በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ልባዊ ፍቅር አላችሁን?

ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ልባዊ ፍቅር አላችሁን?

ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ልባዊ ፍቅር አላችሁን?

“ነፍሴ ምስክርህን [“ማሳሰቢያዎችህን፣” NW ] ጠበቀች፣ እጅግም ወደደችው።”​—⁠መዝሙር 119:​167

1. የይሖዋ ማሳሰቢያዎች በተለይ በተደጋጋሚ ተጠቅሰው የምናገኛቸው የት ነው?

 ይሖዋ ሕዝቡ ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። በእርግጥም እውነተኛ ደስታ ለማግኘት በአምላክ ሕግ መመላለስና ሥርዓቱን መጠበቅ ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ እንድንችልም ማሳሰቢያ ይሰጠናል። እነዚህ ማሳሰቢያዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተለይ ደግሞ በወጣቱ የይሁዳ መስፍን በሕዝቅያስ ሳይጻፍ እንዳልቀረ በሚነገርለት መዝሙር 119 ውስጥ ተደጋግመው ተጠቅሰዋል። የዚህ ግሩም መዝሙር የመክፈቻ ቃላት እንዲህ ይላሉ:- “በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው። ምስክሩን [“ማሳሰቢያውን፣” NW ] የሚፈልጉ፣ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው።”​—⁠መዝሙር 119:​1, 2

2. የአምላክ ማሳሳቢያዎች ከደስታ ጋር የተያያዙት እንዴት ነው?

2 የቃሉን ትክክለኛ እውቀት በመቅሰምና በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ‘በይሖዋ ሕግ እንሄዳለን።’ ይሁን እንጂ ፍጹማን ስላልሆንን ማሳሰቢያ ያስፈልገናል። “ማሳሰቢያዎች” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አምላክ ሕጎቹን፣ ሥርዓቱን፣ መመሪያዎቹን፣ ትእዛዛቱንና ደንቦቹን እንደገና እንደሚያስታውሰን የሚጠቁም ነው። (ማቴዎስ 10:​18-20) ደስተኞች ሆነን መኖር የምንችለው እነዚህን ማሳሰቢያዎች ያለማቋረጥ ከጠበቅን ብቻ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ማሳሰቢያዎች መከራና ሐዘን ከሚያስከትሉ መንፈሳዊ አደጋዎች እንድንጠበቅ ይረዱናል።

የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ሙጥኝ በሉ

3. በ⁠መዝሙር 119:​60, 61 መሠረት ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ነን?

3 የአምላክ ማሳሰቢያዎች “ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። የኀጥአን ገመዶች ተተበተቡብኝ፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም” በማ​ለት ለዘመረው መዝሙራዊ እጅግ የተ​ወደዱ ነበሩ። (መዝሙር 119:​60, 61) ሰማያዊ አባታችን ጠላቶቻችን የሚተበትቡብንን ገመድ እንደሚበጣጥስልን እርግጠኞች ስለሆንን የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ስደትን በጽናት እንድንቋቋም ይረዱናል። የመንግሥቱን የስብከት ሥራችንን ለመፈጸም እንችል ዘንድ በጊዜው እንዲህ ያሉትን መሰናክሎች ያስወግድልናል።​—⁠ማርቆስ 13:​10

4. ለአምላክ ማሳሰቢያዎች ምላሽ መስጠት የሚኖርብን እንዴት ነው?

4 ከይሖዋ ማሳሰቢያዎች እርማት የምናገኝበትም ጊዜ አለ። መዝሙራዊው እንዳደረገው ሁልጊዜ እንዲህ ያሉትን እርማቶች በአድናቆት እንቀበል። በጸሎት መልክ ለአምላክ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ምስክርህም [“ማሳሰቢያህም፣” NW ] ተድላዬ ነው . . . ምስክርህን [“ማሳሰቢያህን፣” NW ] ወደድሁ።” (መዝሙር 119:​24, 119) ዛሬ እኛ ከመዝሙራዊው የበለጡ ብዙ ማሳሰቢያዎች አግኝተናል። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የተወሰዱት ጥቅሶች ይሖዋ በሕጉ ሥር ለነበረው ሕዝቡ የሰጠውን መመሪያ ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ጉባኤን በተመለከተ ያለውን ዓላማም ጭምር ያስታውሱናል። አምላክ ከሕጎቹ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነገሮች እኛን ማሳሰብ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እንዲህ ላለው መመሪያ አመስጋኞች መሆን አለብን። ‘የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ሙጥኝ በማለት’ ፈጣሪያችንን ከሚያሳዝኑትና እኛንም ደስታ ከሚያሳጡን የኃጢአት ማባበያዎች እንርቃለን።​—⁠መዝሙር 119:​31 NW

5. የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ከልብ መውደድ የምንችለው እንዴት ነው?

5 የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ምን ያህል መውደድ ይኖርብናል? መዝሙራዊው “ነፍሴ ምስክርህን [“ማሳሰቢያዎችህን፣”] ጠበቀች፣ እጅግም ወደደችው” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:​167፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ለእኛ ከሚያስብ አባት የተገኙ ምክሮች እንደሆኑ አድርገን የምንመለከታቸውና የምንቀበላቸው ከሆነ ከልብ እንወዳቸዋለን። (1 ጴጥሮስ 5:​6, 7) ማሳሰቢያዎቹ ያስፈልጉናል። ምን ያህል እንደሚጠቅሙን እየተገነዘብን ስንሄድ ለማሳሰቢያዎቹ ያለንም ፍቅር እያደገ ይሄዳል።

የአምላክ ማሳሰቢያዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?

6. የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ያስፈልጉናል የምንልበት አንደኛው ምክንያት ምንድን ነው? እንድናስታውሳቸውስ የሚረዳን ነገር ምንድን ነው?

6 የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ያስፈልጉናል የምንልበት አንደኛው ምክንያት የምንረሳ በመሆናችን ነው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “በጥቅሉ ሲታይ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሰዎች ብዙ ነገሮችን እየረሱ ይሄዳሉ። . . . ምናልባት አንድ ስም ወይም አንድ ሌላ ቀላል ነገር አፋችሁ ላይ እያለ ጠፍቶባችሁ ያውቅ ይሆናል። . . . በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተው እንዲህ ያለው ጊዜያዊ የመርሳት ችግር በአእምሮ ውስጥ ያለውን ነገር ቶሎ ማስታወስ አለመቻል እንደሆነ ይገለጻል። ይህን ሁኔታ ሳይንቲስቶች ምስቅልቅል ባለ ቤት ውስጥ አንዱ ጋር የተሸጎጠን ዕቃ ለማግኘት ከመፈለግ ጋር ያመሳስሉታል። . . . አንድን ነገር ለማስታወስ አስተማማኝ የሆነው ዘዴ ጉዳዩን በደንብ እንደምታውቁት አድርጋችሁ ካሰባችሁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደገና ማጥናት ነው።” በትጋት የሚደረግ ጥናትና መደጋገም የአምላክን ማሳሰቢያዎች እንድናስታውስና ከዚያ ጋር ተስማምተን በመመላለስ ጥቅም እንድናገኝ ይረዳናል።

7. ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ የአምላክ ማሳሰቢያዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?

7 ክፋት በሰው ልጅ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ በመሆኑ የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሚያስፈልጉን ዛሬ ነው። የአምላክን ማሳሰቢያዎች በትኩረት የምንከታተል ከሆነ በዓለም የክፋት መንገድ ከመወሰድ የሚጠብቀንን ማስተዋል እናገኛለን። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ምስክርህ [“ማሳሰቢያህ፣” NW ] ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ።” (መዝሙር 119:​99-101) የአምላክን ማሳሰቢያዎች በመጠበቃችን ‘ከክፉ መንገድ ሁሉ’ እንርቃለን፤ እንዲሁም ‘ልቡናቸው እንደጨለመውና ከአምላክ እንደ ራቁት’ አብዛኞቹ የሰው ልጆች ከመሆን እንድናለን።​—⁠ኤፌሶን 4:​17-19

8. የእምነት ፈተናዎችን በተሳካ መንገድ ለመቋቋም የተሻለ ብቃት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?

