ለማገልገል ተነሳሱ
ለማገልገል ተነሳሱ
ብዙ ነገር መሥራት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ የሚገኙ 24 ባልና ሚስት ቤተሰቦቻቸውን፣ ወዳጆቻቸውንና የለመዱትን አካባቢ ትተው በማያውቁት አገር በሚስዮናዊነት ለማገልገል ሊያነሳሳቸው የሚችለው ምንድን ነው? እንደ ፓፑዋ ኒው ጊኒና ታይዋን ወደመሳሰሉ እንዲሁም በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ወደሚገኙ አገሮች መሄዱ ያስደሰታቸው ለምንድን ነው? የማያውቁትን አገር ማየት ስለሚወድዱ ይሆን? አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው እውነተኛ ፍቅር ተነሣስተው ነው።—ማቴዎስ 22:37-39
እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 109ኛ ክፍል ተመራቂዎች ናቸው። ቅዳሜ፣ መስከረም 9, 2000 በፓተርሰን ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከልና ፕሮግራሙ በሳተላይት በተላለፈባቸው ቦታዎች በድምሩ 5, 198 ሰዎች ለተመራቂዎቹ የሚሰጠውን ስኬታማ ሚስዮናውያን እንዲሆኑ የሚረዳ ፍቅራዊ ምክር ለማዳመጥ ተሰብስበዋል።
የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል የትምህርት ኮሚቴ አባል የሆነው ስቲቨን ሌት ነበር። የመክፈቻ ንግግሩ የተመሠረተው “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” በሚለው በማቴዎስ 5:13 ላይ ነው። ወንድም ሌት የኢየሱስ ቃል በተመራቂ ተማሪዎቹ ላይ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት እንዳለው ገለጸ። ለምሳሌ ያህል ጨው ምግብ የማጣፈጥ ባሕርይ አለው። በተመሳሳይም ሚስዮናውያን ውጤታማ በሆነው የስብከት ሥራቸው አማካኝነት በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደ ጨው ናቸው።
የማበረታቻ ስንብት
ከዚያም ወንድም ሌት ለረጅም ጊዜ ይሖዋን ያገለገሉ ወንድሞችን ተራ በተራ የጋበዘ ሲሆን እነሱም አጭር ሆኖም ኃይለኛ መልእክት ያዘሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግሮች አቅርበዋል። የመጀመሪያው በጽሑፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው ጆን ዊስቸክ ነው። “ከሁሉም የሚያንሰው መዝሙር የሚስዮናዊነትን መንፈስ ያስፋፋል” የሚለው የንግግሩ ጭብጥ በመዝሙር 117 ላይ የተመሠረተ ነበር። ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ ‘ለአሕዛብ’ እና ‘ለወገኖች’ ምሥክርነት መስጠት አስፈላጊ ነው። ተማሪዎቹ ሌሎች ‘ያህን እንዲያወድሱ’ [NW ] በማሳሰብ መዝሙር 117 የሚናገረውን እንዲፈጽሙ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።
ሊቀ መንበሩ በመቀጠል የአስተዳደር አካል አባል የሆነውን ጋይ ፒርስን አስተዋወቀ። ንግግር ያቀረበው “ምክንያታዊ ሆኖም ጥብቅ ሁኑ” በሚል ርዕስ ነበር። የአምላክ ቃል ጠንካራ ነው። ዘዳግም 32:4 [NW ] ላይ ይሖዋ አምላክ ዓለት ተብሎ ተጠርቷል። ሆኖም ቃሉ ልዩ ልዩ ቋንቋና ባሕል ላላቸው ማለትም ለሰው ዘር ባጠቃላይ የተጻፈ በመሆኑ ምክንያታዊ እንድንሆንና ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር እንድንላመድ ያስችለናል። ተማሪዎቹ መልእክቱ የሰዎችን ልብና ሕሊና እንዲነካ በማድረግ የአምላክን ቃል እንዲሰብኩ ተመክረዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:2) ወንድም ፒርስ “ለትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥብቅ ሁኑ፤ ሆኖም ምክንያታዊነት አዳብሩ። በተመደባችሁበት አገር የሚኖሩ ሰዎች የተለየ ባሕል ስላላቸው አትናቋቸው” ሲል በጥብቅ አሳስቧቸዋል።
