በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅራችሁ ምን ያህል ሰፊ ነው?

ፍቅራችሁ ምን ያህል ሰፊ ነው?

ፍቅራችሁ ምን ያህል ሰፊ ነው?

“ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ [“ራስህ፣” NW ] ውደድ።”​—ማቴዎስ 22:​39

1. ይሖዋን የምንወድድ ከሆነ ባልንጀራችንንም መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

 ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” ሲል መልሷል። ከዚያም ከመጀመሪያው ጋር የሚመሳሰል ሌላ ሁለተኛ ትእዛዝ በመጥቀስ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ [“ራስህ፣” NW ] ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:​37, 39) አዎን፣ ባልንጀራን መውደድ የአንድ ክርስቲያን መለያ ምልክት ነው። ይሖዋን የምንወድ ከሆነ ባልንጀራችንን መውደድ አለብን። ለምን? ምክንያቱም ለአምላክ ያለንን ፍቅር የምናሳየው ቃሉን በመታዘዝ ነው፤ ቃሉ ደግሞ ባልንጀራችንን እንድንወድ ያዝዘናል። ስለዚህ ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን ካልወደድን ለአምላክ ያለን ፍቅር እውነተኛ ሊሆን አይችልም።​—⁠ሮሜ 13:​8፤ 1 ዮሐንስ 2:​5፤ 4:​20, 21

2. ለባልንጀራችን ልናሳይ የሚገባን ምን ዓይነት ፍቅር ነው?

2 ኢየሱስ ባልንጀራችሁን ውደዱ ሲል እንዲሁ ስለ ወዳጅነት መናገሩ አልነበረም። በቤተሰብ ውስጥ ወይም በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ከሚኖረው ተፈጥሯዊ ፍቅር የተለየ ፍቅር መጥቀሱ ነበር። ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ፍቅር ይሖዋ ራሳቸውን ለወሰኑ አገልጋዮቹ ያለውንና እነሱም ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 17:​26፤ 1 ዮሐንስ 4:​11, 19) አንድ አይሁድ ጸሐፊ ለአምላክ የሚኖረን ፍቅር “በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም” መሆን አለበት በሚለው በኢየሱስ አባባል መስማማቱን ገልጿል። ይህ ሰው በማስተዋል እንደተናገረ ኢየሱስ ተመልክቷል። (ማርቆስ 12:​28-34) ሰውዬው ትክክል ነበር። አንድ ክርስቲያን ለአምላክም ሆነ ለባልንጀራው የሚያዳብረው ፍቅር ስሜትንና አእምሮን የሚጨምር ነው። ከልብ የሚመነጭና በአእምሮ የሚመራ ነው።

3. (ሀ) ባልንጀራው ማን እንደሆነ በተመለከተ ያለውን አመለካከት ማስፋት እንዳለበት ኢየሱስ አንድን “ሕግ አዋቂ” ያስተማረው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠው ምሳሌ ዛሬ ላሉ ክርስቲያኖች የሚሠራው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ባልንጀራችንን መውደድ አለብን ብሎ ሲናገር “አንድ ሕግ አዋቂ” “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” ብሎ እንደጠየቀ ሉቃስ ዘግቧል። ኢየሱስ አንድ ምሳሌ በመንገር መለሰለት። አንድ ሰው ተደብድቦና ተዘርፎ በሕይወትና በሞት መካከል ሆኖ መንገድ ዳር ወድቋል። በመጀመሪያ አንድ ካህን ከዚያም አንድ ሌዋዊ አይተው ዝም ብለው አለፉ። በመጨረሻም አንድ ሳምራዊ በዚያ ሲያልፍ የቆሰለውን ሰው አየውና በደግነት አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁሉ አደረገለት። ከእነዚህ ከሦስቱ ለተደበደበው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማን ነበር? መልሱ ግልጽ ነበር። (ሉቃስ 10:​25-37) ሕግ አዋቂው ሰው ኢየሱስ ከካህንና ከሌዋዊ ይልቅ ሳምራዊ የተሻለ ባልንጀራ ሊሆን ይችላል ብሎ ሲናገር ሲሰማ ሳይደነግጥ አልቀረም። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ይህ ሰው ባልንጀራውን ይበልጥ ሰፋ ባለ መንገድ መውደድን እንዲማር እየረዳው ነበር። ክርስቲያኖችም እንደዚሁ ማፍቀር አለባቸው። የክርስቲያኖች ፍቅር እነማንን ጭምር እንደሚያጠቃልል ልብ በል።

