በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል

ይሖዋ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል

ይሖዋ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል

“[ይሖዋ ] ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።”​—⁠ኢሳይያስ 40:​29

1. አምላክ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ የሚንጸባረቀውን ኃይል በምሳሌ አስረዳ።

 ይሖዋ ያለው ኃይል ወሰን የለውም። በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ የሚንጸባረቀውም ኃይል እጅግ ታላቅ ነው! ማንኛውም ነገር የተገነባው ደቃቅ ከሆነችው አቶም ሲሆን አንዷ አቶም ኢምንት ከመሆኗ የተነሣ በአንድ ጠብታ ውኃ ውስጥ ብቻ አንድ መቶ ቢልዮን ቢልዮን አቶሞች ይገኛሉ። a በምድራችን ላይ ያለው ሕይወት በአጠቃላይ ሕልውናው የተመካው በፀሐይ ላይ በሚካሄደው የአቶሚክ ኃይል አፀግብሮት ላይ ነው። ይሁንና በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ለማቆየት የሚያስፈልገው የፀሐይ ኃይል መጠን ምን ያህል ነው? ፀሐይ ከምታመነጨው ከጠቅላላው የኃይል መጠን ውስጥ ምድር የምታገኘው ቅንጣት ታክሉን ብቻ ነው። ያም ሆኖ ወደ ምድር የሚደርሰው በጣም አነስተኛ መጠን ያለው የፀሐይ ኃይል በምድራችን ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በጠቅላላ ከሚጠቀሙት ኃይል አንጻር ሲታይ እጅግ ከፍተኛ ነው።

2. ኢሳይያስ 40:​26 የይሖዋን ኃይል በተመለከተ ምን ይላል?

2 ስለ አቶምም ሆነ ሰፊ ስለሆነው አጽናፈ ዓለም ስናስብ ታላቅ በሆነው የይሖዋ ኃይል መደመማችን አይቀርም። ይሖዋ “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት [“በብርታቱ ታላቅነት፣” NW ] አንድስ እንኳ አይታጣውም” በማለት መናገሩ ምንም አያስገርምም! (ኢሳይያስ 40:​26) አዎን፣ የይሖዋ ‘ብርታት ታላቅ’ ነው። እንዲሁም መላውን አጽናፈ ዓለም ለመፍጠር የተጠቀመበት ‘የከፍተኛ ኃይል’ ባለቤት ነው።

ከወትሮው የተለየ ኃይል ያስፈልጋል

3, 4. (ሀ) እንድንደክም ሊያደርጉን የሚችሉት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የትኛው ጥያቄ ነው?

3 የአምላክ ኃይል ውስን አይደለም። ሰዎች ግን ይደክማሉ። በሄድንበት ሁሉ የድካም ስሜት የሚነበብባቸው ሰዎች እናያለን። ድካማቸው ሳይለቅቃቸው ከእንቅልፍ ይነቃሉ፣ እንደ ደከማቸው ወደ ሥራ ወይም ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፣ ደክሟቸው ወደ ቤት ይመለሳሉ፣ ደክሟቸው ብቻ ሳይሆን ኃይላቸው ሁሉ ተሟጥጦ ይተኛሉ። አንዳንዶች እንዲያውም አንድ ቦታ ሄደው ከድካማቸው መገላገልን ይመኛሉ። የይሖዋ አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን ለአምላክ ያደርን በመሆን የምንመራው ሕይወት ተጋድሎ ስለሚጠይቅ እኛም እንደክማለን። (ማርቆስ 6:​30, 31፤ ሉቃስ 13:​24፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​8) ኃይላችንን የሚያሟጥጡ ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ።