በዓለም አቀፉ ዋና መሥሪያ ቤት ዮሐንስ 8:29፤ 10:16
ወደ 53 ለሚጠጉ ዓመታት ያገለገለውና ከጊልያድ አስተማሪዎች አንዱ የሆነው ካርል አዳምስ “ከዚህ ተነስታችሁ የምትሄዱት ወዴት ነው?” በሚል ጭብጥ የሚያመራምር ንግግር አቀረበ። እርግጥ 24ቱ ባልና ሚስት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በተለያዩ 20 አገሮች ውስጥ በሚስዮናዊነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። ሆኖም ጥያቄው ምድብ ቦታችሁ ከደረሳችሁና አገሩን ካያችሁት በኋላ ምን ታደርጋላችሁ? የሚል ነበር። የምንኖረው ተለዋዋጭ መንፈስ ባለው ዓለም ውስጥ ነው። ሰዎች ራሳቸውን ለማስደሰት በሚያደርጉት ጥረት ወደ አዳዲስ ቦታዎች መሄድና አዳዲስ ነገሮች መሥራት ይወዳሉ። በአንጻሩ ተማሪዎቹ ይሖዋ እንዲያገለግሉ በሚፈልግበት ቦታ ሄደው ራስ ወዳድነት በሌለበት ሁኔታ ‘በጎቹን’ እንዲንከባከቡ የአገልግሎት ምድብ ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ የሰውን ዘር በሙሉ ለመባረክ ሊጠቀምባቸው አስቦ የነበረ ቢሆንም ራስ ወዳድ በመሆናቸው ምክንያት እንዲህ ያለው ግሩም አጋጣሚ እንዳመለጣቸው በጥንቷ እስራኤል ይኖሩ እንደነበሩ ሰዎች መሆን የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ራሱን ሳይቆጥብ ምንጊዜም የአባቱን ፈቃድ ያደረገውንና ባጋጠመው ሁኔታ ሁሉ ታዛዥ የነበረውን ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል አለባቸው።—የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጅስትራር የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ ይዞ የቀረበው ጭብጥ “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ” የሚል ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች በበርካታ ቦታዎች ላይ የአምላክን ቃል ከሀብት፣ ከከበሩ ድንጋዮች፣ ከውድ ማዕድናት እና ከፍተኛ ዋጋ ከሚሰጣቸውና ከሚደከምላቸው ነገሮች ጋር ያመሳስሉታል። ምሳሌ 2:1-5 ‘የአምላክን እውቀት ለማግኘት’ “እንደ ተቀበረ ገንዘብ” መፈላለግ እንዳለብን ያሳያል። ተናጋሪው ተማሪዎቹ በተመደቡባቸው ቦታዎች ሲያገለግሉ የአምላክን ጥልቅ ነገሮች መቆፈራቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል። ወንድም ሊቨረንስ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል:- “እንዲህ ማድረጋችሁ በይሖዋ ላይ ያላችሁን እምነትና ትምክህት ስለሚገነባና በተመደባችሁበት ቦታ ለመቀጠል ያደረጋችሁትን ውሳኔ ስለሚያጠናክር ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው። ለሌሎች የአምላክን ዓላማዎች ስታስረዱ በትምክህት እንድትናገሩና ይበልጥ ውጤታማ አስተማሪዎች እንድትሆኑ ይረዳችኋል።”
