በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም”

“ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም”

የሕይወት ታሪክ

“ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም”

ኸርበርት ጄኒንዝ እንደተናገረው

“የጋና የወደብ ከተማ ከሆነችው ከቴማ ወደ መጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በመመለስ ላይ ሳለሁ ወደ ከተማ ለመሄድ መኪና ሲጠብቅ የነበረ አንድ ወጣት አሳፈርኩ። አጋጣሚውን ተጠቅሜ መሰከርኩለት። ግሩም ምሥክርነት እንደሰጠሁት ተሰምቶኝ ነበር! ይሁን እንጂ ወጣቱ የሚወርድበት ቦታ ሲደርስ ዘሎ ከመኪናው ወጣና እየሮጠ ሄደ።”

ይህ አጋጣሚ በሕይወቴ ውስጥ እንግዳ ነገር በመከሰት ላይ እንዳለ የሚጠቁም ፍንጭ ነበር። በሕይወቴ ውስጥ የተከሰተውን ነገር ከመናገሬ በፊት እኔ ካናዳዊ ሆኜ ሳለ ለምን ጋና እንደሄድኩ ላጫውታችሁ።

ጊዜው ታኅሣሥ አጋማሽ 1949 ሲሆን ቦታው ካናዳ ከቶሮንቶ ከተማ ወጣ ብሎ ነበር። ለአንድ አዲስ ቤት ውኃ ለማስገባት እንደ በረዶ የሚቀዘቅዘውን መሬት አንድ ሜትር ያክል ቆፍረን መጨረሳችን ነበር። በጣም በርዶንና ደክሞን ስለነበር ባነደድነው እሳት ዙሪያ ተሰብስበን መጥቶ የሚወስደንን መኪና በመጠባበቅ ላይ ነበርን። አርኖልድ ሎርተን የተባለ አንድ ሠራተኛ ድንገት “ጦርና የጦር ወሬ፣” “የዚህ የዓለም መጨረሻ” እና ከዚያ በፊት ሰምቻቸው የማላውቃቸውን ሌሎች ነገሮች መናገር ጀመረ። ወዲያው ሁሉም ወሬያቸውን አቆሙ፤ ድንግርግር አላቸው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ተናደዱ። በልቤ ‘ይህ ሰው በጣም ደፋር ነው! ማንም ሊያዳምጠው አልፈለገም፤ እሱ ግን መናገሩን ቀጠለ’ ብዬ እንዳሰብኩ ትዝ ይለኛል። ሆኖም የተናገረው ነገር በጣም መሰጠኝ። ጊዜው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሲሆን ከአያት ከቅድመ አያት ጀምሮ ቤተሰባችን ሲከተለው በቆየው የክርስታደልፊያ ሃይማኖት እንደዚህ ያለ ነገር ሰምቼ አላውቅም ነበር። በሚሰጠው ማብራሪያ በእጅጉ ስለተመሰጥኩ የሚናገረውን በደንብ አዳመጥኩ።

ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት አርኖልድን ቀርቤ ለማነጋገር ጊዜ አልወሰደብኝም። ተሞክሮ የሌለኝ የ19 ዓመት ወጣት የነበርኩበትን ያንን ጊዜ መለስ ብዬ ሳስበው እሱና ባለቤቱ ጄን ምን ያህል ቻዮችና ደጎች እንደነበሩ እገነዘባለሁ። እመጣለሁ ብዬ ሳልነግራቸውና ሳልጋበዝ ከእነርሱ ጋር ለመጫወት ብዙ ጊዜ ቤታቸው እሄድ ነበር። አመለካከቴን እንዳስተካክል እንዲሁም ትክክለኛውን የሥነ ምግባር አቋም በተመለከተ በወጣት አእምሮዬ ውስጥ ይጉላላ ለነበረው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ እንዳገኝ ረድተውኛል። መንገድ ዳር ቁጭ ብለን እሳት ስንሞቅ መጀመሪያ ከተመሰከረልኝ ከ10 ወር በኋላ ጥቅምት 22, 1950 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር የሆንኩ ሲሆን የቶሮንቶ ከተማ አካል በሆነው በኖርዝ ዮርክ በሚገኘው የዊልኦዴል ጉባኤ መሳተፍ ጀመርኩ።

