በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍቅር ታነጹ

በፍቅር ታነጹ

በፍቅር ታነጹ

“ጌታ [“ይሖዋ፣” NW ] አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።”​—⁠ማቴዎስ 22:​37

1. (ሀ) አንድ ክርስቲያን የሚያዳብራቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ክርስቲያናዊ ባሕርይ የትኛው ነው? ለምን?

 አንድ ክርስቲያን ውጤታማ አገልጋይ መሆን እንዲችል ሊያዳብራቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ። የምሳሌ መጽሐፍ የእውቀትን፣ የማስተዋልንና የጥበብን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ምሳሌ 2:​1-10) ሐዋርያው ጳውሎስ ጽኑ እምነትና ጠንካራ ተስፋ አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጿል። (ሮሜ 1:​16, 17፤ ቆላስይስ 1:​51980 ትርጉም፤ ዕብራውያን 10:​39) ጽናትና ራስን መግዛትም እንዲሁ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። (ሥራ 24:​25፤ ዕብራውያን 10:​36) ሆኖም የእርሱ መጉደል ሌሎች ባሕርያትን ሁሉ ሊያዳክም አልፎ ተርፎም ዋጋ ሊያሳጣ የሚችል አንድ ባሕርይ አለ። ይህም ፍቅር ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​1-3, 13

2. ኢየሱስ የፍቅርን አስፈላጊነት የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥያቄዎችን ያስነሳል?

2 ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሎ በመናገር የፍቅርን አስፈላጊነት አመልክቷል። (ዮሐንስ 13:​35) ፍቅር የአንድ እውነተኛ ክርስቲያን መለያ ምልክት ስለሆነ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቃችን አስፈላጊ ይሆናል:- ፍቅር ምንድን ነው? ኢየሱስ ከሌሎች ባሕርያት ይልቅ ፍቅር የደቀ መዛሙርቱ መለያ ምልክት እንደሆነ አድርጎ መጥቀሱ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የሆነው ለምንድን ነው? ፍቅርን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ፍቅራችንን ማሳየት የሚኖርብንስ ለማን ነው? እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች እንመርምር።

ፍቅር ምንድን ነው?

3. ፍቅር እንዴት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል? ከአእምሮም ሆነ ከልብ ጋር የተያያዘ የሆነውስ ለምንድን ነው?

3 ፍቅር ‘የሞቀ ወዳጃዊ ቅርርብ፣ የጠበቀ ወይም የሞቀ የመውደድ ስሜት’ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ መሥዋዕትነትንም እንኳ ቢሆን በመክፈል ለሌሎች መልካም እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ባሕርይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ፍቅር ከአእምሮም ሆነ ከልብ ጋር የተያያዘ ባሕርይ ነው። አንድ ሰው ሌሎችን የሚያፈቅረው እርሱም ሆነ የሚያፈቅራቸው ሌሎች ሰዎች ድክመት እንዲሁም ማራኪ የሆኑ ባሕርያት እንዳሏቸው ተገንዝቦ ስለሚሆን አእምሮ ወይም የማሰብ ችሎታ በዚህ ረገድ የሚጫወተው ሚና አለው። አንድ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ምናልባትም አንዳንድ ጊዜ ከእሱ የተፈጥሮ ዝንባሌ ጋር የማይጣጣሙ ሰዎችን ጭምር እንዲወድ አምላክ እንደሚፈልግበት ይገነዘባል። ይህ ደግሞ ፍቅር ከማሰብ ችሎታ ጋር የሚያያዝበት ሌላ ምክንያት ነው። (ማቴዎስ 5:​44፤ 1 ቆሮንቶስ 16:​14) ያም ሆኖ የፍቅር መፍለቂያ ልብ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እውነተኛ ፍቅር በጭንቅላት እውቀት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። ከልብ የሚመነጭና ከውስጥ ፈንቅሎ የሚወጣ ስሜት ነው።​—⁠1 ጴጥሮስ 1:​22

4. ፍቅር ጠንካራ ማሰሪያ የሆነው በምን መንገድ ነው?

