የገና ልማዶች ክርስቲያናዊ ናቸውን?
የገና ልማዶች ክርስቲያናዊ ናቸውን?
የገና በዓል የሚከበርበት ጊዜ ደርሷል። በዓሉ ለአንተ፣ ለቤተሰብህና ለወዳጆችህ ምን ትርጉም አለው? መንፈሳዊ ይዘት ያለው ወቅት ነው ወይስ የግብዣና የፈንጠዝያ ጊዜ? የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚታወስበት ቀን ነው ወይስ ስለ ክርስቲያናዊ ደንቦች መጨነቅ የማያስፈልግበት ጊዜ?
እነዚህን ጥያቄዎች ስትመረምር የገና በዓል አከባበር ከአገር ወደ አገር ሊለያይ እንደሚችል አስታውስ። ለምሳሌ ያህል በሜክሲኮና በሌሎች የላቲን አሜሪካ አገሮች ለበዓሉ የተሰጠው ስም እንኳ የተለየ ነው። አንድ ኢንሳይክሎፔዲያ ክሪስማስ የሚለው የእንግሊዝኛ ስም “በመካከለኛው ዘመን ይሠራበት ከነበረው ክሪስተስ ማስ (ቅዳሴ ክርስቶስ) ከሚለው ሐረግ የተወረሰ” መሆኑን አመልክቷል። ሆኖም በላቲን አሜሪካ አገሮች ላ ናቪዳድ ወይም በእንግሊዝኛ ኔቲቪቲ ተብሎ የሚጠራውን የክርስቶስን ልደት ያመለክታል። ጥቂት ጊዜ ወስደህ በሜክሲኮ ያለውን ልማድ በመጠኑ ጠለቅ ብለህ ለማየት ሞክር። እንዲህ ማድረግህ ይህን በዓል በተመለከተ ያለህን አመለካከት እንድታስተካክል ሊረዳህ ይችል ይሆናል።
ፖሳዳስ፣ “ሦስቱ ጠቢባን፣” እና ናሲምዬንቶ
በዓሉ የሚጀምረው ታኅሣሥ 16 ላይ በፖሳዳስ ነው። ሜክሲኮስ ፊስትስ ኦቭ ላይፍ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ጊዜው የፖሳዳስ ወቅት ነው፤ ከገና ዋዜማ በፊት ዘጠኝ አስደሳች ቀናት አሉ። በእነዚህ ቀናት ዮሴፍና ማርያም በቤተ ልሔም ከተማ ብቻቸውን የተንከራተቱበትና በመጨረሻም ደግነት የሚያሳያቸውና ማረፊያ የሚሰጣቸው ሰው ያገኙበት ጊዜ ይከበራል። ቤተሰቦችና ወዳጆች ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት በነበሩት ቀናት የተከናወኑትን ነገሮች በድራማ መልክ ለመሥራት ማታ ማታ አንድ ላይ ይሰበሰባሉ።”
በርከት ያሉ ሰዎች የማርያምንና የዮሴፍን ምስል ይዘው ወደ አንድ ቤት በመሄድ ማረፊያ እንዲሰጧቸው በመዝሙር መጠየቃቸው ወይም ፖሳዳ የቆየ ልማድ ነው። እንግዶቹ ወደ ቤት እንዲገቡ እስኪፈቀድላቸው ድረስ ቤት ውስጥ ያሉት ሰዎች በመዝሙር ምላሽ ይሰጣሉ። ከዚያም ዓይናቸው በጨርቅ የታሰረ ዱላ የያዙ ጥቂት ሰዎች ፒናታ የሚባል ገመድ ላይ የተንጠለጠለ ያሸበረቀ አንድ ትልቅ ማሰሮ ለመስበር ተራ በተራ ይሞክራሉ። ማሰሮው ከተሰበረ በኋላ በውስጡ የነበሩት (ከረሜላ፣ ፍራ ፍሬና የመሳሰሉ ነገሮች) በዓሉን ለማክበር በተገኙት ሰዎች ይሰበሰባሉ። ከዚህ በኋላ ምግብ፣ መጠጥ፣ ሙዚቃና ጭፈራ ይኖራል። ከታኅሣሥ 16 እስከ ታኅሣሥ 23 ድረስ ስምንት የፖሳዳ ግብዣዎች ይዘጋጃሉ። ታኅሣሥ 24 ላይ ኖቼብዌና (በገና ዋዜማ) የሚከበር ሲሆን የቤተሰብ አባላት በዚህ ቀን በሚዘጋጀው ልዩ እራት ላይ በአንድነት ለመሰባሰብ ጥረት ያደርጋሉ።
ብዙም ሳይቆይ ዘመን መለወጫ ይደርስና ድብልቅልቅ ባሉ ግብዣዎች ተከብሮ ይውላል። ጥር 5 ምሽት ላይ ትሬስ ሬዬስ ማጎስ (“ሦስት ጠቢባን”) ለልጆች አሻንጉሊቶች ያመጣሉ የሚል እምነት አለ። የበዓሉ ማሳረጊያ ጥር 6 ላይ የሚደረገው ግብዣ ሲሆን በዚህ ቀን ሮስካ ዴ ሬዬስ (የቀለበት ቅርጽ ያለው ኬክ) ይበላል። ይህ ኬክ እየተበላ እንዳለ አንድ ሰው በተሰጠው ቁራሽ ውስጥ ሕፃኑ ኢየሱስን የሚያመለክት አንድ ትንሽ አሻንጉሊት ያገኛል። አሻንጉሊቱን ያገኘው ሰው የካቲት 2 ላይ የመጨረሻ ግብዣ አዘጋጅቶ የመጥራት ግዴታ አለበት። (በአንዳንድ ቦታዎች “ሦስቱን ጠቢባን” የሚወክሉ ሦስት ትንንሽ አሻንጉሊቶች ይኖራሉ።) ከዚህ መረዳት እንደምትችለው የገናን በዓል አስመልክቶ የሚደረጉት ግብዣዎች የተንዛዙ ናቸው።
