ወዳጆች ማፍራት የምትችለው እንዴት ነው?
ወዳጆች ማፍራት የምትችለው እንዴት ነው?
“በሕይወት ዘመንህ አንድ ወዳጅ ማግኘት ከበቂ በላይ ነው፤ ሁለት ይበዛል፤ ሦስትማ ፈጽሞ አይታሰብም። —ሄንሪ ብሩክስ አዳምስ
እንዲህ ያሉት አስተያየቶች እውነተኛ ወዳጆች እንደልብ እንደማይገኙ ይጠቁማሉ። አብዛኛውን ጊዜ “የእኔ የምለው ሰው የለኝም፣” “ማንንም ማመን አልችልም፣” ወይም “የቅርብ ጓደኛዬ ውሻዬ ነው” እንደሚሉት ያሉት አስተያየቶች ወዳጆች ማግኘት ከሚፈልጉ በጣም ብቸኛ ሰዎች አንደበት በተደጋጋሚ ይሰማል።
ዘላቂ ወዳጅነት መመሥረትና ይህንንም ጠብቆ ማቆየት ፈታኝ ነገር ነው። አንድ ጥናት እንደጠቆመው “በዩናይትድ ስቴትስ 25 በመቶ የሚሆኑት ትልልቅ ሰዎች ‘ሥር በሰደደ ብቸኝነት’ የሚሰቃዩ ሲሆን . . . በፈረንሳይ ደግሞ ከጠቅላላው ሕዝብ ግማሽ የሚሆኑት ከባድ ራስን የማግለል ችግር ገጥሟቸዋል።” የጓደኛ አፈላላጊ ክበቦች፣ በመረጃ መረብ አማካይነት የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግባቸው ፕሮግራሞችና ለጓደኛ ፈላጊዎች የሚወጡት የጋዜጣ ማስታወቂያዎች መብዛታቸው ሰዎች ሰብዓዊ ግንኙነትን አጥብቀው እንደሚፈልጉ ያሳያል።
ኒውሮሳይኮሎጂስቱ ዶክተር ዴቪድ ዊክስ ብቸኝነት የአንድን ሰው አእምሮአዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ጤንነቱንም እንደሚጎዳ ተናግረዋል። “ብቸኞች ሊባሉ የሚችሉ የተጋነነ ፍርሃትና የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ብዙ ታካሚዎች አሉኝ። በከባድ የብቸኝነት ስሜትና በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት መካከል ቀጥተኛ ተዛማጅነት አለ።”
ፍቺና የቤተሰብ መፈራረስ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች ኑሮአቸውን በብቸኝነት እንዲገፉ አስገድዷቸዋል። በብሪታንያ የተካሄደ አንድ ጥናት በ21ኛው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ ከእንግሊዝ ሕዝብ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው አንድ ሰው ብቻ ባለባቸው ቤቶች ውስጥ ይኖራል ብሎ ነበር።
በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች “በመጨረሻው ቀን” የራስ ወዳድነት መንፈስ እንደሚሰፍን አስቀድመው ተናግረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ብዙዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ወዳጅነት ከመመስረት ይልቅ ትኩረት ያደረጉት እንደ ቤት ወይም መኪና በመሳሰሉት ቁሳዊ ነገሮችና በሥራቸው ላይ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። አንቶኒ ስቶር የተባሉት ደራሲ “ሕይወታቸው ያተኮረው በትዳር ጓደኞቻቸውና ልጆቻቸው ላይ መሆኑ ቀርቶ በሥራቸው ላይ ሆኗል” በማለት ተናግረዋል።
እውነተኛ ወዳጆች ዋጋቸው በገንዘብ አይተመንም
ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ከቻልክ ሕይወትህም የዚያኑ ያህል ጥሩ ይሆናል። ለራሳቸው ብቻ የሚኖሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ደስተኞች አይደሉም። ምክንያቱም ያሏቸውን ነገሮችም ሆነ ሐሳባቸውን የሚያካፍሏቸው ወዳጆች የሏቸውም። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW ] ነው” በማለት የተናገራቸው ቃላት እውነት ናቸው። (ሥራ 20:35) ይህንን እውነታ በማስተጋባት እንግሊዛዊው ባለቅኔ ጆርጅ ባይሮን “ደስታ ያገኙ ሁሉ ይህንን ደስታቸውን ለሌሎች ማካፈል አለባቸው” በማለት ጽፏል።