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ

4. አንድ ክርስቲያን በመጀመሪያ ፍቅሩን ማሳየት ያለበት የት ነው?

4 ክርስቲያኖች የቤተሰባቸውን አባላት ማለትም ሚስት ባልን፣ ባል ሚስትን፣ ወላጆች ልጆችን ይወድዳሉ። (መክብብ 9:​9፤ ኤፌሶን 5:​33፤ ቲቶ 2:​4) እርግጥ ነው፣ በአብዛኞቹ ቤተሰቦች ውስጥ ተፈጥሯዊው የፍቅር ማሰሪያ አለ። ሆኖም ስለ ፈረሱ ትዳሮች፣ በትዳር ጓደኛ ላይ ስለሚፈጸም በደልና ዞር ብሎ የሚያያቸው ስላጡ ወይም በደል ስለተፈጸመባቸው ልጆች የሚገልጹት ሪፖርቶች በዛሬው ጊዜ ቤተሰብ ከባድ ቀውስ እንደገጠመውና እንዲሁ ተፈጥሯዊው የቤተሰብ ፍቅር ብቻ ቤተሰብን አንድ አድርጎ ሊያቆም እንዳልቻለ ያሳያሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-3) ክርስቲያኖች የቤተሰባቸው ሕይወት የተሳካ እንዲሆን ይሖዋና ኢየሱስ ያላቸው ዓይነት ፍቅር ማሳየት ያስፈልጋቸዋል።​—⁠ኤፌሶን 5:​21-27

5. ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያሳድጉበት ጊዜ የማንን እርዳታ ይሻሉ? ብዙዎችስ ምን ውጤት አግኝተዋል?

5 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ከይሖዋ የተቀበሉት አደራ እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸው ሲሆን እነሱን በማሳደግ ረገድም ከእሱ መመሪያ ለማግኘት ይሻሉ። (መዝሙር 127:​3-5፤ ምሳሌ 22:​6) እንዲህ ካደረጉ ወጣቶችን ሊበክሉ ከሚችሉ ተጽእኖዎች ልጆቻቸውን መጠበቅ የሚያስችላቸውን ክርስቲያናዊ ፍቅር ያዳብራሉ። በውጤቱም ብዙ ክርስቲያን ወላጆች በኔዘርላንድስ የምትገኝ አንዲት እናት ያገኘችው ዓይነት ደስታ አግኝተዋል። ይህች እናት ባለፈው ዓመት በኔዘርላንድስ ከተጠመቁት 575 ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ልጅዋ ሲጠመቅ ከተመለከተች በኋላ እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች:- “ላለፉት 20 ዓመታት የደከምኩት ድካም ሁሉ መና ሆኖ አልቀረም። የባከነው ጊዜና የፈሰሰው ጉልበት እንዲሁም ቁስለቱ፣ ልፋቱና ሐዘኑ ሁሉ አሁን ተረስቷል።” ልጅዋ በራሱ ነፃ ፈቃድ ተነሳስቶ ይሖዋን ለማገልገል በመምረጡ ምንኛ ደስተኛ ነች። ባለፈው ዓመት በኔዘርላንድስ ውስጥ ሪፖርት ካደረጉት 31, 089 አስፋፊዎች መካከል ይሖዋን መውደድን ከወላጆቻቸው የተማሩ በርካታ ሰዎች ይገኙበታል።

6. ክርስቲያናዊ ፍቅር የጋብቻ ማሰሪያን ለማጠንከር ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?

