በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ—ሕይወታችንን የምንመራበት መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ—ሕይወታችንን የምንመራበት መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ​—ሕይወታችንን የምንመራበት መጽሐፍ

የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ . . . የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:​12) የአምላክ ቃል ማከናወን የሚችለውን ነገር በተመለከተ የተሰጠው ይህ መግለጫ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያው ጥሩ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ለየት የሚያደርገው ነገር እንዳለም የሚያሳይ ነው።

ሃይማኖታዊ ጽሑፍ የሚያዘጋጅ አንድ ሰው “መልእክቱ የመተንፈስን ያህል ለሕይወታችን በጣም ወሳኝ ነው” ሲል ፍሬ ነገሩን በአጭሩ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። በመቀጠልም “አንድ ሰው በዛሬው ጊዜ ፈውስ ለማግኘት ያለንን ጉጉትና ፍላጎት ግምት ውስጥ አስገብቶ መጽሐፍ ቅዱስን ከዚህ አንጻር ሲያነብ አስገራሚ ውጤት ያገኛል” ሲል አክሎ ተናግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ ደማቅ ብርሃን እንደሚሰጥ መብራት በዛሬው ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን በርካታ ውስብስብ ጥያቄዎችና ችግሮች ላይ የእውቀት ብርሃን ይፈነጥቅልናል።​—⁠መዝሙር 119:​105

በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ጥበብ አስተሳሰባችንን የመቅረጽ፣ ችግሮችን መፍታት እንድንችል የመርዳትና ሕይወታችንን የማሻሻል ኃይል ያለው ከመሆኑም በላይ መለወጥ የማንችላቸውን ሁኔታዎች እንድንቋቋም የሚያስችሉንን ዘዴዎች ያስታጥቀናል። ከሁሉም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እንድናውቀውና እንድንወድደው ያስችለናል።

ዓላማ የሚያስገኝ መጽሐፍ

የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የሆነው ይሖዋ አምላክ ‘መንገዳችንን ሁሉ ያውቃል።’ እኛ ከምናውቀው በላይ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን ይገነዘባል። (መዝሙር 139:​1-3) በአሳቢነት ተነሳስቶ ሰዎች ሊያሳዩት ስለሚገባ ባሕርይ ግልጽ ገደቦች አውጥቷል። (ሚክያስ 6:​8) እነዚህን ገደቦችና መመሪያዎች ለመረዳትና በዚያም መሠረት ለመኖር ጥረት ማድረጉ አግባብነት ያለው ነው። መዝሙራዊው ‘በይሖዋ ሕግ ሐሴት የሚያደርግ’ ሰው ‘የሚሠራው ሁሉ ስለሚከናወንለት’ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል። (መዝሙር 1:​1-3) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ውጤት የሚያስገኝ በመሆኑ በእርግጥ ልንመረምረው ይገባል።

በመምህርነት ሙያ ያገለገለውና በአሁኑ ጊዜ በጡረታ ላይ የሚገኘው ሞሪስ ቀደም ሲልም መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ታሪካዊና ሥነ ጽሑፋዊ ጠቀሜታ አለው የሚል እምነት ነበረው። ሆኖም በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ስለ መጻፉ ይጠራጠር ነበር። ሞሪስ አምላክ በጽሑፍ የሰፈረውን ቃሉን ለሰዎች የሰጠበትን ምክንያት አስመልክቶ የቀረበለትን ማብራሪያ ካዳመጠ በኋላ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መረመረ። ወጣት በነበረበት ጊዜ ታሪክ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሳይንስና ጂኦግራፊ አጥንቷል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት የሚደግፉትን በርካታ ማስረጃዎች በቀላሉ መረዳት እንደሚችል ይሰማው እንደነበር ተናግሯል። “የቅንጦት ኑሮን፣ ሀብትንና ተድላን በጭፍን አሳድድ ነበር። ሆኖም እስከ ዛሬ ከተጻፉት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ መጽሐፍ ያለውን ማራኪ ገጽታና የያዘውን እውነት ሳልገነዘብ መቅረቴ ያሳዝናል።”

አሁን በ70ዎቹ ዕድሜው ውስጥ የሚገኘው ሞሪስ ኢየሱስ ለሐዋርያው ቶማስ መገለጡን የሚገልጸውን ዘገባ በተዘዋዋሪ መንገድ በመጥቀስ “‘የተወጋበትን ቁስል’ በእጄ በመንካቴ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምኛለሁ” ሲል ምስጋናውን ገልጿል። (ዮሐንስ 20:​24-29) ሐዋርያው ጳውሎስ በትክክል እንደገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ የልብን አሳብ የሚመረምር ከመሆኑም በላይ ለሕይወት ትርጉም ይሰጣል። በእርግጥም ሕይወታችንን ለመምራት የሚያስችል መጽሐፍ ነው።