4 አፍቃሪ የሆነ ሰው ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ለማስቀደም ዝግጁ ስለሆነ ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች እውነተኛ ፍቅር ያለበት ወዳጅነት መመሥረት አይችሉም። (ፊልጵስዩስ 2:​2-4) “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW ] ነው” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት እውነት መሆናቸውን መመልከት የሚቻለው በተለይ በፍቅር ተገፋፍቶ የተደረገ ከሆነ ነው። (ሥራ 20:​35) ፍቅር ጠንካራ ማሰሪያ ነው። (ቆላስይስ 3:​14) ፍቅር ብዙውን ጊዜ ወዳጅነትንም ይጨምራል፤ ሆኖም የፍቅር ማሰሪያ ከወዳጅነትም ይበልጥ ጠንካራ ነው። በባልና በሚስት መካከል ያለው የመዋደድ ስሜትም አንዳንድ ጊዜ ፍቅር ተብሎ ይገለጻል፤ ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንድናዳብረው የሚያበረታታን የፍቅር ዓይነት በአካላዊ ውበት ላይ ከተመሠረተ የመሳሳብ ስሜት ይበልጥ ዘላቂ ነው። አንድ ባልና ሚስት በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር ካለ በዕድሜ መግፋት ወይም በሌላ አካላዊ ችግር ምክንያት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ባይችሉ እንኳ አንድ ላይ ጸንተው ይኖራሉ።

ፍቅር​—⁠እጅግ አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ

5. ፍቅር ለአንድ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ፍቅር ለአንድ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት፣ ኢየሱስ ተከታዮቹ እርስ በርስ እንዲዋደዱ አዝዟል። “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ።” (ዮሐንስ 15:​14, 17) ሁለተኛው ምክንያት፣ ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት ነው፤ እኛ ደግሞ አምላኪዎቹ እንደመሆናችን መጠን እሱን መምሰል ይኖርብናል። (ኤፌሶን 5:​1፤ 1 ዮሐንስ 4:​16) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋንና ኢየሱስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ ይናገራል። እሱን ለመምሰል ጥረት የማናደርግ ከሆነ እንዴት አምላክን አውቀዋለሁ ብለን መናገር እንችላለን? ሐዋርያው ዮሐንስ “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” ሲል ተናግሯል።​—⁠1 ዮሐንስ 4:​8

6. ፍቅር በተለያዩ የሕይወታችን ዘርፎች ሚዛናዊ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

6 ፍቅር አስፈላጊ የሆነበት ሦስተኛ ምክንያትም አለ። በተለያየ የሕይወታችን ዘርፍ ሚዛናዊ እንድንሆን ከመርዳቱም በላይ ለምናከናውናቸው ነገሮች ትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት እንዲኖረን ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል የአምላክን ቃል ያለ ማቋረጥ መመገቡ በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነቱ እውቀት ለእሱ እንደ ምግብ ነው። ወደ ጉልምስና እንዲያድግና ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመላለስ ይረዳዋል። (መዝሙር 119:​105፤ ማቴዎስ 4:​4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​15, 16) ሆኖም ጳውሎስ “እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 8:​1) እርግጥ ነው፣ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት በራሱ ምንም ችግር የለውም። ችግሩ ያለው ከእኛው ከራሳችን ማለትም ከኃጢአተኛው ዝንባሌያችን ነው። (ዘፍጥረት 8:​21) ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዳው የፍቅር ባሕርይ ከሌለ እውቀት አንድን ሰው ከሌሎች የተሻለ እንደሆነ እንዲያስብና እንዲታበይ ሊያደርገው ይችላል። ማንኛውንም ነገር በፍቅር ተገፋፍቶ የሚያከናውን ከሆነ ግን እንዲህ ያለው ሁኔታ አይከሰትም። “ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም።” (1 ቆሮንቶስ 13:​4) አንድ ክርስቲያን ከውስጥ የሚገፋፋው ፍቅር ከሆነ ጥልቅ እውቀት ቢኖረውም እንኳ አይታበይም። ፍቅር በትሕትና እንዲመላለስና ለራሱ ክብር ከመፈለግ እንዲቆጠብ ያደርገዋል።​—⁠መዝሙር 138:​6፤ ያዕቆብ 4:​6

7, 8. ፍቅር ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንድናተኩር የሚረዳን እንዴት ነው?