ሌላው የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ መማሪያ ክፍል ውስጥ የሚኖረውን ዓይነት መቼት በመጠቀም ይሖዋ ባለፉት አምስት ወራት የተማሪዎቹን የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ እንዴት እንደባረከላቸው በክለሳ መልክ አቅርቧል። ሎውረንስ ቦወን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን በሕዝብ ፊት ያከናወነውን አገልግሎት በተመለከተ ሥራ 20:20 ላይ የተናገረውን በመጥቀስ ጳውሎስ ምሥክርነት ለመስጠት የነበሩትን አጋጣሚዎች በሙሉ እንደተጠቀመባቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል። ተማሪዎቹ ያጋጠሟቸው ተሞክሮዎች እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ በጊዜያችን ለአምላክና ለሰዎች ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው የሚያገለግሉ ሰዎች እውነትን ከመናገርና የአምላክ ቃል ያለው ኃይል በሌሎች ላይ እንዲሠራ ከመፍቀድ በፍጹም ወደኋላ እንደማይሉ አሳይተዋል። ይህ የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል።
ተሞክሮ ያካበቱት የሰጡት ሐሳብ
የዚህኛው ክፍል የጊልያድ ተማሪዎች በትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት በፓተርሰን የትምህርት ማዕከል ልዩ ሥልጠና ለማግኘት ከ23 አገሮች ከመጡ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ጋር መገናኘት በመቻላቸው ልዩ ጥቅም አግኝተዋል። በአገልግሎት ክፍል የሚሠሩት ሊዮን ዊቨርና መርተን ካምቤል ከተለያዩ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የጊልያድ ተመራቂዎች ነበሩ። ተማሪዎቹ፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው እነዚህ ልምድ ያካበቱ ሚስዮናውያን የተናገሩትን ሲሰሙ ተበረታትተዋል።
ተመራቂ ተማሪዎቹ በተመደቡበት ባዕድ አገር ከሚገጥሟቸው ሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን እንዲያላምዱ ለመርዳት ከቀረበላቸው ምክር መካከል ቀጥሎ ያሉት አስተያየቶች ይገኙበታል:- “አዎንታዊ ሁኑ። ፈጽሞ የማታውቁት ወይም ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ነገር ካጋጠማችሁ ተስፋ አትቁረጡ። በይሖዋ ተመኩ”፤ “ባላችሁ ነገር መደሰት ተማሩ፤ እንዲሁም ይሖዋ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንደሚሰጣችሁ ተማመኑ።” የቀረቡት ሌሎች ሐሳቦች ተማሪዎቹ በተመደቡበት ቦታ ደስታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ በመርዳት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ቀጥሎ ያሉት ጥቂቶቹ ናቸው:- “ምድብ ቦታችሁን ከነበራችሁበት አገር ጋር አታወዳድሩ”፤ “ከሰዎች ጋር መግባባት እንድትችሉ የአገሩን ቋንቋ ተማሩ እንዲሁም አቀላጥፋችሁ ለመናገር ጥረት አድርጉ”፤ “የሕዝቡን ልማድና ባሕል እወቁ፤ ይህ በተመደባችሁበት ቦታ እንድትቀጥሉ ይረዳችኋል።” እነዚህ ሐሳቦች ለአዳዲሶቹ ሚስዮናውያን ከፍተኛ ማበረታቻ ሰጥተዋቸዋል።
