በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ችግር ቢኖርም በሙሉ ነፍስ ማገልገል

ችግር ቢኖርም በሙሉ ነፍስ ማገልገል

የሕይወት ታሪክ

ችግር ቢኖርም በሙሉ ነፍስ ማገልገል

ሮዶልፎ ሎዛኖ እንደተናገረው

የተወለድኩት መስከረም 17, 1917 በሜክሲኮ፣ ዱራጎ ግዛት በምትገኘው በጎሜዝ ፓላሲዮ ነው። በዚህ ወቅት የሜክሲኮ አብዮት ተፋፍሞ ነበር። አብዮቱ በ1920 ያቆመ ቢሆንም እንኳ በምንኖርበት አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት ለበርካታ ዓመታት በመቀጠሉ ኑሮ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።

እማማ በዓማፅያኑና በመንግሥት ወታደሮች መካከል ግጭት እንደሚቀሰቀስ ስለተገነዘበች እኔን፣ ሦስት ወንድሞቼንና ሁለት እህቶቼን ለተወሰኑ ቀናት ከቤት እንዳንወጣ አደረገችን። የምንበላው ምግብ አልነበረንም ለማለት ይቻላል። ከታናሽ እህቴ ጋር አልጋ ሥር ተደብቀን እንደነበር ትዝ ይለኛል። ከዚህ በኋላ እማማ ሁሉንም ልጆች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ይዛን ለመሄድ ወሰነች። ከጊዜ በኋላም አባባ ከእኛ ጋር ተደባለቀ።

ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ዩናይትድ ስቴትስን ከመምታቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ማለትም በ1926 ወደ ካሊፎርኒያ ሄድን። ሳን ጆአኪን ቫሊ፣ ሳንታ ክላራ፣ ሳሊናስ እና ኪንግ ሲቲ የተባሉ ቦታዎችን ጨምሮ ሥራ ፍለጋ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሄደናል። ማሳ ላይ መሥራትንና በርካታ ዓይነት ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን መሰብሰብን ተማርን። በወጣትነቴ ከባድ የጉልበት ሥራ እሠራ የነበረ ቢሆንም ለእኔ አስደሳች ወቅት ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ደረሰን

መጋቢት 1928 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) እቤታችን መጣ። ኤስቴባን ሪቬራ የሚባል ሲሆን በዕድሜ የገፋ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ ነው። “ሙታን የት ናቸው?” የሚል ርዕስ ያለው አንድ ቡክሌት ሰጥቶን ሄደ። የቡክሌቱን ርዕስና የርዕስ ማውጫውን ስመለከት በጣም ተገረምኩ። ልጅ የነበርኩ ቢሆንም እንኳ በጥናቴ ገፋሁና ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መተባበር ጀመርኩ። ቀስ ብሎም እናቴና አውሮራ የተ​ባለችው እህቴ ቀናተኛ የይሖዋ አወዳሾች ሆኑ።

በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ በሳን ሆሴ ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ ጉባኤ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ተሠራ። በዚህ አካባቢ በግብርና የሚተዳደሩ በርካታ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎች ስለነበሩ ለእነርሱ መስበክና የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስብሰባ ማድረግ ጀመርን። ይህን ማድረግ እንችል ዘንድ 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ከሚገኘው ከሳን ፍራንሲስኮ የመጡ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ ምሥክሮች ረድተውናል። ከጊዜ በኋላ በሳን ሆሴ የመንግሥት አዳራሽ በስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስብሰባ ላይ ወደ 60 የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች ይገኙ ነበር።

