የሕይወት ዘመኑ “ወንዶችንም ሴቶችንም” ወልዷል።​—⁠ዘፍጥረት 4:​25፤ 5:​3-5

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት

ስለ መጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የቀረበው ዘገባ ዛሬ ያለው የሰው ዘር ኅብረተሰብ ላለበት ብልሹ ሁኔታ መንስዔ የሆነውን ነገር ከመግለጹም በተጨማሪ አንድ መሠረታዊ ትምህርት ይዟል። ከይሖዋ አምላክ ለማፈንገጥ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ጥረት ፍጹም ሞኝነት ነው። በእርግጥ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች በራሳችን ለመመራት ያስችለናል ብለው በሚያስቡት እውቀት ሳይሆን በይሖዋና በቃሉ ላይ እምነት ያሳድራሉ። መልካሙንና ክፉውን የሚወስነው ይሖዋ ሲሆን በመሠረቱ ትክክል የሆነውን ማድረግ ማለት እሱን መታዘዝ ነው። መጥፎ ተግባር መፈጸም ሕጎቹን መጣስና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ችላ ማለት ይሆናል።

አምላክ ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ የሰው ልጆች ሊመኙት የሚችሉትን ነገር ሁሉ ማለትም የዘላለም ሕይወትን፣ ነፃነትን፣ እርካታን፣ ደስታን፣ ጤንነትን፣ ሰላምን፣ ብልጽግናን እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን የማወቅ አጋጣሚን ከፊታቸው ዘርግቶላቸዋል። ሆኖም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ልናገኝ የምንችለው ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ በሰማያዊ አባታችን በይሖዋ ላይ የተመካ መሆኑን አምነን እስከተቀበልን ድረስ ብቻ ነው።​—⁠መክብብ 3:​10-13፤ ኢሳይያስ 55:​6-13

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አዳምና ሔዋን አፈ ታሪክ የወለዳቸው ናቸውን?

በጥንት ዘመን በኃጢአት ሳቢያ የጠፋ ገነት ነበረ የሚለው እምነት በጥንቶቹ ባቢሎናውያን፣ አሦራውያን፣ ግብጻውያንና በሌሎችም ዘንድ በሰፊው ተሰራጭቶ ይገኝ ነበር። በአብዛኞቹ ዘገባዎች ውስጥ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ፍሬ ስላለው የሕይወት ዛፍ የሚገልጽ ታሪክ ተጠቅሶ ይገኛል። በመሆኑም የሰው ዘር በኤደን አንድ አሳዛኝ ነገር መከሰቱን ያስታውሳል።

ዛሬ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን ዘገባ እንደ ተራ አፈ ታሪክ በመቁጠር አይቀበሉትም። ሆኖም አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች የሰው ዘር የጋራ ምንጭ ያለው አንድ ቤተሰብ መሆኑን ያምናሉ። ብዙ የሃይማኖት ምሁራን የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነው ሰው የፈጸመው የመጀመሪያው ኃጢአት ያስከተለው ውጤት ወደ ሰው ዘር የተላለፈ መሆኑ ሊታበል የማይችል ሐቅ ሆኖ አግኝተውታል። የሰው ዘር ከአንድ እናትና አባት የመጣ አይደለም የሚለው እምነት የመጀመሪያው ኃጢአት የተፈጸመው በተለያዩ አባቶች ነው እንዲሉ ያስገድዳቸዋል። ይህ ደግሞ “ኋለኛው አዳም፣” ክርስቶስ የሰው ልጆች መዋጀቱን እንዲክዱ ያደርጋቸዋል። ሆኖም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ባለው ሐሳብ ግራ አልተጋቡም። የዘፍጥረት ዘገባ በሐቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተገንዝበዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​22, 45፤ ዘፍጥረት 1:​27፤ 2:​24፤ ማቴዎስ 19:​4, 5፤ ሮሜ 5:​12-19