በዚህ ወቅት ናሲምዬንቶ (የኢየሱስን ልደት የሚያሳይ ምስል) ጉልህ ሥፍራ ይኖረዋል። ይህ ምን ነገሮችን
ያካትታል? ሕዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎችም ሆነ በአብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች ከሴራሚክ፣ ከእንጨትና ከሸክላ የተሠሩ ምስሎች (ትልልቅም ሆኑ ትንንሽ) ይቀመጣሉ። ምስሎቹ ዮሴፍና ማርያም ገና የተወለደ ሕፃን ከተኛበት ግርግም ፊት ተንበርክከው እንዳሉ የሚያሳዩ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ እረኞችና ሎስ ሬዬስ ማጎስ (“ጠቢባኑ ሰዎች”) በምስሎቹ ላይ ይታያሉ። ቦታው ጋጣ ውስጥ ሲሆን ትዕይንቱን የተሟላ ለማድረግ በምስሉ ላይ የተወሰኑ ከብቶች እንዲታዩ ይደረጋል። ሆኖም ዋናው ትኩረት ያረፈበት አካል በስፓንኛ ኤል ኒኞ ዴ ዳዮስ (ሕፃኑ አምላክ) ተብሎ የሚጠራው ገና የተወለደው ሕፃን ነው። በገና ዋዜማ የዚህ ሕፃን ምስል ይቀመጥ ይሆናል።ከክርስቶስ ልደት ጋር የተያያዙ ልማዶችን ቀረብ ብሎ መመርመር
በጥቅሉ በዓለም ዙሪያ እንደሚታወቀው ሁሉ የገና በዓልን በተመለከተ ዚ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “በአሁኑ ጊዜ ከገና ጋር ግንኙነት ያላቸው አብዛኞቹ ልማዶች መጀመሪያ ላይ የገና ልማዶች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸው ከክርስትና በፊት የነበሩና ክርስቲያናዊ አመጣጥ የሌላቸው ልማዶች ናቸው። ታኅሣሥ አጋማሽ ላይ የሚከበረው የሮማውያን በዓል ማለትም ሳቱርናሊያ በፈንጠዝያ ለተሞሉት ለአብዛኞቹ የገና ልማዶች ሞዴል ሆኗል። ለምሳሌ ያህል ትልቅ ድግስ ማዘጋጀት፣ ስጦታ መለዋወጥና ሻማ ማብራት ከዚህ በዓል የተወረሱ ልማዶች ናቸው።”
በላቲን አሜሪካ ከክርስቶስ ልደት ጋር የተያያዙት እነዚህ መሠረታዊ ልማዶች ከሌሎች ተጨማሪ ልማዶች ጋር ይከበራሉ። ‘ምንጫቸው ከየት ነው’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ግልጹን ለመናገር መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ መከተል የሚፈልጉ ብዙዎች አንዳንዶቹ ልማዶች ሙሉ በሙሉ የአዝቴክ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች መሆናቸውን ይገነዘባሉ። በሜክሲኮ ሲቲ የሚታተመው ኤል ዩኒቨርሳል የተባለ ጋዜጣ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “የሕንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት አካል የሆኑ በዓላት ከካቶሊክ ሃይማኖታዊ የበዓል ቀናት ጋር በመገጣጠማቸው በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ውስጥ የታቀፉ መነኮሳት የወንጌላዊነትና የሚስዮናዊነት ሥራቸውን ለመደገፍ ይህን ሁኔታ እንደ መሣሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል። ቀደምት የላቲን አሜሪካ ነዋሪዎች ያምኑባቸው ለነበሩ አማልክት መታሰቢያነት የሚከበሩትን ቀናት በክርስትና አማልክት ስም
