ጽኑ እምነት በመያዝ ምሉዓን ሆናችሁ ቁሙ
ጽኑ እምነት በመያዝ ምሉዓን ሆናችሁ ቁሙ
“በመጨረሻም ምሉዓን ሆናችሁና በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯችሁ እንድትቆሙ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።”—ቆላስይስ 4:12 NW
1, 2. (ሀ) በውጭ ያሉ ሰዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ምን ነገር ታዝበዋል? (ለ) የቆላስይስ መጽሐፍ ፍቅራዊ አሳቢነትን የሚያንጸባርቅ የሆነው እንዴት ነው?
የኢየሱስ ተከታዮች ለአምልኮ ባልንጀሮቻቸው በጥልቅ ያስቡ ነበር። ተርቱሊያን (በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የነበረ ጸሐፊ) ወላጆቻቸው ለሞቱባቸው ልጆች፣ ለድሆችና በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ያሳዩ ስለነበረው ደግነት ተናግሯል። እንዲህ ያለው በሥራ የተገለጸ ፍቅር የማያምኑ ሰዎችን በጣም ከማስደነቁ የተነሳ አንዳንዶች ክርስቲያኖችን በማስመልከት ‘እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ ተመልከቱ’ ብለው እንዲናገሩ ገፋፍቷቸዋል።
2 የቆላስይስ መጽሐፍ ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኛው ኤጳፍራ በቆላስይስ ለነበሩ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩትን እንዲህ ያለ ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያል። ጳውሎስ “በመጨረሻም ምሉዓን ሆናችሁና በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯችሁ እንድትቆሙ” ኤጳፍራ “ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይተጋል” በማለት ጽፎላቸዋል። “ምሉዓን ሆናችሁና በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯችሁ [ቁሙ]” የሚሉት ቆላስይስ 4:12 [NW ] ላይ የሚገኙት ቃላት በ2001 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ ሆኖ ያገለግላል።
3. ኤጳፍራ የጸለየው ስለ ምን ሁለት ነገሮች ነው?
3 ኤጳፍራ ለሚወዳቸው ሰዎች ያቀረባቸው ጸሎቶች ሁለት ገጽታዎች እንዳላቸው ልትመለከት ትችላለህ። (1) ‘በመጨረሻም ምሉዓን ሆነው እንዲቆሙ’ እንዲሁም (2) ‘በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯቸው እንዲቆሙ’ ጸልዮአል። እኛም ጥቅም ማግኘት እንችል ዘንድ ይህ ዘገባ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንዲሰፍር ተደርጓል። ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘በመጨረሻ ምሉዓን ሆኜና በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሮኝ መቆም እችል ዘንድ በበኩሌ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? እንዲህ ማድረጌስ ምን ውጤት ያስገኝልኛል?’ እስቲ እንመልከት።
‘ምሉዓን ሆናችሁ ለመቆም’ ጣሩ
4. የቆላስይስ ክርስቲያኖች “ምሉዓን” መሆን የነበረባቸው በምን መንገድ ነው?
