ጦርነት ያስከተለው ጠባሳ እንዲሽር ማድረግ
ጦርነት ያስከተለው ጠባሳ እንዲሽር ማድረግ
አብርሃም ለ20 ዓመታት በደፈጣ ተዋጊነት አገልግሏል። a አሁን ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጦርነትን እርግፍ አድርጎ ትቷል። እንዲያውም ከቀድሞ ጠላቶቹ መካከል አንዳንዶቹ አሁን የቅርብ ወዳጆቹ ሆነዋል። ይህን ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አብርሃም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋና ጥልቅ ማስተዋል ከማግኘቱም በላይ የሰው ልጆችን በአምላክ ዓይን መመልከት ችሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሰው ከጦርነት አባዜው እንዲላቀቅ የረዳው ሲሆን የሐዘን፣ የጥላቻና የምሬት ቁስሉም እየሻረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የልብ ፈውስ እንደሆነ ተገንዝቧል።
የአንድ ሰው የስሜት ጠባሳ እንዲሽር መጽሐፍ ቅዱስ የሚረዳው እንዴት ነው? አብርሃም የደረሰበትን ነገር ሊለውጥለት አይችልም። ቢሆንም የአምላክን ቃል ማንበቡና ማሰላሰሉ አስተሳሰቡ ከፈጣሪው አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ አድርጎለታል። አሁን የወደፊት ተስፋ አለው። ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ላይም ለውጥ አድርጓል። አምላክ አስፈላጊ እንደሆኑ አድርጎ የሚመለከታቸውን ነገሮች እርሱም በዚያው መንገድ ይመለከታቸዋል። እነዚህን ነገሮች ማድረግ ሲጀምር የልቡ ቁስል መሻር ጀመረ። አብርሃም ለውጥ ሊያደርግ የቻለው በዚህ መንገድ ነው።
ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገባ
አብርሃም የተወለደው በ1930ዎቹ በአንዲት የአፍሪካ አገር ውስጥ ነው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ አገሩ ኃያል በሆነ አንድ የጎረቤት አገር ትገዛ ጀመር። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የአብርሃም አገር ሰዎች ነፃነት ይፈልጉ ነበር። በ1961 አብርሃም ኃያል በሆነው የጎረቤት አገር ላይ የደፈጣ ውጊያ ከፍቶ ከነበረው የነፃነት ንቅናቄ ቡድን ጋር ተቀላቀለ።
“እነርሱ ጠላቶቻችን ነበሩ። እቅዳቸው እኛን መግደል ነው። ስለዚህ እኛም እነርሱን መግደሉን ተያያዝነው” በማለት ተናግሯል።
ብዙውን ጊዜ የአብርሃም ሕይወት አደጋ ያጠላበት ስለነበር ከ20 ዓመት የትጥቅ ትግል በኋላ በ1982 ሸሽቶ ወደ አውሮፓ ሄደ። በዚህ ወቅት ዕድሜው በ40ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ የነበረ ሲሆን ወደኋላ መለስ ብሎ ያሳለፈውን ሕይወት ለመቃኘት የሚያስችል በቂ ጊዜ ነበረው። ሕልሙ ምን ላይ ደረሰ? ከዚህ በኋላስ ምን ይገጥመው ይሆን? አብርሃም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘና በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመረ። ከጥቂት ዓመታት በፊት አፍሪካ በነበረበት ጊዜ አንድ ምሥክር ትራክት ሰጥቶት አንብቦ እንደነበር ያስታውሳል። ትራክቱ ወደፊት ስለሚመጣው ምድራዊ ገነትና በሁሉም የሰው ዘሮች ላይ ስለሚገዛ ሰማያዊ መስተዳድር የሚገልጽ ነበር። ይህ እውን ሊሆን ይችላልን?