የተመሰቃቀለን ሕይወት ለማስተካከል የሚበጅ መፍትሔ

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች መጥፎ ልማዶቻቸውን እንዲያስወግዱ የሚረዳ ምክርም ይዟል። ዳንኤል ጎጂ የሆነውን የማጨስ ልማድ ከማሸነፉም በተጨማሪ መረን ከለቀቁ ፓርቲዎች መራቅና የአልኮል መጠጦችን አላግባብ ከመጠጣት መታቀብ ችሏል። (ሮሜ 13:​13፤ 2 ቆሮንቶስ 7:​1፤ ገላትያ 5:​19-21) እንዲህ ዓይነት ልማዶችን ለማስወገድና “አዲሱን ሰው” ለመልበስ ቆራጥነት የተሞላበት ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። (ኤፌሶን 4:​22-24) ዳንኤል “ከፍጽምና በጣም የራቅን በመሆናችን ለውጥ ማድረጉ ከብዶኝ ነበር” ሲል ተናግሯል። ይሁን እንጂ ተሳክቶለታል። በአሁኑ ጊዜ ዳንኤል የአምላክን ቃል በየቀኑ የሚያነብ ሲሆን ይህም ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ አስችሎታል።

ዳንኤል በልጅነት ዕድሜው መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ባያውቅም እንኳ ለመጽሐፉ ጥልቅ አክብሮት ነበረው። በተጨማሪም ሁልጊዜ ማታ ማታ ወደ አምላክ ይጸልይ ነበር። ሆኖም የጎደለው ነገር እንዳለ ሆኖ ስለሚሰማው ደስተኛ አልነበረም። ሕይወቱ መለወጥ የጀመረው ለመጀመሪያ ጊዜ የአምላክን ስም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሲመለከት ነበር። (ዘጸአት 6:​3 የ1879 ትርጉም፤ መዝሙር 83:​18 NW ) ከዚህ በኋላ በሚጸልይበት ጊዜ ይሖዋ የሚለውን ስም ከመጠቀሙም በላይ ከበፊቱ በበለጠ ውስጣዊ ስሜቱን ይገልጽ ጀመር። “ይሖዋ ከማንም በላይ የምቀርበው አካል ሆነ፤ አሁንም ቢሆን የቅርብ ወዳጄ ነው።”

ዳንኤል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መማር ከመጀመሩ በፊት ስለ ወደፊቱ ጊዜ የነበረው አመለካከት የጨለመ ነበር። እንዲህ ይላል:- “ዓለም እያሽቆለቆለች በመሄድ ላይ መሆኗን ማንኛውም ሰው ሊያስተውለው ይችላል። ሁኔታው ስጋት ስላሳደረብኝ ከአእምሮዬ ለማውጣት ስል ራሴን በሥራ አስጠምድ ነበር።” ከዚያም አምላክ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ዘላለማዊ ሰላምና ደስታ በሚያገኙባት የጸዳች ምድር ላይ ለሁሉም ሰው ፍትሕ እንደሚያሰፍን ተማረ። (መዝሙር 37:​10, 11፤ ዳንኤል 2:​44፤ ራእይ 21:​3, 4) አሁን ዳንኤል አስተማማኝ ተስፋ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ያለው የማረጋጋት ኃይል ሕይወትን በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት እንዲይዝ አስችሎታል።

ስሜታዊ ችግሮችን ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ

ጆርጅ እናቱ የሞተችው የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ከእንቅልፍ ስለመንቃቱ እርግጠኛ መሆን ስላልቻለ ሲመሽ መተኛት ያስፈራው ነበር። ከዚያም ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤን አስመልክቶ ‘በመቃብር ያሉት ሁሉ [የኢየሱስን] ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል’ ሲል የተናገረውን ቃል አነበበ። እንዲሁም ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” ሲል የተናገረው ቃል ልቡን ነካው። (ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 11:​25) እነዚህ ሐሳቦች ምክንያታዊ፣ አሳማኝና አጽናኝ ሆነው አገኛቸው። ጆርጅ “ይህ እውነት አእምሮን ከመማረክ አልፎ ልብንም ይነካል” ሲል ተናግሯል።