4 ኤጳፍራ በቆላስይስ የሚገኙ መንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ‘በመጨረሻ ምሉዓን ሆነው እንዲቆሙ’ ልባዊ ምኞቱ ነበር። ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት “ምሉዕ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ፍጹም፣ ሙሉ ሰው ወይም ጎልማሳ የሚል መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። (ማቴዎስ 19:21፤ ዕብራውያን 5:14፤ ያዕቆብ 1:4, 25) አንድ ሰው የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር መሆኑ ጎልማሳ ክርስቲያን ሆኗል ማለት እንዳልሆነ ታውቅ ይሆናል። ጳውሎስ ከቆላስይስ በስተ ምዕራብ በሚገኘው በኤፌሶን የሚገኙ እረኞችና አስተማሪዎች ‘ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እንዲደርሱ’ ለመርዳት ጥረት እንዲያደርጉ ጽፎላቸዋል። በሌላም ቦታ ጳውሎስ “በማስተዋል ችሎታቸው የጎለመሱ” እንዲሆኑ ክርስቲያኖችን አጥብቆ አሳስቧል።—ኤፌሶን 4:8-13፤ 1 ቆሮንቶስ 14:20 NW
5. ምሉዕ መሆንን ዋነኛ ግባችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
5 በመንፈሳዊ ሙሉ ሰው ወደ መሆን ደረጃ ያልደረሱ ወይም ያልጎለመሱ አንዳንድ የቆላስይስ ክርስቲያኖች ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ግብ ማድረግ ነበረባቸው። የእኛስ ግብ ይህ መሆን የለበትምን? የተጠመቅነው ከአሥርተ ዓመታት በፊትም ይሁን በቅርቡ በማመዛዘን ችሎታችንና በአመለካከታችን በሚገባ እድገት እንዳደረግን ሆኖ ይሰማናል? ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመረምራለን? ከአምላክና ከጉባኤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ እየያዙ መጥተዋል ወይስ ሲመቸን ብቻ የምናከናውናቸው ነገሮች ሆነዋል? ምሉዓን ወደመሆን እድገት ማድረጋችንን ልናንጸባርቅ የምንችልባቸውን ሁሉንም አጋጣሚዎች እዚህ ላይ መዘርዘር ባንችልም ሁለት ምሳሌዎችን ግን እንመልከት።
6. አንድ ሰው ይሖዋን በመምሰል ፍጹም ወደመሆን እድገት ሊያደርግ የሚችልበት አንደኛው መስክ ምንድን ነው?
6 የመጀመሪያ ምሳሌ:- ያደግነው ከሌላ ዘር፣ አገር ወይም አካባቢ ለመጡ ሰዎች ጭፍን ጥላቻ በሚያሳይ አካባቢ ነው እንበል። አሁን አምላክ እንደማያዳላና እኛም የእርሱን ምሳሌ መከተል እንዳለብን አውቀናል። (ሥራ 10: 14, 15, 34, 35) በጉባኤያችን ወይም በወረዳችን ከሌላ አካባቢ የመጡ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ አብረናቸው መሆናችን አይቀርም። ታዲያ እነዚህን ሰዎች በተመለከተ ገና ያልተወገደ አሉታዊ ወይም የጥርጣሬ ስሜት በውስጣችን ይኖር ይሆን? ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ በጣም ቀላል የሆነ ስህተት ወይም በደል ቢፈጽምብን አንድ ዓይነት አሉታዊ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እንቸኩላለን? ‘የአምላክ ዓይነት ከአድሎ ነፃ የሆነ አመለካከት ለመያዝ ተጨማሪ እድገት ማድረግ ይኖርብኝ ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
7. እንደ ክርስቲያን መጠን ምሉዕ መሆን ስለ ሌሎች ምን አመለካከት መያዝን ያካትታል?
7 ሁለተኛ ምሳሌ:- ፊልጵስዩስ 2:3 “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር” በማለት ይናገራል። በዚህ በኩል እድገት እያደረግን ያለነው እንዴት ነው? ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ደካማና ጠንካራ ጎን አለው። ከዚህ በፊት ቶሎ ብለን ማየት የሚቀናን የሌሎችን ደካማ ጎን ከነበረ አሁን ‘ፍጽምና’ የምንጠብቅ ባለመሆን ረገድ እድገት አድርገናል? (ያዕቆብ 3:2) ሌሎች ከእኛ የሚሻሉባቸውን መንገዶች ማየት ችለናል? በምን መንገድ ከእኛ የተሻሉ እንደሆኑ ለማየት እንሞክራለን? ‘ታጋሽ በመሆን ረገድ ይህች እህት ከእኔ የተሻለች መሆኗን ማመን አለብኝ።’ ‘እገሌ ከእኔ ይልቅ ጠንካራ እምነት አለው።’ ‘ግልጹን ለመናገር ከእኔ የተሻለ የማስተማር ችሎታ አለው።’ ‘ቁጣን በመቆጣጠር ረገድ ከእኔ እርሷ ትሻላለች።’ አንዳንድ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ አስፈልጓቸው ሊሆን ይችላል። እኛስ?