6 ጳውሎስ ፍቅርን “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ” ሲል የጠራው ሲሆን በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ሳይቀር የትዳርን ጥምረት ጠብቆ ሊያቆይ ይችላል። (ቆላስይስ 3:​14 NW, 18, 19፤ 1 ጴጥሮስ 3:​1-7) ከታሂቲ 700 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኝ ሩሩቱ በምትባል አንዲት አነስተኛ ደሴት የሚገኝ አንድ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በመጀመሩ ሚስቱ አጥብቃ ትቃወመው ነበር። በመጨረሻም ልጆቹን ይዛ ትታው ወደ ታሂቲ ሄደች። ያም ሆኖ በየጊዜው ገንዘብ በመላክና እሷም ሆነች ልጆቹ የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዳለ በስልክ በመጠየቅ ፍቅር ማሳየቱን ቀጠለ። በዚህ መንገድ ክርስቲያናዊ ግዴታውን ለመወጣት የተቻለውን ሁሉ አደረገ። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ቤተሰቡ ተመልሶ አንድ እንዲሆን ያለ ማቋረጥ ይጸልይ የነበረ ሲሆን በመጨረሻ ሚስቱ ተመለሰች። በዚህ ጊዜ ‘በፍቅር፣ በጽናትና በየዋህነት’ ያዛት። (1 ጢሞቴዎስ 6:​11) ይህ ግለሰብ በ1998 የተጠመቀ ሲሆን በኋላም ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በመስማማቷ እጅግ ተደስቷል። ባለፈው ዓመት በታሂቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት ከተደረጉት 1, 351 ጥናቶች መካከል ይህች ሴትም ትገኝበታለች።

7. በጀርመን የሚገኝ አንድ ሰው ጋብቻው እንዲጠነክር ያደረገው ምንድን ነው?

7 በጀርመን አንድ ሰው ሚስቱ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያሳየችውን ፍላጎት ተቃወመ። የይሖዋ ምሥክሮች ሚስቴን ሊያሳስቱብኝ ነው ብሎ አስቦ ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ሚስቱን መጀመሪያ ላነጋገረቻት ምሥክር የሚከተለውን ጽፏል:- “ሚስቴን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስላስተዋወቅሽልኝ አመሰግንሻለሁ። ስለ እነሱ በጣም ብዙ መጥፎ ነገር ሰምቼ ስለነበር መጀመሪያ ላይ ተረብሼ ነበር። ሆኖም አሁን ከባለቤቴ ጋር በስብሰባዎች ላይ ከተገኘሁ በኋላ ምን ያህል ተሳስቼ እንደነበር ተገንዝቤያለሁ። የምሰማው እውነት መሆኑን አወቅሁ፤ ይህም ትዳራችን ይበልጥ እንዲጠነክር አድርጓል።” ጀርመን በሚገኙት 162, 932 የይሖዋ ምሥክሮችና በታሂቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ባሉት ደሴቶች ውስጥ በሚገኙ 1, 773 የይሖዋ ምሥክሮች ውስጥ በአምላካዊ ፍቅር አንድ የሆኑ ብዙ ቤተሰቦች አሉ።

ለክርስቲያን ወንድሞቻችን የምናሳየው ፍቅር

8, 9. (ሀ) ወንድሞቻችንን እንድንወድ የሚያስተምረን ማን ነው? ፍቅር ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል? (ለ) ፍቅር ወንድሞች እርስ በርስ እንዲደጋገፉ ሊያደርግ እንደሚችል የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