ታዲያ ወዳጅ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ መዝገበ ቃላት ወዳጅ የሚለውን ቃል “በፍቅር ወይም በአድናቆት ከሌላው ጋር የሚጣበቅ” ሲል ፈትቶታል። እውነተኛ ወዳጅ በመልካም ነገሮች ላይ እንድታተኩሩ ሊረዳችሁና በችግራችሁ ጊዜ ደግሞ ሊያበረታታችሁና ሊያንጻችሁ ይችላል። እንዲያውም የሐዘናችሁ ተካፋይ ሊሆን ይችላል። ንጉሥ ሰሎሞን “[“እውነተኛ፣” NW ] ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 17:17) ብዙውን ጊዜ ቁሳዊ ነገሮች ከጊዜ ብዛት ዋጋቸውን ሊያጡ ሲችሉ እውነተኛ ወዳጅነት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጠነከረ ይሄዳል።
ቅዱሳን ጽሑፎች ክርስቲያኖች ፍቅራቸውን እንዲያሰፉ “ተስፋፉ” በማለት አጥብቀው ይመክራሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:13) ከሌሎች ጋር ለመተዋወቅ መጣር ጥበብ ነው። በመክብብ 11:1, 2 ላይ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፣ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህና። ለሰባት ደግሞም ለስምንት እድል ፈንታን ክፈል፣ በምድር ላይ የሚሆነውን ክፉ ነገር ምን እንደ ሆነ አታውቅምና።” ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለወዳጅነት የሚሠራው እንዴት ነው? ከብዙ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ከመሠረትክ ችግሮች ሲያጋጥሙህ ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ሊደርሱልህ ይችላሉ።
እውነተኛ ወዳጆች በሌላም መንገድ ከለላ ናቸው። ምሳሌ 27:6 “የወዳጅ ማቁሰል የታመነ ነው” ይላል። ብዙ ሰዎች የሙገሳ ቃላት ሊያዥጎደጉዱልህ ቢችሉም ለአንተ ካላቸው አሳቢነት የተነሳ ያዩትን ከባድ ስህተት የሚነግሩህና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጠቃሚ ምክር የሚሰጡህ እውነተኛ ወዳጆች ብቻ ናቸው።—ምሳሌ 28:23
ጥሩ የሆኑ የቅርብ ወዳጆች በአንተ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ከሚችሉ ብርቅዬ ስጦታዎች መካከል ናቸው። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 10 ላይ ቆርኔሌዎስ በሚባል አንድ ሮማዊ የጦር መኮንን ሕይወት ውስጥ ስለተፈጸመ ሁኔታ እናነባለን። ያቀረባቸውን ጸሎቶች አምላክ እንደሰማቸው አንድ መልአክ ነግሮት ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚመጣ ጠብቆ ስለነበር “ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት [ጠራቸው]።” እነዚህ የቆርኔሌዎስ የቅርብ ወዳጆች ምሥራቹን ለመቀበልና በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት በአምላክ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ ለማግኘት ከበቁት የመጀመሪያዎቹ ያልተገረዙ አሕዛብ መካከል ነበሩ። ይህ ለቆርኔሌዎስ የቅርብ ወዳጆች ምንኛ ታላቅ በረከት ነው!—ሥራ 10:24, 44
ታዲያ ወዳጆች ማፍራት የምትችለው እንዴት ነው? ስለ ወዳጅነት ብዙ የሚናገረው መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ ምክሮች በመስጠት ይህንን
ጥያቄ ይመልሳል። (ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።)እውነተኛ ወዳጆች ማግኘት የምትችለው የት ነው?