በመጨረሻ የካቲት 28, 1940 ሳን ሆሴ ተደርጎ በነበረው አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። በቀጣዩ ዓመት አቅኚ ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። ከዚያም 130 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቃ ወደምትገኘው ስቶክቶን ወደምትባል ከተማ እንድሄድና እዚያም የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጉባኤ እንዳቋቁም ሚያዝያ 1943 ግብዣ ቀረበልኝ። በዚህ ወቅት ሳን ሆሴ በሚገኘው የእንግሊዝኛ ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ እያገለገልኩ በዚህ ከተማ ያለውን የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ ምሥክሮችን ሥራ እከታተል ነበር። እነዚህን ኃላፊነቶች ሌሎች እንዲሠሩት ዝግጅት ካደረግሁ በኋላ ወደ ስቶክተን አመራሁ።

የአቋም ጽናቴ ተፈተነ

ከ1940 ጀምሮ በተደጋጋሚ የምልመላው ቦርድ ፊት የቀረብሁ ሲሆን በሕሊናዬ ምክንያት አልዋጋም በማለት የወሰድኩት አቋም ተከብሮልኛል። ወዲያው ታኅሣሥ 1941 ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በገባችበት ወቅት የምልመላው ቦርድ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እያየለ መጣ። በመጨረሻ በ1944 እስር ቤት ገባሁ። ፍርዴን እየተጠባበቅሁ የነበረው ወንጀለኞች ታሥረው ባሉበት ምድር ቤት ውስጥ ሆኜ ነበር። ብዙዎቹ እስረኞች የይሖዋ ምሥክር መሆኔን በማወቃቸው በፈጸሙት ወንጀል ምክንያት አምላክ እንዴት አድርጎ እንደሚመለከታቸው ለማወቅ ጥያቄ ይጠይቁ ነበር።

ፍርድ ቤት እስክቀርብ ድረስ በሳን ሆሴ የሚኖሩ ምሥክሮች የገንዘብ ዋስ ከፍለው ከእስር ቤት አስወጡኝ። ስለ ሰብዓዊ መብት የሚከራከሩ በሎስ አንጀለስ የሚኖሩ አንድ ጠበቃ ያለምንም ክፍያ ጉዳዬን ለመከታተል ፈቃደኛ ሆኑ። ዳኛውም አቅኚነቴን አቋርጬ ሰብዓዊ ሥራ የምሠራ ከሆነና በየወሩ ለፌደራሉ ባለ ሥልጣናት ሪፖርት የማደርግ ከሆነ ነፃ እንደምለቀቅ ወሰኑ። ይህን ውሳኔ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኔ በዋሽንግተን ግዛት በማክኒል አይላንድ እስር ቤት የሁለት ዓመት እስር ተበየነብኝ። እዚያም መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በማጥናት ጊዜዬን ተጠቀምኩበት። ከዚህም በተጨማሪ ታይፕ ተማርኩ። ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ባሳየሁት ጥሩ ጠባይ ምክንያት ተፈታሁ። ከዚያም በአቅኚነት አገልግሎት ለመቀጠል ወዲያው ዝግጅት አደረግሁ።

እንቅስቃሴው ተስፋፋ

በ1947 የክረምት ወር ከአንድ አቅኚ ጋር ሆኜ በቴክሳስ ኮሎራዶ ከተማ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነ ክልል እንድሠራ ተመደብኩ። ወቅቱ በጣም ብርዳማ ስለነበረ ሙቀት ለማግኘት ስንል ወደ ሳን አንቶኒዮ ሄድን። ይሁን እንጂ እዛም ቢሆን በኃይል ይዘንብ ስለነበር ከቤት ወደ ቤት የምናደርገው አገልግሎት ተደናቀፈ። የነበረን ገንዘብ ሁሉ ወዲያው ተሟጠጠ። ለሳምንታት በጥሬ ጎመን የተሠራ ሳንድዊች በመብላትና የአልፋልፋ ሻይ በመጠጣት ሕይወታችንን ማቆየት ቻልን። አብሮኝ ያገለግል የነበረው ወንድም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እኔ ግን እዛው ቆየሁ። እንግሊዝኛ ተናጋሪ ምሥክሮች ችግር ላይ መውደቄን እንደሰሙ እርዳታ ይልኩልኝ ጀመር።