4 ክርስቲያኖች ብንሆንም በአጠቃላይ ሰዎች ከሚገጥማቸው ችግር ነፃ አይደለንም። (ኢዮብ 14:​1) ሕመም፣ የገንዘብ ችግር ወይም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ሌሎች የተለመዱ ዓይነት ችግሮች ተስፋ ሊያስቆርጡንና ሊያደክሙን ይችላሉ። ከእነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች በተጨማሪ ደግሞ ለጽድቅ ሲሉ በሚሰደዱ ሰዎች ላይ ብቻ የሚደርሱ ፈተናዎችም አሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:​12፤ 1 ጴጥሮስ 3:​14) በየዕለቱ ዓለም በሚያሳድርብን ተጽዕኖና በመንግሥቱ የስብከት ሥራችን ላይ በሚነሣው ተቃውሞ ምክንያት አንዳንዶቻችን እጅግ ከመዳከማችን የተነሳ በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገውን እንቅስቃሴ መቀነስ እንዳለብን ይሰማን ይሆናል። ከዚህም በላይ ሰይጣን ዲያብሎስ ለአምላክ ያለንን የጸና አቋም እንድናላላ ለማድረግ ያገኘውን ዘዴ ሁሉ ይጠቀማል። እንግዲያው በመታከት ሩጫችንን እንዳናቆም አስፈላጊውን መንፈሳዊ ጥንካሬ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

5. ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ለማከናወን ሰብዓዊ ብርታት ብቻውን በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው?

5 መንፈሳዊ ኃይል ለማግኘት መታመን ያለብን እጅግ ታላቅ ኃይል ባለው ፈጣሪ በይሖዋ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያናዊው አገልግሎት ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች አቅም ብቻ የሚሠራ ነገር እንዳልሆነ ተናግሯል። “የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምድራዊ ተስፋ ካላቸው ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን ‘የማስታረቁን አገልግሎት’ በማከናወን ላይ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 5:​18፤ ዮሐንስ 10:​16፤ ራእይ 7:​9) እኛ ፍጹማን ያልሆንን ሰዎች ይህን አምላክ የሰጠንን ሥራ የምንሠራው በተቃውሞ መካከል ቢሆንም ሥራው በራሳችን ብርታት የሚከናወን አይደለም። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ስለሚረዳን የእኛ ድካም የኃይሉን ታላቅነት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ይሆናል። “እግዚአብሔር ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል” የሚለው ማረጋገጫ ምንኛ የሚያጽናና ነው!​—⁠መዝሙር 37:​17

‘ይሖዋ ኃይላችን ነው’

6. ይሖዋ የብርታታችን ምንጭ መሆኑን ቅዱሳን ጽሑፎች የሚያረጋግጡልን እንዴት ነው?

6 ሰማያዊው አባታችን ‘ታላቅ ብርታት’ ያለው በመሆኑ እኛንም በቀላሉ ሊያበረታን ይችላል። እንዲያውም እንዲህ የሚል እናነባለን:- “[ይሖዋ] ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፣ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።” (ኢሳይያስ 40:​29-31) በየጊዜው በሚደርስብን ተጽዕኖ ምክንያት አንዳንድ ጊዜ እግሮቹ ዝለው ሰውነቱን መሸከም እንዳቃተው ሯጭ ልንሆን ብንችልም ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ የመጨረሻ መስመር ላይ ደርሰናል። ተስፋ ቆርጠን ሩጫችንን ማቆም አይኖርብንም። (2 ዜና መዋዕል 29:​11) “እንደሚያገሣ አንበሳ” እየዞረን ያለው ባላጋራችን ዲያብሎስ ሊያስቆመን ይፈልጋል። (1 ጴጥሮስ 5:​8) ‘ይሖዋ ኃይላችንና ጋሻችን’ መሆኑን እናስታውስ። ‘ለደከሙት ኃይል ለመስጠት’ ብዙ ዝግጅቶች አድርጓል።​—⁠መዝሙር 28:​7

7, 8. ይሖዋ ዳዊትን፣ ዕንባቆምንና ጳውሎስን እንዳበረታቸው ምን ማረጋገጫ አለን?