እውነተኛ ወዳጆች ማግኘት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው ቦታ የክርስቲያን ጉባኤ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ፈጣሪህና የሰማዩ አባትህ ከሆነው ከይሖዋ እንዲሁም አዳኝህ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነት ለመመስረት ያለህን አጋጣሚ ልትጠቀምበት ትችላለህ። ወዳጁ እንድትሆን የጋበዘህ ኢየሱስ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:13, 15) ከይሖዋና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነት ከመሰረትክ እነርሱ “በዘላለም ቤቶች” እንደሚቀበሉህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። አዎን፣ ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት መመስረት ማለት የዘላለም ሕይወት ማግኘት ማለት ነው።—ሉቃስ 16:9፤ ዮሐንስ 17:3
የእነርሱን ሞቅ ያለ ወዳጅነት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? የይሖዋ ወዳጅ በመሆን በድንኳን ውስጥ ከሚያድሩት እንግዶች መካከል አንዱ ለመሆን የሚያስፈልጉት ብቃቶች በመዝሙር 15 ላይ ተዘርዝረዋል። መጽሐፍ ቅዱስህን አውጣና አምስቱንም ቁጥሮች አንብብ። በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 15:14
አዎን፣ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ በጥንቃቄ ስታጠናና ተግባራዊ ስታደርግ የይሖዋና የኢየሱስ ወዳጅ መሆን እንደምትፈልግ ታሳያለህ። ይህን ፍላጎትህን ዳር ለማድረስ የይሖዋ አምላክ እውቀት በሚተላለፍባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ
አዘውትረህ መገኘትም ይኖርብሃል። ይሖዋን ለማዳመጥ በታማኝነት ጥረት ባደረግህ መጠን ይበልጥ ወደ እርሱና ወደ ልጁ ትቀርባለህ።በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ ይሖዋን ከሚወዱና በሕይወታቸው ውስጥ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት የመሳሰሉትን የመንፈስ ፍሬዎች ከሚያንጸባርቁ ግለሰቦች ጋር መተዋወቅ ትችላለህ። (ገላትያ 5:22, 23) ወዳጆች በማፍራት ብቸኝነትን ለማስወገድ ልባዊ ፍላጎት ካለህ በየሳምንቱ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኝ። እንዲህ ካደረግህ ከተባረኩት የአምላክ ሕዝቦች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመስረት በሚያስችልህ ትክክለኛ ጊዜና ቦታ ላይ ትገኛለህ ማለት ነው።
የዘላለም ወዳጆች
እውነተኛ ወዳጅነት ከይሖዋ አምላክ የሚገኝ ድንቅ ስጦታ ነው። ይህም ከራሱ ከይሖዋ ባሕርይ የሚመነጭ ነገር ነው። አፍቃሪና ለጋስ ከመሆኑ የተነሣ ምድር ለአንተ ወዳጅ ሊሆኑ በሚችሉ የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጡራን እንድትሞላ አድርጓል። ከክርስቲያን ባልንጀሮችህ ጋር ተቀራረብ። አበረታታቸው። በአገልግሎት አብረሃቸው ተካፈል። ከእነርሱ ጋርም ሆነ ስለ እነርሱ አዘውትረህ ጸልይ። እንዲህ ካደረግህ ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እየመሰልካቸው ነው።
ወዳጅነት ማንኛውም ሰው ሊሰጠውና ሊቀበለው የሚችለው ስጦታ ነው። በቅርቡ ብዙ የተለያዩ ወዳጆች ለማፍራት የሚያስችልህ ሰፊ አጋጣሚ ታገኛለህ። አሁን ካሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በሞት አንቀላፍተው “ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” የሚባልበትን የትንሣኤ ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ካሉት ያለፉ ትውልዶች ጋር እንኳ ሳይቀር ወዳጅነት መመስረት ትችላለህ። (ራእይ 21:4፤ ዮሐንስ 5:28, 29) እስከዚያው ግን ተግባቢ ለመሆን ጥረት አድርግ። ይሖዋን ከሚወዱ ጋር ተወዳጅ። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በማዳመጥ ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነት ለመመስረት ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ብቸኝነትን ለዘላለም አሸንፈህ ትኖራለህ።
[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚረዱ ስድስት ነጥቦች