7 ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል ጽፎላቸዋል:- “ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፣ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፣ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።” (ፊልጵስዩስ 1:​9-11) ክርስቲያናዊ ፍቅር ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንድንለይ የተሰጠንን ይህን ማበረታቻ ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዳናል። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን [“የበላይ ተመልካችነትን፣” NW ] ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል” ሲል ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የተናገራቸውን ቃላት ልብ በል። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1) በ2000 የአገልግሎት ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የጉባኤዎች ቁጥር በ1, 502 የጨመረ ሲሆን ይህም የጉባኤዎችን ጠቅላላ ቁጥር 91, 487 አድርሶታል። ስለዚህ ተጨማሪ ሽማግሌዎች ስለሚፈለጉ ለዚህ መብት ለመብቃት የሚጣጣሩ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል።

8 ሆኖም የበላይ ተመልካችነት መብት ለማግኘት የሚጣጣሩ ሁሉ የዚህ ዓይነቱን መብት ዓላማ በአእምሮአቸው ከያዙ ሚዛናቸውን በሚገባ ሊጠብቁ ይችላሉ። ዋናው ነገር ሥልጣን የማግኘት ወይም ታዋቂ የመሆን ጉዳይ አይደለም። ይሖዋ ለእሱና ለወንድሞቻቸው ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው በሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ይደሰታል። ለራሳቸው ክብር ለማግኘት ወይም በሌሎች ላይ ለመሰልጠን አይፈልጉም። ሐዋርያው ጴጥሮስ የጉባኤ ሽማግሌዎች ትክክለኛውን ዝንባሌ እንዲይዙ ከመከረ በኋላ ‘የትሕትናን’ አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። “ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” ሲል በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ሁሉ መክሯል። (1 ጴጥሮስ 5:​1-6) ለዚህ መብት የሚጣጣር ማንኛውም ሰው በታታሪነታቸውና በትሕትናቸው ለጉባኤዎቻቸው በረከት የሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሽማግሌዎችን ምሳሌ ልብ ቢል ጥሩ ነው።​—⁠ዕብራውያን 13:​7

ትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት እንድንጸና ይረዳናል

9. ክርስቲያኖች ይሖዋ ቃል የገባቸውን በረከቶች በአእምሮአቸው የሚይዙት ለምንድን ነው?

9 አንድን ነገር በፍቅር ተነሳስቶ የማድረግ አስፈላጊነት በሌላም መንገድ ይታያል። በፍቅር ተነሳስተው ለአምላክ የማደርን ባሕርይ የሚከታተሉ ሰዎች አሁን የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያገኙ ወደፊት ደግሞ ይህ ነው የማይባል አስደናቂ በረከት እንደሚጠብቃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጣል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​8 NW ) አንድ ክርስቲያን በእነዚህ ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት መገንባቱና ይሖዋ ደግሞ ‘ለሚፈልጉት ዋጋ እንደሚሰጥ’ ማመኑ በእምነት ጸንቶ እንዲቀጥል ይረዳዋል። (ዕብራውያን 11:​6) አብዛኞቻችን አምላክ የገባልንን ተስፋዎች ፍጻሜ በጉጉት ስለምንጠባበቅ “አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ና” ሲል ሐዋርያው ዮሐንስ የተናገራቸውን ቃላት እናስተጋባለን። (ራእይ 22:​20) ኢየሱስ ‘በፊቱ ስላለው ደስታ’ ማሰቡ እንዲጸና እንደረዳው ሁሉ እኛም የታመንን ሆነን ከተገኘን ምን በረከቶች እንደሚጠብቁን ማሰላሰላችን እንድንጸና ይረዳናል።​—⁠ዕብራውያን 12:​1, 2

10, 11. ዋነኛው የሚገፋፋን ኃይል ፍቅር መሆኑ እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?

10 ሆኖም ይሖዋን እንድናገለግል የሚገፋፋን ዋነኛው ነገር በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት ለማግኘት ያለን ምኞት ቢሆንስ? እንደዚያ ከሆነ ነገሮች እየከበዱ ሲመጡ ወይም እኛ ተስፋ ባደረግነው መንገድ ወይም ጊዜ ሳይፈጸሙ ሲቀሩ በቀላሉ ትዕግሥት ልናጣ ወይም ቅር ልንሰኝ እንችላለን። ቀስ በቀስ የመወሰድ አደጋም ሊያጋጥመን ይችላል። (ዕብራውያን 2:​1፤ 3:​12) ጳውሎስ፣ ትቶት ስለሄደው ዴማስ ስለሚባል የቀድሞ ጓደኛው ጠቅሶ ተናግሯል። ዴማስ ጳውሎስን ትቶት የሄደው ለምንድን ነው? ‘ዓለምን ስለወደደ ነው።’ (2 ጢሞቴዎስ 4:​10) ለጥቅም ሲል ብቻ በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ተመሳሳይ እርምጃ የመውሰድ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል። ዓለም አሁኑኑ በሚያቀርብለት አጋጣሚዎች በቀላሉ ሊሳብና ወደፊት አገኛቸዋለሁ ብሎ ተስፋ ለሚያደርጋቸው በረከቶች ሲል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ሳይሆን ሊቀር ይችላል።