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤልም ፍርሃት ይሰማው ነበር። እናቱ ብቻዋን ልታሳድገው ስላልቻለች በተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያ ቤቶች ለመኖር ተገድዷል። ሁልጊዜ ባይተዋርነት ይሰማው ስለነበር አፍቃሪ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ መኖር የሚያስገኘውን ደኅንነት ለማግኘት ይመኝ ነበር። በመጨረሻ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ አማካኝነት ሲመኝ የነበረውን ነገር አገኘ። ዳንኤል ከክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ በመጀመሩ የመንፈሳዊ ቤተሰብ አባል በመሆን ተቀባይነት የማግኘትና በሌሎች ዘንድ የመወደድ ስሜት ሊሰማው ችሏል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ በሆነና ውስጣዊ ስሜትን በሚያረካ መንገድ ጥቅም ያስገኛል።

ይሖዋ ልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ከማየቱም በተጨማሪ የምንፈልገውን ነገር እንደሚያውቅ አስታውስ። አምላክ ‘ልብን መዝኖ’ “ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ” ይሰጣል።​—⁠ምሳሌ 21:​2፤ ኤርምያስ 17:​10

ለቤተሰብ ሕይወት የሚጠቅም ተግባራዊ ምክር

መጽሐፍ ቅዱስ ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በተመለከተ ተግባራዊ ምክር ይሰጣል። ጆርጅ እንዲህ ይላል:- “የባሕርይ አለመጣጣም ወይም አለመግባባት በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ እጅግ አስጨናቂ ሁኔታዎች መካከል የሚደመር ነው።” ጆርጅ ለዚህ ችግር መፍትሄ ሆኖ ያገኘው ነገር ምንድን ነው? “አንድ ሰው በእኔ ቅር እንደተሰኘ ከተሰማኝ ማቴዎስ 5:​23, 24 ላይ የሚገኘውን ‘ከወንድምህ ጋር ታረቅ’ የሚለውን ቀጥተኛ ምክር በሥራ አውላለሁ። የተፈጠረውን አለመግባባት በመጥቀስ መነጋገር መቻሌ ብቻ እንኳን ውጤት ያስገኛል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለትን የአምላክ ሰላም እንዳገኘሁ ይሰማኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በጣም ተግባራዊ ስለሆነ ውጤት ያስገኛል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

ባልና ሚስት በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር ሁለቱም ‘ለመስማት የፈጠኑ፣ ለመናገርም የዘገዩ፣ ለቁጣም የዘገዩ’ መሆን አለባቸው። (ያዕቆብ 1:​19) እንዲህ ዓይነቱ ምክር የሐሳብ ግንኙነት እንዲሻሻል ይረዳል። ጆርጅ “ባለቤቴን ልክ እንደ ራሴ መውደድና መያዝ እንዳለብኝ የሚናገረውን ምክር በሥራ ሳውል ወዲያው ለውጥ አያለሁ። እኔን ማክበር ይበልጥ ቀላል ይሆንላታል” ሲል አክሎ ተናግሯል። (ኤፌሶን 5:​28-33) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ አለፍጽምናችንን አምነን መቀበልና መታገል የምንችልበትን መንገድ እንዲሁም የሌሎችን አለፍጽምና ችሎ በማሳለፍ ረገድ እንዴት ሊሳካልን እንደሚችል ያስተምረናል።

ዘለቄታ ያለው ምክር

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 3:​5, 6) እንዴት ያልተወሳሰቡና ጥልቅ ትርጉም ያዘሉ ቃላት ናቸው!

መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ለውጥ የሚያስገኝ ኃይል አለው። አምላክን የሚወድዱ ሰዎች ሕይወታቸውን ከፈቃዱ ጋር እንዲያስማሙና ‘በይሖዋ ሕግ በመሄድ’ ደስታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። (መዝሙር 119:​1) ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስፈልገንን መመሪያና ምክር ይዟል። (ኢሳይያስ 48:​17, 18) በየዕለቱ አንብበው፣ በምታነበው ነገር ላይ አሰላስል፣ እንዲሁም በሥራ አውለው። እንዲህ ማድረግህ አእምሮህ ነፃ ሆኖ ንጹህና ገንቢ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ያስችልሃል። (ፊልጵስዩስ 4:​8, 9) ሕይወትህን እንዴት መምራት እንዳለብህና ደስተኛ ሆነህ እንዴት መኖር እንደምትችል ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሕይወትን ፈጣሪ መውደድ የምትችልበትንም መንገድ ትማራለህ።

እንዲህ ዓይነት አካሄድ በመከተል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች እንደተገነዘቡት ሁሉ አንተም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያው ጥሩ መጽሐፍ ብቻ ከመሆን ያለፈ ትርጉም እንዳለው ትገነዘባለህ። በእርግጥ ሕይወትህን ለመምራት የሚያስችል መጽሐፍ ሆኖ ታገኘዋለህ!

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ልማዶችን ለማሸነፍ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠናክርልህ ይችላል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አምላክ መቅረብ የምትችልበትን መንገድ ያስተምርሃል