8, 9. (ሀ) ኤጳፍራ ምሉዓን ሆነው ‘እንዲቆሙ’ ለቆላስይስ ወንድሞች ያቀረበው ጸሎት መንፈስ ምንድን ነው? (ለ) የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ‘ምሉዓን ሆኖ መቆም’ ምን ነገርን ያመለክታል?
8 ኤጳፍራ የቆላስይስ ክርስቲያኖች ‘ምሉዓን ሆነው እንዲቆሙ’ ጸልዮአል። በግልጽ ለማየት እንደምንችለው የቆላስይስ ወንድሞች ምሉዓን፣ የጎለመሱ፣ የበሰሉ ክርስቲያኖች የሆኑበት ደረጃ ምንም ያህል ይሁን ‘እንዲቆሙ’ ወይም ጎልማሳ ሆነው እንዲመላለሱ ወደ አምላክ ጸልዮአል።
9 ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ጎልማሳ የሆነም ጭምር እንዲህ ማድረጉን ይቀጥላል ብለን መገመት አይኖርብንም። ከአምላክ መላእክታዊ ልጆች መካከል አንዱ ‘በእውነት እንዳልቆመ’ ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44) እንዲሁም ጳውሎስ ቀደም ባሉት ጊዜያት ይሖዋን ሲያገለግሉ ቆይተው ከጊዜ በኋላ ግን አገልግሎታቸውን ስላቆሙ ሰዎች በመጥቀስ ለቆሮንቶስ ወንድሞች ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞችን አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 10:12) ይህም የቆላስይስ ወንድሞች ‘በመጨረሻም ምሉዓን ሆነው እንዲቆሙ’ የቀረበውን ጸሎት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። አንድ ጊዜ ምሉዓንና የጎለመሱ ክርስቲያኖች በኋላ በዚያው መጽናት እንጂ ወደኋላ ማፈግፈግ፣ መዛል ወይም ቀስ በቀስ መወሰድ አይኖርባቸውም። (ዕብራውያን 2:1፤ 3:12፤ 6:6፤ 10:39፤ 12:25) እንዲህ ካደረጉ በሚጎበኙበትና የመጨረሻው ፍርድ በሚሰጥበት ቀን ‘ምሉዓን’ ሆነው ይገኛሉ።—2 ቆሮንቶስ 5:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:12
10, 11. (ሀ) ጸሎትን በተመለከተ ኤጳፍራ ምን ምሳሌ ትቶልናል? (ለ) ኤጳፍራ ካደረገው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ ምን ቁርጥ ያለ አቋም መውሰድ ትፈልጋለህ?
10 ስም ጠቅሶ ለሌሎች የመጸለይን አስፈላጊነት ቀደም ሲል ተመልክተናል። ይሖዋ እንዲረዳቸው፣ እንዲያጽናናቸው፣ እንዲባርካቸውና መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣቸው ለይተን በመጥቀስ መጸለይ ይኖርብናል። ኤጳፍራ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ያቀረበው ጸሎት በዚህ መንገድ የቀረበ ነበር። እኛም ራሳችንን በሚመለከት በምንጸልይበት ጊዜ ለይሖዋ ምን ነገር ጠቅሰን መናገር እንዳለብን የሚጠቁም ሐሳብ በእነዚህ ቃላት ውስጥ ልናገኝ እንችላለን። ደግሞ ማግኘትም ይኖርብናል። እንዲያውም እያንዳንዳችን ‘በመጨረሻው ምሉዓን ሆነን እንድንቆም’ የይሖዋን እርዳታ መለመን እንዳለብን ምንም ጥያቄ የለውም። ታዲያ ትጸልያለህ?