11 በረከቶችን ለማግኘት እንዲሁም ከፈተናዎች ለመገላገል መጓጓት ተገቢና ያለ ነገር ቢሆንም ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ ስለሚገባው ጉዳይ በውስጣችን አድናቆት እንዲገነባ ያደርጋል። በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የይሖዋ ፈቃድ እንጂ የእኛ አይደለም። (ሉቃስ 22:​41, 42) አዎን፣ ፍቅር ያንጻል። አምላካችንን በትዕግሥት እንድንጠባበቅ፣ በሚሰጠን በረከቶች እንድንደሰትና የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ የገባልንን ተስፋዎች በሙሉ እንደምንቀበል እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። (መዝሙር 145:​16፤ 2 ቆሮንቶስ 12:​8, 9) ‘ፍቅር የራሱን ስለማይፈልግ’ እስከዚያው ጊዜ ድረስ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንፈስ አምላክን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5

ክርስቲያኖች መውደድ ያለባቸው ማንን ነው?

12. ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ማንን መውደድ አለብን?

12 ኢየሱስ ከሙሴ ሕግ ሁለት አንቀጾችን በጠቀሰ ጊዜ ማንን መውደድ እንዳለብን በተመለከተ አጠቃላይ ደንብ አስቀምጧል። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” ካለ በኋላ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 22:​37-39

13. ልናየው ባንችልም እንኳ ይሖዋን መውደድን ልንማር የምንችለው እንዴት ነው?

13 ከምንም ከማንም በላይ ይሖዋን መውደድ እንዳለብን ከኢየሱስ አነጋገር በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ሆኖም ለይሖዋ የተሟላ ፍቅር ይዘን አንወለድም። ይህ ልናዳብረው የሚገባ ነገር ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ እሱ ስንሰማ የሰማነው ነገር ወደ እሱ እንድንሳብ አድርጎናል። ምድርን ለሰው ልጆች እንዴት እንዳዘጋጃት ደረጃ በደረጃ አወቅን። (ዘፍጥረት 2:​5-23) ኃጢአት ለመጀመሪያ ጊዜ ሰብአዊውን ቤተሰብ ሲበክል የራሳቸው ጉዳይ ብሎ ከመተው ይልቅ እኛን ለመዋጀት እርምጃ በመውሰድ ለሰው ዘር ምን ዓይነት አያያዝ እንዳደረገ ተማርን። (ዘፍጥረት 3:​1-5, 15) የታመኑ ሆነው የተገኙትን በደግነት የያዘ ሲሆን በመጨረሻም ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን አንድያ ልጁን ሰጠ። (ዮሐንስ 3:​16, 36) ይህ እየጨመረ የሚሄድ እውቀት ለይሖዋ ያለን አድናቆት እያደገ እንዲሄድ አድርጓል። (ኢሳይያስ 25:​1) ንጉሥ ዳዊት ከፍቅራዊ እንክብካቤው የተነሳ ይሖዋን እንደ ወደደው ተናግሯል። (መዝሙር 116:​1-9) ዛሬ ይሖዋ ይንከባከበናል፣ ይመራናል፣ ያጠነክረናል እንዲሁም ያበረታታናል። ስለ እሱ ይበልጥ ባወቅን መጠን ፍቅራችን ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል።​—⁠መዝሙር 31:​23፤ ሶፎንያስ 3:​17፤ ሮሜ 8:​28

ፍቅራችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14. ለአምላክ ያለን ፍቅር እውነተኛ መሆኑን በምን መንገድ ማሳየት እንችላለን?