8 የአምላክ ማሳሰቢያዎች የሚያስፈልጉን በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ የሚገጥሙንን ብዙ ፈተናዎች በጽናት እንድንወጣ ብርታት ስለሚሰጡንም ነው። (ዳንኤል 12:​4) ያለ እነዚህ ማሳሰቢያዎች ‘ሰምተን የምንረሳ’ እንሆናለን። (ያዕቆብ 1:​25) ይሁን እንጂ ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ በምናገኛቸው ጽሑፎች በመታገዝ ቅዱሳን ጽሑፎችን በግልና በጉባኤ ማጥናታችን በእምነታችን ላይ የሚሰነዘሩትን ፈተናዎች በተሳካ መንገድ እንድንቋቋም ያግዘናል። (ማቴዎስ 24:​45-47) እንዲህ ያሉት መንፈሳዊ ዝግጅቶች ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በምንገባበት ጊዜ ይሖዋን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንዳለብን እንድናስተውል ይረዱናል።

ስብሰባዎቻችን የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና

9. ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ የተባሉት እነማን ናቸው? የእምነት አጋሮቻቸውንስ የሚረዱት እንዴት ነው?

9 የሚያስፈልጉንን የአምላክ ማሳሰቢያዎች በከፊል የምናገኘው የተሾሙ ወንድሞች ትምህርት በሚሰጡባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ነው። ኢየሱስ ‘ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን እንደማረከና ወንዶችንም ስጦታ አድርጎ እንደሰጠ’ ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል። በመቀጠልም “[ክርስቶስም] አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 4:​8 [NW ], 11, 12) እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ማለትም የተሾሙ ሽማግሌዎች ለአምልኮ አንድ ላይ በምንሰባሰብበት ጊዜ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ላይ እንድናተኩር የሚያደርጉ በመሆናቸው ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን!

10. በ⁠ዕብራውያን 10:​24, 25 ላይ የሚገኘው ዋና ነጥብ ምንድን ነው?

10 ለመለኮታዊ ዝግጅቶች ያለን አመስጋኝነት በየሳምንቱ በሚደረጉት በአምስቱም ስብሰባዎቻችን ላይ እንድንገኝ ያነሳሳናል። ጳውሎስ አዘውትሮ አንድ ላይ የመሰብሰቡን ጉዳይ አጽዕኖት ሰጥቶታል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።”​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

11. እያንዳንዱ ሳምንታዊ ስብሰባ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

11 ስብሰባዎቻችን ለእኛ ያላቸውን ጥቅም ትገነዘባለህ? ሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እምነታችንን ያጠነክርልናል፣ ከይሖዋ ማሳሰቢያዎች ጋር ተስማምተን እንድንመላለስ ይረዳናል እንዲሁም “የዓለምን መንፈስ” ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 2:​12፤ ሥራ 15:​31) በሕዝብ ስብሰባዎች ላይ ተናጋሪዎች የይሖዋን ማሳሰቢያዎችና የኢየሱስን ድንቅ የሆነ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ጨምሮ ከአምላክ ቃል ትምህርት ይሰጣሉ። (ዮሐንስ 6:​68፤ 7:​46፤ ማቴዎስ 5:​1-7:​29) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አማካኝነት የማስተማር ችሎታችን ይበልጥ እየተሻሻለ ይሄዳል። የአገልግሎት ስብሰባ ምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት ስናደርስ፣ ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራና በሌሎቹም የአገልግሎታችን ዘርፎች አቀራረባችንን እንድናሻሽል በመርዳት ረገድ ያለው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ ነው። በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ወቅት የሚኖረው አነስተኛ ቁጥር ከአምላክ ማሳሰቢያዎች ጋር የተያያዙ ሐሳቦችን ለመግለጽ የሚያስችል የተሻለ አጋጣሚ ይሰጠናል።

12, 13. እስያ ውስጥ በምትገኝ አንዲት አገር ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ያላቸውን አድናቆት ያሳዩት እንዴት ነው?