11 ያለህበትን ሁኔታ ለምን በጸሎት አትገልጽም? ‘ምሉዕ’ እና ጎልማሳ በመሆን ረገድ ምን ያህል እድገት እንዳደረግክ ለአምላክ ንገረው። መንፈሳዊነትህን በተመለከተ በምን አቅጣጫ እድገት ማድረግ እንዳለብህ እንዲያሳውቅህ ለምነው። (መዝሙር 17:3፤ 139:23, 24) እድገት ልታደርግባቸው የሚገቡ አንዳንድ መስኮች እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ረገድ ተስፋ ሳትቆርጥ እድገት ማድረግ ትችል ዘንድ እንዲረዳህ አምላክን በግልጽ ተማጸነው። ይህንንም አንድ ጊዜ ብቻ አድርገህ አታቁም። እንዲያውም ‘መጨረሻው ምሉዕ ሆነህ መቆም’ ትችል ዘንድ በሚመጣው ሳምንት ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለምን ወደ ይሖዋ አትጸልይም? እንዲሁም የዓመቱን ጥቅስ በምትመረምርበት ጊዜ ሁሉ ይህን ይበልጥ ለማድረግ እቅድ አውጣ። በምትጸልይበት ጊዜ ከአምላክ አገልግሎት ወደኋላ እንድታፈገፍግ፣ እንድትዳከም ወይም ቀስ በቀስ እንድትወሰድ ሊያደርጉህ በሚችሉ ዝንባሌዎች ላይና እነዚህንም ማሸነፍ በምትችልበት መንገድ ላይ ትኩረት አድርግ።—ኤፌሶን 6:11, 13, 14, 18
ጽኑ እምነት እንዲኖርህ ጸልይ
12. የቆላስይስ ወንድሞች በተለይ “ጽኑ እምነት” መያዝ አስፈልጓቸው የነበረው ለምንድን ነው?
12 የቆላስይስ ክርስቲያኖች በመጨረሻ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንዲችሉ ኤጳፍራ ስለ ሌላ ወሳኝ ነገርም ጸልዮአል። ይህ ጉዳይ ለእኛም የዚያኑ ያህል ወሳኝ ነው። ለመሆኑ ይህ ጉዳይ ምንድን ነው? ኤጳፍራ ‘በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯቸው እንዲቆሙ’ ጸልዮ ነበር። የቆላስይስ ክርስቲያኖች በመናፍቃን ትምህርቶችና ውስጥ ውስጡን በሚሸረሽሩ ፍልስፍናዎች ተከብበው ይኖሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት በአይሁድ አምልኮ ውስጥ ይደረግ እንደነበረው ልዩ ቀናትን በመጾም ወይም ግብዣ በማድረግ እንዲጠብቁ ተጽዕኖዎች ይደርሱባቸው ነበር። የሐሰት አስተማሪዎች ደግሞ ኃያል መናፍስት በሆኑት ማለትም የሙሴን ሕግ ለማስተላለፍ እንደ መሣሪያ ሆነው ባገለገሉት በመላእክት ላይ ትኩረት አድርገው ነበር። እንዲህ ባሉት ተጽዕኖዎች ውስጥ መኖር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን ገምት! እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙ ግራ የሚያጋቡ በርካታ ሐሳቦች ነበሩ።—ገላትያ 3:19፤ ቆላስይስ 2:8, 16-18
13. የቆላስይስ ወንድሞች ምን ነገር መገንዘባቸው ሊረዳቸው ይችላል? እኛንም ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
13 ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጫወተውን ሚና ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ ምላሽ ሰጠ። “እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፣ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ።” አዎን፣ (የቆላስይስ ወንድሞችም ሆኑ እኛ) ክርስቶስ በአምላክ ዓላማ ውስጥም ሆነ በእኛ ሕይወት ውስጥ በሚጫወተው ሚና ላይ የተሟላ እምነት ማሳደር አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ቀጠለ:- “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።”—ቆላስይስ 2:6-10
14. ተስፋ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች እውነተኛ ነገር የነበረው ለምንድን ነው?