ከእምነት አጋሮች ጋር ወደፊት መግፋት

አባቴ አዲሱን ሃይማኖቴን ለመከተል እንደቆረጥኩ ሲያውቅ ከቤተሰብ ጋር መኖር ከዕለት ወደ ዕለት አስቸጋሪ እየሆነ መጣ። በዚያው ሰሞን አባባ፣ ሰክሮ መኪና ሲያሽከረክር ከነበረ ሰው ጋር ፊት ለፊት በመጋጨቱ የደረሰበት ጉዳት ጠባዩን ሁሉ ለዋውጦት ነበር። በእማማ፣ በሁለቱ ወንድሞቼና በሁለቱ እኅቶቼ ላይ ኑሮ በጣም ከብዶባቸው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳልከተል የሚደረግብኝ ጫና እያደር ይባባስ ጀመር። ስለዚህ ከወላጆቼ ጋር ያለኝ ሰላም እንዳይናጋና ‘በእውነት መንገድ’ ላይ ለመቆም ስል ቤቱን ለቅቄ መውጣቱ እንደሚሻል ተሰማኝ።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​2

በ1951 የበጋ ወራት መገባደጃ ላይ አልቤርታ ኮሌማን ወደሚገኝ አነስተኛ ጉባኤ ተዛወርኩ። ሮዝ ሃንት እና ኪዝ ሮቢንስ የሚባሉ ወጣቶች በሙሉ ጊዜ ሕዝባዊ ስብከት ይኸውም በዘወትር አቅኚነት ተሰማርተው ነበር። እኔም በዚሁ የፈቃደኝነት አገልግሎት እንድካፈል አበረታቱኝ። መጋቢት 1, 1952 እንደ እነርሱ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።

የሰጡኝን ማበረታቻ ምን ጊዜም አልረሳውም። ልማራቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች የነበሩ ሲሆን ይህ ደግሞ አንዱ የትምህርት መስክ ነበር። ከጊዜ በኋላ አልቤርታ ውስጥ በሌዝብሪጅ ጉባኤ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ያህል በአቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ያልጠበቅኩት ጥሪ ቀረበልኝ። በካናዳ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ ኒው ብሩንስዊክ ውስጥ ከምትገኘው ከሞንክቶን አንስቶ እስከ ኪውቤክ ጋስፔ ድረስ ባለው አካባቢ ተበታትነው የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች እንድጎበኝ ተመደብኩ።

በተመደብኩበት ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ የጎለመሱ ምሥክሮች ጋር ራሴን ሳወዳድረው ዕድሜዬ ገና 24 ዓመት ስለነበረና በእውነትም ውስጥ አዲስ ስለሆንኩ ለቦታው ብቁ እንደማልሆን ተሰማኝ። በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ልባዊ ጥረት አደረግሁ። እንደገና ሌላ ያልጠበቅኩት መብት ተከተለ።

ጊልያድ ትምህርት ቤትና ወደ ጎልድ ኮስት ጉዞ

መስከረም 1955 ኒው ዮርክ ሳውዝ ላንሲንግ በሚገኘው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለ26ኛ ክፍል ከተጋበዙት ወደ መቶ የሚጠጉ ተማሪዎች መካከል እኔ አንዱ ነበርኩ። እንደዚህ ያለው የአምስት ወራት ጥልቅ ስልጠናና ጥናት ለእኔ በጣም ያስፈልገኝ ነበር። ከፍተኛ ቅንዓት ካለው ከዚህ ቡድን ጋር አብሬ መሆኔ የእኔም ቅንዓት ከፍ እንዲል አድርጎ ነበር። በዚህ ጊዜ እስከ አሁንም ለሕይወቴ መሻሻል ምክንያት የሆነኝን ሌላ አጋጣሚ አገኘሁ።