ቃለ ምልልሶቹ ሲያበቁ አሁን የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ በማገልገል ላይ ያለውና ቀደም ሲል በሚስዮናዊነት ያገለገለው የ42ኛው ክፍል የጊልያድ ምሩቅ ዴቪድ ስፕሌን ዋናውን ንግግር ያዳበረው “ተማሪዎች ናችሁ ወይስ ምሩቃን?” በሚለው ትኩረት የሚስብ ጭብጥ ላይ ነበር። ተመራቂዎቹን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “በሚስዮናዊነት ወደምታገለግሉበት ቦታ ስትሄዱ ራሳችሁን የምትመለከቱት እንዴት ነው? ስለ ሚስዮናዊነት ሥራ ሁሉን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ምሩቅ ነው ወይስ ገና ብዙ መማር እንዳለበት ተማሪ?” ወንድም ስፕሌን ጥበበኛ የሆነ ምሩቅ ራሱን እንደ ተማሪ እንደሚቆጥር ጠቅሷል። ሚስዮናውያኑ በተመደቡበት ቦታ የሚያገኙት ሰው ሁሉ እነሱን አንድ ነገር ሊያስተምራቸው እንደሚችል ሊያስቡ ይገባል። (ፊልጵስዩስ 2:3) ተማሪዎቹ ከሌሎች ሚስዮናውያን፣ ከቅርንጫፍ ቢሮውና ከተመደቡበት ጉባኤ ጋር በቅርብ ተባብረው እንዲሠሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ወንድም ስፕሌን “የመጨረሻውን ፈተናችሁን አልፋችኋል፤ ሆኖም አሁንም ተማሪዎች ናችሁ። የመጣችሁት ለመማር መሆኑን ሁሉም ሰው እንዲያውቅ አድርጉ” ሲል በጥብቅ አሳስቧል።
ንግግሩ ሲያበቃ ተማሪዎቹ ዲፕሎማቸውን የተቀበሉ ሲሆን ምድብ ቦታቸውም ለተሰብሳቢዎቹ በይፋ ተነግሯል። በመቀጠል የክፍሉ ተወካይ ተመራቂዎቹ ከአምላክ ቃል የቀሰሙት ትምህርት የላቀ የቅዱስ አገልግሎት ተግባር ለማከናወን እንዲገፋፋቸው ለመፍቀድ ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ የያዘ የአቋም መግለጫ ሲያነብ ተመራቂ ተማሪዎቹ ስሜታቸው በጥልቅ ተነክቶ ነበር።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የቀረበው ምክር ተመራቂዎቹ ለአምላክ እና ለሰዎች ፍቅር ለማሳየት ያደረጉትን ውሳኔ የሚያጠናክር መሆኑን በቦታው የተገኙት ሁሉ እንደሚስማሙበት አያጠራጥርም። በተጨማሪም በሚስዮናዊነት እንዲያገለግሉ በተመደቡበት አገር የሚኖሩትን ሰዎች በመንፈሳዊ ለመርዳት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች:- 10
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 20
የተማሪዎቹ ብዛት:- 48
አማካይ ዕድሜ:- 33.7
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16.2
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12.5
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁ የ109ኛው ክፍል ተማሪዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ኮሊንስ ኢ፣ ማይልስ ኤል፣ አልቫራዶ ኤ፣ ሌክ ጄ (2) ቫን ዱሰን ኤል፣ ቢሀሪ ኤ፣ ሄኪነን ኤች፣ ኮስ ኤስ፣ ስሚዝ ኤች (3) አሽፎርድ ጄ፣ አሽፎርድ ሲ፣ ቦር ሲ፣ ሪቻርድ ኤል፣ ዊልበርን ዲ፣ ሌክ ጄ (4) ቺቺኢ ኬ፣ ቺቺኢ ኤች፣ ራሚሬዝ ኤም፣ ቦውማን ዲ፣ ቤከር ጂ፣ ቢሀሪ ኤስ፣ ራሚሬዝ ኤ (5) ቫን ዱሰን ደብሊው፣ ለማትሬ ኤች፣ ፒስኮ ጄ፣ ከትስ ኤል፣ ራስል ኤች፣ ጆንሰን አር (6) ቤከር ኤፍ፣ ቦውማን ዲ፣ ጆንሰን ኬ፣ ፓይፈር ኤ፣ ማሰን ሲ፣ ለማትሬ ጄ፣ ሄኪነን ፒ (7) ስሚዝ አር፣ ራስል ጄ፣ ኮሊንስ ኤ፣ ፒስኮ ዲ፣ ዊልበርን አር፣ ኮስ ጂ (8) ከትስ ቢ፣ ቦር ጄ፣ ማሰን ኤን፣ ፓይፈር ኤስ፣ ሪቻርድ ኢ፣ ማይልስ ቢ፣ አልቫራዶ አር