12 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት የአምላክን ትእዛዛት እንድናስብ የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ሌሎችም የእምነት ፈተናዎች እያሉ መንፈሳዊነታችን ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳናል። በአንዲት የእስያ አገር ከቤታቸው ተፈናቅለው ጫካ ውስጥ ለመኖር የተገደዱ 70 የሚያክሉ ክርስቲያኖች የስብሰባዎችን አስፈላጊነት ተገንዝበው ነበር። አዘውትረው አንድ ላይ ያደርጉት የነበረውን ስብሰባ ፈጽሞ ላለማቋረጥ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ በጦርነት ወደፈራረሰችው ከተማቸው ተመልሰው ከመንግሥት አዳራሹ የቀረውን ነገር በመነቃቀል በጫካው ውስጥ መልሰው አዳራሽ ገንብተዋል።

13 በዚችው አገር በሌላኛው ክፍል የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለዓመታት የተካሄደውን ጦርነት በጽናት አሳልፈው አሁንም በቅንዓት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በዚህ አካባቢ ከሚኖሩት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ “ወንድሞችን አንድ ላይ አሰባስቦ ለማቆየት የረዳችሁ ነገር ምንድን ነው?” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ላለፉት 19 ዓመታት አንድም ስብሰባ አምልጦን አያውቅም። አንዳንድ ጊዜ በቦንብ ድብደባ ወይም በሌሎች ችግሮች ምክንያት አንዳንድ ወንድሞች ወደ ስብሰባው መምጣት ሳይችሉ ይቀራሉ። ይሁን እንጂ አንድም ጊዜ ከስብሰባ ቀርተን አናውቅም።” በእርግጥም እነዚህ የተወደዱ ወንድሞችና እህቶች ‘አንድ ላይ መሰብሰባቸውን አለመተዋቸው’ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ተገንዝበዋል።

14. አረጋዊቷ ሐና ከነበራት ልማድ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

14 የ84 ዓመቷ መበለት ሐና ‘ከመቅደስ ተለይታ አታውቅም ነበር።’ ከዚህ የተነሣ ሕፃኑ ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ቤተ መቅደስ በተወሰደ ጊዜ በዚያ ነበረች። (ሉቃስ 2:​36-38) አንድም ስብሰባ እንዳያመልጥህ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃልን? በልዩና በወረዳ እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አንድም ክፍል እንዳያመልጥህ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ እያደረግህ ነውን? በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበው በመንፈሳዊ የሚጠቅም ትምህርት ሰማያዊው አባታችን ለሕዝቡ ያለውን አሳቢነት ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ኢሳይያስ 40:​11) በተጨማሪም እንዲህ ያሉት ወቅቶች ደስታ የሰፈነባቸው ናቸው። እኛም እዚያ መገኘታችን ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ያለንን አድናቆት ያሳያል።​—⁠ነህምያ 8:​5-8, 12

በይሖዋ ማሳሰቢያዎች የተለያችሁ ሁኑ

15, 16. የይሖዋን ማሳሰቢያዎች መጠበቅ በአኗኗራችን ላይ የሚንጸባረቀው እንዴት ነው?

15 የአምላክን ማሳሰቢያዎች መከተል ከዚህ ክፉ ዓለም የተለየን እንድንሆን ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል የአምላክን ማሳሰቢያዎች መከተላችን ወደ ፆታ ብልግና እንዳንገባ ይጠብቀናል። (ዘዳግም 5:​18፤ ምሳሌ 6:​29-35፤ ዕብራውያን 13:​4) እንድንዋሽ፣ እምነት እንድናጎድል ወይም እንድንሰርቅ የሚገጥመንን ፈተና ከመለኮታዊ ማሳሰቢያዎች ጋር በመስማማት በተሳካ ሁኔታ ማሸነፍ ይቻላል። (ዘጸአት 20:​15, 16፤ ዘሌዋውያን 19:​11፤ ምሳሌ 30:​7-9፤ ኤፌሶን 4:​25, 28፤ ዕብራውያን 13:​18) የይሖዋን ማሳሰቢያዎች መታዘዝ የበቀል እርምጃ እንዳንወስድ፣ ቂም እንዳንይዝ ወይም የሌሎችን ስም እንዳናጠፋ ይጠብቀናል።​—⁠ዘሌዋውያን 19:​16, 18፤ መዝሙር 15:​1, 3