ለሚስዮናዊነት አገልግሎት ከሚሰለጥኑት ተማሪዎች መካከል አይሊን ስታብስ የምትባል ወጣት እኅት ነበረች። አይሊን ረጋ ያለች፣ ቁም ነገረኛ፣ ትሑትና የደስተኝነት ባሕርይ እንዳላት አስተዋልኩ። እየተርበተበትኩ ሐሳቤን ስገልጽላት ሳትደነግጥ አልቀረችም። ብቻ ደግነቱ ትታኝ አልሮጠችም! ሁለታችንም ከተስማማን በኋላ አይሊን በሚስዮናዊነት ወደተመደበችበት ወደ ኮስታ ሪካ ስትሄድ እኔም በምዕራብ አፍሪካ ወደምትገኘው ጎልድ ኮስት (የአሁኗ ጋና) ሄድኩ።

ግንቦት 1956 አንድ ቀን ጠዋት ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኝ የማኅበሩ ሕንፃ አሥረኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው የወንድም ናታን ኖር ቢሮ ገባሁ። እሱ በዚያን ወቅት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ነበር። በጎልድ ኮስት፣ በቶጎላንድ (በአሁኗ ቶጎ)፣ በአይቮሪ ኮስት (በአሁኗ ኮትዲቭዋር)፣ በአፐር ቮልታ (በአሁኗ ቡርኪና ፋሶ) እንዲሁም በጋምቢያ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ እንድከታተል የቅርንጫፍ አገልጋይ ሆኜ ተመድቤ ነበር።

ወንድም ኖር የነገረኝን ቃላት ትናንት የሰማኋቸው ያህል አስታውሳቸዋለሁ። “ወዲያው እንደደረስኩ ኃላፊነቱን መረከብ አለብኝ ብለህ ማሰብ የለብህም። ምንም የሚያስቸኩል ነገር የለም፤ እዚያ ካሉ ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች አንዳንድ ነገሮችን ተረዳ። ከዚያም ሁኔታዎችን በደንብ ከተረዳህ በኋላ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይነት ሥራህን መጀመር ይኖርብሃል። . . . መሾምህን የሚገልጸው ደብዳቤ ይኸው። እዚያ ከደረስክ ከሰባት ቀን በኋላ ኃላፊነቱን መረከብ ይኖርብሃል።”

ሰባት ቀናት ብቻ’ ስል አሰብኩ። ‘ታዲያ “ምንም የሚያስቸኩል ነገር የለም” ሲል ምን ማለቱ ነው?’ ግራ ተጋብቼ ከቢሮው ወጣሁ።

የሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ብን ብለው አለፉ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ብሩክሊን ከሚገኙት የማኅበሩ ቢሮዎች ባሻገር ካለው ኢስት ወንዝ ተነስቶ ጎልድ ኮስት ለመድረስ 21 ቀን የሚፈጀውን የባሕር ላይ ጉዞ ጀመርኩ።

እኔና አይሊን ቶሎ ቶሎ ደብዳቤ እንለዋወጥ ነበር። በ1958 እንደገና ተገናኘንና በዚያው ዓመት ነሐሴ 23 ቀን ተጋባን። ግሩም የትዳር ጓደኛ ስለሰጠኝ ይሖዋን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ።

በማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከሚሠሩ ሚስዮናውያን እንዲሁም ከአፍሪካ ወንድሞችና እኅቶች ጋር ለ19 ዓመታት አብሬ የማገልገል መብት በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ። በጣት ይቆጠሩ የነበሩት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ወደ 25 ደርሰው ነበር። እነዚያ ዓመታት ለእኛ ፈታኝ፣ አስደናቂ ድርጊቶች የተከናወኑባቸውና ፍሬያማ ነበሩ። ቢሆንም እውነቱን ለመናገር የሚሞቀውና የሚወብቀው የአየር ጠባይ ከባድ ፈተና ሆኖብኝ ነበር። ሁልጊዜ ያልበኝ፣ ዝልፍልፍ ያደርገኝና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያነጫንጨኝ ነበር። የሆነ ሆኖ በጋና በ1956 ከ6, 000 ትንሽ ይበልጥ የነበረው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር በ1975 ወደ 21, 000 ሲያድግ ማየቱ በጣም የሚያስደስት ነበር። በአሁኑ ጊዜ ከ60, 000 በላይ ትጉህ የይሖዋ ምሥክሮች መኖራቸው ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።