1. ወዳጅ ሁን። አብርሃም በማያወላውለው እምነቱ ምክንያት “የእግዚአብሔር ወዳጅ” ተብሏል። (ያዕቆብ 2:23) ይሁን እንጂ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገ ሌላም ነገር ነበር። አብርሃም ለአምላክ ያለውን ፍቅር እንዳሳየ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ዜና መዋዕል 20:7) ቅድሚያውን በመውሰድ ስሜቱን ለይሖዋ ገልጿል። (ዘፍጥረት 18:20-33) አዎን፣ ወዳጅ መሆንህን የሚሳይ ነገር ለማድረግ ቀዳሚ መሆን ይኖርብሃል። ኢየሱስ “ስጡ ይሰጣችሁማል” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 6:38) የሚያበረታታ ቃል ጣል ማድረግ ወይም በሚያስፈልገው ነገር ማገዝ የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል። አሜሪካዊው ጸሐፊ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር:- “ወዳጅ ለማግኘት ብቸኛው መንገድ ወዳጅ ሆኖ መገኘት ነው።”
2. ወዳጅነት ለማዳበር ጊዜ ዋጅ። አብዛኞቹ ሰዎች ከወዳጅነት የሚገኙትን ጥቅሞች ለማግኘት ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ለዚህ የሚያስፈልገውን ጊዜ አይዋጁም። ሮሜ 12:15, 16 የሌሎችን ደስታና ስኬት፣ ሐዘንና ብስጭት እንድንካፈል ያበረታታናል። እንዲህ ይላል:- “ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፣ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ።” ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ይበዛበት የነበረ ቢሆንም ሁልጊዜ ለወዳጆቹ ጊዜ ይመድብ ነበር። (ማርቆስ 6:31-34) ወዳጅነት ልክ አበባ እንደሚያወጣ ተክል ነው። እንዲፈካ ከተፈለገ ውኃ መጠጣትና ምግብ ማግኘት እንዳለበት አስታውስ። ይህ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል።
3. ሌሎች ሲናገሩ በትኩረት አዳምጥ። ብዙውን ጊዜ ንቁ ሆነው የሚከታተሉ ጥሩ አዳማጮች ወዳጅ ለማግኘት አይቸገሩም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ይሁን” በማለት ተናግሯል። (ያዕቆብ 1:19) ከሌሎች ጋር ስትነጋገር ለስሜታቸው እንደምታስብላቸው አሳይ። ስለ ራሳቸው እንዲናገሩ አበረታታቸው። ለእነርሱ አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ ሁን። (ሮሜ 12:10) እንዲህ ካደረግህ ከአንተ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። በሌላ በኩል ግን ሁልጊዜ እኔ ብቻ ልናገር የምትል ወይም ሁልጊዜ የሰዎች ትኩረት በአንተ ላይ እንዲያርፍ የምታደርግ ከሆነ ሊያዳምጥህ የተዘጋጀ ወይም ስለ ስሜትህና ስለሚያስፈልጉህ ነገሮች የሚጨነቅ ሰው ማግኘት ቀላል አይሆንም።
4. ይቅር ባይ ሁን። ኢየሱስ በአንድ ወቅት “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት [“ሰባ ሰባት ጊዜ፣” NW ] ይቅር ለማለት እንዲዘጋጅ ጴጥሮስን መክሮታል። (ማቴዎስ 18:21, 22) እውነተኛ ወዳጅ ጥቃቅን ስህተቶችን ለማለፍ ፈጣን ነው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንዳንዶች ጥቃቅን ፍሬዎች ስላሉት ዘይቱን መብላት አይወዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህንን የፍራፍሬ ዓይነት የሚወዱ ሰዎች በውስጡ ያሉትን ጥቃቅን ፍሬዎች አያስተውሏቸውም። እውነተኛ ወዳጆች ባሏቸው ጥሩ ባሕርያት ይወደዳሉ፤ ጥቃቅን ጉድለቶቻቸው ግን አይታሰቡም። ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ . . . [“በነጻ፣” NW ] ይቅር ተባባሉ” በማለት አጥብቆ መክሮናል። (ቆላስይስ 3:13) ይቅር ባይነትን የተማሩ ሰዎች ወዳጅነታቸውን ዘላቂ ማድረግ ይችላሉ።
5. የሌሎችን ነጻ ጊዜ አክብር። ወዳጆችህን ጨምሮ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ነጻ ጊዜ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ምሳሌ 25:17 “እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር” በማለት ጥበብ ያለበት ምክር ይሰጣል። በመሆኑም ወዳጆችህን ለመጠየቅ በየስንት ጊዜው ትሄዳለህ? ከሄድክስ ምን ያህል ትቆያለህ? በሚለው ጉዳይ ረገድ ሚዛናዊ ሁን። ወደ ቅንዓት ሊመራ የሚችለውን የእኔ ጓደኛ ብቻ ይሁን የሚለውን መንፈስ አስወግድ። በአንዳንድ ነገሮች ረገድ ያለህን የግል አመለካከት እና አስተያየት ስትገልጽ አስተዋይ ሁን። ይህ ሞቅ ያለና አስደሳች የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
6. ለጋስ ሁን። ልግስና በማሳየት ወዳጅነቶች ይጠነክራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ልንረዳና ልናካፍል የተዘጋጀን እንድንሆን’ መክሮናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:18) ለምሳሌ የሚያበረታቱ ቃላት አካፍላቸው። (ምሳሌ 11:25) ልባዊ ምስጋና ለማቅረብና የሚያንጽ ሐሳብ ለመስጠት አታመንታ። ለሌሎች ደህንነት ልባዊ አሳቢነት ስታሳይ እነርሱም ወደ አንተ ለመቅረብ ይገፋፋሉ። እነርሱ ሊያደርጉልህ በሚችሉት ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ አንተ ምን ልታደርግላቸው እንደምትችል አስብ።