16 የአምላክን ማሳሰቢያዎች በመጠበቅ እርሱ ለሰጠን አገልግሎት የተቀደስን ወይም የተለየን ሆነን እንኖራለን። ከዚህ ዓለም የተለዩ መሆኑ ምንኛ አስፈላጊ ነው! ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ተከታዮችን በተመለከተ የሚከተለውን ልመና አሰምቷል:- “እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።” (ዮሐንስ 17:​14-17) ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት የተለየን እንድንሆን የሚረዳንን የአምላክ ቃል ከፍ አድርገን መመልከታችንን እንቀጥል።

17. የአምላክን ማሳሰቢያዎች ችላ ብንል ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ምን ማድረግ ይገባናል?

17 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን አገልግሎቱን ለማከናወን ተቀባይነት እንዳገኘን መቀጠል እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ የአምላክን ማሳሰቢያዎች ችላ ብንል ኖሮ በአብዛኛው የዓለም ንግግር፣ ሥነ ጽሑፍ፣ መዝናኛና ድርጊት በሚንጸባረቀው የዓለም መንፈስ በተዋጥን ነበር። ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ የማያመሰግኑ፣ ከዳተኞች፣ ጨካኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከአምላክ ይልቅ ተድላን የሚወዱ የተባሉት ዓይነት ሰዎች መሆን እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። እነዚህ ከአምላክ የራቁ ሰዎች ከሚያሳዩአቸው ባሕርያት መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ጠልቀን የገባን በመሆኑ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች መታዘዛችንን በሌላ አባባል ‘ቃሉን መጠበቃችንን’ መቀጠል እንችል ዘንድ መለኮታዊ እርዳታ ለማግኘት መጸለያችንን አናቋርጥ።​—⁠መዝሙር 119:​9

18. የአምላክን ማሳሰቢያዎች መጠበቃችን ምን አዎንታዊ እርምጃዎችን እንድንወስድ ያደርገናል?

18 የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ማድረግ የሌለብንን ነገር በተመለከተ ብቻ በማስጠንቀቅ አይወሰኑም። ማሳሰቢያዎቹን መታዘዝ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን እንዲሁም በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ሐሳባችንና ኃይላችን እንድንወደው በማነሳሳት አዎንታዊ እርምጃዎች እንድንወስድ ይረዳናል። (ዘዳግም 6:​5፤ መዝሙር 4:​5፤ ምሳሌ 3:​5, 6፤ ማቴዎስ 22:​37፤ ማርቆስ 12:​30) የአምላክ ማሳሰቢያዎች ባልንጀሮቻችንንም እንድንወድድ ያነሳሱናል። (ዘሌዋውያን 19:​18፤ ማቴዎስ 22:​39) በተለይ መለኮታዊውን ፈቃድ በማድረግና ሕይወት ሰጪ የሆነውን “የአምላክ እውቀት” ለሌሎች በማካፈል ለአምላክና ለባልንጀሮቻችን ያለንን ፍቅር እናሳያለን።​—⁠ምሳሌ 2:​1-5

የይሖዋን ማሳሰቢያዎች መጠበቅ ሕይወት ያስገኛል!