“ነገ” ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅም

በ1970 ገደማ ይህ ነው ብዬ የማልገልጸው የጤና ችግር ይሰማኝ ጀመር። አጠቃላይ የጤና ምርመራ አደረግሁ፤ ሆኖም ውጤቱ “ጤነኛ” ነህ የሚል ነበር። ታዲያ ሁልጊዜ ጤንነቴ እንደታወከ የሚሰማኝ፣ በጣም የሚያደክመኝና እረፍት የሚያሳጣኝ ምንድን ነው? ሁለት ነገሮች የዚህን ጥያቄ መልስ ያስገኙልኝ ሲሆን ሁለቱም አስደንጋጭ ነበሩ። በእርግጥም ያዕቆብ “ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም” በማለት የጻፋቸው ቃላት እውነት ናቸው።​—⁠ያዕቆብ 4:​14 NW 

የመጀመሪያውን ፍንጭ ያገኘሁት ያንን ወጣት በመኪና አሳፍሬ በመሰከርኩለት ጊዜ ነበር። ያለምንም ማቋረጥ ከመናገሬም በላይ በጣም እየፈጠንኩና እየጋልኩ እንደምሄድ አይታወቀኝም ነበር። ወጣቱ የሚወርድበት ቦታ ስንደርስ ከመኪናው ወጥቶ ሲሮጥ በጣም ተገረምኩ። አብዛኞቹ ጋናውያን ረጋ ያሉና ትዕግሥተኞች ናቸው። የእሱ ሁኔታ ግን ተለየብኝ። ቁጭ እንዳልኩ ስለሁኔታው ሳስብ አንድ ችግር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ምን እንደሆነ አልወቀው እንጂ አንድ ችግር እንዳለብኝ እርግጠኛ ነበርኩ።

ሁለተኛውን ፍንጭ ያገኘሁት ደግሞ አንድ ቀን ከአይሊን ጋር ስለሁኔታው ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ ነው። “እንግዲህ ችግሩ አካላዊ ካልሆነ አእምሮአዊ ሊሆን ይችላል” የሚል ሐሳብ ሰጠችኝ። ስለዚህ ምልክቶቹን አንድ በአንድ ከጻፍኩ በኋላ አእምሮ ሐኪም ዘንድ ሄድኩ። የጻፍኩትን ሳነብለት “ይህ ለየት ያለ ህመም ነው። ማኒክ ዲፕረሽን የተባለ የአእምሮ በሽታ ይዞሃል” አለኝ።

ይህን ስሰማ ክው ብዬ ቀረሁ! በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ትግል ባደርግም በሽታው ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰብኝ መጣ። መፍትሄ ለማግኘት የማደርገውን ጥረት አላቋረጥኩም። ሆኖም መፍትሄውን የሚያውቅ አንድም ሰው አላገኘሁም። እንዴት ያለ ተስፋ አስቆራጭ ትግል ነው!

የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን በሕይወታችን ዋነኛው ሥራችን አድርገን መያዝ የምንጊዜም ምኞቻችን የነበረ ሲሆን ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ሥራዎችም ነበሩ። “ይሖዋ፣ ፈቃድህ ከሆነ ‘በሕይወት መኖርና ይህን ሥራ መሥራት እፈልጋለሁ’” የሚል ልባዊ ጸሎት በተደጋጋሚ አቀረብኩ። (ያዕቆብ 4:​15) ሆኖም እንደዚያ አልሆነም። ስለዚህ እውነታውን ተቀብለን ጋናን እና እዚያ የሚኖሩ ብዙ የቅርብ ወዳጆቻችንን ትተን ሰኔ 1975 ወደ ካናዳ ለመመለስ ዝግጅት አደረግን።

ይሖዋ በሕዝቡ በኩል ድጋፍ ይሰጣል

ብዙም ሳይቆይ ጨርሶ እንዳልተተውኩና ያጋጠመኝ ችግርም በእኔ ላይ ብቻ የደረሰ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። በ⁠1 ጴጥሮስ 5:​9 ላይ የሚገኙት “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ [እወቁ]” የሚሉት ቃላት ይበልጥ ትርጉም ሰጡኝ። ለውጡን ባንወደውም ይሖዋ ሁለታችንንም ለመርዳት ምን እንዳደረገ ለማስተዋል ችያለሁ። ያለንበት ‘የወንድማማች ማኅበር’ በብዙ መንገዶች ድጋፍ ያደረገልን መሆኑ እንዴት ደስ ይላል!

ምንም እንኳ በቁሳዊ ነገር ረገድ ብዙ ባይኖረንም ይሖዋ አልጣለንም። በጋና የሚኖሩት ወዳጆቻችን በቁሳዊም ሆነ በሌሎች መንገዶች እንዲረዱን ልባቸውን አነሳስቷል። በጣም የምንቀርባቸውን ወዳጆቻችንን የተሰናበትነውና ያልጠበቅነውን “ነገ” የተቀበልነው ዝብርቅርቅ ባለ ስሜት ነበር።

የአይሊን እኅት ሌኖራ እና ባለቤትዋ አልቪን ፍሪዘን በደግነት እቤታቸው የተቀበሉን ሲሆን የሚያስፈልገንን ሁሉ በልግስና በማቅረብ ለወራት ተንከባክበውናል። አንድ የታወቀ የአእምሮ ሐኪም በእርግጠኝነት “በስድስት ወራት ውስጥ በደንብ ትድናለህ” አለኝ። እንዲህ ያለኝ ብሩህ ተስፋ እንዲታየኝ አስቦ ሳይሆን አይቀርም፤ ሆኖም እሱ ያለው ነገር እንኳን ከስድስት ወር ከስድስት ዓመት በኋላም አልተፈጸመም። በአሳቢነት ባይፖላር ሙድ ዲስኦርደር የሚል ስያሜ ከተሰጠው ከዚያው የአእምሮ ሕመም ጋር አሁንም እየታገልኩ ነው። ይህ አጠራር ምንም እንኳን የበሽታውን ክብደት የሚያቀለው ቢመስልም በሽታው ምን ያክል ከባድ እንደሆነ የተያዘ ያውቀዋል።

በዚያን ጊዜ ወንድም ኖር ሰኔ 1977 ለሞት ባበቃው በሽታ ይሰቃይ ነበር። ሆኖም እንደምንም ብሎ የሚያጽናኑና ምክር ያዘሉ ቃላትን የያዘ ረጅምና አበረታች ደብዳቤ ጻፈልኝ። እነዚያ ደብዳቤዎች አሁን ድረስ ከእኔ ጋር አሉ። የተጠቀመባቸው ቃላት በግልጽ ይታይብኝ የነበረውን ተገቢ ያልሆነ የከንቱነት ስሜት አስወግደውልኛል።

በ1975 ማገባደጃ ላይ ውድ መብት የሆነውን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት አቋርጠን ለጤንነቴ ትኩረት መስጠቱ ግድ ሆነብን። የተለመደው የቀን ብርሃን ዓይኔን ያሳምመኛል። ድንገተኛ ቀጭን ድምፅ እንደ ጥይት ያንባርቅብኛል። የሰዎች ጫጫታ ያሸብረኛል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንኳ በጣም ይከብደኝ ነበር። የሆነው ሆኖ በመንፈሳዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ሙሉ በሙሉ አምን ነበር። ችግሩን ለማሸነፍ ስል ብዙውን ጊዜ ሰው ሁሉ ቦታ ቦታውን ከያዘ በኋላ ወደ መንግሥት አዳራሽ እገባለሁ፤ እንዲሁም ልክ ፕሮግራሙ እንዳለቀ እወጣለሁ።

