ታስታውሳለህን?
ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃልን? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-
• ከአንድ ሰው ጋር የተፈጠረን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችለን መሠረታዊ ነገር ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ሁላችንም ለተሳሳቱ አስተሳሰቦችና ዝንባሌዎች የተጋለጥን መሆናችንን አምነን መቀበል አለብን። ከዚያም ለተፈጠረው ችግር መንስኤው ሌላኛው ሰው ሳይሆን እኛ ልንሆን እንደምንችል ቆም ብለን ማሰብ አለብን።—8/15 ገጽ 23
• ሥራ 3:21 ላይ የተጠቀሰው ‘ነገር ሁሉ የሚታደስበት ዘመን’ የሚመጣው መቼ ነው?
የመታደስ ዘመን የሚመጣው በሁለት መልኩ ነው። በመጀመሪያ ከ1919 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለው የመንፈሳዊ ገነት ተሐድሶ አለ። ምድር ወደ ገነትነት ስትለወጥ ደግሞ ሌላ የተሐድሶ ዘመን ይመጣል።—9/1 ገጽ 17, 18
• ምሳሌ 6:6-8 ላይ እንደተጠቀሰው ጉንዳን አለቃ ባይኖራትም እንኳ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው እንዴት ነው?
በአንድ የጉንዳን መንጋ አንዲት ንግሥት የምትኖር ቢሆንም ንግሥትነቷ እንቁላል በመጣልና የመንጋው እናት በመሆን ረገድ ብቻ ነው። ጉንዳኖች ታታሪ እንደሆኑ ሁሉ እኛም የሚቆጣጠረን ባይኖርም እንኳ የሥራችንን ጥራት ለማሻሻል በመጣር ታታሪ መሆን አለብን።—9/15 ገጽ 26
• ኢዮስያስ የሞተው በጦርነት ሆኖ ሳለ 2 ነገሥት 22:20 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሕልዳና “በሰላም” ይሞታል ስትል የተናገረችው ትንቢት በትክክል ተፈጽሟልን?
ኢዮስያስ ከ609-607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ከብበው ባጠፉበት ወቅት ከደረሰው መቅሠፍት በፊት በመሞቱ በሰላም ተሰብስቧል ሊባል ይችላል።—9/15 ገጽ 30
• ሰሎሞን ሚስት ‘የተወደደች ዋላ እና የተዋበች ሚዳቋ’ [“የበረሃ ፍየል፣” የ1980 ትርጉም ] እንደሆነች ሲገልጽ ያሞገሳት እንዴት ነው? (ምሳሌ 5:18, 19)
ሴቷ ዋሊያ ወይም የበረሃ ፍየል ረጋ ያለ ተፈጥሮና ውብ የሆነ አካል አላት። ሆኖም የበረሃ ፍየል ምግብ ማግኘት በማይቻልባቸው አለታማ በሆኑና ሰው በማይደርስባቸው ቦታዎች መኖርና መውለድ ትችላለች።—10/1 ገጽ 30, 31
• ሄንሪ ግሪው እና ጆርጅ ስቶርዝ እነማን ነበሩ?
እነዚህ ሁለት ሰዎች በ1800ዎቹ የኖሩ ንቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበሩ። ግሪው ሥላሴም ሆነ ነፍስ አትሞትም የሚለው እንዲሁም የእሳታማ ሲኦል መሠረተ ትምህርቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ አለመሆናቸውን ተረድቷል። ስቶርዝ ደግሞ አንዳንዶች በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚያገኙ ተገንዝቧል። ሁለቱም ይህን መጽሔት በ1879 ማሳተም ከጀመረው ከቻርልስ ቴዝ ራስል በፊት የኖሩ ሰዎች ናቸው።—10/15 ገጽ 26-30
• የይሖዋ ምሥክሮች የራስን ደም በመጠቀም ለሚከናወኑ የሕክምና አሠራሮች ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው?
እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የራሳቸውን ደም አስቀምጠው ከጊዜ በኋላ በደም ሥር አይወስዱም። እያንዳንዱ ክርስቲያን ቀዶ ሕክምና ወይም ምርመራ በሚካሄድበት ወቅት ደሙ በምን መንገድ እንደሚሠራበት ለራሱ ይወስናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደም የሚናገረውን መመርመርና ራሱን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ የወሰነ መሆኑን ማስታወስ አለበት።—10/15 ገጽ 30, 31
• በ2, 000 መጀመሪያ ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት በዓለም ዙሪያ በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስፈልግ ምን ነገር መኖሩን ጠቁሟል?
የገንዘብ እጥረት ባለባቸው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ከ11, 000 በላይ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። በበርካታ አገሮች ከሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚገኘው መዋጮ በቂ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ለመገንባት እየዋለ ነው።—11/1 ገጽ 30
• መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸው ከአምልኮ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው አንዳንድ የግሪክኛ ቃላት የትኞቹ ናቸው?
አንደኛው “ሕዝባዊ አገልግሎት” የሚል ፍቺ ያለው ሌቱሪያ የሚለው ቃል ነው። ሌላው ደግሞ ላትሪያ ሲሆን ይህም “ቅዱስ አገልግሎት” የሚል ፍቺ አለው። (ዕብራውያን 10:11፤ ሉቃስ 2:36, 37)—11/15 ገጽ 11, 12
• መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዳምና ሔዋን ከሚናገረው ታሪክ የምናገኘው መሠረታዊ ትምህርት ምንድን ነው?
ከይሖዋ አምላክ ለማፈንገጥ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ጥረት ፍጹም ሞኝነት ነው።—11/15 ገጽ 24-7
• አምላክ ለአገልጋዮቹ ኃይል እንደሚሰጥ የሚያሳይ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ?
ዳዊት፣ ዕንባቆምና ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ አምላክ ብርታት ወይም ኃይል ሰጥቷቸው እንደነበር የራሳቸውን ምሥክርነት ሰጥተዋል። (መዝሙር 60:12፤ ዕንባቆም 3:19፤ ፊልጵስዩስ 4:13) በመሆኑም አምላክ ለእኛ ኃይል ለመስጠት ፈቃደኛነቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—12/1 ገጽ 10, 11