በቀጣዩ የፀደይ ወር ወደተመደብኩበት ወደ ኮሎራዶ ሲቲ ተመለስኩ። በመጨረሻ አንድ ትንሽ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ ተመሠረተ። ከዚያም ወደ ስዊትዎተር፣ ቴክሳስ ተዘዋወርኩና ሌላ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጉባኤ እንዲቋቋም እርዳታ አበረከትኩ። እዛው ስዊትዎተር እያለሁ ለሚስዮናዊ ሥልጠና የካቲት 22, 1950 በሚጀመረው በ15ኛው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድካፈል ግብዣ ቀረበልኝ። ኒው ዮርክ በሚገኘው ያንኪ ስታዲዮም በበጋ ወር ላይ ተደርጎ በነበረው ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የምረቃው ሥነ ሥርዓት ከተካሄደ በኋላ ብሩክሊን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት ለሦስት ወራት ቆየሁ። እዚያም ሜክሲኮ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ለሚሰጠኝ የሥራ ምድብ ስልጠና አገኘሁ።

በሜክሲኮ መሥራት

ጥቅምት 20, 1950 ሜክሲኮ ሲቲ ደረስኩ። ከሁለት ሳምንት አካባቢ በኋላ የቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። በዚህም ሥራ ለአራት ዓመት ተኩል ሠርቻለሁ። ከአቅኚነት አገልግሎት፣ ከእስር ቤት፣ ከጊልያድና ከብሩክሊን ያገኘኋቸው ተሞክሮዎች ጠቃሚ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ሜክሲኮ እንደደረስኩ የሜክሲኮ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በመንፈሳዊ ወዲያው የመገንባቱ ጉዳይ ታየኝ። በተለይ በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈረውን ከፍ ያለ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃ እንዲጠብቁ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር።

ሜክሲኮን ጨምሮ በላቲን አሜሪካ ባሉ አገሮች አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሕግ ሳይጋቡ እንዲሁ አብሮ መኖራቸው የተለመደ ነገር ነበር። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በተለይ ደግሞ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ልማድ ሲስፋፋ በዝምታ ተመልክተዋል። (ዕብራውያን 13:​4) በመሆኑም አንዳንዶች በሕግ የተጋቡ ባይሆኑም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባል ሆነው ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ጋብቻቸውን እንዲያስተካክሉ የስድስት ወር ጊዜ ተሰጣቸው። እንደዚያ ካላደረጉ ከይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ ተደርገው መቆጠራቸው ያከትማል።

አብዛኛዎቹ ብዙም ችግር ሳይገጥማቸው ጋብቻቸውን ማስተካከል ችለው ነበር። ማድረግ ያስፈለጋቸው ነገር ቢኖር ተጋብተው ግንኙነታቸውን ሕጋዊ ማድረግ ብቻ ነበር። ሌሎቹ ግን ያሉበት ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ ነበር። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶቹ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሳይፋቱ ሁለት አልፎ ተርፎም ሦስት ጊዜ ጋብቻ መሥርተዋል። በመጨረሻ የይሖዋ ሕዝቦች የጋብቻ ሁኔታ ከአምላክ ቃል ትምህርት ጋር ስምም ሲሆን በጉባኤዎች ውስጥ ከፍተኛ መንፈሳዊ በረከት ተገኝቷል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​9-11

በዚህ ወቅት በሜክሲኮ የነበረው የትምህርት ደረጃ በጥቅሉ ሲታይ ዝቅተኛ ነበር። በ1950 እዛ ከመሄዴ በፊት ሳይቀር ቅርንጫፍ ቢሮው በጉባኤዎች ውስጥ ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ዝግጅት አድርጎ ነበር። በዚህ ጊዜ እነዚህ ክፍሎች እንደገና ተደራጁና በመንግሥት ዘንድ እንዲመዘገቡ ለማድረግ ዝግጅቶች ተደረጉ። መረጃዎች በጽሑፍ መሥፈር ከጀመሩበት ከ1946 ጀምሮ ምሥክሮቹ በሚያካሄዷቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሜክሲኮ ከ143, 000 የሚበልጡ ሰዎች ማንበብና መጻፍ ተምረዋል!