በጣም የሚከብደኝ ሌላው ነገር በሕዝባዊ አገልግሎት መካፈል ነው። አንዳንድ ጊዜ በር ላይ ከደረስኩ በኋላ ደወሉን ለመጫን ድፍረት አጣለሁ። ይሁን እንጂ አገልግሎታችን ለእኛም ሆነ በጎ ምላሽ ለሚሰጡ ሰዎች መዳንን እንደሚያስገኝ ስለማውቅ ማገልገሌን አላቋረጥኩም። (1 ጢሞቴዎስ 4:​16) ከጊዜ በኋላ ስሜቴን እንደምንም እየተቆጣጠርኩ ወደሚቀጥለው ቤት ሄጄ አንኳኳለሁ። በአገልግሎት የማደርገውን ተሳትፎ በመቀጠል መንፈሳዊ ጤንነቴን መጠበቅና ችግሮችን ለማሸነፍ የሚያስችል አቅም ማግኘት ችያለሁ።

ባይፖላር ሙድ ዲስኦርደር የተባለው በሽታ በቀላሉ ስለማይድን በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ከዚህ በሽታ እንደማልላቀቅ አውቀዋለሁ። በ1981 የንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት እትሞች ጥሩ ጥሩ ርዕሶችን ይዘው ወጥተው ነበር። a በእነዚህ ርዕሶች አማካኝነት የበሽታውን ባሕርይ ማወቅና በሽታውን መቋቋም የሚቻልባቸውን ውጤታማ ዘዴዎች ይበልጥ መረዳት ችያለሁ።

ችግሮችን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ መማር

ይህ ሁሉ ባለቤቴ መሥዋዕትነት እንድትከፍልና ማስተካከያዎችን እንድታደርግ ጠይቆባታል። በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የምትገኝ አስታማሚ ከሆንክ ስሜቷን ትረዳላት ይሆናል። እንዲህ ስትል ተናግራለች:-

“የስሜት መቃወስ በባሕርይ ላይ ድንገተኛ ለውጥ ያስከትላል። በበሽታው የሚሰቃይ አንድ ሰው ጥሩ ሲጫወት፣ አዳዲስ ዕቅዶችንና ሐሳቦችን እያነሳ ሌሎችን ሲያበረታታ ይቆይና ወዲያው ደካማ፣ ግራ የተጋባ ሌላው ቀርቶ ቁጡ ሰው ይሆናል። ሌሎች እንዲህ የሚሆነው በበሽታው ምክንያት እንደሆነ ካልተገነዘቡ ሊበሳጩበትና ግራ ሊገባቸው ይችላል። ሰውየው ያወጣቸውን እቅዶች ወዲያው ይለውጥና ከተስፋ መቁረጥና አልረባም ከሚለው ስሜት ጋር ትግል ይገጥማል።”

በእኔ በኩል ከመጠን በላይ ደህና እንደሆንኩ ሲሰማኝ ስጋት ያድርብኛል። ከመጠን በላይ ደስ ደስ ካለኝ ድንገት ይህ ስሜቴ እንደሚወርድና ሁሉ ነገር እንደሚያስጠላኝ ይገባኛል። ለእኔ የሚሻለኝ ስሜቴ ከመጠን በላይ “ከሚወጣ” ይልቅ “ቢወርድ” ነው። ምክንያቱም ስሜቴ በሚወርድበት ጊዜ ለተወሰኑ ቀናት አደብ ገዝቼ ቁጭ እንድል ስለሚያደርገኝ ተገቢ ያልሆነ ነገር ከማድረግ እቆጠባለሁ። አይሊን ስሜቴ ከፍ ሲል በማስጠንቀቅ ስሜቴ ሲጨልም ደግሞ በማጽናናት ድጋፍ እየሰጠችኝ በእጅጉ ትረዳኛለች።