14 እርግጥ ነው፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች አምላክን እንደሚወዱት ይናገራሉ፤ ሆኖም ድርጊታቸው ከዚህ አባባላቸው ጋር ይጋጫል። ይሖዋን በእርግጥ እንደምንወደው እንዴት ማወቅ እንችላለን? በጸሎት ወደ እሱ ልንቀርብና ከውስጥ የሚሰማንን ልንነግረው እንችላለን። እንዲሁም እንደምንወደው በሚያሳይ መንገድ መመላለስ እንችላለን። ሐዋርያው ዮሐንስ “ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን” ብሏል። (1 ዮሐንስ 2:​5፤ 5:​3) በተጨማሪም የአምላክ ቃል አንድ ላይ እንድንሰበሰብና በንጹህ ሥነ ምግባር እንድንመላለስ ያሳስበናል። ከግብዝነት እንርቃለን፣ እውነትን እንናገራለን እንዲሁም አስተሳሰባችን እንዳይቆሽሽ እንጠነቀቃለን። (2 ቆሮንቶስ 7:​1፤ ኤፌሶን 4:​15፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:​5፤ ዕብራውያን 10:​23-25) የተቸገሩትን በቁሳዊ በመርዳትም ፍቅርን እናሳያለን። (1 ዮሐንስ 3:​17, 18) እንዲሁም ስለ ይሖዋ ለሌሎች ለመናገር ወደኋላ አንልም። ይህም በዓለም አቀፉ የመንግሥቱ የምሥራች ስብከት መካፈልን ይጨምራል። (ማቴዎስ 24:​14፤ ሮሜ 10:​10) እንዲህ በመሳሰሉት ነገሮች የአምላክን ቃል መታዘዝ ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

15, 16. ባለፈው ዓመት ብዙዎች ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ሕይወታቸው የተነካው እንዴት ነው?

15 ይሖዋን ማፍቀር ሰዎች ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ይረዳል። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ባለፈው ዓመት 288, 907 ግለሰቦች ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑና ይህን ውሳኔያቸውንም በውኃ ጥምቀት እንዲያሳዩ ገፋፍቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ይህ እርምጃቸው ትልቅ ትርጉም ነበረው። በሕይወታቸው ላይ ለውጥ እንዳደረጉ የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል ጋዝመንድ በአልባንያ ውስጥ በኮከብ ቅርጫት ኳስ ተጫዋችነት የሚታወቅ ሰው ነበር። እሱና ባለቤቱ ለተወሰኑ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ሲሆን አንዳንድ መሰናክሎች ቢያጋጥሟቸውም በመጨረሻ የመንግሥቱ አስፋፊ ለመሆን በቅተዋል። ጋዝመንድ ባለፈው ዓመት የተጠመቀ ሲሆን በ2000 የአገልግሎት ዓመት በአልባንያ ከተጠመቁት 366 ሰዎች መካከል አንዱ ነው። አንድ ጋዜጣ ስለ እሱ ሲጽፍ እንደሚከተለው ብሏል:- “ሕይወቱ ዓላማ አለው፤ ስለሆነም እሱና ቤተሰቡ በሕይወታቸው ውስጥ አይተውት የማያውቁትን ደስታ በማግኘት ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት እርሱን የሚያሳስበው ነገር እንዴት አድርጎ ራሱን መጥቀም እንደሚችል ሳይሆን ሌሎችን እንዴት መጥቀም እችላለሁ የሚለው ነው።”

16 በተመሳሳይም በጉዋም ለአንድ የነዳጅ ኩባንያ የምትሠራ በቅርቡ የተጠመቀች አንዲት እኅት ፈታኝ የሆነ አንድ ግብዣ ቀርቦላታል። ለዓመታት የተለያየ የሥራ እድገት ስታገኝ ከቆየች በኋላ በመጨረሻ በኩባንያው ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት እንድትሆን ግብዣ ቀረበላት። ሆኖም አሁን ሕይወቷን ለይሖዋ ወስናለች። በመሆኑም ስለ ጉዳዩ ከባሏ ጋር ከተማከረች በኋላ አዲሷ እኅት ግብዣውን ሳትቀበል ቀረች፤ ከዚህ ይልቅ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ማለትም አቅኚ መሆን ትችል ዘንድ ግማሽ ቀን ለመሥራት ሁኔታዎችን አመቻቸች። የዚህን ዓለም ገንዘብ ከማሳደድ ይልቅ ለይሖዋ ያላት ፍቅር አቅኚ ሆና እንድታገለግለው ገፋፋት። በእርግጥም በ2000 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ 805, 205 የሚሆኑ ሰዎች በተለያየ የአቅኚነት አገልግሎት ዘርፍ እንዲካፈሉ የገፋፋቸው እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ነው። እነዚህ አቅኚዎች ያደረጉት እንዴት ያለ ግሩም የፍቅርና የእምነት መግለጫ ነው!