አብርሃም እንዲህ ይላል:- “በጦርነት ያሳለፍኳቸው እነዚያ ሁሉ ዓመታት ዋጋ ቢስ እንደሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተረዳሁ። ሰውን ሁሉ በእኩልነት ሊይዝ የሚችለው መስተዳድር የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።”
አብርሃም ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ከአፍሪካ ሸሽቶ የሄደ ሮበርት የሚባል አንድ ሰው አብርሃም ወደሚኖርበት የአውሮፓ ከተማ መጣ። ሮበርት እና አብርሃም በተቃራኒ ግንባር ተሰልፈው ተዋግተው ነበር። ሮበርት የሕይወት እውነተኛው ዓላማ ምንድን ነው እያለ በተደጋጋሚ ራሱን ይጠይቅ ነበር። ሃይማኖተኛና አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ያነበበ ሰው በመሆኑ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ከአብርሃም ጋር በአንድ ጉባኤ ይካፈሉ የነበሩ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ መንገድ መረዳት ይችል ዘንድ ያቀረቡለትን ግብዣ ሮበርት ወዲያው ተቀበለ።
ሮበርት እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ገና ከመጀመሪያው ምሥክሮቹ ሁለቱ የተለያዩ አካል መሆናቸውን በመገንዘብ ይሖዋ እና ኢየሱስ የሚሉትን ስሞች የሚጠቀሙበት መንገድ በጣም አስገረመኝ። ይህ ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካነበብኩት ጋር የሚስማማ ነው። ምሥክሮቹ ሥርዓታማ አለባበስ ያላቸው ሲሆኑ ዘር ሳይመርጡ ለሌላው ደግነት ያሳያሉ። እነዚህ ነገሮች በእጅጉ ነክተውኛል።”
በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ ወዳጆች ሆኑ
ቀደም ሲል ጠላቶች የነበሩት ሮበርት እና አብርሃም አሁን የቅርብ ጓደኛሞች ሆነዋል። ሁለቱም በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው ያገለግላሉ። “በጦርነቱ ጊዜ በጎረቤት አገሮች የሚገኙና አብዛኛዎቹ የአንድ ሃይማኖት አባላት የሆኑ ሰዎች እርስ በርሳቸው ለምን እንደሚጠላሉ ይገርመኝ ነበር” በማለት አብርሃም ይናገራል። “ሮበርት እና እኔ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባላት ሆነን ሳለ እርስ በርሳችን ለመዋጋት ግን ወደ ጦር ግንባር ዘምተን ነበር። አሁን ሁለታችንም የይሖዋ ምሥክሮች ስንሆን እምነታችንም አንድ አድርጎናል።”
“ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው” በማለት ሮበርት አክሎ ይናገራል። “አሁን አባል የሆንበት እምነት የእውነተኛ የወንድማማች ማኅበር ክፍል አድርጎናል። ዳግም ወደ ጦርነት ፈጽሞ አንሄድም።” መጽሐፍ ቅዱስ ቀደም ሲል ጠላቶች በነበሩት በእነዚህ ሰዎች ልብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። ጥላቻና ምሬት ቀስ በቀስ ተወግደው መተማመንና ወዳጅነት በቦታቸው ተተክተዋል።
አብርሃም እና ሮበርት ጦርነት ላይ በነበሩበት ወቅት በሌሎች ሁለት እርስ በርስ በሚጎራበቱ አገሮች መካከል በሚደረግ ግጭት ውስጥ በተቃራኒ ወገን ተሰልፈው የሚዋጉ ሌሎች ሁለት ወጣቶች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ወጣቶችም ልብ ፍቱን መድኃኒት ሆኖላቸዋል። እንዴት?
ገድለህ የሰማዕትነት ሞት መሞት
ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ያደገው ጋብሪኤል አገሩ በቅዱስ ጦርነት ውስጥ እንደገባች ተነገረው። ስለዚህ 19 ዓመት ሲሞላው በውትድርና አገልግሎት በፈቃደኝነት ተመዘገበና ወደ ጦር ግንባር እንዲላክ ጠየቀ። ለ13 ወራት በተፋፋመ ጦርነት ውስጥ የነበረ ሲሆን አልፎ አልፎም ከጠላት ጋር እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል ርቀት ድረስ ዘልቆ ይዋጋ ነበር። “በተለይ በአንድ ወቅት የሆነውን አልረሳውም” በማለት ይናገራል። “ጠላት በዚያ ምሽት ጥቃት እንደሚከፍት አዛዣችን ነገሩን። በጣም ከመደናገጣችን የተነሳ ሌሊቱን በሙሉ አዳፍኔ ስንተኩስ አደርን።” በጎረቤት አገር ያሉትን ሰዎች