በሽታው ሲነሳ የሌሎችን ጉዳይ ችላ ብሎ ስለራስ ብቻ የማሰብ ሁኔታ ያጋጥማል። አንድ ሰው ጭንቀቱ በሚያይልበት ጊዜ ራሱን ከሌሎች ሰዎች ሙሉ በሙሉ ያገልላል ወይም ቅጽበታዊ የሆነ የባሕርይ መለዋወጥ በሚያጋጥመው ጊዜ የሌሎችን ሰዎች ስሜት ማገናዘብ ይሳነዋል። በፊት በፊት አእምሮአዊና ስሜታዊ ችግር እንዳለብኝ ማመን አቅቶኝ ነበር። የችግሬ መንስዔዎች ሌሎች ሰዎች ወይም የጥረት አለመሳካትን የመሳሰሉ ውጪያዊ ነገሮች ናቸው ከሚለው ሐሳብ ጋር መታገል ነበረብኝ። ‘በአካባቢዬ ምንም አዲስ የተከሰተ ነገር የለም። ችግሬ ውስጣዊ እንጂ ውጪያዊ አይደለም’ እያልኩ ራሴን ማሳመን ነበረብኝ። ቀስ በቀስ አስተሳሰቤ ተስተካከለ።

ባለፉት ዓመታት ሁለታችንም እኔ ስላለሁበት ሁኔታ እኛም ሆንን ሌሎች ስለሚሰማቸው ነገር ግልጽና ሐቀኞች መሆን እንዳለብን ተምረናል። አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝና በሽታው ሕይወታችንን እንዲቆጣጠረው ላለመፍቀድ እንጣጣር ነበር።

የተሻለ “ነገ” ይመጣል

ከልብ በመጸለይና በብዙ ትግል ይሖዋ ከሚሰጠው በረከትና ድጋፍ ጥቅም አግኝተናል። አሁን ሁለታችንም በዕድሜ ገፍተናል። ዘወትር መጠነኛ መድኃኒት በመውሰድ የማያቋርጥ የሕክምና ክትትል የማደርግ ሲሆን አሁን ጤንነቴ ብዙም አይለዋወጥም። ማንኛውንም ዓይነት የአገልግሎት መብት እናደንቃለን። ሽማግሌ ሆኜ ማገልገሌን ቀጥያለሁ። ምንጊዜም ሌሎች በእምነት እንዲበረቱ ለመርዳት እንጥራለን።

በእርግጥም፣ በ⁠ያዕቆብ 4:​14 ላይ እንደተጠቀሰው ‘ሕይወታችን ነገ ምን እንደሚሆን አናውቅም።’ ይህ የነገሮች ሥርዓት እስካለ ድረስ ሁኔታው እንዲሁ ይቀጥላል። ይሁን እንጂ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና” የሚሉት የ⁠ያዕቆብ 1:​12 ቃላትም እውነት ናቸው። ሁላችንም ዛሬን ጸንተን በመቆም ይሖዋ ነገ የሚያመጣውን በረከት ለማየት ያብቃን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በነሐሴ 8, 1981 ንቁ ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቋቋም ትችላለህ፣” የሚለውን ርዕስ፣ መስከረም 8, 1981 ንቁ!  እትም ላይ የወጣውን “የመንፈስ ጭንቀትን መዋጋት የምትችልበት መንገድ” እንዲሁም በጥቅምት 22, 1981 ንቁ ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውን “ከባድ የመንፈስ ጭንቀትን መዋጋት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብቻዬን መሆን ስፈልግ በሥዕል ስቱዲዮ ውስጥ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከአይሊን ጋር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1963 በጋና፣ ቴማ ውስጥ “የዘላለሙ ምሥራች” በሚል ርዕስ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