7 ዳዊት የሚያጋጥሙትን ከባድ እንቅፋቶች ማሸነፍ ይችል ዘንድ ይሖዋ ጥንካሬ ሰጥቶታል። በመሆኑም ዳዊት በሙሉ እምነትና ትምክህት “በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን፤ እርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 60:​12) ዕንባቆምም የነቢይነት ሥራውን መፈጸም ይችል ዘንድ ይሖዋ ኃይል ሰጥቶታል። ዕንባቆም 3:​19 እንዲህ ይላል:- “ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።” “ኃይልን በሚሰጠኝ በ[አምላክ] ሁሉን እችላለሁ” ሲል የጻፈው የጳውሎስ ምሳሌም ልብ ሊባል የሚገባው ነው።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​13

8 አምላክ ዳዊትን፣ ዕንባቆምንና ጳውሎስን እንዳበረታቸው ሁሉ እኛንም ሊያበረታንና በኃይሉም ተጠቅሞ ሊያድነን እንደሚችል እምነት ሊኖረን ይገባል። ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ‘የታላቅ ኃይል’ ምንጭ እንደሚሆንልን በመገንዘብ አምላክ ካደረጋቸው የተትረፈረፉ ዝግጅቶች መንፈሳዊ ኃይል ማግኘት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመርምር።

ኃይል የምናገኝባቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች

9. ክርስቲያናዊ ጽሑፎች እኛን በመገንባት ረገድ የሚጫወቱት ሚና ምንድን ነው?

9 በክርስቲያናዊ ጽሑፎች እየታገዙ ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ማጥናት ኃይል የሚሰጥና ወደፊት መጓዛችንን እንድንቀጥል የሚረዳ ነው። መዝሙራዊው እንደሚከተለው ሲል ዘምሯል:- “ምስጉን ነው . . . በእግዚአብሔር ሕግ ደስ [የሚለው]፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋንም በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” (መዝሙር 1:​1-3) አካላዊ ጥንካሬያችንን ለመጠበቅ ስንል መመገብ እንደሚኖርብን ሁሉ መንፈሳዊ ጥንካሬያችንንም ለመጠበቅ አምላክ በቃሉና በክርስቲያናዊ ጽሑፎች አማካኝነት የሚያቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ይኖርብናል። እንግዲያው ትርጉም ያለው ጥናትና ማሰላሰል የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ናቸው።

10. ለጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ የምናገኘው መቼ ሊሆን ይችላል?

10 በእርግጥም ‘በአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ ላይ ማሰላሰል የሚክስ ነገር ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:​10) ይሁን እንጂ ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ ማግኘት የምንችለው መቼ ነው? የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ “በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር።” (ዘፍጥረት 24:​63-67) መዝሙራዊው ዳዊት ‘ሌሊቱን ስለ አምላክ ያሰላስል ነበር።’ (መዝሙር 63:​6 የ1980 ትርጉም ) የአምላክን ቃል ጠዋት፣ ምሽት ላይ፣ ሌሊት ማለትም በማንኛውም ጊዜ ልናጠና እና በዚያ ላይ ልናሰላስል እንችል ይሆናል። እንዲህ ያለው ጥናትና ማሰላሰል ይሖዋ ኃይል ወደሚሰጥበት ወደ ሌላኛው ዝግጅት ማለትም ወደ ጸሎት ይመራናል።

11. አዘውትሮ የመጸለዩ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?

11 አዘውትረን ወደ አምላክ መጸለያችን ኃይል እንድናገኝ ይረዳናል። እንግዲያው ‘በጸሎት እንጽና።’ (ሮሜ 12:​12) አንዳንድ ጊዜ አንድን ፈተና ለመቋቋም የሚያስፈልገንን ጥበብና ጥንካሬ ለማግኘት ይህንኑ ጉዳይ ለይተን በመጥቀስ መጸለይ ያስፈልገናል። (ያዕቆብ 1:​5-8) የአምላክ ዓላማ ሲፈጸም ስናይ ወይም በአገልግሎቱ ለመቀጠል የሚያስችል ብርታት እንደሰጠን ስናስተውል ለአምላክ ምስጋናና ውዳሴ እናቅርብ። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) በጸሎት ወደ ይሖዋ ከተጠጋን ፈጽሞ አይተወንም። መዝሙራዊው “እነሆ፣ እግዚአብሔር ይረዳኛል” ሲል ጸልዮአል።​—⁠መዝሙር 54:​4

12. አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መለመን የሚኖርብን ለምንድን ነው?