14 የቆላስይስ ወንድሞች በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ነበሩ። በሰማይ የመኖር ልዩ ተስፋ ነበራቸው። ይህንንም ተስፋቸውን ብሩሕ አድርገው እንዲጠብቁ የሚያነሳሷቸው በርካታ ምክንያቶች ነበሯቸው። (ቆላስይስ 1:5) በተስፋቸው እርግጠኝነት ላይ የጸና እምነት እንዲኖራቸው ‘የአምላክ ፈቃድ’ ነበር። ከመካከላቸው ይህን ተስፋ የሚጠራጠር ሊኖር ይገባልን? በጭራሽ! አምላክ በሰጠው ገነት በሆነች ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሰዎችስ ከቅቡዓኑ የተለየ አቋም አላቸውን? በፍጹም! ይህ ውድ ተስፋ ‘የአምላክ ፈቃድ’ ክፍል ነው። አሁን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ተመልከት:- “ከታላቁ መከራ” በሕይወት ከሚተርፉት ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ መካከል ለመሆን ጥረት የምታደርግ ከሆንክ ተስፋህ ምን ያህል እውን ሆኖልሃል? (ራእይ 7:9, 14) ይህ ተስፋ ‘በአምላክ ፈቃድ ሁሉ በጽኑ ከምታምንባቸው’ ነገሮች መካከል ነውን?
15. ጳውሎስ ተስፋን ጨምሮ ምን የተያያዙ ነጥቦችን ዘርዝሯል?
15 “ተስፋ” ስንል እንዲያው ባዶ ምኞት ወይም ቅዠት ማለታችን አይደለም። ቀደም ሲል ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በዝርዝር ካሰፈራቸው ነጥቦች ይህንን ማየት እንችላለን። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ነገሮች አንዱ ከሌላው ጋር ተዛማጅነት ያለው ወይም ወደሚቀጥለው የሚመራ ነው። ጳውሎስ ባሰፈረው ዝርዝር ውስጥ ‘ተስፋን’ የት ቦታ ላይ እንዳስቀመጠ ልብ በል:- “መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፣ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፣ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።”—ሮሜ 5:3-5
16. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስትማር ምን ተስፋ አግኝተህ ነበር?
16 የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ባካፈሉህ ጊዜ ትኩረትህን የሳበው ሙታን ያሉበት ሁኔታ ወይም እንደ ትንሣኤ ያለ አንድ ዓይነት እውነት ሊሆን ይችላል። የብዙዎችን ትኩረት በአንደኛ ደረጃ የሳበው መጽሐፍ ቅዱስ ገነት በሆነች ምድር ላይ ስለ መኖር የሚናገረው ተስፋ ነው። እስቲ ይህን ትምህርት መጀመሪያ የሰማህበትን ጊዜ ለማስታወስ ሞክር። በሽታና እርጅና እንደማይኖር፣ በድካምህ ፍሬ እየተደሰትክ እንደምትኖርና እንስሳት ሰላማውያን እንደሚሆኑ የሚናገረው ተስፋ እንዴት ያለ ድንቅ ተስፋ ነው! (መክብብ 9:5, 10፤ ኢሳይያስ 65:17-25፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:3, 4) ድንቅ የሆነ ተስፋ አግኝተሃል!
17, 18. (ሀ) ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች ያሰፈረው ዝርዝር ተስፋ ላይ የሚያደርሰው እንዴት ነው? (ለ) በሮሜ 5:4, 5 ላይ የተገለጸው ተስፋ ምን ዓይነት ተስፋ ነው? እንዲህ ያለውስ ተስፋ አለህ?
17 ከጊዜ በኋላ አንድ ዓይነት ተቃውሞ ወይም ስደት ገጥሞህ ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 10:34-39፤ 24:9) እንዲያውም በቅርብ ጊዜያት በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ምሥክሮች ቤታቸው ተበዝብዟል ወይም ስደተኞች ሆነው እንዲኖሩ ተገድደዋል። አንዳንዶቹ አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን ተነጥቀዋል ወይም በመገናኛ ብዙኃን የሐሰት ወሬ ተነዝቶባቸዋል። አንተም ምንም ዓይነት ስደት ቢደርስብህ ሮሜ 5:3 እንደሚናገረው በመከራው ልትደሰት እንዲሁም ግሩም ውጤት ሊያስገኝልህ ይችላል። እንዲያውም ጳውሎስ እንደጻፈው የደረሰብህ መከራ ጽናትን እድታፈራ አድርጎሃል። ጽናት ደግሞ ሞገስ አስገኝቶልሃል። ትክክል የሆነውን ነገር ማለትም የአምላክን ፈቃድ ታደርግ ስለነበር በእርሱ ፊት ሞገስ እንዳገኘህ ሆኖ ይሰማህ ነበር። ጳውሎስ ባሰፈራቸው ቃላት መሠረት “ሞገስ” እንዳገኘህ ተሰምቶሃል። ቀጥሎም ጳውሎስ “ሞገስም ተስፋን [ያፈራል]” በማለት ጽፏል። ይህ እንግዳ ነገር ሊመስል ይችላል። ጳውሎስ “ተስፋን” በዝርዝሩ ውስጥ ወደ መጨረሻ አካባቢ የጠቀሰው ለምንድን ነው? ቀደም ብለህ ማለትም ምሥራቹን መጀመሪያ ከሰማህበት ጊዜ ጀምሮ ተስፋ አልነበረህም?