ሞት የሚገባቸው ጠላቶች እንደሆኑ አድርጎ ነበር የሚመለከታቸው። “የነበረኝ ሐሳብ የተቻለውን ያህል በርካታ ሰዎችን መግደል ነበር። ከዚያም እንደሌሎቹ ጓደኞቼ ሰማዕት ሆኜ መሞት።”ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ጋብሪኤል በግራ መጋባት ተዋጠ። ከዚያም ተራራማ በሆነ አካባቢ በመሸሽ ወደ አንድ ገለልተኛ አገር ከገባ በኋላ ወደ አውሮፓ ሄደ። ሕይወት በችግር የተሞላው ለምን እንደሆነና ምናልባትም ችግር ከእርሱ ዘንድ የሚመጣ ቅጣት ይሆን እያለ አለማቋረጥ አምላክን ይጠይቅ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች አገኙትና በዛሬው ጊዜ ሕይወት በብዙ ችግሮች የተሞላው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩት።—ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ጋብሪኤል መጽሐፍ ቅዱስን እየተማረ በሄደ መጠን በውስጡ ተመዝግበው ያሉት ነገሮች እውነት መሆናቸውን ይበልጥ ተገነዘበ። “ገነት በምትሆን ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንደምንችል ተማርኩ። የሚገርመው ደግሞ ይህ ከልጅነቴ ጀምሮ እመኘው የነበረ ነገር ነው።” ጋብሪኤል ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጽናኛ ከማግኘቱም በላይ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በችግር የከበደውን ልቡን አሳርፎለታል። በስሜቱ ላይ ደርሶ የነበረው ሥር የሰደደ ቁስል ቀስ በቀስ መሻር ጀመረ። ከዚህም የተነሳ ቀድሞ እንደ ጠላት ይመለከተው ከነበረው ከዳንኤል ጋር በተገናኘ ጊዜ ጋብሪኤል ምንም ዓይነት የጥላቻ ስሜት አላሳየም። ይሁን እንጂ ዳንኤል ወደ አውሮፓ እንዲሄድ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
“በእርግጥ ካለህ እባክህ እርዳኝ!”
ዳንኤል ያደገው በካቶሊክ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን 18 ዓመት ሲሞላው ለብሔራዊ ውትድርና ተጠራ። ከዚያም በተቃራኒ ግንባር ተሰልፎ ጋብሪኤል ያለበትን ጦር እንዲወጋ ተላከ። ዳንኤል በተፋፋመው ጦርነት መሃል እያለ ያሽከረክረው የነበረው ታንክ ተመትቶ ፈነዳ። አብረውት የነበሩት ጓደኞቹ ሲሞቱ እርሱ ክፉኛ ቆስሎ ተማረከ። በሐኪም ቤትና በጦር ሰፈር ለወራት ያህል ከቆየ በኋላ ገለልተኛ ወደሆነ አንድ አገር ተላከ። በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጦ ሳለ ራሱን ለማጥፋት ወሰነ። ዳንኤል “በእርግጥ ካለህ እባክህ እርዳኝ!” በማለት ወደ አምላክ ጸለየ። በቀጣዩ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች አገኙትና ለነበሩት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጡት። በመጨረሻም በስደተኝነት ወደ አውሮፓ ተጓዘ። እዚያም እንደደረሰ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱን ቀጠለ። የተማረው ነገር የነበረበትን ጭንቀትና ምሬት አቅልሎለታል።
ዛሬ ጋብሪኤል እና ዳንኤል የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ በጥሩ ወዳጅነትና በመንፈሳዊ የወንድማማች ማኅበር አንድ ሆነዋል። “ለይሖዋ ያለኝ ፍቅርና ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት እውቀት ነገሮችን በእርሱ ዓይን እንድመለከት ረድቶኛል። አሁን ዳንኤልን እንደ ጠላቴ አድርጌ አልመለከተውም። ከዓመታት በፊት ቢሆን ኖሮ ብገድለው ደስ ይለኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ማለትም ለእርሱ ለመሞት ፈቃደኛ መሆንን አስተምሮኛል” በማለት ጋብሪኤል ይናገራል።
“የተለያየ ሃይማኖትና ዘር ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ ሲገዳደሉ ተመልክቻለሁ” በማለት ዳንኤል ይናገራል። “የአንድ ሃይማኖት አባል ሆነው በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው እርስ በርስ የሚገዳደሉ ሰዎችም ነበሩ። ይህን ስመለከት ለዚህ
ሁሉ ተጠያቂው አምላክ ነው ብዬ አሰብኩ። አሁን ግን ከሁሉም ጦርነቶች በስተጀርባ ያለው ሰይጣን እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ። እኔና ጋብሪኤል አሁን የእምነት ባልደረቦች ነን። ዳግመኛ አንዋጋም!”‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው’
አብርሃም፣ ሮበርት፣ ጋብሪኤልና ዳንኤል እንዲህ ያለ ለውጥ ያደረጉት ለምንድን ነው? ከልባቸው ውስጥ ሥር ሰድዶ የነበረውን ጥላቻና ሐዘን ፍቀው ማስወገድ የቻሉት እንዴት ነው?