በሚከበሩት በዓላት ተክተዋል፤ የአውሮፓውያኑን በዓላትና ልማድ አስተዋውቀዋል እንዲሁም የሕንዳውያኑን በዓላት አካትተዋል። ይህም የባሕል ውሕደት እንዲፈጠርና የዛሬው ዓይነተኛ የሜክሲካውያን ልማድ ብቅ እንዲል በር ከፍቷል።”ዚ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የክርስቶስን ልደት በድራማ መልክ ማቅረብ የገና በዓል ክፍል ከሆነ ረጅም ዘመን አስቆጥሯል . . . ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክርስቶስን ልደት [በግርግም የነበረውን ሁኔታ] በድራማ መልክ የማቅረብ ልማድ እንዲቋቋም ያደረገው ቅዱስ ፍራንሲስ እንደሆነ ይነገራል።” የክርስቶስን ልደት የሚያቀርቡት እነዚህ ድራማዎች ሜክሲኮ ቅኝ ግዛት በሆነችበት ወቅት መጀመሪያ ላይ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ይታዩ ነበር። እነዚህ ድራማዎች የሚቀርቡት በፍራንሲስካውያን መነኮሳት ሲሆን ይህም ስለ ክርስቶስ ልደት ሕንዳውያኑን ለማስተማር በሚል ነበር። ከጊዜ በኋላ ፖሳዳስ ይበልጥ ተወዳጅ እየሆነ መጣ። የፖሳዳስ ክብረ በዓል የተጀመረበት ዓላማ ምንም ይሁን ምን ዛሬ በዓሉ የሚከበርበት መንገድ እውነተኛ ገጽታውን ያሳያል። በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ሜክሲኮ ውስጥ ከሆንክ የኤል ዩኒቨርሳል ጋዜጣ አዘጋጅ በሰጠው ሐሳብ ውስጥ ያጎላውን ነገር ማየት ወይም መገንዘብ ትችላለህ:- “የኢየሱስ ወላጆች ሕፃኑ አምላክ የሚወለድበትን ማረፊያ ለማግኘት ያደረጉትን ጉዞ ማስታወስ እንችል ዘንድ የሚከበረው የፖሳዳስ ክብረ በዓል በዛሬው ጊዜ ያለ ልክ የሚጠጣበትና የሚበላበት፣ አልባሌ ተግባሮች የሚከናወኑበት እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ወንጀል የሚፈጸምበት ወቅት ሆኗል።”
የናሲምዬንቶ ጽንሰ ሐሳብ የተወለደው ሜክሲኮ ቅኝ ግዛት በሆነችበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚቀርቡት ከመጀመሪያዎቹ ድራማዎች ነበር። ምንም እንኳ ለአንዳንድ ሰዎች ማራኪ ሆኖ ቢታያቸውም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በትክክል ይወክላል? ይህ አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ኮከብ ቆጣሪዎች የሆኑት ሦስቱ ጠቢባን የሚባሉት ሰዎች ኢየሱስን ለማየት በመጡበት ጊዜ እሱና ቤተሰቡ ካረፉበት ጋጣ ለቅቀው ነበር። የተወሰነ ጊዜ አልፏል። በወቅቱ ኢየሱስና ቤተሰቡ በቤት ውስጥ መኖር ጀምረው ነበር። በማቴዎስ 2:1, 11 ላይ በሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ዘገባ ላይ ይህን ሐሳብ ስታነብ ትኩረት የሚስብ ሆኖ ታገኘዋለህ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የኮከብ ቆጣሪዎቹ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ አለመናገሩን ማስተዋል ትችላለህ። a
በላቲን አሜሪካ ሦስቱ ጠቢባን ለሳንታ ክላውዝ የሚሰጠውን ቦታ ይይዛሉ። ቢሆንም በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ ብዙ ወላጆች ቤት ውስጥ አሻንጉሊቶችን ይደብቃሉ። ከዚያም ጥር 6 ጠዋት ልጆቹ ሦስቱ ጠቢባን ሰዎች እንዳመጡላቸው በማሰብ አሻንጉሊቶቹን ለማግኘት ቤቱን ይፈትሻሉ። ይህ ወቅት አሻንጉሊት አምራቾች ትርፍ የሚያጋብሱበት ወቅት ሲሆን ብዙዎች የሚያምር ሆኖ መቅረቡን በማየት ብቻ በመሸመታቸው አንዳንዶች ገቢያቸውን አደልበዋል። ስለ ሦስቱ ጠቢባን የሚነገረው አፈ ታሪክ በአንዳንዶች ዘንድ አልፎ ተርፎም በትንንሽ ልጆች ዘንድ እንኳ ተአማኒነት እያጣ ነው። ምንም እንኳ ይህ አፈ ታሪክ አማኞች እያጣ መምጣቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ቢያስከፋቸውም ለወግና ንግድ ለማስፋፋት ተብሎ ከተፈጠረ ታሪክ ድሮስ ምን ሊጠበቅ ይችላል?