18 ጳውሎስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ገና መጀመሪያ ላይ የተሰማንን ፍጹም የሆነ ሕይወት የማግኘት ተስፋ አይደለም። ለመግለጽ የፈለገው ነገር ከዚያ አልፎ የሚሄድ ነው። ይበልጥ ጥልቅና ስሜት የሚቀሰቅስ ነው። ታማኝ ሆነን ስንጸናና የአምላክን ሞገስ እንዳገኘን ሆኖ ሲሰማን መጀመሪያ ላይ ያገኘነው ተስፋችን እንዲጨምርና እንዲጠነክር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህ ተስፋ ይበልጥ እውን እየሆነ፣ የበለጠ እየተጠናከረና ይበልጥ የራስህ እየሆነ ይሄዳል። ይህ ጥልቅ የሆነ ተስፋ ይበልጥ ብሩህ ይሆንልሃል። ከሕልውናችን ጋር በመዋሃድ የደመ ሕይወታችን ክፍል ይሆናል። “የአምላክ ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋው አያሳፍረንም።”
19. ተስፋህ ዘወትር የምታቀርበው ጸሎት ክፍል ሊሆን የሚገባው እንዴት ነው?
19 ኤጳፍራ በቆላስይስ የሚገኙ ወንድሞቹና እህቶቹ ከፊታቸው በሚጠብቃቸው ተስፋ ላይ እንዲያተኩሩና “በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት” እንዲያዳብሩ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። እኛም በተመሳሳይ ተስፋችንን በተመለከተ አዘውትረን ወደ ይሖዋ እንጸልይ። በግልህ በምትጸልይበት ጊዜ በአዲሱ ዓለም ላይ ስላለህ ተስፋ ጥቀስ። ይህ ጊዜ እንደሚመጣ የጸና እምነት በመያዝ ምን ያህል በጉጉት እየተጠባበቅከው እንዳለህ ለይሖዋ ግለጽለት። የጸና እምነትህ ይበልጥ ጥልቀትና ስፋት እንዲኖረው እንዲረዳህ ለምነው። ኤጳፍራ በቆላስይስ ያሉ ወንድሞች “በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት” እንዲኖራቸው እንደጸለየ ሁሉ አንተም ጸልይ። ይህንንም በተደጋጋሚ ጊዜ አድርግ።
20. በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ሰዎች ከክርስትና ጎዳና አፈንግጠው ቢወጡ ይህ ሁኔታ ተስፋ ሊያስቆርጠን የማይገባው ለምንድን ነው?