8 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች “እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋል” ብሏቸው ነበር። (1 ተሰሎንቄ 4:​9) አዎን፣ “ከእግዚአብሔር የተማሩ” ሁሉ እርስ በእርሳቸው ይዋደዳሉ። (ኢሳይያስ 54:​13) ጳውሎስ “በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ” ብሎ በመናገር እንዳመለከተው ፍቅራቸው በተግባር ይገለጻል። (ገላትያ 5:​13፤ 1 ዮሐንስ 3:​18) ለምሳሌ ያህል የታመሙ ወንድሞችንና እኅቶችን በሚጠይቁበት፣ የተጨነቁትን በሚያጽናኑበት እንዲሁም ደካሞችን በሚደግፉበት ጊዜ ፍቅራቸውን በተግባር መግለጻቸው ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:​14) እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅራችን ለመንፈሳዊ ገነታችን እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል።

9 በኢኳዶር ከሚገኙት 544 ጉባኤዎች አንዱ በሆነው በአንኮን ጉባኤ የሚገኙ ወንድሞች ፍቅራቸውን ተግባራዊ በሆነ መንገድ አሳይተዋል። ተከስቶ የነበረው የገንዘብ ቀውስ ሥራ ወይም መተዳደሪያ አሳጣቸው፤ ስለዚህ አስፋፊዎቹ ሌሊቱን ዓሣ ሲያጠምዱ አድረው ወደ ቤታቸው ለሚመለሱ ዓሣ አስጋሪዎች ምግብ በመሸጥ ገቢ ለማግኘት ወሰኑ። ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ ሁሉም በዚህ ሥራ ተባበሩ። ዓሣ አስጋሪዎቹ ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ምግቡን ለማድረስ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ሥራ መጀመር ነበረባቸው። የተገኘው ገቢ ለወንድሞች እንደየችግራቸው ይከፋፈላል። እንዲህ ዓይነቱ እርስ በርስ የመረዳዳት መንፈስ የእውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር መግለጫ ነው።

10, 11. በግል ለማናውቃቸው ወንድሞች ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ሆኖም ፍቅራችን በግል ለምናውቃቸው ክርስቲያኖች ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለመላው የወንድማማቾች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 2:​17 NW ) ሁሉም እንደ እኛው ይሖዋ አምላክን የሚያመልኩ ስለሆኑ ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን በጠቅላላ እናፈቅራቸዋለን። ችግሮች የሚከሰቱባቸው አንዳንድ ጊዜያት ይህን ፍቅራችንን የምንገልጽበት አጋጣሚ ሊሰጡን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በ2000 የአገልግሎት ዓመት በሞዛምቢክ ከባድ የጎርፍ ማጥለቅለቅ ደርሶ የነበረ ሲሆን በአንጎላ የሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነትም ብዙዎችን ለድህነት ዳርጓቸዋል። በሞዛምቢክ ከሚገኙት 31, 725 ወንድሞችና በአንጎላ ከሚገኙት 41, 222 ወንድሞች መካከል በጣም ብዙዎቹ በእነዚህ ችግሮች ተነክተዋል። ስለዚህ በአጎራባች ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ምሥክሮች በእነዚህ አገሮች የሚገኙ ወንድሞቻቸውን ችግር ለማቃለል የሚረዳ በጣም ብዙ የእርዳታ ቁሳቁስ ልከዋል። ለተቸገሩ ወንድሞቻቸው ‘ትርፋቸውን’ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያሳዩት ፈቃደኝነት ፍቅራቸውን የሚገልጽ ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:​8, 13-15, 24