19. የይሖዋን ማሳሰቢያዎች መጠበቅ ተግባራዊና ጠቃሚ መሆኑን ሌሎች እንዲገነዘቡ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

19 የይሖዋን ማሳሰቢያዎች የምንታዘዝና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ የምንረዳ ከሆነ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን እናድናለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:​16) የይሖዋን ማሳሰቢያዎች መጠበቅ ተግባራዊና ጠቃሚ መሆኑን ሌሎች እንዲገነዘቡ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ነው። በዚህ መንገድ ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች’ የአምላክ ቃል የሚሰጠውን መመሪያ መከተል ከሁሉ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ በተጨባጭ ሊገነዘቡ ይችላሉ። (ሥራ 13:​48 NW ) በተጨማሪም ‘አምላክ በእርግጥ ከእኛ ጋር እንዳለ’ በማስተዋል ለሉዓላዊው ጌታ ለይሖዋ በሚቀርበው አምልኮ ከጎናችን ሊሰለፉ ይችላሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 14:​24, 25

20, 21. የአምላክ ማሳሰቢያዎችና መንፈሱ ምን እንድናደርግ ይረዱናል?

20 ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናታችንንና የተማርነውን ነገር ሥራ ላይ ማዋላችንን በመቀጠል እንዲሁም ከይሖዋ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ በመሆን ለማሳሰቢያዎቹ ልባዊ ፍቅር ልናዳብር እንችላለን። እነዚህን ማሳሰቢያዎች መከተላችን “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” እንድንለብስ ይረዳናል። (ኤፌሶን 4:​20-24) የይሖዋ ማሳሰቢያዎችና ቅዱስ መንፈሱ በሰይጣን እጅ ያለው ዓለም ከሚያንጸባርቃቸው ባሕርያት ፍጹም በተለየ መልኩ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት የውሃት፣ ራስን መግዛት ያሉትን ባሕርያት እንድናንጸባርቅ ይረዱናል! (ገላትያ 5:​22, 23፤ 1 ዮሐንስ 5:​19) እንግዲያውስ በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን፣ በተሾሙ ሽማግሌዎች እና በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ይሖዋ ስለሚፈልግብን ነገሮች አንዳንድ ማሳሰቢያዎች ስናገኝ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን።

21 ለጽድቅ ስንል ስቃይ ቢደርስብን እንኳ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች በመጠበቃችን ደስ ሊለን ይችላል። (ሉቃስ 6:​22, 23) በጣም አስጊ ከሆኑት ሁኔታዎች እንዲያወጣን ወደ አምላክ ዞር እንላለን። በተለይ ሁሉም ብሔራት ‘ሁሉን ወደሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ማለትም ወደ አርማጌዶን እየተሰባሰቡ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠ራእይ 16:​14-16

22. የይሖዋን ማሳሰቢያዎች በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይገባዋል?

22 ይገባናል የማንለውን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ከልባችን መውደድና በሙሉ ልባችን መጠበቅ ይገባናል። እንግዲያውስ “የማሳሰቢያዎችህ ጽድቅ ለዘላለም ነው። በሕይወት እኖር ዘንድ እንዳስተውል አድርገኝ” ሲል እንደዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት መንፈስ ይኑረን። (መዝሙር 119:​144 NW ) እንዲሁም “[ይሖዋ ሆይ] ወደ አንተ ጮኽሁ፤ አድነኝ፣ ምስክርህንም [“ማሳሰቢያህንም፣” NW ] እጠብቃለሁ” በሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ላይ የተንጸባረቀው ዓይነት ቁርጠኝነት ይኑረን። (መዝሙር 119:​146) አዎን፣ በቃላችንም ሆነ በድርጊታችን በእርግጥ የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ከልብ እንደምንወድድ እናሳይ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• መዝሙራዊው ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች የነበረው አመለካከት ምንድን ነው?

• የአምላክ ማሳሰቢያዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?

• ስብሰባዎቻችን ከመለኮታዊ ማሳሰቢያዎች ጋር በተያያዘ የሚጫወቱት ሚና ምንድን ነው?

• የይሖዋ ማሳሰቢያዎች ከዓለም የተለየን እንድንሆን የሚያደርጉን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መዝሙራዊው የይሖዋን ማሳሰቢያዎች እጅግ ወድዷል

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሐናን ምሳሌ በመከተል ከስብሰባዎች ላለመቅረት ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃልን?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋን ማሳሰቢያዎች መከተል ለይሖዋ አገልግሎት ንጹሕና ብቁ በመሆን የተለየን እንድንሆን ያደርገናል