በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማመን ይኖርብሃልን?

ማመን ይኖርብሃልን?

ማመን ይኖርብሃልን?

የ12 ዓመቱ ተማሪ የአልጀብራን መሠረታዊ ሐሳብ ለመረዳት ትግል ላይ ነው። መምህሩ ግልጽ የሚመስል አንድ የአልጀብራ ስሌት ለክፍሉ ተማሪዎች ያሳያል።

“x=y እንበል። ሁለቱም ዋጋቸው 1 ነው” በማለት ጀመረ።

ተማሪውም በሐሳቡ ‘ይሄ እንኳን ቀላል ይመስላል’ ይላል።

ይሁን እንጂ መምህሩ አንድ አራት መሥመር ያህል ምክንያታዊ የሚመስል ስሌት ከሠራ በኋላ ያመጣው ውጤት እጅግ የሚያስገርም ነበር። “እንግዲያው 2=1!”

ከዚያም ግራ የተጋቡትን ተማሪዎች “ይህ ስህተት መሆኑን አረጋግጡልኝ” አላቸው።

የአልጀብራ እውቀቱ ውስን የሆነው ተማሪ ይህ ስሌት ስህተት መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል አያውቅም። እያንዳንዱ የስሌቱ ቅደም ተከል ፍጹም ትክክል ይመስል ነበር። ታዲያ ይህን እንግዳ የሆነ የስሌት ውጤት አምኖ መቀበል ይገባዋል ማለት ነው? ደግሞም መምህሩ ከእርሱ እጅግ የላቀ የሒሳብ እውቀት ያለው ሰው ነው። ቢሆንም መቀበል አይገባውም! ተማሪው ‘ይህ ነገር ስህተት መሆኑን የግድ ማረጋገጥ አይገባኝም። ትክክል እንዳልሆነ በደመ ነፍስ እንኳ መገመት እችላለሁ’ በማለት ከራሱ ጋር ይነጋገራል። (ምሳሌ 14:​15, 18) መምህሩም ሆነ የትኛውም የክፍሉ ተማሪ ሁለት ብር በአንድ ብር እንደማይለውጡ ያውቃል!

ከጊዜ በኋላ ይህ የአልጀብራ ተማሪ ስሌቱ ላይ የነበረው ችግር ምን እንደሆነ ተረድቶታል። የሆነ ሆኖ የገጠመው ተሞክሮ አንድ ትልቅ ነገር አስተምሮት አልፏል። ስለ ጉዳዩ ከፍተኛ እውቀት ያለው ሰውም ቢሆን በጥበብ የተቀነባበረና የማይታበል የሚመስል ሐሳብ ቢያቀርብ አንድ አድማጭ በጊዜው ስህተት መሆኑን ማረጋገጥ ስላልቻለ ብቻ ያንን የተሳሳተ መደምደሚያ መቀበል አይኖርበትም። ተማሪው አንድ ነገር ከታመነ ምንጭ የመጣ መስሎ በሚታይበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር የሰማነውን ሁሉ ለማመን መቸኮል እንደሌለብን የሚገልጸውን በ1 ዮሐንስ 4:​1 ላይ የሚገኘውን ተግባራዊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ተከትሏል ለማለት ይቻላል።

ይህ ማለት ግን አስቀድሞ የነበረህን ሐሳብ ላለመለወጥ በግትርነት መሟገት አለብህ ማለት አይደለም። የተሳሳቱ አመለካከቶችን ሊያስተካክሉ የሚችሉ እውቀቶችን ላለመቀበል አእምሮን መዝጋት ስህተት ነው። ይሁን እንጂ የተሻለ እውቀት ወይም ሥልጣን እንዳለው የሚናገር ሰው በሚያሳድረው ተጽዕኖ ‘ከአእምሮአችን ቶሎ መናወጥ’ አይገባንም። (2 ተሰሎንቄ 2:​2) እርግጥ መምህሩ ተማሪዎቹን እንዲሁ በቀልድ መልክ እየፈተናቸው ነበር። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ነገሮች በዚህ መልኩ በቅንነት የሚደረጉ አይደሉም። ሰዎች በጣም ‘የረቀቁ የተንኮል ማታለያዎችን’ ሊያቀርቡ ይችላሉ።​—⁠ኤፌሶን 4:​14፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:​14, 23, 24

ኤክስፐርቶች ሁልጊዜ ትክክል ናቸውን?