11 ድሀ በሆኑ አገሮች የመንግሥት አዳራሾችና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች እንዲገነቡ በብዙ አገሮች የሚገኙ ወንድሞች በሚያደርጉት መዋጮም ፍቅር እየታየ ነው። የሰሎሞን ደሴቶች ለዚህ አንድ ምሳሌ ናቸው። በሰሎሞን ደሴቶች አለመረጋጋት ቢኖርም ባለፈው ዓመት 1, 697 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር በማስመዝገብ 6 በመቶ ጭማሪ ያገኙ ሲሆን የትልልቅ ስብሰባ አዳራሽ ለመገንባት እቅድ ነበራቸው። ምንም እንኳ ብዙዎቹ የደሴቶቹ ነዋሪዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳ ደሴቶቹን ጥለው እየሸሹ ቢሆንም በግንባታው ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ ሠራተኞች ከአውስትራሊያ ወደነዚህ ደሴቶች መጥተዋል። ከጊዜ በኋላ ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ደሴቲቱን ለቅቀው እንዲሄዱ የተገደዱ ቢሆንም የተጀመረውን መሠረት እንዴት ማጠናቀቅ እንደሚችሉ እዚያው ለሚኖሩ ወንድሞች አሰልጥነዋቸው ነበር። ለአዳራሹ ግንባታ የሚያገለግለው ተገጣጣሚ ብረት ከአውስትራሊያ የመጣ ሲሆን ሌሎች በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶች በጅምር ሲቀሩ ለአምልኮ የሚያገለግለው ይህ ግሩም ግንባታ መጠናቀቁ ለይሖዋ ስምና ወንድሞች ላሳዩት ፍቅር ግሩም ምሥክርነት ነው።

እንደ አምላክ ሁሉ እኛም ዓለምን እንወዳለን

12. በእምነት ለማይመስሉን ሰዎች ባለን ዝንባሌ ረገድ ይሖዋን የምንኮርጀው እንዴት ነው?

12 ፍቅራችን ለቤተሰባችንና ለወንድሞቻችን ብቻ የተወሰነ ነውን? ‘እግዚአብሔርን የምንመስል’ ከሆንን ፍቅራችን በዚህ ብቻ የሚወሰን አይሆንም። ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ብሏል። (ኤፌሶን 5:​1፤ ዮሐንስ 3:​16) ልክ እንደ ይሖዋ አምላክ እኛም ለሁሉም፣ በእምነት ለማይመስሉን ጭምር ፍቅራዊ የሆነ ነገር እናደርጋለን። (ሉቃስ 6:​35, 36፤ ገላትያ 6:​10) በተለይም የመንግሥቱን ምሥራች እንሰብካለን እንዲሁም አምላክ ለእነሱ ሲል ስላደረገው ታላቅ የፍቅር መግለጫ ለሌሎች እንናገራለን። ይህ ለሚሰሙት ሁሉ መዳንን ሊያስገኝ ይችላል።​—⁠ማርቆስ 13:​10፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​16

13, 14. በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን ሳይቀር ተቋቁመው የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎች ፍቅር ያሳዩ ወንድሞች ያገኟቸው አንዳንድ ተሞክሮዎች ምንድን ናቸው?

13 በኔፓል የሚገኙ አራት ልዩ አቅኚ አገልጋዮች ያደረጉትን ተመልከት። በደቡባዊ ምዕራብ በምትገኝ አንዲት ከተማ እንዲያገለግሉ ይመደባሉ። ላለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋና በአቅራቢያዋ በሚገኙ መንደሮች በትዕግሥት በመስበክ ፍቅራቸውን አሳይተዋል። የአገልግሎት ክልላቸውን ለመሸፈን 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚሞቀው አየር አብዛኛውን ጊዜ ለበርካታ ሰዓታት በብስክሌት ይጓዛሉ። ከእነዚህ መንደሮች በአንዱ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ሲቋቋም ፍቅራቸውና ‘በበጎ ሥራ ያሳዩት ጽናት’ ግሩም ውጤት አስገኝቷል። (ሮሜ 2:​7) መጋቢት 2000 ጎብኚ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የሚሰጠውን የሕዝብ ንግግር ለመስማት 32 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ኔፓል ባለፈው ዓመት 430 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር የነበራት ሲሆን ይህም 9 በመቶ ጭማሪ ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ በዚህ አገር ያሉ ወንድሞች የሚያሳዩትን ቅንዓትና ፍቅር እየባረከው ነው።

