በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ—የተወደደና የተገፋ መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ—የተወደደና የተገፋ መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ​—የተወደደና የተገፋ መጽሐፍ

የ16ኛው መቶ ዘመን ዕውቁ ሆላንዳዊ ምሁር ዴሲዴርዩስ ኢራስመስ “ ቅዱሳን መጻሕፍት በሁሉም ቋንቋዎች እንዲተረጎሙ እመኛለሁ” ሲሉ ጽፈዋል።

የኢራስመስ ጠንካራ ፍላጎት እያንዳንዱ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብና መረዳት እንዲችል ነበር። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠላቶች እንዲህ ያለውን ሐሳብ ክፉኛ አውግዘዋል። እንዲያውም በዚያን ዘመን አውሮፓ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ መጠነኛ ፍላጎት ላሳየ ሰው እንኳ በጣም አደገኛ ቦታ ነበረች። የእንግሊዝ ፓርላማ እንዲህ የሚል ደንብ አውጥቶ ነበር:- “ቅዱሳን ጽሑፎችን በእንግሊዝኛ ያነበበ ማንኛውም ሰው መሬቱን፣ የግል ንብረቶቹንና ሕይወቱን ያጣል . . . በይቅርታ ከታለፉ በኋላ በግትርነታቸው ከቀጠሉ ወይም ወደ ቀድሞ ልማዳቸው ከተመለሱ ደግሞ በመጀመሪያ በንጉሡ ላይ ክሕደት በመፈጸማቸው ከተሰቀሉ በኋላ በአምላክ ላይ በማመፃቸው በእሳት ይቃጠላሉ።”

በአውሮፓ በተካሄደው የካቶሊክ ኢንኩዊዝሽን የፈረንሳይ ዎልደንሳውያንን የመሳሰሉ “መናፍቃን” ቡድኖች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የታደኑ ሲሆን “ተራ ሰዎች እንዳይሰብኩና ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዳያስተምሩ በጥብቅ ተከልክለው ሳለ . . . [ዎልደንሳውያን ] ከወንጌሎችና ከመልእክቶች እንዲሁም ከሌሎች ቅዱስ ጽሑፎች” በመስበካቸው አንድ በአንድ እየተለቀሙ ለሥቃይ ይዳረጉ ነበር። ለመጽሐፍ ቅዱስ ከነበራቸው ፍቅር የተነሳ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ለከፍተኛ ሥቃይና ለሞት ተዳርገዋል። የጌታን ጸሎትና አሥርቱን ትእዛዛት በቃላቸው ለመውጣትና ለልጆቻቸው ለማስተማር ሲሉ ብቻ ራሳቸውን እጅግ አስከፊ ለሆነ ቅጣት አጋልጠዋል።

ለአምላክ ቃል የነበራቸው ይህ ፍቅር ሰሜን አሜሪካን ቅኝ ግዛት ለማድረግ ከተጓዙት ከአብዛኞቹ እንግሊዛውያን ልብ ውስጥ አልጠፋም ነበር። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ፕራይቬት ላይፍ —⁠ፓሽን ኦቭ ዘ ሬነሳንስ የተባለው መጽሐፍ በቀድሞዋ አሜሪካ “ንባብና ሃይማኖት የማይነጣጠሉ ነገሮች ከመሆናቸውም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም የተለመደ ነገር ነበር” ይላል። እንዲያውም በ1767 በቦስተን ታትሞ የወጣው ስብከት እንዲህ የሚል ሐሳብ አቅርቧል:- “ቅዱስ ጽሑፉን በትጋት አንብቡ። ሁልጊዜ ጠዋትና ማታ ከመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ላይ አንድ ምዕራፍ ማንበብ ይኖርባችኋል።”

በካሊፎርኒያ ቬንቱራ የሚገኘው ባርና የምርምር ቡድን እንዳለው ከሆነ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ አሜሪካውያን በአማካይ ሦስት መጽሐፍ ቅዱሶች አሏቸው። ሆኖም በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳሳየው በዚህች አገር መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ቢሆንም “ጊዜ ወስዶ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት እንዲሁም በተግባር ማዋል . . . ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል።” ብዙዎች ስለ መጽሐፉ ይዘት የጠለቀ ግንዛቤ የላቸውም። አንድ የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ እንዲህ ብለዋል:- “[መጽሐፍ ቅዱስ] በዛሬው ጊዜ ላሉ ችግሮችና አሳሳቢ ጉዳዮች ሊሠራ ይችላል የሚለው አስተሳሰብ እየጠፋ ነው።”

የዓለማዊ አስተሳሰብ ማዕበል

ብዙዎች የማመዛዘን ችሎታን በመጠቀምና እርስ በርስ በመረዳዳት ብቻ ሕይወትን ስኬታማ በሆነ መንገድ መምራት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ተጨባጭ ሐቆችና እውነታዎች እንደያዘ መጽሐፍ ሳይሆን ሃይማኖታዊ አስተያየቶችንና የግል ገጠመኞችን ከሚያቀርቡ በርካታ መጻሕፍት መካከል አንዱ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል።

ታዲያ አብዛኞቹ ሰዎች በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ይበልጥ ውስብስብና አስቸጋሪ እየሆኑ የሚሄዱ ጉዳዮች መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? አስተማማኝ የሆነ ሥነ ምግባራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ መመሪያ ስለሌላቸው በመንፈሳዊ ባዶ እንደሆኑ ያክል ነው። ልክ መቅዘፊያ እንደሌላቸው ጀልባዎች “በሰዎች ሽንገላና በአታላይነት ተንኮል በተዘጋጀ በአሳሳች የትምህርት ነፋስ ወዲያና ወዲህ” ይወሰዳሉ።​—⁠ኤፌሶን 4:​14 የ1980 ትርጉም

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያው ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ብቻ ነው? ወይስ ተግባራዊና በጣም አስፈላጊ መረጃ የያዘ እውነተኛ የአምላክ ቃል? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) መጽሐፍ ቅዱስ ልንመረምረው የሚገባ መጽሐፍ ነውን? ቀጥሎ ያለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዴሲዴርዩስ ኢራስመስ

[ምንጭ]

From the book Deutsche Kulturgeschichte

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዎልደንሳውያን ከቅዱሳን ጽሑፎች በመስበካቸው ምክንያት እየተመነጠሩ ለሥቃይ ይዳረጉ ነበር

[ምንጭ]

Stichting Atlas van Stolk, Rotterdam