12 ሰማያዊው አባታቸን በቅዱስ መንፈሱ ወይም በአንቀሳቃሽ ኃይሉ አማካኝነት ያበረታናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለዚህ ምክንያት . . . ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ . . . እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ።” (ኤፌሶን 3:​14-16) ይሖዋ መንፈሱን በመስጠት እንደሚባርከን ሙሉ እምነት ኖሮን መንፈሱን ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። ኢየሱስ አንድ ልጅ ዓሣ ቢጠይቅ አፍቃሪ የሆነ አባት እባብ ይሰጠዋልን? ሲል ጠይቋል። በፍጹም አያደርገውም። ከዚህ በመነሳት እንደሚከተለው በማለት ደምድሟል:- “እንኪያስ እናንተ [ኃጢአተኞችና አነሰም በዛ] ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” (ሉቃስ 11:​11-13) እንዲህ ዓይነት ትምክህት ኖሮን እንጸልይ። እንዲሁም የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች መንፈሱ በሚሰጣቸው ኃይል ‘እንደሚጠነክሩ’ ፈጽሞ አንዘንጋ።

ጉባኤ የብርታት ምንጭ ነው

13. ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?

13 ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ በሚደረጉት ስብሰባዎች አማካኝነት ኃይል ይሰጠናል። ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 18:​20) ኢየሱስ ይህንን የተስፋ ቃል ሲሰጥ እየተናገረ የነበረው በጉባኤ ውስጥ በግምባር ቀደምትነት የሚያገለግሉትን ወንዶች ትኩረት ስለሚሻ ጉዳይ ነበር። (ማቴዎስ 18:​15-19) ይሁን እንጂ ይህ አባባሉ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በእርሱ ስም በሚቀርቡ ጸሎቶች ተጀምረው ለሚደመደሙት ለሁሉም የጉባኤ፣ የልዩና የወረዳ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎቻችን ይሠራል። (ዮሐንስ 14:​14) በመሆኑም በስብሰባው ላይ የሚገኙት ጥቂቶችም ሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በእነዚህ ዓይነት ስብሰባዎች ላይ መካፈል ትልቅ መብት ነው። እንግዲያውስ ለእኛ መንፈሳዊ ጥንካሬ ለመስጠትና እኛን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለማነቃቃት ተብለው ለተዘጋጁት ለእነዚህ አጋጣሚዎች ያለንን የአመስጋኝነት ስሜት እናሳይ።​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 15

14. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከሚያደርጉት ጥረት ምን ጥቅም እናገኛለን?

14 ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታና ማበረታቻ ይሰጣሉ። (1 ጴጥሮስ 5:​2, 3) ጳውሎስ፣ ዛሬ ያሉት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንደሚያደርጉት ሁሉ ያገለግላቸው የነበሩትን ጉባኤዎች ይረዳና ያበረታታ ነበር። እንዲያውም እርስ በርስ ሊተናነጹና ሊበረታቱ ይችሉ ዘንድ የእምነት ባልደረቦቹን ለማየት ይናፍቅ ነበር። (ሥራ 14:​19-22፤ ሮሜ 1:​11, 12) እኛን በመንፈሳዊ በማበርታት በኩል ትልቅ ሚና ለሚጫወቱት የጉባኤ ሽማግሌዎቻችንም ሆነ ለሌሎች ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ዘወትር አድናቆት እናሳይ።

15. ጉባኤ ውስጥ ያሉት የእምነት አጋሮቻችን ‘የብርታት ምንጭ’ የሚሆኑልን እንዴት ነው?

