በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ለሕዝቡ ዕረፍት ይሰጣል

ይሖዋ ለሕዝቡ ዕረፍት ይሰጣል

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

ይሖዋ ለሕዝቡ ዕረፍት ይሰጣል

በተራራማ መንገድ ላይ ለሚጓዝ በድካም የዛለ መንገደኛ ጥላ ያለበት የማረፊያ ቦታ ማግኘት ትልቅ ነገር ነው። ኔፓል ውስጥ እንዲህ ያሉት የማረፊያ ቦታዎች ቻውቴሬ በመባል ይታወቃሉ። ዓይነተኛውን ቻውቴሬ ጥቅጥቅ ካለው የባንያን ዛፍ አጠገብ ማግኘት ይቻላል። ቻውቴሬ ማዘጋጀት የደግነት ተግባር ሲሆን ይህንን የሚያደርጉ አብዛኞቹ ሰዎች እነማን እንደሆኑ እንኳ አይታወቅም።

ይሖዋ አምላክ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ በድካም ለዛሉ ብዙ “መንገደኞች” የደስታና የመንፈሳዊ ዕረፍት ምንጭ የሆነላቸው እንዴት እንደሆነ ከኔፓል የተገኙት ተሞክሮዎች ያሳያሉ።​—⁠መዝሙር 23:​2

• ሊል ኩሜሪ የምትኖረው በበረዶ የተሸፈኑትን የሂማልያ ተራሮች አስገራሚ እይታ መቃኘት በምትችልበት በውቧ ፖከራ ከተማ ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ ሊል ስለ ቤተሰቧ የገቢ ምንጭ ስትጨነቅ የወደፊቱ ጊዜ ጭልም ብሎባት ነበር። አንዲት የይሖዋ ምሥክር ስታነጋግራት መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ብሩሕ የወደፊት ተስፋ በመነካቷ ወዲያው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ጠየቀች።

ሊል ኩሜሪ በጥናቱ ብትደሰትም ከባድ የቤተሰብ ተቃውሞ ስላጋጠማት ጥናቱን መቀጠሉ ቀላል አልሆነላትም። ሆኖም ተስፋ አልቆረጠችም። አዘውትራ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት በተለይ ስለ ሚስት ተገዥነት የተማረቻቸውን ነገሮች ተግባራዊ ታደርግ ነበር። ከዚህ የተነሣ ባሏና እናቷ የእርሷ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት መላውን ቤተሰብ እንደጠቀመ ተገነዘቡ።

በአሁኑ ጊዜ ባሏን ጨምሮ በርካታ ዘመዶቿ የአምላክን ቃል በማጥናት ላይ ሲሆኑ በቅርቡ ፖከራ ውስጥ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ከ15 ዘመዶቿ ጋር ተገኝታለች። እንዲህ አለች:- “በአሁኑ ጊዜ ቤተሰቤ በእውነተኛው አምልኮ አንድ በመሆኑ ቤቴ የእረፍት ቦታ ሆኗል። እውነተኛ የአእምሮ ሰላም አግኝቻለሁ።”

• ኔፓል ውስጥ የመደብ ልዩነት በሕግ የተከለከለ ነገር ቢሆንም በሕዝቡ አኗኗር ላይ ግን አሁንም ድረስ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እኩልነትንና ከአድሎ ነጻ መሆንን አስመልክቶ የሚናገረው ነገር የብዙዎቹን ትኩረት ስቧል። ሱሪያ ማያ አምላክ ‘ለሰው ፊት እንደማያዳላ’ ማወቋ የእርሷንና የቤተሰቧን ሕይወት በእጅጉ ለውጦታል።​—⁠ሥራ 10:​34

ሱሪያ ማያ በምታየው ፍትሕ የጎደለው የመደብ ልዩነትና ሥር የሰደዱ ወጎችና ልማዶች ባመጡት ሸክም ሳቢያ በጭንቀት ተውጣ ነበር። ሱሪያ ማያ የአምልኮ ፍቅር ያላት ሴት ስለሆነች እርዳታ ለማግኘት የጣዖት አማልክቷን ለዓመታት ስትማጸን ቆይታለች። ይሁን እንጂ ያቀረበቻቸው ጸሎቶች መልስ አላገኙም። አንድ ቀን እንዲሁ ስትጸልይ የልጅ ልጅዋ የሆነችው የስድስት ዓመቷ ባቢታ አየቻትና ወደ እርሷ ቀርባ “ምንም ማድረግ የማይችሉትን ጣዖታት የምትለምኚው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀቻት።

የባቢታ እናት ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ ነበር። ባቢታ አያቷ በአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ በጋለ ስሜት ጋበዘቻት። ሱሪያ ማያ በስብሰባው ላይ ተገኝታ የተለያየ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ያላንዳች ልዩነት አብረው ሲደሰቱ በመመልከቷ በአድናቆት ተሞላች። ወዲያው የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ጠየቀች። ከዚህ የተነሣ ጓረቤቶቿ አገለሏት። ሆኖም ተስፋ አልቆረጠችም። ውስን የነበረው የማንበብና የመጻፍ ችሎታዋም ቢሆን መንፈሳዊ እድገት ከማድረግ አላገዳትም።

ከስምንት ዓመታት በኋላ ዛሬ ባሏንና ሦስት ልጆቿን ጨምሮ ስድስት የቤተሰቧ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ ሱሪያ ማያ በዘወትር አቅኚነት ሙሉ ጊዜ እያገለገለች ሲሆን ሌሎች ከባድ ሸክሞቻቸውን ይሖዋ ብቻ በሚያዘጋጀው እውነተኛ የዕረፍት ቦታ እንዲያራግፉ በደስታ በመርዳት ላይ ትገኛለች።