ሃይማኖትን በተመለከተ በሜክሲኮ የነበረው ሕግ በጣም ጥብቅ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚህ ረገድ ጥሩ ለውጦች ታይተዋል። በ1922 ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት አዲስ ሕግ የወጣ ሲሆን በ1993 በሜክሲኮ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት እውቅና አግኝተው ተመዝግበዋል።

እነዚህ ለውጦች ቀደም ባሉት ጊዜያት ይሆናሉ ብዬ ፈጽሞ ያልገመትኳቸው በመሆናቸው ታላቅ የደስታ ምንጭ ሆነውልኛል። ወደ መንግሥት ቢሮዎች ለብዙ ዓመታት በተደጋጋሚ በሄድኩባቸው ጊዜያት ሁሉ በጥርጣሬ ዓይን ነበር የሚያዩኝ። ይሁን እንጂ በቅርንጫፍ ቢሮአችን የሚገኘው የሕግ ክፍል እነዚህን ጉዳዮች ሲከታተልና በዚህም የተነሳ በስብከቱ ሥራችን ላይ የሚገጥመን ችግር በአንጻራዊ ሁኔታ ረገብ እያለ ሲሄድ መመልከቱ በጣም የሚያስደስት ነው።

ከሚስዮናዊ የትዳር ጓደኛ ጋር አብሮ ማገልገል

ሜክሲኮ ስደርስ ቀደም ሲል ከተካሄዱት የጊልያድ ትምህርት ቤቶች የተመረቁ ሚስዮናውያን በአገሪቱ ውስጥ ይገኙ ነበር። ከእነዚህ መካከል በቫሌጆ፣ ካሊፎርኒያ በ1942 አቅኚነት የጀመረችው ኤስተር ቫርታንአይን የምትባል አንዲት የአርመን ተወላጅ የሆነች ምሥክር ትገኝበታለች። ሐምሌ 30, 1955 ተጋባንና በሜክሲኮ መሥራታችንን ቀጠልን። እኔ በማገለግልበት በቅርንጫፍ ቢሮ እየኖርን ኤስተር በሜክሲኮ ሲቲ በሚስዮናዊ ሥራዋ ቀጠለች።

ኤስተር የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ምድቧ ወደሆነው ወደ ሞንትሬይ፣ ኑቮ ሊዮን፣ ሜክሲኮ የሄደችው በ1947 ነበር። በዚያን ጊዜ በሞንትሬይ 40 ምሥክሮች የሚገኙበት አንድ ጉባኤ ብቻ ነበር። ሆኖም በ1950 ወደ ሜክሲኮ ሲቲ በተዘዋወረችበት ወቅት አራት ጉባኤዎች ተመሥርተው ነበር። ኤስተር ሞንትሬይ በምታገለግልበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናቻቸው የነበሩ ቤተሰቦች ዘመድ የሆኑ ሁለት ወጣቶች ሜክሲኮ ሲቲ አቅራቢያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሯችን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

በ1950 ሚስዮናውያኑ የሚሰብኩበት የአገልግሎት ክልል መላውን ከተማ የሚሸፍን ነበር። ተመድበው በሚሠሩበት ቦታ የሚጓዙት በእግራቸው አለዚያም ሰዎችን አጨናንቀው በሚጭኑ በጣም ያረጁ አውቶቡሶች ነበር። በ1950ዎቹ መገባደጃ ላይ ወደዚህ ስመጣ የነበሩት ጉባኤዎች ሰባት ብቻ ነበሩ። አሁን ግን እነዚህ ጉባኤዎች ወደ 1, 600 የደረሱ ሲሆን ከ90, 000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አስፋፊዎችም በሜክሲኮ ሲቲ የሚገኙ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከ250, 000 የሚበልጡ ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል! ባለፉት በርካታ ዓመታት እኔና ኤስተር ከእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ በብዙዎቹ የማገልገል መብት አግኝተን ነበር።