ኢየሱስን ለመውደድ መገፋፋት

17. ኢየሱስ ፍቅርን በተመለከተ ምን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል?

17 አንድን ነገር በፍቅር ተነሳስቶ በማድረግ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ነው። ሰው ከመሆኑ በፊት አባቱንና የሰውን ዘር ይወድድ ነበር። በጥበብ ተመስሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፣ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ።” (ምሳሌ 8:​30, 31) ኢየሱስ ሰማያዊ መኖሪያውን እንዲተውና ራሱን ምንም መከላከል የማይችል ሰብአዊ ሕፃን ሆኖ እንዲወለድ የገፋፋው ፍቅሩ ነው። የተቸገሩትንና ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን በትዕግሥትና በደግነት ከመያዙም በላይ በይሖዋ ጠላቶች እጅ ሥቃይ ደርሶበታል። በመጨረሻም ለመላው የሰው ዘር ሲል በመከራ እንጨት ላይ ሞቷል። (ዮሐንስ 3:​35፤ 14:​30, 31፤ 15:​12, 13፤ ፊልጵስዩስ 2:​5-11) ትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት በማሳደር ረገድ ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

18. (ሀ) ለኢየሱስ ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስን እንደምንወደው የምናሳየው በምን መንገድ ነው?

18 ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገሩትን የወንጌል ዘገባዎች ሲያነቡና የተከተለው የታማኝነት ጎዳና ያስገኘላቸውን በረከት ሲገነዘቡ ለእሱ የጠለቀ ፍቅር ያድርባቸዋል። እኛ ዛሬ ጴጥሮስ “እርሱንም [ኢየሱስን] ሳታዩት ትወዱታላችሁ” ሲል እንደጻፈላቸው ሰዎች ነን። (1 ጴጥሮስ 1:​8) በእሱ ስናምንና እሱ የተወልንን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ አኗኗር ስንኮርጅ ፍቅራችን ይታያል። (1 ቆሮንቶስ 11:​1፤ 1 ተሰሎንቄ 1:​6፤ 1 ጴጥሮስ 2:​21-25) ሚያዝያ 19, 2000 ዓመታዊው የሞቱ መታሰቢያ በተከበረበት ዕለት በዚያ የተገኙ 14, 872, 086 ሰዎች ኢየሱስን እንድንወደው የሚገፋፉን ምክንያቶች ምን እንደሆኑ እንዲያስታውሱ ተደርገዋል። ይህ ምንኛ ከፍተኛ ቁጥር ነው! እንዲሁም በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት መዳንን ለማግኘት የሚፈልጉ ይህን ያህል ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ማወቅ እንዴት የሚያበረታታ ነው! በእርግጥም ይሖዋና ኢየሱስ ለእኛ ባላቸው ፍቅርና እኛ ለእነሱ ባለን ፍቅር ታንጸናል።

19. ፍቅርን በሚመለከት የትኞቹ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራሉ?

19 ኢየሱስ በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችን፣ አሳባችንና ኃይላችን ይሖዋን መውደድ እንዳለብን ተናግሯል። ሆኖም ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ እንዳለብንም ተናግሯል። (ማርቆስ 12:​29-31) ታዲያ ይህ እነማንን ይጨምራል? ባልንጀራችንን መውደዳችን ተገቢ በሆነ መንገድ ሚዛናችንን እንድንጠብቅና ትክክለኛ የውስጥ ግፊት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራሉ።

ታስታውሳለህን?

• ፍቅር እጅግ አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው?

• ይሖዋን መውደድን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

• አኗኗራችን ይሖዋን እንደምንወድ የሚያሳየው እንዴት ነው?

• ኢየሱስን እንደምንወደው የምናሳየው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍቅር ከመከራ የምንገላገልበትን ጊዜ በትዕግሥት እንድንጠባበቅ ይረዳናል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የከፈለው ከፍተኛ መሥዋዕትነት እንድንወደው ይገፋፋናል