14 በኮሎምቢያ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎች የዋዩ ሕንዳውያን በሚኖሩበት አካባቢ ለመስበክ ሄዱ። ይህን ለማድረግ አዲስ ቋንቋ መማር ነበረባቸው። ሆኖም ዶፍ ዝናብ በመዝነብ ላይ ሳለ 27 ሰዎች የሕዝብ ንግግር ለማዳመጥ በመገኘታቸው ያሳዩት ፍቅራዊ አሳቢነት ተክሷል። እነዚህ አቅኚዎች ያሳዩት ፍቅራዊ ቅንዓት በኮሎምቢያ 5 በመቶ ጭማሪና 107, 613 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር እንዲገኝ አስተዋጽኦ አድርጓል። በዴንማርክ አንዲት አረጋዊት እህት ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ፈለጉ፤ ሆኖም የአካል ጉዳተኛ ነበሩ። ሆኖም ይህ ሳያግዳቸው ደብዳቤ በመጻፍ ፍላጎት ካሳዩ ሰዎች ጋር መገናኘት ችለዋል። በአሁን ጊዜ ከ42 ሰዎች ጋር ደብዳቤ የሚጻጻፉ ሲሆን 11 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችንም ይመራሉ። ባለፈው ዓመት በዴንማርክ ሪፖርት ካደረጉት 14, 885 አስፋፊዎች መካከል እኚህ እህትም ይገኙበታል።

ጠላቶቻችሁን ውደዱ

15, 16. (ሀ) ኢየሱስ ፍቅራችን እስከ ምን ድረስ ሰፊ መሆን እንዳለበት ተናግሯል? (ለ) ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሐሰት ክስ የሰነዘረን አንድ ግለሰብ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የያዙት እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ ሳምራዊ የሆነ ሰው እንደ ባልንጀራ ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል ለዚያ ሕግ አዋቂ ነግሮታል። እንዲያውም ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” በማለት ከዚያም ያለፈ ነገር ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:​43-45) አንድ ሰው ቢቃወመን እንኳ ‘ክፉውን በመልካም ለማሸነፍ’ እንጥራለን። (ሮሜ 12:​19-21) ከተቻለም ከምንም ነገር የላቀ ውድ ሀብታችንን ማለትም እውነትን እናካፍለዋለን።

16 በዩክሬይን ክሪሚንቹክ ሄራልድ በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ የይሖዋ ምሥክሮች አደገኛ ኑፋቄዎች ናቸው ብሎ ነበር። በአውሮፓ አንዳንዶች የምሥክሮቹ እንቅስቃሴ መታገድ አለበት በሚል ሰዎችን ለማሳመን የይሖዋ ምሥክሮችን ኑፋቄዎች ናቸው ይሉ ስለነበረ ይህ ጉዳይ እንዲያው በቀላሉ የሚታለፍ አልነበረም። የአምዱ አዘጋጅ ቀደም ሲል ያወጣውን ዘገባ የሚያስተካክል ጽሑፍ እንዲያወጣ ተጠየቀ። በጥያቄው ተስማምቶ ባወጣው ጽሑፍ ላይ የመጀመሪያው ዘገባ በሐቅ ላይ የተመሠረተ እንደነበረ የሚጠቅስ አንድ አረፍተ ነገር አከለበት። ስለዚህ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ተጨማሪ መረጃዎችን በመያዝ በድጋሚ ቀርበው አነጋገሩት። በመጨረሻም የአምዱ አዘጋጅ መጀመሪያ ያወጣው ዘገባ ስህተት መሆኑን በመገንዘብ ያንን የሚሽር ትክክለኛ ዘገባ አወጣ። ከእሱ ጋር በግልጽነትና በደግነት በመወያየት ጉዳዩ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የተያዘ ሲሆን ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።