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ገናን ወይም የክርስቶስን ልደት አላከበሩም። ይህን በተመለከተ አንድ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “በዓሉ በክርስትና እምነት የመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት አይከበርም ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ክርስቲያኖች ታዋቂ የሆኑ ሰዎች የተወለዱበትን ሳይሆን የሞቱበትን ቀን የማክበር ልማድ ስለነበራቸው ማቴዎስ 14:6-10
ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ የልደት ቀን የማክበርን ልማድ የሚያያይዘው ከአረማውያን እንጂ ከእውነተኛዎቹ የአምላክ አምላኪዎች ጋር አይደለም።—እንዲህ ሲባል ግን ከአምላክ ልጅ ልደት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ትክክለኛ ክስተቶች መማርና ማስታወስ ጠቀሜታ የለውም ማለት አይደለም። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ጠቃሚ የሆነ ግንዛቤና ትምህርት ያስጨብጣቸዋል።
የኢየሱስ ልደት ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ሲታይ
የኢየሱስን ልደት በተመለከተ በማቴዎስና በሉቃስ ወንጌሎች ላይ እምነት የሚጣልበት መረጃ ታገኛለህ። የወንጌል ዘገባዎቹ መልአኩ ገብርኤል የገሊላ ከተማ በሆነችው በናዝሬት የምትኖረውን ማርያም የተባለች ያላገባች ወጣት ሴት እንዳነጋገረ ይገልጻሉ። የነገራት መልእክት ምንድን ነው? “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”—ሉቃስ 1:31-33
ማርያም ይህን መልእክት ስትሰማ በጣም ተደነቀች። ያላገባች በመሆንዋ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለች። መልአኩ እንዲህ ሲል መለሰላት:- “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።” ማርያም ነገሩ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ስትገነዘብ እንዲህ አለች:- “እነሆኝ የጌታ ባሪያ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ።”—ሉቃስ 1:34-38
ዮሴፍ፣ ማርያም መጸነስዋን ካወቀ በኋላ ሊፈታት አቅዶ ስለነበር ይህን ከማድረግ እንዲቆጠብ አንድ መልአክ በተአምራዊ መንገድ ስለምትወልደው ልጅ ነገረው። ከዚህ በኋላ የአምላክን ልጅ የመንከባከቡን ኃላፊነት ለመረከብ ፈቃደኛ ሆነ።—ማቴዎስ 1:18-25
ከዚያም አውግስጦስ ቄሣር ያወጣው አዋጅ ዮሴፍና ማርያም ከገሊላ ናዝሬት ተነስተው አያቶቻቸው ይኖሩባት ወደነበረችው በይሁዳ ወዳለችው ወደ ቤተ ልሔም ከተማ ሄደው እንዲመዘገቡ አስገደዳቸው። “በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፣ የበኩር ልጅዋንም ወለደች፣ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።”—ሉቃስ 2:1-7