20 ምሉዓን የሚሆኑትና ጽኑ እምነት ያላቸው ሁሉም አለመሆናቸው እንዲያዘናጋህ ወይም ተስፋ እንዲያስቆርጥህ መፍቀድ አይኖርብህም። አንዳንዶች ሊዳከሙ፣ ሊንሸራተቱ ወይም እንዲሁ ተስፋ ቆርጠው ሊያቆሙ ይችላሉ። ይህ ሁኔታ ለራሱ ለኢየሱስም ሆነ ለሐዋርያቱ ቅርብ በነበሩት በአንዳንዶች ላይ ደርሷል። ይሁን እንጂ ይሁዳ ከዳተኛ በሆነ ጊዜ የቀሩት ሐዋርያት አፈግፍገው ወይም አቁመው ነበር? ፈጽሞ እንደዚያ አላደረጉም! ጴጥሮስ መዝሙር 109:8ን በመጥቀስ የይሁዳን ቦታ ሌላ ሰው እንደሚይዝ ተናግሯል። እርሱን የሚተካው ሰው ተመረጠ፤ እንዲሁም የአምላክ ታማኞች በተሰጣቸው የስብከት ሥራ በንቃት መካፈላቸውን ቀጠሉ። (ሥራ 1:15-26) ጽኑ እምነት በመያዝ ምሉዓን ሆነው ለመገኘት ቆርጠው ነበር።
21, 22. ጽኑ እምነት ኖሮህና ምሉዕ ሆነህ መቆምህን ሌሎች የሚመለከቱት በምን መንገድ ነው?
21 በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሮህና ምሉዕ ሆነህ ለመቆም የምታደርገውን ጥረት የሚመለከት እንደሚኖር እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ይህን ጥረትህን ተመልክቶ የሚያደንቀው ማን ነው?
22 የሚያውቁህና የሚወዱህ ወንድሞችህና እህቶችህ ይመለከታሉ። ምንም እንኳ ብዙዎች በአንደበታቸው ባይናገሩም 1 ተሰሎንቄ 1:2-6 ላይ ከምናነበው ጋር የሚመሳሰል ተጽዕኖ ያሳድራል። “በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፣ የእምነታችሁን ሥራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፣ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤ . . . ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ . . . እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ።” በአካባቢህ ያሉት ወንድሞች ‘በመጨረሻም ምሉዓን ሆነህና በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሮህ እንደቆምክ’ ሲመለከቱ እነርሱም ተመሳሳይ ስሜት ያድርባቸዋል።—ቆላስይስ 1:23
23. በዚህ ዓመት ቁርጥ ውሳኔህ ምን መሆን ይኖርበታል?
23 ሰማያዊ አባትህም እንደሚመለከትና እንደሚደሰት ፍጹም እምነት ይኑርህ። በዚህ ነገር እርግጠኛ ሁን። ለምን? ምክንያቱም “በአምላክ ፈቃድ ሁሉ” ጽኑ እምነት ኖሮህና ምሉዕ ሆነህ ቆመሃል። ጳውሎስ ‘በነገር ሁሉ ደስ እያሰኙ ለይሖዋ እንደሚገባ’ መመላለስን በተመለከተ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የሚያበረታታ ደብዳቤ ጽፏል። (ቆላስይስ 1:10) አዎን፣ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች አምላክን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት ይችላሉ። በቆላስይስ የነበሩ ወንድሞችህና እህቶችህ እንዲህ አድርገው ነበር። በዙሪያህ ያሉ ክርስቲያኖችም በአሁኑ ጊዜ እንዲሁ እያደረጉ ናቸው። አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ! እንግዲያው በመጪው ዓመት በሙሉ ዕለታዊ ጸሎትህም ሆነ ድርጊትህ ‘በመጨረሻም በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሮህና ምሉዕ ሆነህ ለመቆም’ የቆረጥክ መሆንህን የሚያረጋግጥ ይሁን።
ታስታውሳለህን?
• ‘ምሉዕ ሆነህ ለመቆም’ ምን ነገር ማድረግ ይጠይቃል?
• ያለህበትን ሁኔታ በተመለከተ በጸሎትህ ውስጥ ልታካትታቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
• በሮሜ 5:4, 5 ላይ በሰፈረው ሐሳብ መሠረት እንዲኖርህ የምትፈልገው ምን ዓይነት ተስፋ ነው?
• ያጠናነው ትምህርት በዚህ ዓመት ምን ግብ እንዲኖርህ አነሳስቶሃል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤጳፍራ ወንድሞቹ ምሉዓን እንዲሆኑ፣ ክርስቶስንና ተስፋቸውን በተመለከተ ጽኑ እምነት እንዲኖራቸው ጸልዮአል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአንተው ዓይነት እርግጠኛ ተስፋና ጽኑ እምነት ያላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