ፍቅርን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

17. ሌሎችን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መያዝ ሁልጊዜ ቀላል እንዳልሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

17 አንድ ሕፃን ገና እንደተወለደ ወላጆቹ በጣም ይወድዱታል። አዋቂዎችን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መያዝ ሁልጊዜ እንዲህ ቀላል አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ጊዜ እርስ በርስ ተዋደዱ የሚል ማሳሰቢያ የሚሰጠን ለዚህ ሊሆን ይችላል፤ ልናዳብረው የሚገባ ነገር ነው። (1 ጴጥሮስ 1:​22፤ 4:​8፤ 1 ዮሐንስ 3:​11) ኢየሱስ ወንድማችንን “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት” ይቅር ማለት እንዳለብን ሲናገር ፍቅራችን እንደሚፈተን ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 18:​21, 22) ጳውሎስም ‘እርስ በርሳችን ትዕግሥትን እንድናደርግ’ አጥብቆ መክሮናል። (ቆላስይስ 3:​12, 13) “ፍቅርን ተከታተሉ” መባላችን ምንም አያስገርምም። (1 ቆሮንቶስ 14:​1) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

18. ለሌሎች ፍቅር እንድናዳብር የሚረዳን ምንድን ነው?

18 አንደኛ፣ ለይሖዋ አምላክ ያለንን ፍቅር ሁልጊዜ በአእምሮአችን መያዝ እንችላለን። ይህ ፍቅር ባልንጀራችንን እንድንወድ ትልቅ ግፊት ይሆነናል። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን የሰማያዊ አባታችንን ባሕርይ በሚገባ የሚያንጸባርቅ ከመሆኑም በላይ ክብርና ውዳሴ ያመጣለታል። (ዮሐንስ 15:​8-10፤ ፊልጵስዩስ 1:​9-11) ሁለተኛ፣ ነገሮችን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ ለማየት መጣር እንችላለን። ምንጊዜም ኃጢአት ስንሠራ ኃጢአት የምንሠራው በይሖዋ ላይ ነው። ሆኖም በተደጋጋሚ ይቅር በማለት እኛን በፍቅር መመልከቱን ይቀጥላል። (መዝሙር 86:​5፤ 103:​2, 3፤ 1 ዮሐንስ 1:​9፤ 4:​18) የይሖዋን አመለካከት ካዳበርን ሌሎችን ለማፍቀርና የፈጸሙብንን በደል ይቅር ለማለት እንገፋፋለን። (ማቴዎስ 6:​12) ሦስተኛ፣ እኛን እንዲይዙን በምንፈልገው መንገድ ሌሎችን መያዝ እንችላለን። (ማቴዎስ 7:​12) ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ሁልጊዜ ሌሎች ይቅር እንዲሉን እንፈልጋለን። ለምሳሌ ያህል ንግግራችን ሌሎችን በሚጎዳበት ጊዜ አልፎ አልፎ በአንደበቱ የማይበድል ሰው እንደሌለ ያስታውሳሉ ብለን እንጠብቃለን። (ያዕቆብ 3:​2) ሌሎች ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዲይዙን የምንፈልግ ከሆነ እኛም እነሱን በፍቅር ልንይዛቸው ይገባል።

19. ፍቅርን በማዳበር ረገድ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ መጠየቅ የምንችለው እንዴት ነው?

19 አራተኛ፣ ፍቅር አንዱ የመንፈስ ፍሬ ስለሆነ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ መጠየቅ እንችላለን። (ገላትያ 5:​22, 23) ለጓደኛ፣ ለቤተሰብና ለተቃራኒ ጾታ የሚኖረን ፍቅር አብዛኛውን ጊዜ በተፈጥሮ የሚመጣ ነገር ነው። ሆኖም ፍጹም የአንድነት ማሠሪያ የሆነውን ይሖዋ የሚያንጸባርቀውን ፍቅር ለማዳበር የመንፈሱ እርዳታ ያስፈልገናል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ መፈለግ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ስለ ኢየሱስ ሕይወት ካጠናን ሰዎችን እንዴት አድርጎ እንደያዘ እንረዳለን፤ እንዲሁም የእሱን ባሕርያት መኮረጅን መማር እንችላለን። (ዮሐንስ 13:​34, 35፤ 15:​12) ከዚህም በተጨማሪ በተለይ ሌሎችን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መያዝን አስቸጋሪ የሚያደርጉብንን ሁኔታዎች በተመለከተ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንዲሰጠን ይሖዋን ልንጠይቀው እንችላለን። (ሉቃስ 11:​13) በመጨረሻም፣ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ተጠግተን በመኖር ፍቅርን መከታተል እንችላለን። አፍቃሪ ከሆኑ ወንድሞችና እኅቶች ጋር መሆን ፍቅርን እንድናዳብር ይረዳናል።​—⁠ምሳሌ 13:​20

20, 21. የይሖዋ ምሥክሮች በ2000 የአገልግሎት ዓመት የፍቅር መግለጫ የሆነ ምን ታላቅ ነገር አከናውነዋል?

20 ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ 6, 035, 564 የደረሰ ከፍተኛ የምሥራቹ አስፋፊዎች ቁጥር ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ምሥራች ለሰዎች በመናገር በጠቅላላው 1, 171, 270, 425 ሰዓት አሳልፈዋል። የፀሐይ ትኩሳት፣ ዝናብና ቁር ሳይበግራቸው ይህን ሥራ እንዲያከናውኑ ያደረጋቸው ፍቅር ነው። አብረዋቸው ለሚማሩም ሆነ አብረዋቸው ለሚሠሩ ሰዎች እንዲናገሩ እንዲሁም ጭራሽ ዓይተዋቸው ለማያውቋቸው ሰዎች በመንገድ ላይና በሌሎች ቦታዎች ቀርበው እንዲያነጋግሩ የገፋፋቸው ፍቅር ነው። ምሥክሮቹ ያነጋገሯቸው አብዛኞቹ ሰዎች ለመልእክቱ ግድ የለሾች ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ ተቃዋሚዎች ነበሩ። ሆኖም ፍላጎት ያሳዩ አንዳንዶችም በመኖራቸው 433, 454, 049 ተመላልሶ መጠየቆች የተደረጉ ሲሆን 4, 766, 631 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል። a

21 ይህ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክና ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ማስረጃ ነው! ይህ ፍቅር ፈጽሞ አይቀዘቅዝም። በ2001 የአገልግሎት ዓመት ለሰው ዘር ከዚህ የበለጠ ምሥክርነት እንደሚሰጥ ትምክህት አለን። ታማኝና ቀናተኛ የሆኑ አምላኪዎቹ ‘ሁሉን በፍቅር ለማድረግ’ ሲጥሩ የይሖዋ በረከት እንዳይለያቸው ምኞታችን ነው!​—⁠1 ቆሮንቶስ 16:​14

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ2000 የአገልግሎት ዓመት ዝርዝር ሪፖርት ለማየት ከገጽ 18-21 ላይ የሚገኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ባልንጀራችንን ስንወድ ማንን እየመሰልን ነው?

• ፍቅራችን ምን ያህል ሰፊ መሆን አለበት?

• ክርስቲያናዊ ፍቅር የተገለጠባቸው አንዳንድ ተሞክሮዎች የትኞቹ ናቸው?

• ክርስቲያናዊ ፍቅርን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 18-21 የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የ2000 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

(መጽሔቱን ተመልከት)

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያናዊ ፍቅር የአንድን ቤተሰብ አንድነት ጠብቆ ሊያቆይ ይችላል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍቅር ተስፋችንን ለሌሎች እንድናካፍል ይገፋፋናል