እኔና ኤስተር መጽሐፍ ቅዱስን ለአንድ ሰው ማስተማር ስንጀምር መላው ቤተሰብ በጥናቱ ተካፋይ እንዲሆን ለማድረግ የቤተሰቡን አባወራ ፍላጎት ለመቀስቀስ እንጥራለን። በዚህ መንገድ በርካታ ሰፊ ቤተሰቦች ይሖዋን ሲያገለግሉ ለመመልከት ችለናል። በሜክሲኮ ፈጣን እድገት እንዲኖር አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ብዙውን ጊዜ መላው ቤተሰብ በእውነተኛው አምልኮ መተባበራቸው እንደሆነ ይሰማኛል።

ይሖዋ ሥራውን ባርኮታል

ከ1950 ጀምሮ በቁጥርም ይሁን በድርጅታዊ ለውጦች ረገድ በሜክሲኮ ያለው ሥራ ያሳየው እድገት ከፍተኛ ነው። እንግዳ ተቀባይና ደስተኛ ከሆኑት ሰዎች ጋር ተባብሮ በመሥራት ለዚህ ጭማሪ ጥቂት ድርሻ ማበርከት በእርግጥም የሚያስደስት ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ የሚያገለግለው ካርል ክላይን እና ባለቤቱ ማርጋሬት ከጥቂት ዓመት በፊት ለእረፍት መጥተው ጎብኝተውን ነበር። ወንድም ክላይን በሜክሲኮ የአገልግሎት ክልላችን እየተከናወነ ያለውን ሥራ በቅርብ ለማየት ፈልጎ ስለነበር እርሱና ማርጋሬት ሜክሲኮ ሲቲ አቅራቢያ ስብሰባ ወደምናደርግበት ወደ ሴን ዌን ቴሶንትላ ጉባኤ መጥተው ነበር። መሰብሰቢያችን 4.5 ሜትር ስፋትና 5.5 ሜትር ርዝመት ያለው ጠባብ ክፍል ነበር። እዚያ ስንደርስ 70 የሚያክሉ ተሰብሳቢዎች ቀድመው በክፍሉ ውስጥ ተገኝተው ስለነበር ለመቆሚያ እንኳ የሚሆን ቦታ አልነበረም። በዕድሜ የገፉት ወንበር ላይ፣ ወጣቶች አግዳሚ ላይ ልጆች ደግሞ ጡብ ወይም ወለል ላይ ተቀምጠዋል።

ወንድም ክላይን ሁሉም ልጆች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እንደያዙ ሲመለከት በጣም ተደነቀ፤ እንዲሁም ተናጋሪው ጥቅስ በሚጠቅስበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እያወጡ ይከታተሉ ነበር። ከሕዝብ ንግግሩ በኋላ ወንድም ክላይን ማቴዎስ 13:​19-23ን መሠረት አድርጎ ባቀረበው ንግግር ኢየሱስ የጠቀሰው “መልካም አፈር” በሜክሲኮ በብዛት መኖሩን ተናገረ። በዚህ ስብሰባ ላይ ተካፍለው ከነበሩ ልጆች መካከል ሰባቱ በአሁኑ ጊዜ ሜክሲኮ ሲቲ አቅራቢያ የሚገኘውን የቅርንጫፍ ቢሮ ለማስፋፋት በሚደረገው ግዙፍ የግንባታ ሥራ ላይ በመሥራት ላይ ናቸው። ሌላው ደግሞ በቤቴል እያገለገለ ሲሆን ሌሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ደግሞ አቅኚ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ!