15 በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ የእምነት አጋሮቻችንም ‘የብርታት ምንጭ’ ሊሆኑልን ይችላሉ። (ቆላስይስ 4:​10, 11 NW ) ‘እውነተኛ ወዳጆች’ እንደመሆናቸው መጠን በችግራችን ጊዜ ሊረዱን ይችላሉ። (ምሳሌ 17:​17) ለምሳሌ ያህል 220 የሚሆኑ የአምላክ አገልጋዮች በናዚ ጠባቂዎች ታጅበው በ1945 ከሳክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ በወጡ ጊዜ ከፊታቸው የ200 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ ይጠብቃቸው ነበር። በቡድን ሆነው ሲጓዙ ጠንከር ጠንከር ያሉት ደካማዎቹን በትናንሽ ጋሪዎች ላይ አስቀምጠው ይጎትቷቸው ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ከ10, 000 የሚበልጡ እስረኞች ባለቁበት በዚያ የሞት ጉዞ አንድም የይሖዋ ምሥክር አልሞተም። የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ እና የይሖዋ ምሥክሮች —⁠የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የተባሉትን መጻሕፍት ጨምሮ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ የሚወጡት እነዚህን የመሳሰሉ ዘገባዎች አምላክ ሕዝቦቹ እንዳይታክቱ ለመርዳት ኃይል እንደሚሰጣቸው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው።​—⁠ገላትያ 6:​9 b

ከመስክ አገልግሎታችን ኃይል ማግኘት

16. አዘውትሮ በአገልግሎቱ ተሳትፎ ማድረግ መንፈሳዊነታችንን የሚያጠናክረው እንዴት ነው?

16 በመንግሥቱ የስብከት ሥራ አዘውትሮ መሳተፍ መንፈሳዊ ጥንካሬ ይሰጠናል። እንዲህ ያለው ሥራ በአምላክ መንግሥት ላይ እንድናተኩር እንዲሁም ዘላለማዊነትንና ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን በረከቶች ዘወትር እንድናስብ ያደርገናል። (ይሁዳ 20, 21) በአገልግሎታችን ለሌሎች የምንናገረው በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የሰፈረው የተስፋ ቃል ተስፋ እንዲኖረን ከማድረጉም ሌላ “ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፣ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን” እንዳለው እንደ ነቢዩ ሚክያስ ቁርጥ ያለ አቋም እንድንይዝ ሊያደርገን ይችላል።​—⁠ሚክያስ 4:​5

17. የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በተመለከተ ምን ሐሳብ ተሰጥቷል?

17 ሌሎችን ለማስተማር በቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ በተጠቀምን መጠን ከይሖዋ ጋር ያለን የግል ዝምድናም የዚያኑ ያህል እየጠነከረ ይሄዳል። ለምሳሌ ያህል ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል አንዳንዶቹን እያወጡ ማንበብና በእነዚያ ላይ መወያየቱ ጥበብ ይሆናል። ይህ ተማሪውን የሚጠቅም ከመሆኑም በተጨማሪ የእኛንም መንፈሳዊ ግንዛቤ ያሳድግልናል። ተማሪው አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ወይም ምሳሌ መረዳት ከከበደው አንዱን የእውቀት መጽሐፍ ምዕራፍ ለመሸፈን ከአንድ ጊዜ በላይ የጥናት ክፍለ ጊዜ መመደብ ሊያስፈልግ ይችላል። ሌሎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት ስንል ጥሩ ዝግጅትና ተጨማሪ ጥረት ማድረግ በመቻላችን ምንኛ ደስተኞች ነን!