ሉቃስ 2:8-14 ቀጥሎ የሆነውን ነገር እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፣ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፣ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው:- እነሆ፣ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ:- ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።”
ሰብአ ሰገል
የማቴዎስ ዘገባ ሰብአ ሰገል የአይሁድ ንጉሥ የተወለደበትን ቦታ እየፈለጉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣታቸውን ይጠቅሳል። ንጉሥ ሄሮድስ ስለዚህ ጉዳይ የማወቅ ፍላጎት አድሮበት ነበር፤ ሆኖም በጥሩ ዓላማ አልነበረም። “ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ:- ሂዱ፣ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው።” ሰብአ ሰገል ሕፃኑን አገኙትና “ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።” ሆኖም ወደ ሄሮድስ አልተመለሱም። ‘ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው ነበር።’ አምላክ በመልአክ ተጠቅሞ የሄሮድስን ዕቅድ ለዮሴፍ አሳወቀው። ከዚህ በኋላ ዮሴፍና ማርያም ልጃቸውን ይዘው ወደ ግብፅ ሸሹ። ቀጥሎም ጨካኙ ንጉሥ ሄሮድስ የተወለደውን ንጉሥ ለማስገደል ሲል በቤተ ልሔም አካባቢ ያሉ ወንዶች ልጆች እንዲገደሉ አዘዘ። የትኞቹን ልጆች? ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸውን ልጆች ነው።—ማቴዎስ 2:1-16
ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
ሕፃኑን ለማየት የመጡት ሰብአ ሰገል ብዛታቸው ምንም ይሁን ምን እውነተኛውን አምላክ አያመልኩም ነበር። ላ ኑኤቫ ቢብሊያ ላቲኖአሜሪካ (የ1989 እትም) የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በግርጌ ማስታወሻው ላይ ቀጥሎ ያለውን አስፍሯል:- “አስማተኞቹ ጠንቋዮችና የአረማዊ ሃይማኖት ካህናት እንጂ ነገሥታት አልነበሩም።” ወደዚህ የመጡት ሥራዬ ብለው በያዙት ስለ ከዋክብት ባላቸው እውቀት ተመርተው ነበር። አምላክ ወደ
ሕፃኑ ሊመራቸው ቢፈልግ ኖሮ መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ሄሮድስ ቤተ መንግሥት መሄድ ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ ወደ ትክክለኛው ቦታ በወሰዳቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ አምላክ ልጁን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል አቅጣጫቸውን ለማስቀየር ጣልቃ ገብቷል።ዋናው ቁም ነገር ለማርያምና ለእረኞቹ እንደተነገራቸው ታላቅ ንጉሥ የሚሆን ሕፃን መወለዱ ሆኖ ሳለ በገና በዓል ወቅት ይህ ዘገባ ብዙውን ጊዜ ቁም ነገሩን በሚያደበዝዙ አፈ ታሪኮችና ፈጠራዎች ይዋጣል። አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃን ልጅ አይደለም። በቅርቡ የአምላክን ፈቃድ የሚቀናቀኑትን አገዛዞች በሙሉ በሚያስወግደውና የሰው ልጆች ለገጠሟቸው ችግሮች ባጠቃላይ መፍትሔ በሚያስገኘው በአምላክ መንግሥት ላይ የተሾመ ንጉሥ ነው። በጌታ ጸሎት ላይ እንዲመጣ የምንጸልይለት መንግሥት ይህ ነው።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10