በየትኛውም መስክ የተሠማሩ ኤክስፐርቶች የቱንም ያህል እውቀት ቢኖራቸው በመካከላቸው የሐሳብ ልዩነት ከመኖሩም ሌላ ሐሳባቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ። በሕክምናው ሳይንስ ውስጥ ለሕመም ምክንያት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው የሚለውን በመሰሉ መሠረታዊ ነገሮች ላይ የሚደረገውን መቋጫ የሌለው ክርክር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚያገለግሉ አንድ የሕክምና ፕሮፌሰር “በበሽታዎች ረገድ ተፈጥሮአችንና ውጫዊ ነገሮች ያላቸው ሚና ምንድን ነው የሚለው ርዕሰ ጉዳይ በሳይንቲስቶች መካከል ከፍተኛ የመወዛገቢያ ነጥብ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። ዲተርምኒስት ተብሎ በሚጠራው ጎራ ያሉት ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች መጋለጣችንን የሚወስነው ቁልፍ ነገር በራሂ (gene) ነው የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ሌሎች ደግሞ በሰው ልጅ ፓቶሎጂ ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወቱት አካባቢያችንና አኗኗራችን ናቸው በማለት ይከራከራሉ። ሁለቱም ወገኖች ሐሳባቸውን የሚደግፍ የጥናት ውጤትና አኃዛዊ መረጃ ከመጥቀስ ወደኋላ አይሉም። የሆነ ሆኖ ክርክሩ ቀጥሏል።

በጣም ታዋቂ የነበሩ ፈላስፎች የተናገሯቸው ሐሳቦች በጊዜው ምንም እንከን የሚወጣላቸው መስለው ባይታዩም ከጊዜ በኋላ አንድ በአንድ ስህተት መሆናቸው ተረጋግጧል። በርትረንድ ራስል የተባሉት ፈላስፋ አርስቶትልን “ከፈላስፎች ሁሉ ይበልጥ ተደማጭነት የነበረው ፈላስፋ” ሲሉ ጠርተውታል። ይሁንና ራስል ብዙዎቹ የአርስቶትል መሠረተ ትምህርቶች “ጨርሶ ሐሰት” እንደነበሩ አልሸሸጉም። “በዘመናዊው ዓለም ውስጥ በሳይንስ፣ በሎጂክ ወይም በፍልስፍና ረገድ የተገኘው እያንዳንዱ እድገት ከአርስቶትል ደቀ መዛሙርት ጋር ከባድ ትንቅንቅ ገጥሞታል።”​—⁠ሂስትሪ ኦቭ ዌስተርን ፊሎዞፊ

‘በሐሰት እውቀት የተባለ’

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እንደ ሶቅራጥስ፣ ፕላቶ እና አርስቶትል ካሉት ስመ ጥር የግሪክ ፈላስፎች ደቀ መዛሙርት መካከል ከብዙዎቹ ጋር ተገናኝተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በዘመኑ የነበሩት የተማሩ ሰዎች ከአብዛኞቹ ክርስቲያኖች የላቀ እውቀት እንዳላቸው አድርገው ያስቡ ነበር። “እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች” የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቁጥራቸው እምብዛም ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:​26) እንዲያውም የዘመኑን ፍልስፍና የተማሩ ሰዎች ክርስቲያኖች የሚያምኑበት ነገር “ሞኝነት” ወይም “የለየለት ቂልነት” እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር።​—⁠1 ቆሮንቶስ 1:​23 ፊሊፕስ

ከእነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች አንዱ ብትሆን ኖሮ በዘመኑ የምሁራን ቁንጮ የነበሩት ሰዎች በሚሰነዝሩት የሚያባብል መከራከሪያ ትመሰጥ ወይም በጥበባቸው ትደመም ነበርን? (ቆላስይስ 2:​4) እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አገላለጽ እንደዚያ የምታደርግበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም። ይሖዋ “የጥበበኞችን ጥበብ” እና “የአስተዋዮችንም ማስተዋል” የሚቆጥረው እንደ ሞኝነት ነው ሲል እነዚያን ክርስቲያኖች አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:​19) ‘የዚህ ዓለም ፈላስፎች፣ ጸሐፊዎችና ተቺዎች ጥበባቸውን ያሳዩበት ነገር የት አለ?’ ሲል ጠይቋል። (1 ቆሮንቶስ 1:​20 ፊሊፕስ ) በጳውሎስ ዘመን የነበሩት ፈላስፎች፣ ጸሐፊዎችና ተቺዎች የቱንም ያህል እውቀት ቢኖራቸው ለሰው ዘር ችግሮች ምንም ፋይዳ ያለው መልስ አላገኙም።

በመሆኑም ክርስቲያኖች ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በውሸት እውቀት የተባለ ክርክር’ ሲል ከጠራው ነገር መራቅን ተምረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​20) ጳውሎስ ይህንን እውቀት ‘ውሸት’ ሲል የጠራው አንድ መሠረታዊ ነገር ስለሚጎድለው ነው። ከአምላክ ዘንድ የሚጠቅሱት ምንም ዓይነት ማስረጃ ስለ ሌለ ንድፈ ሐሳባቸውን ማረጋገጥ አይቻልም። (ኢዮብ 28:​12፤ ምሳሌ 1:​7) ይህ መሠረታዊ ነገር የሚጎድላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በቀንደኛው አሳሳች በሰይጣን የታወሩ በመሆናቸው እንዲህ ያለውን እውቀት ሙጥኝ ያሉ ሰዎች እውነትን አገኛለሁ ብለው ፈጽሞ ተስፋ ሊያደርጉ አይችሉም።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​6-8, 14፤ 3:​18-20፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​4፤ 11:​14፤ ራእይ 12:​9

መጽሐፍ ቅዱስ—⁠በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መመሪያ

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አምላክ ፈቃዱን፣ ዓላማውንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደገለጠ ተጠራጥረው አያውቁም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) ይህም ‘እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል እንዳይማረኩ’ ጠብቋቸዋል። (ቆላስይስ 2:​8) ዛሬም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ግራ ከሚያጋቡና እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ የሰው ሐሳቦች በተቃራኒ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ለምናምንባቸው ነገሮች ጠንካራ መሠረት ይሆነናል። (ዮሐንስ 17:​17፤ 1 ተሰሎንቄ 2:​13፤ 2 ጴጥሮስ 1:​21) ይህ መመሪያ ባይኖር ኖሮ እንደ አሸዋ ወዲያና ወዲህ በሚዋልለው የሰው ልጅ ንድፈ ሐሳብና ፍልስፍና ላይ ጠንካራ ነገር ለመገንባት የመሞከርን ያህል ፍጹም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንወድቅ ነበር።​—⁠ማቴዎስ 7:​24-27

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘የሳይንስ እውነታዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት እንደሆነና በየጊዜው ከሚቀያየረው የሰው ልጅ ፍልስፍና የተሻለ ነገር እንደሌለው ማረጋገጣቸው የሚታበል ነገር ነውን?’ ይል ይሆናል። ለምሳሌ በርትራንድ ራስል “ኮፐርኒከስ፣ ኬልፐር እና ጋሊሊዮ ምድር የአጽናፈ ዓለም ዕምብርት አይደለችም የሚለውን አመለካከት ለማስረጽ ከአርስቶትል እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መታገል አስፈልጓቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ለምሳሌ ያህል ዛሬ ምድር በቢልዮን የሚቆጠሩ ዓመታት እንደኖረች የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች እያሉ ምድር ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደተፈጠረች መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል በማለት ክርኤሽኒስቶች ይከራከሩ የለምን?

እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ምድር የአጽናፈ ዓለሙ እምብርት ነች አይልም። ይህንን ትምህርት ያፈለቁት የአምላክን ቃል አጥብቀው የማይከተሉ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ናቸው። ስለ ፍጥረት ሥራ የሚገልጸው የዘፍጥረት ዘገባ ምድር በቢልዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ኖራለች የሚለውን ሐሳብ አይቃወምም። እንዲሁም እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን የ24 ሰዓት ጊዜ ነው የሚል ገደብ የለውም። (ዘፍጥረት 1:​1, 5, 8, 13, 19, 23, 31፤ 2:​3, 4) መጽሐፍ ቅዱስን በሐቀኝነት ስንመረምረው የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም “የለየለት ቂልነት” እንዳልሆነ በግልጽ መረዳት እንችላለን። እንዲያውም ከትክክለኛ ሳይንስ ጋር ፍጹም ተስማሚ ነው። a

‘የማመዛዘን ችሎታ’

ብዙዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተራ ሰዎችና ምናልባትም ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ የነበራቸው ወንዶችና ሴቶች ቢሆኑም ከአምላክ ያገኙት ሌላ እሴት ነበራቸው። የግል ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉም የማመዛዘንና የማሰብ ችሎታ ተሰጥቷቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹ ‘የማመዛዘን ችሎታቸውን’ ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ‘በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ፈትነው እንዲያውቁ’ አበረታቷቸዋል።​—⁠ሮሜ 12:​1, 2 NW 

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አምላክ የሰጣቸውን ‘የማመዛዘን ችሎታ’ በመጠቀም ከተገለጠው የአምላክ ቃል ጋር የማይጣጣም ማንኛውም ፍልስፍና ወይም ትምህርት ሁሉ ከንቱ እንደሆነ በግልጽ ተረድተው ነበር። በዘመኑ የነበሩ ጥበበኞች አምላክ እንዳለ የሚያስረዱትን በዙሪያቸው ያሉ ማስረጃዎች ቸል ብለው ‘እውነቱን ለመደበቅ’ ሞክረዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ” በማለት ጽፏል። ስለ አምላክና ስለ ዓላማው የሚናገረውን እውነት ለመቀበል እምቢተኞች በመሆናቸው “በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ።”​—⁠ሮሜ 1:​18-22፤ ኤርምያስ 8:​8, 9

ብዙውን ጊዜ ጥበበኞች ነን የሚሉ ሰዎች መጨረሻ ላይ የሚደርሱበት መደምደሚያ “አምላክ የለም” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስ የሚታመን መጽሐፍ አይደለም” ወይም “የምንኖረው ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት’ አይደለም” የሚል ነው። እንደነዚህ ያሉት ሐሳቦች “2=1” የማለት ያህል በአምላክ ዓይን ሞኝነት ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 3:​19) ሰዎች አለን ብለው የሚያስቡት ቦታ ምንም ይሁን ምን ከአምላክ ጋር የሚጋጩ፣ ቃሉን ችላ የሚሉና በደመ ነፍስ እንኳ የሚታወቁትን ነገሮች የማይቀበሉ ከሆነ የእነርሱን የመደምደሚያ ሐሳብ የግድ መቀበል አይኖርብህም። ለማጠቃለል ያህል በማንኛውም ጊዜ ‘ሰው ሁሉ ውሸተኛ ቢሆን እግዚአብሔር እውነተኛ’ ሆኖ እንዲገኝ ማድረግ የጥበብ ጎዳና ይሆናል።​—⁠ሮሜ 3:​4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ተጨማሪ ዝርዝር ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጁትን መጽሐፍ ቅዱስ —⁠የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? እና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባሉትን መጻሕፍት ተመልከት።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተለዋዋጭ ከሆነው የሰዎች ሐሳብ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ለምናምንባቸው ነገሮች ጠንካራ መሠረት ይሆነናል

[ምንጭ]

በስተግራ፣ ኤፊቆሮስ:- Photograph taken by courtesy of the British Museum; ከላይ ወደ መሃል፣ ፕላቶ:- National Archaeological Museum, Athens, Greece; በስተቀኝ፣ ሶቅራጥስ:- Roma, Musei Capitolini