18. የእውቀት መጽሐፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት እየተሠራበት እንዳለ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

18እውቀት መጽሐፍ ቀደም ሲል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ ያልነበራቸውን ሰዎች ጨምሮ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለመርዳት ውጤታማ በሆነ መንገድ እያገለገለ ነው። ለምሳሌ ያህል በስሪላንካ የሚገኝ አንድ የሂንዱ እምነት ተከታይ ልጅ ሳለ አንዲት ምሥክር ስለ ገነት ስትናገር ጆሮው ውስጥ ጥልቅ ይላል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ያነጋግራትና ከባሏ ጋር ማጥናት ይጀምራል። እንዲያውም በየቀኑ ያጠና ስለነበር የእውቀት መጽሐፍን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አጠናቀቀ። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ከዚያም ከቀድሞ ሃይማኖቱ ጋር ያለውን ማንኛውንም ግንኙነት አቋረጠና የመንግሥቱ አስፋፊ ሆነ። በተጠመቀበት ጊዜ አንድ የሚያውቀውን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠና ነበር።

19. አስቀድመን መንግሥቱን ከፈለግን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

19 መንግሥቱን በማስቀደም የምናገኘው ደስታ የብርታት ምንጭ ይሆንልናል። (ማቴዎስ 6:​33) የተለያዩ ፈተናዎች ቢደርሱብንም ምሥራቹን በደስታና በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥላለን። (ቲቶ 2:​14) ብዙዎቻችን በሙሉ ጊዜ አቅኚነት ለማገልገል የሚያስፈልገውን ብቃት የምናሟላ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ወንጌላውያን ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች እያገለገሉ ነው። የመንግሥቱን ጥቅም በደስታ እየደገፍን ያለነው በእነዚህም ሆነ በሌሎች መንገዶች ይሖዋ ሥራችንንና ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር እንደማይረሳ እርግጠኞች ነን።​—⁠ዕብራውያን 6:​10-12

ከይሖዋ በምታገኙት ብርታት ወደፊት ግፉ

20. ብርታት ለማግኘት በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

20 በዚህም ሆነ በዚያ ይሖዋን ተስፋ እንደምናደርግና ኃይል ለማግኘትም ፊታችንን ወደ እርሱ እንደምናዞር እናሳይ። ይህን በተሟላ መንገድ ማድረግ የምንችለው ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ካደረገልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ስንጠቀም ነው። (ማቴዎስ 24:​45) በክርስቲያናዊ ጽሑፎች እየታገዙ የአምላክን ቃል በግልም ሆነ በጉባኤ መልክ ማጥናት፣ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ፣ ከሽማግሌዎች የሚገኘው መንፈሳዊ እገዛ፣ የታመኑ የእምነት አጋሮች የሚያሳዩት ግሩም ምሳሌነት እንዲሁም አዘውትሮ በአገልግሎት መካፈል ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ከሚያጠናክሩልንና የእርሱን ቅዱስ አገልግሎት ለማከናወን የሚያስችለንን ኃይል ከምናገኝባቸው ዝግጅቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

21. ሐዋርያው ጴጥሮስና ጳውሎስ አምላክ የሚሰጠው ብርታት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት እንዴት ነው?

21 ሰብዓዊ ድክመት ቢኖርብንም ይሖዋ እንዲረዳን እስከተማመንበት ድረስ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ያለው እርዳታ እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ “የሚያገለግልም ቢሆን፣ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 4:​11) ጳውሎስም “ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና” በማለት አምላክ በሚሰጠው ኃይል እንደሚተማመን አሳይቷል። (2 ቆሮንቶስ 12:​10) እኛም ተመሳሳይ እምነት እንዳለን በማሳየት ለደከሙት ኃይል የሚሰጠውን ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋን የምናስከብር እንሁን።​—⁠ኢሳይያስ 12:​2

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ይህ ቁጥር በዩናይትድ ስቴትስ ሥርዓተ አኃዝ መሠረት ከ1 በኋላ 20 ዜሮዎች ማስከተል ማለት ይሆናል።

b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የይሖዋ ሕዝብ ከወትሮው የተለየ ኃይል የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

• አምላክ ለአገልጋዮቹ ኃይል እንደሚሰጥ የሚያረጋግጥ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?

• ይሖዋ እኛን ለማበርታት ያደረጋቸው አንዳንዶቹ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ምንድን ናቸው?

• ብርታት ለማግኘት በአምላክ እንደምንታመን እንዴት ማሳየት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሌሎችን ስናስተምር ከይሖዋ ጋር ያለን የግል ዝምድና ይጠናከራል