እነዚህ ሰዎች ‘ሕያውና የሚሠራ’ የሆነውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት አንብበዋል፣ አሰላስለውበታል እንዲሁም ተምረዋል። (ዕብራውያን 4:12) የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የሰው ዘር ፈጣሪ ሲሆን እርሱም ለመስማትና ለመማር ፈቃደኛ የሆነን ሰው ልብ እንዴት ለበጎ ነገር መለወጥ እንደሚቻል ያውቃል። “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” አንድ አንባቢ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲመራው ከፈቀደ አዳዲስ የሥነ ምግባር ደንቦችንና አቋሞችን መከተል ይጀምራል። ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት እያወቀ ይሄዳል። ይህ ሂደት ጦርነት ያስከተለውን ቁስል መፈወስን ጨምሮ በርካታ ጥቅሞች አሉት።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
የአምላክ ቃል አንዱ ብሔር፣ ዘር ወይም ጎሳ ከሌላው ይበልጣል ወይም ያንሳል ብሎ አይናገርም። ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላም፤ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው።’ ይህን የሚቀበል አንባቢ ለአንድ ዘር ወይም ብሔር የሚሰማውን የጥላቻ ስሜት ቀስ በቀስ ማስወገድ ይችላል።—ሥራ 10:34, 35
አምላክ ዛሬ ያለውን በሰብዓዊ አገዛዝ የሚመራ የነገሮች ሥርዓት በመሢሐዊ መንግሥቱ እንደሚተካው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያሳያሉ። አምላክ በዚህ መስተዳድር አማካኝነት “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል።” ለጦርነት የቆሙና ሰዎችን ለጦርነት የሚያደፋፍሩ ተቋማት ይወገዳሉ። በጦርነት የሞቱ ሰዎች በትንሣኤ ይነሱና ገነት በሆነ ምድር ላይ እንዲኖሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ወረራን ወይም ግፍን ፈርቶ ለመሸሽ የሚገደድ ሰው አይኖርም።—መዝሙር 46:9፤ ዳንኤል 2:44፤ ሥራ 24:15
በዚያን ጊዜ ስለሚኖሩት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም . . . በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።” ፈውስ ሊያገኝ የማይችል ምንም ዓይነት ጥፋት ወይም ጉዳት አይኖርም። እንዲህ ባለው ተስፋ ላይ እምነት ማሳደር አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ያለውን ሐዘን ቀስ በቀስ እንዲያስወግድ ያስችለዋል።—ኢሳይያስ 65:21-23
በእርግጥም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለልብ ፍቱን መድኃኒት ነው። በውስጡ ያሉት ትምህርቶች ዛሬም ቢሆን የጦርነትን ጠባሳ እንዲሽር እያደረጉ ነው። ቀደም ሲል በጠላትነት ይፈላለጉ የነበሩ ሰዎች በአንድ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ እንዲታቀፉ አድርጓል። ከሰው ዘር ልብ ውስጥ ጥላቻ፣ ምሬትና ሐዘን ሙሉ በሙሉ እስኪወገዱ ድረስ ይህ የፈውስ ሂደት በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥም ይቀጥላል። ፈጣሪ “የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም” በማለት ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 65:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞት ተለውጠዋል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በጦርነት ያሳለፍኳቸው እነዚያ ሁሉ ዓመታት ዋጋ ቢስ እንደሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተረዳሁ”
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ ቀደም ሲል ጠላቶች በነበሩት ሰዎች ልብ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ጥላቻና ምሬት ውሎ አድሮ በመተማመንና በወዳጅነት ተተክተዋል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ አንባቢ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲመራው ከፈቀደ አዳዲስ የሥነ ምግባር ደንቦችንና አቋሞችን መከተል ይጀምራል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀደም ሲል ጠላቶች የነበሩት ሰዎች አሁን በአንድ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ታቅፈዋል
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የስደተኞች መጠለያ:- UN PHOTO 186811/J. Isaac