ወደ ሜክሲኮ ሲቲ በመጣሁበት ወቅት የቅርንጫፍ ቢሯችን አባላት 11 ብቻ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት 1, 350 የሚሆኑ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 250ዎቹ በአዲሱ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ሥራ ላይ የሚካፈሉ ናቸው። ይህ የግንባታ ሥራ (2002 ያልቃል የሚል ተስፋ አለን) ሲጠናቀቅ ተስፋፍቶ በተሠራው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ 1, 200 የሚጠጉ ተጨማሪ ሰዎችን ማስተናገድ ያስችላል። በ1950 በመላው አገሪቱ የነበረው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ7, 000 የማይበልጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከ500, 000 የምንበልጥ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በአገሪቱ ውስጥ እንገኛለን! ይሖዋ እርሱን ለማወደስ ጠንክረው የሚሠሩትን ትሑታን የሜክሲኮ ወንድሞቻችንን ጥረት የባረከበትን መንገድ ስመለከት ልቤ በደስታ ይሞላል።

አንድ ከባድ ፈተና መወጣት

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከገጠሙኝ ተፈታታኝ ችግሮች መካከል አንዱ ሕመም ነው። በጥቅሉ ጥሩ ጤንነት የነበረኝ ሲሆን ኅዳር 1988 በስትሮክ ምክንያት ከፍተኛ የአካል ችግር ደረሰብኝ። ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና በአካል እንቅስቃሴና በተለያዩ የሕክምና ዓይነቶች በተወሰነ ደረጃ ጤናዬ የተመለሰልኝ ቢሆንም እንኳ አንዳንዶቹን የአካል ክፍሎቼን እንደምፈልገው ማዘዝ አልችልም። የሚሰማኝን ከባድ የራስ ምታትና በሽታው ያስከተለብኝን ሌሎች ችግሮች ለመከላከል ያልተቋረጠ ሕክምና ይደረግልኛል።

የምፈልገውን ያህል መሥራት ባልችልም እንኳ የይሖዋን ዓላማ እንዲያውቁና ራሳቸውን የወሰኑ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ በርካታ ሰዎችን በመርዳቴ እርካታ ይሰማኛል። ቅርንጫፍ ቢሯችንን ለመጎብኘት ከሚመጡት ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች መካከል የቻልኩትን ያህል ማነጋገር ያስደስተኛል። እንዲህ ማድረጌም እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል አጋጣሚ እንደ ሆነ ይሰማኛል።

ይሖዋ ለእርሱ ያበረከትነውን አገልግሎት በአድናቆት እንደሚመለከትና የሠራናቸው ሥራዎች ሁሉ ዋጋ ቢስ ሆነው እንደማይቀሩ ማወቄ በእጅጉ ጥንካሬ ይሰጠኛል። (1 ቆሮንቶስ 15:​58) የአቅም ገደብና ሕመም ቢኖሩብኝም በ⁠ቆላስይስ 3:​23, 24 ላይ የሠፈሩት ቃላት በእጅጉ ያጽናኑኛል:- “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት [“በሙሉ ነፍስ፣” NW ] አድርጉት፣ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና።” ከዚህ ምክር ጋር በመስማማት መከራ ቢኖርብኝም እንኳ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገልን ተምሬአለሁ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1942 አቅኚ እያለሁ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለቤቴ በሜክሲኮ የሚስዮናዊነት አገልግሎቷን የጀመረችው በ1947 ነበር

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከኤስተር ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ በስተግራ:- በ1952 ሜክሲኮ የነበረው የቤቴል ቤተሰብ፤ ከፊት ያለሁት እኔ ነኝ

ከላይ:- በ1999 በዚህ የሜክሲኮ ሲቲ ስታዲየም ተደርጎ በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከ109, 000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል

ከታች በስተግራ:- ሊጠናቀቅ ጥቂት የቀረው አዲሱ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃችን