ጦርነት የሚያስከትለው ጠባሳ
ጦርነት የሚያስከትለው ጠባሳ
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተዋጋ አንድ የቀድሞ ወታደር “በጦርነት ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ የለም” በማለት ተናግሯል። ብዙዎች በእርሱ አባባል ይስማማሉ። ጦርነት የሚያስከትለው ኪሣራ በጣም አስከፊ ነው። አሸናፊዎቹም ሆኑ ተሸናፊዎቹ የሚከፍሉት ዋጋ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። አንድ የጦር መሣሪያ ግጭት ካቆመ በኋላ እንኳ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጦርነቱ ጥሎ በሚያልፈው ከባድ ጠባሳ መሠቃየታቸው የማይቀር ነው።
የምን ጠባሳ? ጦርነት ብዙ ሕዝብ ሊያጠፋና በርካታ ቁጥር ያላቸውን ልጆች ያለ ወላጅ፣ ሴቶችን ደግሞ ያለ ባል ሊያስቀር ይችላል። በሕይወት የሚተርፉትም ብዙ ሰዎች ቢሆኑ የሥነ ልቦና ጠባሳን ጨምሮ አስከፊ የሆነ አካላዊ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም በችግር አለንጋ ሊገረፉ ወይም በስደተኝነት ለመኖር ሊገደዱ ይችላሉ። እንዲህ ከመሰሉ ግጭቶች የተረፉ ሰዎች ልብ ውስጥ ምን ያህል ጥላቻና ሐዘን ሊፈጠር እንደሚችል መገምት እንችላለን?
የሚያመረቅዙ ቁስሎች
የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ፣ የጦር መሣሪያ ድምፅ መሰማቱ ካቆመና ወታደሮችም ወደ ካምፓቸው ከተመለሱ ከረዥም ጊዜ በኋላ እንኳ ሳይቀር ጦርነት በሰዎች ልብ ላይ የሚያስከትለው ቁስል እያመረቀዘ ሊቀጥል ይችላል። በቀጣዮቹ ትውልዶች መካከል ሥር የሰደደ ጥላቻ ሊፈጠር ይችላል። በዚህ መንገድ አንድ ጦርነት የሚያስከትለው ቁስል ለሌላኛው ጦርነት መንስኤ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ያህል አንደኛ የዓለም ጦርነትን በኦፊሴላዊ መንገድ ለማስቆም በ1919 የተፈረመው የቬርሳይ የሰላም ስምምነት በጀርመን ላይ የጣለው ዕቀባ በጀርመናውያን ዘንድ ኢፍትሐዊና የብቀላ እርምጃ እንደሆነ ተቆጥሯል። ዚ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ በሚለው መሠረት በስምምነቱ ላይ የሰፈረው ቃል “በጀርመን ሕዝብ ዘንድ ቅሬታ ከመፍጠሩም በላይ የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ ገፋፍቷቸዋል።” “የሰላሙ ስምምነት የፈጠረው ቅሬታ” ከጥቂት ዓመታት በኋላ “ሂትለር ብቅ እንዲል” ያስቻለው ከመሆኑም በላይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዲቀሰቀስ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ሆኗል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በምዕራብ አውሮፓ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ባልካን አገሮች ተዛመተ። በ1940ዎቹ በአካባቢው ያሉት ጎሳዎች አንዳቸው በሌላው ላይ የፈጠሩት ቁስል በ1990ዎቹ በባልካን አካባቢ ለተካሄደው ጦርነት መንገድ ጠርጓል። “ማለቂያ የሌለው የጥላቻና የበቀል እሽክርክሪት እየተባባሰ ሄዶ እስከ ጊዜያችን ድረስ ዘልቋል” በማለት ዲ ሳይት የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ተናግሯል።
በእርግጥም፣ የሰው ዘር በሰላም እንዲኖር ከተፈለገ ጦርነት ያስከተለው ጠባሳ መሻር ይኖርበታል። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ጥላቻና ሐዘንን ለማስቀረት ምን ሊደረግ ይችላል? ጦርነት ያስከተለውን ጠባሳ እንዲሽር ማድረግ የሚችለው ማን ነው?
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
COVER: Fatmir Boshnjaku
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
U.S. Coast Guard photo; UN PHOTO 158297/J. Isaac