መልአኩ ለእረኞቹ ያሳወቃቸው ነገር የምሥራቹን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ የመዳን አጋጣሚ ክፍት መሆኑን የሚጠቁም ነው። የአምላክን ሞገስ ያገኙ ሁሉ ‘በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች’ ይሆናሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ሥር በመላው ዓለም ሰላም የሚሰፍንበትን ግሩም ጊዜ በተስፋ እንጠብቃለን። ሆኖም ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። የገና በዓል የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ አመቺ የሆነና ይህን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስን መከተል የሚፈልጉ ቅን ልቦና ያላቸው ብዙ ሰዎች መልሱ ምንም እንደማያሻማ ይገነዘባሉ።—ሉቃስ 2:10, 11, 14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሌላም መታለፍ የሌለበት ጉዳይ አለ፤ በሜክሲካውያን ናሲምዬንቶ ላይ ያለው ልጅ “ሕፃኑ አምላክ” በሚል የሚታወቅ ሲሆን ይህም ሕፃን ሆኖ ወደ ምድር የመጣው አምላክ ራሱ ነው ከሚለው ሐሳብ የመነጨ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ኢየሱስ ምድር ላይ የተወለደ የአምላክ ልጅ መሆኑን ነው። ልክ እንደ ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ወይም ከእሱ ጋር እኩል አይደለም። የዚህን ጉዳይ እውነተኝነት በተመለከተ በሉቃስ 1:35፤ በዮሐንስ 3:16፤ 5:37፤ 14:1, 6, 9, 28፤ 17:1, 3፤ 20:17 ላይ የተሰጠውን ሐሳብ ተመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ይገረሙ ይሆናል
ዘ ትረብል ዊዝ ክሪስማስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ደራሲው ቶም ፍሊን በገና በዓል ላይ ለበርካታ ዓመታት ጥናት ካካሄዱ በኋላ የደረሱበትን መደምደሚያ እንዲህ ሲሉ አስፍረዋል:-
“በአሁኑ ጊዜ ከገና ጋር የምናያይዛቸው በርካታ ልማዶች ከክርስትና በፊት ከነበሩ አረማዊ ሃይማኖታዊ ልማዶች የመጡ ናቸው። የተማሩና ባህል ነክ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጡ ዘመናውያን ሰዎች ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹ አመጣጥ ከማኅበራዊ፣ ከፆታዊ ጉዳዮች ወይም ከኮከብ ቆጠራ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ መረዳታቸው ልማዶቹን እንዲተዉ ሊያደርጋቸው ይችላል።”—ገጽ 19
ፍሊን ድጋፍ የሚሆኑ በርካታ መረጃዎች ካቀረቡ በኋላ ወደ ዋናው ነጥብ በመመለስ እንዲህ ብለዋል:- “ገናን በተመለከተ በጣም አስገራሚ ከሆኑት ነገሮች አንዱ በአብዛኛው እውነተኛ የክርስትና ይዘት የሌለው መሆኑ ነው። የቅድመ ክርስትና ክፍሎቹን ካስወገድን በኋላ የሚቀሩት አብዛኞቹ ልማዶች በትክክል ከክርስትና እምነት የተገኙ ሳይሆን ከዚያ በኋላ የመጡ ልማዶች ናቸው።”—ገጽ 155
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስን ልደት አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ ወደፊት በአምላክ የተመረጠ ንጉሥ በመሆን ለሚኖረው ሚና መሠረት ጥሏል